Scholarship Part Two

የትምህርት እድል (Scholarship)

ከአርሲ ሴሩ እስከ ኮፐንሀገን ዴንማርክ

በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረተ

ፍቃዱ ረታ አለማየሁ

ሀምሌ 2010 ዓ.ም.

ሀዋሳ፣ ኢትዮጵያ

 

 

ማስታወሻ፡ የዚህ መፅሀፍ ዋጋ ቀድሞ የተወሰነ አይደለም

ይገባዋል የሚሉትን ዋጋ በንግድ ባንክ ቁጥር 1000160852902 ይላኩልኝ

ከገቢው 20% በአርሲ ሴሩና ሮቤ ዲደአ ትምህርትቤቶች ቤተ-መፅሀፍት ለመክፈት ይውላል፤

የመፅሀፉ ዋና አላማ የገንዘብ ትርፍ ለማግኘት ሳይሆን ወጣቶችን እንዲፅፉና እንዲያነቡ ማነሳሳት ነው

 

ያለውን የሰጠ ንፉግ አይባልም…

 

መግቢያ

የተለየ ታሪክ አልፃፍኩም፣ ያየሁትን፣ የኖርኩትን፣ የምመኘውን፣ ልንወያይበት ይገባል ብዬ የማስባቸውን ሀሳቦች ነው የፃፍኩት፤ አደራ ልብ አንጠልጣይ የፍቅር ታሪክ ጠብቃችሁ እንዳይሆን፣ እኔ የኔ ፍቅር ለሀገራችን ህዝቦች ነው፤ ታላቅ ሆነን ራሳችንን መቻል ግራ ለሚገባን ነው፤ በዚህ መጽሀፍ ውስጥ ሀገሬን የምመኝላትን ምኞት ከራሴ የህይወት ተሞክሮ ለመፃፍ ሞከርኩ… የተበታተነ ሀሳብ ቢገጥማችሁ፣ እኔ በሃሳቤ ያንን ያህል እንደተበታተንኩኝ ልብ በሉ…. የሆነ ሆኖ፣ ያለውን የሰጠ ንፉግ አይባልም…

ይህንን መፅሀፍ ለመፃፍ ከ10 አመት በላይ በሀሳብ ዝግጅት ያደረግኩ ሲሆን ለመፃፍም የተነሳሳሁበት ምክንያት ጥሩ ፀሀፊ ስለሆንኩ ወይም መፅሀፍ በመሸጥ ሀብታም ለመሆን ሳይሆን ለሀገራችን የጋራ እድገትና የተሻለ ትውልድን ለመፍጠር ሁሉም የበኩሉን ሊያደርግ ይገባል ከሚል እምነት የተነሳ የሚቻለኝን የመወያያ ሀሳብ ለልጆቼና ለነገው ትውልድ ለማበርከት ነው፡፡ ይህ መፅሀፍ ለእኔ ማሟሻዬ ነው፤ እናቶቻችን አዲስ የእንጀራ ምጣድ ገዝተው ለመጀመሪያ የሚጋግሩት እንጀራ እንደማለት ነው፡፡ ማሟሻ እንጀራ ሲጋገር ምጣድዋን ለማለማመድ እንጂ ለድግስ ወይም ለእንግዳ የሚቀርብ አይነት ጥራት ያለው እንጀራ አይጠበቅም፡፡ ስለሆነም ይህች መፅሀፍ ለትውውቅ ያህል የተጻፈች ናት፡፡

 

ከዚህ በፊት የተወሰኑ የምርመር ፅሁፎች ያሳተምኩ ቢሆንም ይህ መጽሀፍ ታዋቂ ፀሀፊዎች የሚፅፉትን አይነት ልብ አንጠልጣይ ድርሰት ወይም ላቅ ያለ የሀሳብና የአጻጻፍ ስልት ያለው አይመስለኝም፡፡  ቢሆንም ከትምህርት ህይወት ጋር የተያያዙ የራሴን የህይወት ልምዶች መሰረት በማድረግ መጪው ትውልድ ይወያዩበት ዘንድ ጀባ ብያለሁ፤ በተጨማሪም መጽሀፉ ብዙ የንባብ ልማድ ላላቸው  አንባቢዎች ታስቦ ባይፃፍም የሁሉም አንባቢ ገንቢ አስተያየት ግን ያስፈልገኛል ፡፡ ማሟሽያ ነው ያልኩትም ለዛው ነው፡፡

 

መፅሀፉን በመፃፉ ሂደት ብዙ ልምድ አግኝቻለሁ፤ የመጀመሪያው ልምድ ጥሩ ፀሀፊ ለመሆን ለህትመት የሚበቃ ሀሳብ መኖሩ በቂ አለመሆኑን ነው፤ ብዙዎቻችን እጅግ አስተማሪ የሆኑ ብዙ ታላላቅ ሀሳቦች ሊኖሩን ይችላል፤ ነገር ግን እነኛን ሀሳቦች ወደህትመት ለማድረስ ከሁሉ በላይ እጅግ አድካሚ የሆነውን የፅሁፍ ስራ በተለይ ሀሳቡን በኮምፒውተር በአማርኛ ፊደሎች አንድ በአንድ ለቅሞ በትእግስት መጨረስ መቻል መሰረታዊው ጉዳይ ነው፡፡ በእርግጥ የመጀመሪያውን ረቂቅ ኮምፒውተር ላይ መፃፍ ሳያስፈልግ ወረቀትና እስክሪብቶ ብቻ በቂ ሊሆን ይችላል፡፡ የዛን አይነቱ አጻጻፍ ፅሁፉን ለህትመት ለማድረስ ሌላ ፀሀፊ በመቅጠር የፀሀፊ ወጪ ስለሚጠይቅ ለእኔ አይነቶቹ በኢኮኖሚ ዝቅተኛ ደረጃ ላሉት ወጣቶች አይመከርም፡፡ ስለሆነም በዚህ መጽሀፍ ሰበብ አማርኛ መፃፍ ተለማምጃለሁ፤ አስፈላጊ ከሆነ በፀሀፊነት ሙያ መተዳደር እችላለሁ ማለት ነው፤ ከሁሉ በላይ ግን ይህ የመፃፍ ሂደት ትእግስትም ጭምር አስተምሮኛል፡፡

 

ሁለተኛው ትምህርት ደግሞ አይሆንም የሚለውን የውስጥ የሀሳብ ሙግት ይሆናል በሚለው አሸንፎ፣ ሀሳብን ወደተግባር ለመለወጥ መውጣት መቻል ነው፡፡ ታሪክ የአሸናፊዎች ነው ይባላል፤ ምክንቱም አሸናፊዎች ታሪካቸውን ስለሚፅፉ፤ እኔም ለመፅሀፍት ታላቅ ክብር ስላለኝ፣ አንድ ቀን የራሴን መፅሀፍ ለልጆቼ በስጦታ መልክ የማበርከት ህልም ነበረኝ፤ ቢሆንም ለህትመት የሚበቃ ሀሳብ የለኝም በሚል  \ለብዙ ጊዜ ከፍርሀትና በራስ መተማመን አለመኖር/ ስጋት እንዲሁም ለህትመት የሚያስፈልገውን ገንዘብ የለኝም ከሚሉ ሀሳቦች የተነሳ ላለመፃፍ ራሴን አሳምኜም ነበረ፡፡ ቢሆንም ይህንን መፅሀፍ ለመጀመር የመጨረሻውን ስወስን በውስጤ የነበሩትን የፍርሀትና በራስ መተማመን ማጣትን ሀሳቦች አሸንፌ በመውጣት ነው፤ ስለሆነም አይቻልም የሚለውን ሀሳብ ከውስጤ አውጥቼ ይቻላል በሚለው በመተካት ከራሴ ውሳኔ ተማርኩኝ፤ እኔም አሸናፊ ሆንኩ ማለት ነው፡፡ በራሴ ላይ ድል ተቀዳጀሁ፡፡ ሂደቱ ለደራሲያንም የነበረኝን አክብሮት የበለጠ እንዲጠነክር አድርጎታል፤ በዚህ አጋጣሚ ለደራሲያን ሁሉ ምስጋናዬንም ላቀርብ እወዳለሁ፡፡ በተለይ ለሰመመን ደራሲ ሲሳይ ንጉሱ፣ ሰመመን መፅሀፍ ዩኒቨርሲቲ ከመግባቴ በፊት በአማርኛ መምህሬ በጀማል ባዲ እንዳነበው ተነግሮኝ አንብቤው ነበረ፤ በወቅቱ የዩኒቨርሲቲ ህይወት ምን አይነት እንደሆነ መፅሀፉ እንደቅርብ ጓደኛ አሳይቶኛል፡፡ ይህንን መፅሀፍ ለመፃፍ አንዱ መነሻዬ ሰመመን መፅሀፍ ነው፡፡

 

ይህንን መፅሀፍ በመጻፍ ሂደት፣ ማንም ታላቅ ነገር ለማድረግ መጀመሪያ ትልቁ ድል በራስ መተማመንና የራስን ጥረት ይዞ የሚቻለውን ያህል መሄድ እንደሚያስፈልግ ራሴን በተግባር አስተማርኩ ፡፡ ስለሆነም በዚህ አጋጣሚ ወጣቱ ትውልድ ራሱን ለማሻሻል ይቻለው ዘንድ ያለው ብቸኛው አማራጭ ጥረት ስለሆነ ሁሉም ሰው በራስ በመተማመን መስራት እንዳለበት ላስታውስ እወዳለሁ፡፡ በተጨማሪም ህይወት ደረጃ በደረጃ ከራሳችን ስህተት የምንማርት ትምህርትቤት ስለሆነች ራሳችንን ለማሻሻል ፈጥነን ወደተግባር መግባትና እግረ-መንገዳችንንም መማር አለብን፡፡ አንድ ጀማሪ ጸሀፊ በመጀመሪያው መፅሀፍ የሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህንን ወይም የበአሉ ግርማን አይነት መፅሀፍ መፃፍ ሊከብደው ይችላል፤ ነገር ግን የተቻለውን ያህል ጥረት በማድረግ ከስራው እየተማረ፣ ሌሎች የደረሱበት የታላቅነት ደረጃ መድረስ ለሁላችንም እድሉ ክፍት መሆኑን መረዳትም ያስፈልጋል፡፡

 

በዚህ ፅሁፍ ውስጥ፣ ከማህበራዊ ድህረገፆችና   እንዲሁም ከራሴ ህይወት ተሞክሮ በተለይ  ውጪ ሀገር ለትምህርትና ለአጫጭር ስልጠናዎች በሄድኩበት ጊዜ ያየሁዋቸውን ገጠመኞች ለልጆቼና እንዲሁም ለሀገራችን ተተኪ ትውልድ ሊያስተምር በሚችል መልኩ አቅርእቤያለሁ፡፡ መፅሀፉ የልጅነት ህይወቴን፣ የእረኝነት ጊዜ ትዝታዎቼን፣ በአርሲ ሴሩ ትምህርት ቤት ከነበረኝ ቆይታ፣ ሊስትሮ ስሰራ ካሳለፍኩት፣ በአርሲ ሮቤ ዲደአ ት/ት ቤት ካሳለፍኩት፣ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪ ስማር፣ ከምርቃት በኋላ እዛው ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከነበረኝ የስራ ቆይታ፣ ወደ ትዳር ህይወት ገብቼ የመጀመሪያ ልጃችን መወለድ ጋር የተያያዙ የህይወት ልምዶችንና የትምህርት እድል አግኝቼ ወደ ዴንማርክ ሀገር  ስሄድ የገጠመኝን፣ ታይላንድ፣ ጀርመን፣ ስዊዲን፣ኬንያ፣ ዩጋንዳ ሀገሮች ከነበረኝ ቆይታዎች የተወሰዱ፣ እንዲሁም እዛው ዴንማርክ ሀገር ሁለተኛ ልጃችን ስትወለድ ድረስ የነበሩትን ገጠመኞች አጠር አድርጌ አቅርቤያለሁ፡፡ እንዲሁም በሀገር ውስጥና በውጪ ሀገር የነበረኝን የስራ ልምድ፣ ከዛም ወደኢትዮጵያ ለመመለስ ስንዘጋጅ፣ ተመልሰን ቤት ስንሰራና በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት ያጋጠሙኝን ገጠመኞች፣ ወደተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ስሄድ ያየሁትንና ከማህበራዊ ድህረገፆች ያነበብኩትን ሀሳቦች ለሀገራችን እድገትና ለአዲሱ ትውልድ ሊያስተምሩ በሚችሉበት መልኩ ለማቅረብ ጥረት አድርጌያለሁ፡፡

 

በመግቢያው ላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት የፅሁፉን ስራ ሙሉ በሙሉ በራሴ ነው የፃፍኩት፣ በገንዘብእና በጊዜ እጥረት የቃላት ግድፈቶችን፤ የአማርኛ ሰዋሰው አገባብ ክፍተቶችን በጥልቀት መርምሬ ማቅረብ አልቻልኩም፡፡ ቢሆንም መፅሀፉን ወደህትመት ከመላኬ በፊት በማህበራዊ ሚዲያ በኩል ለንባብ በማቅረብ ብዙ ብዙ ገንቢ ሀሳቦችን አግኝቻለሁ፤ ከጠበቅኩት በላይም አበረታች አስተያየቶች ደርሰውኛል፣ እኔ የፀሀፊነትን ስራ ቀለል አድርጌ ነው የጀመርኩት፣ ይህንን አይነት መፅሀፍትም ብዙም የተለመዱ ስላልሆኑ፣ ለማሳተም አልቸኮልኩም፡፡ እስካሁን ድረስ እያስነበብኩ ያለሁት በማህበራዊ ድህረ-ገፆች መሰረት ነው፤ በዚህ መፅሀፍ ማካተት የምፈልገው ብዙ የሚፃፉ ሀሳቦች አሉ፤ በየአመቱም አንድ ጊዜ እየከለስኩ፣ እየጨመርኩ፣ እየቀነስኩ አቀርባለሁ፤ ስለሆነም አልፎ አልፎ ግድፈቶች ሲያጋጥሙ በሚቀጥለው ህትመት እንደሚስተካከል ቃል እየገባሁ፣ አስተያየታችሁን እንድትልኩልኝ በአክብሮት እጠይቃለሁ፡፡

 

ሀሳቦቹ ሙሉ በሙሉ ከእውነተኛ መረጃ የተነሱ ቢሆኑም አልፎ አልፎ አንዳንዶቹን ሀሳቦች በቀጥታ መፃፍ አላስፈላጊ መስሎ ሲታየኝ በልብ ወለድ መልክ አቅርቤያለሁ፡፡  ሆን ብዬ የጠቀስኩዋቸው የቤተሰቤ አባላትና ወዳጆቼ ደግሞ ይህ ፅሁፍ የጋራችን እንደሆነና የፅሁፌ ዋና አላማ የተሻለ ትውልድን ከመፍጠርና የማንበብ ልምድ እንዲበረታታ ከማድረግ አልፎ ማንንም ለመጉዳት የፃፍኩ እንዳልሆነ እንደሚገነዘቡኝ ባለሙሉ እምነት ነኝ፡፡  በተጨማሪም፣ አልፎ አልፎ ሀሳቤን ለማጠናከር ሌሎች ወዳጆቼ በፌስቡክና በሌሎች ማህበራዊ ድህረገፆች የፃፉትን ፅሁፎች በተጨማሪነት አቅርቤያለሁ፡፡ ስለሆነም ታሪኩ የግሌ ታሪክ ብቻ አይደለም፤ የፅሁፉ ዋና ጭብጥ የትምህርት እድል እንዲሆን የመረጥኩበት ምክንያት ለጽሁፉ መታተም ይበልጡን ምክንያት የሆነኝን ሀሳብ ያገኘሁት ለትምህርት ከሀገራችን ውጪ ካየሁትና ካጋጠሙኝ ሁኔታዎች በመነሳት ስለሆነ ነው፡፡ ነገርግን በመፅሀፉ ውስጥ ብዙ ሀሳቦች ተካተዋል፤ ስለሆነም ይህች አጭር ፅሁፍ የራሴ የህይወት ታሪክ ዝርዝር ሳትሆን የህይወት ልምዴን መነሻ በማድረግ ለሀገራችን አጠቃላይ እድገት አማራጭ ሀሳቦችን ነው ለመፃፍ የሞከርኩት፡፡

ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩት ይህ የመጀመሪያ መጽሀፌ እንደመሆኑ መጠን ቆንጆ እንዲሆን ብዙ የሞከርኩ ቢሆንም የተለያየ ግንዛቤና የእውቀት ደረጃ ያላቸው ወገኖቼ ሲያነቡት የየራሳቸው የሆኑ ገንቢ ሀሳቦች/እንዲሁም ተቃራኒ ሀሳቦች/ ይኖራቸዋል ብዬ አምናለሁ፤ ስለሆነም ሁልጊዜም አስተያየታችሁን ለመቀበል ዝግጁ ነኝ፡፡  ይህቺ ሟሟሻ ሀሳብ ለትውውቅ መንደርደሪያችን ትሁን እንጂ፣ እድሜና ጤና ከተሰጠን፣ ብዙ ለመማማርና ሀሳብ ለመቀያየር የቴክሎጂው እድገትና አዳደዲስ የሚፈጠሩት የህይወት ገጠመኞች ብዙ መጫወቻ ሜዳዎቻችን ናቸው፡፡

 

ይህንን መፅሀፍ ለህትመት ለመላክ እየተዘጋጀሁ ባለሁበት ወቅት ከ2009-2010 መጨረሻ ያለው የሀገራችን የፀጽታ ሁኔታ ጥሩ ስላልሆነ፣ በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች በተፈጠሩት ግጭቶች ህይወታቸው ያለፈውን ዜጎች ሁሉ ነብሳቸውን ይማርልን፤ በተጨማሪም ለወዳጅ ዘመዶቻቸው መጽናናትን እመኛለሁ፡፡ የፖለቲካው ችግርም በአጭር ጊዜ መፍትሄ እንደሚበጅለትም ምኞቴ ነው፡፡ የዶክተር አብይ አመራርም ውስብስብ የሆነውን የሀገራችንን ፖለቲካ ወደሰለጠነ የሀሳብ ሙግትና በህዝብ ተጠቃሚነት መርህ የነገዋን ሀገራችንን የተሻለች እንድትሆን፣ ሁሉም የሀገራችን ዜጎች የሚደሰቱባት ሀገር እንድትገነባ የጀመሩትን በጎ ስራ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ምኞቴ ነው፤ የሀገራችን የወደፊት እጣ ፈንታ፣ በኛ በልጆችዋ መሪነት፣ የተሻለ እንዲሆን ሁላችንም የሚቻለንን እናድርግ፡፡

 

ላለፉት አስርተ አመታት በመካከለኛው ምስራቅ፣ በቅርቡም በሴሪያና በሊቢያ ያለውን የእርስ በእርስ ጦርነቶች በቅርበት እየተከታተልኩ ነው፡፡ ጦርነትና ግጭቶች እጅግ አሳዛኝና በተለይ ደግሞ ደሀውን የህብረተሰብ ክፍል በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚጎዱ ተጨባጭ ምስክሮች አሉ፡፡ ሀገራችንም በተለያዩ ጊዜያት በሚከሰቱ የውስጥና የውጪ ጦርነቶች ሰበብ የደረሰብንን ሀገራዊ ኪሳራና የህይወት ጥፋት ስለምናስታውስ ሁላችንም ለጋራ ሰላም የሚቻለንን ብናደርግ ቆንጆ ነው፤ በተጨማሪም በስልጣን በመባለግና በሙስና ምክንያት ለተፈጠረው ችግር መሰረታዊ መንስኤ የነበሩት ግለሰቦችና ቡድኖች ለሀገርና ለትውልድ ዘላቂ ልማት በማሰብ ከእኩይ ስራቸው እንዲታቀቡ መልእክቴን አስተላልፋለሁ፡፡

 

አርቆ የሚያስብና ከኛ የተሻለ ትውልድ ይፈጠር ዘንድ ሁላችንም ሀላፊነት አለብን! ያለውን የሰጠ ንፉግ አይባልም ይላል የሀገራችን ሰው፡፡ እኔ ያፈራሁትን እንካችሁ፤ ሁሉም የተቻለውን ያድርግ፡፡ እግዚአብሄር ሀገራችንንና አለማችንን ሰላም ያድርልን! መልካም ንባብ፡፡

ልዩ ማስታወሻ

ከሁሉ አስቀድሜ ይህ ፅሁፍ በቅርቡ ከዚህ አለም በሞት ለተለየችን ለእናቴ ለወይዘሮ አበራሽ ሮቢ መታሰቢያ እንዲሆንልኝ እፈልጋለሁ፡፡ ለእናቴ ነብስም በገነት እንድትኖርልኝ ምኞቴ ነው፡፡ በተጨማሪም በሀገራችን በተለያዩ ጊዜያት በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ ምክንያት ወዳጅ ዘመዶቻችሁን በሞት ለተለያችሁት ሁሉ መፅናናትን እመኛለሁ፤ እንዲሁም ለሞቱትም ዘላለማዊ ህይወት እመኛለሁ፡፡

 

በዚህች አጭር ማስታወሻም እናቴን ለሞት ስላደረሰው ህመም ምንነትና እንዲሁም ለማስታመም በሆስፒታል ቆይታዬ ያስተዋልኩትን አጠር ያለ አስተያየት መስጠት እወዳለሁ፡፡ እናቴ ወይዘሮ አበራሽ ሮቢ በሸዋ ዞን፣ ፊቼ፣ ደገም ተብሎ በሚጠራ መንደር እንደተወለደች ከአያታችን ከወ/ሮ አደሱ አረዶ በልጅነቴ መስማቴ ትዝ ይለኛል፡፡ እናቴ የተወለደችው ሸዋ ቢሆንም ወደአርሲ ዞን የመጡት ተወልዳ በሁለት አመትዋ ነው፤ በትዳርም ከአባቴ ከአቶ ረታ አለማየሁ ጋር ተጋብተው እኔን ጨምሮ 8 ልጆችን የወለደች ሲሆን ሁለቱ ወንድ ልጆች በልጅነታቸው ሲሞቱ ሶስት ወንዶችና ሶስት ሴት ልጆች ግን አድገን ለዛሬ ደርሰናል፡፡ የቤተሰባችንን ዝርዝር በተመለከተ በሚቀጥለው ክፍል እመለስበታለሁ፡፡ ለመግቢያ ያህል ስለእናቴ ሞትና ተያይዞ የተሰማኝን ጉዳይ ልጥቀስ፤ ለእናቴ ህይወት ማለፍ ምክንያት ስለነበረው ህመም ከህክምና ምርመራው ውጤት እንደተረዳነው፣ እናቴን ለሞት ያበቃው ህመም ስሙ ብሬይን ቱበርክሎሲስ/የአእምሮ ነቀርሳ/ የሚባል ህመም ሲሆን የሳምባ ነቀርሳ በመባል የሚታወቀውን ህመም የሚያመጣው ባክቴሪ ወደጭንቅላት ውስጥ ገብቶ ጉዳት ሲያደርስ የሚከሰት ህመም ነው፡፡

 

የህመሙም ምልክት በዋናነት ከፍተኛ የራስ ምታት ሲሆን በመጨረሻ ደረጃ ግን ከአእምሮ ውስጥ ደም መፍሰስ ጋር ተመሳሳይ የሆነ አንድ ጎን ሰውነትን ፓራላይዝ /የማደንዘዝ/ የማድረግ ምልክት ነበረው፡፡ መንስኤው የተለያየ ቢሆንም ብዙ ጊዜ የእናቶችን የራስ ምታት ህመም ችላ የምንለው ጉዳይ ሊታሰብበት ይገባል እላለሁ፤ እናታችን ለብዙ ጊዜ የራስምታት ህመም የነበረባት ሲሆን መንስኤው አላስፈላጊ ሀሳብና ጭንቀት እንደሆነ በማሰብ ችላ ብለን ነበረ፤ ለኛ ለልጆችዋና ለቤተሰባችን መሻሻል ካላት ጉጉት የተነሳ ቀን ተለሊት ትጣጣር ነበረ፣ እንዲሁም ከሚገባው በላይም ትጨነቃለች፣ ታስባለች፤ ለምሳሌ እኔ በተፈጥሮዬ ሰውነቴ ወፍራም አይደለሁም፤ ቀጠን ያለ ቁመናዬ እናቴን ያሳስባታል፤ በተደጋጋሚ የኔ ሰውነት ክብደት ያለመጨመር ጉዳይ ሲያሳስባት ትነግረኝ ነበረ፤ ይህም ብቻ ሳይሆን፣ ከትውልድ ከተማችን ከእሲ ሴሩ በርቀት ሀዋሳና አልፎ አልፎም ውጪ ሀገር ስለምኖር ናፍቆትዋም እንዲሁም ሀሳብዋ ጭነቀትዋ ተጨማምሮ ለከባድ የራስ ምታት ህመም እንደዳረጋትና በመጨረሻም ትልቅ ዋጋ እንደከፈልን አምናለሁ፡፡

በዚህ አጋጣሚ ይህንን ፅሁፍ የምታነቡት ወዳጆቼ እናቶችንና የቤተሰብ አባላታችንን አላስፈላጊ የሆነ ጭንቀት ሲጨነቁ መዘዙ ብዙ መሆኑን ተረድተን ነገሮችን ቀለል አድርገው እንዲያዩ ብንመክር ቆንጆ ነው፡፡ የሰው ልጅ በህይወቱ ማድረግ የሚችለው ትልቁ ነገር ባለው አቅምና ጊዜ በርትቶ መስራት ሲሆን ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚመጣውን ደስታና ሀዘን ቀለል አድርጎ አምላኩን አመስግኖ ነገን ደግሞ ተስፋ አድርጎ መኖር ይመስለኛል፡፡

 

ስለተጨነቅን ችግሮቻችንን ማባባስ እንጂ የምንለውጠው ነገር አለመኖሩን መረዳት አለብን!

 

በተጨማሪም የህመም ስሜት ሲሰማን የህመም ማስታገሻ ወስደን ህመሙን ከማከም ይልቅ ወደሀኪምቤት ሄደን የባለሙያ እርዳታ ማግኘት ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ተረድቻለሁ፤ ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ እንደሚባለው… ከዚህ በተረፈ ግን በሆስፒታሎቻችን አገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ያለውን ክፍተት በአጭሩ ልጠቅስ እወዳለሁ፡፡

 

 

በመጀመሪያ የራሴ የሆስፒታልና የጤና ተቋማት ቆይታ በጣም ውስን መሆኑን አውቃለሁ፤ የስድስተኛ ክፍል ተማሪ ሳለሁ በፅኑ ታምሜ በባህላዊ ህክምና እየታከምኩ ከሞት አፋፍ ተመለስኩኝ፤ ለመጀመሪያ ታምሜ ወደዘመናዊ ሀኪም ቤት የሄድኩበት ጊዜ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ መምህር ሆኜ ሳለሁ ወባ ይዞኝ በቀላሉ ፈውስ አግኝቼ ነበረ፤ ስለሆነም ሆስፒታል ተኝቶ የመታከሙ አጋጣሚ አልነበረም፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ዴንማርክ ለትምህርት ሄጄ ወባዋ ሰውነቴ ውስጥ ነበረችና አገርሽታብኝ በአምቡላንስ ሆስፒታል ሄጄ ታከምኩ፡፡ የዴንማርኩን የህክምና አሰጣጥ እናቴን ሳስታክም ካየሁት የኛ ሀገሩ ጋር ሳስተያይ እኛ እጅግ ብዙ ርቀት መሄድ እንዳለብን ይሰማኛል፡፡ ለምሳሌ፡- ዴንማርክ በታመምኩበት ወቅት ማንም አስታማሚ በአጠገቤ አልነበረም፣ ወባዋ የተነሳችብኝ ወደትምህርት ቤት እየሄድኩ መንገድ ላይ አዙሮኝ ቁጭ ብዬ አምቡላንስ እንዲመጣልኝ ስልክ ደወልኩ/ የአምቡላንስ ስልክ ቁጥር ለሁሉ አዲስ ገቢ ተማሪዎች በመጀመሪያ የዩኒቨርሲቲው አቀባበል ቀን ተሰጥቶን ነበረ/ ታዲያ መንገዱ ዳር ሆኜ ስልክ ደውዬ በ10 ደቂቃ ጊዜ ውስጥ አምቡላንሱ ከች ብሎ እንደነበረ አስታውሳለሁ፡፡

 

እናቴ ስትታመም ወደሆስፒታል ለማድረስ የትውልድ ከተማችን አርሲ ሴሩ ጤና ጣቢያ ቢኖርም ቶሎ ጤና ጣቢያ ለመሄድ ባጃጅ መፈለግ ወይም በሸክም መሄድ ግድ ነበረ፤ የሀገራችን የጤና አገልግሎት ችግር ከትራንስፖርት አገልግሎት ይጀምራል፡፡ ከጊዜ ወደጊዜ መሻሻል ቢኖርም አለማቀፍ ደረጃ ለማድረስ ደግሞ ብዙ መስራት ያለብን ወደህክምና ተቋማት ያለው የመንገድ ሁኔታ የመጀመሪያው የቤት ስራችን ነው፤ መንገዶቻችን በዝናብ ወቅት ተሸከርካሪ ቀርቶ ሰውም ሊሄድባቸው ወደማይችል ደረጃ የሚደርሱበት ጊዜ አሉ፣ ነገር ግን ወደህክምና ተቋማት የሚወስዱ መንገዶችን ስናስብ ህሙማን የሚመላሱበት መንገድ ስለሆነ ከሌሎች መንገዶች በተሸለ ሁኔታ መሰራት እንደሚገባው ልብ ማለት አለብን፡፡ ከመንገዶቹ ቀጥሎ ደግሞ ህሙማንን በአስቸኳይ ወደህክምና የሚያደርሱ ብዙ የአምቡላንስ አገልግሎትን ማዳረስ ከመስጠት ይኖርብናል ማለት ነው፤ እስካሁን ባለው የሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ፣ አምቡላንስ አገልግሎት ያለው በዋናነት ለወሊድ አገልግሎት ነው፡፡ ነገር ግን ከባድ ህመም ያለበት የሀገሪቱ ህዝብ ሁሉ ከገጠር እስከ ከተማ ድረስ ደረጃውን የጠበቀ የትራነስፖርት አገልግሎት ያስፈልገዋል፡፡ መንገዱም ምቹ መሆን አለበት፤ እንዲሁም ብዙ አምቡላንሶች መኖር አለባቸው፡፡ በሸክምም ይሁን በአምቡላንስ ወይም በሌላ ትራንስፖርት፣ ታማሚ ሆስፒታል ከደረሰ ጀምሮ ደግሞ ፈጣን የህክምና እርዳታ ያስፈልገዋል፡፡

እናቴ ሆስፒታል ስትደርስ በድንገተኛ ክፍል ውስጥ የነበረው ግርግር እንዲሁም ከመኪና አውርደናት ወደሆስፒታሉ ውስጥ ለማስገባት የበሩ መግቢያ አከባቢ የነበረው መንገድ አመቺ አለመሆን፤ እንዲሁም ባለተሸከርካሪ ጎማ ወንበርም ችግር መሆኑን ሳይ ከልቤ አዘንኩኝ፤ የሆስፒታሉ መግቢያ በር ላይ ህሙማንን ለመጠየቅ የሚመጡት ሰዎች ወደውስጥ እንዳይገቡ ዘበኞች ዱላ ይዘው ሲከላለኩ ነበረ፡፡ መቼም በሀገራችን ባህል በሽተኛ መጠየቅ የተለመደ ልምዳችን ነው፣ ታዲያ ዘመናዊ ህክምና ስንሄድ ግን ጠያቂ ሁሉ ወደበሽተኞች መታከሚያ ክፍል እንዲገባ ከተፈቀደ ካለው ጠባብ የህክምና ክፍል የተነሳ ከፍተኛ መጨናነቅ እንደሚፈጠር ምንም ጥያቄ የለውም፡፡ አንዳንዱን ታማሚ፣ በተለይ የታመመው ግለሰብ በኑሮው ሻል ያለ ከሆነ ሰውየው ታሞ ሆስፒታል ሲገባ ጎሮቤቱ ሁሉ ተሰብስቦ ሲመጣ ሀኪም ቤቱ ገበያ ቦታ እስኪመስል ሰው ይበዛል፡፡ ስለሆነም ህዝባችን ታማሚ ለመጠየቅ ሲሄድ ዘበኞች የሚነግሩትን ምክር ተቀብሎ ቢታዘዝ ጥሩ ነው፡፡ አንዳንዱ ጠያቂ ካልገባሁ ብሎ ከዘበኞች ሲጣላም አይቻለሁ፡፡ ለአንድ ታማሚ ቢበዛ ሁለት አስታማሚ መሆኑ ትክክል ነው፡፡ በሽተኞች መታከሚያ ክፍል ሰው በዝቶ ለስራ አመቺ ያልሆነ ሁኔታ እንዳይፈጠር፡፡

 

ነገር ግን፣ ዛሬ የሀገራችን ኢኮኖሚ ከደረሰበት ደረጃ እንኳን ሲታይ በሆስፒታሎቻችን የታካሚ መኝታ አልጋና ባለጎማ ወንበርም ጭምር ችግር መሆን ተቀባይነት የለውም፤ በእርግጥ የታካሚዎች መኝታ አልጋ ችግር ያልሆነበት ሌሎች የግል ሆስፒታሎችም አሉ፣ ቢሆንም ዋጋቸው በሽተኛውን ለማስታከም ሳይሆን በታመመው በሽተኛ ሰበብ ገንዘብ ለመሰብሰብ የተመቻቹ ነው የሚመስሉት፣ በተለይ ከፍተኛ የህክምና አገልግሎት የሚሰጡት ሆስፒታሎች በአብዛኛው የሀገራችን ህዝብ ገቢ የሚቻሉ አይደሉም፡፡

በሆስፒታሎቻችን ያለው የህክምና አገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን መዘርዘር በራሱ አንድ መፅሀፍ የሚያስፈልገው ይመስለኛል፤ ህክምና የሰው ልጆች ህይወት ጉዳይ ነውና አንድ ሙሉ መፅሀፍም ቢፃፍበትም ለአገልግሎቱ መሻሻል ቆንጆ ነው እንጂ ጉዳቱ አይታየኝም፤ ስለሆነም በዚሁ በመግቢያዬ ስለህክምና አገልግሎታችን እናቴስ ሳሳክም ያስተዋልኩትን ትንሽ ዘርዘር አድርጌ መፃፌ አንባቢያንን እንደማያሰለች ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

 

እናታችንን እያሳከምን እዛው ኢመርጀንሲ ዋርድ/የድንገተኛ ህክምና ክፍል/ ሆነን ግሉኮስ የሚቀጥልልን ሀኪም እስኪመጣ ብዙ ጠብቀናል፤ አንድ በሽተኛ የድንገተኛ ህክምና ክፍል ሲገባ ከፍተኛ የባለሙያ ክትትል እንደሚስፈልገው መቼም ማንም ያውቃል፤ ቢሆንም በእለቱ ምሽት ተረኛ የነበረው አንድ ተለማማጅ ሀኪም ብቻ ነበረ፣ የሀኪሙን እርዳታ የሚፈልጉት ታካሚዎች ቁጥር ብዙ ስለነበሩ፣ ሀኪሙ ከአንዱ በሽተኛ ወደሌላኛው ስመላለስ እያየሁ ለሀኪሙ እያዘንኩ ለእናቴም እያዘንኩኝ ነበረ፤ በዛ የድንገተኛ ክፍል ውስጥ ስንደርስ ከምሽቱ አንድ ሰአት ገደማ የነበረ ሲሆን፣ በግምት በአንድ ጊዜ እስከ አስር በሽተኞች የሀኪሙን እርዳታ ይፈልጉ ነበረ፤ ሌሎቹ ሀኪሞች የት ሄዱ ብለን ስንጠይቅ እረፍት ናቸው የሚል መልስ ተሰጠ፤ ሌላው አሳዛኝ ጉዳይ ደግሞ፣ ተለማማጁ ሀኪም ለሊቱን ሙሉ ለብቻው ሰርቶ በማግስቱ ቀኑን ሙሉ ስራ ላይ ነበረ፤ የማስታምማት የራሴን እናት ህመም እያሰብኩ በመሀል የተለማማጁን ሀኪም የስራ ጫና ሳይ ሀዘኔን አበዛው፡፡ ግን ለምን? ሀኪም አይደክመውም ያለው ማን ነው? በግል ሆስፒታሎች የስራ ጫናው ያንን ያህል ላይሆን ይችላል፡፡ በህዝብ ሆስፒታሎች ግን፣ ዋጋው የህዝቡን ገቢ የሚመጥን ስለሆነ የታካሚው ብዛትና የሀኪሙ ብዛት ተመጣጣኝ መደረግ የለበትም? እግዚአብሄር አያምጣውና ትንሽ የበሽታ ወረርሽኝ ቢነሳ እኮ ሰዎች በህክምና እጦት እንደሚሞቱ ምንም ጥርጥር የለውም፤ ምክንያቱም አሁን የህክምና አገልግሎት እየሰጠን ያለንበት ሁኔታ ከፍላጎቱ ጋር ስታይ እጅግ አነስተኛ ነው፤ ከሁሉ በላይ ደግሞ ሀኪሞቻችን የስራ ጫና ይበዛባቸዋል፤ ያለእረፍት ይሰራሉ፤ እረፍት ማጣቱና የስራው ብዛት እንዲሁም ክፍያቸውም የድካማቸውን ያህል ያለመሆኑ ጉዳይ ሀኪሞቹ ወደግል ሆስፒታል እንዲሄዱ ወይም ሀገር ጥለው እንዲሰደዱ እያደረጋቸው ነው፡፡ ይህ ችላ መባል የለበትም፤ ሁላችንም በየደረጃው ልናስብበት ይገባል፡፡

 

ሀኪሙ በዛሁሉ ታማሚ መሀል ከወዲህ ወዲያ እየሮጠ፣ የአንዱን ሳይጨርስ ሌላውን እየጀመረ፣ ማታም አድሮ በማግስቱም ስራ መስራቱ፣ በእኔ አስተያየት ትክክለኛ አሰራር አይደለም፡፡ በእርግጥ የህክምና ሙያ የራሱ የሆነ የስራ ዲሲፕሊን ያለው ቢሆንም ለወደፊቱ፣ የተማረ የሰው ሀይል አቅማችን እየጨመረ ሲሄድ ሀኪሞች በብዛት ተመድበው በመረዳዳት ስራቸውን በደስታና በተረጋጋ ሁኔታ የሚሰሩበት ደረጃ መድረስ አለብን፤ ምክንያቱም፣ ባለሙያው እረፍት ያስፈልገዋል፣ ሀኪም ቢሆንም እኮ የሰው ልጅ ስጋ ለባሽ ነው፤ ሀኪሙም ይታመማል፣ ይደክመዋል፣ ይሰላቻል ወዘተ፡፡ ሀኪሙ ረጅም ሰአት በመስራት፣ እየተሰላቸና እቅልፍ ሳይተኛ በደከመ መንፈስ ለበሽተኞች አስፈላጊውን እርዳታ ላይሰጥ ይችላል፤ ታዲያ ይህን አይነቱ አሰራር ሊታሰብበት ይገባል፡፡ በሰለጠነው አለም አንድ ሀኪም አንድ በሽተኛን በአግባቡ አክሞ ነው ወደሚቀጥለው የሚሄደው፤ በተለይ በድንገተኝ ክፍል፤ በሀገራችን ግን አሁን ያለው የህክምና አገልግሎት አሰጣጥ እጅግ ብዙ ስራ ይጠይቃል፡፡

 

ከድንገተኛ ክፍል ወጥተን በሽተኞች ተኝተው ወደሚታከሙበት ክፍል ስንሄድ ደግሞ ችግሩ ለታካሚው መኝታ ማግኘት ከባዱ መሆኑ፣ ያለችውም አልጋ በዝምድናና በሙስና እንደምትሰጥም ሰምቻለሁ፣ እንደምንም አንድ አልጋ አግኝተን ወደክፍሉ ስንሄድ ችግሩ ከመኝታቤቱ ሽታ ይጀምራል፡፡ የቤቱ አሰራር አየር እንደልብ የሚገባበት ስላልሆነ፣ ብዙ ታካሚዎች በአንድ ክፍል ተኝተው ስለሚታከሙ፣ አንዳንዱ ታካሚ ጠያቂውም ከአምስት ሰው በላይ ስለሆነ፣ የበሽተኛው ንፅህና ጉዳይም ጥሩ ስላልሆነ፣ ከአስታማሚ ብዛት፣ ወዘተ ጋር ተደምሮ ታካሚዎች ተኝተው የሚታከሙበት ክፍል አከባቢውን ደስ የማይል ሽታ እንዲኖረው አድርጎታል፡፡

 

ሆስፒታሎቻችን የታካሚዎችን ብዛት ከግምት ውስጥ በማስገባት የአልጋ ብዛት የላቸውም፤ አንዳንድ ታካሚዎች ተኝተው ለመታከም አልጋ ስለሌለ የሚፈለገውን ያህል የህክምና እርዳታ ሳያገኙ ህይወታቸው እንደሚያልፍም ሰምቻለሁ፤ ይህም የአደባባይ ሚስጢር ስለሆነ ችግሩን በጥልቀት ልናስብበት ይገባል፡፡ በእርግጥ ሙያው ውስጥ ያሉና ችግሩ የደረሰባቸው ብዙ የሚነግሩን ጉዳዮች ይኖራሉ፤ ቢሆንም በሀገራችን ብዙ ገንዘብ አለ፣ ብዙ ባለሙያም አለ፤ ስለሆነም የአስተዳደር ችግር ካልሆነ በስተቀር፣ የበሽተኛ መታከሚያ አልጋ ችግር መሆን የለበትም፤ በእርግጥ ዋጋቸው እጅግ ከፍተኛ የሆኑ የህክምና ቁሳቁስ ባለመኖራቸው ምክንያቱ የገንዘብም እጥረት ነው ማለት ይቻላል፤ ነገር ግን በሽተኞች ተኝቶ የሚታከሙበት አልጋ ግን ሙሉ በሙሉ ማዳረስ የሚያስችል የኢኮኖሚ እድገት ደረጃ የደርስን ይመስለኛል፣ ችግሩ በትኩረት አለመስራታችን ነው፡፡

ብዙዎቻችንም ስለህክምና ተቋማት የምናስበው ተቸግረን ሀኪምቤት ስንሄድ እንጂ ወደቤታችን ስንመለስ እንረሳዋለን፤ በየቀኑ ሆስፒታል ውለው ታካሚዎችን ሲያገለግሉ የሚውሉትን ሀኪሞችና የህክምና ተቋማት ሰራተኞችን ሳስብ ግን ስለእነሱ እኔ ይጨንቀኛል፡፡ ያንን ሁሉ የሰው ህመምና ስቃይ ለማስታገስ የሚሮጡትን የህክምና ባለሙያዎቻችንን ከባድ የሀገራችን ባለውለታዎች መሆናቸውንም ማሰብ ያስፈልጋል፤ አስበንም የስራ ቦታቸውን ቆንጆና ዘመናዊ በማድረግ እነሱ ደስተኛ ሆነው ህዝቡን በደስታ እንዲገለግሉ ማድረግ አለብን፡፡

ችግሩ ብዙ ነው፣ ዝርዝሩንም የደረሰበት ያውቀዋል፤ ታዲያ እዛች በአንዲት ክፍል 6 ታማሚ ባለበት ክፍል ውስጥ ከጎን አንዱ በሽተኛ ሲሞት ክፍሉ ለቅሶ በለቅሶ ይሆናል፤ የአስታማሚዎች ለቅሶ አከባቢውን ይረብሸዋል፤ ባህላችንም አብሮ መሻሻል ያለበት ይመስለኛል፤ አንዳንዱ ዘመድ ሲያለቅስ ከእብደት የማይተናነስ ነገሮችን እያደረገ ችግር ይፈጥራል፤ በድንጋጤ የሚፈጠር ከቁጥጥር ውጪ ነገሮች እንደተጠበቁ ሆነው ማለት ነው፤ ስለሆነም ሁሉ ነገር/ለቅሶንም ጨምሮ/ በስርአቱ ሲሆን ይሻላል፡፡ የዘመድ ሞት እጅግ ቢያሳዝንም ያሳብዳል ማለት አይደለም፤ ከሁሉ በፊት ታሞ ሆስፒታል የገባ ታካሚ ሁሉ ድኖ ይወጣል ብለን ማሰብ ያለብን አይመስለኝም፣ አንዳንዱ አስታማሚ፣ በሽተኛው ሲሞት ሀኪሞቹን ካልገደልኩ የሚልም መኖሩን ነግረውኛል፤ በህክምና ሙያ ስህተት አይፈጠርም ማለቴ ሳይሆን፣ አንድ ታማሚ ሆስፒታል ገብቶ ሲሞት በሀኪሞች ስህተት ብቻ እንደሞተ አድርጎ ማሰብም ከባድ ስህተት ነው፤ ሰው ይታመማል፣ የታመመው ሰው ታክሞ ሊድንም ላይድንም ይችላል ብሎ ማሰብ ቆንጆ ነው፤ ስለሆነም ለምሳሌ ሆስፒታል ውስጥ ሰው ሲሞት የሆስፒታሉን ግቢ በሙሉ በኡኡታ ማስረበሽ ለሞተው ሰው ማዘን ብቻ ሳይሆን እየታከሙ ላሉት ታማሚዎች ምንም አለማሰብ ነው፡፡ እዛው ሆስፒታል ግቢ ውስጥ ሆነን አንድ ወጣት መርዝ ጠጥቶ ይዘውት ይመጡና ሆስፒታል ከገባ ከአንድ ሰአት ቆይታ በኋላ ሞቶ ነበረ፤ ወጣቱ መሞቱን የሰሙት ወዳጆቹና ዘመዶች ሆስፒታሉን ብጥብጥ አድረገው በፖሊስ ሀይል እንዲወጡ መደረጉን አይቼ እጅግ ነው ያዘንኩት፤ ስለሆነም ማህበረሰባችንም ተመሳሳይ ችግሮችን ማስተካከል አለበት፡፡ በተቻለን አቅም ሰው ከመሞቱ በፊት እርዳታ እናድርግለት፤ ከሞተ በኋላ ግን በሰከነ መንገድ ሀዘናችንን ገልፀን ለተቀሩት ዘመዶች ማሰብ እንጂ፣ ሆስፒታል የገባ ሁሉ የግድ መዳን አለበት በሚል የተሳሳተ ግንዛቤ ከሀኪሞች አቅም በላይ ሆኖ ለሞተ ዘመዳችን ሆስፒታሎችን በለቅሶና በጩሀት መረበሽ፣ እንዲሁም ሀኪሞችንም መሳደብና ለሌላ ጥል መጋበዝ አግባብ አይደለም፡፡ አልፎ አልፎ በሀኪሞች ስህተት የሚሞቱ ታካሚዎች መኖራቸው የሚታወቅ ቢሆንም ለቅሶና ሀዘናችን ስለበዛ የሞተው ተመልሶ አይመጣም፡፡

 

እግዚአብሄር ይመስገን እኛ የተወሰነውን ህክምና ከግል ሀኪም ቤት ለማግኘት ችለን ነበረ፤ በሀገራችን ከባድ ህመሞችንና ከአእምሮ ጋር የተያያዙ በሽታዎችን ለመመርመር የሚያስችሉት ዘመናዊ መሳሪያዎች ከመንግስት ሆስፒታል ይልቅ በብዛት በግል ሆስፒታሎች ውስጥ ይገኛሉ፤ ግን ለምን? ግለሰቦች ሊገዙት የቻሉትን መሳሪያ መንግስት እንዴት መግዛት አልቻለም? በህዝብ ሆስፒታል ያሉትን አንዳንዶቹን መሳሪያዎች ደግሞ ታካሚው ወደግል ህክምና እንዲሄድ ሆን ብለው እንደሚያበላሹዋቸውም ሰምቻለሁ፡፡

 

እናታችንን ይዘን አንዱ የግል ሆስፒታል ስንሄድ አንድ አርሶ አደር ሽማግሌ ወጣት ልጃቸው በጠና ታሞ ለማሳከም ወደዛ ሆስፒታል ልጃቸውን ይዘው መጡ፤ ቀድመውኝ ሰለነበረ የእሳቸውን ተራ እየጠበቅን ነበር የምንጠጋው፣ ሽማግሌው ገበሬ ለምርመራ ለመድረስ ሶስት ሺ አምስት መቶ ብር አከባቢ ከከፈሉ በኋላ ገንዘብ አለቀባቸው፤ በመሆኑም ለሚቀጥለው ወጪ ገንዘብ ስለሌላቸው ገንዘባቸውን ከስረው፣ ልጁም ሳይታከም ተመልሰው ሲሄዱ አይቼ አንጀቴ ነው የተላወሰው፡፡ በአንዱ ሰው ስቃይ ሌላው ገንዘብ ሲሰበስብ፣ እጅግ አሳሳቢ ጉዳይ ነው፡፡ በእርግጥ የግል ሆስፒታሎችም የማህበረሰቡን ጤና ለማሻሻል የበኩላቸውን ሚና እየተወጡ ቢሆንም፣ የአገልግሎታቸው ዋጋ ለድሆች ተደረሽ አለመሆኑ፣ ቢሆንም ህመም የታማሚውን ኪስ ለይቶ ስለማይመጣ፣ አገልግሎታቸው ለሁሉም እንዲደርስ መንግስት ቢደጉማቸውና የህክምና ዋጋ ሁሉ ቦታ ተመሳሳይ እንዲሆን ቢደረግ ብዬ አምናለሁ፡፡

 

 

ስለሀገራችን ህክምና ሌላው ያስተዋልኩት ጉዳይ ሀኪሞች በሽተኛውን ከመረመሩ በኋላ ለአስታማሚ ብዙም ስለበሽታው ምንነት ሳያስረዱ ቶሎ ማዘዣ ሰጥተው መድሀኒት እንዲገዛ ትእዛዝ የሚሰጡት ጉዳይ ነው፡፡ በእርግጥ ሀኪሞቹ ለእያንዳንዱ በሽተኛ መድሀኒት ቤት ድረስ ሄደው መድሀኒት እንዲገዙ ባይጠበቅም፣ ሆስፒታሉ ግን መድሀኒቱን እስከታካሚው አልጋ ድረስ ማድረስ መቻል አለበት፤ ምክንያቱም ለምሳሌ ታማሚው አስታማሚ ላይኖረው ስለሚችል፣ አስታማሚ ቢኖርም በሽተኛው የቅርብ ክትትል ስለሚያስፈልገው፣ አስታማሚዎች የሚገዙት መድሀኒት አገልግሎቱ ያለፈ ሊሆን ስለሚችል፣ አልፎ አልፎ ደግሞ የሚፈለጉት መድሀኒቶች በገበያ ላይ ስለማይገኙ ሆስፒታሎች መድሀኒቶችን የማቅረቡን ሙሉ ሀላፈነት መውሰድ አለባቸው… ለምሳሌ በሁሉም ፋርማሲዎች የማይገኝ መድሀኒት ሲታዘዝ አይተናል፤ ተፈልጎ የሌለ መድሀኒት አስታማሚዎችን አምጡ ብለው ከመጠየቅ ይልቅ መድሀኒቱ የት ሊገኝ እንደሚችልና የሚመጣበትን መንገድ ሆስፒታሉ ማመቻቸት አለበት፡፡ ይህም ከባድ ችግር ስለሆነ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ በአጠቃላይ የህክምና አገልግሎታችን ያለበት ደረጃ ዝቅተኛ ነው፣ የቅርብ ክትትልና የቁሳቁስ ድጋፍ ያስፈልጋል፡፡ በየከተሞቻችን በከፍተኛ ገንዘብ የመንግስት ግንባታዎች ሲገነቡ እናያለን፣ ታዲያ ሆስፒታሎች በሶስት ወይም አራት እጥፍ ቢገነቡ ምን አለበት? ለምሳሌ በቅርቡ በታላላቅ ከተሞቻችን የተገነቡትን የመዘጋጃቤቶችን ከሆስፒታሎች ጋር ብናወዳድር፣ የሆስፒታሎቹ ህንፃዎች ዝቅተኛ ነው፡፡ ለምን? ግንፅ ነው፣ ያንን ያህል አርቀንና ትኩረት ሰጥተን አላሰብንበትም፤ በእርግጥ ሀኪሞች ህዝቡን ማከም እንጂ የሀገሪቱ ገንዘብ ወደህክምና አገልግሎት በበቂ ሁኔታ መመደብ እንዳለበት የመወሰን አቅም የላቸውም፡፡

የህዝብን ሀብት ሰብስበን፣ በተራ የቢሮ ማሳመሪያ ማዋልና ሆስፒታሎችንና የህክምና ተቋማትን ችላ ማለት ትልቅ የአስተሳሰብና የንቃተ ህሊና ችግር ያሳያል፡፡ ሆስፒታሎች እኮ የሁላችንም ናቸው፣ የራሳችንና የዘመዶቻችን እንዲሁም የወገናቸውን፣ የህዝባችን ጤንነት የተሻለ እንዲሆን እየሰሩ ናቸው፣ ታዲያ እንዴት የታካሚ አልጋ መስራት ይከብደናል? እስቲ በህዝብ ሆስፒታሎቻችን ያለውን የመፀዳጃ ቤቶችና የውሀ አቅርቦት እንመልከት፡፡ ቶሎ መፍትሄ ካልተበጀላቸው፣ አብዛኞቹ የህዝብ ሆስፒታሎች ያላቸው የመፀዳጃቤትና የውሀ አቅርቦት እጅግ ያሳፍራል፤ ዴንማርክ ትምህርት ላይ ሆኜ አንዲት የአውሮፓ የበጎ አድራጎት ሰራተኛ እዚህ ሀገራችን አንዱ ሆስፒታል ታገለግል ነበረ፣ ሰራተኛዋ የቀን ተቀን ውሎዋን በራስዋ የኢንተርኔት ድህረገፅ እየፃፈች ነበረ፣ በየቀኑ የምትፅፈውን በአጋጣሚ አይቼው ነበር፣  ብዙ አሳዛኝ ትዝብት ትፅፍ ነበር፡፡ ትዝ የሚለኝን በአጭሩ ልጥቀስ፣ አንድ የማዋለጃ ክፍል ውስጥ አንዲት እናትን እያዋለዱ ሳለ መብራት ይጠፋል፣ መብራት ጠፍቶ ወሀም ይቆማል፣ ሀኪምዋ ቶሎ ብላ የሆስፒታሉ ሀላፊ ጋር ሄዳ ችግራቸውን ስታስረዳ ሀላፊው ሊሰማት ፈቃደኛ አለመሆኑንና በመሀል የወላድዋ እናት ህይወት እንዳለፈ ፅፋ አንብቤ ነበረ፡፡ ተመሳሳይ የሆስፒታሎች አስተዳደር ችግር የጤና ባለሙያ ወዳጆቼ ሲማረሩበት እንደነበረ ሰምቻለሁ፡፡ ችግሩ አሳሳቢ ነው፣ ሀገራችንን ማሳደግ ከፈለግን መጀመሪያውን ትኩረታችንን ጤና ላይ ማድረግ ያለብን ይመስለኛል፡፡ ሌሎችን ተቋማት እንደምናደርገው ህክምናንም በፖለቲካ አይን ማየት ከባድ ዋጋ ያስከፍለናል፡፡ የሆስፒታሎች አስተዳደር ሙያውን የሚመጥንና ለሀኪሞች አስተያየት የሚመጥን ደረጃውን የጠበቀ መሆን አለበት፡፡

 

የበሽተኞች መረጃ አያያዝም መሻሻል አለበት፣ ካርድ ገንዘብ ለመሰብሰብ ብቻ ሳይሆን የታካሚውን ታሪክ ማሳየት በሚችል መልኩ በወረቀት ወደኮምፒውተር መረጃ አያያዝ ተቀይሮ አንድ ታካሚ ወደህክምና ተቋም ሲሄድ በየጊዜው ካርድ ግዛ ከሚባል የጤናው ታሪክ በየጊዜው ተመዝግቦ በቀላሉ ሊገኝ በሚችል መልኩ ዘመናዊ በሆነ አሰራር ቢተካ ቆንጆ ነው፡፡ አንድ ወዳጄ የሚሰራበት ካድ ክፍል የሚሰሩ ሰራተኞች በብዛት የአስም ህመም ታማሚ መሆናቸውን ነግሮኛል፤ ምክንያቱም ብዙ ዘመናት ያስቆጠሩ የታካሚ ካርዶች በስብሰው የሚፈጥሩት ሽታ የካርድ ክፍል ሰራተኞችን ለሳንባ ህመም መዳረግ እጅግ ያሳዝናል፤ መልካሙ ዜና ደግሞ ሀገራችን ብዙ የኮምፒውተር ሙያ ተማሪዎችን እያስመረቀች ነው፣ ከታሰበበት የወረቀትን ካርድ ወደዘመናዊ ካርድና መረጃ አያያዝ ለመለወጥ በቂ ሀብትና እውቀት አለን፣ ዋናው የጤና አስተዳደር አስተሳሰብ ስልጣኔ ነው፤ አልግሎታቸው ጊዜ ያለፈ መድሀኒት ይሸጣሉ ስባል የምንሰማው ፋርማሲዎችም ባካችሁ አስተውሉ፣ አገልግሎቱ ያለፈ መድሀኒት ማለት መርዝ ማለት ነው፣ እባካችሁ ለሀገርና ለወገናችን እናስብ፡፡

የሀገር ፍቅር/የህዝብ ፍቅር

ሀገር ምንድን ነው? አንዳንዱ ጠያቂ ደግሞ ዛሬ ቁርስ ምን በላህ የማለትን ያህል ቀለል አድርጎ “ሀገር ምንድን ነው?” ይልሀል…. ምን ልመልስለት? ሀገር ወንዝ ነው ልበለው? ሀገር ጋራ ሸንተረሩ ነው ልበለው? ሀገር ህዝብ ነው ልበለው? ሀገርህ ኪስህ፣ገንዘብህ ነው ልበለው? ሀገርህ ደስ ብሎህ የምትኖርበት ሀገር ነው ልበለው? ሀገር መስዋእትነት የምትከፍልለት፣ እትብትህ የተቀበረበት አፈርህ፣ ደምህ ነው ልበለው? ሀገርህ በአስተሳሰብህ ስፋትና ጥበት የሚወሰን የአለም ክፍል ነው ልበለው? ሀገርህ ከአድማስ እስከ አድማስ፣ ሰማዩና ምድሩ፣ ንፋሱና ፀሀይ፣ ጨረቃና ኮከቦቹ፣ ፈጣሪ የፈጠረው ሁሉ ነው ልበለው? ሀገር ባህል ነው ልበለው? ሀገር ማለት የራስህንና የወገኖችህን ህይወት የምታገለግልበት ቦታ ነው ልበለው? እስቲ አግዙኝ፤ ሀገር ምንድን ነው?

የሀገርን ምንነት ጥያቄ መልስ ለአንባቢያን ልተውና በ2008/09 ዓ.ም. ወቅታዊው የሀገራችን ሁኔታ፣ እንዲሁም የሀገራችን ታሪክ፣ መንግስትንና የመንግስት ሀላፊነት ቦታ ያሉ ግለሰቦችን ማንነትና ሊኖራቸው የሚችለውን የአስተሳሰብ ደረጃ እንድንገመግም ያስገድደናል፡፡ አንዱ ወዳጄ የኪራይ ቤት ህይወት ከአከራዮቹ ጋር የማያልቅ ጭቅጭቅ ውስጥ ስላስገባው ዘላቂ መፍትሄ ይሆናል ብሎ፣ ከወር ደሞዙ ቆጥቦ እቁብ እየጣለ ገንዘብ ቆጥቦ በሚኖርበት ከተማ ወጣ ብሎ ለቤት መስሪያ የሚሆን የገበሬ መሬት ይገዛል፡፡ መሬቱን የራሱ ለማድረግ ሲል መሬት የገዛበት ቀበሌ ገበሬ መህበር የሶስት አመት የመሬት ግብር ከፍሎ፣ የነዋሪነት መታወቂያም ወሰደና ቤት መስራት ጀመረ፡፡

ነገር ግን ለቤቱ መስሪያ መሰረት መቆፈር ሲጀምር የቀበሌው ሊቀመንበር ይመጣና ‹ቤቱን መስራት አቁም!› ይለዋል፤ ልጁም ለቀበሌው ሀላፊ የሆነ ነገር ያስጨብጠዋል፡፡ የቀበሌው ሀላፊ እሺ መስራትህን ቀጥል ብሎት ያልፋል፤ መሰረቱን ቆፍሮ ሳይጨርስ ሌላ የቀበሌው አመራር አባል ይመጣና ‹ቤት መስራቱን አቁም!› ብሎ ያዘዋል፤ አሁንም ወዳጄ ለአመራሩ የሆነ ነገር ያስጨብጠዋል፤ ሁለተኛው አመራርም ዝም ብሎት ይሄዳል፡፡

በብዙ ውጣ ውረድ ቤቱ ተሰራ፤ ቤቱ ተሰርቶ አልቆ ወዳጄም ከኪራይ ቤት ተገላገልኩ ብሎ ቤተሰቡን ሰብስቦ አዲሱ ቤት መኖር ይጀምራል፤ ከዛም ህገወጥ ቤቶችን የማፍረስ ዘመቻ ተጀመረና በስንት መከራ የሰራት ቤቱም ፈረሰች፡፡ ቤተሰቡን ይዞ ወደኪራዩ ቤት ተመለሰ፡፡

ታዲያ ሰላማዊ አእምሮ ያለው ማንም ሰው እንደዚህ አይነት አጋጣሚዎችን ሲያስተውል፣ ሀገር ምንድን ነው? ዜግነትስ ምንድን ነው? ብሎ በጥልቀት እንዲጠይቅ ይገደዳል፡፡ በሀገራችን ውስጥ ሀላፊነት የጎደላቸውና የተጣለባቸውን የህዝብ አደራ ለራሳቸው ጊዜያዊ ጥቅም አሳልፈው የሰጡ የመንግስት ሰራተኞች ብዙ ናቸው፡፡ ምን ይደረግ የሚለውም ትልቅ ጥያቄ ነው፡፡ ቢሆንም አንድ ሰው ሲሰርቅ ተይዞ ምንም ካልተደረገ፣ ደግሞ ለመስረቅ መነሳሳቱ አይቀርም፣ ሌሎችም ሌባውን አይተው ለመስረቅ መነሳሳታቸው አይቀርም፡፡

ብዙ ሰው ሀይማኖቱን አጥብቆ የሚይዘው የሀጢያት ደሞዝ ሞት መሆኑን ስለሚያውቅ ነው፡፡ ጥሩ ስራ ገነት፣ መጥፎ ስራ ደግሞ ሲኦል እንደሚያሰገቡ ስለሚማር ራሱን ከሀጥያት ለመጠበቅ ይታገላል፡፡ አውቆ በድፍረት ሳያውቅ በስህተት ለሰራው ሀጢያት ደግሞ ንሰሀ ይገባል፣ ይቅርታም ይጠይቃል፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን መስረቅና ሙስና መስራት ምንም ጉዳት አያመጣም ወደሚለው መስመር የሄድን ይመስለኛል፡፡ የህዝብ ንብረት በመንግስት ሰራተኛው እየተዘረፈ ግን ሀገር መገንባት፣ ድህነትን ማስወገድ አይቻልም፡፡ ለመፍትሄው የራሴን አስተያየት፣ ከሌሎች ሀገራት ያየሁትንም ልምድ ጨምሬ በሚቀጥሉት ክፍሎች ለመጥቀስ እሞክራሉ፡፡ ሁላችንም ባለንበት እንወያይበት፡፡

ለመነሻ ያህል ሀገር ምንድን ነው? በሚለው ጥያቄ ዙሪያ የተወሰነ መወያየት ሊያሰፈልግ ይችላል፡፡ ሀገር እጅግ ትልቅ ነገር ነው፤ አንድ ግለሰብ ወይንም ማህበረሰብ ክብር የሚኖረው በግለሰብ ጥረት ከደረሰበት የእድገት ደረጃ ብቻ በመነሳት ሳይሆን እንደ ሀገር ከደረሰበት እድገትና ብልፅግናም ጭምር ነው፤ ለምሳሌ አሜሪካንን ብንወስድ እጅግ ታላቅ ሀገር ናት፤ ከህዝቦችዋ አልፋ ከታዳጊው አለም ተሰደው ለሚኖሩባት ዜጎች ሳይቀር ኩራት መሆን የቻለች ታላቅ ሀገር፤ በአሜሪካን ዜግነት ውስጥ ብዙ ታላላቅ ነገሮች አሉ፤ አንዱ ታላቅነት አሜሪካዊ ዜጋ የሆነ ሰው የሚሰጠው ክብርና የሕይወት ዋስትና ነው፤ ስለሆነም በአብዛኛው ከአለማችን ሀገራት ሰዎች እንደምንም ብለው ተሰደው አሜሪካን ይገባሉ፤ የተማሩት፣ ያልተማሩት፣ ሀብታሞች፣ ድሆች፣ ተማሪዎች ወዘተ፡፡  አንድ የመጀመሪያ ዲግሪ ተመራቂ አሜሪካዊና አንድ የመጀመሪያ ዲግሪ ተመራቂ ኢትዮጵያዊ ዜጎችን ብናወዳድር በዜግነታቸው ብቻ በአለም አቀፍ ደረጃ የሚሰጣቸው ቦታ እኩል አይደለም፡፡

 

ቢሆንም ታላቅነት ለአሜሪካን ብቻ የተሰጠ እድል አይደለም፤ በቅርቡ እነቻይናም እጅግ ታላቅ ሀገራት ተርታ ለመሰለፍ የቻሉበት ሂደት ለሀገራችን ህዝቦች ምሳሌ መሆን ይችላል፡፡  ሌሎች የደረሱበት ደረጃ ለመድረስ ከሁሉ በፊት ሀገራዊ ፍቅር ያስፈልጋል፡፡ የሀገር ፍቅር ሲባል ደግሞ የመጀመሪያው ተግባር የዛን ሀገር ዜጎች በሙሉ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መቀበልና የዜግነት ክብራቸው ሳይሸራረፍ በሀገራቸው ላይ ደስ ብሎአቸው የተሳካ ህይወት እንዲኖሩ ማድረግ በታሪክ አጋጣሚ በየትኛውም ጊዜ ከሚኖሩት ዜጎች በተለይ ደግሞ ከመሪዎች ይጠበቃል፡፡ ሀገር በአንድ ትውልድ ብቻ ተገንብታ አታበቃም፤ እንዲሁም ሀገር በአንድ ትውልድ ጉድለት ብቻ ወድቃ አትቀርም፡፡ በአንድ ሀገር በተወሰነ ጊዜ የሚኖር ትውልድ ጊዜና ሁኔታዎች በፈቀዱለት መጠን ይሰራል ሰርቶም ራሱን፣ ቤተሰቡን፣ ወገኖቹን፣ በአጠቃላይ ሀገሩን ያሳድጋል፡፡ ለእኔ የሀገር መኪና አሽከርካሪ መንግስት ነው፤ ከህዝቦችም ደግሞ በየደረጃው በአመራር ላይ ያሉ ዜጎች የሀገርን እድገትና የወደፊት እጣ ፈንታ የመወሰን እድል አላቸው፤ ስለሆነም የዜጎች እድገት የራሴ እድገት ነው ብሎ የሚያስብ ብዙሀን ያሉበት አመራር ለሀገር ፍቅርና ለሀገር እድገት እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡

የአንድ ሀገር መሰረቱ ህዝብ ነው፤ በአለማችን የተፈጠረውም ታላቁ ፍጡር የሰው ልጅ ነው፤ በሀገራዊ ፍቅር የተሞላ ዜጋ ለሀገሩ ህዝቦች ፍፁም ታማኝ በመሆን መገለፅ አለበት፤ የኛም ኢትዮጵያዊነታችን ለሀገሪቱ ህዝቦች ሁሉ እኩል ክብርና እኩል በማገልገል መገለፅ አለበት፤ ይህ ካልሆነ የኛ የሀገር ፍቅር በወሬ ብቻ ይቀራል ማለት ነው፡፡ አሁን ያለንበት ዘመን እጅግ የረቀቀ ዘመን ነው፤ ታዲያ ረዘም አድርገን ማሰብ ካልቻልን ዝንብ ቢሰበሰብ መግላሊት አይከፍትም እንደሚባለው አንድ መቶ ሚሊየን ህዝብ ይዘን ለተወሰነ ጊዜ ድርቅ ሲከሰት የእርዳታ ስንዴ እየተቀበልን በአለም መድረክ እያቀረቀርን መኖራችንን እንቀጥላለን፤ መቼም የሀገሩ ህዝቦች የእርዳታ ስንዴ እየተሰጣቸው ኩራት የሚሰማው ዜጋ ካለ፣ አእምሮው ስለታወረበት መሰረታዊ የንቃተ ህሊና እገዛ ያስፈልገዋል፡፡

ውጪ ሀገር ትምህርት ላይ ሆኜ አለም አቀፍ የአመጋገብ ስርአት በሚባል ኮርስ የሀገራችን የረሀብ ታሪክና በዛን ጊዜ የተወለዱ የተራቡ ህፃናት ፎቶዎች ለተማሪዎቹ እንደምሳሌ ሲቀርብ አይቼ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ በሀገሬና በማንነቴ እጅግ እንዳሳፈረኝ መቼውንም የሚረሳኝ አይደለም፡፡ በዛን ጊዜ ለተፈጠረው ረሀብ ማን ሀላፊነት ይወስዳል? ባለፈው አመት ለተፈጠረው ድርቅና ረሀብስ ማን ሀላፊነት ይውሰድ? እግዚአብሄርን ተጠያቂ እንዳናደርግ፣ ለምሳሌ እንደእስራኤል ያሉ ሀገራትን ስንመለከት፣ ከሀገራችን እጅግ የሚያንስ ዝናብ እያገኙ በአለማችን ምሳሌ የሚሆን ግብርናና የመስኖ ውሀ አጠቃቀም መመስረት ችለዋል፡፡ ሀገራችን እኮ የአፍሪካ የውሃ ማማ/ The Water Tawer of Africa/ በመባልም  ትታወቃለች፤ እንደአለመታደል ሆኖ ግን፣ የህዝብና የሀገር ፍቅር የሌላቸው፣ አርቀው የማያስቡ መሪዎች ነበሩን፡፡ የሀገር ፍቅር ቢኖረን እኮ ተቀዳሚ ነገራችን በረሀብ ለሚሞቱት ዜጎቻችን ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት ቀን ተለሊት እንሰራ ነበረ፤ ነገር ግን ዜጎች በድህነት እየማቀቁ የህዝብ ንብረት የሚዘርፉ የአመራር አካላት የሀገር ፍቅር ነበራቸው ማለት እንችላለን? የህዝብ ፍቅር የሚገለጠው የዛን ህዝብ ባህላዊ ልብስ በመልበስ ብቻ አይደለም፤ ወይም የዛን ሀገር ቋንቋ በመናገር ብቻ አይደለም፤ ወይም የዛን ሀገር ባህላዊ ምግብ በመመገብ ብቻ አይደለም፤ የዛን ሀገር ዘፈንም በመዝፈንም አይደለም፤ የዛን ሀገር ክብረ በአላት በማክበር ብቻም አይደለም፤ ሀገራዊ ፍቅር ከነኚህ ትንንሽ ነገሮች በዘለለ ለሀገሪቱ ዞጌች ታማኝ በመሆን ለዘላቂ ልማት በመስራት በተግባር የሚገለፅ ነው፤ አንድን ህዝብ ማፍቀር የሚገለጠው ለዛ ህዝብ የሚያስፍልገውን መስዋእትነት በመክፈል ነው፡፡ በመገዳደልና የወገኖችን ደም በማፍሰስ ሳይሆን አርቆ በማሰብ፣ የራስን ጥቅም ከሀገራዊ ጥቅም በማሳነስ፣ ህዝብን ከድህነት በማላቀቅ ይገለፃል ሀገራዊ ጥቅም፡፡

እንደማንኛውም የሀገራችን ዜጋ ለሀገራችን ብዙ በጎ ነገሮችን እመኛለሁ፤ በጎ የምመኘውም ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለኤርትራም፣ ለሱዳንም፣ ለኬንያም፣ ለደቡብ ሱዳንም፣ ለሶማሊያም፣ ለጂቡቲም፣ ለየመንም፣ ለሴሪያም በአጠቃላይ ለአለማችን ህዝቦች ሁሉ ነው፡፡ ምክንያቱም በሁሉም ሀገራት ያሉ ህዝቦች የእግዚእሁር ፍጡሮች ስለሆኑና እኔ የማምነው እምነትና ዛሬ የደረስኩበት የአስተሳሰብ ደረጃ ሰዎችን በሙሉ በእኩል አይን እንዳይ ስለሚያስገድደኝ ነው፡፡ ሰዎችን በሙሉ በእኩል አይን ማየት ደግሞ በመጀመሪያ ጠቀሜታው ለራሴ የመንፈስ እርካታ ነው፡፡ ወገንተኝነትና አድልዎ የሰይጣናዊ አስተሳሰብ ውጤት ስለሆኑ፣ ሁሉ ሰው ራሱን ከእርኩስ የአድልዎ ስሜት መጠበቅ አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡

ሀገራዊ ፍቅርን በተግባር ካሳዩት ወገኖች ውስጥ የማቂዶኒያ ማእከል መስራቹን ቢኒያምን እንደምሳሌ ልጠቅስ እወዳለሁ፤ ጠንካራና ለህዝብ ታማኝ የሆነ መንግስትና ስርአት ባለመኖሩ ምክንያት ያለጠያቂ ሜዳላይ የቀሩትን ወገኖች የተቻለውን ያህል ከለላ በመስጠት ታላቅ ምስክርነት ሊሆን የሚችል ማእከልን ስላደራጀ ለማቂዶኒያው መስራች ለቢኒያም ያልኝን ታላቅ አክብሮት ልገልፅ እፈልጋለሁ፤ ስራውን በቦታው ተገኝቼ የማየቱ እድሉ ነበረኝ፣ ማእከሉን በማየቴም በሀገሬ ተስፋ እንዳልቆርጥ ተበረታታሁ፤ የሰው ልጅ መስዋእትነት ለመክፈል ከተነሳ ያንን ያህል ርቀት መሄድ እንደሚችልም አየሁ፤ በእርግጥ ያንን አይነት ውሳኔና ቆራጥነት እጅግ ከፍ ያለ ስብእና ይጠይቃል፣ የኔ አይነቶቹ ዜጎች እዛ ደረጃ ለመድረስ ብዙ ትግል ይጠብቀናል፤ ካራስ በላይ ለሌሎች መኖር ማለት እንደዛ ስለሆነ፡፡  ስለዚህ እውነተኛ ሀገራዊ ፍቅር ራስን ለሌሎች አሳልፎ በመስጠት የሚገለፅ ይመስለኛል፡፡ ብዙዎቻችን ሀገራችንን እንወዳለን ብንልም የራሳችንን ግን አሳልፈን ለሌሎች ዜጎች አንሰጥም፤ አንዳንዶቻችን ደግሞ ሀገሬን እወዳለሁ እያልን ህዝብን ወደጦርነት የሚጋብዙ ሀሳቦችንም የምናራምድ መኖራችንን በማህበራዊ ሚዲያ በየቀኑ እያየን ነው፤ የቢኒያም አይነቶቹ ግን፣ ራሳቸው ተቸግረው  ሌሎቹን እየረዱ ነው፤ የሀገር ፍቅራቸውን ከተግባራቸው መመስከር ይቻላል፡፡

እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ፣ አልፎ አልፎ በማህበራዊ ድህረገጾች በተለይ ፌስቡክ ላይ ባንዲራችንን በተመለከተ ሰፋ ያለ ውይይትና ክርክር አነባለሁ፤ በሀገራችን የነበሩ የባንዲራ አይነቶችም ለምርጫ ቀርበው አይቻለሁ፤ አንዳንዱ ‹የኛ ባንዲራ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ብቻ ነው ምንም ሌላ ምልክት የለውም› ይላል፤ ሌላው ደግሞ ‹አይ የኛ ባንዲራ ባለአንብሳው ነው› ይላል፤ ሌላው ደግሞ ‹ተሰስታችሁዋል፣ ባንዲራችን አሁን የምንጠቀመው ባለኮከቡ ነው› ይላል፤ ሌላው ደግሞ አይ ባንዲራችን የግመል ምስል ያለበት መሆን አለበት ይላል፤ ሌላው ደግሞ ባንዲራችን ቀይ አረንጓዴ ቀይ ነው ይላል…ወዘተ፡፡

የኔ አስተያየት ለየት ያለ ነው፤ ባንዲራችንን በተመለከተ በማህበራዊ ድህረ ገፆች የሚደረጉት ክርክሮች ሁሉ አግባብ አይመስሉኝም፤ ባንዲራ ትልቅ ነገር ነው፤ እጅግ ትልቅ ነገር ነው፤ ይህንንም የበለጠ የተረዳሁት ዴንማርክ ሀገር ነው፡፡ በባንዲራ ውስጥ ዜጎችና ዜግነት አለ፤ ስለሆነም የሀገራችን ባንዲራ ማለት የሀገራችን ዜጎች የጋራ ምልክትና መታወቂያ ማለት ነው፤ ዜግነት ማለት ደግሞ ማንነት ነው፤ ስለሆነም በተለያዩ መንግስታት ወቅት የባንዲራው ይዘት በተወሰነ መልኩ ቢቀየርም፣ ባንዲራን በተመለከተ ምን የሚሰማን ስሜት አለ? ዜግነታችንስ ለህዝቦቹ ምን ያህል ከለላ ሆነ? የሚሉትን መወያየት የበለጠ ትርጉም የሚሰጥ ይመስለኛል፡፡

ምክንያቱም፡-

ባንዲራችን ትርጉም መስጠት ያለበት ለሁላችንም ነው፤ ሁሉም ከልጅነት እስከ ሽምግልናው ድረስ የቻለውን ያህል የሀገራችን ባንዲራ ትርጉም ሊሰጠው ይገባል፤ እኔ እስከሚገባኝ ድረስ የአንድን ሀገር ባንዲራ ማክበር ማለት የዛን ሀገር ዜጎችም ማክበር ማለት ነው፤ ይቅርታ ይደረግልኝ በዚህ ፅሁፍ ውስጥ ዴንማርክን ደጋግሜ ነው የምጠቅሰው፤ ለአንድ የዴንማርክ ዜጋ ባንዲራ ማለት የመኖሩ ዋስትና ማለት ነው፤ የዴንማርክ ዜግነት ዴንማርክ ካፈራቻቸው ሀብቶች አንድ የዛ ሀገር ዜጋ ለመኖር የሚያስፈልገውን መሰረታዊ ነገሮች የሚያገኝበት ማለት ነው፤ የዴንማርክ ዜጋ ልጁ ሲታመም በነፃ ህክምና ያገኛል፤ ለምግብና ለመጠለያ የሚበቃ ገንዘብ ያገኝበታል፤ ልጆቹን በነፃ ትምህርት ቤት ይልካል፣ እንዲሁም በዜግነቱ መሰረታዊ የኑሮ ነገሮች እንዳይቸግሩት ገንዘብ ይከፈለዋል፤ በዜግነቱም ስለሀገሩ የፈለገውን መነፃነት እንዲናገር ሙሉ መብት አለው፤ ወዘተ… ዜግነት ማለት እንደዛ ነው፤ የሀገራችንን ሁኔታ ስናይ ዜግነታችን ለሁሉም እኩል የመኖር ዋስትና አልሰጠም፤ ኢትዮጵያዊ ዜግነት ከሌሎች ዜግነቶች እኩል ለመሆን ብዙ ርቀት መሄድ ይገባዋ፤ በውጪው አለም ዜጎቻችን ዘንድ፣ ሀገራዊ ባንዲራችንና ዜግነታችን በቀላሉ ለሌሎች ሀገራት ዜግነት እየተቀየረ ይገኛል፤ በቅርቡም ወደሀገር ቤት የተመለሱት የፖለቲካ መሪዎች የሌላ ሀገር ዜግነት እንዳላቸው ሲነገር ነበረ፤ ይህ ለምን ሆነ ብለን ራሳችንን መጠየቅ አለብን፤ ሀገራችን ጥልቅ ናት፤ እጅግ ትልቅ ሀገር፣ 107 ሚሊየን ህዝብ የሚኖርባትና ከ70 በላይ ብሄረሰብ ያላት ሀገር፤ ይህንን ታላቅ ህዝብ አንድ አድርጎ፣ ፍለጎቱን ሁሉ አቻችሎ ወደስልጣኔ ማምራት ከባንዲራ ቀለማት በላይ ብዙ መሰረታዊ ስራዎችን ይጠይቀናል፡፡

ዜጎቻቸን ዜግነታቸውን የቀየሩት በሀገር ጥላቻ ሳይሆን እዚህ ሀገር ቤት ስንኖር ዜግነታችን ወይም ባንዲራችን  ከለላ ስላልሰጣቸው፣ ዜግነትና መንግስት ለደሀው ዜጋ ታች ድረስ ወርዶ ለሁሉም የሀገራችን ዜጎች ትርጉም መስጠት ወይም የኑሮ ዋስትና መሆን አለመቻሉ ነው፡፡  ዜግነት ወይም በአንድ ሀገር ተወላጅ መሆን በዛች ሀገር በሰላም ለመኖርና ዘላቂ ኑሮ ለመመስረት ካላበቃ ዜግነቱ ምኑ ላይ ነው? ባንዲራውም ቢሆን ተመሳሳይ ነው፤ ራቅ አድርገን ካየነው መሰረታዊው ጉዳይ የባንዲራው ቀለማት አቀማመጥ ሳይሆን የዛች ሀገር ዜጋ መሆን ለዜጋው በዜግነቱ ከለላ መስጠቱ ላይ ነው፡፡ ስለሆነም የሀገራችንን ባንዲራ በተመለከተ ለእኔ እጅግ ትርጉም ያለው ውይይት ዜግነታችን ለዜጎች ምን ትርጉም አለው የሚለው ነው፡፡ እኔ እስከማውቀው ድረስ መጠኑ ቢለያይም በሁሉም የሀገራችን መንግስታት ዘመን ወገኖቻችን ወደውጪ እየተሰደዱ ነበረ፤ አሁንም እየተሰደዱ ነው፤ ስደቱም እየጨመረ ነው፤ ወገኖቻችን ወደውጪ ተሰደውም የኛን ሀገር ዜግነት ትተው የሰለጠኑ ሀገራትን ዜግነት  እየወሰዱ ነው፡፡ ይህ ለምን ሆነ? መልሱ ግልፅ ነው፤ ሀገራዊ ዜግነታችን ለሁላችንም እኩል ዋስትና ሊሆነን አልቻለም፡፡

 

 

እስቲ አስቡት፤ ጎዳና ላይ ለሚኖሩ ወገኖቻችን ኢትዮጵያዊ ዜግነት ትርጉም ምን ያህል ነው? ሀገራችንን ዜጎችዋ በባህርና በአየር ቀን ተለሊት እንደምንም ጥለዋት ሊሰደዱ የሚፈልጉ ከሆነ የውይይታችን ዋና ርእስ መሆን ያለበት ስለዜግነታችን ትርጉምና ለዜጎች የሚሰጠው ዋስትና ነው፡፡ በእርግጥ ባንዲራችን መንግስት በተቀየረ ቁጥር ባይቀያየር ደስ ይለን ነበረ፤ ነገር ግን ያለፈ አለፈ፤ ዱሮ የነበሩት አሁን የሉም፤ ይህ ትውልድ ደግሞ በሰለጠነ አስተሳሰብ ሀገሩንና ዜጎቹን ለማስከበር ድህነትንና አድልዎን በጋራ በመዋጋት ሀገሪቱ ለዜጎችዋ ሁሉ እኩል ትርጉም እንድትሰጥ ማድረግ አለበት፡፡ ስለባንዲራችን ቀለማት ደግሞ ቀስ በቀስ ተወያይተን መግባባት እንችላለን፡፡ ቅድሚያ ለሚሰጥ ቅድሚያ እንስጥ! የሰው ልጆች በረሀብ እየሞቱ ስለባንዲራ ቀለም መነታረክ አግባብ አይመስለኝም፡፡

ስለሆነም ሁላችንም የባንዲራችንን ክብር ከፍ ለማድረግ ለኢትዮጵያ ዜጎች ሁሉ የመኖር ዋስትና መስጠት እንድንችል ማድረግ ይጠበቅብናል፤ ተግባራዊነቱ ከባድ ቢሆንም ቢያንስ ያንን አይነት ህልም እንዲኖረን እንጂ ስለባንዲራችን ቀለማት ብቻ ጭቅጭቅ ውሀ የሚቋጥር አይመስለኝም፡፡ አዎ! ወኔ ያስፈልጋል፤ ለባንዲራችን ክብር ስንል፣ ለዜግነታችን ክብር ስንል፣ የሀገራችን ዜጎች ሁሉ በሀገራቸው ላይ ሰላማዊና የተረጋጋ ህይወት እንዲኖሩ የማድረግ ቆራጥነትና መስዋእት ለመክፈል ወኔ ያስፈልገናል፡፡  በፍፁም የሀገራችን ዜጎች ለምግብና ለመጠለያ ፍለጋ ሲባል ዜግነታቸውን መቀየር የለባቸውም! ዜጎቻችን ከሀገር ቤት ይልቅ ውጪ ሄደው ነፃነት ሊሰማቸው አይገባም፤ በአውሮፓ የስደተኞች ጣቢያ ካሉት የሀገራችን ስደተኞች አንዱ ለቃለመጠይቅ ሲቀርብ ከሚሰጣቸው ምክንያቶች ሊነገረን ቢችል፣ ለምን ጥገኝነት ትጠይቃለህ ቢባል መኖር ስላልቻለኩ፣ ስለራበኝ፣ ቤትና ንብረት ማፍራት ስላቻልኩ፤ የፖለቲካ መብት፣ የመናገር መብት፣ የመተቸት መብት፣ የመጠየቅ መብት፣ ሰርቶ የመለወጥ እድለ ማጣት ወዘተ ሊል ይችላል፤ አንድ አሜሪካዊ ዜጋ ግን እንደዛ ይላል ብለን መጠበቅ የለብንም፤ ስለሆነም ለእኔ ባንዲራ ትርጉሙ ለሁሉም ዜጎች ዋስትና መስጠት ሲችል ነው እንጂ ለክብረ በአላት ብቻ ስለምንጠቀመው አይደለም፡፡

ሀገራችን በውጪ ሀገራት ሀይሎች በተወረረች ጊዜ በሁሉም መንግስታት ጊዜ ወንድሞቻችን ደማቸውንና ህይወታቸውን ሰውተዋል፤ ባለአንበሳውም ቢሆን፣ ምንም ተጨማሪ ምልክቶች ያልነበሩትም ቢሆን፣ አሁን የምንጠቀመው ባለኮከቡም ቢሆን፣ ሁሉም የነበሩን ባንዲራችን መስዋእትነት ተከፍሎባቸዋል፤ በንጉሱ ዘመን፣ ወይም በደርግ ፣ ወይም በአሁኑ መንግስት ለሀገርና ለባንዲራ ክብር ደማቸውንና ህይወታቸውን ለከፈሉት ወገኖቻችን ክብር ስንል የባንዲራ ቀለማት ውይይታችንን ልብ ማለት አለብን፡፡ ህይወታቸውን የከፈሉትን ወገኖቻችንን፣ ባንዲራችን ትክክል ስላልሆነ ትግሉ ልክ አይደለም ማለት የምንችል ይመስለናል? እውነታው ግን የሁሉ ነገር መሰረት ህዝባችን መሆኑን መረዳቱ ላይ ነው፤ የትኛውንም ባንዲራ ይዘው ቢዘምቱም፣ ወንድሞቻችን በዋናነት የዘመቱት የሀገራችንን ህዝቦች ከጠላት ለመከላከልና ሀገራችንን ወደስልጣኔ ለማድረስ ነው እንጂ አንዱ ባንዲራ ላይ የተጨመረው ወይም የተቀነሰው ምልክት ከሌላው የተለየ ስሜት ስለሚሰጣቸው አይደለም፤ በአጭሩ ሀገራዊ መሰረታችንን ህዝብን ብናደርግ ይህ ሁሉ ጥቃቅን ውይይት ባልተሰማ ነበረ፡፡ ክብር ለህዝባችንና ለባንዲራችን ሲባል ህይወታቸውን ለከፈሉ ጀግኖቻችን፡፡

ስለሆነም የባንዲራና የሀገር ትርጉም ሊነጣጠሉ አይችሉም፤ ግን ሀገር ምንድን ነው? ሰዎች የአንድን ሀገር ዜግነት የሚመርጡት ምን ምን መስፈርቶችን በመጠቀም ነው? የሚሉ ጥያቄዎችን መጠየቅ ስለኢትዮጵያዊ ዜግነታችን እንድናስብ ያደርገናል፤ በሀገራችን ከፍተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉት ጭምር ልጅ ለመውለድ ወደአሜሪካን መሄድና ለሚወለዱት ልጆች አሜሪካዊ ዜግነት መፈለግ የተለመደ እንደሆነ እያወቅን፣ ለዜግነታችን ክብርና ትርጉም ለማስገኘት መስራት አለብን እንጂ፣ በልዩነቶች ላይ አትኩረን የአንድነት ሀይላችን ማዳከም የለብንም፡፡ አባቶቻችን የተወሰነውን ትክክል ሌላውን ደግሞ ስህተት ሰርተዋል፡፡ እኛ ከነሱ የተሻለ ማድረግ አለብን፡፡

ፌስቡክ ላይ በቅርቡ ተመሳሳይ ሀሳብ ማንበቤ ትዝ ይለኛል፤ ፀሀፊውን ስለዘነጋሁ ይቅርታ፤ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ልጆቻቸው ኢትዮጵያ እንዲወለዱ የሚፈቅዱ ወላጆች ጥቂት ናቸው ወይም ውጪ የመውለድ እድሉ የሌላቸው ናቸው። የባለሀብት ፣ የባለስልጣን ፣ የፓይለት ፣ የሆስቴስ ፣ ወዘተ ልጆች በብዛት የሚወለዱት አሜሪካ ነው ብሏል። ሀሳቡ የተጋነነ ቢሆንም ሙሉ በሙሉ ውሸት አይደለም፤ ለብዙዎች ኢትዮጵያ አንድ ቀን አሜሪካ ጠቅለው እስኪሄዱ መሸጋገሪያቸው ናት። እነዚህ ኢትዮጵያ የልጃቸው መኖሪያ እንድትሆን ያልፈቀዱ ዜጎች “ኢትዮጵያ ሀገሬ እወድሻለሁ› ሲሉ በዘፈንም ሆነ በተለያዩ አጋጣሚዎች ይደመጣሉ ነገር ግን አውድሻለሁ ሊሉ እንዴት ይችላሉ? ሰው እንዴት በእንግድነት ካለበት ቤት በፍቅር ሊወድቅ ይችላል? ምንድነው ሀገር መውደድ? ፀሀፊው ቀጥሎም፣ እነዚህ ሀገሪቱን ጊዜያዊ መኖሪያ ያደረጉና በቀጣይ ሀገሪቱ የተሻለች መኖሪያነቷ ላይ ጥያቄ ያላቸው ዜጎች የሚበዙት በተለያየ ጊዜ ከነበሩት የሀገራችን መንግስታት ስርዓት ተጠቃሚዎች  የነበሩ ናቸው። ስለሆነም ኢትዮጵያዊነት ብዙ ሊፈተሹ የሚገባ ጉዳዮች አለበት፡፡ ብዙ ታዋቂ ሰዎች ልጆቻቸውን ውጪ ሀገር ቢወልዱም የድምፃዊ ቴዲ አፍሮ አይነቶቹን ደግሞ በዚህ አጋጣሚ ማመስገን ያስፈልጋል፤ ብዙ የመንግስት ሰራተኞችና ዘፋኞች ያለምንም ምክንያት ከሀገር ወጥተው ውጪ ልጆቻቸውን ቢወልዱም ቴዲ አላደረገውም። ልጆቹን ለሀገሩ ነው የሰጣቸው። የቴዲ ልጅ ኢትዮጵያዊ ሆኖ ተወለደ ። ይህ ብዙ ማለት ነው ። ትልቅ ውሳኔ ነው ። ብዙዎች ግን አፋቸው እንጂ ተግባራቸው ኢትዮጵያዊነት ይጎድለዋል በማለት ሀሳቡን ይደመድማል፡፡ ግድ ነው፣ ራሳችችን መጠየቅ አለብን፤ ሀገራዊ ፍቅራችን ምን ያህል ነው?

ከወሊድ ጋር በተያያዘ ብቻ ሳይሆን የገራችን ዜጎች በተለያዩ አጋጣሚዎች ከሀገራቸው ሲወጡና በተለይ ወደአውሮፓና አሜሪካ እንደሁም ወደካናዳ ሲገቡ ከጥገኝነት ጥየቃ ጋር በተያያዘ ዜግነታቸውን ይቀይራሉ፤ አንዳንዶቹ ደግሞ የጥገኝነት ጥያቄው ሀገርን እንደሚያስክድ የሚሰሙት ከሀገር ወጥተው አውሮፓ ወይም አሜሪካን ሀገር ከደረሱ በኋላ ነው፤ እኔ ዴንማርክ በነበርኩበት ጊዜ አንድ ወዳጄ ጥገኝነት እንደሚጠይቅ አውቆ በአጭር ስልጠና ሰበብ ከሀገር ቤት ቢሰደድም ዴንማርክ ከደረሰ በኋላ ስለጥገኝነት አጠያየቅ ዝርዝር ሲረዳ ከሀገር ቤት ለመውጣት የወሰነው ውሳኔው ትክክል አልነበረም ሲል ሰምቼዋለሁ፤ ምክንያቱም አንድ ሰው እንደስደተኛ ጥገኝነት ሲጠይቅ ብዙውን ጊዜ ጥገኝነት የሚጠይቅበትን ምክንያት ለነብሱ ዋስትና እንደሌለው በመጥቀስ ነው፤ ይህም ማለት ከተቃዋሚ ፖለቲካ ጋር በተያያዘ ወይም ደግሞ በተፈጥሮ አደጋ ምክንያት በሀገሩ ለመኖር የሚያስችለው ሁኔታ የለም በማለት ነብሱን ለማትረፍ ጥገኝነት ይጠይቃል፤ ለዚህ ሁሉ ደግሞ ተጨባጭ መረጃ ያስፈልገዋል፡፡ ለምሳሌ ይህ መጽሀፍ እየተፃፈ በነበረበት ወቅት የሴሪያ ዜጋ የሆነ ሰው ሀገሩ ላይ ለህይወቱ አስጊ ነገር እንዳለ ለማሳወቅ ምንም ማስረጃ ላይጠየቅ ይችላል፤ ምክንያቱም ሴሪያ በጦርነት እየታመሰች ስለሆነ የሴሪያን ፓስፖርት ወይም መታወቂያ መያዝ ለጥገኝነት ጥያቄ በቂ ማስረጃ ይሆናል፤ እኔ ዴንማርክ በነበርኩበት ወቅት ከምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ለጥገኝነት ጥያቄ ብዙ ማስረጃ የማይጠየቀው ለኤርትራዊና ለሶማሊያ ዜጎች ነው፡፡ ሌሎቹ ሀገራት ሰላማዊ ናቸው ተብሎ ስለሚታመን ጥገኝነት ለሚጠይቁት ዜጎች የመጡበት ሀገር ሰላማዊ መሆን ጥሩ ዜና አይደለም፡፡ ሀገራቹ ሰላም ነው ተብለን ጥገኝነት መጠየቅ አልቻልንም በሚል ሰበብ ሀገር ቤት ጦርነት እንዲነሳ የሚፈልጉ ጥገኝነት ካምፕ ያሉ ወገኖቻችን መኖራቸውን መዘንጋት የለብንም፡፡

ምክንቱም፣ አጠያየቁ ከሀገር ሀገር ቢለያይም፣ በጥገኝነቱ ጥያቄ ወቅት ጥገኝነት የሚጠይቀው ግለሰብ መታወቂያውን ይዞ ፖሊስ ጋር በመሄድ ከሀገሩ ህይወቱን ለማትረፍ አምልጦ መምጣቱንና ጥገኝነት እንደሚፈልግ ያሳውቃል፤ ቀጥሎ ወደስደተኞች ማረፊያ ይወሰድና መታወቂያውን ለፖሊሶች ይሰጣል፤ ከዛ ጊዜ ጀምሮ የሀገሩን ዜግነት አልፈልግም ብሎ ሰጠ ማለት ነው፤ ስለሆነም የተቀበለው ሀገር ስሙን ግለሰቡ ለመጣበት ሀገር የውጪ ጉዳይ ቢሮ ሪፖርት ያደርግና ጥገኝነት ጠያቂውን ግለሰብ በስደተኞች ካምፕ ያቆዩታል፤ ቀስበቀስም የጥገኝነት ጠያቂው ጉዳይ ለፍርድቤት ይቀርብና ውሰኔ ይሰጥበታል፡፡ ይህን ውጣውረድ እኔ አጠር አድርጌ ያስቀመጥኩትን ያህል በአጭር ጊዜ የማያልቅ፣ ምናልባትም እስከ አስር አመት የሚወስድ ሂደት መሆኑንም መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ በዴንማርክ ሀገር ይህ ሂደት ቢያንስ ሰባት አመት ይወስዳል፤ ይህ ማለት ደግሞ ጥገኝነት ጠያቂው ግለሰብ ለሰባት አመታት በስደተኞች ካምፕ ውስጥ በቁም እስር ይኖራል ማለት ነው፡፡ በዚህ መሀል ተስፋ መቁረጥ፣ ሱስ መጀመር፣ ጭንቀት፣ የወላጆችና የቤተሰብ ናፍቆት ይኖራል፣ እጅግ ከባድ ችግር ሀገር ቤት ቢከሰትም ጥገኝነት ጠያቂው የሌላ ሀገር ዜግነት እስኪያገኝ ድረስ ወደሀገሩ መመለስ አይችልም፤ በአጭሩ ራስን በፈቃደኝነት እስርቤት ማስገባት ማለት ነው፤ ስለሆነም ምንም ሳይቸግራቸው ከሞቀ ቤት ተነስተው ስደትን የሚመርጡ ወጣቶቻችን ደግመው ደጋግመው ሊያሰቡበት ይገባል፡፡

ከላይ እንደጠቀስኩት ለምሳሌ በዴንማርክ ሀገር ህግ መሰረት ግለሰቡ ጥገኝነት ከጠየቀበት ጊዜ ጀምሮ ህጋዊ የመኖሪያ ፍቃድና የስራ ፍቃድ እንዲሁም ፓስፖርት እስኪያገኝ ድረስ ቢያንስ 7 አመት ሊፈጅ ይችላል፤ ስለሆነም ጥገኝነት ጠያቂው ግለሰብ በስደተኞች መጠለያ ለመኖር መሰረታዊ ነገሮች እየተሰጡት ለሰባት አመት ይኖራል ማለት ነው፡፡ እጅግ ከባድ የሚባለው የጥገኝነት ኑሮ ጊዜ ይህ ጊዜ ነው፤ ምክንያቱ ጥገኝነት የጠየቀው ግለሰብ እጅግ አስቸኳይ ጉዳይ ቢኖረውም ወደሀገሩ መመለስ አይችልም፤ እንደልብ መስራትና መማር አይችልም፤ ስለሆነም ህይወቱ ተስፋ አስቆራጭ ይሆናል፤ በዚሁ ምክንያትም ብዙዎቹ የአደገኛ ሱስና የአእምሮ ህመም ሰለባ ይሆናሉ፡፡

በዴንማርክ ቆይታዬ ኮፐንሀገን አቅራቢያ ያለ የቀይመስቀል የስደተኞች ጣቢያን መጎብኘት አጋጣሚው ነበረኝ፤ በጣቢያው ካሉት ስደተኞች ሁለት የሀገራችንን ወጣቶች የማነጋገሩ እድል ነበረኝ፤ ልጆቹ መጀመሪያ ወደዴንማርክ የገቡት በትራንዚት ወደስዊዲን ከወላጆቻቸው ጋር እየሄዱ ቢሆንም፣ ኮፐንሀገን አውሮፕላን ጣቢያ ወላጆቻቸው ጥለዋቸው ተሰወሩ፣ ፖሊሶ ልጆቹን ወስደው የስደተኞች ካምፕ እንዳደረሱዋቸው ነግረውኝ፣ ልጆቹ ህይወታቸው እጅግ አሰልቺና ከባድ እንደሆነም አስረድተውኛል፤ ስለሆነም ከባድ ሱስ ተጠቂ ናቸው፤ ሀገራቸውና ዘመዶቻቸውን እጅግ እንደናፈቁም ነግረውኛል፤ እነኛን ልጆች እዛ ካምፕ ያየሁ እለት እጅግ አዝኜ ነበረ፤ በልቤም አለቀስኩኝ፤ በአብዛኛው የምእራቡ አለም የስደተኞች መጠለያ ውስጥ ካሉት የሀገራችን ወጣቶች አብዛኞቹ እዚህ ሀገር ቤት ጥሩ ገንዘብ ያላቸው ቤተሰቦች ልጆች ናቸው፤ ተስፋ ለመቁረጥና ለአደገኛ ሱስ ሰለባ የሚሆኑትም ከሀገር ቤት ከመሄዳቸው በፊት ምንም አይነት የህይወት ፈተና አይተው ስለማያውቁ ነው፤ በህገወጥ መንገድ በሶማሊያና በሊቢያ ባህር አቆራርጠው ከሀገር የሚወጡት ወጣቶች እጣ ፈንታ ደግሞ የባሰውን የተወሳሰበ ነው፤ ምንክያቱም እነኚህ ወጣቶች  በአውሮፓ፣ በአሜሪካ፣ በካናዳና በአውስትራሊያ የስደተኞች መጠለያ ከመድረሳቸው በፊት ከባድ የህይወት ፈተና ይፈተናሉ፤ አንዳንዶቹ ተገድለው ኩላሊታቸውና ሌሎች የሰውነት ክፍሎቻቸው እንደሚወሰዱም አንብቤያለሁ፤ ለዚህ ሀሳብ ማጠናከሪያ በቅርቡ በሜዲትራኒያን ባህር ስደተኞችን ይዘው የሚሰምጡ ጀልባዎችን ዜና ብዛት ማየቱም በቂ ነው፡፡

በስደት ሕይወት ልጆቻቸውን ጥለው የሚጠፉም ወላጆች አሉ፤ በእርግጥ ልጅን የሚያህል ነገር ጥሎ ለመሄድ የሚያስደፍር ከባድ ችግር ሊሆን እንደሚሆን ለመገመት ቢቻልም ሁሉ ወላጅ ግን እኩል ችግረኛ ናቸው ማለት አይቻልም፤ አንዳንዶቹ ወላጆች ለብልጭልጭ ነገር ያላቸው ጉጉት እጅግ ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ የልጆቻቸውን ህይወትም አሳልፈው ሊሰጡ እንደሚችሉ ምንም ጥያቄ የለውም፤ በእርግጥ ዴንማርክ ሀገር በህይወቱ የደረሰ ማንኛውም ጤናማ ሰው ምግብና መጠለያ በቀላሉ ከስደተኞች ካምፕ ሊያገኝ ይችላል፤ ነገር ግን በተለይ ህፃናትን ለጥገኝነት ሕይወት ለብቻቸው ጥሎ መሄድ ከባድ ጭካኔ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡  ስለዚህ ሁላችንም ሀገራችንን ዜግነታችንንና እጃችን ላይ ያሉትን በጎ ነገሮች አክብረን በሀገራችን ላይ ጠንክረን ብንሰራ ከፀፀት ራሳችንን እናድናለን፤ ልብ ያለው ልብ ይበል፡፡

ህንዶች ብዙ የሚያስቀና ሀገራዊ ፍቅር አላቸው፤ ከህንዶች ጋር ሲወዳደር ብዙዎቻችን ለሀገራችንና ለሀገር ምርቶች ያለን ፍቀር በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ ከህንዶች ብዙ መማር እንችላለን፡፡ እስከዛሬ በተለያዩ አጋጣሚዎች ያገኘሁዋቸው ህንዶች የሚለብሱት የሀገራቸውን ባህላዊ ልብስ ነው፡፡ የሚመገቡትም የራሳቸውን ምግብ ነው፡፡ የሚገዙትም የሀገራቸውን ምርቶች ነው፡፡ በህንድ ሀገር የተሰራ የሚለው ለነሱ ትልቅ ዋጋ አለው፡፡ ለኛ ደግሞ በሀገራችን የተመረቱ ምርቶች የዝቅተኛ ጥራት ምሳሌ ናቸው፡፡ ጫማ ወይም ሱሪ ስንገዛ ባለሱቆቹ ‹የውጪ ሀገር ምርት ነው፣ የቱርክ ምርት ነው፤ የጣሊያን ሀገር ምርት ነው፤ የታይላንድ ነው ወዘተ› ብለው ነው ከፍ ባለዋጋ መግዛት እንዳለብን የሚያስረዱን፡፡ በጣም የሚገርመው ነገር ህንዶች ለብዙ ዘመናት የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ሆነው የቆዩ ቢሆንም የራሳቸውን ባህል አስጠብቀው መቆየት ችለዋል፡፡ ለራሳቸው ሀገርና ባህል ያላቸው ክብርና ፍቅር ለኛ አይነቶቹ ህዝቦች ጥሩ ምሳሌ ያደርጋቸዋል፡፡ የህንድ አለባስ እና የህንድ ሀገር ፊልሞችም ጭምር ወደኛ ሀገር በገፍ እየገቡ ነው፡፡ ቅኝ ግዛት ሳንገዛ እንዴት ከህንዶች ባነሰ የሀገራችንን አለባበስና የሀገር ምርትን ትተን የውጪሀገር ምርትን መጠቀም እንደቻልን ግራ ያጋባል፡፡ ሳናውቅ ልባችን ከሀገር ውስጥ የለም፤ ልባችን ውጪ አምላኪ ሆኖብናል፡፡ በእርግጥ ከዱሮው በተሻለ አሁን አሁን የሀገራችን ብሄር ብሄረሰቦች ልብሶች ለክብረ በአላት መልበስ እየተለመደ መጥቷል፡፡ ነገር ግን ከባህላዊ ሸማኔዎች በተጨማሪ ዘመናዊ ፋብሪካዎችም ሀገር በቀል ልብሶችን በብዛትና በጥራት ለገበያው ማቅረብ አለባቸው፤ እኔ ራሴም ሱሪ ወይም ሸሚዝ መግዛት ሲኖርብኝ አንድም ቀን ባህላዊ የልብስ ቤቶችን ጎብኝቼ አላውቅም፡፡ ሀሳቡም ባህለዊ ልብስ መግዛት ትዝ ብሎኝም አያውቅም፤ የሀገራችንን ልብሶች ለበአል ቀናት ብቻ የሚለበሱ አድርገን አእምሮአችን ውስጥ ስለናል፤ ቢሆንም የሀገራችን ባህላዊ አልባሳት በልብስ ዲዛይነሮች ተሻሽለውና በብዛት ተመርተው በየቡቲኮች መግባት እንዲችሉ መደረግ ያለበት ይመስለኛል፡፡ ከሁሉ በላይ ግን የአልባሳቱ ጥራት የበለጠ መሻሻል አለበት፡፡  በጫማዎች በኩል እየተደረገ ያለውን እድገት እንደምሳሌ መውሰድ ይቻላል፡፡ ዛሬ ዛሬ እዚሁ ሀገራችን የተመረቱ ብዙ ቆንጆ ቆንጆ ጫማዎች በአነስተኛ ዋጋ ገበያ ላይ ማግኘት ተችሎአል፡፡ ዱሮውንም በአፍሪካ በቀንድ ከብት ብዛት አንደኛ የሆነች ሀገር ቆዳና ሌጦን ወደውጪ ልካ የጫማና የሌዘር ምርቶችን ከውጪ ማስገባትዋ የሀገሪቱን የማምረት ኢንዱስትሪ የእድገት ደረጃ ዝቅተኛነት ቆንጆ ማሳያ ነው፡፡ ካልሆነ ጥሬ እቃው እዚሁ ሀገራችን እያለ እንዴት የቆዳ ምርቶች ከውጪ ወደሀገራችን እናስገባለን? የቆዳ ኢንዱስትሪያችን እድገት ቢኖረው አብዛኛው የሀገራችን ህዝቦች በሀገራቸው የተመረቱ የሌዘር ምርቶችን መልበስ ነበረባቸው፡፡ ሁላችንም ወደቡቲኮች ስንሄድ የሀገራችንን ምርቶች፣ የሀገር ባህል ልብሶችና አልባሳት፣ የሀገር ውስጥ ጫማዎችን ወዘተ በመጠቀም የሀገራችንን አምራች ኢንዱስትሪዎች ብናበረታታ ከህዝባችን ብዛት የተነሳ የአምራች ፋብሪካዎች ገቢ ከፍ ይላል፡፡ እኛም ለራሳችንና በሀገራችን ምርቶች ያለን መተማመን እየጨመረ ይሄዳል፡፡ ልብ ማለት ያለብን የሀገር ፍቅር ስንል የገንዘብ አጠቃቀምንም ያጠቃልላል፡፡

እዚህ ሀገራችን በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ተቀጥረው የሚያስተምሩ የህንድ መምህራን የወር ደሞዛቸውን ተቀብለው በቀጥታ ወደሀገራቸው ባንኮች ልከው ያጠራቅማሉ፡፡ እኛስ? ውጪ ሀገር ካሉ ኢትዮጵያውያን ስንቶቹ ናቸው እዚህ ሀገራችን ባንኮች ውስጥ ብራቸውን የሚያጠራቅሙት? ኢትዮጵያውያኑ እንደዛ እናድርግ ብለው ቢያስቡስ የሀገራችን የባንኮች አሰራር ምን ያህል ቀልጣፋ ነው? አንዳንዴ የባንክቤት ሰራተኞች የራሳችንን ብር ለማውጣት ስንሄድ ብር ልመና የሄድን ይመስል ስናናግራቸው ተኮሳትረውና እየተነጫነጩ ተቃጥለን እንመለሳለን፡፡ አሁን ያለው የባንኮቻችን አሰራር ውጪ ሀገር ያሉዜጎችን ገንዘባቸውን ሀገራችን ባንኮች ውስጥ እንዲያስቀምጡ ማበረታታት አለበት፡፡ ለሁሉም የሀገር ፍቅርን ከህንዶች ብንማር፡፡

የልጅነት ጊዜ

የተወለድኩት በቀድሞው የአርሲ ዞን ሴሩ ወረዳ ሴሩ 01 ቀበሌ ነው፤ የሴሩ ከተማ ከ1935 ጀምሮ በጣሊያን ወታደሮች መመስረትዋን ወላጅ አባቴ አጫውቶኛል፤ በወቅቱ የባእዳ ጦርነት በሚባል የጣሊያን ጦር ከተማዋን መቆጣጠሩንም ሰምቻለሁ፤ ቀደምት የሴሩ ከተማ ነዋሪ ሆነው ከሚታወቁት መካከል አቶ በላቸው መሸሻ፣ ደሳለኝ ሀብተየስ፣ አበበ አገኘሁ፣ አለሙ ዲሪሳ፣ ሁሴን ቱቄ፣ አሊዪ ጂብሮ፣ ሙሀመድ ከብርሳሊያ ወዘተ መሆናቸውንም ጭምር አባቴ ነግሮኛል፡፡ አባቴ በሶራ ጦርነትም ተሳትፎ ነበረ፣ በ1969ዓ.ም. ሶማሊያ ሀገራችንን በወረረችበት ጊዜ የሀገራችን መንግስት ከኩባ መንግስት ድገፍ ጠይቆ ጦርነቱን ማሸነፋንንም ሰምቻለሁ፡፡

አባቴ አቶ ረታ አለማየሁ ከአባቱ ከአቶ አለማየሁ ገብረጻዲቅና ከእናቱ ከወ/ሮ ይመኙሻል ናደው በአርሲ ዞን ሴሩ ወረዳ መሪቃ ቀበሌ ገበሬ ማህበር በ1940 አካባቢ ተወለደ፤ ወደ ዝርዝር የልጅነት ጊዜዬ ከመግባቴ በፊት የተነገረኝን ያህል ለልጆቼ ማስታወሻ ይሆን ዘንድ የቤተሰቦቼን የዘር ሀረግ ልዘርዝር፤ መምህር ናደው ወልደየስ፣ ወልደየስ ሀብተ ገብርኤል፣ የትውልድ ሀገራቸው ወደምንጃር ሲሆን በልጅነታቸው ወደሀረር ጨርጨር ኖረዋል፣ አቶ ናደው ቄስ ነበሩ፣ ነገር ግን በጣሊያን ጊዜ በኣዳ ጦርነት ጊዜ ከሀረር ወደአማለማ ታቦት የአሁኑን የሴሩ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ታቦት ይዘው ተሰደዱ፤ አማለማ ሆነው አከባቢው ስላልተመቻቸው ፣ ለተወሰነ ጊዜ ከኖሩ በኋላ ሌሎች ክርስቲያኖች ጋር ለመቀራረብ ወደሴሩ መጡ፣ በቅርበቱ የነበረው የአርቦኜ ጎሎ ኪዳነ-ምህረት ቤተክርስቲያን ነበረ፣ ስለሆነም ታቦቱንና ቤተሰባቸውን ይዘው አርቦኜ ይገባሉ፤ ነገር ግን ቀስ በቀስ ሴሩ አከባቢ ሰው እየበዛ ሲሄድ፣ ቄስና ዲያቆን የሌለ ስለሆነ ለአከባቢው ሰው የሚባርክና ክርስትና የሚያነሳ ካህን ይፈለግ ነበረ፣ ስለሆነም ታቦቱን ይዘው ሴሩ መጡ፣ ቀጥሎ ከእነ ሀብተየስ የአቶ ሳህለ ሀብተየስ አባት ጋር ተገናኙ፣ ቀጥሎ ሴሩ ከተማ ምሬ ማዶ ተብሎ በሚጠራው ቦታ የቤተክርስቲያን መስሪያ ቦታ ተሰጣቸው፣ ገብረኤል ቤተክርስቲያንም ሴሩ ምሬ ማዶ ተሰርቶ ኑሮ ተጀመረ፣ ነገር ግን በአከባቢው በተደጋጋሚ የሰደድ እሳት ይነሳ ስለነበረ ቤተክርስቲያኑን ከነበረበት ወደአሁኑ የሴሩ ገብረኤል መቀመጫ መቀየር አስፈላጊ ነበረ፡፡ የመጀመሪያው የሴሩ ገብረኤል ካህን መምህር ናደው ነበሩ፤ ታቦቱም በ1906ዓ.ም. በምሬ ማዶ ተመሰረተ ብሎ አባቴ ነግሮኛል፡፡

የመምህር ናደው ባለቤት እህተስላሴ ሀብተወልድ ነበሩ፤ ልጆቻቸውም ወደሬ ናደው(የመምህር ጥበቡ እናት ጂዳ ሀሊላ)፣ ይመኙሻል  ናደው (የአቶ በቀለ፣ የረታ፣ የቡዝዬ፣ የበለጠ፣ የጀማነሽ፣ የንጋትዋ፣ የበላይነሽና የጎርፌ እናት)፣ ፈቀደ ናደው (የውዴና የጌጤ እናት)፣ ማህደረ ናደው (የደስታ፣ የታዬ፣ የቀለሟ፣ የስንቅነሽ፣ የከበቡሽ፣…. የዳምጠው፣ የተሸመ እናት)፣ መከበበ ናደው (የክትነሽ፣ የየምሩ፣ የሽመልስ፣ የብሩክ፣ የመስፍንና የዝማም እናት)፣ ሀይለስላሴ ናደው፣ ይጥና ናደው፣  ቀፀላ ናደው (ልጆቹ አያሌው፣ ይገዙ፣ እታገኝ፣ ደጅጥኑ)፡፡ የአባቴ የአቶ ረታ እናት ወ/ሮ ይመኙሻል ናደው የአቶ በቀለ መኮንን (ልጆቹ ዘሪሁንና ሄኖክ) ረታ አለማየሁ (ልጆቹ አልማዝ/ዘውዴ፣ ፍቃዱ፣ ታዬ፣ አበበች፣ ወገኔ፣ ወይንሸት) ቡዝዬ አለማየሁ( ልጆችዋ አበራሽ፣ አበበ፣ ተዋበች፣ አክሊለ፣ አሰለፈች፣ከበደ፣ ክትነሽ፣ ሲሳይ) በለጠ አለማየሁ (ልጆቹ አባይነሽ፣ መሰረት፣ አቡ፣ ጎሳ፣ ሙሉ፣ ወይኑ፣ ጋሻው፣ጫልቱ፣ ሲሳይ፣ ብሩክ)፣ ጀማነሽ አለማየሁ (ልጆችዋ ሸዋዬ፣ ገላኔ፣ ፈይሴ፣ ሁሪያ)  ንጋትዋ አለማየሁ (ልጆችዋ አረጉና ሲሳይ) ፣ በላይነሽ አለማየሁ (ልጆዋ ሽመልስ፣ ወይንሸት፣ ጥላሁን፣ ሚሚ) ጎርፌ አለማየሁ (ልጆችዋ አስናቀች፣አልማዝ፣ ዜና፣ ዝማርጌ፣ ሚሚ፣ አቡ) ናቸው፡፡

የአባቴ አባት አቶ አለማየሁ ገብረፃዲቅ ደግሞ የዘር ሀረግ መነሻ መንዝ ሲሆን አቶ አለማየሁም የጣሊያንን ጦር ተዋግተው ነበረ፣ አቶ አለማየሁ አንድ ወንድምና አንድ እህትም ነበራቸው፣ ስማቸውም መርኔ ገብረፃዲቅ(ልጆቻቸው የሺጥላ እና አስናቁ ይባላሉ) እና ጌጤ ገብረፃዲቅ (ልጆቻቸው በቀለ ሰጉ፣ አስታጥቄ ሰጉ ና ይርጉ ሰጉ ነበሩ)፡፡ የበቀለ ሰጉ ልጆች ከበደ፣ ማሚቱ፣ ባዩ፣ ሰለሞን፣ ሽመልስ፣ ታደሰ፣ መለሰ፣ ተገኔ፣ እሸቱና ጓዳዬ ናቸው) እንዲሁም የይርጉ ሰጉ ልጆች አብሬ፣ ስንቅነሽ፣ ቦጋለች፣ አስናቁ፣ ይመኙ፣ መዳኒት ) ሲሆኑ የአስጣጥቄ ሰጉን ልጆች ስም ዝርዝር ማግኘት አልቻልኩም፡፡

በቅርቡ አባቴ ሊጠይቀኝ ሀዋሳ ነበርና በተገኘው አጋጣሚ ስለሀገራችን ወቅታዊ ጉዳይና ስለቤተሰባችን የዘር ሀረግ የሚያውቀውን ያህል ጠይቄው ነበረ፤ አባቴ መንግስት ቆራጥ መሆን አለበት የሚል አቋም አለው፣ እንዲሁም ሰራተኞቹ የመንግስትን ህግ በትክክል ተግባራዊ ማድረግ አለባቸው ካልሆነ ሀገር ይዳከማል፣ ሙስና ይስፋፋል የሚል እምነት አለው፡፡ አባባሉም የህግ የበላይነት መከበር አለበት፣ መመሪያዎችና ፖሊሲዎች ተፈፃሚ መሆን አለባቸው የሚል እንደሆነ እገነዘባለሁ፡፡

የእናቴን ዝርዝር የዘር ሀረግ አሁንም በማጥናት ላይ ነኝ፤ ቢሆንም የተወለደችው ከፊቼ ገጠር ውስጥ ደገም በሚባል አከባቢ ከአባትዋ ከአቶ ሮቢ አያኔ እና ከእናትዋ ከወ/ሮ አደሩ አረዶ ነው፡፡ እናቴ ሶስት ወንድሞችና ሶስት እህቶች አላት (ቶሎሳ፣ ደምሴ፣ በደሳ፣ አባነሽ፣ እሰዪ፣ ጂቱ) ነብሱን ይማረውና ቶሎሳ የደርግ ወታደር የነበረ ሲሆን ልጆቹም ደረጄ፣ አስቻለው፣ ማርሸት፣ ቡዝዬ፣ መካሻ ሲሆኑ የበደሳ (ነብሱን በገነት ያኑረው) ልጆች ንጋቱና አብዮት ናቸው፣ የእሰዪ ልጆች ሺብሬ፣ ታዬ፣ ቹቹ ሲሆኑ የጂቱ ልጆች ደግሞ ፀጋዬ፣ መንግስቱ፣ ፀጋዬ፣ አባና ሚሚ ናቸው፡፡ እናቴ ከትውልድ ቦታዋ ከሸዋ ደገሞ ወደአርሲ የመጣችው በልጅነትዋ በወላጆችዋ አለመግባባት ሲሆን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ወደ ሸዋ ሄዳ ታውቅም ነበረ፡፡ ከቦታው ርቀት የተነሳ፣ እኛም ከዘመዶቻችን ሳንተዋወቅ ብዙ ጊዜ ቆየን፤ በአርሲ ሴሩና አከባቢው ብዙ ከሸዋ ወደአርሲ የመጡ ሰዎች አሉ፤ ወደአርሲ የመጡበትም ዋናው ምክንያት ሰፋፊ የእርሻ መሬት በአርሲ ይገኝ ስለነበረ ነው፡፡

ይህ መፅሀፍ ብዙ ቦታዎች ይደርሳል፤ ብዙ ሀሳቦችንም ይነካካል፤ በዚህ ሁሉ ሀሳብ ውስጥ ግን የልጅነት ጊዜዬን ያሳለፍኩበትንና የተወለድኩባትን የሴሩን ከተማ መጥቀስ የግድ ነው፤ ሴሩ ከተማ የዚህ መፅሀፍና የእኔ ህይወት መነሻ ናት፤ ይህንን መፅሀፍ ለልጆቼ ብዬ ስለምፅፍ፣ ልጆቼ ደግሞ ከሁሉ ታሪክ በፊት ቀድሞ እንዲነገራቸው የሚፈልጉት የራሳቸው ማንነትን ነው ብዬ አምናለሁ፤ ምክንያቱም እኔ የራሴን ወላጆች የዘር ሀረግ ለማወቅ ብዙ ጉጉት የነበረኝ ቢሆንም በዚህ መልኩ የተጻፈ መረጃ ቢኖር ብዬም እመኝ ነበረ፡፡

የኔ የትውልድ በአርሲ ዞን፣ ሴሩ ወረዳ፣ ሴሩ 01 ቀበሌ ሲሆን የትውልድ ዘመኔ መች እንደሆነ በትክክል ሊነግረኝ የሚችል ሰው አልተገኘም፡፡ ስለሆነም የእኔ እድሜ ስንት እንደሆነና የልደት ቀኔን ስጠይቅ ከእናቴና ከአባቴ የማገኘው መልስ የተለያየ ነው፡፡ እናቴ የተወለድከው በጥቅምት ወር ነው ስትለኝ አባቴ ደግሞ አይ አይደለም ያንተ የልደት ወር ሀምሌ ነው ይሉኝ ነበረ፡፡ ማንኛቸውን ልመን? በስንት አመተ ምህረት ብዬ ስጠይቅ አባቴ በ1973 ሲለኝ እናቴ ደግሞ አመተ ምህረቱን አላውቀውም ትለኛለች፡፡ ለትምህርት ወደውጪ ሀገር ሄጄ በተደጋጋሚ እድሜዬንና የልደት ቀኔን ስጠየቅ ለመመለስ ሳቅማማ ጠያቂዎቹ ግራ ይገባቸው ነበረ፤ የኢትዮጵያዊነት / በተለይ ከገጠር ለመጣነው ማለቴ ነው/ አንዱ መገለጫችን እድሜያችንንና የልደት ቀናችንን በትክክል መናገር አለመቻላችን ነው፡፡ በእርግጥ ትክክለኛ እድሜያቸውን እያወቁ ወጣት ለመባል ቀንሰው የሚናገሩ ቢኖሩም፡፡ ለሁሉም የራሴን እድሜ ለማወቅ ትምህርት ቤት የገባሁበትን አመት 1980/ እንደመነሻ አድርጌ በራሴ የሂሳብ ስሌት ትምህርት ቤት ስገባ ገና የልጅነት /የወተት/ ጥርሴን መንቀሌ ስለነበረ 7 አመቴ እንደሆነ በመውሰድ ከ1980 ላይ 7 በመቀነስ 1973 ተወለድኩ ብዬ እጀምራለሁ፡፡ ከዛ 12 አመት ትምህርት ቤት ቆየሁ፡፡ አራተኛ ክፍል ስደርስ ለሁለት አመት አቋርጬ ስለነበረ አስራ ሁለተኛ ክፍል ስጨርስ የ7+12+2 በድምሩ የ21 አመት ወጣት ነበርኩ ማለት ነው፡፡ ከዛ 4 አመት ለመጀመሪያ ዲግሪ ፣ 2 አመት ለሁለተኛ ዲግሪ፣ 2 አመት ለመጀመሪያ ስራ ልምድ፣ 6 አመት ከሁለተኛ ዲግሪ ጀምሮ በስራ ላይ በአጠቃላይ 21+4+2+2+6 በድምሩ በ2008 አ.ም. የ35 አመት ጎልማሳ ነኝ ማለት ነው፡፡

እንግዲህ አስቡት እድሜየን ለማወቅ ይህንን ሁሉ ስሌት ማስላት ነበረብኝ፡፡ የተወለድኩት ዴንማርክ ሀገር ቢሆን ኖሮ /አይደለም እንጂ/ የልደት ቀኔ፣ሰአቱ እንዲሁም ደቂቃው ጭምር በፌደራል የጤና ማህደር ውስጥ ተመዝግቦ ይቀመጥ ነበረ፡፡ ስለሆነም ከተወለድኩበት ቀን ጀምሮ የራሴ የሆነ መታወቂያ ቁጥርም ይኖረኝ ነበረ፡፡ እኛ ሀገር ግን ዛሬም ድረስ አይደለም ገጠር ለሚወለዱት ህፃናት፣ አዲስ አበባ ከተማ ለሚወለዱት ህፃናትም ቋሚ የልደትና የጤና መረጃ የለንም፡፡ ሰዶ ማሳደድ ቢያምርህ ዶሮህን በቆቅ ለውጥ ማለት ይህ አይደለም እንዴ? ልጆቹ እንደተወለዱ ለምን መረጃቸውን በቋሚ መልኩ አንመዘግብም? ኮምፒተሮች ስለሌሉን ነው ወይስ አዋላጅ ነረሶች ስለሌሉን ?

ወላጆቼ ከኔ ልደት ይልቅ የታላቅ እህታችን እድሜዋን ለመርሳት አስቸጋሪ ነው ይሉናል፡፡ ምክንያቱም ታላቅ እህታችን ስትወለድ ሶማሊያ ሀገራችንን ወረራ አካሂዳ ወደመሃል ሀገር ድረስ ገብታ ስለነበር፤ በስደት ጉዞ ላይ እንዳሉ በሶማሌ ታጣቂዎች ተይዘው አባታችን ከታጣቂዎቹ ጋር መጋጨቱንና ሊገድሉት አስበው ስለህፃንዋ ሲባል ይቅርታ እንደተደረገላቸውና ከዛም ስምዋ ዘውዴ መባሉ ተነግሮናል፡፡ ትክክለኛ ኢትዮጵያዊ ስም አወጣጥ፤ ስም ሁሉ ይህንን አይነት ታሪካዊ ትርጉም ሲኖረው ደስ ይላል፤ እኔም ፍቃዱ የተባልኩት ስወለድ በምጥ ወቅት ብዙ ተጠብቄ እንደነበረና ብዙ ጠብቀው በመሀል የልምድ አዋላጆች ተዘናግተው ሳለ መወለዴንና በአከባው የነበረ አንድ አባት ይህ ልጅ ስሙ ፈቃዱ መሆን አለበት፤ የተቀለደው በእግዚአብሄር ፍቃድ ነው እንጂ እኛ በጠበቅነው አይደለም ብለው ስሜ ፍቃዱ ሆኖ መቅረቱን ሰምቻለሁ፡፡

የህፃናትን እድሜ በተመለከተ ግን ዛሬም ድረስ ገጠር ለስራ ስንወጣ እናቶች የልጆቻቸውን እድሜ የሚነግሩን ከተለያዩ ገጠመኞች ጋር በማያያዝ ነው፡፡ ድርቅ ወይም ሌላ የተለየ የተፈጥሮ አደጋ እንዲሁም የምርጫ ጊዜዎች ለልጆች ልደት እንደማስታሻነት ይጠቀሳሉ፡፡ በገጠር የሀገራን ክፍሎች የልጆን እድሜ ለማወቅ አብሮ ታሪክም ማወቅ ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡ ለምርምር ስራ የተለያዩ መረጃዎች ሲሰበሰቡ የአከባቢውን ቋንቋና ባህል የሚያውቅ ሰው ቢሆን ይመረጣል የሚባለውም ለዚሁ ነው፡፡ የገጠሩ ማህበረሰብ የተለያዩ መረጃዎችን ሲነግረን በቀጥታ ሳይሆን በተዘዋዋሪ ነው፤ እናቴም የታላቅ እህታችን እድሜ ስንት እንደሆነ ብትጠየቅ የምትመልሰው መልስ ‹ሶማሌ ሀገራችንን በወረረች ወቅት የአንድ አመት ልጅ ነበረች› ትለናለች እንጂ ትክክለኛውን እድሜ አታውቅም፡፡ ሶማሊያ ሀገራችን የወረረችው መች ነበረ?

 

 

የልጅ እድሜ ግን ለሀገራችን የህብረተሰብ ጤና እቅድና የልጆች ጤንነት መረጃ ትልቁ ግብአት ነው፤ ምክንቱም የአንድን ልጅ አመጋገብና አስተዳደግን ሁኔታ የምንገመግመው የእድሜ፣ የቁመትና የክብደትን ልኬት ከአለም አማካይ እድገት ጋር በማወዳደር ነው፤ ልጆች ሲታመሙም መድሀኒት ለመስጠት እድሜ ማወቅ ያስፈልጋል፤ ታዲያ ከልጆች እድሜ ላይ የተወሰኑ ወራትን መቀነስ ወይም መጨመር በልጁ የጤና ሁኔታ ላይ ትልቅ ልዩነት ያመጣል፡፡ አንዲት የገጠር እናት የልጅሽ እድሜ ስንት ነው ብትባል 5 አመት ነው ብላ ልትመልስ ትችላለች፤ አምስት የሆነው ግን አራት አመቱ አለፎ በሁለተኛው ወር ሊሆን ይችላል፤ ስለሆነም ልጆ ከተወለደ 50 ወራት ሲሆን በስህተት 60 ወራት ተብሎ ሊመዘገብ ይችላል፤ ይህም ምክንያቱ ብዙ ጊዜ እናቶች የልጆችን እድሜ የሚናገሩት በሙሉ ቁጥር ስለሆነ ነው፤ አንድ፣ ሁለት፣ ሶስት፣ አስር ወዘተ እንጂ የልጆቹን እድሜ አመቱን፣ ወሩንና ቀኑን መጥቀስ እንደሚያስቸግራቸው በምርምር ወቅት መስክ ላይ መረጃ ስንሰበስብ በተግባር አይቻለሁ፡፡ አንዲት የስድስት ልጆች እናት እድሜሽ ስንት ነው ተብላ ተጠይቃ አስራ ስምንት ብላ እንደመለሰች ትዝ ይለኛል፡፡

ስለሆነም የእድሜን ጉዳይ ለልደት በአል አከባበር ብቻ ሳይሆን ለልጆችና እናቶች ጤንነት መለኪያና እቅድና ግምገማ እንደግብአት ስለምንጠቀምበት መረጃው በሚገባ መመዝገብ አለበት፡፡ ለምሳሌ መቀንጨር /እስተንቲንግ/ የሚባለው የአመጋገብ ችግር መለኪያ የሚታወቀው ከህፃናት እድሜና ቁመት በመነሳት ነው፡፡ የልጁ ቁመት በትክክል ቢለካም እድሜው በትክክል ካልታወቀ መረጃው የተሟላ መሆን አይችልም፡፡ ስለሆነም የልጆች የልደት መረጃ በጤና ተቋማት በተገቢው ሁኔታ መቀመጥ አለበት፡፡

ሴሩ ከተማ የአርሲ ዞን የጠረፍ ከተማ ናት፣ በአርሲ በባሌና በሀረርጌ ክፍላተሀገራት ድንበር ላይ የምትገኝ የወረዳ ከተማ ናት፤ ሴሩ መልከአምድርዋ በገደል የተከበበች ሆና አንዲት የ50 ሜትር ያህል ስፋት ያላት ኡላ የምትባል ከገሉ ዙሪያ መውጫ መንገድ አላት… ሴሩ ከተማ በገደል የተከበበች መሆንዋ እጅግ ውብ ተፈጥሮ ነው ያላት… በየአቅጣጫው ዞሮ የባሌንና የሀረርጌን ዳገትና ሸንተረሮች ማየት ታላቅ የመንፈስ እርካታ ይሰጣል.. ወዳጆቼ ከቻላችሁ አርሲ ሴሩ ከተማን እንድትጎበኙ አበረታታለሁ፡፡ እንግዲህ እኔ የማስታወሰው የልጅነት ህይወቴ የተጀመረው ሴሩ ከተማ በነበረ የህዝብ መዋለ ህፃናት ነው፡፡ ከመዋለ ህፃናት መልስ የበጎች እረኝነት ስራ የልጅነት ትዝታዬ ነው፤ የበግ እረኝነቱ እጅግ ብዙ ደስ የሚሉ ትዝታዎችም አለው፣ ለምሳሌ የበጎቻችን ግልገሎች ሲወለዱ ተሸክመናቸው ወደቤት ስንገባ የነበረው ትዝታ አይረሳኝም፤  ከእረኝነቴ ከነበረኝ አሳዛኝ ትዝታዎች፣ አንድ የበግ ሙክት ሌባ ሰርቆብኝ የተገረፍኩት ግርፍ ነው፡፡ ከእለታት አንድ ቀን መምሻ ላይ በጎቼን ከሜዳ ወደቤት እየነዳሁ ወደግቢያችን እንደርስ በጎቹ ከግቢው የሚወጣ ውሻ አስደንብሮዋቸው በሩጫ ወደመጡበት የተመለሱ ሲሆን ፈልገን ሳናገኛቸው ቀርተን በአንድ ምሽት ስምንት በጎችን ጅብ እንደጨረሰብን አስታውሳለሁ፡፡ በጎች አንዴ ከደነበሩ ሲሮጡ ከኋላ የራሳቸው ጭራ እንቅስቃሴ የበለጠ ስለሚያስደነብራቸው በቀላሉ አይቆሙም የሚባለው እውነት ነው ማለት ነው፤ ፍየሎች ግን እንደበጎች አይታለሉም፤ ሮጥ ብለው ወደኋላ ዞረው ያያሉ፤ በጎች ግን አንዴ መሮጥ ከጀመሩ በቀላሉ መቆም የለም፡፡  በግ ሞኚናት ቢባል ስህተት አይደለም

ዋናው የእረኝነት ቦታችን ሴሩ አባስ ሜዳው ነበረ፤ ሴሩ አባስ ደኑ ጥቅጥቅ ሲሆን የተከለለ ነበረ፡፡ አባስ ደን ውስጥ ጅብ፣ ድኩላ፣ ሚዳቆ፣ አሳማ፣ ቀበሮ፣ አልፎ አልፎም ነብር እንዳለ ይወራ ነበረ፡፡ ዛሬ ግን ያሁሉ ደን የለም፤ ዝግባው ሁሉ ተቆርጦ በእርሻ መሬት ተተክቷል፣ መሬቱ አፈሩ ተሸረሸረ፣ በመሆኑም በሀገራችን በረሀማነት ተስፋፋ፡፡ የግብርና ቢሮና የአከባቢ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ቢሮዎች ግን በየወረዳው መኖራቸው ፋይዳው ምን እንደሆነ በፍፁም አይገባኝም፡፡ በእርግጥ የህዝቡ ብዛትና አማራጭ የገቢ ምንጭ ሊታሰብበት ያስፈልጋል፡፡ ምክንቱም ብዙ ወገኖቻችን በከሰል ስራና በእንጨት መሸጥ ይተዳደራሉ፤ ደንና ተፈጥሮ ሀብትን ማልማት ከፈለግን ለነኚህ ወገኖች አማራጭ የስራ እድል መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ የንብ እርባታ፣ የቱሪስት መዝናኛ ለስራ እድል መፍጠሪያ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ወደውጪ ከመሄዴ በፊት የአውሮፓ ሀገራት ከፋብሪካዎች በሚወጣ የተቃጠለ አየር የተበከሉ ናቸው ብዬ አስብ ነበረ፤ ሀገራችንም በተፈጥሮ ሀብት የታደለች ናት ሲባል ስለምሰማ ከሌሎች በተሻለ ደረጃ ያለን ይመስለኝ ነበረ፤ እውነታው ግን ተቃራኒ ነው፤ በአውሮፓ ያሉ ሀገራት ከምንገምተው በላይ ብዙ ጥቅጥቅ ደን አላቸው፡፡  ሀገራችን እየተራቆተች ነው፣ ደኖችን ተጨፍጭፈው፣ ወንዞች ደርቀው፣ አፈር ለምነቱን እያጣ ድህነትን ለመቀነስ ከባድ እየሆነ ይሄዳል፡፡ ስለሆነም ይታሰብበት፡፡

ሴሩ አባስ ሜዳ እረኞች ሆነን፣ የፈረስ ጭራ ሰርቀን ቆርጠን ከቆላ ለሚመጡ ሴቶች እንሸጥ ነበረ፡፡ በሴሩ ቆላማ ክፍሎች የሚኖሩ ወጣት ሴቶች ለትዳራቸው ሲዘጋጁ ከስንደዶና ከፈረስ ጭራ የተዘጋጀ የሚያምር ስፌት ይሰፉበታል፤ እኛም በስርቆት ከተገኘው የፈረስ ጭራ ሽያጭ የዋጂ ሙዝና ሸንኮራ እንዲሁም ቁልቋል እንገዛበት ነበረ፡፡ በዛን ጊዜ በአስር ሳንቲም ሶስት ሙዝ እንገዛ ነበረ፤ ሴሩ በፍራፍሬ የታደለች ከተማ ነበረች፡፡ በተለይ ከዋጂና ከዋቤ  የሚመጣው ሙዝ፣ ፓፓያ፣ ሸንኮራ፣ ብርትኳን የሚገርም ነበረ፡፡ በሴሩ ልጆች ዘንድ ሙዝ ንግድ የታወቀ ስራ ነበረ፤ በተለይ ከዋቤ ወንዝ ውስጥ የሚኖሩት ወረዱቤዎች የሚያመጡትን ጭነት ሙዝ በጅምላ ገዝቶ መቸርቸር በሴሩ ወጣቶች ዘንድ የተለመደ ስራ ነበረ፡፡ እነ አቡሸት፣ ኑራ፣ ሰለሞን፣ ተፈሪ፣ ታዱ፣ አቡ ከበደ፣ ወዘተ ታዋቂ የሙዝ ነጋዴዎች ነበሩ፡፡ የሙዝ ንግዱ ስራ የበለጠ አትራፊ እየሆነ ሲመጣ ወጣቶቹ ለቅዳሜ ገበያ ቀደም ብለው አርብ ምሽት ጎልባ ወደምትባል የወረዱቤዎች ማደሪያ ሰፈር በመሄድ ሙዙን ቀድመው ይገዙ ነበረ፡፡ የሙዝ ንግዱ ትዝታ ለሴሩ ልጆች ብቻ ሳይሆን ከአቅራቢያው ከጂዳና ከበሌ እንዲሁም ከአዴሌ፣ ከሀቤ እንዲሁም ከሮቤ ድረስ ለሚመጡ ነጋዴዎች ቆንጆ ስራ ነበረ፡፡

የሴሩ ሌላው ትዝታዬ ሾካ/ቁልቋል ነው፤ በአስር ሳንቲም 20 ቁልቋል እንገዛ ነበረ፤ አልፎ አልፎም ከመክፈላችን በፊት እየበላን በቁጥር እያጭበረበርን የምንጠግብበት ጊዜም ብዙ ነበረ፡፡ ቁልቋል ሰርቀን ብዙ እርግማንም ተረግመን ነበረ፤ አምላክ ልጅነታችንን አይቶ እርግማኑን ችላ ባይለው ኖሮ፣ የበላነው ቁልቋል መርዝ ሆኖ ይገድለን ነበረ፡፡ በነገራችን ላይ እውነት እርግማን ይደርሳል? ተበድለንም ይሁን ሳንበደል፣ በተለይ በገጠሩ የሀገራችን ክፍል እርግማን የተለመደ ነው፣ ፈጣሪስ እርግማንን ሰምቶ የተረገሙትን ሰዎች ይቀጣ ይሆን? በአርሲ ሴሩ እኛ ልጆች በነበርንበት ጊዜ በባህል አምልኮ እርግማን የተለመደ ነበር፡፡ እስከ ሰባት ቤት ድረስ ዘርን የሚጨርስ ሀይል አለ ተብሎም ይነገር ነበረ፡፡  ይህ ጉዳይ ከባድ ችግር ላይመስለን ይችላል፤ ነገር ግን የገጠሩን ማህበረሰብ አልፎ አልፎ ለመጣላትም የሚያደርስ ጉዳይ ነው፣ በተቃራኒው ደግሞ እርግማንና የባህላዊው አምልኮ በተለይ ሌብነትን ከመከላከል አኳያ ሲታይ እርግማን የፖሊስ ሚና ያለውን ይመስለኛል፡፡ በአንድ ወቅት በሬ ጠፍቶብን ሌቦቹ እርግማን በመፍራት የተሰረቀውን በሬ ከአንድ ወር በኋላ መልሰውልናል፡፡ በመሆኑም የእርግማን ጉዳይ በማህበራዊ ሳይንስ ባለሙያዎች ጥናት ቢደረግበት ቆንጆ ይመስለኛል፡፡ የባህል ሀይማኖትን በተመለከተ ጥናት ለሚያደርጉ ቆንጆ የምርምር ሀሳብ ይመስለኛል፡፡ ከእርግማን ጋር ስለትንም በተመለከተ የሀይማኖት ሳይንስ ተመራማሪዎች አጥንተው የተጨበጠ መረጃ ቢሰጡን ቆንጆ ነው፡፡ ድግምት ደግሞ ሌላው ሁሌም የሚገርመኝ ነገር ነው፤ ለመሆኑ ድግምት እውነት ይሰራል? በልጅነታችን ከብት ስጠፋብን ጅብ እንዳይበላቸው ድግምት ማስደገም የተለመደ ነገር ነበረ፤ ነገር ግን ጅብ አህያን በምሽት ሜዳ ላይ ቢያገኛት ድግምት ስለተደገመባት የሚተዋት ከሆነ ይህንን ጉዳይ በተግባር አንዲት አህያ ገዝቶ አስደግሞ ወደጫካ መልቀቅ ነበረ፤ በሰላም አድራ ከተመለሰች እውነትም ድግምት ይሰራል ማለት ነው፡፡ ከልጅነቴም ጀምሮ ስለድግምት የምሰማውን ማመን አልቻልኩም ነበረ፤ ውሸት ነው፣ አህያዋን ጅብ ቢገኛት እንክት አድርጎ ይበላታል ብዬም አምን ነበረ፡፡ ይህ አስተሳሰቤ ትክክል ካልሆነ በተግባር ተሞክሮ የሚሞግተኝ ሰው ቢሆር ደስ ይለኛል፡፡

በሴሩ ከተማ አባስ ጎሎቤ ተብሎ የሚታወቀው ቦታ ሼክ ሁሴንን /ሼክ ሁሴን በባሌ፣ በአርሲና በሀረርጌ ድንበሮች የሚገኝ ትልቅ የአምልኮ ቦታ ነው/ ለማምለክ ከጂማ ድረስ የሚመጡ ገሪቦች ነበሩ፡፡ የገሪቦቹን መንፈሳዊ ዜማ እያየን ስንደመም እንውል ነበረ፤ ቢሆንም በመሀል ከብቶቻችንን እየረሳናቸው የሰው እርሻ ገብተው እህል ተበልቶ ማታ ግርፍም ይጠብቀናል፡፡ የሴሩ ከተማ ነዋሪ እናቶች የሼክ ሁሴን ሙዳ ጊዜ ሲደርስ በምእመናኑ ምግብ በመሸጥ ቆንጆ ገቢ ያገኙ ነበረ፡፡

 

 

ከእረኝነቱ ጎን ለጎን የአንደኛ ክፍል ትምህርት በ1980 ዓ.ም ጀመርኩ፡፡ በወቅቱ አባቴ የህብረት ሱቅ ዘበኛ ነበረ፡፡ እኔ አንደኛ ክፍል እንደጀመርኩ አባቴም ዘበኝነት ተቀጥሮ ሴሩ ትምህርትቤት ስራ ጀመረ፡፡ በዛን ወቅት የአባቴ የወር ደሞዙ 60 ብር እንደነበረ ትዝ ይለኛል፤ በ60 ብር ደሞዝ የስምንት ቤተሰብ አባላትን የወር ቀለብ ይሸፍናል፡፡ አንደኛ ክፍል ለመመዝገብ እድሜው አልደረሰም ተብዬ በብዙ ልመና ነው የተቀበሉኝ፡፡ ለምዝገባ ስሄድ ከ15 ቀን በፊት ተገርዤ ቁስሉ ስላልዳነ ትምህርት ቤት የሄድኩት ሽርጥ አሸርጬ ነበረ ፡፡ ዛሬ ድረስ ዪገርመኝ የአባቴ ድፍረት ነው፤ አባቴ ወንድ ልጆችን ግርዛት ለመጀመሪያ ጊዜ የጀመረው እኔኑ ልጁን በመገረዝ ነበረ፡፡ እጅግ ከባድ ስህተት ይሳሳት ነበረ፤ የሚገርመው አልተሳሳተም፤ ብዙ ቢያሳምመኝም ቆንጆ አድርጎ ነው የገረዘኝ፤ ቀላል ያሳመመኝ አይምሰላችሁ፤ ኡኡ ነው ያስባለኝ፤ የሰፈራችን ሴት ልጆች ጭምር መጥተው እየተገረዝኩ ለማየት ችለዋል፡፡ ትዝ ይለኛል፣ በግርዛቱ ወቅት ንቅንቅ እንዳልል ሶስት ጎረምሶች ዐጥብቀው ይዘውኝ ነበረ፡፡ ሌላው የሚገርመው ጉዳይ፣ ገርዞኝ እንደጨረሰ የእጅ ባትሪ ድንጋይ የውስጡን ጥቁር ዱቄት ቁስሌ ላይ አደረገልኝ፣ የበለጠ ተቃጠልኩ…ኡኡኡ አልኩ…. (ለመሆኑ የባትሪ ድንጋይ ዱቄት የቁስል መድሀኒት ሊሆን የቻለበት ምክንያት ምን ይሆን? ከኔ ቀጥሎ ወንድሜ ታዬ ነበረ የተገረዘው፡፡

እሱ ግን የኔን ያህን አልጮሀም፤ ከግርዛቱ በኋላ የፈሰሰውን ደማችንን ለመተካት በግ ታረደልን፣  ከዛን ጊዜ ጀምሮ አባቴ የተዋጣለት የባህል ሀኪም ሆነ፡፡ በየቤቱ ተጠርቶ የወንድ ልጆችን ይገርዛል፤ እንጥልም ይቆርጣል፤ ቡዳና ሰይጣን ያስለቅቃል፤ የምች መድሀኒት ይቀምማል፤ የእግር ወይም የእጅ ውልቃት ያክማል ወዘተ ፡፡ የአባቴ የቀልድ ስሙ ዶክተር ረታ አለማየሁ ነበረ፡፡ እውነትም የከተማው የጤና ባለሙያዎች ሳይቀሩ ልጆቻቸውን እንጥል ለማስቆረጥ እኛ ቤት ይመጡ ነበረ፤ አባቴ ጎበዝ አልሞ ተኳሽም ነበረ፡፡ ለፋሲካ፣ ለአዲስ አመትና ለመስቀል በአላት በምንሽሩ ከአባስ ጫካ ውስጥ  ትልልቅ ድኩላ አድኖ ያመጣልን ነበረ፤ ምንሽርና ዲሞፍተር አባቴ ለአደን የሚተማመንባቸው መሳሪያዎቹ ነበሩ፤ ክላሽ ደካማ ናት ይላል አባቴ፣ ለአንድ እንሰሳ አንድ ጥይት ብቻ ነው የሚተኩሰው፤ ጥይት ውድ ስለሆነ ዝም ብሎ መተኮስ የለም፤ ስለሆነም አባቴ ለሚዳቆ ጥይቴን አላባክንም ብሎ እንደሚተው ነግሮኛል::

 

አባቴ የልብስ ስፌት ባለሙያም ነው፤ አዳዲስ ልብሶችንም ይተኩሳል፤ እንዲሁም ገበሬም ነው፤ በአጭሩ ሁለገብ የሆነ ሳይማር ብዙ ስራ መስራት የቻለ ጀግና ነው፡፡

 

እናቴም በሴትነትዋ ጀግና ነበረች፤ ታታሪነትዋና ቁጡነትዋ ሁሌም ይገርመኛል፤ ቁጣን በተመለከተ ከአባቴ ተቃራኒ ናት፤ እሱ ቁጣ የሚባል ነገር የለበትም፤ እስዋ ከተቆጣች የሚያቆማት አልነበረም፤ ቁጡነት በዘር ተላልፎባት ነው መሰለኝ፤ እናትዋም እጅግ ታታሪና ቁጡ ነበሩ፤ እረኛ ሆኜ በጎቹ ጎሮቤት የሰው አትክልት ሲበሉና አትክልት የተበላባቸው ጎሮቤቶች መጥተው ከተናገሩ ጉዴ ይፈላ ነበረ፤ ሁለት አርጩሜ ነው የሚያልቅብኝ፤ እየተገረፍኩ ጭጭ ማለትም ግድ ነው፡፡ እናቴ አረቄ አውጥታ ቤታችን ትቸረችር ነበረ፤ ማታ ማታ አረቄ ለመጠጣት የሚመጡት ደንበኞችዋ የሚያወሩትን ወሬ መስማት ደስ ይለኝ ነበረ፤ አንዳንዱ ሰክሮ የጠጣውን መለኪያ ብዛት የሚረሳም ነበረ፤ ሌላው እዛው የተቀመጠበት መበድ ላይ ሰክሮ ሲመሽ ወደቤቱ ለመሄድ ሲነሳ መነሳት አቅቶት ሲቸገር ማየት ቆንጆ ድራማ የማየት ያህል ደስ ይለኝ ነበረ፤ እንደምንም ከቤት ይወጣና ወደአጥር ስር ጠጋ ብሎ ሽንቱን ሊሸና ሺሞክር ላዩላይ የሚሸናም ብዙ ነው፤ ጊዜው ክረምት ሲሆን በተለይ ጭቃ ውስጥ የሚወድቅም አለ፤ እኛም ሆን ብለን መንገዱን በጭቃ እንዲያዳልጥ አድርገን ሰካራሞችና ገበያተኞች ሲወድቁ እንደሰትባቸው ነበር፤ አንዳንዱ ሰካራም ደግሞ ሞቅ ሲለው የሙዝ መግዣ ይሰጠኝ ነበረ፤ ሙዝ መግዛት ለምጄም ከእናቴም ስር ገንዘብ እሰርቅና በታናሹ ወንድሜ በታዬ አሳብቤ እሱን አስገርፌው አውቃለሁ፡፡ ለሁሉም አረቄ የብዙ ደሀ እናቶች የገቢ ምንጭ ስለሆነች ክብር ይገባታል፤ በዛው ልክ ደግሞ የብዙ ቤተሰብ ትዳር መፍረስም ምክንያት ነበረች፣ በአባቶች ስካር ምክንያት ማለት ነው፡፡ እናቴ አረቄ ስታወጣ እሳቱን በመቆስቆስ ስለማግዛት ከገቢዋ የሙዝ መግዥ ትሰጠኝ ነበረ፡፡ የአረቄ አወጣጥ ቴክኖሎጂ በልጅነት አእምሮዬ ጥያቄ ይፈጥርብኝ ነበረ፤ በጣም የሚገርመው ያለምንም የመንግስት የሙያ ድጋፍ የሀገራችን ደሀ እናቶች የአረቄን አሰራር ቴክኒክ በተሳካ ሁኔታ ከጫፍ እስከ ጫፍ ኢትዮጵያ ማዳረስ መቻላቸው ያስደንቃል፡፡ የአረቄ ነገር መቼም ትዝታው ብዙ ነው፤ የሰፈራችን አብሮ አደጌ የነበረው መገርሳ ወዳጆ ይህችን ተጨማሪ ማስታወሻ ልኮልኝ ነበረ፡፡ “ፍቄ ብዙ ትዝታዎችን አስታወስከን!, ማራኪ ነው፤ ነገር ግን በተጨማሪ ታርኩ ሌላ ነጥብ አስታወሰኝ! ለአረቄ መውጫ የሚሆን ማገዶ/እንጨት/ ስንለቅም ለሙዝ መግዣ የሚሆን ሣንቲም ከሚሰጠን በተጨማሪ አንድ ሁለት መለኪያ የሚሆን አረቄም ይሠጠን ነበር; ሌላው ጉድ ደግሞ ሳንቲም ከመስረቅ በተጨማሪ ሹቢቲም/አረቄ/ ይሠረቅ ነበር”:: በየቤቱ ብዙ ታሪክ ይኖራል፤ እኔም ብሆን ቤተሰብ ቤት በሌሉበት ወቅት የተቀመጠ አረቄ ካለ ትንሽ ጎንጨት ማድረጌ የተለመደ ነበረ፤ የአረቄ ታሪክ ተወስቶ አያልቅም…. በነገራችን ላይ እናቴ በዛ ሁሉ ድካም የምታወጣውን አረቄ ዱቤ ጠጥቶ የማይከፍልም ብዙ ነው፡፡ አንድ አረቄ ዱቤ በመጠጣት ታዋቂ ሰውም ነበረ፤ ያ ሰው ቤታችን ድጋሜ ሲመጣ ገንዘብ ቀድማ ተቀብላ ነበረ የሚጠጣው፤ ምክንያም ከጠጣ በኋላ ብር የለኝም ዱቤ ብሎ ስለሚጠይቅ፡፡

 

 

አንደኛ ክፍል ስማር አመቱን ሙሉ ስሜን መፃፍ የቻልኩ አይመስለኝም፡፡ ቢሆንም 17ኛ ደረጃ ወጣሁ፤ደስ የሚሉኝ የትምህርት ክፍለጊዜያት ሙዚቃና እስፖርት ነበሩ፡፡ በአንድ ክፍል እስከ 70 ተማዎች ነበርን፤ አንደኛ ክፍል ስንማር የሂሳብ መምህራችን አንድ ተማሪ የቤት ስራ ሳይሰራ ስለመጣ 40 ጊዜ መቀመጫው ላይ እንደተገረፈው አይረሳኝም፡፡ በወቅቱ የክፍል አለቃችን ጎሳዬ ደሳለኝ ነበረ፡፡ የአማርኛ መምህራችን የተለመደ ስድቡ /አበያ/ የሚል ነበረ፡፡ ሁለተኛ ክፍል 8ኛ ሆኜ ጨረስኩ፡፡ ትምህርት ደስ እያለኝ መጣ፤ ቀስ በቀስ ለትምህር ትኩረት እየሰጠሁ መጣሁ፡፡ በመሆኑም ሶስተኛ ክፍል ስገባ 4ኛ ሆኜ ጨረስኩ፡፡ አራተኛ ክፍል ስገባ አመቱን ሁለተኛ ሆኜ ጨረስኩ፤ አምስተኛ ስገባ አባቴ ለስራው የሚመጥን በቂ ትምህርት የለውም በሚል ከዘበኝነቱ ስራ ተባረረ፣ ስለሆነም ለእርሻ የሚሆን መሬት ፍለጋ ጥቅጥቅ ደን በዲ መደርሾ ገበሬ ማህበር ጩሌ የምትባል ቦታ ተመርቶ መሬቱን መንጥረን እርሻ መጀመር እንዳለብን አሳምኖኝ፣ ትምህርት ማቋረጥ እንዳለብኝ ተስማማን፡፡ እግዚአብሄር ነብሱን ይማረውና የልጅነት ወዳጄ ተረፈ ጆሮ ትምህርት እንዳላቋርጥ ብዙ ለምኖኝ ነበረ፡፡ ነገር ግን አባቴ እንዳቋርጥ መክሮኝ ስለነበረ የተረፈን ምክር አልሰማ አልኩኝ፡፡ አባቴም መሬቱን ከጎሮቤታቸን ከአቶ አስፋው ጋር ተመርተው የደን ምንጣሮው ስራ ተጀመረ፡፡ እኔም አብሬ ደን መመንጠሬን ጀመርኩ፡፡ የድኩላ፣ የሚዳቆ፣ የጅብ፣ የአሳማ፣ የነበር፣ የጦጣና የዝንጀሮ ወዘተ የዱር እንሰሳት ቤት የነበረውን ጥቅጥቅ ደን ጨፈጨፍነው፣ የደረቀውን እሳት ለቀቅንበት፤ በ6ወር ገዜ ውስጥ ጫካውን ድራሹን አጠፋነው፡፡ መሬቱም ታርሶ በቆሎ፣ ገብስ፣ ስንዴ፣ ሽንብራ፣ በርበሬ፣ አጃና ዘንጋዳ ተዘራ፡፡ ለከብቶቻችንም ግጦሽ እንደልብ ሆነ፤ እኔም ከትምህርት እየራቅኩ ሄድኩ፡፡ ለሁለት አመት ከትምህርት መራቅ ግድ ነበረ፤ በሁለተኛው አመት መጨረሻ ወደትምህርት ተመለስኩ፤ ስመለስ የመማሪያ ቋንቋ ከአማርኛ ወደ ኦሮምኛ ተቀይሮ ነበረ፡፡

 

 

 

የባህላዊ ጋብቻ ተረት ተረት …

ልጅ ሳለሁ እናቴ ስለጎጂ ባህልና ስለአንዲት ልጅ የትዳር ሁኔታ ተረት ትነግረኝ ነበረ፤ ተረቱ በአጭሩ እንዲህ ነው፤ አንዲት ቆንጆ ልጅ ሰባተኛ ክፍል ትማር ነበረ፤ የመማር ፍላጎትዋ እጅግ ከፍተኛ ነበረ፤ ቢሆንም ከእለታት አንድ ቀን አባትና እናትዋ ድምፃቸውን ዝቅ አድርገው ደብዳቤ ያነባሉ፤ ደብዳቤው የጋብቻ ጥያቄ ነበረ፤ በማግስቱ ጠዋት አንድ የጎረቤታቸው የሀገር ሽማግሌ መጥተው ስለደብዳቤው ሀሳብ ያወያያሉ፡፡ ሽማግሌው ለልጅት ወላጆች እንዲህ ሲሉ ተናገሩ ‹ ስሙኝ አቶ አሸናፊና ወይዘሮ አባይነሽ፣ ትዳር የተባረከ ነው፣ በዛሬ ጊዜ ለትዳር መጠየቅ መታደል ነው፡፡ ሴት ልጅ ማሳደግ ፈተና ነው፤ በአሁን ጊዜ ሴቱ ሁሉ በእናትና በአባት ቤት መውለድ ሆነ፡፡ ታላቅ ውርደት ነው፤ የናንተ ልጅ ደግሞ እድለኛ ናት፡፡ ለትዳር ያጫት ልጅ የተማረ ነው፣ ልጃችሁ የሰው አይን ገብታለች፡፡  ስለዚህ ይህንን እድል አታሳለፉ፡፡ እግዚአብሄር የተባረከ ትዳር ያድርግላችሁ!› በማለት ሽማግሌው ራሳቸው ጠይቀው፣ ራሳቸው የትዳሩን አስፈላጊነት ወስነው ሄዱ፣ ልጅትም ለትዳር እንድትሰጥ ተወሰነ፡፡ ቢሆንም ልጅት ስለትዳሩ ስትሰማ አንድ ምሽት እጅግ አምርራ አለቀሰች፡፡ ልጁ ማን እንደሆነ አይታውም አታውቅም፣ ልጅት ፈቃደኛ ባትሆንም በቤተሰብና በሽማግሌዎች ውሳኔ ጋብቻው ፀደቀ፤ የሰማኒያ ቃል ማሰሪያ ቀን ተወሰነ፣ ሰማኒያ ታሰረ፡፡ ቀጥሎም ከሁለት ወር በኋላ ሊያገባ ያጫት ሰው ከሌላ ሴት ሁለት ልጆች ወልዷል ተባለ፤ በልጅትዋ ቤት ታላቅ ሀዘን ሆነ፤ ወላጆቹ በፍጹም ለዚህ ሰው ልጃችንን አንድርም ሲሉ ዛቱ፤ ሽማግሌዎች የሰርግ ቀን ለመወሰን ሲመጡ፣የልጅት ወላጆች በፍፁም ትዳሩ ይሰረዝ ሲሉ ተናገሩ፤ ሰውየው ደግሞ የሰማኒያ ሚስቴን እምቢ ተባልኩ ሲል መዛት ጀመረ፡፡ ሊጠልፉ እያቀዱ መሆኑም ተሰማ፡፡ ለጊዜው ተብሎ ልጅት አከባቢውን ለቃ እንድትሄድ ተደረገ፡፡ በየሳምንቱ እሁድ ቀን ሽማግሌዎች ይመላለሳሉ፤ ጥያቄያቸው የሰርግ ቀን ይነገረን ነው፤ የልጅት ወላጆች ደግሞ ትዳሩን አንፈልግም፤ ልጁ ሌሎች ልጆች አሉት በማለት እምቢተኝነታቸውን ገለፁ፤ ቢሆንም ሰውየውም በእምቢታው ቀጠለ፣ በመጨረሻ የልጅት ወላጆች ተሸነፉ፤ ሳይወዱ በግዳቸው፣ የውዴታ ግዴታ የሰርግ ቀን ተቆረጠ፣ ልጅትም ትምህርት አቋርጣ ተዳረች፡፡ ትዳሩም ሊዘልቅ አልቻለም፤ ልጅት ልጅ መውለድ አልቻለችም፤ ጤናዋም ታወከ፤ ትዳሩም ፈረሰ፤ ተለያዩ፤ አሁን ልጅት ጎበዝ ነጋዴና ክርስቲያን ናት፡፡ ተረቱ አለቀ፡፡ በጎጂ ባህል ምክንያት፣ ያለፍላጎት የሚደረግ ጋብቻ መጨረሻው ጥሩ አይሆንም፡፡

ወደትምህርት ለመመለስ ስወስን ለአባቴ አላማከረኩትም ነበረ፤ ምክንያቱም ፈቃደኛ ስለማይሆን፤ በዛን ክረምት ወቅት የእርሻ መሬታችን አከባቢ ሀሽም የሚባል አርሶአደር ጋር የደረቀ በቆሎ ምርት መሰብሰብ የጉልበት ስራ ሰርቼ ለጉልበቴ ክፍያ 50 ኪሎ ግራም አከባቢ የሚሆን በቆሎ ተከፍሎኝ ነበረ፡፡ ያችን በቆሎ ሸጬ ደብተር ገዛሁ፤ አዲስ ልብስም ገዛሁ፡፡ ወደ ትምህርት ስመለስ የመማሪያ ቋንቋ ከአማርኛ ወደ ኦሮምኛ ለውጥ ተደርጎ ነበረ፤ እኔ ሳቋርጥ አማርኛ ነበረ፤ ኦሮምኛ የአፍ መፍቻ ቋንቋዬ ቢሆንም ላቲን ፅሁፍ ግን አልችልም ነበር፡፡ ወደትምህርት ስመለስ ተማሪዎቹ በኦሮምኛ አቀላጥፈው ይፅፋሉ፡፡ ለእኔ ግን ከበደኝ፤ ቢሆንም የቋንቋው ተናጋሪነቴን ተጠቅሜ በ4 ወር ጊዜ ውስጥ ኦሮምኛ ማንበብና መፃፍ ጀመርኩ፡፡ ቋንቋውንም ለምጄ አምስተኛ ክፍል በደረጃ ጨረስኩ፤ ስድስተኛ ክፍል ስገባ በጣም ታምሜ ነበረ፤ ህመሜም ልክፍት ነው ተብሎ በባህላዊ መንገድ ፈውስ ሊደረግንልኝ ብዙ ተሞከረ፤ ሆኖም መፈወስ አልቻልኩም ነበረ፤ በሞትና በህይወት መካከል ሆንኩ፤ ለ15 ቀናት ያህል መናገር አልችልም ነበረ፤ ከባህላዊው ህክምና ቦታም ሊሞት ስለሆነ ወደቤት ውሰዱት ተባለ፤ ቤተሰባችን ውስጥ ሞቴን መጠባበቅ ተጀመረ፤ በሚገርም ሁኔታ ከሳምንት በኋላ መናገር ጀመርኩ፤ አከባቢው ሁሉ ጉድ አለ፤ ይሞታል ተብሎ የነበረው ልጅ ሊድን ነው በሚል የሰፈሩ ሰው ሁሉ መጥቶ ያየኝ ነበረ፤ ወይ የእግዚአብሄር ታሪክ ተባለ፤ እኔም ከዛን ጊዜ ጀምሮ ባህላዊ ህክምናና ባህላዊ አምልኮ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከህሊናዬ አወጣሁ፤ በተለይ ልክፍት ተብሎ ህመም ውሸት መሆኑን ተረዳሁ፤ ማህበረሰባችን ምንነቱ የማይታወቅን ህመም ሁሉ ልክፍት ብሎ ነው የሚጠራው፤ ልክፍት ሰው ቢገድል እኔ ስድስተኛ ክፍል ሆኜ ሞቼ ነበረ፤ ልክፍት ውሸት መሆኑን በራሴ አረጋግጫለሁ፤ በየሰፈሩ ልክፍት እናድናለን ብለው ህብረተሰቡን የሚያታልሉት አጭበርባሪዎች ውሸታቸው ሊታወቅ ይገባል፡፡

ስድስተኛ ክፍልን ሀገር አቀፍ ፈተና በከፍተኛ ውጤት ጨርሼ 7ኛ ክፍል ገባሁ፡፡ ሰባተኛ ክፍል ትምህርት በእንግሊዘኛ ነበረ፡፡ የጂኦግራፊ ትምህርት ስለጋላክሲ ስንሸመድድ ትዝ ይለኛል፤ the group of stars is called Galaxy….the solar system is the sun system, made of the sun, the nine known planets, their comites, metroels and meteortists ወዘተ፡፡

ሊስትሮ

ከአራተኛ ክፍል ጀምሮ የሊስትሮ ስራም ጀምሬ ነበረ፤ የቤተሰባችን የኢኮኖሚ ደረጃ ዝቅተኛ ስለሆነ ተጨማሪ ገቢ ፈጥረን የደብተርና የእስክሪብቶ ማግኘት ነበረብን፤ እኔ ሊሰትሮ ታላቅ እህቴ ደግሞ የጨው ንግድ የልጅነት ስራችን ነበረ፡፡የሊስትሮው ስራ ገቢ ቆንጆ ነበረ፡፡ የአከባቢውን አርሶ አደር ጫማ ሰፍተን፤ አሳምረን፣ ጥሩ ገቢ እናገኝ ነበረ፤ አልፎ አልፎም ሁለት ብር የተስማማነውን ስራ ሁለት ብር የአንድ እግር ዋጋ ነው ብለን እጥፍ እያስከፈልን፤ ያገለገለ የጽሁፍ ካርቦን እየቀባን የጫማ ማሳመሪያ ኬሚካል ተጠቅሜያለሁ እያልን፤ በአንድ ገበያ ጥሩ ገንዘብ እናገኝ ነበረ፤ ቢሆንም ያገኘነውን ገንዘብ መልሰን እናጠፋዋለን፡፡ የሊስትሮው ስራ ለትምህርቴም አደጋ ነበረ፡፡ ሴሩ ከተማ የገበያ ቀን ቅዳሜና ማክሰኞ ነው፤ ማክሰኞ ከትምህርት ይልቅ ቅድሚያ ለሊስትሮ ገበያ እሰጥ ነበረ፡፡ ያ ወቅት እጅግ አደገኛ ነበረ፡፡

ሰባተኛ ክፍል እየተማርኩ ውጤቴ ቆንጆ ነበረ፡፡ ስለሆነም ከጂኦግራፊ መምህራችን ከመምህር ንጉሴ ፋንቴ ጋር ተግባባን፡፡ ፈተናዎቹን ሁሉ እደፍን ስለነበረ በጣም ያበረታታኝ ነበረ፡፡ እቤቱ ድረስ ጠርቶ ይመክረኝ ነበረ፤ ጎበዝ ተማሪ ሆነህ ለምን ከዱርዬዎች ጋር ታዘወትራለህ፤ አንተ ትምህርትክን በርትተህ ከተከታተልክ ጥሩ ቦታ ትደርሳለህ እያለ ይመክረኝ ጀመረ፤ ከዛን ጊዜ ጀምሮ ስለወደፊት ህይወቴ በጥልቀት ማሰብ ጀመርኩ፡፡ መምህራን ለተማሪዎቻቸው ከወላጅ በላይ ተሰሚነት ያላቸው ስለሆነ ትውልድን የተሻለ ለማድረግ ያላቸው ሚና ከፍተኛ ነው፡፡

 

 

ሚስት ቤትዋን ዘረፈች ተብላ ስትታሰር!

ሰባተኛ ክፍል ተማሪ ሆኜ ጎሮቤታችን አንዲት ልጅ ከባሏ ተጣልታ መጥታ ነበረ፡፡ ባልየውም ዘርፋኝ ስለሄደች ትታሰርልኝ ብሎ ለፖሊስ አመለከተ፤ ፖሊሶቹም እቃ ዘርፈሽ ሄደሻል በሚል ልጅትዋንና አባትዋን አንድ ቀን እስር ቤት አሳደሩዋቸው፡፡ ይህ በሴሩ የሆነ እውነተኛ ታሪክ ነው! ሚስት ቤትዋን ዘረፈች ተብላ ስትታሰር! ባልየው ለፖሊሶች ጉቦ ሰጥቶ ነው ያሳሰራት እየተባለም ይነገር ነበረ፡፡

ባህላዊ አምልኮ

በልጅነቴ ካሳለፍኩት ታሪኮች አንዱ የባእድ ወይም ባህላዊ አምልኮ ትዝታ ነው፤ በልጅነቴ ባህላዊ አምልኮ ቤት ሄጄ እናቶች ውቃቢ ሲነሳባቸው በእሳት የተያያዘ የከሰል ፍም ሲልሱ በአይኔ አይቻለሁ፤ እንዲሁም የሚነድ እሳት ውስጥ ሲቆሙ አይቻለሁ፤ በተለየ ቋንቋም ሲነጋገሩ ሰምቻለሁ፡፡ ያ ሁሉ እንዴት ሊሆን ቻለ? እሳቱ እንዴትስ አያቃጥላቸውም? ማጂክ ነገር እየሰሩ ነው እንዳልል እናቶቹ ያንን ያህል የተማሩ አልነበሩም፤ የሚናገሩትስ ቋንቋ ምንድን ነው? ለነኚህ ጥያቄዎች ዛሬም ድረስ መልስ አላገኘሁም፡፡

ልጆች ብዙ ያውቃሉ፣ ራሳቸውንም ለአደጋ ያጋልጣሉ

ከራሴ የልጅነት ህይወት ከማስታውሰው፣ ወላጆቼ እኔን የሚስሉበት ማንነትና እኔ ከሌሎች ልጆች ጋር ስውል የማደርጋቸው ነገሮች በጣም የተራራቁ ነበሩ፤ ለምሳሌ ገና የሶስተኛ ክፍል ተማሪ በነበርኩበት ወቅት ህይወቴን ሊያጠፋ የሚችል ድርጊት ከሌሎች ልጆች ጋር ሆነን እናደርግ ነበረ፤ ለምሳሌ መራሮ በሚባለው ሰፈር ሄደን 15 ሳንቲም ለሶስት ሰው ከፍለን ያደረግነውን ድርጊት መቼም አልረሳውም፡፡ ወላጆች የልጆቻቸውን ድርጊትና የየቀን ውሎአቸውን መከታተል እንዳለባቸው ልብ ማለት ያስፈልጋል፤ ያቺ አጋጣሚ የሶስታችንንም ህይወት የዘላለም ፀፀት ታደርገው ነበረ፡፡ በልጅነቴ ከእለታት አንድ ቀን ተደብቄ፣ አባቴ ዘበኝነት ሲሰራ ይጠቀምበት የነበረውን ዲሞፍተር ጠመንጃ መክፈትና መዝጋት ስለማመድ ጥይት ውስጡ ስለነበረ ወደሰዎች ቤት ተተኩሶብኝ ነበረ፤ በተመሳሳይ አጋጣሚ አንድ ልጅ እናቱን ገድሎ የወንድሙን እግሮች የቆረጠበትን አሳዛኝ አጋጣሚም አስታውሳለሁ፤ ልጆች አዋቂ የሚሰራውን ሁሉ መስራት ይፈልጋሉ፤ መድሀኒትም ልጆች ከማይደርሱበት ቦታ መቀመጥ ያለበትም ለዚሁ ነው፡፡

አርሲ ሴሩ

በትምህርት ቤት ከነበረኝ ቆይታ በአርሲ ሴሩ ትምህርት ቤት የነበረኝን ትዝታዎች በሙሉ መዘርዘር በራሱ አንድ መፅሀፍ የሚበቃው አይመስለኝም፡፡ እኔ ከ1-8ኛ ክፍሎች ስማር እድለኛ ነበርን ማለት እችላለሁ፡፡ ምክንቱም በወቅቱ የነበሩን መምህራን በሙሉ የየራሳቸው የሆነ ቆንጆ ነገሮች ነበራቸው፡፡ አርሲ ሴሩ በአርሲ ዞን ካሉት ከተሞች ቀደምት ከሚባሉት የመጀመሪያዋ ሳትሆን አትቀርም፡፡ ከተማዋ የአርሲ ዞን የጠረፍ ከተማ ናት፤ ነገር ግን ብዙዎቹ መምህራን ሴሩ ከተማ ከደረሱ በኋላ በከተማው ካላሰቡት ጊዜ በላይ እንደሚቆዩ ይናገሩ ነበረ፡፡ አንዱን መምህር ከሌሎቹ ማስበለጥ እንዳይሆንብኝና ከትግራይ መጥቶ ሴሩ ትምህርትቤት ይሰራ የነበረውን መምህር መንግስቱ ገብረህይወትን እንደምሳሌ መጥቀስ እችላለሁ፡፡ መምህር መንግስቱ የተፈጥሮ ሳይንስ በተለይ የባዮሎጂ ትምህርትን ጥሩ መሰረት አስጨብጦናል፡፡ መንግስቱ የትውልድ ስፍራው ሩቅ ቢሆንም ከአከባቢው ህዝብ ጋር በመስማማት፣ በከተማው ህዝብ ዘንድ ልዩ ፍቅርና አክብሮት የነበረው፣ ሙያውንና ስራውን የሚያገብር ታላቅ መምህር ነው፡፡ በተጨማሪ ሴሩ ትምህርት ቤት ያስተማሩኝ መምህር ንጉሴ ፋንቴ፣ ገርማሞ ጋኔቦ፣ ደምሴ በለው፣ ጀማል ባዲ፣ አስራት ጌታቸው /ነብሱን ይማረው/፣ ክትነሽ ከበደ፣ ካሳሁን እጅጉ፣ ወርቅነህ ጂዳ፣  ቃዲ ሳኒ፣ ሀጂ ዋዶ፣ ማንያዘዋል ሸጋው፣ ዳምጠው ሀይለማሪም፣ ሙሉጌታ ከበደ፣ ነብሱን ይማረውና አይቲ ከተማ፣ ዝማርጌ፣ መምህርት ጎጃም፣ ግርማ በጂጋ፣ ሰለሞን፣  ወዘተ ስማቸው ያልተጠቀሰውንም ጨምሮ ለሁሉም ሴሩ ትምህርትቤት ለነበሩት መምህራን ሁሉ ላቅ ያለ ምስጋናዬን ላቀርብ እወዳለሁ፡፡

 

በልጅነቴ በሴሩ ከተማ ዙሪያ ያሉትን ብዙ ቦታዎች ሄጃለሁ፤ ለምሳሌ ቁልቋል ለመልቀም ጎቤሳ፣ሂኢስ፣ ጩሌ ፣ ጎልባ ድረስ ሄደናል፡፡ እንዲሁም ከአረብ ልጅ፣ ከቃንቁ፣ ሞዶሌ፣ ከ መራሮ፣ መደርሾ፣ጎልባ፣ ሀዲዶ፣ ዲሬዛራ፣ ሊሎ፣ ሙሪ፣ ሀሊላ፣ ተፋለጣ፣ ሀዶቻ፣ መሪቃ፣ ማዘዛ፣ ጂዳ፣ በሌ፣ አስካልቱ፣ ጠቄ፣ አዴሌ፣ ሀቤ፣ አዩባ፣ ሮቤ፣ ሀሊላ፣ ቡላላ፣ ዲክሲስ፣ ሲሬ፣ ሁሩታ፣ ኢተያ፣ ዴራ፣ አዋሽ፣ አዳማ፣ መተሃራ፣ ሸገር፣ እነኚህን ቦታዎች በመዘዋወር ከልጅነት አሁን እስካለሁበት ድረስ ብዙ ትዝታዎች አሉኝ፡፡

 

እንዲሁም ጩሌ እርሻ እያረስን ከድንጋይ ስር ይወጣ የነበረው እባብ፣ በቆሎ የሚጨርሱብን ዝንጀሮ፣ ከርከሮ፣ ጦጣ፣ ወፎች፣ አረም፣ ነቀዝ፣ ዝናብ፣ አይጥ ወዘተ ትዝታዎቼ ናቸው፡፡ የሀገራችን ገበሬዎችም ከግብርና ጋር በተያያዘ እነኚህን ሁሉ በባህላዊውም ይሁን በመናዊ መልኩ መከላከል አለባቸው፡፡ ነቀዝና አይጥብ ብቻ ብንወስድ እህል በማሳም ላይ ሆነ ከተሰበሰበ በኋላ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳሉ፤ የእህሉንም ምርት ብዛትና ጥራት ይቀንሳሉ፡፡

 

ጩሌ በመባል በሚታወቀው የእርሻ ቦታችን እጅግ ብዙ ትዝታዎች አሳለፌያለሁ፤ የመስቀል በአል ጩሌ ከነበሩ ጎሮቤቶቻችን ደመቅ ባለ ሁኔታ ይከበር ነበረ፡፡ Goobeen dhuftee yaa dureesa koo jabileen oofaa kara naaf bani. Sibadhaasuun dhufe yaa duresakoo, si badhaasuun dhufe yaa dureeesakoo… እየተባለ የሚዘፈነው የእረኞች ዘፈን፣ እንዲሁም ፎሌ ሲባል የነበረው ጭፈራ፣ ለቡሄ፣ በጥምቀት የነበረው ደስታ ገደብ የለውም፡፡ ከሴሩ አፋፍ ወደሀረርጌ ያለው የአቡልቃሲም ዳገትም ትዝታዬ ነው፡፡

ቁጠባ ፣የወላጆች ጥል

ሴሩ ከሰባተኛ ክፍል ወደ ስምንተኛ ክፍል ስንዘዋወር የስምንተኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተናና ሴሩ ከተማ ከ9-12 ስለሌለ ለዘጠነኛ ክፍል ከሴሩ ወደሌላ ከተማ የመሄዱ ጉዳይ ትልቅ ሀሳባችን ነበረ፡፡ ለእኔ ትልቁ ሀሳብ እስከ ስምንት እየሰራሁ ገቢ የማገኝበት የነበረውን የሊስትሮ ስራ ወደዘጠነኛ ክፍል ስዘዋወር እንዴት መስራት እንደምችል ነበረ፡፡ ቀድሞ ዘጠነኛ እየተማሩ ካሉት ተማሪዎች እንደሰማነው ዘጠነኛ ክፍል ትምህርቱ ይከብዳል፤ በተለይ ሂሳብ ና ፊዚክስ ከባድ ትምህርቶች መሆናቸውን ዝናቸውን ሰምቻለሁ፤ ስለሆነም በደንብ ማንበብ እንደሚገባ ሰማሁ፤ ስለሆነም ቀደም ብዬ ገንዘብ መቆጠብ እንዳለብኝም ተረዳሁ፤ ምክንያቱም የእኔ ወላጆች የገንዘብ ችግር እንዳለባቸው ስለማውቅ ከሊስትሮው ስራ የሚገኘውን ገቢ ለዘጠነኛ ክፍል ትምህርት እንዲጠቅመኝ መቆጠብ ነበረብኝ፡፡

 

ለዚህም ሲባል አንድ ትንሽዬ የገንዘብ ማስቀመጫ ሳጥን/ባኮኒ/ ገዛሁኝ፤ ባኮኒውን ሁሌም ለማመሰግነው ግርማ አባተ ሱቅ አስቀመጥኩኝ፡፡ ከዛ በየቀኑ ከማገኘው ገቢ 50 ፐርሰንቱን ገንዘብ ዘርዝሬ ማጠራቀም ጀመርኩ፡፡ በየቀኑ ገንዘብ ለመቆጠብ ወደግርማ ሱቅ ስሄድ ስሄድ እሱም በጣም ያበረታታኝ ነበረ፡፡ የስምንተኛ ክፍል ፈተናን 99.9 ከመቶ አምጥቼ ወደዘጠነኛ ክፍል አለፍኩ፡፡

ውጤት ከመምጣቱ ቀደም ብሎ በእናቴና በአባቴ መካከል የተፈጠረው አለመግባባት ከፍተኛ ደረጃ በመድረሱ እናታችን የመጨረሻ እህታችንን ይዛ ከቤት ጠፍታ ነበረ፡፡ ወዴት እንደሄደች ማንም ሊነግረን አልቻለም፡፡ በቤታችን ታላቅ ሀዘን ሆነ፤ እናቶች ለልጆቻቸውና ለቤታቸው ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆኑ የተረዳሁት በዛ አጋጣሚ ነው፡፡ በእናታችን አለመኖር ምክንያት ቤታችን እጅጉን ቀዘቀዘ፤ በጭቅጭቃቸው መሰላቸቴ ቆጨኝ፤ እናቴ በተደጋጋሚ ወደቤት እንድመጣ ትለምነኝ ነበረ፤ እኔ ግን አንደኛ ስራ ላለመታዘዝ፣ ሁለተኛ የሁለቱ ጥል ስለነበረ፣ ሶስተኛ ለሊስትሮው ስራ ሲባል ልመናዋን ችላ ብዬ ነበረ፡፡ እስዋ ስለሌለች ከዘጠነኛ ክፍል ስንቅ ማን ዘጋጅልኝ? ምግብ ማን ይስራልን? ላሞቹን ማን ይለባቸው? አባታችን የሚያደርገውን አጣ፤ ሄዶ እንዳይፈልጋት የት እንዳለች አያውቅም፤ አባታችን እናታችንን ስላስቀየማት እንደተፀፀተ ከፊቱ ላይ ይታይ ነበረ፡፡ እናታችን በሌለች ጊዜ የቤተሰቡ ሀላፊነት በታናሽ እህታችን በአበበች ላይ ሆነ፤ አበበች ምግብ ታበስልልን ጀመረች፣ ለመታጠብ ጊዜ ስለሌላትም  ልብሶችዋ ቆሸሹ፣ ፀጉርዋ ቀጨመ፣ እጆችዋ በብርድ ተሰነጣጠቁ፤ እጅግ ከባድ ችግር ነበረ፡፡ ለመለያየት ያደረሳቸውን የጭቅጭቅ ሀሳብ ቀለል አድርገውት ቢሆን ያ ሁሉ ባልደረሰ፤ በእነሱ ስህተት እኛ ተቀጣን፡፡

 

 

 

የእናታችንን አለመኖር በመረዳት፣ ቁርጤን አውቄ፣ ለዘጠነኛ ክፍል ትምህርት የሚሆነኝ ስንቅ ማዘጋጀት ጀመርኩ፡፡ ከእለታት አንድ ቀን ስንዴው ተገዝቶ ተፈተገ፣  ስንዴውን ለመፈተግ ስወቅጥ የእጆቼ መዳፍ ተላላጡ፤ ከዛ ስንዴውን ፀሀይ ላይ አስጥቼ ወደሊስትሮ ስራዬ ሄድኩ፡፡ ከቀኑ ወደ10 ሰአት አከባቢ ከባድ ዝናብ ዘነበ፤ ስንዴውን ማስጣቴን ረስቼው ነበረ፤ ትዝ ሲለኝ ለካ ስንቄን ውጪ አስጭቼ ረስቼዋለሁ፤ ሮጬ ቤት ስደርስ ዝናቡ እህሉን ጥርግ አድርጎ ይዞት ሄዷል፤ በዝናቡ ውስጥ ሮጬ ስደርስ የቀረችው 5 ኪሎ አትሆንም፤ እጅግ አለቀስኩ፡፡

 

በማግስቱ የበሶውን እህል ማዘጋጀት ጀመርኩ፤ ገብስ እየቆላሁ ለካ ምጣዱ ስር እሳት በዝቶ ነበረ፤ ገብሱ ተቃጥሎ መጨስ ሲጀምር የእሳቱ ነበልባል ከታች ወደእህሉ አለፈ፤ ገብሱ መንደድ ጀመረ፤ ውሀ በጄሪካን አፈሰስኩበት፤ የበሶው እህል ኬኔቶ መሳይ ውሀ ሞላው፤ ይህ ሲሆን በአጋጣሚ ያየችው ጎሮቤታችን የግርማ እናት ተቀብላ በሶውን ቆላችልኝ፤ እንደምንም ሆኖ ስንቁ ተዘጋጀ፡፡

 

ለዘጠነኛ ክፍል ትምህርት ዝግጅት፣ የገንዘብ ሳጥኑን መሙላቱን ስራ ክረምቱንም አጠናክሬ ቀጠልኩ፤ ዘጠነኛ ክፍል ለመማር ወደአርሲ ሮቤ ለመሄድ ስዘጋጅ ሳጥኑን ከፈትኩት፡፡ የተጠራቀመው ገንዘብ ግርማ ሱቅ ተከፈተ፤ 650 ብር አከባቢ ሆነልኝ፡፡ በሰአቱ ለሚያስፈልገኝ ወጪ ከበቂ በላይ ነበረ፡፡ ግርማ አባተ ትልቅ ባለውለታዬ ነው፤ ላመሰግነው እወዳለሁ፤ ሊስትሮ እየሰራሁ የማጠራቅመውን የገንዘብ ሳጥን ማስቀምጠው ግርማ ሱቅ ነበረ፤ እሱም ብዙ እንዳጠራቅም በረታታኝ ነበረ፤ ይህቺን ሳጥን መሙላት አለብህ እያለ ብዙ ገንዘብ ተቀማጭ እንዳደርግ በሞራል አግዞኛል፡፡

ወደአርሲ ሮቤ /ዲደአ

የስምንተኛ ክፍል ውጤት እንደመጣ ለምዝገባ አርሲ ሮቤ መሄድ ፈለግን፤ ቢሆንም ሴሩ ከተማ ትራንስፖርት የሚገኘው በሳምንት አንድ ቀን ብቻ ነበረ፡፡ አንድ ሳምንት ከጠበቅን ምዝገባ ሊያልፈን ሆነ፤ እኔና ወዳጄ በላይ ካሱ በእግራችን ለመሄድ ቆርጠን ተነሳን፡፡ ከሴሩ ሮቤ ድረስ ያለው መንገድ ርቀት 75ኪሎ ሜትር ነው፡፡ ሌሊት ዶሮ ሲጮህ ጉዞ ተጀመረ፡፡

እኔ ከአባስ በላይ ደግሞ ከኤጄርሳ መጀመሪያ ወደ ኡላ፣ ቀጥሎ ወደ ሙሪ፣ ቀጥሎ ዲዲሚና፣ ቀርሎ ደዎሌ፣ ቀጥሎ ተፋለጣ፣ ቀጥሎ ጂዳ ሆጃዱሬ፣ ቀጥሎ ሀዶቻ፣ አስካልቱ፣ ጎቦርባር፣ በሌ፣ አዴሌ ድረስ 42 ኪሎ ሜትር በእግራችን ገሰገስን፤ የትምህርት መረጃችንንና ሮቤ ከተማ ከባድ ዱርዬዎች አሉ ስለሚባል ቆንጆ ቆንጆ ዱላ ይዘን ነበረ፡፡ አዴሌ ከ9-12 ትምህርትቤት አለ፡፡ እኛ ግን የተሻለ ትምህርት ቤት ፍለጋ ወደሮቤ ዲደአ ነው ያቀድነው፡፡ ከቀኑ ምሳ ሰአት አከባቢ አዴሌ ስንደርስ ድክም ብሎን ነበረ፤ እንደ እድል ሆኖ ወደሮቤ የሚሄድ አንድ የጭነት መኪና  መጣልን፡፡ እንደምንም ለምነን አስቆምነው፤ ከሴሩ ድረስ በእግራችን መጣን ስንለው ሾፌሩ አዘነልን፤ ከዛም በጭነቱ መኪና ሮቤ ገባን፡፡

 

አርሲ ሮቤ ስንደርስ ከሴሩ ልጆች በስነ-ምግባሩና በትምህርት ችሎታው ግንባር ቀደም ተጠቃሽ የሆነው ወንድማችን መስፍን ስሜ መኪና ተራ ጠበቀንና ተቀበለን፡፡ ዱላችሁ ለምን አስፈለገ ሲለን  ሮቤ ሌቦች አሉ ስለተባልን ለመከላከያ ነው ስንለው ሳቀብን፡፡ ሌባ ለመከላከል ዱላ ከሴሩ ይዘን መምጣታችን ገርሞት ነው፤ ወይ የገጠር ልጅ ነገር፤ ወደከተማ ሲሄድ እዘረፋለሁ የሚለው ስጋት ሁሌም አለ፡፡ የሴሩ ነጋዴዎች አዲስ አበባ ሲሄዱ አልፎ አልፎ ይዘረፉ እንደነበረም ሰምተናል፡፡ እኛ ለዘጠነኛ ክፍል ምዝገባ ስንሄድ መስፍን የ10ኛ ክፍል ትምህርት ጀምሮ ነበረ፤ መስፍን ይኖር የነበረው ሮቤ ግብርና ቢሮ አከባቢ የአሜሪካን ግቢ በሚል ቅፅል ስም ይታወቅ በነበረ ግቢ ከወንድማችን ጌታቸው ተፈሪ ጋር ነበረ፤ ጌታቸው ተፈሪም በጉብዝናው ታዋቂ ወንድማችን ነበረ፤ እኔና በላይ ካሱ ስለጌቾና መስፍን ጉብዝናና የጥናት ባህል ብዙ ጊዜ ተወያይተናል፤ እንደነሱ ለማጥናትም ተስማምተናል፡፡ መስፍን ቤት ስንደርስ በቤቱ የውስጥ ውበት ተደመምኩ፡፡ ትንሽዬ አንድ ክፍል ቤት ናት፤ የማንበቢያ ጠረጴዛና አንድ አልጋ እንዲሁም የደብተር ማስቀመጫ ካርቶኒዎችና መሶብ እንዲሁም ቡታጋዝ፣ የሻይ ማንቆርቆሪያና የብረት ድስት አለ፤ እቃዎቹን በዝርዝር ማወቅ የነበረብኝ ለእኔ ምን ያስፈልገኛል? ዋጋቸውስ ስንት ይሆኑ? ለሚሉት ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ነበረ፡፡ የቤት ኪራዩ በወር 22 ብር አከባቢ ይመስለኛል፣ ውድ ነው፤ በዛን ጊዜ 22 ብር ሙሉ ከየት ይገኛል? በአስር ወር 220 ብር መሆኑ ነው፤ ወዳጄ በላይ ካሱ መስፍን ስሜ ጋር ሊኖር ተስማተዋል፡፡ በላይ እድለኛ ነው አልኩ በልቤ፣ ምክንያቱም 9ኛ ክፍል ልመዘገብ ወደሮቤ ስመጣ እኔ የት ልኖር እንደምችል ምንም መልስ ስላልነበረኝ፡፡

መልካም ዜና

እኔ ከ8ኛ ወደ 9ኛ ሳልፍ እናታችን ከቤት አልነበረችም፤ ከአባታችን ተጣልተው ጠፍታ ነበረ፤ ሮቤ ደርሰን ከመስፍን ጋር ስንወያይ በንግግራችን መሀል የነገረኝን ማመን አልቻልኩም፤ ልብስ ለማጠብ ወደሮቤ ወንዝ ሲሄዱ እናቴን ሮቢ 02 ቀበሌ እንዳገኛት ነገረኝ! ውስጤ በደስታና በፍርሀት ተሞላ፤ በሰአቱ የተሰማኝን ስሜት መግለፅ ይከብደናኛል፤ መናገር አቃተኝ፤ በውስጤ አለቀስኩ፡፡

 

እናታችን ከቤት ከወጣች ከሶስት ወር በኋላ መሆኑ ነው የት እንዳለች የሰማሁት፤  እህታችን ወይንሸትም ናፍቃኝ ነበረ፤ ያኔ ወይንሸት እድሜዋ ሁለት አመት አከባቢ ነበረ፡፡ መስፍን ወዲያውኑ እናቴን ያየበት ቤት እንዲያደርሰኝ ለመንኩት፤ መስፍንም እናቴ ያለችበት ቤት ሊያደርሰኝ ተስማማ፡፡ ተያይዘን ወጣን፤ መንገዱ ረዘመብኝ፤ ደርሰን አንኳኳን፤ አንድ ወጣት ልጅ የግቢውን በር ከፈተንል፡፡ ወደውስጥ ስንገባ እህቴ እየተሯሯጠች ስትጫወት አየሁዋት፤ እግሬ ተንቀጠቀጠ፤ አይኖቼ በእምባ ተሞሉ፡፡  እናቴም ድምፃችንን ስትሰማ ከኩሺና ብቅ አለች፤ ከመስፍን ጋር ሰላም ከተባባሉ በኋላ እኔና እናቴ ስንተያይ ሁለታችንም ማልቀስ ጀመርን፤ መነጋገር አልቻልንም፡፡ ምንም ሳንነጋገር ለተወሰነ ጊዜ ቁጭ አልን፤ ከየት እንጀምረው? ምን ልበላት? ሰአቱም እየመሸ ስለነበረ በማግስቱ ለመመለስ ቀጠሮ ይዘን አመስግነን ወጣን፡፡

 

እናቴ ከቤት ስትወጣ አላማዋ አርሲ ሮቤ መኖር ፈልጋ እንዳልነበረ ነገረችን፣ አላማዋ ወደ ትውልድ ሀገሯ ወደሰላሌ፣ ፊቼ አከባቢ ለመመለስ ነበረ፡፡ ነገር ግን ከዛ በፊት ሄዳ ስለማታውቅ፣ እንዲሁም በቂ ገንዘብ ይዛ ስላልወጣች ለተወሰነ ጊዜ ሰው ቤት ሰርታ ገንዘብ ለማጠራቀም እዛ ቤት በሰራተኝነት ተቀጥራ መሆኑን ሰማሁ፡፡

መልካም ሰው/አቶ በላቸው

በማግስቱ ስንመለስ ሁለት አላማ ነበረኝ፤ አንደኛ እናቴ ወደቤት እንድትመለስ ማሳመንና ለትምህርት ቤት ምዝገባ ተያዥ የሚሆነኝ ሰው ማግኘት፡፡ ጠዋት ሄድን፤ እናቴንም በሰፊው አነጋገርኩዋት፤ እህቴንም አጫወትኩ፤ በዛው አጋጣሚ ለትምህርት ቤት ተያዥ የሚሆነኝ ሰው ካለ ጠየቅኩ፡፡ እናቴ የነበረችበት ቤት ባለቤት የግብርና ባለሙያ ስለነበረ ወደመስክ ሄዶ ነበረ፤ በመሆኑም የእሱ የስራ ባልደረባ አቶ በላቸው ተያዥ ሊሆነኝ እንደሚችል ተነገረኝ፡፡ አቶ በላቸው ተጠየቀና ፍቃደኝነቱን ገለፀ፤ በማግስቱ ሊያስመዘግበኝ ተያይዘን ወደ ዲደአ ትምህርት ቤት ሄድን፡፡ እግረ-መንገዱን አቶ በላቸው የትምህርት መረጃዬን ተቀበለኝና አነበበው፤ ውስጡን ሲያይ ውጤቴ በጣም ቆንጆ እንደነበረ ተረዳ፤ አንተን የመሰለ ጎበዝ ልጅ እያላት እናትህ ለምን ከቤት ትወጣለች ሲል ጠየቀኝ፤ እኔ ምንም የማውቀው ነገር እንደሌለ ነገርኩት፡፡

 

ከአቶ በላቸው ጋር ዲደአ ትምህርት ቤት ስንደርስ የመጨረሻው የምዝገባ ቀን ነበረ፤ ብዙዎቹ መምህራን አቶ በላቸውን ያውቁት ነበረ፤ ልጅ እንደነበረህ አናውቅም ነበር እያሉ ከተቀላለዱ በኋላ አንዱ መምህር የትምህርት መረጃዬን ተቀብሎ ተመለከተው፡፡ ከሴሩ የሚመጡ ተማሪዎችን አንቀበልም ነበረ፤ ነገር ግን ልጁ ውጤት ቆንጆ ስለሆነ እንመዘግበዋለን ብለው መዘገቡኝ፡፡ ጎበዝ ተማሪ መሆን ጠቀሜታው ብዙ መሆኑን በዛ አጋጣሚ ተረዳሁ፤ የዲደአ መምህራንና አቶ በላቸውም በውጤቴ ምክንያት ሊተባበሩኝ ፈቃደኛ ነበሩ፤ ዲደአ በመመዝገቤ ትልቅ ጭንቀት ቀለለልኝ፤ ምክንያቱም የሴሩ ተማሪዎች አዴሌም የመመዝገብ እድል ስለነበረን ዲደአ ለመቀበል አንገደድም ብለው ይመልሱኛል የሚል ስጋትም ነበረብኝ፡፡   ተመዝግቤ ስመለስ አቶ በላቸው እናቴ ወደትዳርዋ እንድትመለስ እንደሚያሳምናት ቃል ገባልኝ፤ እኔም በጣም ደስ አለኝ፡፡ እናቴንም አነጋግሮ አሳመናት፤ እኔም እጅግ ተደሰትኩ፡፡ አቶ በላቸው ሁሌም የማመሰግነው ታላቅ ባለውለታዬ ነው፡፡ በ1990ዓ.ም አከባቢ ሮቤ ግብርና ቢሮ ይሰራ ነበረ፡፡ /ይህንን ፅሁፍ አንብቦ ምስጋናዬን የሚያደርስልኝ ሰው ቢኖር ደስ ይለኛል/፡፡ ቀስ በቀስ ጭንቀቴ መልስ እያገኘ መጣ፤ ትምህርት ተመዘገብኩ፤ እናቴን አገኘሁ፤ እስዋም ወደቤት ለመመለስና ለሚቀረኝ የትምህት ጊዜ እንደምትረዳኝ ተወያየን፡፡

 

በዚህ አጋጣሚ ለወላጆችና ለወጣቶች ማስተላለፍ የምፈልገው መልእክት፣ አንደኛ ወቅታዊ ለሆነና ለሚያልፍ ችግር እጅ ሰጥተን ትዳራችንን መፍታት እንደሌለብን ነው፤ ምክንቱም በትእግስትና በበጎ ጎኑ ካየነው በትዳር ውስጥ የሚፈጠር አለመግባባት ለመለወጥ ምክንት ሊሆን ይችላል፤ እንዲሁም ወላጆች በትእግስት የሚከፍሉት መስዋእትነት የልጆን ህይወት ይታደጋል፡፡ በተጨማሪም ወጣቶች በተለያዩ ምክንያቶች ለሚፈጠሩ ችግሮች እጅ ሳይሰጡ ጠንክረው ተምረው የተሻለ ደረጃ ለመድረስ መታገል አለባቸው፡፡ ወላጅነት የሚጠይቀውን መስዋእትነት ለመቀበል ዝግጁ ያልሆነ ወጣት ልጅ ከመውለዱ በፊት ደጋግሞ ማሰብ አለበት፤ ልጅ ከተወለደ በኋላ ግን ወላጆች የሚወስኑት ማንኛውም ውሳኔ የሰው ልጅ ህይወት ላይ የሚወሰን መሆኑን በመረዳት ሁሌም ራስን ለማሻሻል መሞከር ያስፈልጋል፡፡

 

አንዳንድ ወላጅ እያረጀም የማይሻሻል ይኖራል፤ ከወለዳቸው ልጆች የወደፊት ህይወት ይልቅ የራስ ደስታን በማስቀደም ልጆች ተበትነው ቤተሰብ ይፈርሳል፤ ከእኔ አባትና እናት የተማርኩት ነገር በወቅቱ ሁለቱም እርስ በእስር እልህ እንደተያያዙ ነው፤ በብዛት የሚጨቃጨቁበት የነበሩት ጉዳዮች ከባድ አልነበሩም፤ ነገር ግን በሰከነ መንፈስ ከመነጋገር ይልቅ በሀይል ችግሮቻቸውን መፍታት ይሞክሩ እንደነበረ አስታውሳለሁ፡፡ ከወላጆቼም ይሁን ከራሴ የትዳር ቆይታ የተማርኩት ዋናው ነገር ማንም ሰው ትዳር ሲመሰርት ማንነቱንና አስተሳሰቡን ይዞ ነው፤ ያ ማንነትና አስተሳሰብ ደግሞ ከትዳር አጋሩ ጋር ተመሳሳይ ላይሆን ይችላል፤ ስለሆነም ቀስ በቀስ ለመቀበል የሚከብዱትንም ጉዳዮች ቢሆን ለጋራ ልጆች የወደፊት ተስፋ ሲባል ተቀብሎ ሰላም ፈጥሮ፣ መተሳሰብን በመጨመር ኑሮን የተሻለ ለማድረግ መጣጣር ያስፈልጋል፤ በተጨማሪም አብሮ የሚኖሩ ሰዎች መካከል በተለይ በትዳር ውስጥ፣ በተለይም ልጆች ከተወለዱ በኋላ፣ አልፎ አልፎ የሀሳብ ልዩነት ሊፈጠር እንደሚችል አምነን መቀበል አለብን፡፡

 

ወደጀመርኩት ልመለስና ፣ ከትምህርት ቤት ምዝገባዬ በኋላ እኔና እናቴ እንዴት እስዋን ወደቤት መመለስ እንዳለባት መወያየት ጀመርን፡፡ እኔ የሽምግልናውን ስራ ተያያዝኩት፤ አዴሌ ገጠር ውስጥ ፈጀፈጄ ቀበሌ ያለችው አክስቴ ጂቱ ጋር ሄደን እስዋ እናቴን ወደቤት ወስዳ ከአባቴ እንድታስታርቃቸው አደረግኩ፤ እናቴም ወደቤት ተመልሳ እኔንና ልጆችዋን ማስተማር ጀመረች፡፡ ሰላም ወረደ፣ ከዛ በኋላ ሁለቱ ባልና ሚስት አዲስ ፍቅር ጀመሩ፤ ቤታችን ዳግም የደስታ ቤት ሆነ፡፡

 

እኔ ሮቤ ለመማር ስሄድ የት እንደምኖርና ከማን ጋር እንደምኖር ምንም የማውቀው ነገር አልነበረም፤ ከተመዘገብኩ በኋላ እግዚአብሄር ነብሱን ይማረልኝና የልጅነት ወዳጄ 5ኛ ክፍል እኔ ትምህርት ሳቋርጥ የተለየሁት ወዳጄ ተረፈ ጆሮና ወንድሙ ገበየሁ ጆሮ እነ አቶ መኮንን ጌታነህ /የውድዋ ባለቤቴ አባት/ ግቢ የተከራዩት ትንሽዬ አንድ ክፍል ቤት ውስጥ በደባልነት አብረው ሊያኖሩኝ ተስማሙ፡፡ በዛን ወቅት ሮቤ ዲደአ እየተማሩ ከነበሩት የሴሩ ተማሪዎች፤ አሳምነው ታደሰ፣ ገብሩ ታደሰ፣ ጌቱ ቲሊንቲ፣ ጌቱ ማሬ፣ መላኩ ፅጌ፤ ወንድወሰን፣ ደስታ፣ ውዴ ለገሰ፣ ኩማ ጀማል፤ ኢሳ ጀማል፣ አብዱልካሊቅ ረሺድ፣ አልማዝ አደሬ፣ ሂሩት አደሬ፣ አማረች ዘገየ፣ አዜብ ዘገየ ነብሷን ይማረውና አየለች ዘገየ፣ ቤተልሄም ለገሰ፣ ሲሳይ አደሬ፣ ቦጋለች አደሬ፣ አየለ መኮንን፣ መስፍን ስሜ፣ በላይ ካሱ፣ ኢብራሂም አብዱልፈታይ፣ መለሰ ጌታቸው፣ ፍሰሀ በቀለ፣ ሰለሞን ደስታ፣ ግርማ ጌታቸው፣ ብርሀኑ አባቡ፣ አለማየሁ ለታ፣ መንግስቱ ገብሬ፣ ብርሀኑ መረጋ፣ አበራ ነገዎ፣ አስቻለው አባተ፣ መስፍን ታደሰ፣ ማርቆስ ሸጋው፣ አበራ ግዛቸው፣ ጀንበሩ ፈለቀ ወዘተ ነበሩ፡፡ ከነኚህ ሁሉ ጋር እጅግ ብዙ የማይረሱ ትዝታዎች አሉኝ፤ ለጊዜው ግን ስማቸውን ብቻ መጥቀሱ በቂ ነው፡፡ ሁላችንም አንድ የሚያደርገን ዋናው ጉደይ ዲደአ ለመማር የነበረውን የትራንስፖርት ችግርና እንዲሁም በዛ እድሜ ከቤተሰባችን ተለይተን፣ ቂጣ ጋግረን በልተን፣ በራሳችን ኖረን ውጤታማ መሆን መቻላችን ነው፡፡

 

ወዳጄ ተረፈ ጆሮና ወንድሙ ገበየሁ ጆሮ ጋር መኖር በመጀመሬ እጅግ ደስ አለኝ፤ የእናቴ ልጆች ጋር የገባሁ ያህል ነው የተሰማኝ፡፡ በነገራችን ላይ የወዳጄ የተረፈ ጆሮ ሞት እስካሁን በሞት ከተለዩኝ ዘመዶቼ ሁሉ ባስታወስኩት ቁጥር ሀዘን የሚሰማኝ አጋጣሚ ነበረ፡፡ ይህ መፅኀፍ ለህትመት በዝግጅት ላይ እያለ የእናቴ መሞት ደግሞ የበለጠ ስለሞት እንዳስብ እያደረገኝ፣ መንፈሴ እየተረበሸ ነው፤ ለሁለቱም ነብሳቸውን በገነት ያኑርልኝ፤ የ9ኛ ክፍል ትምህርቴን እንደጀመርኩ አንድ አልጋ ላይ ለሶስት እንተኛ ነበረ፤ የተረፈ ጫወታ ሁሌም አይረሳኝም፤ ከዲደአው ጓደኝነት በተጨማሪ እኔና ተረፈ ከአንደኛ ክፍል እስከ 4ተኛ ክፍል ስንማር ብዙ የጋራ ትዝታዎች ነበሩን፤ በተጨማሪም አባቴ የትምህርት ቤት ዘበኛ በነበረበት ወቅት የነተረፈ ቤት ትምህርት ቤቱ አጠገብ ስለነበረ ሁሌም እንገናኝ ነበረ፡፡  እኔና ተረፈ ጆሮ እጅግ ብዙ ብዙ ገጠመኞች ነበሩን፡፡ ሶስተኛ ክፍል ተማሪ ሆነን እጅግ እንቀራረብ ነበረ፡፡ ተረፈም ጎበዝ ተማሪ ነው፡፡ እኔና እሱ እኩል ውጤት ማምጣት እንፈልግ ነበረ፡፡ አንድ የማይረሳኝ ትዝታ፣ የሂሳብ ፈተና ተፈትነን ሁለታችንም 9 ከ10 አገኘን፡፡ በዛን ወቅት አባቴ የትምህርቤት ዘበኛ ስለነበረ የመምህራኑን መሰብሰቢያ ቢሮ ቁልፍ እሱ ጋር ነበረ፤ በመሆኑም እኔ የመምህራኑን ዶክመንት ማስቀመጫ የት እንደሆነ አውቅ ነበረ፡፡ ቀስ ብዬ ቁልፉን ከአባቴ ሰርቄ፣ የኔንም የተረፈንም ፈተና ወረቀቶች አውጥቼ የተሳሳትነውን ጥያቄ መልስ አስተካክዬ አስቀመጥኩ፡፡ ከዛ ሁለታችንም 10 ከ10 አገኘን፤ ከዚህም በተረፈ ሌሎች ብዙ የልጅነት ትዝታዎች ነበሩን፤ ወዳጄ ተረፈ ሁሌም አስታውስሀለሁ፤ ነብስህ በሰላም እረፍት ታድርግ፤ ለወላጆችህና ለወንድሞችህ ለእህቶችህ መፅናናትን እመኛለሁ፡፡

 

እንግዲህ ሮቤ ዲደአ የነበረኝ ደስ ደስ የሚሉ የተማሪነት ህይወት ቀጭኑ ወንዝ፤ ወደጢቾ መንገድ ዳር ባለው መስጊድ አጠገብ፤ አቶ መኮንን ጌታነህ ግቢ ተጀመረ፡፡ በዚህ አጋጣሚ እጅግ የማከብረውና በወቅቱ ለሴሩ ልጆች ለሁላችንም የጠንክሮ መስራት ምሳሌ ለነበረው መስፍን ስሜ የአሁኑ የአዳማው ዶክተር መስፍን ስሜ ታላቅ አክብሮቴንና ምስጋናዬን ላቀርብ እወዳለሁ፡፡ በዲደአ ቆይታችን መስፍንን እንደታላቅ ወንድማችን ነበር የምንመለከተው፡፡ መስፍን እጅጉን ቆንጆ የሆነ ስብእና ያለው ጠንካራ ተማሪ የነበረ ሲሆን በጥሩ ስነምግባሩ ለብዙ ተማሪዎች ምሳሌ እንደነበረ አብረውት ተማሩና በዲደአ መምህራን የነበሩት የሚመሰክሩት ሀቅ ነው፡፡ ከሚገርሙኝ የመስፍን ባህሪያት፣ ሮቤ ወንዝ ልብስ ለማጠብ ስንሄድ ሰውነቱን ሲታጠብ ቆዳውን መፋቅ ነበረ የሚቀረው፤ እሱ ለመታጠብ ለሚወስደው ጊዜና ጉልበት እኔ ይደክመኝ ነበረ፡፡ መስፍኔን ደፈር ብሎ ያናግረው የነበረው ተረፈ ነው፣ መስፍን ሰውነቱን ሲታጠብ ‹ምነው ይሄንን ያህል ቆዳ የምታለሰልስ መሰለህ እንዴ?› እያለ ይቀልድበት ነበረ፡፡

 

የሮቤ ዲደአ የመጀመሪያ  አመት ቆይታችን

 

የሮቤ ከተማ በዋናነት የምትታወቀው ከአከባቢው ካሉት የገጠር ከተሞች ማለትም ከሰዲቃ፣ ከበሌ፤ ከሀቤ፤ ከአዴሌ፣ ከጄና፣ ከቡላላ፣ ከዲክሲስ፣ ከሀሊላ ወዘተ በሚመጡ ተማሪዎች ነው፡፡ በሮቤ ከተማ ለተማሪዎች የሚከራይ ቤት የተለመደ ነው፡፡ ሮቤ የተማሪዎች ከተማ ናት ማለትም ይቻላል፡፡ ታዲያ እንደኛ ራቅ ካሉት ቦታዎች ለምሳሌ ከሴሩ ለሚመጡት ተማሪዎች ስንቅ መጨረስና በረሀብ መቸገር የተለመደ ገጠመኛችን ነበረ፡፡ ዋናው ችግር ከሴሩ በቀጥታ ወደሮቤ የሚመጡ መኪኖች በጣም ውስን መሆናቸውና በዝናብ ወቅት የበሌን ከተማ አቋርጦ የሚያልፈው የጎበርባር ወንዝ ይሞላና መኪኖች ማለፍ ያቅታቸዋል፡፡ እንዲሁም መንገዱ በዝናብ እየተበላሸ መኪኖች በጭቃ ተይዘው እስከ አስራ አምስት ቀን መንገድ ላይ ይቆሙ ነበረ፡፡ ስለሆነም ብዙ መኪኖች ከሮቤ ተነስተው በሌ ድረስ ብቻ ይሄዱ ነበረ፤ በመሆነም ወላጆቻችን ከሴሩ ስንቅ ለመላክ ይቸገሩ ነበረ፡፡

 

ለሴሩና ለአከባቢዋ ህዝቦች ከሁሩታ ጀምሮ ሴሩ ድረስ የመኪና መንገድ ችግር ለብዙ አመታት ከባድ ችግር የነበረ ሲሆን አሁን ድረስም ችግሩ አልተቀረፈም፡፡ በቅርቡ የአስፋልት መንገድ ስራ ይጀመራል እየተባለ ነው፤ በተስፋ እንጠብቃለን፡፡

 

ከተረፈና ከገበየሁ ጋር ስንኖር በተለይ ጥቅምት ወር ላይ ማታ ማታ ብርዱ ስቃያችንን ያሳየን ነበረ፡፡ ሮቤ ከፍተኛ ቦታ ስለምትገኝ እጅግ ቀዝቃዛ ከተማ ናት፡፡ ሌላው የማይረሳኝ የሮቤ ትዝታዬ ታዋቂው የሻቶ ማገዶ እንጨት ነው፡፡ በሮቤ ቆይታችን ሻቶ እንጨት ስንገዛ መሬት የነበረችው የመኝታ ፍራሻችንን ጊዜያዊ አልጋ ከማገዶው ሰርተን ከፍ እናደርጋታለን፡፡ ወሩ እየተጋመሰ ሲሄድ ሻቶው እንጨት ለቂጣ መጋገሪያነት እየተመዘዘ ያልቅና ፍራሻችን ወደነበረችበት ወደመሬት ትመለሳለች፡፡ ደግሞም ገንዘብ ከቤተሰብ ሲላክልን ሄደን አንድ ጭነት ሻቶ እንጨት በ6 ወይ በ7 ብር እንገዛና ጊዜያዊ አልጋችን ተሰርቶ ፍራሻችን አልጋ ላይ ትሆናለች፡፡

 

በዘጠነኛ ክፍል ቆይታዬ ዋናው ፈተና ቂጣ መጋገር መለማመድ ነበረ፤ የስንዴ ሊጥ ኩፍ ተደርጎ ኩፍታ ዳቦ ይጋገራል፤ ስሙን ቂጣ ነው የምንለው፤ ቂጣው የሚበላው በሽሮ ወጥ ሲሆን ከመስከረም እስከ ሰኔ ድረስ ዋና ምግባችን ነው፡፡ ወጥ መስራትም ራሱ ልምድ ይጠይቃል፡፡ የሽሮ ወጥ በቀላሉ ይወፍራል፤ ለማብሰልም ቀላል ነው፤ ሌላው የሚገርመኝ ትዝታ አብዛኛችን ቤት ጭልፋ አለመኖሩ ነው፤ የተሰራውን የሽሮ ወጥ በቂጣው ከድስቱ ውስጥ እንበላዋለን፡፡ ብዙው ጊዜ አንዴ የሚሰራ ወጥ ለአንድ ጊዜ ይበላና ያልቃል፡፡ በሮቤ ዲደአ ቆይታችን ማህበራዊ ህይወቱ እጅግ ደስ ይል ነበረ፡፡ አንዱ ምግብ ማዘጋጀት ሲጀምር የደረሰ ሁሉ ተመግቦ ነው የሚሄደው፣ ከአንዳችን ቤት ስንቅ ሲያልቅ ምግብ ፍለጋ ወደሌላው የሴሩ ልጅ ቤት መሰደድ ነው፡፡ ዱሮ የተማሩ የሀገራችን ተማሪዎች ስንቅ/በኛ አጠራር ሬሽን/ አልቆባቸው ሽሮ በጥብጠው እስከመጠጣት መድረሳቸውን ነግረውናል፡፡

 

በኛ የትምህርት ዘመን ግን ዋናው ችግር የትራንስፖርትና የኪራይ ቤት ክፍያ ችግር ነበረ፡፡ ዘጠነኛ ክፍል ሮቤን እስክለማመድ ከነተረፈና ከገበየሁ ጋር ከቆየሁ በኋላ ከመለሰ ጌታቸው ጋር ለመኖር ወስነን ሮቤ ጠቄ ተብሎ በሚጠራው ሰፈር ተከራየን፡፡ የተከራየነው የአንድን ቤተሰብ የመኝታ ቤት ነበረ፤ በመሆኑም ቤታችን መስኮት እንጂ በር አልነበረውም፤ የምንገባውና የምንወጣው በአከራዮቹ ሳሎን ውስጥ ነበረ፡፡ የቤቱ ኪራይ በወር 12 ብር ነበረ፡፡ ትንሽ ከቆየን በኋላ መለሰ ከፍሰሃና ከሰለሞን ስዩም ጋር በመሆን ሶስቱ የሀዋሬ ቀበሌ ተማሪዎች አብረው አንድ ቤት የመከራየታቸውን ሂደት ከዘጠነኛ/አስረኛ ክፍል የታሪክ ትምህርት ጋር በማገናኘት ዪኒፊኬሽን ኦፍ ጀርመኒ የሚለውን ዩኒፊኬሽን ኦፍ ሀዋሬ በማለት ሰየምነው፡፡ መለሰም ሊደር ኦፍ ዘ ዩኒፊኬሽን የሚል የቀልድ ስም ወጣለት፤ ከዛ ጊዜ ጀምሮ ብዞዎቻችን መለሰን ሊደር ብለን እንጠራው ነበረ፡፡ መለሰ ከነፍሰሃ ጋር ለመኖር ወደነ አየለ ግቢ ሲመለስ እኔ ደግሞ ከብርሀኑ አባቡ ጋር እዛው ጠቄ መኖር ጀመርኩ፤ ከብርሀኑ አባቡ ጋር እየኖርን እነመስፍን ስሜ ግቢ /አሜሪካን ግቢ/ አንዲት ክፍል ተለቀቀች፤ ክፍሏ ኩሺና አጠገብ ስትሆን ብዙ ቀዳዳዎች ነበራት፡፤ ቢሆንም ከጠቄ ወደዲደአ መመላለሱ ብዙ ርቀት ስለሆነብን አሜሪካን ግቢ ትንሽዬዋን ክፍል በወር 6 ብር ተከራይተን ገባን፡፡ ለሁለት የቤት ኪራይ ክፍያችን ሶስት ሶስት ብር መሆኑ ነው፡፡ የክፍልዋ ሌላው ችግር መብራት አልነበራትመ፡፡ ፋኖስ መግዛት የሚያስችል ገንዘብ ስላልነበረን ኩራዝ ነበር የምንጠቀመው፡፡ እንደሚታወቀው የኩራዝ መብራት ጭስ ስለሚበዛው ጭሱን ለመቀነስና ጋዝም ለመቆጠብ የኩራዙን ክር ወደውስጥ እንስበዋለን፡፡ ራሳችን የፈጠርነው ዘዴ ነው፤ እንደዛ ስናደርግ የኩራዙ ጭስ ይቀንሳል፡፡ ታዲያ የምናነበውን ደብተር በደንብ ወደኩራዙ ማስጠጋት ነበረብን፡፡ በዛን ጊዜ ከነበረው ህይወታችን ምንም የፎቶ ትዝታ ልናስቀር ባለመቻላችን ያሳዝነኛል፡፡

 

ዘጠነኛ ክፍል ተማሪ ሆኜ በ10 ወር ውስጥ 3 ጊዜ መኖሪያ ቤት ቀየርን፤ በሶስት ወር አንድ ቤት እንደማለት ነው፤ እንደዛም በችግር ተምረን የትምህርትቤት ውጤቴ ቆንጆ ነበረ፤ ዘጠነኛ ክፍልን ሁለተኛ ሆኜ አመቱን አጠናቀቅኩ፡፡ አስረኛ ክፍል ስንገባ በተሻለ ልምድ በተሻለ ዝግጅት ነው የመጣሁት፡፡ እናቴ ወደቤት ስለተመለሰች ነገሮች ተስተካክለዋል፤ ከአባታችንም ጋር ሰላማቸው ጥሩ ደረጃ ነበረ፤ ለአስረኛ ክፍል ከመስፍን ታደሰ ጋር እነ አየለ ግቢ ገባን፤ አሁን የተረጋጋ ትምህርት መማር ጀመርን፡፡

 

 

 

 

ከመስፍን ጋር ያሳለፍኩት ጊዜ እጅግ ደስ የሚል ነበር፤ መስፍኔ/ፍሬሹ/ ወደዲደአ ሲመጣ ትንሽ ልጅ ነበረ፡፡ ከእለታ አንድ ቀን ምን እንዳጠፋ ባላውቅም ገርፌው ነበረ፤ ከመታሁት በኋላ ሲያለቅስ ደግሞ አሳዘነኝ፤ የመታሁህ እኮ እንደታናሽ ወንድሜ ስለማይህ ነው ብዬ አባበልኩት፡፡ ታዲያ መስፍኔም ጎበዝ ተማሪ ነበረች….ዘጠነኛ ክፍል የደረጃ ተማሪ እንደነበረ፡፡ መስፍኔ ደስ የሚለው ባህሪው ረሃብ አይችልም፤ ሲርበው ጫወታ ያቆማል፤ ከንፈሮቹ ይደራርቃሉ፤ ስለሆነም ርቦት ምግብ ሲበላ ከሰው ጋር ንግግር ያቆማል፤ ምግቡ ትኩስ ቢሆንም ዝም ብሎ ይበላል… ሌሎቻችን አፉ ውስጥ ፍሪጅ ሳይኖረው አይቀርም ብለን እንቀልድበት ነበረ:: ከበላይ ካሱና ከኢብራሂም (በቀልድ ስሙ ያሲር አረፋት) ጋርም እጅግ ብዙ ትዝታዎች አሉኝ፡፡

 

ዲደአ ከምንመገባቸው ምግቦች ውስጥ በስንዴ ሊጥ የሚሰራው ፉል የሚባል ምግብ ነው፡፡ አሰራሩ የስንዴ ዱቄት በወፍራሙ ይቦካና ይድቦለቦላል፤ የተድቦለቦለው ሳይደርቅ የፈላ ውሃ ውስጥ ይጨመርና ይበስላል፤ ከዛ ዘይትና በርበሬ ተጨምሮበት ደስ የሚል ምግብ ይወጣዋል፡፡ ብዙ ጊዜ ፉል የሚሰራው አርብ ቀን ወይም ስንቅ ሲያልቅብን ነው፡፡ ሌላው የሮቤ ዲደአ ትዝታዬ ቅዳሜና እሁድ ከጥናት በኋላ ወደወህኒቤቱ ጋር ሄደን የምንበላው ጣፋጭ ሸንኮራ አገዳ ነው፡፡ በወቅቱ ከሮቤ ከተማ በወህኒቤቱ ጋር ወደሰዲቃ የሚወስደው መንገድ አዲስ መሰራቱ ነበረ፡፡ መንገዱ ለማታ ማታ የእግር ጉዞ በጣም ደስ ይላል፡፡ ሌላው የዲደአ ትዝታዬ የመምህራኖቹ ነው፡፡ ገና ከዘጠነኛ ክፍል ስንጀምር የፊዚክስ መምህሩ ደረጀ ችሎታው እጅግ ይገርማል፡፡ እኛን ከብዶን የምንማረውን ትምህርት ለማስተማር ወደክፍል ሲመጣ ቾክና ዳስተር ብቻ ይዞ ይመጣል፡፡ ፊዚክስን በጥብጦ ነው ሚያጠጣው ብለን እናሞግሰዋለን፡፡ ደረጄ ፊቱ ላይ ፈገግታ ታይቶ አይታወቅም፤ እንደሚያስተምረው ትምህርት ኮስተር ያለ ነው፡፡ መምህር መስፍን፤ ልሳነወርቅ፣ ተስፋዬ፣ ሸዋአማረህ፣ አማረ፣ አይችሉህም/ሽልንጌ/፣ በሺር፣ ጤናዬ…በድፍረት ኪሱውስጥ አድስ ኪዳን መፅሀፍ ይዞ ክፍል ውስጥ መጥቶ የሚሰብከን…ከፈለጋችሁ ክሰሱኝ እያለ…መምህር የሱነህ፣ መምህር ይህደጎ፣ መምህር ከበደ፣ ጋሽወገኔ፣ ዘበኛው ጀማል፤ ጀማል….አርፋጆችን የሚገርፍበት አለንጋው፣ መምህር ደሜ፣ መምህር ደጀኔ ደለለኝ፣ መምህር ነገራ፣ መምህር ሽፈራው፣ መምህር ተከስተ፣ ሙሉጌታ፣ መምህር ብርሀኑ ባዮሎጂ መምህር/ነብሳቸውን ይማር/….ከመምህራኑ ቀጥሎ ከየትምህርትቤቱ የተውጣጡት የዲደአ ተማሪዎች ናቸው….የዲደአ ትምህርትቤት ቆንጆ የመማሪያ ቦታ ነው፡፡ ተማሪዎች መካከል ሰላማዊ የውድድርና የጥናት መንፈስ አለ፡፡ ቀድሞ ስለነበሩት ጎበዝ ተማሪዎች ለምሳሌ ስለነእንዳልካቸው ደቻሳ፤ ስለነ ዳመኑ ሽፈራው፣ ስለነ ፍቃዱ ፈጠነ፣ ስለነ  ታገል አበራ ወዘተ የሚነገረው ታሪክ ለስራ ያነቃቃል፡፡

መምህር አላሮ

ከአርሲ ሮቤ ዲደአ ከፍተኛ ትምህርትቤት ካስተማሩኝ መምህራን ሁሌም በአእምሮዬ ካሉት መምህራን ውስጥ የታሪክ መምህሩ አላሮ ነው፡፡ መምህር አላሮ እጅግ ጎበዝ መምህር ነው፡፡ ማየት የተሳነው ቢሆንም የሰው ልጅ አይን አእምሮ እንጂ አይን ብዙም መሰረታዊ እንዳልሆነ ህያው ምስክር ነው፡፡ መምህር አላሮ አይነስውር ቢሆንም ከቤቱ ተነስቶ በእግሩ እስከ ዲደአ ትምህርት ቤት ይሄዳል፤ በተጨማሪም በክፍለጊዜው ከአንዱ ክፍል ወደሌላው ክፍል ያለምንም ረዳት መንቀሳቀስ መቻሉና ክፍል ውስጥ በሚያስተምርበት ወቅት ረባሽ ተማሪዎችን ለይቶ ማወቁ ሁሌም የሚገርመኝና የማደንቀው ነው፡፡ በተጨማሪም አላሮ የሚያስተምረውን የታሪክ ትምህርት በጥልቀት ስለሚያውቅ ለተማሪዎቹ ትልቅ መምህር ነው፡፡ እንደ አላሮ ባሉ መምህራን መማር እጅግ መታደል ነው፡፡ መምህር አላሮ እግዚአብሄር እድሜህን ያርዝመው፡፡ በአርሲ ሮቤ ዲደአ ከፍተኛ ትምህርትቤት የነበረኝ የተማሪነት ቆይታ መቼም ከአእምሮዬ የማይጠፋ ትዝታዬ ነው፡፡ እስካሁን በትምህርት ህይወቴ ካሳለፍኩባቸው ትምህርትቤቶች ውስጥ ለየት ያለ የትህምህርት ጊዜ የነበረኝ በኢደአ ነው፡፡ ከሁሉ በላይ ለትዳር የበቃው የፍቅር ህይወቴም እዛው ዲደአ እያለሁ የተጀመረ ስለሆነ የዲደአ ትዝታዎቼ ተነግረው አያልቁም….

 

 

የዚህን መፅሀፍ የመጀመሪያ ረቂቅ ያነበበ አንዱ የቀድሞ የዲደአ ተማሪ ቀጥሎ የተጠቀሰውን ሀሳብ ልኮልኝ ነበረ /….ፍቄ በጣም የሚገርምና ሁላችንንም ወዳኋላ ተመልሰን ያለፈውን ጊዜ በትዝታ አንድናስታውስ ነው ያደረከን፡፡ መምህር አላሮ ቲቶ የሚገርም ተሰጥኦ ያለው ሰው ነው፡፡ አንድ ገጠመኝ ላክል፣ እኔ የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ ሆኜ ረባሽ ነበርኩ እና አንድ ቀን አርፍጄ ስመጣ መምህር አላሮ በከፍተኛ ተመስጦ ተማሪዎቹን እያስተማረ ነበር፤ ክፍለ ጊዜው እንዲያመልጠኝ አልፈልግም ነበርና ጫማዬን አውልቄ ድምጽ ሳላሰማ ቀስ ብዬ ግድግዳውን ታክኬ ኮሽ ሳላደርግ ወንበሬ ላይ ቁጭ ብዬ ትምህርቴን መከታተል ጀምርኩ፡፡ መምህር አላሮ አሁንም በተመስጦ እያስተማረ በወንበርና የጠረጴዛ ረድፍ መሃል በመግባት ሌክቸሩን ሳያቋርጥ እኔ ወደተቀመጥኩበት ወንበር በመምጣት ጆሮዬን በመጎተት ከክላስ ያስወጡኝን ሁኔታ መቼም አልረሳውም፡፡ በኋላም ውጪ ጠብቄ ይቅርታ ጠይቄ፣ ተመክሬ፣ በጣም አቅርቦኝ፣ እንደጓደኛ ነበር የምንተያየው፡፡ ረጅም እድሜና ጥና ለመምህር አላሮ ቲቶ…/

የዲደአ ምርጦች፣ ወጣትነት፣ መረጃ

በዲደአ የቀድሞ ተማሪ ከነበሩት ውስጥ የነእንዳልካቸው ደቻሳና የነዳመኑ ሽፈራው ጉብዝና ብዙዎቻችንን የበለጠ እንድናጠና ያበረታታን ነበረ፡፡ እኔ የ9ኛ ክፍል ተማሪ ሆኜ የ11ኛ ክፍል ተማሪ የነበረው እንዳልካቸው የሂሳብና የፊዚክስ ትምህርቶች ጉብዝናው በግቢው በሰፊው  ይወራለት ነበረ፡፡ እንዳልካቸው የ11ኛ ክፍል ተማሪ ሆኖ የ12ኛ ክፍል የሀገር አቀፍ ፈተና ሰርቶ መልሱን ለተፈታኞች አርሞላቸዋል ሲባል ሰምቼ ልጁን ሳየው በመገረም ነበር የምመለከተው፡፡ እንደ እንዳልካቸው መሆን አለብኝ ብዬም አጠና ነበረ፡፡ ዲደአ ተማሪ ሆኜ እንዳልካቸውን በክብር ነበረ የምመለከተው፤ በአጠገቤ ሲያልፍ ኩራት ይሰማኝ ነበረ፡፡ እንደ እንዳልካቸው ጎበዝ ብሆን ብዬም እመኝ ነበረ፤ ይህ የሚያሳየን ተማሪዎች ከታላቆቻቸው መልካም ስራ የስራ አርአያ የሚወስዱ መሆኑን ነው፡፡ የአንዱ ተማሪ ስኬት የራሱን ታናናሾችና በክፍል ውስጥ አብረውት የሚማሩትን እንዲሁም ለትምህርት ቤቱ ተማሪዎችና መምህራን ኩራት መሆኑንም መገንዘብ አለብን፡፡

 

 

 

ዲደአ አስረኛ ክፍል ተማሪ ሆኜ ሂሳብ ትምህርት 100 ከ100 ለማምጣት ቀድሜ ወሰንኩ፤ ምንም ስህተት አልቀበልም ብዬ ለራሴ ነገርኩ፡፡ የራሴ እቅድ ራሴን አስጨንቆኝ ነበረ፤ የሚገርመው ነገር የመጀመሪያውን ከ20 ፈተና 15 አመጣሁ፣ ከዛ ገጠመኝ አንድ ነገርም ተማርኩኝ፣ አንድ ሰው ስራ ሲሰራ ውጤቱን ሙሉ በሙሉ ቀድሞ በማስቀመጥ ራሱን አላስፈላጊ ጭንቀት ውስጥ ማስገባት እንደሌለበት ነው፡፡ በሂሳብ ትምህርት ከፍተኛ ውጤት ለማምጣት ማጥናት ቆንጆ ቢሆንም 100 ከ100 ማምጣት አለብኝ ብሎ ራስን ምንም እንከን የሌለበት ተማሪ አድርጎ መቁጠር አላስፈላጊ ነው፡፡ ትምህርት ከስህተትም የምንማርበት እንጂ ሁሉንም የምንማረውን ፈተና መመለስ ላይሆን ይችላል፡፡ አንድ ተማሪ 90፣ 80፣75 ወይም 50 ከዛምበታች ሊያመጣ ይችላል፡፡ ዋናው ጉዳይ ተማሪው ጊዜውን በአግባቡ ተጠቅሞ የሚችለውን ያህል መጣጣሩ ላይ እንጂ በአንድ ክፍል ውስጥ የሚማሩት ተማሪዎች ሁሉ ተመሳሳይ ከፍተኛ ውጤት ማምጣት አለባቸው ማለት አይቻልም፡፡

 

በዲደአ ከነበረው ልምዳችን አልፎ አልፎ ይታይ የነበረው የኩረጃ ችግር ነበረ፡፡ በዲደአ ብዙ ታታሪ ተማሪዎች የመኖራቸውን ያህል ዱርዬነትን ብቻ ከሁሉ አስበልጠው የነበሩ ተማሪዎችም ነበሩ፡፡ በእርግጥ ከ9- 12 ያለው የትምህርት ጊዜ አፍላ ወጣትነት የሚጀምርበት ጊዜም ነው፣ ስለሆነም በተቃራኒ ፆታ ፍቅር ህይወታቸው የሚሰናከል ወጣቶችም ብዙ ነበሩ፡፡ እነኚህ አይነቶቹ ወጣቶች ደግሞ ወላጆቻቸው ነገ ተምሮ የሆነ ደረጃ ይደርስልኛል ብለው የሚጠብቁትን ተስፋ አላስፈለጊ የሆነ የአንድ ወገን የፍቅር ህይወት ውስጥ ገብተው የወደፊት ህይወታቸውን ሊያጨልሙ ይችላሉ፡፡ በተጨባጭ ችግር የገጠማቸውን ተማሪዎችንም አይተናል፤ ጎበዝ ተማሪዎች ሆነው፤ በትምህርታቸው ከፍተኛ ውጤት ማምጣት እየቻሉ፣ አላስፈላጊ ወደሆነ ነገር ትኩረታቸውን በማድረግ ከትምህርታቸውና ከወደፊት ህይወታቸው የተሰናከሉ ተማሪዎችንም አይቻለሁ፡፡ ስለሆነም ወላጆች የቅርብ ክትትል ማድረግ ጠቃሚ ነው፡፡

 

 

ወጣትነት አደገኛ ጊዜ ነው፤ ወጣት ብዙ ነገሮችን ማድረግና ማግኘት ይችላል፤ ነገር ግን መታገስና ፈተናን ማለፍ የግድ ነው፡፡ በተለይ እንደ እኔ የወላጆቻቸው የኢኮኖሚ አቅም ዝቅተኛ ከሆነ ቤተሰብ የተወለዱ ወጣቶች የሚፈልጉትን ሁሉ ለማድረግ ነገሮች ምቹ ላይሆኑ ስለሚችሉ እጅግ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

 

እኔ የ12ኛ ክፍል ተማሪ ሆኜ ትልቁ ጭንቀቴ ዩኒቨርሲቲ መግባት ባልችል ምን እሆናለሁ የሚለው ጥያቄ ነበረ፡፡ ምክንያቱም የትምህርቱ ህይወት ባይሳካ ወደንግድ ወይም ግብርና ስራ ለመግባት የመነሻ ገንዘብ ወይም የእርሻ መሬትና ሌሎቹ ነገሮች ያስፈልጋሉ፡፡ ከ4-8 ስማር ሊስትሮ እየሰራሁ ተማርኩ፤ ከ9-12 ደግሞ በወላጆቼ እርዳታ በብዙ ችግር ተማርኩ፤ ዩኒቨርሲቲ መግባት ግን ለእኔ እጅግ አስፈላጊ ነበረ፡፡ ስለሆነም እኔና አብረውኝ የነበሩት የትምህርትቤት ወዳጆቼ ብዙውን ጊዜያችን በትምህርትና በጥናት ነው ያሳለፍነው፡፡ እጅግ የሚገርም የጥናት ጥረትና ጉጉት ነበረን፡፡ አሁን ያሉት ተማሪዎች በፌስቡክና በእንግሊዝ ፕሪሜርሊግ ጫወታ ጊዜያቸው እንደሚከፋፈል ምንም ጥያቄ የለውም፡፡ ዛሬ ያለው ቴክኖሎጂ እኔ ተማሪ በነበርኩበት ጊዜ አልበነረም፡፡ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪ ትምህርት እየተማርኩ ሞባይል ስልክ የነበራቸው ሁለት ወይም ሶስት ተማሪዎች ነበሩ፡፡ ዛሬ ደግሞ የ5ኛ ክፍል ተማሪ ፌስቡክ በስልኩ ከፍቶ ሲጠቀም ማየት የተለመደ እየሆነ ነው፡፡

 

ቴክኖሎጂው ግን ሙሉ በሙሉ ጎጂ ነው ማለት አይደለም፤ ተማሪዎች በሚገባ ጊዜያቸውንና ቴክኖሎጂውን ከተጠቀሙበት፣ ኢንተርኔትን በመጠቀም ለሚማሩት ትምህርት ተጨማሪ መረጃ ማግኘት ይችላሉ፤ በተጨማሪም ዩቱብ በመባል የሚታወቀው /www.youtube.com/ እጅግ ብዙ ትምህርት ነክ ቪዲዮዎች አለው፡፡ ለምሳሌ በሰውነታችን ውስጥ የደም ዝውውር እንዴት እንደሆነ በቀላሉ እዚህ ድህረገፅ ውስጥ ቪዲዮ በማየት መማር ይቻላል፡፡ በመሆኑም በክፍል ውስጥ መምህራን የሚያስተምሩትን ትምህርት የሚደግፉ ብዙ መረጃዎችን ከኢንተርኔት ማግኘት ይቻላል፡፡ ስለሆነም ወጣቱ የሞባይል ስልክንና የኢንተርኔትን ቴክኖሎጂ ፌስቡክ ላይ ፎቶና ሌሎች ነገሮችን ከማየት በተጨማሪ ትምህርት ነክ ለሆኑ አላማዎች ሊጠቀምበት እንደሚገባ ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡ /www.youtube.com/ በሚለው ድህረገፅ ምህንድስና የሚማሩ፣ የህክምና፣ የግብርና የኬሚስትሪ፣ የባዮሎጂ፣ የኮምፒውተር ወዘቱ ለሁሉም የስልጠና ዘርፎች የሚሆኑ ተጨማሪ መረጃዎች ማግኘት እንደሚቻል ለተማሪዎች ግንዛቤ ማስጨበጥ ያስፈልጋል፡፡ የኢንተርኔት ቴክኖሎጂ መስፋፋት አንዱና ትልቁ ጠቀሜታ እውቀትና መረጃ በአጭር ጊዜ በአለማችን እንዲሰራጭ ማድረግ ማስቻሉ ነው፡፡

 

በአሁኑ ሰአት ከኢንተርኔት፣ ከመዋለህጻናት ጀምሮ እስከ ሶስተኛ ዲግሪ ለሚማሩ ተማሪዎችና እንዲሁም ተመርቀው በስራ ላያ ላሉ ባለሙያዎች የሚሆን መረጃ በሰፊው ማግኘት ይቻላል፡፡ ይህ ማለት ግን በኢንተርኔት ተፈልጎ የሚገኝ መረጃ በሙሉ ታማኝነት አለው ማለት አይደለም፤ ቢሆንም ወጣቱ ትውልድ ፌስቡክ ላይ ከሚያሳልፈው ጊዜ የተወሰነውን ሌሎች ሳይንሳዊ የሆኑ ነገሮችን ለማንበብ ቢጠቀምበት ድምር ውጤቱ ለወጣቱም ለሀገራችንም ነው፡፡ ፌስቡክም ጠቃሚና ጎጂ ጎኖች ስላሉት አጠቃቀሙን በተመለከተ የወላጆችና የመምህራን ምክር ያስፈልጋል፡፡ ዋናው ችግር ብዙዎቹ ወላጆቻችን የልጆቻቸውን ያህል ለመረጃና ለቴክኖሎጂ ቅርብ ስላልሆኑ ለልጆቻቸው የሚጠቅመውንና የሚጎዳውን ለይቶ ከማስረዳት ይልቅ ሙሉ በሙሉ ወደመከልከል እንደሚሄዱ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ልጆቻችንን አታድርጉ ብለን አስገድደን ስለከለከልናቸው የሚፈልጉትን ሳያደርጉ ይቀራሉ ማለት አይቻልም፡፡

ከራሴ የልጅነት ህይወት የማስታውሰው ወላጆቼ አታድርግ የሚሉኝ የነበሩትን አብዛኞቹን ነገሮች ተደብቄ አደርግ ነበረ፤ ስለሆነም ልጆቻችንን አላስፈላጊ ከሆኑ ነገሮች ለመጠበቅ ቁጣና ክልከላ ሳይሆን በጎ በጎውን ወስደው መጥፎውን እንዲተዉ በትእግስትና አርቆ በማሰብ ማስተማር ያስፈልጋል፡፡ ልብ በሉ፣ ልጆቻችን ከኛ የበለጠ ያውቃሉ፣ ያታልሉናልም! ስለሆነም ከልጆቻችን ጋር ድብበቆሽ ውስጥ ከመግባት መወያየትና የነሱንም ፍላጎት በተቻለ መጠን ማሟላት ያስፈልጋል፡፡  ልጅ ማሳደግ ቀላል አይደለም፤ እንዲሁም ለልጆች የሚያስፈልጉትን ነገሮች በሙሉ ወላጆች ማቅረብ ላይችሉ ይችላሉ፣ ስለሆነም ልጆችም የወላጆችን የኢኮኖሚ ደረጃ ማወቅ፣ ራሳቸውን መርዳትና ከአደገኛ ነገሮች ራሳቸውን መጠበቅ አለባቸው፡፡

ድህነትና ወጣትነት

እኔ ብዙ ባይሆንም የተወሰኑ የህይወት ፈተናዎችን አሳልፌ ነበረ፡፡ ከፈተናዎች አንዱ ድህነት ነው፡፡ ድህነት ከባድ ፈተና ነው፡፡ የወጣትነት እድሜን ለአደጋ ያጋልጣል፡፡ አንዳንዶቹ ወጣቶች ከድህነት በቶሎ ለመላቀቅ አላስፈላጊ እርምጃ ይወስዳሉ፤ ወንጀሎች ይሰራሉ፣ ወይም በተቃራኒ ፆታ ፍቅር ይወድቁና ከማፍቀሩ ጋር ተያይዞ ለሚመጣው የመንፈስ መረበሽና ውጥረት በተነሳ ለህይወታቸው አደገኛ የሆኑ ተግባራት ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ አንድ ወጣት ያፈቀራትን ወጣት ፈቃደኝነት ሳያገኝ ሲቀር ጎጂ የሆኑ ድርጊቶችን ለማድረግ ሊነሳሳ ይችላል፡፡ እንዲሁም የሚያፈቅራትን ወጣት ከማንም ወንድ ጋር ግንኙነት እንዳይኖራት ሊፈልግ ይችላል፡፡ ፍላጎቱም ቀስ በቀስ ወደቅናት ሲሸጋገር ከፍቅረኛውና ከወዳጆቹ ጋረ ያለው ግንኙነት አስፈላጊ ወዳልሆነ አቅጣጫ ሊሄድ ይችላል፡፡ ስለሆነም ወጣትነት እጅግ ጥንቃቄ የሚፈልግ ጊዜ መሆኑን ወጣቶችና ወላጆች እንዲሁም ማህበረሰቡ በጥልቀት ሊረዳው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡

ሌላው ማስተዋል የሚገባው ጉዳይ አንድ ልጅ ወይም ወጣት ተምሮ ጥሩ ቦታ ለመድረስ ብዙ ገንዘብና የወላጆች ሀብት የግድ እንዳልሆነ ልብ ማለት ይገባል፡፡ በሀገራችን በአሁኑ ወቅት በከባድ ሱስና ዱርይነት ተጋልጠው ህይወታቸው በአደገኛ ደረጃ ከሚገኙት ወጣቶች ውስጥ ከፊሎቹ ከሀብታም ወላጆች የወጡ ናቸው፡፡ በተለይ አደገኛ ሱስንና በአልኮል መመረዝን በተመለከተ ዋነኞቹ ሰለባዎች የሀብታም ቤተሰብ ልጆች ናቸው፡፡ ይህ ችግር የሚባባሰው ደግሞ ልጆቹ ከወላጆቻቸው ቁጥጥር ወጥተው ወደዩኒቨርሲቲ ሲገቡና ስራ ይዘው የራሳቸውን ህይወት መምራት ሲጀምሩ ነው፡፡ ሀገራችን በብዙ ጎኑ ከደሀ ሀገራት ተርታ ብትሰለፍም የድህነታችን መሰረታዊው መንስኤ ግን የገንዘብና የሀብት እጦት ሳይሆን ያለውን ሀብት በአግባቡ ያለመጠቀም ችግር ነው፡፡ ትልቁ ሀብታችን ደግሞ የሰው ሀይላችን ነው፤ ከሰው ሀይልም ወጣቱ የሰው ሀይል፤ ችግሩን ለመቅረፍ ደግሞ ከራሱ ከወጣቱ ጀምሮ በየደረጃው ወላጆች፣ ትምህርት ቤት፣ የሀይማኖት ተቋማት፣ ማህበረሰቡ፣ ባለሀብቱ፣ ፖሊስ፣ መንግስት፣ የከተማ አስተዳደሮች ሁሉም ሀላፊነት አለበት፡፡ ይህንን ሀሳብ በሚቀጥሉት ክፍሎች በሰፊው እመለስበታለሁ፡፡

ስለምሁራንና ስለምርምሮቻችን ያለኝ አስተያየት

ለሀገራችን ድህነት ብዙ ጉዳዮችን እንደመንስኤ መጥቀስ ቢቻልም፣ የምሁራንና የምርምር ተጨባጭ ለውጥ ውስንነት አንዱ ችግር ነው ተብሎ ቢጠቀስ ማጋነን አይመስለኝም፡፡ ለምሳሌ ብዙ የግርብርና ባለሙያዎችና ምሁራን አሉን ነገር ግን ገበሬው ዛሬም ድረስ በዶማና በበሬ በሞፈርና በቀንበር እያረሰ ነው፤ ፖለቲከኞች ከጫወታው ውጪ አድርገውናል፤ እኛ በዩኒቨርሲቲ ግቢውስጥና በምርምር ተቋማት ውስጥ ተገድበን እንድንቀር ሆነናል፤ ወይም ፖለቲካውን እንደምክንያት አድርገን ህዝባችንን ድህነት ውስጥ ጥለን ወደሀብታም ሀገራት ተሰደናል፡፡ ይህ ታሪክ ነው መለወጥ ያለበት!

በሀገራችን ብዙ አዋቂዎችና ተመራማሪዎች አሉ፤ ብዙ ፕሮፌሰሮች አሉ፤ ነገር ግን አብዛኞቹ ፕሮፌሰሮቻችን ከህዝባችን ብዙ ርቀው ነው ያሉት፤ ለምሳሌ ውጪ ሀገር ብዙ የሀገራችን የተማሩ ዜጎች አሉ፣ የነሱን የአእምሮ ሀብት ሀገራችን በቀጥታ ልትጠቀምባቸው አትችልም፣ ምክንያቱ ምንድን ነው፣ መፍትሄውስ ምን መሆን                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                           አለበት የሚለውን ይህንን ጽሁፍ የምታነቡት ሁሉ እንድታስቡበት መልእክቴ ነው፡፡ በየቴሌቪዥን ጣቢያውና በየመገናኛ ብዙሀኑ የምናየው፣ ለልጆቻችንና ለህዝባችን በተደጋጋሚ የሚነገረው ዜና የዘፈንና የፊልም  ዜና ነው፤ ይህች ሀገር ለመለወጥ አሰራርና አስተሳሰባችንን መቀየር አለብን፡፡  ስለሆነም ምን መሆን ትፈልጋለህ ተብዬ ብጠየቅ መሆን የምፈልገውን መሆን ከማልፈልጋቸው ነገሮች ዝርዝር በመጀመር አስረዳለሁ፡፡ እኔ በትምህርት ከፍተኛ ደረጃ መድረስ እፈልጋለሁ፤ ነገር ግን ዶክተር ወይም ፕሮፌሰር ፍቃዱ መጡ ተብሎ ሰዎች ከመቀመጫቸው ተነስተው እንዲቀበሉኝ ወይም ፍቃዱ ብሎ ሲጠራኝ የነበረ ሰው ፕሮፌሰር ፍቃዱ ብሎ እንዲጠራኝ ሳይሆን የተማርኩት ትምህህርት ለሀገሬና ለወጣቱ እንዲሁም ለአለም ህዝብ ለውጥ ማምጣት እንዲችል እመኛለሁ፡፡ ይህን አይነት ምኞት ደግሞ የኔ ብቻ ሳይሆን የብዙ የሀገራችን ምሁራን ምኞት ነው፡፡ ምኞታችንን ወደተግባር ለመለወጥ ዋናው ማነቆ ሀሳባችንና ተግባራችን በቀጥታ ህዝብ ጋር የሚደርስበትን መንገድ አለማመቻቸታችን ነው፡፡ ለምሳሌ ምሁሮቻችን ብዙ ምርምር ሳትማሉ፣ ነገር ግን ከታተሙት ምርምሮች ህዝባችን ስንቶቹን ነው የሚነባቸው? ስንቶቹስ ምርምሮች ወደተግባር ተለውጠዋል? ስንቶቹ ምርምሮች ወደራሳችን መግባቢያ ተተርጉመዋል?

 

ችግሩ፣ በሀገራችን ከተግባር በፊት ስም ይቀድምና ብዙ ታላላቅ ምሁሮቻችን ከሰሩትና ለማህበረሰቡ ካበረከቱት በላይ ስማቸው ብቻ ትልቅ ተራራ ሆኖብን፤ አንቱ እሳቸው ምናምን እያልን ከመጥራት የዘለለ ህዝባችንን ከድህነትና ካለማወቅ ጭለማ ውስጥ ለማላቀቅ የተማረው ሰው ሚና ውስን ሆነ፡፡ ተመራማሪዎች የድርሰት አይነት ፅሁፍ የማይጽፉበት ምክንያትም አይገባኝም? ህዝቡና ወጣቱ በብዛት የሚያነበው የልብ ወለድ ድርሰቶችን ነው፤ ዋናው ምክንያት ደግሞ የምርምር ፅሁፎች ለህዝቡና ለወጣቱ ትርጉም በሚሰጥ መልኩ አለመዘጋጀታቸውና ተደረሽ እንዲሆኑ አለመደረጋቸው ነው፡፡

 

ብዙ የምርምር ስራ ውጤቶች በየዩኒቨርሲቲዎቻችን ውስጥ ሞልተዋል፣ ነገር ግን ምርምሮቹ ሲጠናቀቁ ወደማህበረሰብ ደርሰው የህዝቡን ውጤት የቀየሩት እጅግ አነስተኛ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ያህል የግብርናን ምሁራን ብንወስድ የእነሱ ምርምርና የገበሬው የእርሻ ስራ ብዙ ተራርቀው ነው ያሉት፡፡ ዛሬም ድረስ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ገበሬዎቻችን በማረሻ፣ በቀንበር፣ በሞፈር በጅራፍ ና በእንሰሳት ጉልበት ነው የሚያርሱት፡፡ በተጨማሪም ቡና በአለማችን ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘው ሀገራችን ቢሆንም፣ እንዲሁም የቡና ምርት የሀገራችን ትልቁ የውጪ ንግድ ሸቀጥ ቢሆንም፣ ቡናን በዘመናዊ መልኩ የሚያቀነባብሩ ማሽኖችን በሙሉ ከውጪ ወደሀገር ውስጥ እናስገባለን…፡፡ ከሞኚ ደጅ ሞፈር ይቆረጣል የተባለውም አንዱ ማሳያችን ይህ ነው፡፡ ስለሆነም የተማሩ የምንባለው የሀገራችን ዜጎች የህዝባችንን ችግር መፍታትና ወደህዝቡ ቀረብ ብለን ችግሮቹን ልናዳምጥ ያስፈልጋል፡፡ ስለሆነም ሳይንሳዊ እውቀታችን ወደሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ መምጣት አለበት፡፡ ካልሆነ ግን ሁላችንም ኪሳራ ነን ማለት ነው፤ ምክንያቱም አንድ ሀገር መቀየር ካለባት የለውጡ ሞተር መሆን ያለበት የሀገሪቱ የተማረ ሀይል ነው፡፡ ስለዚህ የሀገራችን ምሁራን ያለንበት ደረጃ ምን ይመስላል የሚለውን ራሳችንን እንድንጠይቅ ያስፈልጋል፡፡

ትዝታ፣ የመንገድ ጉዳይ

በአርሲ ሮቤ ዲደአ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርትቤት የነበረኝን ቆይታ እጅግ አስደሳችና የማይረሳ ከሚያደርጉት ጉዳዮች መካከል በትምህርት ቤት ህይወቴ እጅግ ከፍተኛ ውጤት ያመጣሁት ዲደአ ትምህርት ቤት ሲሆን ከውድዋ ባለቤቴ ጋርም የተገናኘነው እዛው አርሲ ሮቤ ከተማ እኔ የ11ኛ ክፍል ተማሪ ሆኜ እስዋ ደግሞ የ9ኛ ክፍል ተማሪ ሆና ነበረ፤ ስለሆነም አርሲ ሮቤ በእኔ ህይወት ውስጥ ከፍተኛውን ቦታ ትይዛለች፡፡

 

በተጨማሪም ከአርሲ ሴሩ 75ኪሎ ሜትር ርቀን ዲደአ ትምህርታችንን በመከታተል በዛ ለጋ እድሜ ራስን በራስ ማስተዳደርን የተማርኩበት ከተማ ናት አርሲ ሮቤ፣ ዲደአ ትምህርት ቤት በሀገራችን ካሉ ታዋቂና ባለውለታ ትምህርትቤቶች አንዱ ነው፡፡ ዲደአ የተማሩ ተማሪዎች በሀገራችን ትልልቅ የልማት ስራዎች ውስጥ ታላቅ ሚና እየተጫወቱ እንደሆነ አውቃለሁ፣ እንዲሁም የትምህርትቤቱ መምህራን ጎበዞችና ለሙያቸው ታማኝ ነበሩ፤ የከተማዋም ህዝብ ለተማሪዎች በጣም ጥሩ ነበረ፡፡

 

ከዲደአ ትዝታዎቻን አንዱ ሮቤ ዲደአ ተማሪ ሆነን የምግብ ስንቅ እያለቀብን የምንቸገረው  ነው፤ ምክንያቱ ደግሞ ከሴሩ ሮቤ ድረስ ያለው የመኪና መንገድ በተለይ በክረምት ወራት ስለሚበላሽ ትራንስፖርት አይገኝም ነበረ፤ የሚገርመው፣ ከ15 አመት በኋላ አሁንም ከሁሩታ አርሲ ሴሩ ድረስ ያለው የሀገራችን ህዝብ አንዱና ትልቁ የልማት ጥያቄ የመንገድ ችግር ነው፡፡ ከዴንማርክ ወደ ሀገራችን ተመልሰን ወላጆቻችንን ለመጠየቅ ሴሩ ደርሰን ለመመለስ ሄደን፣ በጉዞ ወቅት በመኪናው ገጭገጭ ስንናጥ ነው ሴሩ የደረስነው፤ መንገዱ እጅግ የተበላሸ ነበረ፤ በዛ መንገድ ላይ ነብሰጡር እናቶች እንዴት እንደሚሄዱ ሳስበው ያሳዝናል፣ በዛ መንገድ ላይ የሚነዳ መኪናም በቀላሉ ለብልሽትና ለኪሳራ እንደሚጋለጥ ግልፅ ነው፡፡ ከሁሩታ አርሲ ሴሩ እንዲሁም ከሴሩ ድሬ ሼሁሴን ድረስ ያለው መንገድ አስፋልት ሆኖ ቢሰራ የአከባቢያው ህዝብና ሀገራችን ተጠቃሚ እንደሚሆን አያጠያይቅም፡፡

 

የአከባቢው የሀገር ሽማግሌዎች ስለዚህ መንገድ ጉዳይ ብቻ ተብሎ ተልከው አዲስ አበባ ይመላለሱ እንደነበረ አውቃለሁ፡፡ ይህ መጽሀፍ ለህትመት በዝግጅት ላይ እስከነበረበት ጊዜ ድረስ ግን የአስፋልት መንገድ ስራውን ማየት አልተቻለም፤ ከሁሩታ እስከ ሴሩ ከዛም አልፎ እስከ ሊሎና በረከት ከዛም እስከ ድሬ ሼሁሴን ላለው የሀገሬ ህዝብ ያ መንገድ ቢሰራ ለህዝቡም፣ ለሀገራችንም ትልቅ የልማት ማነቆ ተቀረፈ ማለት ነው፤ በነገራችን ላይ አርሲ ዞን የሀገራችን የዳቦ ቅርጫት /the breadbasket of Ethiopia/ ተብላ ትጠራ ነበረ፡፡ ለምሳሌ አርሲ ሮቤንና አርሲ ሴሩን ብንወስድ የሽንኩርት፣ የጤፍ፣ የቀንድ ከብት፣ የበጎች፣ የፍየሎች፣ የባቄላ፣ የገብስ፣ የስንዴ ወዘተ ምርቶች በብዛት የሚመረቱበት በተፈጥሮ የታደለ አከባቢ ነው፡፡ መሰረተ ልማቱ ግን በሀገራችን አቅም በጣም አነስተኛ ነው፡፡

 

የዲደአ ቆይታችንን የሀገር አቀፉ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ማትሪክ ፈተና ሲቃረብ እጅግ አስጨናቂ እንደነበረ ትዝ ይለኛል፤ለፈተናው በሰፊው እያጠናን መዘጋጀት የጀመርነው ከ11ኛ ክፍል ጀምሮ ነበረ፡፡ ብዙ ብናጠናም ጊዜው እየተቃረበ ሲመጣ በራስ መተማመናችንን በተወሰነ መልኩ መቀነሱ ትዝ ይለኛል፡፡ በደንብ ተዘጋጅተን ስለነበረ ለብዙዎቻችን ውጤቱ እጅግ አስደሳች ነበረ፡፡

 

አይጧ

11ኛ ክፍል ጨርሰን ለ12 ሀገር አቀፍ ፈተና ክረምቱን እያጠናሁ አንዲት አይጥ ቤቴ ገብታ ትረብሸኝ ነበረ፤ ካልሲ፣ ፓንት፣ ሽሮ ወዘተ ትበላብኝ ነበረ… የሚገርመው ምንም አትፈራኝም ነበረ፤ አሁን ድረስ አስታውሳታለሁ፤ ምክንያቱም እኔ አይጥ እፈራለሁ፤ በልጅነቴ አስደንግጠውኛል

 

ኩረጃ

በ2008 ዓ.ም. ሀገር አቀፍ የ12ኛ ክፍል ዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና መሰረቁም ስሰማ ኩረጃና የፈተና መሰረቅ ቀድሞውንም የነበረ መሆኑ በተወሰነ መልኩ የሚታወቅ ቢሆንም የመረጃ ልቅውት ቴክኖሎጂ መስፋፋት ግን ጉዳዩን በቀላሉ ሀገር አቀፍና ከሀገር ውጪም ላሉ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ድረስ በአንድ ሰአት ጊዜ ውስጥ መረጃው መዳረሱ ወደፊት የትምህርትና የፈተና ስርአታችንን አሁን ካለው አሰጣጥ መቀየር እንደሚያስፈልግ ተገንዝበናል፡፡ በቴክኖሎጂ እገዛ አንድ ትምህርት ቤት ውስጥ የተሰረቀ ፈተና ለሀገራችን ሁሉ ተማሪዎች እንዲዳረስ ለመሆን ቻለ፤ በእርግጥ በዚህ አመት የነበረው ፈተና ለየት ያለ ነበረ፤ ምክንያቱም ከፈተናው በፊት በብዙ ትምህርትቤቶች ግጭቶች ስለነበሩ ትምህርት ተቋርጦ ስለነበረ ትምህርት የተቋረጠባቸው ትምህትርቤት ተማሪዎች ለፈተናው ዝግጅት ተቸግረው እንደሚሆን ምንም ጥያቄ የለውም፤ ለወደፊቱ የሚመለከታቸው አካላት ጥንቃቄ ያደርጋሉ ብለን በማሰብ ስለኩረጃ አጠቃላይ ጎጂነት ስምምነት ላይ መድረስ ያለብን ይመስለኛል፤ ምክንያቱም ተማሪዎች በራስ መተማመናቸው ይቀንሳል፤ ሰርተው ከመለወጥ ይልቅ ኮርጀው ማለፍን እንደ ጥሩ አማራጭ ሊቀበሉት ይችላሉ፡፡

 

ወጣቱም መረዳት ያለባቸው ጉዳይ ኮርጀው ዩኒቨርሲቲ ቢገቡም ሌላ ፈተና ስለሚጠብቃቸው በሌላ ሰው ስራ ከመተማመን በራሳቸው ሰርተው ለማለፍ መዘጋጀት አለባቸው፡፡ ወደዩኒቨርሲቲ በኩረጃ የሚገቡት አብዛኛው ተማሪዎች መባረራቸው የማይቀር ነው፣ በተጨማሪም ትምህርት ስለሚከብዳቸው አላስፈላጊ ለሆነ ጭንቀትና ሱስ ይዳረጋሉ፤ በመሆኑም የኩረጃ ጉዳይ እጅግ ጎጂ ስለሆነ ሊታሰብበት ይገባል፤ ኩረጃ የለመዱ ተማሪዎች ዩኒቨርሲቲ ከገቡ ቀሚሳቸውና ጃኬታቸው ላይ ጭምር መልስ ይሆናል ብለው የሚገምቱትን ሀሳብ ፅፈው ፈተና ክፍል ገብተው ሲያዙ እያየን ነው፡፡

የዩኒቨርሲቲ ምደባ ምርጫ

 

የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ከወሰድናቸው ስምንት ትምህርቶች /ሂሳብ፣ ኢንግሊዘኛ፣ አማርኛ፣ አፋን ኦሮሞ፣ ኬሚስትሪ፣ ባዮሎጂ፣ ፊዚክስ፣ ጀነራል ሳይንስ/ ስምንቱንም A ነጥብ አመጥቼ ለራሴም ለወላጆቼም እንዲሁም ለትምህርትቤታችን ታላቅ ደስታ ሆነ፡፡ እጅግ ተደሰትኩ፤ ወላጆቼ፤ ያስተማሩኝ መምህራን የሴሩ ወዳጆቼ ሁሉ ተደሰትን፡፡ ለ12ኛ ክፍል ከፍተኛ ውጤት ስላመጠሁ እንደ ሽልማት አዲስ አበባን እንድጎበኝ ዘመዳችን ዮሀንስ ኬኔ ይዞኝ ሄደ፤ በነገራችን ላይ ዮሀንስ ኬኔ ብዙ የሴሩ ልጆችን ያስተማረ ባለውለታችን  ነው፤ ስንቃችንንና እኛን በማመለሳለስ፤ ከባድ ባለውለታችን ስለሆነ ሁሌም እናስታውሰዋለን፡፡

 

አዲስ አበባ እንድጎበኝ የተደረገበት ምክንያትም ዩኒቨርሲቲ የምማረው እዛ ይሆናል ብዬ ስለወሰንኩ ነበረ፤ ስለሆነም የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተናውን ማለፌን ሳረጋግጥ 4ኪሎ አከባቢን ቀደም ብዬ ለመለማመድም ነበር የሄድኩት፡፡ የሚገርመው ነገር ለ12ኛ ክፍል ውጤት መምጣት በጣም ብደሰትም የት ዩኒቨርሲቲ ልማር፤ ምን ሙያ ልማር የሚለው ጥያቄ እጅግ አስጨናቂ ነበረ፡፡ ብዙ የገጠር ተማሪዎች ተመሳሳይ የመረጃ ችግር እንደሚኖራቸው እርግጠኛ ነኝ፡፡ ሰው መጠየቅ ደግሞ ችግሩ የሚጠየቀው ሰው የራሱን ፍላጎት ነው ሚነግረን እንጂ ሰከን ባለ መንፈስ ተማሪው ምን ይፈልጋል፣ ዝንባሌው ምንድን ነው ብሎ አያስረዳንም፡፡ ለምሳሌ የራስን ሙያ አወድሶ ሌላውን ሙያ እንዳንመርጥ ወደተሳሳተ መንገድ ሊወስደን ይችላል፡፡ መጀመሪያ የራሴን ልምድ ላካፍልና መጨረሻ ላይ አስተያየትም እሰጣለሁ፡፡

 

በ1993 ዓ.ም. እኛ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት መምረጥ የነበረው ምርጫ 4 ብቻ ነበረ፤ መምረጥ የምንችለው የተፈጥሮ ሳይንስ፣ የማህበራዊ ሳይንስ፣ ኮተቤ እስፖርትና አርባምንጭ ውሀ ምህንድስና ብቻ ነበሩ፡፡ ዩኒቨርሲቲ መምረጥ አልነበረም፤ ስለሆነም እኔ መጀመሪያ ተፈጥሮ ሳይንስ፣ ቀጥሎ አርባምንጭ ውሀ ምህንድስና፣ ቀጥሎ ማህበራዊ ሳይንስና መጨረሻ ላይ ኮተቤ እስፖርትን ሞላሁ፡፡ ኮተቤ እስፖርትን መጨረሻ የሞላሁት እስፖርት ሰነፍ ስለሆንኩኝ ነው፤ ስምንተኛ ክፍል ተማሪ ሆኜ በእስፖርት ክፍለጊዜ አግንብሳችሁ ጉልበት ሳይታጠፍ የእግራችሁን ጣቶች ንኩ ሲባል እያቃተኝ እገረፍ ነበረ፡፡

 

ለሁሉም ፎርም ተሞላ፤ ፎርም ተሞልቶ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ድልድል በኛ ፍላጎት ሳይሆን በትምህርት ሚኒስቴር ፍላጎት ብቻ ስማችን በጋዜጣ መውጣት ጀመረ፤  ትዝ ይለኛል ድልድሉ ከሰኞ እስከ አርብ በየቀኑ ነበር በአዲስ ዘመን ጋዜጣ የሚወጣ የነበረው፤ ከሰኞ እስከ ሀሙስ ድረስ በወጡት ጋዜጦች ላይ የኔ ስም አልነበረም፤ በአምስተኛው ቀን አርብ ለት ደቡብ ዩኒቨርሲቲ ግብርና ኮሌጅ የሚል ዝርዝር ውስጥ ስሜን አገኘሁት፤ በፍጹም ያልተጠበቀ ነበረ፤ እኔ ሀዋሳ የሚባል ከተማ መኖሩን እንጂ ዩኒቨርሲቲ እንደነበረ አላውቅም ነበረ፤ ደጋግሜ ለማስታወስ ሞከርኩ፤ ነገር ግን የሀዋሳን ስም ሰምቻለሁ ነገር ግን ስለደቡብ ዩኒቨርሲቲ ምንም የሰማሁት አልነበረም፡፡ የተመደብኩት ደቡብ ዩኒቨርሲቲ ነው፤ ታዲያ እንዴት ልሂድ? ከማን ጋር ልሂድ? ለብቻዬ፤ እጅግ እየፈራሁ፤ እየቀፈፈኝ፤ ምንም ሳላምንበት ጉዞዬን ቀጠልኩ፡፡

ግብርና ስልጠና

የግብርና ሙያ ለመማርም ምንም ሀሳብና ፍላጎት አልነበረኝም፡፡ ለምን የሚለው ትልቅ ጥያቄ ቢሆንም፡፡ ከሁሉ በላይ የመረረኝ ግብርና ኮሌጅ በመመደቤ ነበረ፤ ለምን ግብርና እንደዛ እንደተጠላ እይገባኝም፡፡ አብዛኛው የ12ኛ ክፍል ተማሪ ዩኒቨርሲቲ ስትገባ ምን መማር ትፈልጋለህ ተብሎ ቢጠየቅ ግብርና መማር እፈልጋለሁ የሚል ብዙ የሚኖር አይመስለኝም፤ በተለይ ጎበዝ ተማሪዎች ሀኪም ወይም መሀንዲስ መሆን እፈልጋለሁ ማለት የተለመደ ይመስለኛል፡፡ እኔም ሀሳቤ የኮምፒውተር መህንድስና መማር ነበረ፤ ታዲያ እድል ግብርና ላይ ጣለኝ፤ የሀገራችን ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ግብርና፤ ብዙ የሀገራችን ህዝቦች የሚተዳደሩበት የስራ መስክ ግብርና፤ ቢሆንም እስካሁን ህዝባችንን ከድርቅና ከተደጋጋሚ የምግብ እጥረት መታደግ የተሳነው ግብርና ነው፤ የግብርና ሙያ፡፡ የግብርና ሙያ ሳይንስ እንደ አውሮፕላን በረራ ወይም የስነህዋስ ጥናት ጠጣር ሳይንስ ባይሆንም ለማንኛውም ሀገር እድገት የጀርባ አጥንት ነው፡፡ ይህንን የግብርናን ሙያ ጉዳይ በሚቀጥለው ክፍል ከዴንማርክ ሀገር ቆይታዬ ጋር አስተያይቼ ሀሳብ እሰጥበታለሁ፡፡

 

ሀዋሳ ስደርስ ከመኪና ወርጄ አንዲት እናትን  ሀዋሳ ግብርና ኮሌጅ የት ነው ብዬ ጠየቅኩ፣ እናትየዋ  ወደመምህራን ኮሌጅጠቆሙኝ፡፡ ትልቅ እናት ነበሩ፤ ሌላ ሰው አትጠይቅ ዝም ብለህ በዚህ  ቀጥ ብለህ ሂድ ትዘረፋለህ ተባልኩ፤ በተነገረኝ መንገድ ብዙ ከሄድኩ በኋላ  ስጠይቅ አልፈሀዋል ተባልኩ፤ ግብርና ኮሌጅ ዋና መግቢያው በር ላይ ስደርስ አዲስ ገቢ ተማሪዎችን ለመቀበል የተዘጋጁ ነባር ተማሪዎች በር ላይ ተቀበሉኝ፤ ነባሮቹ ተማሪዎች አዲስ ገቢ ተማሪዎችን እንዲቀበሉ በሀይማኖት ተቋማት በኩል ተመድበው እንደሆነም ቆይቼ ተረዳሁኝ፤ ተማሪዎቹ ተቀበሉኝ፤ ተመዘገብኩ፤ ብሎክ 301 ዶርም ቁጥር 17 ተመደብኩ፡፡

 

የስልጠና ሙያ መስክን መምረጥ ለተማሪዎች እጅግ ከባድ ነው፤ ከራሴ ልምድ የተማርኩትም ይህንኑ ነው፤ የምንማረው የሙያ መስክ ወደፊት የሚኖረንን የህይወት ስኬት በብዙ መልኩ ይወስናል፡፡ የዩኒቨርሲቲ ህይወትን ስኬታማ ከሚያደርጉት ጉዳዮች አንዱ ተማሪዎች የሚፈልጉትን ሙያ ቢሰለጥኑ ነው፤ ነገር ግን እስካሁን ካለኝ ልምድ ብዙ ተማሪዎች የስልጠና መስክ ሲመርጡ በመተያየት እንጂ የወደፊት ህልማቸውንና የሚችሉትን የትምህርት መስክ በማየት አይደለም፤ ለምሳሌ በታሪክ ትምህርት ጎበዝ የሆነ ተማሪ ወደሂሳብ ትምህርት ነክ ሙያ ቢገባ ተመሳሳይ ውጤት ላያመጣ ይችላል፤ በተጨማሪም ተማሪዎች የምርጫቸውን ሙያ ማግኘት እንዲችሉ ጥሩ ውጤትም ማምጣት አለባቸው፤ ዩኒቨርሲቲ ገብተው በመጀመሪያው አመት 10 የሙያ መስክ ቢኖር 10ኛውን ወይም 9ኛውን ምርጫ የሚያገኙ ተማሪዎች ብዙ ናቸው፤ ሌላው ከባዱ ጉዳይ አንዳንድ ሙያ መስኮች ተማሪዎች ባይፈልጉም ለሀገራችን ስለሚያስፈልገን፣ የግድ ተማሪዎችን መመደብ አለብን፡፡ ያንን አይነቱ አመዳደብ የተማሪዎችን ፍላጎት ገናዘበ አይሆንም፡፡ ለሁሉም እኔ ግብርና ግቢ መመደቤን ሳልወድ የተቀበልኩት ነገር ነው፤ ነገር ግን ጠንክሬ ሰርቼ የተሻለ የምለውን ስራ ማግኘት ችያለሁ፤ ዞሮ ዞሮ የኑሮስኬት የጥረት ፍሬ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ የግብርና ሙያ እንዲሁም መምርነት ከሌሎች ሙያዎች እኩል ተፈላጊ እንዲሆን አሁን በስራ ላይ ያሉት ምሁራን መፍትሄ መፈለግ አለባቸው፡፡

 መጀመሪያ ዲግሪ አንደኛ አመት

ቀጥሎ የአንደኛ አመት ትምህረት ተጀመረ፤ እስካሁን የሚገርመኝ ግብርና ኮሌጅ ግቢ ውስጥ ዶርሜ ጠፍቶብኝ በብዙ ፍለጋ ያገኘሁት ቀን ነው፤ ምሳ በልቼ ወደዶርም ልመለስ ስል መንገዱ ጠፋብኝ፤ ብዙ ዞርኩ፤ ዞሬ ዞሬ ሲያቅተኝ አንድ ተማሪ ጠየቅኩ፤ ተማሪውም ብሎክ 301 ዶርም 17ትን አሳየኝ፡፡

 

አንደኛ አመት የመጀመሪያው ሴሚስተር የዩኒቨርሲቲ ቆይታዬ ብዙም የተረጋጋ ነው ማለት አይቻልም፡፡ ምክንያም የዩኒቨርሲቲ ህይወትን እጅግ ከባድ አድርጌ ነበረ የሳልኩት፡፡ ስለሆነም ብዙ ፍርሀት ነበረብኝ፤ በተለይ ለመጀመሪያው ሴሚስተር መጫረሻ ወይም መባረር የሚባለው አደገኛ ነገር ና እንዲሁም ጥሩ ውጤት ማምጣት የሚለውም ሀሳብ ስላለ፤ ሁለቱ ተደምረው በራስ መተማመኔን ከኔ አራቁት፡፡

 

የመጀመሪያ ሴሚስተር የዩኒቨርሲቲ ትምህርት ቆይታዬ አስቸጋሪ ጉዳዮች ከትምህርት ክፍለጊዜ ሰሌዳ ይጀምራል፡ ሰኞ ማለት Mተብላ ነው ፕሮግራም ላይ የምትፃፋ፤ ለምሳሌ Physics M1-3 room Audit የሚል የጊዜ ሰሌዳ ሰኞ ቀን ከ1ኛ ክፍለ ጊዜ እስከ 3ኛ ድረስ ኦዲቴሪየም የሚባል መማሪያ ክፍል ውስጥ ይሰጣል ማለት ነው፡፡ የመማሪያ ፕሮግራም አወጣጡ ስላልገባኝ ለሶስት ቀናት ያህል እዛው ግቢ ውስጥ እያለሁ ትምህርት አምልጦኛል፡፡ እኔ የትምህርት ክፍለ ጊዜ ሰሌዳ ያየሁትም ስለሆነም በጣም ማጥናት ነበረብኝ፡፡ የመጀመሪያ ሴሚስተር ውጤቴን ሁሉንም ኮርሶች ኤ በማምጣት በ4፡00 ነጥብ ጨረስኩ፡፡

 

የአንደኛውን አመት የመጀመሪያ ሴሚስተር በ4 ነጥብ ስለጨረስኩ በራስ መተማመኔ ጨመረ፡፡ ለሁለተኛ ሴምስተር ተረጋግቼ ማጥናት ጀመርኩ፡፡ በመጀመሪያው ሴሚስተር እጅግ ጎበዝ ተማሪዎች በመምሰል እኛን ስያሸብሩን የነበሩት አብዛኞቹ ያን ያህል ጠንካራ አለመሆናቸውን ተገነዘብኩ፡፡ ከመጀመሪያ አመት የዩኒቨርሲቲ ቆይታዬ የተማርኩት ነገር በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ውጤታማ ለመሆን መረጋጋትና ተማሪዎች ብዙ ያልተጣራ ወሬ በማውራት የሚያጠኑትን ተማሪዎች ስነልቦና እንደሚሰርቁ ነው፡፡ ፈተና ይከብዳል ተባለ፣ ይህ መምህር አምና ምንም ኤ አልሰጠም፣ ፈተናችን ተሰርቆ ወጣ፣ መምህራን ያዳላሉ ወዘተ የሚሉ የውሸት መረጃዎች በስፋት ይነገራሉ፤ በተለይ በፈተና ወቅት፡፡ ስለዚህ ማንኛውም የዩኒቨርሲቲ ተማሪ በመጀመሪያ ማድረግ ያለበት ነገር የተረጋጋ ምንፈስና ተፈትኖ ጥሩ ውጤት ለማምጣት በደንብ ማንበብን ነው፤ በተጨማሪም ተማሪው ራሱን ለመረጃ ቅርብ በማድረግ ከተቻለ ከሱ በፊት ያሉ ተማሪዎች የተፈተኑትን ሞዴል ፈተና ፈልጎ ራሱን ከፈተናው ጋር ማለማመድ ያስፈልጋል፡፡

 

ሌላው የዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ አመት ትዝታዬ የሀይማኖት፣ የፖለቲካና የብሄረሰብ ጉዳይ ነው፤ እኔ ዩኒቨርሲቲ እስክገባ ድረስ ስለብሄረሰብና ስለቋንቋ አስቤ የዋልኩበትን ቀን አላስታውስም፡፡ ከመጀመሪያ አመት የዶርሜ ተማሪዎች ጋር ፖለቲካ ቀመስ ሀሳቦች መለዋወጥ ጀመርን፤ እኔም የሀገራችንን ፖለቲካና ተያይዞ ያሉትን ሀሳቦች ከዶርሜ ተማሪዎች መማር ጀመርኩ፡፡ ከዛ ጊዜ ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ የማስተውለው ጉዳይ ሀገራችን ብዙ አይነት የፖለቲካና የብሄረሰብ ጥያቄዎች እንዳሉባት ነው፡፡ ቢሆንም ፖለተካውን በሰከነ ና ሚዛናዊ የሆነ አስተያየት የሚሰጥበት ኢትዮጵያዊ ውስን ነው፡፡ ምክንያቱ ከቤተሰብ ጀምሮ የአንድ ወገን ታሪክን ብቻ ከሁሉ አስበልጦ ደጋግሞ ከመስማት የሚመጣ ይመስለኛል፡፡ ነገር ግን የዪኒቨርሲቲ ወዳጆቼ የነገሩኝ እንዲሁም እኔም በተለያየ አጋጣሚዎች የማውቃቸው ብዙ መሰረታዊ የሆኑ የፖለቲካ ጥያቄዎች በሀገራችን አሉ ፡፡  ለሁሉም መልሱ ደግሞ የህግ የበላይነትና አቅም በፈቀደ መልኩ ከወገንተኝነት ነፃ የሆነ የህዝብን የልማት ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ነው፡፡ በዛሬው የሀገራችን ፖለቲካ ውስጥ ጥቂት ለህዝብ የሚሰሩ ታማኝ ዜጎች ቢኖሩም ብዙዎች ደግሞ በብሄረሰብ ወይም በአከባቢ ልዩነት ውስጥ ተደብቀው የግላቸውን አላማ እየነገዱ ይገኛሉ፡፡ ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆነው በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ውስጥ በራሳቸው የትውልድ አከባቢ እየሰሩ ያሉ ሆነው ህዝቡን በሙስና ሲበዘብዙ ብዙዎች መኖራቸው ነው፡፡ ስለሆነም የሀገራችን የልማት ጥያቄም ሆነ የፖለቲካ ልዩነቶችን በትክክል ለመረዳት ፖለቲከኞቻችን የሚነግሩንን የፖለቲካ ጥያቄዎች ብቻ ሳይሆን አብዛኞቹ በአመራር ደረጃ ያሉት አካላት በህዝብ ስም የሚነግዱትን ንግድና ሙስና ስፋት መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

 

ከፖለቲካው ውጪ ትዝ የሚለኝ የመጀመሪያ አመት የዩኒቨርሲቲ ቆይታዬ ካፌ/ምግብ/ የመመገቢያ ሰአት ከመድረሱ በፊት ቀድሞ ተሰልፎ /ሰቅሎ/ መብላትን እንደ እፍረት መረዳቴ ነው፡፡ ከሁለተኛ አመት ጀምሮ ካፌ ሰቀላ ጀምሬ እስክ ምርቃት ድረስ ካፌ ሰቃይ ሆኜ መጨረሴ ነው፡፡ በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ዘንድ ሰቃይ ማለት በዩኒቨርሲቲው ፈተናዎችን ከፍተኛ ውጤት የሚያመጣ ተማሪ ማለት ነው፡፡ ስለሆነም ካፌ መስቀል የሚለው አባባል ከሌሎች ተማሪዎች ቀድሞ መብላት ማለት ነው፡፡ አዲስ ገቢ ተማሪዎች ካፌ ቀደም ብሎ ለመብላት ያፍራሉ፤ ቢሆንም ሰቀላውን ቀስ በቀስ ይለማመዱታል፡፡ በኛ ጊዜ ሰቅሎ መብላት ቆንጆ ነበረ፤ ምክንያቱም መጀመሪያ ላይ ያለው ወጥ ዘግይቶ ከሚወጣው በጣም ይለያል፡፡ ለዚህ ደግሞ ከኔ ጋር በግብርና ኮሌጅ የካፌ ሰቀላ ባልደረቦቼ የነበሩት እነ ሚስጢር ታዬ፣ እነ ዳኒንኤል ማሞ፣ እነ እስጢፋኖስ ሽፈራው፣ እነ ፍቃዱ ቱሉ፣ እነ ሴይፉዲን ማህሙድ ፣ ዳዊት መልኬ፣ ሰማሀኝ ደሳለኝ ወዘተ በትክክል ምስክርነት ሊሰጡ ይችላሉ፡፡

 

የመጀመሪያ አመት የዩኒቨርሲቲ ህይወታችን ሌላው ትዝታ የበግ ተራ ነገር ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በግ ተራ ማለት ፍቅረኛሞች የሚገናኙበት ቦታ ማለት ነው፡፡ በግ ተራ ለመታየትም አልፎ አልፎ የዶርም ውስጥ ቀልድ መሆኑ ትዝ ይለኛል፡፡ ቢሆንም ትምህርቱም ከባድ ስለሆነ ወደተቃራኒ ፆታ ፍቅር የመሄዱ ሀሳብ ብዙውን ጊዜ ለተማሪዎች ውጤት መቀነስ መንስኤ ነው፡፡ ከበግ ተራ ቀጥሎ ተማሪዎችን የሚጎዳው የሱስ ጉዳይ ነው፡፡

የሱሱን ርእስ በሚቀጥሉት ክፍሎች በሰፊው እመለስበታለሁ፡፡ ብዙ ተማሪ ግን ሱሰኛ ሆኖ የሚቀረው ጫት መቃም ለጥናት ቆንጆ ነው የሚለውን የተሳሳተ ምክር አምኖ በመቀበል ነው፡፡ ጉብዝና በሚርቃና የሚመጣ ሳይሆን ትምህርትንና ከትምህርት ጋር ተያይዞ ያሉትን እያንዳንዱን ስራ በእቅድና በትኩረት ጠንክሮ በመስራት ነው፡፡ ማንም ተማሪ በርትቶ ከሰራ፣ ጊዜውን በአግባቡ ከተጠቀመና ከኩረጃ ራሱን ካራቀ የፈለገበት መድረስ ይችላል፡፡ ዋናው ችግር የትምህርት ጊዜን ከማባከን ይጀምራል፤ ብዙ ተማሪ በተለይም ከከተማ የሚመጡ ተማሪዎች ቀደም ብሎ ማጥናትን እንደፋራነት የሚቆጥሩት ብዙ ናቸው፡፡

 

ስለሆነም ቀደም ብለው ከማጥናት ይልው ፈተና አንድ ወይ ሁለት ሳምንት ሲቀረው ማጥናት ይጀምራሉ፡፡ ወደፈተና አከባቢ መምህራንም ኮርስ ለመጨረስ ስለሚጣደፉ ውጥረት ይበዛል፤ ይሄኔ ተማሪው ፍርሀት ይይዘውና ቁጭ ብሎ ያድራል፤ ጫት ቁጭ ብሎ ለማደር ያነቃቃል፤ ነገር ግን አእምሮአችን በአንድ ለሊት ሁሉን ነገር ተቀበል ብለን ስላስገደድነው አይቀበልም፤ ተማሪው መርቅኖ ሲያነብ ያድራል፤ ጠዋት ራስ ምታት ነው፤ ክላስ አይገባም፤ ይጫጫነዋል፤ ክፍል ቢመጣም ያዛጋል፤ ይነጫነጫል፤ እንቅልፍ እንቅልፍ ይለዋል፤ አሁንም ጫት ቤት ይሄዳል… በአጭሩ አይኑን ለመክፈትና ለመረጋጋት ጫት የግድ እየሆነ ይሄዳል… ገንዘብ ይጨርሳል… የሌሎችን ተማሪዎች ብድር መጠየቅ ይጀምራል… ለቤተሰቡም የውሸት መረጃ እየሰጠ ገንዘብ ያስልካል፣ ሳይታመም አመመኝ፣ ስልኩ ሳይሰረቅ ስልኬ ተሰረቀ፣ ሱሪውንም ጭምር ይሸጣል… ወደስርቆት ይገባል.. ውጤት ዝቅ ይላል…. በሱስ ተጠመደ ማለት ነው፡፡ ይህ ከባድ ሞኝነት ነው…. አንድ አራዳ ነኝ ብሎ የሚያምን ወይም ዩኒቨርሲቲ ለመግባት የበቃ ተማሪ በዚህ አይነት አካሄድ ህይወቱን አደጋ ላይ ሲጥልና ሰብአዊ ክብሩን ስያዋርድ ማየት እጅግ ያሳዝናል፡፡ ስለሆነም ወጣቶች ባካችሁ ባካችሁ ራሳችሁን ከሱስ ጠብቁ፡፡

 

ሁለተኛ አመት

 

የአንደኛ አመት የዩኒቨርሲቲ ትምህርታችን ከተጠናቀቀ በኋላ ወደሁለተኛ አመት ስንገባ የዲፓርትመንት መረጣ ማድረግ ነበረብን፡፡ ከ12ኛ ክፍል ዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና በኋላ የነበረው የምርጫ ሀሳብ አይነት ሀሳብ አሁንም ተጀመረ፡፡

 

የትኛውን ልምረጥ የሚለው ጥያቄ አሁንም ተደገመ

 

መምረጥ ከምንችላቸው የስልጠና ዘርፎች ውስጥ የጤና መኮንን፣ ግብርና ምህንድስና፣ የተክሎች ሳይንስ፣ የእንስሳት ሳይንስ፣ ገጠር ልማትና ቤተሰብ ሳይንስ ነበሩ፡፡ ጤና መኮንን የመሆኑ ፍላጎት አልነበረኝም ምክንያቱም ህክምና ስለምፈራ፣ ግብርና ምህንድስና ደግሞ ተምረው ሲመረቁ የትራክተር ሾፌር ነው የሚሆኑት የሚል ትክክል ያለሆነ መረጃ ሰምተን አልፈለግነውም፣ የእንሰሳትና የተክሎች ሳይንስ ደግሞ ሙሉ በሙሉ ግብርና ስለሆኑ አልፈለግኩዋቸውም፣ የገጠር ልማትና ቤተሰብ ሳይንስ አዲስና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ውስጥ በጥሩ ደሞዝ ለመቀጠር ያስችላል ስለተባለ ገጠር ልማቱን መረጥኩ፡፡

 

የግብርና ሙያ ለሀገራችን እጅግ ብዙ ስራ ልንሰራበት የምንችለሁ ሙያ ሆኖ ሳለ፣ የሀገራችንን ወጣቶች የትምህርት ህልም ግን ሊሆን አለመቻሉ ትልቅ ጥያቄ ነው፡፡ እኔ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ግብርና ኮሌጅ ስገባ፣ በምርጫዬ ግብርና ገባሁ የሚል ተማሪ አላጋጠመኝም፡፡ ቀስበቀስ ስናየው ግን ግብርና ሙያ ለምህንድስና ድረስ የሚደርስ ብዙ ያልተመለሱ ጥያቄዎች ያሉበት ነው፡፡ በእርግጥ የሀገራችንን የግብርና ልማት ደረጃ ስናይ ብዙም ለተማሪዎች የሚያጓጓ ላይሆን ይችላል፡፡ እኔ በበኩል ዛሬም እድሉን ባገኝና የግብርና ምህንድስና ብማር ወይም በግብርናው መስክ ለሀገራችን ብዙ ባበረክት እጅግ ደስ ይለኛል፡፡ ምክንቱም ሀገራችን ካለባት ከባዱ ችግር የመጀመሪያው የገጠሩ ማህበረሰብ በድህነት ውስጥ መኖሩ ነው፡፡ ገበሬዎቻችን በዝናብ እጥረት ምርታቸው ሲበላሽ ለእርዳታ እህል ሰልፍ ሲመጡ እጅግ ያሳምማል፤ እኛ የተማርነው ዜጎች ይህንን አሳፋሪ ታሪካችንን በቴክኖሎጂና በስልጣኔ መተካትና ህዝባችን ራሱን እንዲችል ማድረግ አለብን፡፡

 

የገጠር ልማቱን ዲፓርትመንት መርጠን እንደገባን በግቢው አሉ የሚባሉ ቆነጃጅትም እኛ ጋር መመደባቸውን አወቅን፤ ፈተናው ብዙ ነው ማለት ነው፡፡

 

የገጠር ልማትና ቤተሰብ ሳይንስ ዲፓርትመንት መርጠን እንደገባን እኔና አብረውኝ የነበሩት ብዙዎቹ ወንዶች በአይን ፍቅር መሰቃየት ጀመርን፤ ሁለተኛ አመት ስንደርስ የመረጋጋት ስሜትም ስለነበረ በግ ተራም እያማረን መጣ፡፡ በግ ተራ ማለት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ከተቃራኒ ፆታ ወዳጆቻቸው ጋር ቁጭ ብለው ስለፍቅር የሚወያዩበት፣ የፍቅር ሜዳ እንደማለት ነው፡፡ እኛ ጋር የነበሩትን ቆነጃጅት ሌላ ትምህርት ክፍል ያሉ ወንዶችም ይፈልጉዋቸው እንደነበረ በተለያዩ አጋጣሚዎች ይነገረን ነበረ፤ የኛ ዲፓርትመንት ሴት ተማሪዎች በሌሎቹም የኮሌጁ ተማሪዎች ዘንድ የመነጋገሪያ ርእስ መሆናቸውንም መስማት ጀመርን፡፡

 

እኛንም፤ ፈተና ውስጥ እንደገባንም በመረዳት ብርታቱን ይስጣችሁ ብለውም ፀሎት አድርገውልናል፡፡  ለኔ ሁለት ዋና ዋና አሳሳቢ ነገሮች ነበሩ ማለት ነው፤ አንደኛ ጥሩ ውጤት የማምጣትና በርትቶ መማር ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በቆነጃጅቶቹ ሰበብ የሚፈጠረውን የውጤት መቀነስና እጫራለሁ የሚለው ስጋት በማሸነፍ በቆንጆ ውጤት መመረቅ፡፡

 

ቢሆንም በሁለተኛ አመት የዩኒቨርሲቲ ቆይታዬ ሙሉ ትኩረቴን ትምህርቴ ላይ ማድረግ ሲገባኝ ወደበግተራና ወደቆነጃጅቶቹ ሴት ተማሪዎች በማድረጌ ከአራቱ አመት ዝቅተኛውን ውጤት አመጣሁ፡፡ ዩኒቨርሲቲ ስገባ አንዱ አላማዬ የነበረው ከፍተኛ ውጤት አምጥቼ እዛው ዩኒቨርሲቲ ውስጥ መቀጠርና ውጪ ሀገር ሄጄ መማር ነበረ፡፡ ነገር ግን በሁለተኛ አመት የዩኒቨርሲቲ ቆይታዬ ሀሳቤን በሙሉ ወደትምህርት ስላላደረግኩ ውጤቴ በጣም ዝቅ ብሎ ነበረ፡፡ በአመቱ መጨረሻ ያመጣሁትን ውጤት ሳስብ እጅግ ተፀፀትኩኝ፤ አላማዬ መማር ሆኖ ሳለ ቆንጆ ተማሪ ስላየሁ ያንን ያህል መጃጃሌ ቆጠቆጠኝ፤ ለሶስተኛ አመት ሙሉ ሀሳቤን ወደትምህርት ብቻ ለማድረግ ወሰንኩኝ፡፡ ሁለተኛ አመት ተማሪዎች ሆነን ብዙዎቹ የዶርሜ ልጆችም ወሬያቸው ሁሉ ስለሴቶቹ ቁንጅና ብቻ ነበረ፤ በመሆኑም ዲደአ ተማሪ በነበርኩበት ወቅት የጀመርኩትን ፍቅር አጠናክሬ ቀጠልኩኝ፡፡

 

ከሁለተኛ አመቱ የዩኒቨርሲቲ ቆይታዬ የተማርኩት ነገር ለማንኛውም የዩኒቨርሲቲ ተማሪ የተቃራኒ ፆታ ፍቅር/አባዜ/ ለውጤት መቀነስ አንዱ ምክንያት እንደሚሆን ነው፤ ስለሆነም ተማሪዎች አላማቸውን ማስተካከል ይገባቸዋል፡፡ ምክንያቱም ጊዜያዊ የሆነው የዩኒቨርሲቲ ፍቅር ሲያልፍ ፀፀት ስለሚከተል መጀመሪያውኑ ሙሉ ትኩረትን ትምህርት ላይ ማድረግ ያስለፍጋል፡፡

 

በጣም የሚገርመው ጉዳይ፣ በዩኒቨርሲቲ ቆይታ ወቅት ከተቃራኒ ፆታ ጋር ፍቅር ውስጥ የሚገቡትና በግ ተራ የሚያዘወትሩት ተማሪዎች በትምህርታቸው ያን ያህል ጎበዝ የሚባሉ አለመሆናቸውን ነው፡፡ አንዳንዶች በግ ተራ መታየትን እንደአራዳነትም ይቆጥሩታል፤ አሁን አሁን ደግሞ በየመንገዱ መሳሳምም የዘመናዊነት መገለጫ አይነት ነገር እያየን ነው፤ ዘመናዊነት በየመንገዱ ስለተሳሳምን አይመስለኝም፤ ወጣት የሚዘምነው በአስተሳሰቡና በድርጊቱ የሰለጠነ ሲሆን ነው፤ በሱስ ራሱን እያጠፋ፣ ወይም የትምህርት ጊዜን ውጪ በዙረት ስላሳለፈ ስልጣኔ የሚመስለው ተማሪ በጊዜ ራሱን መፈተሽ አለበት፡፡ የሰለጠኑ በሚባሉትም ሀገራት እንዳየነው ከሆነ የስራ ሰአት ስራ ነው የመዝናናት ስአት መዝናናት ነው፤ የኛ ሀገሩ ግን ስልጣኔውን በተጣመመ መንለኩ እየተገበርነው ነው፡፡ ሲጋራ ስላጨሰ የሰለጠነ የሚመስለውም ብዙ ነው፤ ፈረንጆች ሲጋራ ያጨሱት ግን ከጭንቀት ለመደበቅ አስበው ሱስ ሆነባቸው እንጂ ሲጋራ ምንም የሚጠቅም ነገር ስለተገኘበት አይደለም፡፡

 

ለሁሉም በዩኒቨርሲቲ ቆይታችን ወቅት ስለእውነተኛና ዘላቂ ፍቅር ማሰብ የለብንም ማለቴ አይደለም፡፡ ነገር ግን የዩኒቨርሲቲ ቆይታ ዋናው አላማ ጠንክሮ በመማር ለወደፊት ህይወት መሰረት መጣል ስለሆነ፣ ቅድሚያ መሰጣት የሚገባው ለትምህርት ነው፤ ፍቅር ህይወት ከምርቃት በኋላ በሰፊው ሊደረስበት የሚችል ሲሆን የዩኒቨርሲቲ ትምህርት ግን አንዴ ካመለጠ ተመልሶ ስለማይገኝ ነው፡፡

 

ስለሆነም ለሁሉም የዪኒቨርሲቲ ተማሪዎች ከተቻለ የዩኒቨርሲቲ ቆይታን ቅድሚያውን ለትምህርት በመስጠት በጥሩ ውጤት መመረቅ ለሁሉ ተማሪዎች የሚመከር ነው፡፡ ካልሆነ ደግሞ በተረጋጋ መንፈስ ዘላቂ ህይወትን በማሰብ የት/ት ቤት ፍቅራችንን ወይም የዩኒቨርሲቲ ወዳጅነታችንን ወደትዳር መቀየር ቆንጆ ነው፡፡ ታዲያ ጭልጥ ያለ ፍቅር ውስጥ ተገብቶ ትምህርት ውጤት ላይ ተፅእኖ እንዳይኖር ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

ሶስተኛ/አራተኝ  አመት

ለእኔ ሶስተኛ አመት የዩኒቨርሲቲ ቆይታዬ በሁለተኛ አመት የፈጠርኩትን ስህተት ለማስተካከል ራሴን በራሴ እርምጃ የወሰድኩበት ጊዜ ነበረ፡፡ የሶስተኛ አመት ስማር አይኔን ሙሉ በሙሉ ወደትምህርት መልሼ ነበረ፡፡ ስለሆነም ውጤቴ በጣም ቆንጆ ሆነ፤ ወደነበረውም የውጤት ደረጃዬም ተመለስኩ፡፡ የአራተኛው አመት የዩኒቨርሲቲ ቆይታዬ ደግሞ ከክፍላችን ተማሪዎች ጋር እጅግ ጥሩ የሚባል መቀራረብ የነበረን ጊዜ ነበረ፡፡ በፊት ተራርቀን የነበርነው ተማሪዎች ተቀራረብን፤ ሁሉን ሀሳብ በመቀራረብ መነጋር ተጀመረ፤ ከወንዶች ተማሪዎቸም ማን በማን ፍቅር ሰለባ እንደሆነ መወያየት ተጀመረ፤ ሚስጥሮቻችን ለሴቶቹ ተነገሩ፡፡ በተለይ ወዳጃችን ደረጄ ምናሴ የሚያነብልን የግጥም ጽሁፎች እጅግ አሪፍ ነበሩ፤ ደሬ ባክህ ደራሲ ሁን ብዬም ለምኜዋለሁ፤ አሁንም በድጋሜ እጠይቀዋለሁ፤ ደሬ ባክህ ግጥሞችህን አሳትምልን፤ ታሪካችንንም በግጥም አስነብበን፡፡

 

በ1997 ዓ.ም. የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የገጠር ልማትና ቤተሰብ ሳይንስ/ገልቤሳ/ ተማሪዎች በግብርና ኮሌጅ ታዋቂ መቀራረብና ታታሪነት የነበረን ነን፡፡ ለታታሪነታችን ማሳያ፣ የመጨረሻ አመት ትምህርታዊ ጉብኝታችንን የተሳካ ለማድረግ ኮሚቴ አዋቅረን፣ የትምህርት ክፍሉን በማገዝ በኮሌጃችን የመጀመሪያ የሆነውን ረጅሙን ጉዞ አደረግን/ ከሀዋሳ እስከ ጂንካ፣ ከጂንካ እስከ አውራምባ፡፡

 

በዛም አጋጣሚ ስለሀገራችን በጣም ብዙ ለማወቅ ቻልን፤ እርስ በእርስም የማይረሳ ትዝታ ኖረን፡፡ ለምሳሌ ኮንሶ አድረን ከበላነው ምግብ  የተነሳ ብዞዎቹ የክፍላችን ተማሪዎች ተቅማጥ አህመም አሰቃይቶናል፡፡ መኪና ውሰጥ የተቅማጥ ማከሚያ ኦአርኤስ እየጠጣን ነበር የምንጓዘው፡፡ በዛው የጉዞ ወቅት ጂንካ ከተማ ያየነው ከሀመሮች ጋር እንደ አሽከርነት የሚኖር አሜሪካዊ ዜጋ ትዝ ይለኛል፡፡ እንዲሁም ዎይጦ በረሃው ላይ ፍየል ገዝተን ጠብሰን በህብረት የበላነውና  ከአከባቢው ሰዎች ጋር የጨፈርነው የማይረሳ ትዝታችን ነው፡፡

አውራምባና ዙምራ

ከኮንሶ መልስ ደግሞ ወደባህርዳር ተጉዘን፣ የአባይ በረሀን ተሻግረን አውራምባ ሄደን ዙምራን አግኝተነዋል፡፡ ዙምራም እጅግ ታላቅ የህይወት ተሞክሮውን አካፈለን፤ እስከዛሬም የማይረሳ ብዙ ትምህርት አስተማረን፡፡

 

ከአውራምባና ከዙምራ የህይወት ልምድ፣ ማህበረሰብ በህብረት ሲሰራ ምን ያህል ልዩነት ማምጣት እንደሚቻልና አንድ ሰው ብቻውን ምን ያህል ልዩነት መፍጠር እንደሚች፣ በቆራጥነት ከተሰራ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል በተግባር አይተን ተመለስን፡፡ የአውራምባ ማህበረሰብ ለሌሎች የገጠሩ የሀገራችን ህዝብ ምሳሌ የሚሆኑ ብዙ ነገሮች አሉዋቸው፤ ለምሳሌ ለአረጋዊያን የሚደረገው እንክብካቤ፣ ለልጆቻቸው ትምህርትቤት የተሰራው ቤተመፅሀፍት፣ በህብረት ሰርተው በህብረት የሚጠቀሙት የግብርናና የእደጥበብ ስራቸው፣ የማህበረሰባቸውን ፀጥታ የሚጠብቁበት ሁኔታ ወዘተ እጅግ ያስደስታሉ፡፡

 

በአውራምባ ጉብኝታችን ወቅት ዙምራ ያልጠበቅነውንም ሀሳብ አቀረበ፤ አንደኛው ጊዜያቸውን ስላባከንን የማካካሻ የሚሆን ገንዘብ አሰባስበን ልንሰጠው ስንል አልቀበልም አለ፡፡

 

ሁሌም የማልረሳው አባባሉን ነው፡

 

የተቀባይ እጅ ሁሌም ከታች ነው፤ እኛ ሰርተን እንተዳደራለን፤ የማንም እርዳታ አንፈልግም፤

ይልቅ የኛን የኑሮ ዘይቤ ለሌሎች ንገሩ፤ ሌሎችም እንደኛ በህብረት እንዲኖሩ አስተምሩ፤ ብሎ የሰበሰብነውን ገንዘባችንን አልቀበልም አለ፡፡

 

በሌላ አጋጣሚ ፎቶ ከዙምራ ጋር ልንነሳ ስንዘጋጅ፣ ካሜራውን ከአንዱ ተማሪ ወዳጃችን ተቀበለና ፈረንጅ ካሜራ ስለሰራ በካሜራው ፎቶ መነሳት ብቻ ሳይሆን ይህ ካሜራ እንዴት ተሰራ ብላችሁ ሌላ ካሜራ መስራት ነው እንጂ ፎቶ መነሳት ብቻውን ከምሁራን አይጠበቅም ብሎ አሳፈረን፡፡ ሁላችንም የዙምራን ታላቅነትና አዋቂነት አድንቀን ጉዞ ወደአዋሳ ተጀመረ፡፡

ገልቤሳና ምርቃት

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የገጠር ልማትና ቤተሰብ ሳይንስ/ገልቤሳ/ ተማሪዎች የነበርነው ሌሎችም ብዙ ትዝታዎች ነበሩን፡፡ ለምሳሌ ከጥናት ጋር በተያያዘ ብረት ለበስ እና ስፖር ፎርመርስ በመባል የታወቁ ቀን ከለሊት ያለ ድካም የማጥናት ጉልበት ያላቸው ተማሪዎች ነበሩ፡፡ እኔ የነበርኩበት ዶርም በዋናነት ከባድ አንባቢ ከሚባሉት የሚመደብ ሲሆን ብዙ ጊዜ ዶርማችን ዝግ ሆኖ ድምጽም ስለማይሰማበት ቤርሙዳ የሚባል ቅፅል ስም ተሰጥቶት ነበረ፡፡ በተጨማሪም በሪሁ የሚባለው የኛ ተማሪ ከሁላችንም አርቆ አሳቢና ፈላስፋም ነበረ፡፡ ሁሌም የማይረሳኝ አንድ ካርቶኒ ሙሉ መፅሀፍ ኖሮት ገንዘብ ሲያገኝ ሌላ መፅሀፍ መግዛቱ ነው፡፡

 

 

 

 

 

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ጊዜዬን ጨርሼ እንደተመረቅኩ ዋናው አሳሳቢ ነገር የስራ እድል ጉዳይ ነበረ፡፡ የተማርነው ትምህርት መስክ /የገጠር ልማትና ቤተሰብ ሳይንስ/ በወቅቱ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ብቻ የሚሰጥ ስለነበረ ብዙ ቀጣሪ ድርጅቶች አያውቁትም ነበረ፡፡ ነገር ግን ለሀገራችን የገጠር ህዝብ ብዙ አስፈላጊ ኮርሶችን ስለተማርን በተለይ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ውስጥ ስራ ማግኘት ቀላል ነበረ፡፡ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ካለው ቤሰብ ስለወጣሁ ቶሎ ስራ ማግኘትና ራሴን መቻል ታላቅ ጉጉቴ ነበረ፤ ዩኒቨርሲቲ ሆኜ ከወላጆቼ በተጨማሪ ዘመዶችና ወዳጆቼ ለምሳሌ ደምመላሽ ከበደ፣ ተረፈ ጆሮና ሁንዱማ ሰቦቃ ያደረጉልኝ የገንዘብ ድጋፍ መቼውንም አይረሳኝም፡፡ በተለይ ሁንዱማ ሰቦቃ የመጀመሪያ አመት ተማሪ ሆነን አንድ ዶርም የኖርን ሲሆን በጣም እንቀራረብ ነበረ፡፡ እሱ የዲፕሎማ ፕሮግራም ተማሪ ስለነበረ በሁለተኛው አመት ተመርቆ ወጣ፡፡ እንደተመረቀም ቶሎ ስራ አገኘ፡፡ ስራ ሲዝ፣ ከወር ደሞዙ ቀንሶ ገንዘብም ይልክልኝ ነበረ፡፡ ሁንዱማ ዘመዴ አይደለም፣ ዩኒቨርሲቲ ከመግባታችን በፊትም አንተዋወቅም ነበረ፤ ነገር ግን የሁንዱማ ድርጊት የሚያሳየን የዩኒቨርሲቲ ህይወት ደስ የሚል የወንድምነት ያህል ወዳጅነት የሚፈጠርበት አጋጣሚም መሆኑን ነው፡፡ ስለሆነም ወጣቶች በትምህርትቤት ህይወታቸው መተሳሰብንና መረዳዳትን ልምዳቸው እንዲያደርጉ እመክራለሁ፡፡

 

 

የሀዋሳ ዪኒቨርስቲ ግብርና ኮሌጅ ትዝታዎቼ (በታሪኩ ዋቁማ)

በገጠር ልማትና ቤተሰብ ሳይንስ (ገልቤሳ) ሙያ አብሮኝ ተማሪ የነበረው ወጃጄ ታሪኩ ቀጥሎ ያለውን ሀሳብ እንደማስታወሻ ልኮልኝ ነበረ፤

“ገልቤሳ ከመምረጤ በፊት የጤና መኮንን ለመምረጥ ሞክሬ ነበር ፡፡ ቢሆንም በእጣ ሞክሬ ስላልተሳካልኝ ወደ ገልቤሳ ገባሁ፡፡የሚገርመው እኛ ሀዋሳ ዪኒቨርስቲ ስንመደብ ለተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪ ከግብርና ቀመስ ትምህርቶችና እና ከአፕላይድ ሳይንስ ትምህርቶች ውጪ ብዙም አማራጭ አልነበረም፡፡ በጤና ሳይንስ ዲላ ካምፓስ የነበሩት የጤና መኮንንነትና የአካባቢ ሳይንስ የሚባሉ ትምህርቶች ነበሩ፡፡ እንደ እኔ አይነቱ ህክምና መማር ይፈልግ ለነበረ ሰው ፍላጎቱ ህልም ሆኖ ቀርቷል ማለት ነው፡፡  በወቅቱ ገልቤሳ ካሉት የግብርና ኮሌጅ ዲፓርትመንቶች ተፈላጊው ነበር፡፡ ሰለሆነም በውጤት የተሻሉ ተማሪዎች ናቸው የተመደቡት ሲባል ሰምቻለሁ፡፡ ሀዋሳ ከመሄዳችን በፊት የተወሰንን ተማሪዎች አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ለአንድ ሴሚስተር ቆይተን ነበር፡፡ አዲስ አበባ የቆየነው ሀዋሳ ዪኒቨርስቲ ቦታ እስኪያዘጋጅልን ድረስ ተብሎ ነው፡፡ እኔ የነበርኩት አራት ኪሎ ካምፓስ ነበር፡፡አራት ኪሎ ግቢ የነበረው ነገር ምንም ለተማሪ ሳቢ ያልነበረ መምህራኑ በጣም እንዲፈሩ የሚፈልጉ ተማሪ በስርአት የማያናግሩ ነበሩ፡፡

ላይብረሪውም ቢሆን መጽሀፍ እንደልብ የማይገኝበት ወረፋው የበዛ ነበር፡፡ በአጠቃላይ የግቢው ሆኔታ ከመማሪያነት ይልቅ ለእስር ቤት የቀረበ ነበር፡፡ ስለሆነም የብዙዎቻችን ውጤት ጥሩ አልነበረም፡፡ ወደሀዋሳ ግብርና ኮሌጅ ስንመለስ ግን በጣም ዘና ያለ የመማሪያ አካባቢ ነበር የጠበቀን፡፡ መምህራኑ ለተማሪ ቅርብ ነበሩ፣ ላይብረሪው እንደ አራት ኪሎው ወረፋና የመጽሀፍ እጥረት አልነበረውም፡፡ ከእኛ በፊት የነበሩት ተማሪዎችም ዘና ብለው የሚኖሩ ነበሩ፡፡ የመጀመሪያ ሴሚስተር ውጤታቸውም በአብዛኛው ጥሩ ነበር፡፡ አዲስ አበባ የነበርነው ተማሪዎች በውጤት ተጎድተን ስለነበር ከባድ ጥናት የጀመርነው ወዲያው ነበር፡፡ ግብርና ኮሌጅ የቆዩት ተማሪዎች በዚህ ሁኔታ ትንሽ ግር ብሏቸው ነበር፡፡ ይሄ ከባድ ጥናት ውጤታችንን እንድናሻሽል ረድቶናል፡፡ ገልቤሳ የተማርናቸው ትምህርቶች ቡፌ እንደማንሳት ነበሩ፡፡ ከጤና፣ከግብርና፣ከማህበራዊ ሳይንስ የተውጣጡ ሆነው በየትኛውም ዘርፍ ግን ጠለቅ ያለ ክህሎት ያልጨበጥንባቸው ነበሩ፡፡ ቢሆንም ግን በዲፓርትምንቱ የነበሩ መምህራን ጥሩ ስለነበሩ እና ለዲፓርትምንቱም የመጀመሪያ የዲግሪ ተማሪዎች ስለነበርን በጣም ጥሩ ጊዜ ነበረን፡፡

በርካታ የመስክ ጉብኝቶችም ነበሩን፡- በደቡብ እስከ ኮንሶ፣ በሰሜን እሰከ አውራምባ ሄደን ነበር፡፡ የአቶ ዙምራ ፍልስፍና የስነ ጾታ ትምህርት በተግባር እንዲገባን አድርጎን ነበር፡፡ የዲፓርትመንቱ ተማሪዎች በጣም እንግባባና እንዋደድ ነበር፡፡ የተለያዩ ቅጽል ስሞችም ነበሩን፡፡ እኔ ለምሳሌ ዘ ፋይቭ ከቤስ ከሚባሉት ተማሪዎች ውስጥ ነበርኩ፡፡ ይህ ስም የተሰጠኝ ነገሮችን በመርህ ለመምራት ከማደርገው ጥረት ይመስለኛል፡፡የበግ ተራ ልምድ አልነበረኝም ፡፡ የተቃራኒ ጾታ ቅርርብ ከትምህርቴ የሚያደናቅፈኝ ስለሚመስለኝ  በጣም ነበር የምሸሸው፡፡ በስህተት ሴቶች ዶርም አካባቢ ከታየው ጓደኞቼ ያበሽቁኝ ነበር፡፡ በዚህ አጋጣሚ ግን ይሄ አካሔዴ ባለማወቅ የተደረገ እና ጠቃሚ እንዳልነበረ ዘግይቶ ገብቶኛል፡፡ ሁሉም ነገር በጊዜው ሚዛናዊ በሆነ ሁኔታ ቢደረግ ጥሩ ነው ባይ ነኝ፡፡

በግቢ ቆይታዬ ላይ በጣም ጠቃሚ አስተዋጽኦ ከነበራቸው ነገሮች አንዱ የግቢ ጉባኤ (የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ተሰባስበው የተለያዩ መንፈሳዊ ትምህርቶችንና ተግባራትን የሚከውኑበት ጉባኤ) ነበር፡፡ ይሄ ተሳትፎ ወጨጌ የሚያስብል ቢሆንም ፈሪሃ እግዚአብሔር እንዲኖርና የስነምግባር ሰው ለመሆን በጣም ጠቃሚ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ ለተሳካ የትምህርት ሕይወት እና ከሱሰኝነት ለመራቅም ትልቅ ሚና አለው፡፡ ምናልባት ይሄ መንፈሳዊ ተሳትፎ አሁን በግቢዎች ውስጥ እየታየ ላለው ስር የሰደደ ዘረኝነትን ማከሚያ ሊሆን ስለሚችል አንዱ የሌላውን ሃይማኖት በማክበር ሁሉም የሃይማኖቱን መሰረታዊ መርሆች ቢያውቅና ቢኖርበት መልካም ነው እላለሁ፡፡

በፍቄ መፅሀፍ ላይ ስለፍቄ አለመናገር ተገቢ አይደለም፡፡ ፍቄ በጣም ተጫዋች፣ ተግባቢና ጎበዝ ጓደኛችን ነበር፡፡ የሆነ ሴሚስተር ላይ ካጋጠመው የውጤት መዋዠቅ በስተቀር የዲፓርትመንታችን ባለከፍተኛ ውጤት ተማሪ ነበር፡፡ ነገሮችን ቀለል አድርጎ የሚያይ ቢሆንም ጥናት ላይ ግን ቀልድ አያውቅም ነበር፡፡ ካለው አቅም አንጻር እዚህ ደርሶ በማየቴ እጅግ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡ ወደፊትም ለሀገሩ በጣም ብዙ አስተዋጽኦ ያደርጋል ብዬ አምናለሁ፡፡ ፈጣሪ እድሜና ጤና ይስጠው፡፡…” ወዳጄ ታሬ አመሰግናለሁ፡፡ ሀሳብህን ቃል በቃል ነው የጠቀስኩት፤ በዛ ብታደርገው ቆንጆ ነበረ፡፡

ከምርቃት በኋላ

ከምርቃት በኋላ ነገሮች እንደተማሪነቱ የሚመቹና በደስታ የተሞሉ አልነበሩም፡፡ ምክንያቶቹም፣ ብዙዎቻችን እንደተመረቅን ቶሎ ስራ የምናገኝ መስሎን ነበረ፤ እኛ የተመረቅነው ሀምሌ 7 ሆኖ እኔ የመጀመሪያ ደሞዜን የተቀበልኩት በጥቅምት ወር ነበረ፤ ተመርቄ ከ4 ወር በኋላ፡፡ ስራ አጥቼ ብዙ ቆየሁ ማለት ባይቻልም ስራ ያገኘሁበት ሁኔታ እልህ አስጨራሽ ነበረ፡፡

 

ለማኝኛውም የዩኒቨርሲቲ ተመራቂ ወጣት እጅግ ፈታኝ ከሚሆኑት ጊዜያት አንዱ ከምርቃት ጊዜ ጀምሮ ስራ እስኪገኝ ድረስ ያሉት ቀናት ወይም ወራት ናቸው፡፡

 

በአሁኑ ጊዜ ከዩኒቨርሲቲ የሚመረቀው የተማሪ ብዙ ነው፡፡ ብዙ መሆኑ ለሀገራችን እድገትና ለቀጣሪ ድርጅቶች ቆንጆ ነው፡፡ ምንክቱም በሀገራችን የተማረ የሰው ሀይል ብዛት ከህዝቡ ቁጥር ጋር ሲነፃፀር በቂ አይደለም፡፡ በተጨማሪም ብዙ ወጣት ዩኒቨርሲቲ ገብቶ ተምሮ ሲመረቅ በቀለም ትምህር ብቻ ሳይሆን በአመለካከትና በማህበራዊ ህይወትም የተሻለ ሆኖ ይመረቃል፡፡ ስለዚህ ወጣቱ ትውልድ ጊዜው የውድድር መሆኑን በመገንዘብ የበለጠ በማንበብና ጊዜውን ለትምህርት በመስጠት በጥሩ ውጤት መመረቅ መቻል አለበት፡፡

 

እኔ ተመርቄ ከአንድ ወር በኋላ የትምህርት ክፍላችን የስራ ማስታወቂያ አወጣ፡፡ ሀዋሳ የነበሩ ወዳጆቼ አስመዘገቡኝ፡፡ የሚገርመው ለቃለመጠይቅ ስንጠራ ወላጆቼ ደግሞ የምረቃ በኣል አዘጋጅተውልኝ ነበር፡፡ ቅድሚያ ለተማርኩለት ስራ መስጠት ስለነበረብኝ ድግሱን ጥዬ ወደ ሀዋሳ ለቃለ መጠይቅ መምጣት ነበረብኝ፡፡

 

 

 

 

በዚህ አጋጣሚ ማስታወስ የምፈልገው ተማሪ ከዩኒቨርሲቲ ሲመረቅ ወላጆች ለልጆቻቸው ደስታ ሲባል የምርቃት ድግስ ለመደገስ ብዙ ይደክማሉ፤ ከመጠን ያለፈው ድካምና ወጪ ግን አስፈላጊ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም አንድ ተማሪ ከዩኒቨርሲቲ ተመረቀ ማለት ወዲያውኑ ራሱን ቻለ ማለት አይደለም፤ ይልቁንስ ለድግስ የሚወጣው ወጪ ለተማሪው ስራ መፈለጊያና ከተቻለም የራሱን ስራ ለመፍጠሪያ ድጋፍ ቢውል ይሻላል፡፡

 

እኔ የወላጆቼን የምርቃት ድግስ ጥዬ ወደ ሀዋሳ ለስራ ቃለመጠይቅ ስመጣ ብዙ ገንዘብ አልነበረኝም፤ ሀዋሳ እንደደረስን ለአርብ የተባለው የቃለ-መጠይቅ ፈተናም ለሰኞ ተላለፈ ተባለ፡፡ ለሆቴል አልጋ ለመክፈል የሚበቃ ገንዘብ ስለሌለኝ ወዳጄ ተስፋዬ ሽፈራው/ ተስፋዬም ዩኒቨርሲቲውስጥ የተዋወቅኩት ነገር ግን ጥሩ ወንድምና ባለውለታዬ የነበረ ነው/ ጊዜያዊ መጠለያ ሰጠኝ፡፡ ቅዳሜና እሁድ እሱ ጋር አሳልፌ ፈተናውን ተፈትኜ ወደሀገሬ ወደሴሩ ተመለስኩ፡፡… የቃል ፈተናዎቹ ጥያቄዎች የነበሩት አንደኛው ራስህን አስተዋቀውቅ፤ ሁለተኛ ለምን ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ለመቀጠር ፈለግክ፤ ሶስተኛ አንድ ትምህርት መርጠህ አስተምረና፤ አራተኛ አንድ መምህር ማሟላት አለበት ብለህ የምታስበው ነገሮች  ምን ምን ናቸው የሚሉ ነበሩ፡፡ ከነኚህ ጥያቄዎች ከበድ የሚለው አንድ ትምህርት መርጠህ አስተምረን የሚለው ነው፡፡ ምክንያቱም በፈተና ወቅት ፈታኞቹን ቆሞ ለማስተማር መሞከር እጅግ ስለሚያስፈራ፡፡ እዛው የቃለመጠይቅ ፈተና ላይ ከፈታኞቹ አንዱ መምህር ደክሞት ነው መሰለኝ እያንቀላፋም ነበረ፤ ሰውየው ማንቀላፋቱን ሳይ ሳቄ እንዳይመጣ ወደሱ አላይም ነበረ፡፡ ይመስለኛል ለመታዘብም ነው የመጣው እንጂ ጠያቂም አልነበረም… እንደምንም ጨርሼ ከፈተና ክፍሉ ስወጣ፣ እኔ በጭንቀት ተወጥሬ ፈታኙ ሰው  ማንቀላፋቱን ሳስብ አይ የሰው ልጅ ነገር …

 

ወደሴሩ ተመልሼ ከሶስት ሳምንት በኋላ፣ እኔና ወዳጄ ጌታሁን ፈተናውን ማለፋችን ተነገረን፤ ስለሆነም ወደሀዋሳ መጥተን የቅጥር ፕሮሰስ ጀመርን፤ መጥተን የሜዲካልና የፖሊስ መረጃ ለሰው ሀብት አስገባን፤ ቀጥሎም የመጨረሻው የቅጥራችን ደብዳቤ እስኪሰጠን ከሶስት ሳምንት በላይ ጠበቅን፤ ይሁን እንጂ መልሱን ቶሎ የሚነግረን አካል ማግኘት አልቻልንም፡፡ ሰው ሀብት ስንጠይቅ ወደዩኒቨርሲቲው ስለተላከ ጠብቁ ይሉን ነበረ፤ በመጨረሻ ግን የናንተ ቅጥር ልክ አይደለም ብለው ቅስማችንን ሰበሩት፤ ለኔና ለጌታሁን እንዲሁም ነወላጆቻችን ታላቅ ሀዘን ማለት ነው! ለምን ስንል፣ ከተቀጠራችሁ ምን ስራ እንደምትሰሩ ትምህርት ክፍላችሁ ደብዳቤ ይላክ ተባልን፤ ጥያቄው ምንም ሊገባኝ አልቻለም፡፡ ይህ ጥያቄ መጠየቅ የነበረበት ሰው ከተወዳደረና ተወዳድሮ ካለፈ በኋላ ነው ወይ ብለን ብንጠይቅም መልስ የሚሰጥ የለም፡፡

 

በየቢሮው እየሄድን ስንጨቃጨቅ፣ አልፎ አልፎም በንዴት አላስፈላጊ ነገሮችን ስንነጋገር፣ ሁለተኛ እዚህ ቢሮ አትምጡ የሚል ማስፈራሪያ ጭምር ይነገረን ጀመረ፡፡ እንዲሁ መሃል ላይ ስንመላለስ ያየችው ባልውለታችን ዶክተር የውልሰው አበበ፣ አንድ እስዋ የምታስተባብረው ፕሮጀክት ነበረ፣ እዛው ዲፓርትመንት በምርምር ስራ በኮንትራት በተሻለ ደሞዝ ቀጠረችን፡፡ እፎይ ብለን እዛው ት/ት ክፍል ስራ መስራት ጀመርን፡፡ ስራችን በዋናነት የምርምር ስራ ስለነበረ፣ አልፎ አልፎ ወደመስክ የመሄዱ እድል ነበረን፣ የመስክ ስራውም ስለሀገራችን የአመጋገብ ስርአትና በገጠሩ ማህበረሰብ ዘንድ ያሉትን የግንዛቤ ክፍተቶች እንዲሁም ችግራቸውን የበለጠ እንድናውቅ ጥሩ እድልን ፈጠረልን፡፡

 

የመጀመሪያውን የሙያ ስራዬን በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስጀምር ለመጀመሪያዎቹ ሁለት አመታት በተደጋጋሚ በሀዋሳ ዙሪያ ወዳሉት የሲዳማ ገጠራማ ሰፈሮች እየሄድን መረጃ እንሰበስብ ነበረ፡፡ ዛሬም ድረስ አእምሮዬ ውስጥ ያለው የሲዳማ ማህበረሰብ እንግዳ ተቀባይነት ነው፤ መረጃ ለመሰብሰብ ቤታቸው ስንሄድ ለኛ መቀመጫ አምጥተው በክብር አስቀምጠውን በቅርበት እንደሚተዋወቅ ሰው ሰላም ተባብለን መረጃችንን እንሰበስብ ነበረ፡፡

 

የእኔ ትምህርት ለነኛ የዋህ እናቶች ኑሮ መሻሻል ተጨባጭ ድጋፍ ማድረግ ቢችል እጅግ ደስ ይለኛል፡፡ በምርምሩ አጋጣሚም የሲዳማ ገጠራማ ቦታዎች በጣም ብዙ የልማት አቅም እንዳለው እንዲሁም ለአትክልትና ለፍራፍሬ ለእንሰሳት እርባታ ምቹ መሆኑንም አይቻለሁ፡፡ በተቃራኒው ደግሞ በህዝብ ብዛት የእርሻ መሬት ጥበት መኖሩንና እናቶችም ብዙ የጤና ድጋፍ እንደሚስፈልጋቸው ተረድተናል፡፡ የወጣቶች ስራ አጥነትም አንዱ አሳሳቢ ልማት ጥያቄ ነው፡፡

 

የሀዋሳ የመጀመሪያ አመት የስራ ቆይታዬ በብዙ ትዝታዎች የተሞላ ነው፡፡ ለምሳሌ ከእለታት አንድ ቀን  ገንዘብ አጥቼ እስክሪብቶ ሸጬ በታክሲ የሄድኩትን አጋጣሚ አልረሳውም፡፡ ለቅድስት ማርያም ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ቱተር ለመስጠት እየሄድኩ ረፍዶብኝ ታክሲ ልይዝ ፈልጌ ነበረ፣ ነገር ግን ኪሴ ባዶ ነበረ፣ ኪሴ ውስጥ አንዲት እስክሪብቶ ብቻ ነበረችኝ፣ እስክሪብቶዋን ለአንድ ሊስትሮ በ50 ሳንቲም ሸጬ ወደስራው ቦታ ደረስኩ፣ ያን ለት ያቺን እስክሪብቶ የገዣኝ ልጅ ምን ያህል ትልቅ ውለታ እንደዋለልኝ በሰአቱ ከነበረው ችግር ጋር ሳስተያየው ታላቅ ነው፡፡ ምክንያቱም ቱተር የማድረጉን ስራ ሰርቼ ገንዘብ የምቀበልበት ቀንም ስለነበረ፣ ተማሪዎቹ የለም ብለው እንዳይመለሱ ፈርጄ ነበረ፤ እኔ ገንዘብ አባካኝ ሰው አይደለሁም፤ የተቻለኝን ያህል እቆጥባለሁ፤ ነገር ግን በወቅቱ ደሞዜ ወር ሳይደርስ አልቆ ስለነበረ ምንም ገንዘብ ኪሴ ውስጥ አልነበረኝም፤ የሚገርመው ብዙ ጊዜ፣ ገንዘብ ለመበደር እፈልግና የሚያበድረኝ ሰው እንዳይታዘበኝ ስል በባዶ ኪሴ ደሞዝ እስኪደርስ ለአስር ቀናት አከባቢ የምጠብቅበትም ጊዜ ነበረ፡፡ ታዲያ ያንኑ እለት ከስራው ስመለስ 700 ብር ተከፍሎኝ ደስ ብሎኝ ቤቴ ገባሁ፡፡

አባትነት

ምርምሩ ላይ መስራት ከጀመርኩ በ8 ወር በኋላ የመጀመሪያ ልጃችን ህሊና ተወለደች፡፡ በህይወታችንም ውስጥ እጅግ ታላቅ ክስተት ሆነ፤ እግዚአብሄር ፍቅራችንንና ትዳራችንን በዘላለማዊ ፍቅር ባረከው፡፡

 

ማንም ሰው በምድር ላይ ሲኖር ከልጅ የበለጠ ታላቅ ነገር ሊኖረው እንደማይችልና ልጅ መውለድ ደግሞ እጅግ ታላቅ በረከት መሆኑን ቀስ በቀስ እየተረዳሁ ሄድኩኝ፤ በእርግጥም ከሰው ልጅ የበለጠ ነገር ምን አለ?

 

ይሁን እንጂ አሁን ሀገራችን ውስጥ ካለው ተጨባጭ ሁኔታ ስንነሳ ብዙ ሰዎች የልጅን ታላቅነት የተረዱት አይመስለኝም፤ በሀገር አቀፍ ደረጃም ቢሆን በየጎዳናው ወላጅ አልባ ህፃናትን የምናየው ወላጆች ልጆቻቸውን በሚፈለገው ትኩረት ለማሳደግ ቁርጠኝነት ሳይኖራቸው ስለሚቀር ነው፤ ብዙ ህፃናት እናትና አባት ቢኖራቸውም ወደጎዳና ተጥለዋል፤ ወላጅ የሞተባቸውም ደግሞ የሚፈለገውን ያህል እንክብካቤ የሚያደርግላቸው መንግስታዊ አካል አልተገኘም፡፡

 

ስለሆነም በሀገራችን በችግረኞችና በህፃናት ማሳደጊያ ዙሪያ ለሚሰሩት ድርጅቶች ታለቅ አክብሮት አለኝ፤ ከዴንማርክ እንደተመለስኩ የማቂዶንያን ማእከልና የሜሪ ጆይ ፕሮጀክቶችን የማየቱ እድል ነበረኝ፤ እግዚአብሄር ቢኒያምንና ሲስተር ዘቢደርን እንዲሁም በየአከባቢው ችግረኞችንና ጠያቂ ያጡ ዜጎቻችንን ለሚረዱት ሁሉ ውለታቸውን ይክፈላቸው፤ የሀገራችንና የህዝቦቻችን ባለውለታ ናቸውና፤ እድሜቸውንም ያርዝምልን፤ እንዲሁም ሌሎች  በተመሳሳይ የበጎ አድራጎት ስራ ላይ የተሰማሩትን ድርጅቶች ያብዛልን፤ ያሉትንም ብርታቱን ይስጥልን፡፡

 

 

የራሴ ልጅ መወለድ ስለሌሎች ልጆች የበለጠ እንዳስብ እድሉን አገኘሁ፤ እናቶችም የልጅን ነገር ወልደህ እየው የሚሉትም ለዚሁ ይመስለኛል፤ በዚህ አጋጣሚ የሀገራችንን ወጣቶችና ባለሀብቶች የተቸገሩትንና ወላጅ አልባ የሆኑትን ልጆች ለመርዳት የሚቻላቸውን ሁሉ እንዲያደርጉ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡ በቅርብ ከአሜሪካን ሀገር የመጡ የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎች በሀዋሳ ከተማና በአከባቢዋ ጉብኝት አድርገው ነበረ፤ እግረ መንገዳቸውን አንድ የጤና ተቋም ጎብኝተው በምግብ እጥረት የተጎዳ ህፃን አይተው እጅግ እንዳዘኑና እንዳለቀሱ ነገሩኝ፤ ይህ አይነቱ የሀገራችን ችግር፣ ለዚህች ሀገር ዜጎች ሁሉ የጋራ የቤት ስራችን ነው፡፡ እስከመቼ ድረስ ነው የኛ ሀገር ልጆች በዚህ ሁኔታ የሚያድጉት? እኛ ምን ማድረግ አለብን? ከኛ ምን ይጠበቃል? እኛ በየቀኑ ለቢራና ለድራፍት የምንከፍለው ገንዘብ እኮ እጅግ ብዙ ብር ነው፤ በሀገራችን ያሉትን ችግረኞች ችላ ብለን ግን አንዘልቀውም፡፡

 

ልጃችን ህሊና ስትወለድ የነበርንበት የገንዘብ አቅም ደካማ ነበረ፤ ስለሆነም የተወሰኑ ችግሮች ነበሩ፤ ቢሆንም ልጃችን ጤናማና እጅግ ደስ የምትል ስለነበረች ከስራ መልስ በጣም ጥሩ ጊዜ ማሳለፍ ጀመርኩ፤ የሌሎች ህፃናትም ለቅሶ የራሴ ልጅ ለቅሶ ያህል እስኪሰማኝ ድረስ፤  ነገርግን የህሊና መምጣት ህይወቴን በጥንቃቄና በተሻለ ሀላፊነት እንድኖር ምክንያት ሆነችኝ፡፡ ስለሆነም በወጣትነት ህይወታችን ወደትዳር መግባትና ለውጥ የግድ መሆኑን አምነን መቀበልና ሀላፊነት ቀደም ብለን መውሰድ ለህይወታቸን ስኬት በጣም ጥሩ ነው፡፡

 

እኔ ምን ያህል እድለኛ እንደሆንኩ የሚሰማኝ በልጅነት የተወለደችው ልጄ የምፅፈውን መፅሀፍ አንብባ ታሪኮቹ ላይ መስተካከል ያለባቸውን ነገሮች ስትነግረኝ ነው፡፡

 

በመግቢያው ለመግለጽ እንደሞከርኩት እኔ ይህንን ፅሁፍ የምፅፈው ደራሲ ስለሆንኩ ወይም ጥሩ የስነፅሁፍ ችሎታ ስላለኝ አይደለም፡፡

 

 

 

ይህ መፅሀፌ ለራሴ ልጆች ስጦታ ነው፤ ሙያዊ ይዘቱ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ እኔ ለመፅሀፍት ከፍተኛ ፍቅር አለኝ፤ በተለይ ለትምህርት መፅሀፍት፤ ስለትምህርት እድል የምጽፈውም ለዚሁ ነው፡፡ ስራዬም ማስተማር ስለሆነ ወላጆችና ወጣቶች ለትምህርት ትኩረት በመስጠት ልጆቻቸውን ውጤታማ አድርገው ሀገራችንም ከድህነት እንድትወጣ የሚቻለኝን ለመሞከር ነው፡፡

 

ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከገባሁና እጅግ የምወዳት ልጄ ህሊና ከተወለደች በሁለተኛው አመት እግዚአብሄር ለእስዋ ያዘጋጀውን የትምህርት እድል ዴንማርክ ሀገር አገኘሁ፡፡ በዛ አመት ወደ አስራ ሰባት የሚደርሱ የትምህርት እድል ደብዳቤዎች የፃፍኩ ሲሆን ከአስራ ሰባቱ ውስጥ የዴንማርኩ ብቻ ተሳካ፤ ይህም ወጣቱን ትውልድ የሚያስተምረው ትምህርት፣ አንድን ነገር ለማግኘት ያለመሰላቸት በተለያየ እድል መሞከር  እንሚያስፈልግ ነው፡፡

 

ብዙዎቻችን የስራ ህወታችንን የተሳካ ለማድረግ 12 አመት በትምህርት ቤት፤ 4 አመት መጀመሪያ ዲግሪ፤ 2 አመት በሁለተኛ ዲግሪ፤ 4 አመት በዶክተሬት ዲግሪ እንማራለን ወይም ለመማር እንመኛለን፡፡ ነገር ግን እንዴት ጥሩ ወላጅ መሆን እንዳለብን በቀጥታ የሚስተምረን አካልና ተቋም የለም፡፡ ስለሆነም አልፎ አልፎ በሙያዊ ህይወታቸው እጅግ የተዋጣላቸው የሚባሉ ምሁራን በወላጅነት ህይወታቸው ብዙም የተሳካላቸው አይሆኑም፡፡ ምንክያቱም ወደሙያቸው አብዛኛውን ትኩረታቸውን በማድረግ ለቤተሰብና ለትዳር ህይወት አነስ ያለ ትኩረት ስለሚሰጡም ሊሆን ይችላል፤ አንድ ዶክተር እሱ በሚያስተምርበት ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ሌሎች ገብተው ጥሩ ዜጋ ሆነው ሲወጡ የራሱ ልጅ ግን በሱስ ተለክፎ በተበላሻ ማንነት ሲመረቅ አይተናል፡፡

 

እኔ የትዳር ህይወትን በልጅነት የጀመርኩ ቢሆንም እድለኛ ነበርኩ ማለት እችላለሁ፤ ምክንያቱም በጊዜ የተጀመረው የትዳር ህይወት በወቅቱ ፈተናዎች ቢኖሩበትም ዛሬ ላይ ሆነን ስናየው እጅግ ደስተኛ የሚያደርገን ውጤት አይተንበታል፤ ምክንያቱም የመጀመሪያዋ ልጃችን ጓደኛችን ሆናለች፤ ትልቅ ልጅ ሆና ትልልቅ ሀገራዊ ጉዳዮችን እየተወያየን ነው፤ ስለሆነም ህወታችንን በደስታ እንድንኖር አድርጋዋለች፡፡ የህሊና ታናሽ፣ ሎዛም፣ አስተዋይነትዋና የስእል ችሎታዋ እንዲሁም በትኩረት የሚሰሩ ስራዎችን በጥንቃቄ ስትሰራ ሳይ፣ በኩራት፣ እውነትም ለሀገራችን እነኚህ ወጣቶች ታላቅ ተስፋ ናቸው እላለሁ፡፡

 

በሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ልጅ በልጅነት የመውለዱ ዋናው ጉዳይ ለልጁና ለትዳር የሚያስፈልጉትን ነገሮች ማሟላት ላይ ነው፤ ዋናው ችግር ገንዘብ ነው፡፡  እንደምንም የገንዘብን ችግር ተቋቁሞ፣ በተስፋ ህይወትን መኖር ደግሞ መጨረሻው ያማረ ይሆናል፤ አንድ መታመን ያለበት እውነታ አለ፤ ልጅ ማሳደግ ከባድ ነው፤ ስለሆነም አርቆ አሳቢ ወላጆች ያስፈልጉታል፡፡ ቢሆንም ወላጆች ከህይወታቸው እየተማሩ ቀስ በቀስ ወደተሻለ ደረጃ መድረስ ይጠበቅባቸዋል፡፡

 

የመጀመሪያ ልጃችን ስትወለድ አንድ ክፍል ቤት ነበር የተከራየሁት፤ ነብሳቸውን ይማርና አቶ ባደግ ቤት፡፡ ከአቶ ባደግና ከቤተሰባቸው ጋር  ደስ የሚል የአባትና የልጅ ያህል ቀረቤታ ነበረኝ፤ ወይዘሮ ፈቀደችና ልጆቻቸው ረዳ፣ ገበየሁ፣ አስቻለው፣ መስከረም፣ ሰላም፣ ቤተልሄምና ምህረት በትምህርታቸው ስኬታማ ሆነው ገበየሁም ትዳር ሊመሰርት መድረሱን ሳይ እጅግ ደስ ይለኛል፡፡ ገበየሁ ትለዳር መብቃቱም በጣም ደስ ይላል፣ እኔም ወጉ ደርሶኝ፣ ልጅትዋ ቤተሰቦች ጋር የጋብቻ ጥያቄ ሽምግልና ሄደን ደስ የሚል የጉራጌ ቤተሰብ የሽምግልና ባህልም አየሁ፡፡ ወንድም ገበየሁ፣ ትዳራቸው የተሳካ እንዲሆን ምኞቴ ነው፡፡

 

እኔ ትዳር ስመሰርት የነበረን የገንዘብ አቅም ሁለት ክፍል ቤት ለመከራየት አያስችለንም ነበረ፤ ቢሆንም ልጆች ሲወለዱ ለነሱ የሚሆነው ነገር አብሮ ይመጣል እንደሚባለው፤ ልጃችን ተወልዳ በሁለተኛ አመትዋ የትምህርት እድላችን ተገኘ፤ የገንዘብ ችግራችንም ታሪክ ሆነ፤ ቢያንስ ለልጃችን ማሳደጊያ በቂ ገንዘብ የምናገኝበት አጋጣሚ ተፈጠረ፡፡

 

 

 

ቢሆንም አንድ እድል ሲገኝ አብሮት የሚመጣ ፈተናም አለ፤ ለምሳሌ ልጅ ወልዶ ለትምህርት ወደሌላ ሀገር መሄድ ፈታኝ ነው፤ በተለይ ለእናቶች ደግሞ ችግሩ የባሰ አንደሆነ ይታወቃል፤ ለምሳሌ ልጅ ወልዳ በ8 ወር የትምህርት እድል ያገኘች እናት ልጅዋን ትታ ስትሄድ ሊገጥማት የሚችለውን ፈተና ልጆች ያለን ሁሉ እናውቃለን፡፡ እኔም የአባትነቴን ያህል ፈተናውን አይቼዋለሁ፡፡ ለሁሉም ለዛሬው ህይወቴ መሰረት የሆኑትን፣ ወላጄቼም ለእኔ ያላቸውንም ስሜት መረዳት እንድችል ላደረጉኝ፣ ለልጆቼ ለህሊናና ለሎዛ፣ እናንተን የሰጠኝን አምላክ እጅግ አመሰግነዋለሁ፡፡ ያላችሁን ብሩእ አእምሮና ትምህርት  ተጠቅማችሁ የወደፊት ለሀገራችንን ህዝቦች በተለይም ለሴቶችና ለድሆች ጠቃሚ የሆኑ ስራዎችን እንደምትሰሩም በዚህ አጋጣሚ ምኞቴን እገልፃለሁ፡፡

የትምህርት እድል

የትምህርት እድል በማግኘቴ እጅግ ደስ አለን፤ ከባለቤቴ ጋር ብዙ ተወያየን፤ የእድሉን ደብዳቤውን ተቀብዬ ከሁለት ወር በኋላ ቪዛ ተሰጠኝ፤ በወቅቱ ለእኔ ከባድ የነበረው አንደኛ ሚስቴንና ልጄን ጥዬ መሄዴ ሲሆን ሁለተኛ ለአውሮፕላን ቲኬት መግዣ ገንዘብ መቸገሬ ነበረ፡፡

የሁል ጊዜም ባለውለታዬ ተስፋዬ ሽፈራው በሰአቱ የትምህርት እድል አግኝቶ ኖርዌይ ነበረ፤ ስለትምህርቱ እድል ስነግረው የራሱን ችግር በማስታወስ፣ የአውሮፕላን ቲኬት እንደሚገዛልኝና ዴንማርክ ከደረስኩ በኋላ ደሞዜን ቆጥቤ እንደምከፍለው ነገረኝ፡፡ የተማረ ይግደለኝ የሚባለው ለዚህ ነው፤ እግዚአብሄር መፍትሄ አመጣልኝ፤ ቤት ገብቼ ለባለቤቴ ስነግራት እስዋም እጅግ ተደሰተች፡፡ መማር ማለት ምን ማለት እንደሆነ በተለይም ደግሞ ከደሀ ቤተሰብ ተወልዶ ትምህርት መማር ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ያለፈበት ሰው በትክክል ይረዳዋል፤ አብዛኛው የኛ ሀገር ዘመድ ዝምድናውን የሚያስታውሰው ጥቅሙን አስቦ ነው፤ አንዳንዱ ሀብትም ቢኖረው፣ ገንዘቡን ከዘመዶቹና ከሌሎች ሰዎች በላይ አድርጎ ስለሚቆጥር ለችግር ጊዜ ላይደርስ ይችላል፡፡  እዚህ ሀሳብ ላይ ብዙ ተጨባጭ መረጃዎችን ብጨምር ደስ ቢለኝም ለጊዜው ግን በዚሁ ወደሌላ አልፋለሁ፡፡

 

ወዳጄ ተስፋዬ ባደረገልኝ ድጋፍ ወደ ዴንማርክ ለመሄድ ዝግጅቴን ጨረስኩ….. ቪዛ ልወስድ ዴንማርክ ኢምባሲ ስሄድ ትምህርትህን ስትጨርስ ምን ማድረግ ትፈልጋለህ ተባልኩ….በልበ ሙሉነት መለስኩ፤ ትምህርቱን ስጨርስማ ወደሀገሬ ተመልሼ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት እሰራለሁ፤ ይሀው  ድጋፍ ደብዳቤዬ ብዬ ከዩኒቨርሲቲው የተሰጠኝን አሳየሁ….

 

ጠያቂዋ ሳቀችብኝ…

 

ያቺ ሳቅ ምን ማለት እንደሆነች የገባኝ ትምህርቴን ጨርሼ ለተወሰነ ጊዜ እዛው ዴንማርክ ለመቆየት ሳስብ ነው፡፡

 

ትምህርቱን ጨርሼ ቶሎ ወደሀገር ቤት ከመመለስ፣ ቆንጆ ስራ ካገኘሁ፣ እዚሁ ሰርቼ ሀገሬ ትልቅ ፋብሪካ እከፍታልሁ ምናምን ብዬ ራሴን ማሳመን ጀምሬ ነበረ፡፡

 

በሀገራችን ዩኒቨርሲቲ መምህርነት ቆንጆ ስራ ሆኖ ሳለ፣ ወደኪስ አቅም ስንመጣ ግን ያሳቅቃል፤ ውጪ ሀገር ሰው የፅዳት ስራ ሰርቶ ከሀገራችን ፕሮፌሰር በላይ ኑሮ ይኖራል (የቁሳቁስ ኖሩ ማለቴ ነው፣ የህሊና ኑሮው ግን በፍፁም አይወዳደርም፤ ለራስ ሀገርን ለራስ ወገን መስራት የማንኛውም ሰው ምኞት ስለሆነ፤ በተለይ የተማረ ሰው ከሀገሩ ተሰዶ ሌላ ሀገር ሲኖር፣ በተለይ ሀገሩ ድህነት መኖሩን ስለሚያውቅ፣ ውስጡ ደስታ ሊኖረው አይችልም)

 

ለምሳሌ ከሀዋሳ ወደዴንማርክ ከመሄዴ በፊት አንዱ ትዝታዬ፣ ከሁለት አመት ስራ በኋላ የነበረኝ ቁጠባ 2000 ብር ብቻ ነበረ፤ የቪዛ ክፍያ ለመክፈል ራሱ በቂ ብር አልነበረኝም….

 

 

 

ትምህርት ትልቅ ነገር ነው፤ የተማረ ሰው በብዙ መልኩ ለራሱም፣ ለቤተሰቡም፣ ለወላጆቹም እንዲሁም ለሀገሩ ጠቀሜታ ይሰጣል፡፡ ትምህርት ስንል የግድ ከትምህርት ቤት በመምህራንና ከመፅሀፍት ብቻ የምንማረው ማለት አይደለም፤ ትምህርት ከህይወት መማር ይቻላል፤ በዚህ መጽሀፍም ውስጥም ትምህርት የሚለው ቃል ከተለመደው የዪኒቨርሲቲዎች ትምህርት በተጨማሪ ከህይወት የተማርኩትንም ይጨምራል፡፡

 

በሀገራችን  ለትምህርት የምንሰጠው ግምትና ዴንማርክ ሀገር ለትምህርት የሚሰጠው ግምት ተመሳሳይ አለመሆኑን ተረድቻለሁ፤ ዋናው ልዩነትም፣ በሀገራችን ትምህርት ከድህነት ማምለጫ ተደርጎ ሲታሰብ በዴንማክ ሀገር ደግሞ ትምህርት መርጠው የሚማሩትና ማንም መማር የሚፈልግ ሰው መርጦ መማር ይችላል፡፡ የዴንማርክ ተማሪ ሲማር ለተማሪነቱ ገንዘብ ተከፍሎት ይማራል፤ ቶሎ ትምህርት ለሚጨርሱም የማበረታቻ ክፍያ አለ፤ ሀገራችን ደግሞ በየደረጃው ፈተናዎች ስላሉ ብዙ ተማሪ በርትቶ የሚያጠናው ፈተናዎቹን ላለመውደቅና ስራ ለማግኘት እንጂ ሀገራዊ ጠቀሜታው ብዙም ላይታሰብ ይችላል፤ ስለሆነም ብዙ ወጣቶች ተምረው እድሉን ሲያገኙ ወደሀብታም ሀገር ሄደው እዛው ይቀራሉ፤ ሀገራቸውን መርዳት ቢፈልጉም የራሳቸው የኑሮ ፍላጎት የሚፈልጉትን ሳያደርጉ ያስቀራቸዋል፡፡ በተለይ ለኔ አይነቱ የደሀ ልጅ፣ ተምረን ስራ ካላገኘን፣ በሌላው መስክ ስራ ለማግኘት፣ የነጋዴ ቤተሰብ ወይም ሀብታም ዘመድ ወይም ሰፊ የእርሻ መሬት ማስፈለጉ ግድ ነው፡፡ ይህ ተምሬ ስራ ካላገኘሁ ምን እሆናለሁ የሚለውን ስጋት ከወጣቶችና ከነገው ትውልድ አእምሮ ለማስወጣት፣ ሀገራችን ስራ ለሚፈልጉትም እንዲሁም የራሳቸውን ስራ መፍጠር ለሚፈልጉትም የተዘረጋ ጠንካራ ስርአት ሊኖራት ይገባል፡፡ ይህንን ሀሳብ ስለወጣት ስራ አጥነት ደግሜ አጠናክረዋሁ፡፡ ቢሆንም ይህንን ስርአት መዘርጋት የሁላችንም ሀገራዊ ግዴታችን ነው፡፡ ካልሆነ ሀገራችንን በምኞት ብቻ ልናሳድጋት አንችልም፡፡

 

 

 

 

እኔ የመጀመሪያ ዲግሪዬን ስማር ዩኒቨርሲቲ ውስጥ መምህር የመሆን ፍላጎቱ ነበረኝ፤ ስለሆነም በጥሩ ውጤት ለመመረቅ የተቻለኝን ያህል በርትቼ አጠና ነበረ፤ እንዳሰብኩትም ተሳክቶልኝ ከምርቃት በኋላ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት ከተቀጠርኩ ጀምሮ ሁለተኛ ዲግሪዬን ለመማር የትምህርት እድል ወይም ስኮላርሺፕ እፈልግ ነበረ፤ ስለሆነም ብዙ ሰአት ኢንተርኔት ላይ ማንበብ እንዲሁም የተለያዩ ሀገራት እድሉን መሞከር ነበረብኝ፤ ለሁለት ተከታታይ አመታት በየአመቱ ቢያንስ 15 የስኮላርሺፕ ማመልከቻዎችን ልኬያለሁ፤ ብዙዎቹ ማመልከቻዬን ይቀበሉና ለትምህርቱ ተቀብለንሀል ነገር ግን የትምህርቱን ክፍያ ከራስህ መክፈል አለብህ የሚል ነበረ መልሳቸው፤ የሀገራችን ተማሪዎች በቀላሉ የአውሮፓና የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ለሁለተኛ ዲግሪ መመዝገብ እንደሚችሉ ወይም አድሚሽን እንደሚያገኙ ተረዳሁ፤ ዋናው ችግር የነበረው የትምህርቱን ወጪ የሚከፍል ስኮላርሺፕ ወይም የገንዘብ ድጋፍ ማግኘት ነበረ፡፡

 

በበኩሌ ለውጪ ሀገር ትምህርት ያንን ያህል ጉጉት የነበረኝ አንደኛ ውጪ ዩኒቨርሲቲያቸው ሁሉ ነገር የተሟላ ነው ብዬ አስብ ስለነበረና ሁለተኛ በትምህርቱ ሰበብ ገንዘብ ለማግኘት ነው፤ ሀገርም የማየት ፍለጎቱ ነበረኝ፡፡ ስለሆነም የትምህርት እድሉን ለማግኘት ብዙ ማመልከቻ ላኩኝ፤ እንዲቀበሉኝም ብዙ የማሳመኛ ምክንያቶች መጻፍ ነበረብኝ፤ ሁሉም እድሎች ለምን እኛ ጋር መማር ፈለግክ፣ ከጨረስክስ በኋላ ምን ማድረግ ትችላለህ ብለው ይጠይቃሉ፡፡ ሀገራችን ደሃ ናት፤ እኔም ተምሬ ሀገሬም ከድህነት እንድትወጣ ማገዝ እፈልጋለሁ፤ ነገር ግን ሀገራችን የሁለተኛ ዲግሪ ትምህር እድል ውስን ነው፤ እንዲሁም ያሉትም ዩኒቨርሲቲዎች የትምህርቱ ጥራት ጥሩ አይደለም ወዘተ እያልኩኝ ዘመናዊ የልመና ደብዳቤዬን /ሞቲቬሽን/ ለብዙ ዩኒቨርሲቲዎች እልክ ነበረ፡፡ ዘመናዊ ልመናዬ ተሳክቶ በሁለተኛው አመት ከላኩት 17 ማመልከቻዎች ውስጥ የዴንማርክ ሀገሩ ተሳካልኝ፤ እጅግ ተደሰትኩ፡፡ ጎበዝ ዘመናዊ ለማኝ ነኝ ብዬም ራሴን አሞገስኩ፤ የትምህርት እድሉን ሙሉ በሙሉ በራሴው ጥረት ነው ያገኘሁት፤ እድሜ ለኢንተርኔት፤ ኢንተርኔት ባለውለታዬ ነው፡፡

ህልም

የዴንማርኩ የትምህርት እድል ሲሳካልኝ ስለዴንማርክ ሀገር ማንበብ ጀመርኩ፤ ስለዴንማርክ ያነበብኩት መረጃ የምሄድበትን ቀን እንድናፍቅ አደረገኝ፤ አንዳንዴ ተኝቼም የትም የማላውቃት ዴንማርክ በህልሜ መምጣት ጀመረች፤  ሌላ ጊዜ ህልም የማላየው ሰውዬ በየምሽቱ ገና ሸለብ ሲያደርገኝ ኮፐንሀገንን ማየት ሆነ፤ አንዳንዴ መንገድ ጠፍቶብኝ ስጨነቅ አያለሁ፤ አንዳንዴ ደግሞ ብዙ ገንዘብ ኖሮኝ አውሮፕላን ስገዛ ይታየኛል፤ አንዳንዴ ደግሞ ወደዴንማርክ ስሄድ አውሮፕላኑ ይከሰከሳል፤ ብንን ስልም ድንግጥ እላለሁ፤ ለምን እንዲህ አይነት ሰይጣናዊ ህልም ያሳየኛል ብዬ በህልሜም የተናደድኩበት ጊዜ አለ፡፡

 

ከሁሉ በላይ ግን የሚከሰከሰው አውሮፕላን ጉዳይ ከተራ ህልምነት የዘለለ የሆነ እውነታ ይኖረው እንደሆነ ከህልሜ ከባነንኩ በኋላም ሀሳቡ ይመጣብኝ ጀመረ፤ ሳስበው ፍራት ፍራት ይለኝም ጀመር፤ ብቻ የትምህርት እድሉ ደብዳቤ ከመጣልኝ ቀን ጀምሮ ተነግሮ የማያልቅ የህልምና የእውን የሀሳብ ጭንቀቶች ይረብሹኝ ጀመረ፡፡ እንደ እድል ሆኖ የትምህርቱን እድል ሳገኝ ዶክተር እስክንድር ሎሀ የቅርብ አለቃዬ ነበርና ደብዳቤውን አስነበብኩት፤ እንኳን ደስ አለህ፤ እዛ ዩኒቨርሲቲ ተምሬ ነበረ፤ በጣም ቆንጆ ዩኒቨርሲቲ ነው፤ ዴንማርክም እጅግ ደስ የሚል ሀገር ነው ብሎ የበለጠ አስደሰተኝ፡፡ አውሮፕላኑ ሊሰከስ ይችላል የሚለው ስጋት ግን በተደጋጋሚ ይመጣብኝ ነበረ፡፡

 

የውጪ ሀገር ትምህርት እድል ደረሰኝ ብዬ ለእናቴም ደውዬ ስነግራት ደስ አላላትም፤ ልጄ ምነው የተማርከው ቢበቃህስ? ለራስህም ክስት ብለሀል፤ የተማርከውን እግዚአብሄር ያባረክልህ፤ ተወው ይቅርብህ አለችኝ፤ የእናት ነገር፣ ለልጅዋ እረፍትን መመኘትዋ ነው፤ መለያየቱንም፤ ውጪ ሀገር ድረስ መሄዴንም አልወደደችውም፡፡ እስዋ እንዲህ ካለችኝ ጊዜ ጀምሮ የአውሮፕላኑን በህልሜ መከስከስ እያስታወስኩ ልቤን ፍራት ፍራት ማለቱ ተጠናክሮ ቀጠለ፤ በራስ መተማመኔ እየጠፋ ሲሄድ ይታወቀኛል፡፡

 

የመጀመሪያ ልጄንም እያሰብኩ የበለጠ ፈራሁ፤ ለትምህርት ብዬ ልጄን ያለአባት ላስቀራት ነው አይደል ብዬ የሆነ ሰይጣናዊ ሀሳብ ማሰብም ጀመርኩ፤…. የህልሙ ነገር አይነቱን እየቀያየረ ያስጨንቀኝ ቀጠለ፡፡ ቀስ በቀስም የምግብ ፍላጎት እየቀነሰ ሄደ…

የአውሮፕላን ጉዞ

ዴንማርክ ለመሄድ ቲኬት ልገዛ አዲስ አበባ ሄድኩ፤ መሄድ የምፈልገው በኢትዮጵያ አየር መንገድ ነበረ፤ የጉዞ ወኪሎችን ስጠይቅ ርከሹ የቱርክ አውሮፕላን ነው…. ከኁሉም ርካሹን ቲኬት፣ በቱርኩ አየር መንገድ ልሄድ፣ ገዛሁ፡፡ የጉዞዬ ቀን ታወቀ፤ አሁን የበለጠ ፍርሀት ፍርሀት ይለኝ ጀመረ፡፡ ዴንማርክ ሀገር ሄጄ ብቸገርስ? ብሞስት? ልጄ አባት የሌላት ልትሆን ነው አይደል? መንገድ ቢጠፋብኝስ?…አዲስ አበባን በደንብ ሳላውቅ ዴንማርክ ሀገር ሄጄ ምን ሊውጠኝ ነው ወዘተ የሚሉ ጥያቄዎች እየመጡ ልቤን ፍርሀት በፍርሀት አደረገኝ፡፡ የምግብ ፍላጎቴም እየቀነሰ መጣ፤ ከባድ የራስ ምታት ህመምም ይሰማኝ ነበረ፤ ቢሆንም ፍርሀቴን ዋጥ አድርጌ፣ ማታ ማታ እንቅልፍ ባይዘኝም፤ የመሄጃዬን ቀን መድረስ መጠባበቅ ጀመርኩ፤ ጊዜው ደግሞ አልሄድ አለኝ፣ ሶስት ሳምንት ሲቀረው ሶስት አመት ያህል ረዝሞ አሰለቸኝ፤ ቶሎ ልሂድና ቁርጡን ልወቀው አይነት ስሜት መሆኑ ነው፡፡

 

ሌላው የጭንቀቴ ሰበብ፣ ዴንማርክ እንደደረስኩ ከምን ያህል ጊዜ በኋላ ገንዘብ እንደሚሰጠኝ እያሰብኩኝ ነበረ…ምክንያቱም ምንም ለቤተሰቤና ለወላጆቼ የተውኩት ገንዘብ የለም….በኪሴም ለመያዝ ምንም ብር የለኝም፤ እንደምንም የመሄጃ ቀኔ ደርሶ የአውሮፕላኑ በረራ ሰአት ምሽት 7፡30 ነበረ፡፡ ለሊቱ አንድ አመት ሆነብኝ፤ እስከ ቦሌ ተሸኘሁ፤ ልጄ ህሊና አንጀቴን በላችኝ፤ መቼ ነው የምትመለሰው? ብላ ስትጠይቀኝ የምሞት መስሎኝ ደነገጥኩ፤ ቶሎ ነው የምመለሰው፤ ደግሞም ሁሌ ማታ ማታ እደውልልሻለሁ አልኩዋት፤ እሺ አለች፤ እሺታው የደስታ እንዳልሆነ አውቃለሁ፤ ተሰነባብተን ወደውስጥ ገባንና ሻንጣዬን ሰጥቼ ወደበረራ መጠበቂያ ቦታው ሄድኩኝ….ሌላው ስጋት ኮፐንሀገን ስደርስ ማን ይቀበለኝ የሚለው ነበረ፡፡

 

ቀደም ብሎ ዴንማርክ የነበረው ወዳጄ ሰለሞን ሊቀበለኝ ተስማምተናል… ነገር ግን እርግጠኛ አልነበረም፤ ምክንቱም ስራ ስለነበረበት፤…አውሮፕላኑ ተነስቶ ለበረራ ሲንደረደር ለቅሶ ቤት ወደቀብር ቦታ ሲኬድ የሚሰማው አይነት ስሜት ነበረ የሚሰማኝ፤ ምኑም አልተመቸኝም፤ ፍርሀት ፍርሀት ብሎኛል፤ አውሮፕላኑ መሬት ለቆ ሲነሳ ልቤን የሆነ ነገር ስልብ አደረገኝ፤ የመጀመሪያ ጊዜ በረራ ስለሆነ ሁሉም ሰው ያቺን ስሜት ሊሰማው እንደሚችል እገምታለሁ፤ እኔ ግን ምነው በቀረብኝ፤ ምነው በድህነቴ ብኖርስ? የሚል አይነት ስሜት ተሰማኝ፤ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ስለአደጋ ጊዜ የሚደረጉ ጥንቃቄዎች ማሳየት ጀመሩ…አሁንም የበለጠ አስፈራሩኝ፤ ሁሉንም ሂደት በትክክል ለማስታወስ መሞከር ነበረብን የሚል ሀሳብም መጣብኝ፡፡ የበውቀቱ ስዩምን መፅሀፍ ሳነብ ስለበረራ የሰጠው አስተያየት በትክክል የእኔን ስሜት የፃፈ ነው የመሰለኝ፡፡

 

ከተወሰነ ጊዜ በኋላ አስተናጋጆቹ ምግብ አመጡልን፤ ምግቡ እንዴት ይሁን የሚበላው? ግራ ገባኝ፤ አጠገቤ ከተቀመጠው ዝምተኛ ፈረንጅ መኮረጅ ጀመርኩ…. በምግብ አበላልም ለካ ኩረጃ አለ፤ ሰውየው የሚያደርገውን በጥንቃቄ እየደገምኩ ምግቡን መመገብ ጀመርኩ፤ የምግብ ፍለጎት ምንም አልነበረኝም፤ ይልቁንስ ምግባቸው የሆነ ደስ የማይል ስሜት ፈጠረብኝ…. ያ ሁሉ ሲደረግ እኔ ለቅሶ ቤት ያለሁ እንጂ ወደተሸለ ነገር የምሄድ አልመሰለኝም፤ ይባስ ብሎ አውሮፕላኑ መንገጫገጭ ጀመረ፤ ይሄኔ ትክክለኛው የመሞቴ ሰአት እየተቃረበ መሆኑን ገመትኩ…. ዞር ዞር ብዬ የሰዉን ስሜት ለማየት ስሞክር ብዙዎቹ ተኝተዋል…. ጉዳችሁን አልሰማችሁም በሚል አይነት ስሜት አሳዘኑኝ፤ ያቺን የአደጋ ጊዜ የተባለችውን ላስቲክ ማውጣት አሰብኩ፤ ግን ከማን ልኮርጅ? ሌላው ሰው ፊልም እያየ ነው…ሌላው ተኝተዋል…ከዛ መንገጫገጩ አለፈ…. ተረጋጋሁ፤ ጠዋት ቱርክ ኢስታንቡል ደረስን፤ አሁንም ሌላ አውሮፕላን ይዘን ወደ ኮፐንሀገን መሄድ አለብን፣ የት መሄድ እንዳለብኝ ሰዎች ጠይቄ ወደመግቢያው ደረስኩና ሰአቱን ሳይ አንድ ሰአት መጠበቅ አለብኝ፤ ከዛ እዛው መቀመጫው ወንበር ላይ ጋደም ብዬ እንቅልፍ ሸለብ አደረገኝ፤ ትንሽ ቆይቼ ብንን አልኩ…. ስነሳ ከባድ የራስ ምታት እየተሰማኝ ነበረ፡፡

 

ሊያቅለሸልሸኝም ፈለገ….ረሀብም ነው መሰለኝ…ምን ልግዛ? ምንም መግዛት አልቻልኩም…. የራስምታቱ ስሜት ለቅሶ ቤት ውዬ የገባው አይነት ነው…. አሁንም ጊዜው አልሄድ ብሎኝ ስቸገር አንድ ጥቁር የሀገሬን ሰው ሚመስል አየሁኝ…. እጅግ ደስ አለኝ፤ ራስምተቱ ተወኝ፤ ሰውየው ሲያየኝ ፈገግ አልኩ፤ እባክህ አናግረኝ የማለት አይነት ፈገግታ ነው፡፡

 

ሰውየውም አላሳፈረኝም፤ ጠጋ አለና ኢትዮጵያዊ ነህ አይደል ሲለኝ አዎ አልኩኝ በፍጥነት….ወዴት እየሄድክ ነው ሲለኝ ወደ ዴንማርክ አልኩት፤ ዋው.. ዴንማርክ ቆንጆ ሀገር ነው አለኝ፤ ምን ልትሰራ ለምንድን ነው ሲለኝ ለትምህርት አልኩት፡፡ በጣም እድለኛ ነህ ብሎ የበለጠ ተጠጋኝ፡፡ ዴንማርክ ሀገር ለትምህር ሲሄዱ አልሰማሁም እንዴት አገኘህ ሲለኝ ስኮላረሺፕ ነው አልኩት…. እኔ አሜሪካን ሀገር 20 አመት ሞላኝ አሁን ወደኢትዮጵያ እየሄድኩ ነው፤ አንድ ወንድም አለኝ፤ ውጪ እንዲማር እፈልጋለሁ፤ እስቲ ንገረኝ እንዴት ማመልከት እንዳለበት፤ ልጁ ግን ምንም አልሳካ ብሎታል አለኝ፡፡ ሁሉን ነገር ነገርኩት፤ በጣም አመሰገነኝ፤ ተለያየን፡፡ ስንለያይ ከራስ ምታቱ ህመሜም ተፈወስኩኝ፤ የሀገሬን ሰው ማየት ራስምታቴን አባረረው፤ ደስ አለኝ፡፡

 

ከዚያ ወዲያው ወደኮፐንሀገን መብረር ጀመርን….አሁን ጉዞው በቀን ስለሆነ ከፕሌኑ ላይ ወደታች   በደንብ ማየት ይቻላል፡፡  ኢስታንቡል ቆንጆ ከተማ ናት፡፡ ቱርክ ሲባል ያንን ያህል ቆንጆ ሀገር አትመስለኝም ነበረ፡፡ ኮፐንሀገን ስንደርስ በረራው አጭር ስለሆነ  ሳያሰለቸን ደረስን፤ እንደደረስኩ ሻንጣዬን ወስጄ ወደውጪ ስወጣ ወዳጄ ሰለሞን በርላይ እየጠበቀኝ ነበረ፤ እጅግ ተደሰትኩኝ… አሁን ስራዬ እሱን መከተል ብቻ ሆነ፤ የሆነ አሳንሱር ውስጥ ገባንና ከዛ ሾፌር የሌለው ባቡር ውስጥ ይዞኝ ገባ፤ ባቡሩ እንዴት ያለሾፌር ሊሄድ ይችላል?   ቢጋጭስ?  ባቡሩ በመሬት ውስጥ በከተማዋ ስር ነው የሚሄደው…ልክ እንደ አይጦቹ ጉድጓድ የተሰራለት መንገድ አለ፤ ማድነቅ ተጀመረ፤ በዛን ወቅት አዲስ አበባ ባቡር አልነበረም፤ አውሮፕላኑም፣ ባቡሩም አዲስ ነው… ሁሉን ነገር መአግራሞት መመልከቱን ጀመርኩኝ፡፡ ባቡሩ ቢሄድ ቢሄድ ከመሬት ውስጥ አልወጣንም፤ ገረመኝ፡፡

 

ወይ ፈረንጅ ሀገር….ወይ ስልጣኔ ማለት ተጀመረ…. ከተወሰነ ደዊቃ በኋላ ከባቡሩ ወረድንና በእግራችን ተጉዘን አውቶቢስ ያዝን፤ ሰለሞን ሁሉንም ሲያደርግ እኔ መከተል ብቻ ነው፤ እቤቱ ደረስን…. በጣም ደስ አለኝ፡፡

የዶርም  ኑሮ  በኮፐንሀገን

 

በነገራችን ላይ ዴንማርክ በስተምስራቅ ከስዊዲን፣ መስተምእራብ ከእንግሊዝ፣ በስተደቡብ ከጀርመንና በስተሰሜን ከኖርዌይ ትዋሰናለች፡፡ ዋና ከተማዋ ኮፐንሀገን ሲሆን የህዝብዋ ብዛትም 5 ሚሊየን አከባቢ ነው፡፡ አጠቃላይ የዴንማርክ ሀገር ህዝብ ብዛት ከአዲስ አበባ ህዝብ ያንሳል፤ ነገር ግን 107 ሚሊየን ህዝብ ላላት ሀገራችን እርዳታ ትሰጠናለች፡፡

ዋናው ሚስጥር የህዝብ  ብዛት ሳይሆን የህዝብ ጥራት ነው!!

ኮፐንሀገን…… የተያዘልኝ ቤት እዛው ነበርና ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የመጣው ወዳጄ ዳንኤል ጋር ተገናኘን…. እጅግ ደስ አለኝ፤ ከሀገሬ ልጅ ጋር አንድ ዶርም ተመደብን፡፡ ዶርሙ መኝታና ምግብ ማብሰያ፤ መታጠቢያ ሽንትቤትና ፍሪጅ አለው፡፡ ሁሉ የተሟላ ነው፡፡ ጭልፋ፤ መንኪያ፤ ቢለዋ፤ መክተፊያ… ሁሉ የተዘጋጀ፡፡ ወይ ፈረንጅ፤ ወይ ዴንማርክ… አድናቆታችን ጨመረ፡፡

 

ኮፐንሀገን ደርሰን የመጀመሪያዎቹ ሳምንታት ሱፐርማርኬት ሄደን የምግብና የተለያዩ እቃዎችን ዋጋ እያየን ወደሀገራችን ብር እየቀየርን መደነቅና ማወዳደር ነበረ፤ ታዲያ ቋንቋ ዋናው ችግራችን ነበረ፤ ሁሉ ነገር የተፃፈው በራሳቸው ቋንቋ ስለሆነ ከቁጥሮቹ ውጪ ሌሎቹን ለማንበብ ችግር ነው፡፡ ለምሳሌ ነጭ ሽንኩርት ሎይ ትባላለች፤ ሎይ ቀረብ የሚለው የአማርኛ አፃፃፍ እንጂ ሰዎቹ ሲያነቡት ምን ብለው እንዳነበቡት ሰምተን ለመድገም ይቸግረን ነበረ፤ ስድስት ፍሬ ነጭ ሽንኩርት 12.99 ተለጥፎበታል፡፡ 12.99የዴንማርክ ብር ማለት ወደ 40 የኢትዮጵያ ብር ነው፡፡ አስር ፍሬ የሚሆን ትንንሽ ቲማቲም 13.95 ተለጥፎበታል፤ በሀገራችን ብር ወደ 44 ብር አከባቢ ነው፡፡

 

ታዲያ እነሽንኩርትና ቲማቲም አይቶ ለመለየት ቀላል ስለሆኑ ነው፡፡ ከእለታት አንድ ቀን ወዳጄ ዳንኤል ከምንኖርበት የቶሲንጊጌድ ሰፈር ቤታችን ስር ካለችው ፋክታ ሱፐርማርኬት ዘይት ሊገዛ ሄደ፤ ይዞ የመጣውን ዘይት የተከተፈው ሽንኩርት ድስት ውስጥ ሲጨምርበት ደነገጥን፤ ለካ ዳኒ የገዛው ዘይት ሳይሆን አቼቶ ነበረ፡፡ ግራ ያጋባው ስሙ ነው፤ የቋንቋ ችግር፡፡

 

ከቋንቋ ችግር ጋር በተያያዘ ብዙ ደስ ደስ የሚሉ ትዝታዎቹ አሉን ፤ በእርግጥ ብዙ የዴንማርክ ዜጎች እንግሊዘኛ ይናገራሉ፤ ነገር ግን ለእንግሊዘኛ ይልቅ የራሳቸውን ቋንቋ መናገር ነው የሚመርጡት፡፡ የዴኒሽ ቋንቋ ዋናው ችግር ፅሁፉና የሚናገሩት ድምፅ ተመሳሳይ አለመሆኑ ነው፤ ለምሳሌ Fredriksberg የሚለውን ቃል ፌስቢያ ብለው የነቡታል፡፡ እኛ ደግሞ ፍሬድሪክስበርግ ብለው እንዲያነቡት ነው የምንፈልገው፡፡

 

ዴንማር ኮፐንሀገን ከተማ ከኛዋ አዲስ አበባ ጋር ስትወዳደር የሳይክል ከተማ ናት ማለት ይቻላል፤ በጣም ብዙ ሰው በሳክል ይጓዛል፤ በመኪናም ብዙ የሚጓዙ ቢኖሩም፡፡ ለብርዱ ጊዜ ሳይክል መንዳት ቀላል ባይሆንም በበጋውና በፀደይ ወቅት ብዙ በሳይክል መጓዝ ደስ ይላል፡፡ እኔ የሳይክል ችሎታዬ አስተማማኝ ስላልሆነ ደፍሬ መንዳት አልቻልኩም፤ ታዲያ በኮፐንሀገን ከተማ አልፎ አልፎ ሳይክል መሰራረቅ የተለመደ ነው፤ ስለሆነም ሁሉም ሰው ሳይክሉን ቆልፎ ነው የሚያቆመው፤ አንድ የዛ ሀገር ተወላጅ ወዳጄ ፤ ኮፐንሀገን ከተማ ውስጥ ሳይክል በመስረቅ ብቻ የሚተዳደሩ የውጪ ሀገር ስደተኞች መኖራቸውን ነግሮኛል፡፡ ኮፐንሀገን ደርሰን በሶስተኛው ቀን ከሌላ ሀገር ለመጡት አዲስ ተማሪዎች ዴንማርክን የማስጎብኘት ፕሮግራም ነበረ፡፡ ለዚሁ ፕሮግራም የተዘጋጀ መኪናና አስጎብኚ ባለሙያ አለ፤ መጀመሪያ ቤተመንግስታቸውን፤ ቀጥሎም ስለዴንማርክ ታሪክ ገለፃ፤ ከዛም ከኮፐንሀገን ወጣ ብሎ ያለ ደን ልማት፤ የግብርና ኮሌጃቸውን ወዘተ አስጎበኙን፡፡

 

 

ትምህርት ከፕሮፌሰሮችና ከክፍል ውስጥ ብቻ የሚገኝ እንዳልሆነ የዴንማርክ ሀገር ቆይታዬ በደንብ አስተምሮኛል፤ ከማህበረሰቡ ጋር በመኖርና በጉብኝት ብዙ መማርና ብዙ ልምድ መቅሰምም ይቻላል፡፡

 

ቀጥሎም ዴንማርክ ደርሰን በ5ኛው ቀን የባንክ አካውንት ተከፍቶልን የማስተር ካርድ በፖስታችን ተላከልን፡፡ የዩኒቨርሲቲው የመጀመሪያ ዙር ክፍያም ወዲያውኑ ተከፈለን፡፡

 

አቤት ቅልጥፍናቸው፤ አቤት ሰው ማክበራቸው፡፡

 

በመንፈሳዊ ቅናት ተቃጠልኩኝ፤ የኛ ሀገር ባንኮች የነበረው አገልግሎት እኔ ዴንማርክ ሀገር ከመሄዴ በፊት እጅግ የተበላሸ ነበረ፡፡ በብዙ ጎኑ የሀገራችንን አሰራር ከዴንማርክ ጋር ማወዳደር ህፃናትን ከአዋቂ እንደማወዳደርም ሊቆጠር ይችላል፤ አልፎ አልፎ እኛ የተሻሉ ነገሮች ቢኖሩንም የመንግስት ስርአትንና የህዝብ መሰረተ ልማትን ስንመለከተ እኛ መንግስት አለን ብሎ ማለት ያጠራጥራል፡፡ ለምን ቢባል ዝርዝሩን እመለስበታለሁ…. ለወቀሳና ራሳችንን ዝቅ ለማድረግ አይደለም የምዘረዝረው… እኛም የት ድረስ መሄድ አለብን የሚለውን ለማሳየት ብቻ ነው፡፡

የዴንማርክ ሀገር ትምህርት አሰጣጥ

ትምህርት ስንጀምር በአመት ሴሚስተራቸው አራት መሆኑን ተረዳን…አንድ ትምህርት ሁለት ወር አከባቢ ይቆያል…ከዛ ፈተና ነው…..ታዲያ ተማሪዎች የሚማሩትን መምረጥ ይችላሉ…እኔ ለምሳሌ ለማስተሬት ዲግሪዬ መማር ካለብኝ ኮርሶች ውስጥ ሶስቱን ብቻ ነበረ እንድወስድ የምገደደው…ሌሎቹን እኔ መምረጥ ነበረብኝ…ስለሆነም ከሶስት የግብርና ልማት ኮርሶች ውጪ ሌሎቹን ከአመጋገብ ስርአት መርጬ ተማርኩ….ይህ በጣም ቆንጆው የትምህርታቸው አካል ነው፣ በተጨማሪም ፕሮፌሰሮቹ እጅግ በጣም ነው ተማሪዎችን የሚንከባከቡት….ሁሉንም የተማሪን ጥያቄ ይመልሳሉ…ሲጠየቁም ደስ ይላቸዋል…ይህ ማለት ሰነፍ መምህራን የሉም ማለት አይደለም….  ትዝ ይለኛል አንዲት የደከመች መምህርም ነበረችን፣ ክፍል ገብታ እሳስቃን መሄድ የምትፈልግ፣ በትምህርቱ መጨረሻ ታዲያ በተማሪዎች ግምገማ ወርደውባታል…..

 

ዴንማርክ ከሁሉ ያልተመቸኝ ጉዳይ የቃል ፈተናቸው ነው…..አንድን ኮርስ በ10 ደቂቃ ቃለመጠይቅ ይጨርሱታል…. ፊትለፊት በመቀመጥ በቃል ፈተና…እኔ ያንን አይነት ፈተና በፍፁም ውጤታማ ሊያደርገኝ አልቻለም…. ፈተናው የእድል ወይ መምህሩ ወዶ ለተማሪው የሚሰጠው አይነት ነበረ….

 

የፅሁፍ የተፈተንኩት ሶስት ትምህርት ብቻ ነው …. ከሶስቱ አንዱ የ48 ሰኣት ፈተና ነበረ…. ፈተናውን ወደቤት ይዞ በመሄድ የሚቻለውን ሁሉ መረጃ መሰብሰብ ይቻላል፣ ነገር ግን መምህሩን መጠየቅ ነው የማይቻለው፡፡ ከባድ ፈተና ነው…ፈተናው የታተሙ የምርምር ስራዎችን ሂስ ማድረግ ነበረ፤ ጠንካራና ደካማ ጎኖችን ማውጣት፤ ሌላውም ደግሞ ኦፕን ቡክ የሚባለው መፅሀፍና ደብተር ከፍቶ ማንበብና መስራት የሚፈቀድበት ፈተና ነበራቸው፡፡  እነኚህ የወደድኩዋቸው ፈተናዎች ናቸው….

 

ሌላው የዴንማርክ ትምህርት ቆንጆ ነገር ተማሪዎች ልምድ እንዲያገኙ ብለው ወደሌላ ሀገር ለትምህርታዊ ጉዞ የሚወስዱት ነገር ነው….እኔ ትምህርቴ ግብርና ልማት ስለነበረ ታይላንድ ሀገር ወደሰሜን ታይላንድ ቻንግ ማይ ግዛት ባን ፓን ኢካ የሚባል ቀበሌ ውስጥ ስለ ማህበረሰብ አቀፍ ተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤና አጠቃቀም በተመለከተ ከታይላንድ ተማሪዎች ጋር አንድ ቡድን በመስራት አብሮ ፕሮጀክቶችን መስራት ነበረ፤ እጅግ አስተማሪ ነበረ….. ከታይላንድ ብዙ ተማርኩኝ…. ታይላንድ ቆንጆ ሀገር ናት፡፡ ብዙ ደን አላቸው…ብዙ ቱሪስት ወደታይላንድ ይሄዳል….እባብም፣ እንቁራሪትም፣ አይጥም፣ የጉንዳን እንቁላልም ይመገባሉ…..በተረፈ እንግዳ አክባሪ ናቸው…ትንሽ ደስ ያላለኝ ነገር እጅግ ብዙ ሴትኛ አዳሪዎች አሉ…አንድ ሆቴል ስንገባ በየወንበሩ 4 ወይ 5 የሴት አስተናጋጆች ቆመዋል…

 

ባንኮክ አየር ማረፊያ እንደደረስን የሴቶችን ፎቶና ስልክ ቁጥር የያዘ አልበም እያሳዩ የሚደልሉ ብዙ ሰዎች አይቼ በጣም ደነገጥኩኝ…..የኔ ሀገር በዚህ ጎኑ ከታይላንድ በጣም ትሻላለች፡፡ ሴተኛ አዳሪነት እኛም ሀገር ቢኖርም ያንን ያህል ደረጃ ግን እንዳልደረሰ እርግጠኛ ነኝ፡፡

 

ከታይላንድ መልስ ጀርመን የመሄድ እድልም አግኝቼ ነበረ….የጀመርመኑ ጉዞ ደግሞ ስለመመረቂያ ምርምሬ ኮንፈረንስ ላይ ለማቅረብና ከአውሮፓ ወጣቶች ጋር ስለትምህርትና ምርምር ለመወያየት ነበረ….ጀርመን ሀገር ስቱትጋርት ከተማ…..

 

የመጀመሪያው አመት የዴንማርክ ቆይታዬ በጣም ጥሩ ነበር፤ ቢሆንም የትምህርት ውጤቴ ያንን ያህል አመርቂ አልነበረም፣ ዋናው ምክንያቱ ደግሞ የፈተናው ሁኔታ የቃል ፈተና ብቻ መሆኑ ነበረ፤ ልጄና ባለቤቴም ከኔ ጋር ስላልነበሩም ሀሳቤ የተረጋጋ አልነበረም….

 

ዴንማርክ ሀገር ቢራ መጠጣት የተለመደ ነገር ነው….ለዛ ሀገር ሰው ቢራ ማለት ለሀገራችን ሰው ቡና እንደማለት ነው፤ ቡናም ከኛ የበለጠ  ነው የሚጠጡት፤ ያውም ስኳር የሌለው ቡና፣….. ዴንማርክ እንደደረስን የመጀመሪያው ሳምንት ስለሀገሩ እንድናውቅ ገለፃ ሲደረግልን፣ አርብ አርብ ቢራ በርካሽ ከተማሪዎች ጋር በተማሪ መዝናኛ መግዛትና መዝናናት እንደምንችል በዪኒቨርሲቲው መምህር ሲነገረን ምን አይነት ሀገር መጣን ብለን ነበረ፤ ምክንያቱም እንደሚታወቀው ሀገራችን ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ቢራ ተማሪዎች እንዲጠጡ ማበረታታት ነውር ነው….ዴንማርክ ደግሞ ጠጡ ተብሎ ይነገራል፡፡ የተለያየ ባህል፤ በተጨማሪም ዴንማርክ ሀገር ሴቶቹ ሁሉ ሲጋራ እንዲያጨሱ የተገደዱ ነው የሚመስለው….ሁሉም ማለት ይቻላል ያጨሳሉ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ሴት ልጅ ሲጋራ ስታጨስ ያየሁት ዴንማርክ ሀገር ነው፤ ወንዶችም ቢሆኑ ሀገራችን ብዙ አያጨሱም…በተለይ በተለይ ዴኒሾቹ አልኮል ሲጠጡ በጣም ነው ሚያጨሱት…..የሀገሬ ሴቶች በሲጋራው ሲታይ ከዴንማርክ ሴቶች ይሻላሉ….

 

ሌላው ዴንማርክ ሀገር በስውር የሚደረግ ነገር ግን የተስፋፋው የወጣቶች ችግር የሱስ ነገር ነው…ኮፐንሀገን ከተማ ብዙዎቹ የሀገሪቱ ህጎች የማይሰሩበት የከተማዋ ክልል አለ….ክሪስሻኒያ በመባል ይታወቃል፡፡ ሰፈሩ ከጦርነት የተመለሱ የሀገሪቱ ዜጎች ይኖሩበት እንደነበረ ይነገርለታል…ነገር ግን ራስን በራስ የማስተዳደር አይነት መብት አላቸው….እዛ ሰፈር ሀሽሽና ሌሎች ከባድ እፆች በአደባባይ ይሸጣሉ….ነገር ግን ይዞ መውጣት ያስቀጣል…. ለኮፐንሀገን የወጣቶች ሱስ መለከፊያ ቦታ እዛ ነው ማለት ይቻላል፡፡

 

የዴንማርክ ትምህርቴ ሌላው ለየት የሚለው ልምድ የዩኒቨርሲቲው ላይብራሪ አሰራር ነው….. ላይብራሪያቸው በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት መስጠቱ አይደለም….ቴክኖሎጂን በተመለከተ የተራቀቀ እንደሚሆን ከመሄዴም በፊት የምገምተው ነገር ነበረ፤ የሚገርመው ላይብራሪ ውስጥ ማንም ገብቶ መጠቀም መቻሉ ነው፤ ተማሪው ከፈለገ ወላጆቹን ይዞ መጥቶ ኮምፒውተር ከፍቶላቸው የተለያዩ ነገሮችን እንዲያነቡ ማድረግ ይችላል፡፡ በተጨማሪም አንዲት ተማሪ በትምህር ላይ እያለች ልጅ ብትወልድና ልጅዋ ከተወለደ በኋላ ቶሎ ወደትምህርት ብትመለስ ልጅዋን ይዛ ላይብራሪ መምጣት ትችለለች፤ ለዚሁ ተብሎም ህፃናት ይዘው ለሚመጡ እናቶች የተመቻቸ ወንበር ሰፊ ቦታና እንዲሁም ለልጆቻቸው መጫወቻ አሻንጉሊቶችና የልጆች መፅህት በላይብራሪው ውስጥ ይገኛሉ፤ ሌላው ደግሞ ላይብራሪ ውስጥ መነጋገርና አልፎ አልፎም መሳቅ ይቻላል፡፡ ተረበሽኩ የሚል ካለ ራሱ ቤት ማንበብ ይችላል ካልሆነም ደግሞ የመማሪያ ክፍሎች ውስት ማንበብ ይችላል አይነት ነው፤ አንዱን የላይብራሪ ሰራተኛ የድምፁ ነገር እንዴት ነው ለምን እንዲቀንሱ አትነግሩም ስለው ማንም ተማሪ ድምፅ እንደረበሸው አስተያየት የሰጠ የለም ብሎ ነገረኝ፡፡

 

የዴንማርክ ህዝብ ሲበዛ ዝምተኛ ህዝብ ነው፤ አንድ መኪና ሙሉ ሰው ሞልቶ ሲሄድ መኪናው ባዶ ነው የሚመስለው፤ ማንም ድምፁን ከፍ አድርጎ ሲናገር መስማት የተለመደ አይደለም፤ ይልቁንም ብዙ ሰዎች ወሬያቸው ከመፅሀፍ ጋር ነው፤ በብዛት ያነባሉ፤ ጋዜጣውን፣ መፅኀፉን ወዘተ…..

 

ዴንማርክ ሀገር ፕሮፌሰሩ በስማቸው ነው የሚጠሩት፣ ፕሮፌሰር እከሌ ብሎ ሰው መጥራት የተለመደ አይደለም….በስሙ ነው የሚጠራው…ከሀገራችን ጋር ሲታይ የነሱ ይሻላል፤ ምክንያቱም እኛ ሀገር በስም ልዩነት ማድረግ ሊመስልብን ይችላል፤ እነሱ ሀገር ግን ልዩነቱን ሰርተን እናሳያለን ማለት ይመስላል፤ እኛ ሀገር ፒኤች ዲ ስለተመረቀ ለምን ዶክተር እከሌ አላልከኝም ብሎ ቅር ሊሰኝ ይችላል፤ ጀርመኖች ደግሞ ዶክተር ፕሮፌሰር ኢንጂነር እከሌ ብለው እንደሚጠሩም ሰምቻለሁ፤ እኔ የዴንማርኩ ይመቸኛል፡፡

 

የዴንማርክ ሌላው ደስ የሚለው ጉዳይ ህዝባቸው የተወሰነ መሆኑና እያንዳንዱ ዜጋ፣ በስደት ከውጪ የመጣውንም ጨምሮ መሰረታዊ ፍለጎቶቹና ሰብአዊ መብቶቹ ይከበሩለታል፡፡ ለምሳሌ አንድ ልጅ ሲወለድ ለልጁ ማሳደጊያ መንግስት የተወሰነ ሀላፊነት ይወስዳል፤ ነፃ የትምህርት እድል ይሰጣል፤ ነፃ ህክምና እንዲሁም ለልጁ ወላጆች የገንዘብ ድጎማ ያደርጋል፤ ለወላጆች በወሊድ ወቅት /ለአባትም ለእናትም/ እስከ አንድ አመት የሚደርስ የወሊድ ፍቃድ ይሰጣል…. ዴንማርክ የተረጋጋ መንግስት ካላቸው ሀገራት አንዷ ናት ….በአለማችንም ላይ እጅግ ደስተኛ ሀገር ተብላ በተደጋጋሚ ተመርጣለች፤ ዋናው ምክንያት ይህ የተረጋጋና እምነት የሚጣልበት ዜጎቹን የሚንከባከብ መንግስት መኖሩና ወላጆች ያለስጋት ልጆቻቸውን ማሳደግ መቻላቸው፤ ከታመሙ በሰላም መታከማቸው ነው፡፡

 

ዴንማርክ ሀገር እንዳንዱ ልጅ መቼ እንደተወለደና የት እንደተወለደ ከማን እንደተወለደ ሲወለድ የነበረው ክብደትና ቁመት እንዲሁም የጤናው ሁኔታ ይመዘገባል፤ ልጁ እንደተወለደም መረጃው ወደማእከላዊ የመረጃ ማእከል ይላካል፤ የሞተ ሰውም ካለ እንደዛው ነው፤ ስለሆነም በማንኛውም ሰኣት ሀገራቸው ውስጥ ምን ያህል ሰው እንዳለ በቀላሉ መናገር ይችላሉ፤ እኛ ሀገር መታወቂያ ሳይኖረው የሚሞት ሽማግሌ ሊኖር እንደሚችል ስገምት ሀገራችን ምን ያህል ከአለም ርቃ እንደምትገኝና እንደሌሎቹ ለመበልፀግ የሰው ልጆቻችንን ሙሉ መረጃ መያዝና መንከባከብ እንዳለብን አስባለሁ፡፡

 

 

የሀገራችን አንዱና እጅግ ትልቁ ስህተት የሰው ልጆችንና ህጻናትን እንደሀብት አለመቁጠራችን ነው፣ ምክንያቱም መኪና ቢሆን ታርጋ ቁጥር ሰጥተነው ወዲያውኑ ነው የማን መኪና እንደሆነ የሚታወቀው፡፡ ዴንማርክ ሀገር የልጆችን መረጃ መመዝገቡ እስከ ወላጆችም ይደርሳል፤  ማንናውም የዴንማርክ ሀገር ነዋሪ ሰው አንድ የራሱ የሆነ መታወቂያ ቁጥር ይኖረዋል፤ ያ መታወቂያ ቁጥር ስለሰውየው፤ አድራሻ፣ የስራ ሁኔታ፣ የጤና ሁኔታ፣ ሀብት፣ ገቢ፣ ቀረጥ፣የባንክ ቁጥሩ፣ ቤተሰቦቹ፣ የትምህርት መረጃው፣ ወዘተ የያዘ ነው፡፡ የዴንማርክ ዜጋ መታወቂያ ካርድ የትም ቢሄድም አይቀየርም፤ ምክንቱም ያሰውየው መለያ ቁጥር ስለሰውየው ሙሉ መረጃ ከልጅነት ጀምሮ የያዘ ነው፤ በሀገራችን አንድ ሰው ከሀዋሳ አዲስ አበባ ሲገባ ሌላ መታወቂያ ወጣል፣ የሀዋሳ ታሪኩ ተረሳ ማለት ነው፡፡

 

በዴንማርክ ሀገር ሁሉም ዜጋ እኩል የተገመተበትን ቀረጥም ይከፍላል፤ ምክንቱም የያንዳንዱ ዜጋ ሀብትና ገቢ በትክክል ይታወቃልና፤ ይህንን በሀገራችን ጋር ሳወዳድረው ሀገራችን በጭለማ ውስጥ አይንን ጨፍኖ የመሄድ ያህል ችግር ያለባት ይመስለኛል፡፡

 

ምክንያቱም ለምሳሌ ሙስና በሀገራችን ውስጥ እጅግ አሳሳቢ ነገር መሆኑ ግልጽ ነው፤ ሙስና እጅግ አሳሳቢ ቢሆንም ሙስናን ለመከላከልና ሙስና የሚሰሩትን ፈልጎ ለፍርድ ለማቅረብ የባንክቤትና የዋና ዋና ንብረቶች ባለቤትነት መረጃ ስለሌለን አንድ ሰው በየባንኮቹና በየከተማው የፈለገውን ገንዘብ እየዘረፈ ቢያስቀምጥ ለምን አስቀመጥክ፤ ከየት አመጣሀው ብሎ የሚጠይቅ ምንም ስርአት የለንም፡፡

 

ሌላ ምሳሌ ልጨምር፤ እኔ ከተመቸኝ ሀዋሳ ከተማ ውስጥ ባሉት የኢትዮጵ ንግድ ባንክ ቅርንጫፎች ሁሉ የባንክ አካውንት መክፈት እችላለሁ፤ ከዛም በየቅርንጫፎቹ ገንዘብ ማስቀመጥ እችላለሉ፤ ካስፈለገም በየግል ባንኮቹ ሁሉ የባንክ ደብተር አወጣለሁ፤ ዘርፌ የማገኘውን ገንዘብ በታትኜ አስቀምጣለሁ፤ ካልሆነም ደግሞ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ አንድ ትልቅ ፎቅ እሰራለሁ፤ ከየት አመጣሀው?  ገቢህ ምንድን ነው? የፎቁ ቤትህ ኪራይ የገቢ ስንት ነው? ሀዋሳ ቤት አለህ ወይስ የለህም? ወዘተ ብሎ የሚጠይቀኝ ስርአት የለንም፡፡

 

አሁን ባለንበት በ21ኛው ክፍለ ዘመን፣ አንዲት ሀገር ዜጎችዋ ባንክ ቤት የሚያስቀምጡትን ገንዘብ ምንጭና በየከተሞቹ የሚሰራው ህንፃ ባለቤት እንዲሁም የያንዳንዱን ግለሰብ የገቢ ምንጭን ማወቅና መቆጣጠር አለመቻል፣ ሀገሪቱ አይኗን ጨፍና በጨለማ ውስጥ እየሄደች ነው ቢባል ማጋነን የሚሆን አይመስለኝም፡፡

 

ስለሆነም ተቀጥረው የሚሰሩ የሀገራችን ሰራተኞችና የተወሰነውን ያህል በከተማ ሱቅ ከፍተው የሚነግዱ ዜጎች የገቢ ቀረጥ ይከፍላሉ፤ መኪና ገዝተው የሚነግዱ፣ ፎቆችን የሚያከራዩ፣ ወይም ከወደገጠር ቦታ 100 ሰንጋ በሬዎችን በየሳምንቱ የሚነግዱ ነጋዴዎች፣ ሌቦችና ዘራፊዎች ሁሉ ሀብታቸውና ንብረታቸው እንዲሁም የገቢ ቀረጥ ሳይከፍሉ በአጭር ጊዜ ሀብታም ይሆናሉ፡፡

 

ግብር እኮ የሀገር መሰረታዊ ገቢ ነው፡፡

 

አሜሪካኖች ለሀገራችን እርዳታ ሲሰጡ ወይም ቻይናዎች ለሀገራችን ሲረዱ ወይም አውሮፒያዊያን ለኛ እድራታ ሲሰጡን ዋናው የገንዘብ ምንጫቸው ከህዝባቸው የተሰበሰበ ቀረጥ መሆኑን መረዳት አለብን፡፡ ሀገራችን ራስዋን ከውጪ እርዳታ ለማላቀቅ ከሁሉም ዜጎችዋ መሰብሰብ ያለባትን የገቢ ቀረጥ በትክክል መሰብሰብ መቻል አለባት፤ እንዲሁም ሙስናን ለማስቀረት ለሙስና የማይመች የባንክ አስራርና ኣያንዳንዱን ቋሚ ንብረት በተለይ መሬት፣ መኪና፣ ቤት፣ የእርሻ ቦታ ወዘተ በትክክል በባለቤቶቻቸው ስም መመዝገብና ከነጋዴውም ከአርሶ አደሩም ከደላላውም ከቤት ሰራተኛዋም…ከሚሰራው ዜጋ ሁሉም ላይ መከፈል ያለበትን ያህል ቀረጥ መሰብሰብ አለባት፡፡ ካልሆነ የመንግስት ሰራተኛ ብቻ የገቢ ቀረጥ በትክክል ከፍሎ ሌሎች ደግሞ ገቢያቸውን እየደበቁ በሚኖሩበት ስርአት ውስጥ ልማትን ማሰብ  ከባድ እንደሆነ ታሪካችን ምስክራችን ነው፡፡

 

 

100 ሚሊየን ህዝብ ይዘን ከ5 ሚሊየን ህዝብ እርዳታ የምንቀበልበት አንዱ ምክንያት የመንግስትን ግብር ከከፋዮች በትክክል መሰብሰብ አለመቻላችን ነው፡፡

 

የዴንማርክ ሀገር ሌላው ደስ የሚለው ነገር ፖለቲከኞቹ አምርረው አለመጣላታቸው ነው….ለምርጫ ሰሞን ብዙ ይከራከራሉ፤ ጋዜጣ ላይም ብዙ ይፅፋሉ፤ ቢሆንም የከፋ ጥልና ወደብጥብጥ መሄድ ብዙም የተለመደ አይደለም፡፡

 

የሀገራችን ፖለቲካም ሰላማዊ ይሆን ዘንድ ፖለቲከኛ እንደፈለገ የሚዘርፈውና የሚነካካው የገንዘብና ትቅማጥቅምን መዝጋት ያስፈልጋል፡፡ የሀገራችን ፖለቲከኞች እጅግ የሚጠላሉበት ምክንያት የፖለቲካ ወንበራቸው ከመጠን በላይ ጥቅም ስለሚሰጣቸውና ያንን ጥቅም አንዱ ለሌላው አሳልፎ መስጠት ስለማይፈልጉ ይመስለኛል፡፡ የፖለቲካ ስልጣኑ ህዝብን ማገልገል ቢሆንማ ደከመኝ ሰለቸኝ፤ እንተጋገዝ፤ ወዘተ የሚሉ የፖለቲካ ባለስልጣናትን እናይ ነበረ፤ የአፍሪካችን መሪዎች ስልጣን ላይ ነው የሚያረጁት፤ በጊዜ ለተተኪ ትውልድ ማስተላለፍ የሚባል ነገር የለም፤ ለምን ቢባል ቦታው ከባድ ጥቅም ስለአለው ነው፡፡

 

ሌላው ምክንያት ሊሆን የሚችለው ነገር መሪዎቻችን ስልጣን ሲለቁ አዲሶቹ መሪዎች ወደበቀል ስለሚገቡ ነው፤ የዚን አይነት አሰራር ግን ዘመናዊ እንዳልሆነ መረዳት አለብን፡፡ የሀገር መሪዎች ሀገራቸው ላይ ዋስትና ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ ምንም ክፉ ቢሆንም ሀገርን የሚያህል ነገር ሲያስተዳድር የኖረ መንግስት ከስልጣኑ መጨረሻ ሲደርስ ከለላና ዋስትና ከሌለው ምን ዋጋ አለው? አዲሶቹም ምሪዎች ፍርሀት ይወርሳሉ፤ ፍርሀት ደግሞ ራሰን ለመከላከል ዝግጅትን ይጠይቃል፤ ከዛም ጦርነት ያከተላል፤ ሀገርም ዋጋ ትከፍለነች፤ ድህነት ይስፋፋል፡፡

 

 

 

እስቲ ሴሪያን እንመልከት፤ ወይም ሊቢያን ምሳሌ እናድርግ፡፡ እነኚህ ሀገራት እኮ ሀብታም ሀገራት ነበሩ፤ ነገር ግን ፖለቲካቸው መቻቻል ስለጎደለው፣ ለሀገራቸው ውድቀት መስመር ሆነ፤ የዛሬው የሀገሬ ትውልድ አሁን ካለንበት አለም ብዙ መማርና አንዱ ለሌላው ይቅር በመባባል ፖለቲካውንም ሆነ ሌሎቹን ጉዳዮች ወደህዝብ ጥቅም መመለስ ያስፈልጋል፡፡ መቼም ሁሉም የሀገራችን ፖለቲከኞች የህዝብን ጥቅም ይጎዳሉ ብሎ ማሰብ ከባድ ነው፤ የጋራ ሀገራችን ስለሆነ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሀገራችን እንድትቀየርና ከሌሎች ሀገራት እኩል እንድትሆን እንደሚፈልግ ምንም ጥያቄ የለውም፡፡

 

ስለሆነም ወደስህተት የሚሄዱትን ወንድሞቻችንን ኣርቀን በማሰብ የሀገርንና የወገንን ተጠቃሚነት እያሰብን ወደሰላም መመለስ ያስፈልጋል፡፡ እኔ አሁን እስካለሁበት እድሜ ብዙ ልምድ አለኝ ብዬ በድፍረት ለመናገር አልችልም፤ ይህንን ፅሁፍ እንድፅፍ ብርታት የሚሆነኝ ግን ለራሴ ልጆችና ሌሎችም የሀገሬ ወጣቶች እንዲሁም ለሀገራችን ህዝቦች በሙሉ ሰላማዊና የተሻለች ሀገርን ለመፍጠር ያለኝን ያህል ላበርክት በሚል ሀሳብ ነው፡፡ ለውጥ ካስፈለገ፣ ዜጎች ለሀገራቸውና ለወገናቸው የሚቻላቸውን ማድረግ አለባቸው፤ እኔም የምችለውን ለማድረግ ሞከርኩ፡፡

በዴንማርክ ቆይታ የጉልበት ስራ ልምዳችን

የመጀመሪያ አመት የዴንማርክ ሀገር ትምህርቴ እንደተጠናቀቀ፣ ክረምቱን ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት ስራ ማፈላለግ ተያያዝኩኝ፡፡ እንደ እድል ሆኖ ደቡብ ዴንማርክ ወደሰሜን ጀርመን አንድ የአሜሪካን ድርጅት በጎመንዘር ላይ ምርምር ይሰራ ነበርና ሶስት ኢትዮጵያዊያን ስራውን አገኘን፡፡ ተያይዘን ስራው ቦታ በባቡር ሄድን፤ ከዛም የድርጅቱ ሀላፊ ከባቡር ጣቢያ ወሰደንና የምርምር ጣቢያው የሚገኝበት ቦታ ወሰደን፡፡ የምርምር ጣቢያው ገጠር ውስጥ ከከተማ ራቅ ብሎ ነው ያለው፡፡ የድርጅቱ ስም ዶው አግሮ ሳይንስስ የሚባል ሲሆን አድራሻውም ማሪቦ ከምትባል ከተማ ወደ ሶሊስትድ በሚወስደው መንገድ መካከል አቤድ ይባላል፤ ለሁለቱ ወር መኖሪያ የተሰጠን ቤት እዛው የስራቦታችን አከባቢ ያለ አንድ ባዶ ቤት ነበር፤ ቤቱ በአሞራ ክንፍ አይነት ከፍ ያለ ጣሪያ ያለው ሆኖ፣ ወደውስጥ ስንገባ ኮርኒሱ በመሰላል መወጣጫ ያለው መኝታቤት ተሰርቶለታል፣ ታዲያ ቤቶ ለብዙ ጊዜ ተዘግቶ የቆየ ቢሆንም መብራቱም ውሀውም ይሰራ ነበር፡፡ የዛን ቤት አሰራርና የኛ ሀገሩን የቤት ስራ ስናስተያይ፣ ኮርኒስን ከፍ አድርገን ብንሰራም፣ ለመኝታ ባይሆን ለእቃቤትም አለመጠቀማችን የቦታ አጠቃቀምን በተለመከተ ከዴንማርኮቹ መማር እንደምንችል ይሰማኛል፡፡ እኛ ቤትን ስናስብ እስከኮርኒሱ ያለውን ነው፡፡ የኮርኒሱን ውስጥ እንደመኖሪያ ቤት አድርገን ስንጠቀምበት አላጋጠመኝም፣ ያቺ እኛ የኖርንበት ቤት ግን ከውጪ ስትታይ ፎቅ አይደለችም፣ ውስጥ ስንገባ ግን በውስጥ በኩል የተሰራ ፎቅ ናት ማለት ነው…. የደቡብ ዴንማርክን የህይወት ልምድ ከቤቱ አሰራር ጀምረን ወደሚቀጥሉት ትዝታዎቼ እንሄዳለን፡፡  እዛ ገጠር ውስጥ ውሃም መብራትም ያለው ኦና ቤት መኖሩን እያደነቅኩ ስለዴንማርክ ሀገር ግብርናና ገበሬዎች ለማወቅ ክረምቱን ወደደቡብ ዴንማርክ መሄዳችን በጣም ምቹ ሁኔታን ፈጠረልን፡፡

 

ስራው ቆንጆ ክፍያ ቢኖረውም እጅግ ከባድ ነበረ፤ እኔ የከተማ ልጅ ነኝ ማለት አልችልም፤ በልጅነቴ ብዙ የግብርና ስራ ሰርቻለሁ፤ ከከብት እረኝነት እርሻ ማረስና እህል ማጨድ፤ መውቃት፣ ማታ ማታ በቆሎ ከከርከሮ መጠበቅ ወዘተ ብዙ የግብርና ስራዎችን ሰርቻለሁ፡፡

 

የዴንማርክ ሀገሩ የምርምር  ስራ ግን ኣንደኛ ክፍያው በሰአት ስለሆነ ከሻይ እረፍት በስተቀር ያለእረፍት በፍጥነት መስራትን የሚጠይቅ ነበረ፤ እኔ ግን ስራው በጣም ከበደኝ፤ ስራውን እየሰራሁ በራሴ ግን እበሳጭ ነበረ፤ ራሴንም እጠይቅ ነበረ፤ የክፍል ተማሪ ወዳጆቼ ወደእረፍት ሲሄዱ እኔ በእረፍት ወቅት ይህንን ከባድ ስራ ለምን እሰራለሁ ብዬ ራሴን ጠይቃለሁ፤ ይህንን ያህል ራሴን የማሰቃየው ገንዘብ ለማግኘት ነው ፤ እንዲህ ሆኜ ያገኘሁትን ገንዘብ ምን ላደርግበት ነው? ለልጄ ማሳደጊያ፤ ለወንድሞቼ ወይም ለእናትና ለአባቴ፤ለዘመዶቼ፣ ለደሀው የሀገራችን ህዝብ ? ወይም ሀገርቤት ቤት ለሰራበት ነው፣ ነገር ግን እኔ የተማርኩ ሰው ነኝ፤ የተማርኩ ስለሆንኩኝ ለመኖር የሚያስፈልጉትን ነገሮች በትምህርት ማግኘት አለብኝ….ታዲያ ለምን ራሴን ላሰቃይ፤ ይህ ጥያቄ ውስጤ ይመላለሳል፤ ስራውን መስራቴ የውዴታ ግዴታ ነው፣ ከሁሉ በላይ ገንዘቡን ነው የምፈልገው፣ ስራው የጉልበት ስራ ቢሆንም፣ ያገኘሁት ደግሞ በስለት ነው፡፡

 

ከብዙ ጊዜ ፍለጋ በኋላ የተገኘውን ስራ የግድ መስራት አለብኝ ብዬ ራሴን አበረታታሁ፡፡ ጠዋት 1 ሰኣት ስራ ጀምረን 3፡30 ላይ እረፍት እንወጣለን፤ ለእረፍት ቡናና ሻይ ይሰጠናል፤ ቤታችንም ቅርብ ስለሆነ ወደቤትም ሄደን ምግብ መብላት አንችላለን፡፡ ከ30 ደቂቃ እረፍት በኋላ ቶሎ ወደስራ መመለስ አለብን፡፡ እኔ እረፍት ወጥተን ስንመለስ የበለጠ ይደክመኛል፤ በእረፍት ላይ እያለንም እቅልፍ ሊይዘኝ ይሞክር ነበር፣ እንደምንም ዋጥ አድርጌ እሰራለሁ፤ 6 ሰኣት ለምሳ እንወጣለን፤ ምሳ በልተን አረፍ ስንል አሁንም እንቅልፋችን ይመጣል፤ ልክ ስምንት ሰአት ላይ ወደስራ ነው፤ ስራው እጅግ ያደክማል፡፡

 

ስራችን የነበረው በመስመር የተዘራ የጎመንዘር ሰብል ከወደቀበት አንስቶ ለአጨዳ ማስተካከል ነው፣ ለመታጨድ ሲደርስ ሰብሉ ትልልቅ ከመሆኑ የተነሳ አልፎ አልፎ ወድቋል፣ እንዲሁም ቅርንጫፎቹ ተያይዘዋል፤ ጎመንዘሩ በመስመር የተዘራ ሆኖ አንዱ መስመር ከሌላው ዘሩ ስለሚለያይ በተቻለመጠን በአጨዳም ወቅት ተለያይቶ ታጭዶ ተለያይቶ መወቃት አለበት፣ ስለሆነም ስራችን ጎመንዘሩን  በመኪና ለማጨድ እንዲመች መስተካከልና የወደቀውን ከፍ ከፍ በማድረግ፤ በመስመሮቹ መሀከል ክፍተት መስራት ነው፡፡ ቀኑን ሙሉ ጎንበስ ቀናው ወገባችንን አሳመመው፡፡

 

እንደምንም ብለን ከ3 ሳምንት በኋላ ስራውን ተለማመድነው፡፡ አንድ ቀን ስራ ቦታ ሙቀቱ ከብዶኝ በጣም እልቦኝ ነበረ፤ አብሮን የሚሰራ የዛው ሀገር ዜጋ የነበረ ገበሬ እንዲህ ሲል ጠየቀኝ፣  አንተ ልጅ ከአፍሪካ የመጣህ አትመስልም! ምነው እንዲህ አላበህሳ፣ አፍሪካዊያን እኮ የጉልበት ስራ አይከብዳቸውም ሲል ጠየቀኝ፤ ለምን ስለው ይህ ሁሉ ላብ እንዴት ነው፤ ሙቀት አፍሪካ የተለመደ አይደለም እንዴ ሲለኝ አይ እኔ ቀዝቃዛ አከባቢ ነው እድገቴ ብዬ ስንፍናዬን  አስተባበልኩ፡፡ ሰውየው ልምድ ስለላው፣ ብቻውን ከሶስታችንም በላይ ይሰራ ነበረ፡፡ ሀገራቸው በበረዶ ወቅት (ታህሳስ፣ ጥር፣ የካቲትና መጋቢት ወራት) እጅግ ቀዝቃዛ ሲሆን ክረምቱን (ሰኔ፣ ሀምሌና ነሀሴ ደግሞ) እጅግ ይሞቃል፡፡ በክረምት ፀሀይዋ ከቤትዋ ወደታች ዝቅ ብላ፣ በበረዶ ወቅት ያልሰጠቻቸውን ሙቀትና ብርሀን በክረምት ወቅት ለማካካስ አይነት ሀይል ነው ያላት፤ ታዲያ በሀገራችን ግብርና ስራ ወቅት፣ አንደኛ ቀስ ብለን እንሰራለን፣ ሁለተኛ ሲደክመንም ዛፍ ጥና ስር አረፍ ብለን እረፍት እንወስዳለን፣ ካልሆነም ጠዋትና ማታ ብቻ ሰርተን የቀኑን ፀሀይ እናሳልፋለን፡፡

 

በዴንማርኩ የግብርና የጉልበት ስራችን ወቅት ግን፣ ደከመኝ ብሎ መቀመጥ ነውር ነው፣ ምክንያቱም ደሞዝ የሚከፈለን በሰአት ነውና፣ ስራውን እየሰራሁም በመሀል ወይኔ ለአባቴ እንደዚህ ሰርቼ ቢሆን፣ እንዲሁም የሀገራችን የስራ ባህል በዚህ ፍጥነት ቢሰራ ኖሮ አባቴም የሀገራችን ገበሬዎችም ከድህነት በቀላሉ ይላቀቁ ነበር የሚል ሀሳብ ይመጣብኝና ነገር ግን የሀገራችን ገበሬ ስራውን በብዛት በሰውና በከብት ጉልበት እንጂ በቴክኖሎጂ በታገዘ አይሰራም፡፡ ዴንማርክ ሀገር ግን በሰው ጉልበት የሚሰራው ስራ የግብርናው ስራ እጅግ ጥቂት ነው፡፡ አብዛኛውን ስራ የሚሰሩት በዘመናዊ ማሽኖች ነው፡፡ ስለሆም አንድ ገበሬ በቀን የሀገራችንን 100 ገበሬዎች በላይ ስራ ሰርቶ ይውላል፡፡

 

የሆነ ሆኖ፤ ቀስ በቀስ ሀገሩንም ስራውንም እየተለማመድን ስንሄድ ቤንትና ኒክ ከሚባሉ የአከባቢው ነዋሪዎች ተዋወቅን፤ ቤንት በጣም ተግባቢ ሰው ነው፤ ከስራ መልስና ቅዳሜና እሁድ ከነሱ ጋር ማሳለፍ ጀመርን፤ የነሱንን ቋንቋ መናገር መለማመድ ጀመርን፤ ስለሀገራቸውም ከነሱ መስማት ጀመርን፤ በተለይ ቤንት ስለሀገራችን ታሪክና የቱሪስት መስቦች የማወቁ ጉጉት ከፍተኛ ነበር፣ አማርኛ ለመናገርም ብዙ ሙከራ እያደረገ ነበረ፡፡

 

የዴንማርክ ገበሬና የግብርናው አሰራር በሀገራችን የመንግስት ሰፋፊ እርሻዎች ማለት ነው፤ አንዱ ገበሬ እስከ 300 ሄክታር መሬት ነው የሚያርሰው፤ ስሆነም ገበሬው የራሱ ትራክተሮች፣ የራሱ ኮምባይነሮች፣ የራሱ መኪናዎች ወዘተ አሉት፡፡ በተጨማሪም የዴንማርክ ገበሬዎች ከምርት ስብሰባ በኋላ ምርታቸውን በአንድነት ሰብስበው የሚያስቀምጡበት የጋራ ጎተራ አላቸው፤ ምርቱ የገበሬዎቹን ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ በመአከላዊነት በገበሬዎች ቡድን ይሸጣል፡፡  የዴንማርክ ገበሬዎች በአውሮፓ እጅግ የተሳካላቸው ገበሬዎች ናቸው፤ በአውሮፓ ኢኮኖሚያቸውን በዋናነት ግብርና ላይ በማተኮር ያሳደጉት ሀገራት ዴንማርክና ኔዘርላንድ ብቻ መሆናቸውን ደቨሎፕመንት ኢኮኖሚክስ የሚባል ኮርስ ያስተማረን ፕሮፌሰር ነግሮናል፡፡ ነገር ግን ግብርናቸው እጅግ የተራቀቀና እያንዳንዱን የግብርና ጥሬ እቃ ወደኢንዱስትሪ በማስገባት እጅግ አትራፊ እንዲሆን አድርገው ወደገበያ ያቀርቡታል፡፡

 

የሀገራችንን ግብርና ባህሪ ስናይ በአብዛኛው ለኢንዱስትሪ ጥሬ እቃ የሚሆኑትን ቆዳ፤ የቅባት እህሎች፣ ጥሬ ቡና ወዘተ በቀጥታ ወደውጪ መላክ ነው፡፡ ሀገራችን ከዴንማርክ የግብርና ታሪክ መማር የምትችለው ከሁሉ በፊት ገበሬዎቻችን ጠንካራ ህብረት ኖሮዋቸው መሬታቸውን በተበጣጠሰ መልኩ ሳይሆን በግብርና ባለሙያዎች እገዛ ለሚኖሩበት አከባቢ ይበልጥ ተስማሚ የሆነው የግብርና ምርት ከተመረጠ በኋላ መሬታቸው በትራክተርና ዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም እንዲችል መደረግ አለበት፡፡ በተጨማሪም ለተመረጡት የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች ምርቶቹ የሚመረቱበት አከባቢ መሆን አለባቸው፡፡ በተጨማሪም ጠንካራ እምነት የሚጣልበት የገበሬዎች ህብረት ያስፈልጋል፡፡ እስካሁን ባለው ልምዳችን የሀገራችን ገበሬዎች ጠንካራና እምነት የሚጣልበት ህብረት መፍጠር አልቻሉም፡፡ በደርግ ጊዜ ተጀመሮ ነበረ ሲባል የሰማነውም የገበሬዎች/ የአምራቾች/ የህብረት ስራ ማህበራት በከፍተኛ ሙስናና ብልሹ አሰራር የተጋለጡ እንደነበረ እንረዳለን፡፡ የገበሬዎቹን ህብረት ደካማ ከሚያደርጉት ጉዳዮች አንዱ የገበሬዎች ህብረት አባላቱ በአብዛኛው ያልተማሩ መሆናቸው ነው፡፡

 

ደቡብ ዴንማርክ ለክረምት ስራ ሄጄ በነበረበት ወቅት ከእለታት አንድ ቀን አንድ የዛ ሀገር ገበሬ የስንዴ ምርቱን በመኪና እያጨደ ነበረ፤ እኔም አብሬው መኪናው ውስጥ ገብቼ ገበሬው ምርቱን እየሰበሰበ ስለስንዴው ምርት ብዛት ጥራት ከመኪናው ላይ እያየ ይነግረኝ ነበረ፤ ምርቱን የሚሰበስብበት መኪና እጅግ ዘመናዊ ከመሆኑ የተነሳ ገበሬው ስንዴውን እየሰበሰበ ምርቱ በአንድ ካሬ ሜትር ምን ያህን እንደሆነና በስንዴው ውስጥ ያለው እርጥበት በመቶኛ ከመኪናው ላይ በየጊዜው ያነባል፤ ስለሆነም ገበሬው የትኛው የእርሻው ክፍል የአፈር ለምነቱ ቆንጆ እንደሆነና የትኛው ጋር የበለጠ ማዳበሪያ መጠቀም እንዳለበት ምርቱን እየሰበሰበ መረጃ ይወስዳል፤ በተጨማሪም የሚሰበሰበው ምርት እርጥበት ካለው በጎተራ ውስጥ ስለሚበላሽ ምን ያህል ሙቀት መጠቀም እንደሚያስፈልገው ለመረዳት ያግዘዋል፡፡  ከገበሬው ጋር መኪናው ውስጥ ሆኜ የሀገራችን ገበሬ እንዴት እዛ ደረጃ ሊደርሱ እንደሚችሉ እያሰላሰልኩ ነበረ፤ የሀገራችን ገበሬ መቼ ያንን አይነት ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ሳስበው ከሁሉ በፊት አሁን ያለው የመሬት ይዞታና የእርሻ ሁኔታ መስተካከል እንዳለበት ተረዳሁ፡፡

 

ምክኒያቱም አብዛኛው የሀገራችን ገበሬ የእርሻ መሬት ከአመት ወደ አመት ለልጆችና ለልጅ ልጆች ሲከፋፈል  የመሬቱ ስፋት እየጠበበና ለዘመናዊ እርሻ አመቺ ወደማይሆንበት ደረጃ ይደርሷል፤ ስለሆነም የሀገራችን ገበሬዎች ብቸኛው አማራጫቸው መሬታቸውን በማዋጣት ህብረት ፈጥረው ዘመናዊ ግብርና የሚጠቀሙበት መንገድ መመቻቸት አለበት፡፡ የገበሬዎች ህብረት መፍጠር ቀላል አይደለም፤ ነገር ግን ገበሬዎቹ አሁን ባለው የመሬት አስተራረስ ዘዴ ከድህነት መውጣትና ሀገርን መመገብ የማይችሉበት ሁኔታ እየተፈጠረ ነው የሚሄደው፤ ግብርና መልማት ካለበት የግድ ዘመናዊ ቴክኖሎጊ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡

 

ባደጉት ሀገራት በግብርና ስራ ላይ የተሰማራው የሰው ሀይል ከ10 በመቶ አይበልጥም፤ የተቀረው 90 ከመቶ በፋብሪካዎች፣ በትምህርት፣ በአገልግሎት ዘርፍ የተሰማራ ነው፤ የሀገራችን ግብርና ደግሞ አሁን ባለው ሁኔታ ከ70 በመቶ በላይ ህዝብ ነው እየሰራው ያለው፤ ቢሆንም ውጤታማነቱ አነስተኛ ነው፡፡ ቀላል ምሳሌ፣ አንድ ገበሬ በትራክተር ሲያርስ በቀን ምን ያህል መሬት አርሶ እንደሚውል አስቡት እስቲ፤ ተመሳሳዩን ስፋት ያለውን መሬት በበሬ ለማረስ የብዙ ገበሬዎችን ጉልበት መጠየቁ ግድ ይላል፤ ስለሆነም ዘመናዊ ያልሆነ ግብርና የገበሬዎቹን ምርታማነት ይቀንሰዋል፡፡

 

 

 

በደቡብ ዴንማርክ ያሉት የዴንማርክ ገበሬዎች ብዙዎቹ የስኳር ድንች ያመርታሉ፤ ምርታቸውንም እዛው አቅራቢያ ለሚገኝ የስኳር ፋብሪካ ይሸጣሉ፤ ፋብሪካው ለገበሬዎቹ የስኳር ድንች ምርት ዋስትና ሰጥቶዋቸዋል፤ ስለሆነም ገበሬዎቹ የዘሩት የስኳር ሰብል ቢበላሽ ወይም የስኳር ዋጋ ቢቀንስ ፋብሪካው ከገበሬዎቹ በተወሰነ ዋጋ ሊገዛቸው ስምምነት አላቸው፡፡ ይህንን ያህል ርቀት መሄድ ለሀገራችን ገበሬዎች ብዙ ዘመናት የሚፈጅ ጉዳይ ነው፡፡ ነገር ግን ያንን ያህል ርቀት መሄድ ይቻላል ብለን ማሰብ አለብን፡፡ አስበንም መንገዱን መጀመር አለብን፡፡ ሀገርን ማሳደግ የአንድ ትውልድ ብቻ ሀላፊነት አይሆንም፣ ነገር ግን የአሁኑ ትውልድ ለተተኪው ትውልድ መንገዱን መጀመር አለበት፡፡

 

እዛው ደቡብ ዴንማርክ እያለን ምርት ተሰብስቦ የእርሻ መሬታቸው ባዶውን ባለበት የበጋ ወቅት ከከተሞች የመፀዳጃ ቤት ቆሻሻ አምጥተው በማሳቸው ላይ ከአፈሩ ጋር ይቀላቅሉ ነበረ፡፡ ለዚሁ ስራም የተዘጋጀ መኪና አላቸው፡፡ መኪናው መሬቱን እያረሰ ፍሳሹን ያፈሳና መልሶ በአፈር ያለብሰዋል፡፡ ይህ ፍግ መሆኑ ነው፡፡ ጀርመን ሀገር ስቱትጋርት ከተማ ለኮንፈረንስ በሄድን ጊዜ ከወተት ላሞች በረት ፍሳሽ በመጠቀም ትልቅ የባዮጋስ የኤሌክትሪክ ማመንጫ  አስጎብኝተውን ነበረ፤ ተመሳሳይ ቴክኖሎጂ በአርብቶ አደር የሀገራችን ክፍሎች ቢሰራ የብዙ የገጠር ከተሞችን የመብራት ችግር የሚፈታ ይመስለኛል፡፡

 

እዛው ደቡብ ዴንማርክ ዶው አግሮ ሳይንስ በምንሰራበት ወቅት ድርጅቱ ከተለመደው የሰራተኞች ቁጥር በላይ ሶስት ተጨማሪ ሰራተኞችን/እኛን/ ስለቀጠረ የደረጃና ድርጅት ተቆጣጣሪዎች ባስቀመጡት መመሪያ መሰረት ጊዜያዊ መታጠቢያ ክፍል በኪራይ ማስገባት ነበረባቸው፤ ለመታጠቢያው ክፍልም ሲባል ድርጅቱ ብዙ ገንዘብ እንደሚከፍል ተነገረን፤ ይህ የሚያሳየው ማንኛውም ቀጣሪ ድርጅት ለሰራተኞቹ የሚያስፈልገውን መሰረታዊ የደህንነትና ሌሎችን አገልግሎቶች ማሟላት የግድ ስለሆነ ነው፡፡ በተጨማሪም ድርጅቱ ለሰራተኞቹ የስራ ጫማ፣ የእጅ ጓንትና መነፅር እነዲሁም የፀሀይ መከላከያ ኮፊያና ካፖርት መስጠት የግድ ነበረ፡፡

 

ይህንን ከሀገራችን የሰራተኞች የስራ ቦታ ደህንነት ጋር ለማነፃፀር አዲስ አበባ የታዘብኩትን እንደምሳሌ ልጥቀስ፡፡ ቦታው ከጎተራ ወደቄራ በሚወስደው መንገድ ላይ ከንግድ ባንኩ ዝቅ ብሎ በግራ በኩል ሲሚንቶ የሚሸጥበት ቦታ አለ፤ እዛ ሲሚንቶ መሸጫ ውስጥ የሚሰሩት ሰራተኞች ከሰአት በኋላ ሲታዩ ፀጉራቸው፤ ቅንድባቸው፣ የአይናቸው ሽፋሽፍት፣ አፍንጫቸው…በአጠቃላይ ፊታቸው በሲሚንቶ ብናኝ ተሸፍኖ ማየት የተለመደ ነው፤ ነገር ግን እዛ ቦታ ላይ የሚሰሩት ሰራተኞች ደህንነት በተለይ የሲሚንቶ ብናኝ ወደሳምባቸው ገብቶ ሊመጣባቸው የሚችለውን የጤና ጠንቅ ማሰብ ይቻላል፤ የሰራተኛ ደህንነት ቁጥጥር ማለት እነኛን ሰራተኞች ቀጥሮ የሚሰራው ድርጅት ከሁሉ በፊት የሰራተኞቹን ደህንነት ማረጋገጥ እንዲችል ማድረግ ማለት ነው፡፡

 

ሌሎች ብዙ ተመሳሳይ ምሳሌዎችን መጥቀስ እንችላለን፡፡ በሀገራችን የስራ ቦታዎች የመታጠቢያ ክፍልና ሽንትቤት እዲሁም ለሰራተኞች ደህንነት የሚያስፈልጉ ነገሮችን መሟላት የሚከታተል የመንግስት መስሪያቤት ያስፈልጋል፤ ምክንያቱም ትክክለኛ ጥንቃቄ ሳይደረግ የሚሰራ ስራ ሁሉ መጨረሻው የሰው ህይወትና ጤና መጎዳት ነው፡፡ ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ የሚባለውም ለዚሁ ነው፡፡ እዛው የክረምት ስራ ቦታ ከሰራናቸው ስራዎች አንዱ የተሰበሰበውን ምርት በማሽን ገለባውን ከዘሩ የመለየት ስራም ነበረበት፡፡ ማሽኑ ድምጽ ስለነበረው ለጆሮአችን ደህንነት ተብሎ የውጪውን ድምጽ የሚቀንስልን የድምፅ መከላከያም ተገዝቶልን ነበረ፡፡ ያንንም ስራ እየሰራሁ በሀገራችን የእህል ወፍጮቤት ሰራተኞችን እያሰብኩ ነበር፤ እዛ ሁሉ የሚጮህ ማሽን ውስጥ እየሰሩ፣ ያሁሉ የእህል ዱቄት ባለበት ክፍል ውስጥ ምንም የአቧራና የድምጽ መከላከያ አለመኖሩ፣ ስለሰራተኞች ደህንነት መስራት ያለብንን የቤት ስራ ብዛት አስቤ፣ አንድ ቀን ሀገራችንም ተመሳሳይ የስራ ቦታ ህግ እንደምታወጣ ተስፋ በማድረግ ራሴን አሳምን ነበረ… ይህንን መጽሀፍ ለመፃፍ ከሚያነሳሱኝ ጉዳዮች አንዱም ይህኑን የሀገራችንን የስራ የወደፊት የልማት አቅጣጫ ከሌሎች ሀገራት ካየሁት ጋር በማስተያየት ለነገው ትውልድ ልምዴን ለማካፈል ነው፡፡

ሲራሮና የብላቴ ወንዝ

ከደቡብ ዴንማርክ ተመልሰን የሁለተኛ አመት ትምህርት ከጀመርን በኋላ ለምርምር ስራ ወደሀገራችን መመለስ ነበረብኝ፤ ለምርምሩ የሚያስፈልገውን ገንዘብ በአጭር ጊዜ ተሰጥቶኝ ህዳር ወር መጨረሻ ላይ ወደኢትዮጵያ መጣሁ፡፡ ለምርምሬ አማካሪ የነበረችው የዴንማርክ ዜጋ ጂማ ዩኒቨርሲቲ ምርምር የነበራት ሲሆን ለኔ ምርምር ስራ የተሻለ አማካሪ መሆን እንደምትችል ተነግሮኝ ሳናግራት ፈቃደኛ ሆነች፡፡ ምርምሬንም የሰራሁትም ከሻሸመኔ ወደ አላባ በሚወሰደው መንገድ አጄን አልፎ ወደግራ 17 ኪሎ ሜትር አከባቢ ገባ በማለት በሚገኘው የሴራሮ ወረዳ ውስጥ ነው፡፡

 

ምርምሩ በእናቶችና ህፃናት አመጋገብና ጤንነት ጋር የተያያዘ ነበረ፤ በወቅቱ ሴራሮ ወረዳ የነበረው የምግብ ችግር የሚያሳቅቅ ነበረ፤ በተጨማሪም የአከባቢው ነዋሪዎች ውሃ የሚቀዱት ከብላቴ ወንዝ ነው፤ የወንዙን ውሀ ለመቅዳትም እስከ 5 ኪሎሜትር ድረስ በእግራቸው ይሄዳሉ፤ ቢሆንም አከባቢው በቤት እንሰሳት ምርት የተሻለ ነበረ፡፡ በጣም ደስ የሚለው ነገር የምርምሬ አማካሪ የነበረችው የዴንማርክ ዜጋ ስራዬን ለማየት መስክ ድረስ አብራኝ ሄዳለች፤ ይህ ጉዳይ የሀገራችንን የድህረ ምረቃ ተማሪዎች የአማካሪ መምህራን  አሰራር ጋር ሲነፃፀር የኛ ሀገር አማካሪዎች አይደለም መስክ ድረስ መሄድ የተላከልንንም ፅሁፍ ለማንበብ ተለምነን ነው፤ አንድ በሀገር ውስጥ የፕኤች ዲ ዲግሪ ተማሪ የነበረ ወዳጄ እንደነገረኝ በሀገራችን የድህረ-ምረቃ ትምህርትን እጅግ አስቸጋሪ ከሚያደርጉት ነገሮች ውስጥ አንዱ አማካሪ መምህራን የተማሪዎቻቸውን ስራ በቅርበት ለመከታተል በጣም አነስተኛ ጥረት ማድረጋቸውን ነው፡፡ ከዚህም የተነሳ በአሁኑ ጊዜ በሀገራችን ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የጥናታዊ ፅሁፍ ኩረጃና ንግድ እየተካሄደ እንደሆነ ተማሪዎች የሚሰጡን ጥቆማ ያሳያል፡፡ ይህን ችግር የሀገራችንን የትምህርት ጥራት እየጎዳ መሆኑን አውቀን ጉዳዩ የሚመለከተን ግለሰቦችና ተማሪዎችን በቅርበት በመከታተልና በመደገፍ የሚቻለንን ጥረት ማድረግ አለብን፡፡

 

በምርምሩ ወቅት ካጋጠመኝ ችግሮች መካከል መረጃ እንዲሰበስቡልን የተቀጠሩት ሰራተኞች ቃለመጠይቅ ሳያደርጉ ጥያቄዎቹን በራሳቸው ሞልተው መምጣታቸው ነበረ፤ ይህ ችግርም በሀገራችን የሚሰበሰቡ መረጃዎችን በሙሉ ታማኝነታቸውን ዝቅ እንደሚያደርገው ግልፅ ነው፡፡

 

በሁለተኛው አመት የዴንማርክ ቆይታዬ ለምርምር ስራ ወደኢትዮጵያ መጥቼ በነበረበት ወቅት አንድ ወዳጄን አዲስ አበባ አገኘሁት፤ እኔ ወደ ዴንማርክ ስሄድ ልጁ በግሉ ለመስራት ድርጅት እያቋቋመ ነበረ፡፡ ልጁ በሁለት አመት ጊዜ ውስጥ ቤት ገዝቶ ጠበቀኝ፤ ቢሆንም ወዳጄ ወደውጪ ሄዶ መስራት እደሚፈልግ ነገረኝ፤ እጅግ ነው የደነገጥኩት፡፡ ሁለት አመት በማይሞላ ጊዜ ውስጥ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ቤት መግዛት የሚያስችል ድርጅት እያለው ውጪ ሀገር ሄጅ መስራት እፈልጋለሁ የሚል ሀሳቡ እጅግ የተሳሳተ መሆኑን አስረዳሁት፡፡ እኔ ከማገኘው የስኮላርሺፕ ገንዘብ እየቆጠብኩና የክረምቱን ሁለት ወራት ሰርቼ የቆጠብኩት ገንዘብ እንኳን ቤት ሊገዛ ይቅርና ለ5ወር ኪራይ አይችልም ነበረ፤ ስለሆነም ብዙ የሀገራችን ወጣቶች በተለይ ደግሞ እዚህ ሀገር ሰርተው መለወጥ የቻሉት ለምን የውጪ ሀገር ህይወት እንደሚናፍቃቸው አይገባኝም፡፡ ከወዳጄ ጠይቄ የተረዳሁት ነገር ገንዘቡ የሚገኝበት መንገድ ብዙ ሙስና ስላለበት እንደሆነ ነገረኝ፤ ቢሆንም በሁለት አመት ቤት  መግዛት የቻለ ድርጅት ያለውን የሀገሬን ወጣት ምንም ቢሆን ውጪ ሀገር ብትሄድ የተሻለ ኑሮ ትኖራለህ ብሎ መምከር ትልቅ ስህተት ነው፡፡

 

የምርምር ስራዬን ጨርሼ ወደዴንማርክ ስመለስ ባለቤቴንም ወስጄ ሀገሩን አይታ መመለስ እንዳለብን ተስማምተን ሄድኩ፡፡ ዴንማርክ እንደደረስኩ ቤተሰቤን ማምጣት እፈልጋለሁ ብዬ አመለከትኩ፤ ፕሮሰሱም ቶሎ ተጠናቀቀ፤ ባለቤቴና ልጄ ቪዛ ተሰጣቸው፤ ቢሆንም አሁንም የገንዘብ አቅሜ በቂ ስላልሆነ የክረምቱን ስራ ማጠያየቅ ጀመርኩ፤ ባለፈው ክረምት የሰራንበት ድርጅት ሊያሰራን እንደሚፈልግ ተነገረን፡፡

 

 

የስራውን ክብደት ባውቀውም ገንዘቡን ስለምፈልገው ሳላመነታ ስራውን እሺ ብዬ ተቀበልኩ፡፡ የክረምቱን ስራ ጥርሴን ነክሼ ሰራሁ፤ ቢሆንም ለሶስታችን የሚሆን የመኖሪያ ቤት በቀላሉ ማግነት አልቻልኩም፡፡

 

የውጪ ሀገር ህይወትን ከባድ ከሚያደርጉት ነገሮች አንዱ የመኖሪያ ቤት ጉዳይ ነው፡፡ ርካሽ የኪራይ ቤት ለማግኘት ቤቶች የሚያከራዩ ድርጅቶች ጋር ማመልከቻ ማስገባትና ተራ መጠባበቅ ያስለፍጋል፤ የተራው የመጠበቂያ ጊዜ እስከ አንድ አመት ሊሆን ይችላል፤ እኔም የቤቶች ድርጅት ጋር አመለከትኩ፡፡ በሆንም ልጄና ባለቤቴ ከመምጣታቸው በፊት ማግኘት አልቻልኩም፡፡ ቤት ሳይገኝ እነሱ ወደዴንማርክ መጡ፤ ስለሆነም መጀመሪያ እኖርበት የነበረው የተማሪዎች መኖሪያ ውስጥ ለሶስት መኖር ጀመርን፡፡ በዴንማርክ ህግ ለአንድ ሰው የተሰራ ቤት ውስጥ ከአንድ ሰው በላይ እንዲኖር አይፈቀድም፤ በድብቅ መኖር ይቻላል፤ ነገር ግን በተመሳሳይ አድረሻ ለመመዝገብ ነው የማይቻለው፡፡ ነገር ግን ማንኛውም ህጋዊ ሆኖ የሚኖር ግለሰብ ልጆችንም ጨምሮ የየራሱ የመታወቂያ ቁጥርና አድራሻ ያስፈልገዋል፡፡ ቤተሰቤ በሰላም ወደዴንማርክ መጥተው  መታወቂያ ቁጥርና ለምዝገብ መዘጋጃቤት የሄድን ቀን ያስተናገደኝ ባለሙያ ደግ ሰው ነበረ፤ ቤቱ ለአንድ ሰው የተሰራ መሆኑን ቢያውቅም ቤት ለመከራየት ተመዝግቤ እስካሁን እየጠበቅኩ ነው ስለው ሶስታችንንም በዛው በአንድ ክፍል ቤት አድራሻ ተመዘገብን፡፡ ተመዝግበን ወደቤታችን ተመልሰን ለወዳጆቻንን ስንነግራቸው እጅግ ሲበዛ እድለኖች ናችሁ ተባልን፤ ምክንያቱም ለአንድ ሰው አድራሻ ሶስት ሰዎችን መመዝገብ የተለመደ ስላልሆነ ነው፡፡

 

የተማሪዎቹ ዶርሚተሪ ለ16 ተማሪዎች የተዘጋጀ ነው፡፡ 16ቱ ተማሪዎች የየራሳቸው ክፍሎች ያላቸው ሲሆን ማብሰያው ክፍል ግን የጋራ ነው፤ የማብሰያ ክፍሎቹ ውስጥ ያሉት እቃዎች በሙሉ የድርጅቱ ናቸው፤ ተማሪዎች አንዱን ማቀዝቀዣ ለሁለት ወይም ለሶስት ይጠቀሙታል፡፡ ተማሪዎቹ ከጀርመን፣ ከፈረንሳይ፤ ከፖላንድ፣ ከሩሲያ፣ ከስፔን፣ ከአይስላንድ፣ ከጣሊያንና ከቻይና ሀገራት የመጡ ነበሩ፡፡

 

ስለሆነም ምግብ ማብሴያው ክፍል ውስጥ የተለያዩ ሀገራን የምግብ አበሳሰል ማየት የተለመደ ነው፤ ከሁሉም ግን የሀገራችን የዶሮ ወጥ አሰራር የብዙዎቹን ቀልብ የሚስብ ነበረ፤ በተለይ ከፈረንሳይ የመጣች ተማሪ ለዶሮው መስሪያ የተዘጋጀውን የሽንኩርት ብዛት በማየት ተገርማ ነበረ፡፡

 

ታማኝነት

ስለዴንማርክ በጎ ነገሮች ዘርዝሬ ለመጨረስ ያስቸግረኛል፤ ከዋና ዋናዎቹ ውስጥ ለምሳሌ በኮፐንሀገን ዩኒቨርሲቲ ያስተዋኩትን ልጥቀስ፤ በዩኒቨርሲቲው ላይብረሪ ውስጥ ተማሪዎች እያነበቡ ሲደክማቸው ወይም የረሃብ ስሜት ሲሰማቸው አትክልት፣ ቡና፣ ለስላሳ መጠጦች፣ ውሃ፣ ቸኮሌት ወዘተ መግዛት ይችላሉ፡፡ ቡና፣ ለስላሳና ቸኮሌት የመሳሰሉትን ከማሽን ስለሚገዙ ዝርዝር ሳንቲም ወደማሽኖቹ በማስገባት መግዛት ይቻላል፤ የሚገርመው የአትክልት አገዛዙ ሁኔታ ነው፡፡ አንድ ተማሪ ሙዝ መግዛት ቢፈልግ ላይብረሪው ውስጥ መግቢያ በር አከባቢ እንግዳ መቀበያው ጋር የአትክልት ቅርጫት አለ፤ ቅርጫቱ አጠገብ የሳንቲም ማስቀመጫ ትንሼዬ ሳጥን አለ፤ ለምሳሌ አንድ ሙዝ ዋጋው 2 ብር ከሆነ ተማሪው ሁለት ብሩን ሳጥኑ ውስጥ አስቀምጦ ሙዙን ወስዶ ይሄዳል፡፡ ይህንን ሲያደርግ ማንም አያስተናግደውም፡፡

 

ተማሪው በታማኝነት ነው ራሱን የሚያስተናግደው፡፡ ከእለታት አንድ ቀን እኔም ሙዝ መግዛት ፈለግኩ፤ ሙዙን ልገዛ ስሄድ ኪሴ ውስጥ የበረው 10 ብር ነበረ፤ የአንድ ሙዝ ዋጋ 2 የዴንማርክ ብር ነው/ሰባት የኢትዮጵያ ብር ገደማ ማለት ነው/፤ አንድ ሙዝ ወስጄ አስር ብር አስቀመጥኩኝና ስምንት ብር መልስ ወስጄ ወደመቀመጫዬ ሄድኩ፤ ነገር ግን ማንም አስተናጋጅ በቦታው ስለሌለ ገንዘብ ሳልከፍል ሙዙን ብቻ የወሰድኩ እደዳይመስላቸው፣ መቼም የጥቁር ነገር አያምርም፤ ሁላችንንም ሌቦች አድርገው ነው የሚቆጥሩን፡፡

 

 

 

 

 

እስቲ ይህንን ሀሳብ ወደሀገራችን ላይብራሪ እናምጣ፤ ተማሪዎች ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተናግዱበትን የአትክልት መግዛት አገልግሎት ብንጀምር ምን የሚፈጠር ይመስልዎታል፤ መልሱ ግልፅ ነው፤ ተማሪዎቻችን ሙዙን ብቻ ወስደው ገንዘብ ሳያስቀምጡ ይሄዳሉ….ቀስ በቀስም የተቀመጠ ገንዘብም ካለ የሚሰርቁት ይመስለኛል፡፡ ፍራፍሬው ከሌለ የፍራፍሬ ማስቀመጫ ቅርጫቱንም የሚሰርቁት ይመስለኛል፡፡ እንግዲህ ታማኝ የሆነ  ዜጋ መፍጠር ማለት እዛ ድረስ ይረድሳል፡፡

ሀይማኖት በዴንማርክ

በዴንርክ በነበረኝ ቆይታ ከታዘብኳቸው ጉዳዮች አንዱ የሀይማኖት ጉዳይ ነው፤ ዴንማርክ ሀገር አብዛጃው ህዝብ እግዚአብሄር የለም በማለት የሚያምኑ ናቸው፤ ነገር ግን የሰው ነገር አይነኩም፤ ታማኞች ናቸው፤ ሙስናም የለም ማለት ይቻላል፡፡

 

የኛ ሀገር ሁኔታስ?

 

ሀይማኖት ቢኖረንም ጥሩ ስነምግባር በእጅጉ የሚያንሰን ይመለኛል፤ ምክንያቱም ሌብነት፣ ሙስናና ስርቆት በእንዳንዳችን ቤት በተለያየ መልኩ ያለ መስለኛል፡፡  በነገራችን ላይ በፈረንጆች አቆጣጠር በ2008 እኔ ወደዴንማርክ ስሄድ በኮፐንሀገን ከተማ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች የራሳቸው ቤተክርስቲን አልነበራቸውም፤ ስለሆነም የግብፅ ወይም የሩሲያ ቤተክርስቲያን ይጠቀሙ ነበረ፡፡ እኛ እዛ እንደደረስን ከኔ ጋር የሚኖረው ዳንኤን ከሌንሳ ከመንግስቱና ከደረጄ ጋር ሆነው የዶርም የፀሎት ፕሮግራም ጀመሩ፤ በቀላል የተጀመረው የዘወትር ፀሎት በከተማው ያሉትን ኦርቶዶክሶች ኤርትራዊያንንም በማሳተፍ ሰፋ ተደርጎ ተጀመረ፤ ቀስ በቀስም ከተማሪዎች ዶርም ወጣ ብሎ የዴንማርክ ክርስቲያኖች የሚጠቀሙትን ቤተክርስቲያን መጠቀም ተጀመረ፡፡

 

በሰአቱ የፀሎት ፕሮግራም የጀመሩት ወዳጆቼ ሊመሰገኑ ይገባቸዋል፤ ምክንቱም በከተማው የሚኖሩት ኢትዮጵያዊያን በእምነቱም ሰበብ እንዲሰባሰቡና ሀገራቸውን በበለጠ እንዲያስታውሱ ማድረግ በመቻላቸው፡፡ ሌላው ያስተዋልኩት ነገር ሀይማኖት ከኢትዮጵያ ውጪ ሲወጣ ብዙ የሚሻሻሉ ነገሮች እንዳሉት ነው፡፡ ለምሳሌ እዛው ዴንማርክ ሀገር የነበረው ቤተክርስቲያን እየተጠናከረ ሲመጣ ታቦትም ማምጣት እንደተቻለና ንግስን ማክበር መጀመሩን አይቻለሁ፡፡ ነገር ግን ይህ ሁሉ ሲደረግ ቤተክርሲቲያኑን በፈረቃ ነበር የምንጠቀመው፤ ጠዋት የዴንማርክ ክርስቲያኖች ከተጠቀሙት ከሰአት ደግሞ እኛ እንጠቀም ነበረ፤ በሀገራችን አጠራር ጠዋት ፕሮቴስታንቶች የተጠቀሙትን ቤተክርስቲያን ከሰኣት ደግሞ ኦርቶዶክሶች ተጠቀሙት ማለት ነው፤ እንዲሁም እዛው የፕሮቴስታንት ቤተክርስቲያን ውስጥም ታቦት ማስገባት የግድ ነበረ፤ ያ የዴንማርክ ሀገር ተሞክሮ በሀገራችን ያሉትን ክርስቲያኖችን /ኦርቶዶክስና ፕሮቴስታንትን/ ለማቀራረብ እንደ ጥሩ ተሞክሮ መነገር ያለበት ስለመሰለኝ ነው እዚህ መጥቀሱ ያስፈለገው፡፡

 

መቼም ሁለት ኢየሱስ ክርስቶስና ሁለት እግዚአብሄር ሊኖሩ አይችሉም፤ ነገር ግን ብዙ የክርስትና አይነቶች አሉ፡፡ በክርስቲያኖች መካከል ደግሞ ልዩነትን የፈጠርነው እኛው ሰዎች ነን እንጂ ያንን ያህል የመፅሀፍ ቅዱስ መሰረት ያለው አይመስለኝም፡፡ ስለሆነም ዴንማርክ ሀገር የፕሮቴስታንትን ቤተክርስቲያን ከኦርቶዶክስ ጋር በጋራ መጠቀም ከተቻለ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት ኦርቶዶክሶችና ፕሮቴስታንቶች እንዲሁም ሙስሊሞች ጋር የበለጠ መቀራረብና አንዱ የሌላውን ሀይማኖት የመረዳት መንሰፍ መጀመር ያለበት እዲሁም ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ይመስለኛል፡፡ በተለይ በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ጋር ተያይዞ ተሀድሶ የሆኑና ያልሆኑ አይነት ሀሳቦች ከዚህም ጋር ተያይዞ በማህበራዊ ድህረገፆች ሲፃፉ የማያቸው አላስፈላጊ ጭቅጭቆች ህዝቡን ውዝግብ ውስጥ መክተታቸው አያጠያይቅም፡፡ ሰባኪዎች ማህበራዊ ድህረገጽ ድረስ በመምጣት አንዱ ሌላውን ሲሳደቡም እያየን ነው፣ ስለሆነም ህዝቡንና ክርስትናን ለመግባባት መጠቀም ቢቻል ለልዩነትና ለግጭት የሚደርሱ ሀሳቦች ቀስ በቀስ እየቀነሱ የሚመጡበት ይመስለኛል፡፡

 

ስለሆነም ከኢትዮጵያ ውጪ ስንወጣ በሀይማኖታችን ላይ እንደአስፈላጊለቱ ማሻሻል ማድረግ ከተቻለ፣ ሀገር ቤት ያለውን ክርስቲያን አላስፈላጊ በሆኑ የመንደር ውስጥ ወሬዎች ለመያየቱ በመጀመሪያ ህዝቡን፣ ቀጥሎም ቤተክርስቲያናቱን እንዲሁም ትልቁን የክርስትና እምነት የሚጎዳ ይመስለኛል፡፡ ዴንማርክ በነበርኩበት ወቅት ያስተዋልኩት የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ስርኣት ሀገር ቤት ከማውቅው ጋር ሳወዳድረው በብዙ ሁኔታ የተሻሻለ ነበረ፤ ለምሳሌ ታቦትን በፕሮቴስታንት ቤተክርስቲያን ውስጥ ማስገባቱ፣ ነገር ግን ያ ሁሉ ማሻሻል የተደረገው በወቅቱ ለህዝቡ ሀይማኖታዊ አገልግሎት ለመስጠት ያሉትን ቤተክርስቲያኖች መጠቀሙ የግድ ስለሆነ ነበረ፤ ስለዚህ እባካችሁ ስለእውነትና ስለክርስቶስ ብለን በክርስቲያኖች መካከል ልዩነት የሚፈጥሩትን አላስፈላጊ ነገሮች ብንተው፤ ተሀድሶ ምናምን እያልን ምእመኑን ግራ ከምናጋባው፤ ይልቅ ለህዝቡ ትክክለኛ የክርስቲያን ስነምግባር፣ በመተዛዘንና በመደጋገፍ እንዲሁም ይቅር በመባባል ለህዝቡ የክርስትና ስብእና እናስተምር፡፡

 

ካልሆነ አንዳችን እንደቤተክርስቲያን ጠባቂ ሌላውን ደግሞ እንደቤተክርስቲያን ጠላት አድርገን የራሳችንን ወንድሞች የምንወቅሰው ነገር ትክክል አይመስለኝም፡፡ እኔ ክርስቲያን ብሆንም ከማንኛውም ሀይማኖት ተከታይ ጋር በሰላም እኖራለሁ፤ ለምሳሌ ልጆች ሆነን ከእስልምና እምነት ተከታዮች ጋር አብረን አድገናል…. ከቤታችን ወደሩቅ ቆላ ሄጄ የእስልምና እምነት ተከታዮች ጋር በእንግድነት አድሬ አውቃለሁ፤ በክብርም ማታ ማር ቆርጠው አብልተውኛል፤ ትኩስ ወተት ጠጥቻለሁ፡፡

 

ዛሬ ዛሬ ያለውን የፖለቲካ ውጥረት ስናይ፣ ክርስቲያን ክርስቲያንን ጠላት አድርጎ ጥላቻን ስሰብክ ስናይ፣ ስለሀይማኖት መናገርና መፃፍ ባንፈልግም አስገዳጅ ሁኔታዎች ውስጥ እንገባለን፡፡ እኔ ስለሀይማኖት ምንም ባልል ደስ ይለኛል፤ ነገር ግን የሀገራችንን ህዝቦች አንድነት በሀይማኖት ሰበብ የሚከፋፍሉትን ግን ዝም ማለት ደግሞ ከባድ ነው፡፡ ለሁሉም ከባዱ ጠላታችን የአስተሳሰብ ድህነት ነው፤ በጋራ ልንዋጋው ያስፈልጋል፡፡

 

የመፅሀፍት ፕሮጀክት

ዴንማርክ በነበርኩ ጊዜ የማህበራዊ ድህረ ገፆችን /በተለይ ፌስቡክን/ ተጠቅመን ከሰራናቸው ስራዎች ውስጥ አንዱ ለሀገራችን ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መጽሀፍት አሰባስበን ወደኢትዮጵያ መላክ ነበረ፡፡ መፅሀፍት የመሰብሰቡ ሀሳብ የተጀመረው የኮፐንሀገን ዩኒቨርሲቲ ብዙ መጽሀፍትን ሊያቃጥል እንደሆነ ከተነገረ ጀምሮ ነው፡፡ ዜናውን እንደሰማን ዴንማርክ ለት/ት አብረውኝ ከነበሩት ካሌብና ሽመልስ ከሚባሉ ወዳጆቼ ጋር ተነጋገርን፤ ለምን መጽሀፍቱን ወደሀገራችን አንልክም ተባባልን፤ ከዛ የዩኒቨርሲቲውን ላይብራሪ ሀላፊዎች ጠየቅናቸው፤ ጥያቄያችንን ተቀበሉ፤ መፅሀፍቱን መውሰድ እንደምንችል ተነገረን፤ አንድ ቀን መጽሀፍቱ ያሉበትን ክፍል አሳዩንና የሚመቹንን እንድንመርጥ ተደረገ፤ ሌሎች ኢትዮጵያዊያን ተማሪዎች ስለመፅሀፍት መሰብሰቡ ዜና ፌስቡክ ላይ አይተው መጥተው ተባበሩን፡፡ ከብዙ መፅሀፍት ውስጥ 7 ካርቶኒ የተሻሉ የምንላቸውን መፅሀፍት መረጥን፡፡  ቀጥሎም ለምን ከተማሪዎች አሮጌ መፅሀፍትን አንሰበስብም ብለን ተነሳን፤ ከዛም በየዩኒቨርሲቲው ላይብራሪ ሄደን ሀላፊዎቹን አነጋገርን፤ ሁሉም ሊተባበሩን ፈቃደኞች ነበሩ፤ በየኮሌጆቹ ላየብራረሪ በር ላይ ካርቶኒ አስቀምጡና መምህራንም እንዲሰጡ እናደርጋለን እኛም እንሰጣለን አሉ፤ መፅሀፍት ለኢትዮጵያ ተማሪዎች ይለግሱ የሚል ጽሁፍ ለጥፈን ካርቶኒዎች በዩኒቨርሲቲው ላይብራሪዎች አስቀመጥን፡፡

 

ዜናውንም በዩኒቨርሲቲው ድህረገጽ ለቀቅነው፤ በማግስቱ ብዙ መጽሀፍት ተሰበሱ፤ ድካማችንን ያየ አንድ የዩኒቨርሲቲው የላይብራሪ ሰራተኛ አንድ ሳጥን ሰርቶ፤ ቁልፍ ገዝቶ እንዲቆለፍ አድርጎ ሰጠን ‹ድካማችሁን ሳየው ልረዳችሁ ወሰንኩ፤ እውቀትን ለማዳረስ የምታደርጉት ጥረት እጅግ ደስ ይላል› አለንና አበረታታን፤ ሳጥኑን በፌስቡክ ለወዳጆቻችን አሳየን፤ ኮፐንሀገን ያሉትን የሀገራችንን ዜጎች ለትራነስፖርት ብር እንዲያዋጡልን ፌስቡክ ላይ ጠየቅን፤ ከሳምንት በኋላ ወደ40ሺ ብር ተሰበሰበ፤ ከተገኙት መፅሀፍት ውስጥ የቅርብ ጊዜ እትም የሆኑትና ቢላኩ ለሀገራችን ተማሪዎች ጠቃሚ የሆኑትን መፅሀፍት ብቻ መረጥን፤ 168 ምርጥ መፅሀፍትን መረጥን፡፡

 

 

ከተሰበሰቡት መፅሀፍቱም ወደኢትዮጵያ በገልፍ አየር መንገድ ተላኩ፤ የሚገርመው መፅሀፍቱን በሀገራችን አየር መንገድ ለመላክ የዋጋ ቅናሽ እምቢ መባላችን ነበረ፤ ምክንያቱም የሀገራችን አየር መንገድ እጅግ ውድ ነው፤ ገልፍ አየር መንገድ ርካሽ ነበረ፤ ገንዘብ ጨምረን በሀገራችን አየር ለመላክ በቂ ብር አልነበረንም፤ ከዛ የመጽሀፍት ፕሮጀክት የተማርኩት ነገር የዴንማርክ ዜጎች ምን ያህል የበጎ ፈቃደኝነት ስራ እንደለመዱና ሌሎችን ለመርዳት በልበ ንፁህነት እንደሚሰሩ ነው፤ የሀገራችንም ዜጎች ምስጋና ይገባቸዋል፡፡

 

ነገር ግን የተወሰኑት የሀገራችን ዜጎች ስራችንን ከፖለቲካ ጋር ለማገናኘት ይሞክሩ እንደነበረም አይተናል፡፡

 

በዚህ አጋጣሚ በዲያሰፖራው ላለው የሀገራችን ዜጋ ከፖለቲካ ልዩነት ላይ ማተኮርን ትቶ ደሀውን የሀገራችንን ህዝብ በተናጠል ሳይሆን በአንድነት የሚረዳበትን መንገድ ቢፈላልግ ጥሩ ነው፤ ብዙ የወረደ አስተሳሰብ ያላቸው ነገር ግን በሰለጠነ ሀገር የሚኖሩ ዜጎች እንዳሉንም መርሳት የለብንም፡፡ ምንም ቢሆን ዲሞክራሲ ከዲያስፐራው መጀመር አለበት፡፡ ዘመናዊ አስተሳሰብን ከአከባቢ መማር ለዲያስፖራው ዜጎቻችን ቀላል መሆን አለበት፡፡

 

ሀገራችን ያላትን ሀብት በአግባብ ከተጠቀመች ድህነትዋን ታሪክ ማድረግ ይቻላል፤ ከሀገራችን ሀብት ደግሞ ትልቁ ሀብታችን የሰው ልጆቻችን መሆኑን መረዳት አለብን፤ በተለይ በተለይ የተማሩት የሀገራችን ዜጎች፤ የተማሩት ዜጎች ደግሞ የፖለቲካውን ሁኔታ ሰበብ በማድረግ ደሃውን ህዝብ ለብቻው መተው ያለባቸው አይመስለኝም፤ ምንም ሆነ ምን ሀገር መለወጥ ካለበት ህዝብ ያስፈልጋል፡፡ በተለይ የተማረ የሰው ሀይል፤ ብዙው የተማረ የሀገራችን ዜጋ ደግሞ ወደውጪ ሀገር ይሰደዳል፡፡

 

 

 

 

ስለሆነም የሀገራችንን ልጆች ከያሉበት ሆነው ሀገራቸውን እንዲረዱ ማስተባበርና ልዩነትን ወደኋላ ትተው ህዝብን ከድህነት ውስጥ ለማውጣት እንዲረባረቡ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ካልሆነ 100 ሚሊዮን ዜጎች እያሉን 5 ሚሊዮን ህዝብ ካላቸው ሀገራት እርዳታ መቀበላችን ይቀጥላል፡፡ ነገር ግን ታላቅም ነበርን፤ ታላቅም እንሆናለን፣ ስለዚህ እርዳታ ለሚሰጡት እርዳታ የምንሰጥበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም፡፡

 

መተባበር ብቻ ያስፈልገናል፤ ድር ቢያብር አንበሳ ያስር!!

 

ፌስቡክ ላይ ከሰራናቸው ስራዎች ሌላው ሮቤ ዲደኣ ለሚገኘው ት/ት ቤታችን ያደረግነው የመጽሀፍት ግዢ ይጠቀሳል፡፡ ዲደአ የተማሩ የዱሮ ተማሪዎችን ህብረት ለመመስረት የታቀደ ተግባር አካል የነበረው የመጽሀፍት ፕሮጀክት በአጨር ጊዜ ውስጥ ለአባላቱ ማነቃቂያ የሆነ ስራ ነበረ፤ እኔ ውጪ ሆኜ እነ እንዳልካቸው ደቻሳ፣ ፍቃዱ ፈጠነ፣ ደረጄ ዳርጌ፣ መሰረት መንግስቱ፣ ፍቅርነህ ነጋሽ የመሳሰሉት የኮሚቴው አባላት ብዙ የማስተባበር ስራ ሰርተዋል፡፡

 

ከዲደአው የመጽሀፍት ፕሮጀክት የተማርነው ነገር የሀገራችን የተማሩ ወጣቶች አስተባባሪ ካገኙ ብዙ መስራት እንደሚችሉና ለመስራትም ሙሉ ፈቃደኛ መሆናቸውን ነው፤ በተለይ ትምህርት ቤቶችን ማጠናከር ብዙዎችን የሚያስደስት ስራ ነው፤ ባደጉት ሀገራት ትምህርትቤቶች የቀድሞ ተማሪቸዎቻቸው ህብረት ስላላቸው ከተማሪዎቻቸው ብዙ ድጋፍ ያደርጋሉ፤ አጋጣሚውን ባንጠቀምበትም ዛሬ በሀገር ውስጥም በሀገር ውጭም በተለያዩ ደረጃዎች ያሉት እጅግ የተማሩ ወገኖቻችን ለተማሩበት ትምህርትቤቶች ትልቅ ሀብት ናቸው፡፡

 

 

ስለሆነም የትምህርትቤቶች ርእሰ መምህራን በየትምህርቤታቸው የቀድሞ ተማሪዎች ማህበርን ቢያቋቁሙ ለሚመጣው ትውልድ ብዙ ስራ መስራት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም ጥሩ ስብእና ያለውና ተወዳሪ ያለው ጠንካራ ዜጎችን ለመገንባት የትምህርትቤቶች አቅም ከመዋለ እፃናት ጀምሮ ደረጃውን የጠበቀ መሆን አለበት፡፡ ትምህርትቤቶችን ለማጠናከር ፍላጎት ላላቸው አንባቢዎቼ የማስተላፈው መልእክት የሚፈልጉትን ስራ ቶሎ መጀመር አለባቸው፤ ብዙ ሰው በበጎ አድራጎት ስራ መሳተፍ ይፈልጋል፤ ነገር ግን የተቀደሰውን አላማ ወደተግባር የሚተረጉሙት እጅግ ጥቂቶች ናቸው፤ ብዙ ሰው ስራውን ለመጀመር የተመቻቸ ጊዜ እስኪመጣ ይፈልጋል፤ የተመቻቸ የሚባል ጊዜ ግን የለም፤ ሁሉ ሰው የራሱ ስራ አለው፤ ነገር ግን ከሁሉ በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው ለልጆቹ ነውና ልጆቹ የሚውሉበት ትምህርትቤት ደረጃውን የጠበቀ ካልሆነ ተማሪዎቹ ጥሩ ትምህርት አግኝተው በቴክኒክም በአመለካከትም እዲሁም በስብእናም የሚጠበቅባቸው ደረጃ ይደርሳሉ ብሎ መጠበቅ ያልዘሩትን ለማጨድ እንደመጠበቅ ነው፡፡

 

እንደ ሀገር የሰው ሀይላችን በተመለከተ ያሉብን ክፍተቶች መጀመሪያቸው በቤተሰብና በመጀመሪያ የትምህርት ቤት ህይወታችን ይጀመምራል፤ ቤተሰብን በተመለከተ ወላጆች በተለያየ የኢኮኖሚና የትምህርት ደረጃ መሆነቸው የሚታወቅ ሲሆን ትምህርቤቶች ግን በህጋዊ ስርአት ውስጥ የሚታቀፍና በተማሩ ሰዎች የሚተዳደሩ ናቸው፤ እንዲሁም ትምህርት ቤቶች አለም አቀፍ የጥራት መለኪያ መስፈርቶች አላቸው፤ ስለሆነም ማህበረሰባችን ያሉት ትምህርት ቤቶች መዋለ ህፃናትንም ጨምሮ ምን ያህል አለም አቀፍ ጥራትን ያሟላሉ የሚውን እንዲያውቅ ግንዛቤ ያስፈልገዋ፡፡

 

በዚህ መፅሀፍ ውስጥ ለምጠቀማቸው የውይይት ሀሳቦች እነንደማስረጃ የማቀርበው ውጪ በነበርኩ ጊዜ ያየሁትን ተጨባጭ ተሞክሮዎች ነው፤ እኔ የዴንማርክ ሀገርን ምሳሌ እጠቅሳለሁ፤ ሌሎች ፀሀፊያን ደግሞ በአዲስ አበባም፣ በአሜሪካም፣ በቻይናም ሌላም ሀገር ያጋጠማቸውን በጎ ተሞክሮ ለሀገራችን ይጠቅማል ያሉትን መፃፍ ይችላሉ፡፡ በዴንማርክ ኮፐንሀገን ከተማ ስንኖር ለልጄቼ መዋለ ህፃናት ያየሁትን እጠቅሳለሁ፡፡

 

መዋለ ህፃናት

 

የልጆች መዋያ በሁሉም የአለማችን ክፍሎች እንደየሀገሮቹ እድገትና እንዲሁም እንደወላጆች ግንዛቤና የገቢ መጠን ብዙ አይነት ነው፤ እጅግ የባሰባቸው መዋለ ህፃናት የሚባሉት ወላጆቹ እናቶች ሳይዘጋጁ ወልደው ልጆቻቸውን በተለያዩ ቦታቸዎች ጥለው በህይወት የሚገኙት/ከሞት የሚተርፉት ደግሞ በህፃናት ማሳደጊያዎች ወይም በየጎዳዎች ላይ ሊያድጉ ይችላሉ፡፡ እነኚህ አይነቶቹ ህጻናት ከሁሉ በላይ ከለላ የሚያስፈልጋቸው ናቸው፤ በተጨማሪም የተለያዩ የተፈጥሮ አደጋዎቺ ሲኖሩ ህፃናት ከወላጆቻቸው ሊለያዩ ይችላሉ፤ እንዲሁም ወላጆቻቸው ለህጻናቱ የሚያስፈልጉትን መሰረታዊ ነገሮች ማሟላት ሊከብዳቸው ይችላል፤ መንግስትም ህጻናትን በጊዜያዊ ካምፖች ሊያቆይ ይችላል፤ ተላላፊ በሽታዎች የሚከሰቱትና ብዙ ልጆች የሚሞቱበት አጋጣሚም ሊኖር ይችላል፤ አደጋውን ለመቀነስ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስራና የግብአት ዝግጅትም ያስፈልጋል፡፡ በሀገራን ደረጃ በአለም አቀፍ መድረክ አንገታንን የሚያስደፉን አደጋዎች የመጀመሪያ ተጠቂ ህፃናት ናቸው፤ በተለይ ድርቅን ተከትሎ በሚከሰት ረሀብ፤ ነገር ግን ቀድመን ከተዘጋጀንበት አደጋዎቹን መቀነስ ይቻላል፡፡ ሌላው አይነት መዋለ ህፃናት ደግሞ በቤትና በወላጆች ስራ ቦታ ነው፤ በተለይ በገጠሩ የሀገራን ክፍል እናቶች ገበያ ሲሄዱም፣ ውሀ ሲቀዱም፣ የቤት ስራ ሲሰሩም፣ በግብርና ማሳ ላይ ስራ ሲሰሩም፣ ልጆቻቸውን አዝለው ይሄዳሉ፣ ወይም በስራው አከባቢ እንዲተኙ ያደርጋሉ፤ ካልሆነም ልጆች ከሰፈር ልጆች ጋር በመጫወት ጊዜያቸውን ያሳልፋሉ፡፡ በገጠር ህዝባችን ዘንድ ልጆች እህቶችን ከባድ የስራ ጫና ያሳድሩባቸዋል፤ እንዲሁም ለልጆቹ አስፈላጊ የሆኑ የጤና ክትትሎች ሳይደረጉ ይቀራሉ፤ ነገር ግን በየገጠር ቀበሌው ውስጥ የህፃናት መዋያ ቦታዎች ቢኖሩ ለእናቶቹም የተወሰነ እረፍት ይሰጣል፤ ለገጠር ወጣቶችም የስራ እድል ሊሆን ይችለል፡፡ ይህ ሀሳብ ዛሬ ባለው የሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ እንደ ቅንጦት ይቆጠር ይሆናል፤

 

 

ወደከተማው ስንመጣ ደግሞ መዋለህፃናቶቻችን እንደማንኛውም ሀገራት በወላጆች የገቢ መጠንና ግንዛቤ ይወሰናሉ፤ በተለይ በትልልቅ ከተሞች የልጆች መዋለህጻናት በመንግስትም፣ በግልም ድርጅቶች ከተፍተው ይገኛሉ፡፡ የክፍለ ሀገር ከተሞችን ትተን አዲስ አበባ ውስጥ ያለውን ብቻ ብንመለከት በተለይ በግሉ ዘርፍ ብዙ የመዋለህጻናት ተከፍተዋል፡፡ ጅማሮው የሚበረታታ ስራ ነው፤ መሻሻል ያለባቸውም ብዙ ጉድለቶች አሉ፡፡ የመጀመሪያው መዋለህጻናቱን የሚከፍቱት በዋናነት ባለሀብቶችና መምህራኑ ለህፃናቱ የሚስፈልገውን ሙያዊ ደረጃዎች ፣ ለልጆቹ ጤናማ የአካል፣ የአእምሮና የባህሪ እድገት ወዘተ የሚያስፈልጉትን ሳያስተውሉ ለትርፍ ብቻ ነው፡፡

 

ለምሳሌ በአንድ ክፍል ውስጥ የሚማሩትን የተማሪዎች ብዛትና የመጫወቻ ቦታዎችን ብንመለከት አብዛኛዎቹ አመቺ አይደሉም፡፡ አብዛኞቹ የአንድ ግለሰብን የመኖሪያቤት ተከራይተው መዋለ ህፃናት ያደርጉታል፤ ከዛ የተገኘው ያህል ህፃናት ይቀበላሉ፤ በተለያየ አጋጣሚም ከወላጆች ገንዘብ ይሰበስባሉ፡፡ የምዝገባ፣ የጥናት፣ የዩኒፎርም፣ የወረቀት፣ የመፅሀፍ፣ የወር ክፍያ፣ የበአል ማክበሪያ ወዘተ፡፡ በሀገራችን አቅም ወላጆች ብዙ ክፍያ ለልጆች ትምህርት ቤት ይከፍላሉ፤ የመዋለህጻናቱ ባለሀብቶች ግን የመዋለህጻናትን ስራ ከሬስቶራንት ስራ እኩል አላማውን ትርፍ አድርጎ ብዙ ትርፍ እንዲያስገኝ ነው የሚሰሩት፡፡ መሆን የነበረበት ቤቶቹ ከመከፈታቸው በፊት የልጆቹ መጫወቻ ቦታና ትምህርቤቱ ውስጣዊ ቁሳቁሶች መሟላት፣ የመምህራኑ የስልጠና ደረጃ ወዘተ ከአለም አቀፍ ደረጃዎች ጋር ተገምግመው ማለፍ ነበረባቸው፡፡ እስካሁን ጠለቅ ያለ የደረጃ ግምገማ የሚደረግ አይመስለኝም፡፡ መንግስትም ለልጆች ትምህርትቤት የሚከፍቱትን ባለሃብቶች መደጎም አለበት እንጂ ከሌላው የንግድ ዘርፍ እኩል የገቢ ቀረጥ መክፈል የለባቸውም፤ እንዲሁም ለትምህርትቤት የሚመጥን ሰፋፊ ቦታ መስጠት አለበት፡፡

 

 

 

 

ወደ ዴንማርክ ስንሄድ የመጀመሪያ ልጄ አራት አመት ሞልቷት ነበረ፤ ከማሄዷ በፊት ሀዋሳ ኮምቦኒ መዋለ ህፃናት ገብታ ለአንድ አመት ቆይታለች፤ በአንድ አመት የመዋለ ህፃናት ቆይታዋ አማርኛ ፊደላትን ለምዳ ማንበብ እየሞከረች ነበረ፤ ያንን ሁሉ የተማረችው በዛ እድሜዋ በአርጩሜ እያስፈራሩ ሀሁ እንድትሸመድድ ተደርጋ ነው፤ ዴንማርክ መዋለ ህፃናት ስናስገባት ምንም ፊደል ቆጠራ የሚባል ነገር የለም፤ ቀኑን ሙሉ ጫወታ ነው፤ የመጫወቻ ቦታው ስፋትና የልጆች መጫወቻ ቁሳቁስ ብዛት እጅግ አስደመመን፤ ትዝ ይለኛል፣ ከመዋለ ህፃናት መልስ ልጄን ‹ዛሬ ምን ተማራቹ› ብዬ ስጠይቃት ነበረ፤ ‹ምንም አልተማርንም፤ እዚህ ሀገር እኮ ትምህርት የለም› ብላ ትመልስልኝ ነበረ፤ የሚገርመው እዛ ገብታ በስድስት ወር የዛን ሀገር ቋንቋ መናገር ቻለች፤ በጫወታ መሀል ህፃናቱ በወረቀት መጫወት ሲፈልጉ ነጭ ወረቀትና እርሳስ ይሰጣቸዋል፤ ልጆቹ የፈለጉትን እንዲፅፉ ያደርጋሉ፤ ህፃናቱ የፃፉትን ስእል ለወላጆቻቸው ይሰጣሉ፤ ለልጆቹ የመጀመሪያ ስእላቸው ማስታወሻ ማለት ነው፡፡

 

እዚህ ሀገር ቤት ሁለተኛ ልጃችን ኬጂ 2 የሚማሩበት የእንግሊዘኛ መፅሀፍ እኔ አራተኛ ክፍል የተማርኩት አይነት ነው፤ ይህ ትልቅ ክፍተታችን ነው፤ ልጆቻችን በመዋለ ህፃናት ውሎአቸው ብዙ የወረቀት ትምህርት እንዲማሩ ይደረጋሉ፤ ስለሆነም የትምህርት ፍላጎታቸው ይቀንሳል፤ መጫወት ባለባቸው እድሜ ቀኑን ሙሉ አንድ ክፍል ውስጥ ታጉረው ፊደል ሲሸመድዱ ይውላሉ፤ እስቲ አስቡት የአራት አመት ልጅ አንድ ወንበር ላይ በተከታታይ ለሁለት ሰአት ሲቀመጥ! በአመቱ መጨረሻ ደግሞ አንደኛ ወጣ ተብሎ ሽልማት ይሸልሙታል፤ ወላጆችን ማስደሰቻ መሆኑ ነው፡፡ በፍጹም የማልቀበለው አሰራር ነው ግን ምን ላድርግ ፤ እኔ ትምህርት ሚኒስተር አይደለሁም፡፡

 

አማራጭ ቢኖረኝ ልጆቼን በራሴ ነበረ የማስተምራቸው፤ የትምህርት ስርአታችን ልክ አይደለም፤ ብዙ መሻሻል አለበት፡፡ አስተዋይ ሰው ቤቱን በአለት ላይ ይሰራል፣ የማያስተውል ደግሞ አሸዋ ላይ ይሰራል የሚል ነጥብ አለ በመፅሀፍ ቅዱስ ማቲዎስ ወንጌል 7፡24-27. 

ልጆቻችንና የሀገራችን የወደፊት ጊዜ የተሻለ እንዲሆን የሰው ሀይላችን በጠንካራ መሰረት ላይ መመስረት አለበት፡፡ ካልሆነ ደግሞ ትንሽ ችግር ስትፈጠር የሚሸበርና ከድህነት መውጣት የማይችል ህዝብ ይፈጠራል ማለት ነው፡፡ ምርጫው የኛ ነው፤ አሁንም ጊዜ አለ፡፡

የቀብር ስነስርአት በዴንማርክ

አንድ በኮፐንሀገን ዩኒቨርሲቲ አብሮኝ ይማር የነበረ ተማሪ አያቱ በጣም ማርጀታቸውንና ሊሞቱ መሆኑን ነግሮኝ አያቱ ከመሞቱ በፊት ሄዶ እንደሚሰናበተው ነገረኝ፤ ይህን ሲነግረኝ አነጋገሩም ሆነ ፈቱ ላይ ምንም የሀዘን ስሜት የለውም፤ ለማረጋገጥ ጠየኩት፤ እንደሚሞት በምን አወቃችሁ ስለው ሀኪሞቹ ነግረውናል፤ ሁለት ቀን እድሜ ነው የቀረው አለኝ፤ በኣያትህ ሞት ምን ይሰማሀል ስለው ምንም አይሰማኝም፤ መሞት አለበት፤ ይበቃዋል፤ ህይወቱን ሙሉ ደስተኛ ጊዜ ነበረው፤ አሁን መሞቱ ትክክል ነው፤ ስለዚህ ምንም አናዝንም አለኝ፤ በሁለተኛው ቀን አያቱ መሞቱን ነገረኝ፤ ታዲያ ቀብራቸው መቼ ነው፤ ቀብር ትሄዳለህ ወይስ አትሄድም ስለው፣ አረ ቀብር የሚባል ስነስርአት የለንም፣ እዛው ራሳቸው ይቀብሩታል አለኝ፡፡ አንድ ቀንም ቤተክርስቲያን ውስጥ አራት ሰዎች የሬሳ ሳጥን ይዘው ሲገቡ አይቻለሁ፤ እስቲ ከኛ ሀገር ጋር አስተያዩት፤ አንድ አዛውንት በ120 አመታቸውም ቢሞቱ ሙሾ ይወረዳል፤ ጥቁር ይለበሳል፤ ቀብሩ ላይ ለመገኘት ቀን ተለሊት ይኬዳል፤ በቀብሩ ያልተገኘ ዘመድ ቅያሜ ይከተለዋል፤ ከቀብር መልስ እስከ አንድ ወር ቁጭ ተብሎ ዘመድ በመጣ ቁጥር ይለቀሳል፤ አረ ስንቱ፡፡ ልዩነታችን ይደንቃል፡፡

 

ስቃይ ለመቀነስ ሞቶ እንዲያርፍ ማድረግ??

የህብረተሰብ ጤና መሻሻል አንዱ ጎን እድሜያቸው ከ100 አመት በላይ የሆኑ ብዙ ሰዎች በህይወት ይኖራሉ፤ በቅርቡ ኔዘርላንድ ሀገር በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተና በሀኪሞች የተደገፈ ሞት ህጋዊ ተደረገ የሚል አነበብኩ፤ በቤልጂየምም ይተገበራል፤ ጉዳዩ ዝም ብሎ መግደል ሳይሆን አንዳንድ እድሜያቸው በጣም የገፋ ሰዎች ነብሳቸው ብቻ አልወጣ ብላ በከፍተኛ ህክምና ወጪ ለብዙ ጊዜ ይኖራሉ፤ መጨረሻ ግን መሞታቸው ግድ ነው፤ ጋዜጣው እንደዘገበው ከሆነ የአንዱ አዛውንት የወር የህክምና ወጪው ታዳጊ ሀገሮች ላይ አንድ መለስተኛ ክሊኒክ ይሰራል፤ መንግስትም እጅግ ከፍተኛ ወጪ ያወጣል፤ ስለሆነም ሽምግልና በመምእራቡ አለም አንዱና አሳሳቢው ጉዳይ ነው፡፡ ጡረታ የሚወጡት ሰዎች ቁጥር ከሚወለዱት ልጆች የሚበልጥበት የምእራቡ አለም ሀገራት እየበዙ ነው፡፡ በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተውን በሽተኞችን የመግደሉን ጉዳይ እንዴት ይመለከቱታል?? የበሽተኛው ወላጆችና ሀኪሞች ሲፈቅዱ፤ ታማሚው ግለሰብ ህይወቱ እንድታልፍ እርዳታ ይደረግለታል፡፡ ይህ ጉዳይ አሁንም ድረስ ብዙ እያጨቃጨቀ ነው፡፡

ቋንቋ ትምህርት ቤት

የዴንማርክ ህዝብ ብዛት አምስት ሚሊዮን አይበልጥም፤ ነገር ግን በአለማችን ካሉት ሀያላን ሀገራት ዴንማርክ አንዷ ናት፤ ለሀገራችንም አልፎ አልፎ እርዳታ ትሰጣለች፤  ከታዳጊ ሀገራት ስደተኞች ሊደርሱባት ከሚፈልጉት ሀገሮች ውስጥ ዴንማርክ አንዷ ናት፤ እኔም ዴንማርክ በቆየሁበት አምስት አመት ቆይታዬ ቋንቋቸውን የመማርና ስለሀገራቸው ታሪክ ለማወቅ እድሉ ነበረኝ፤ የዴንማርክ ቋንቋ ከዴንማርክ ውጪ ብዙ ተናጋሪ የለውም፡፡

 

ስለዴንማርክ የልማት ታሪክ ደቨሎፕመንት ኢኮኖሚክስ በሚባል ኮርስ ላይ የተወሰነ ተምረን ነበረ፤ ዴንማርክ ኢኮኖሚዋ ታሪክ በዋናነት ግብርናን መሰረት ያደረገ ነው፤ ነገር ግን ግብርናቸው እጅግ የተራቀቀና ቴክኖሎጂን በመጠቀም ከፍተኛ ደረጃ የደረሰ ነው፡፡  በተጨማሪም የዴንማርክ ህዝብ ከአንድ መቶ አመታት በፊት የነበረውን የእድገት ደረጃ በሀገራቸው ታዋቂ ፀሀፊ የነበረው ሀንስ ክሪስሻን አንደርሰን ስለራሱ ህይወት ታሪክ ከፃፈው መረዳት ይቻላል፡፡ ሀንስ ክሪስሻን አንደርሰን ልጅ በነበረበት ወቅት አባቱ ጫማ ሰፊ የነበረ ሲሆን እናቱ ደግሞ የሰዎችን ልብስ በማጠብ ትተዳደር ነበረ፤ ልብስ የምታጥበውም በልብስ ማጠቢያ ማሽን ሳይሆን በእጅዋ እንደነበረና በበረዶ ወቅት ብርዱን ለመቋቋም አልኮል መጠጥ ጠጥታ ልብስ ታጥብ እንደነበረ ጽፏል፡፡ የዴንማርክ መንግስት በሀገራቸው ለሚኖሩ የውጪ ዜጎች ነፃ የቋንቋ ትምህርት ይሰጣል፡፡ ዋና አላማውም ሰዎች የሀገሩን ቋንቋ ተጠቅመው በቀላሉ ስራ እንዲያገኙ ነው፡፡

 

 

ቋንቋ መማሩ ለስራ ብቻ ሳይሆን ከሀገሩ ህዝብ ጋርም በቀላሉ ለመግባባትና ስለሀገሩ የበለጠ ለማወቅ ይረዳል፤ በመሆኑም እኔም ቋንቋቸውን ተማርኩ፤ የህዝቡንም አስተሳሰብና የዘወትር የውይይት አጀንዳዎች ለመረዳትም ቻልኩ፤ ዴንማርክ ህዝብ ንግግር ውስጥ አሽሙር ይበዛል፤ እንዲሁም በተገኘው አጋጣሚ ደስታና ሳቅ የፈጥራሉ፤ በዴንማርክ ህዝብ ዘንድ ራስን ከፍ ማድረግ የሚባል ነገር ቦታ የለውም፤ ለምሳሌ በስራ ቦታ ሙሉ ልብስና ሸሚዝ እንዲሁም ከረባት መልበስ እንደኋላቀርነት ይወሰዳል፤ ብዙውን ጊዜ ሰዎች ቲሸርቶች ይለብሳሉ፤ እንዲሁም ዶክተርና ፕሮፌሰር ብሎ መጠራራት የተለመደ አይደለም፤ አሰራራቸውም ቅልጥፍናን የተሞላ እጥር ምጥን ያለ ነው፤ ለምሳሌ ስብሰባዎቻቸው ብዙ ቢሆኑም ብዙ ሰአት ግን መሰብሰብ የተለመደ አይደለም፤ ቢሰበሰቡም አብዛኛውን በሳቅና በፈገግታ ስለሚታጀብ ስብሰባዎቻቸው አሰልቺ አይደሉም፡፡ በሀገራችን የስብሰባዎች ርዝመትና የስልጣን ተዋረድ ብዛት ስራዎችን ስለሚጎትት ከዴንማርክ ቀለል ያለና የተቀላጠፈ አሰራር ብዙ መማር እንችላለን፡፡ በተጨማሪም የሀገራችንን ብሄረሰቦች ቋንቋ ብንማር የበለጠ ለመግባባት ቀላል ይሆናል፡፡

 

የውጪ ሀገር የስራ ቆይታዬ

 

ኮፐንሀገን ዩኒቨርሲቲ ለመማር የትምህርት እድል ሳገኝ እጅግ ደስ ብሎኝ ነበረ፤ የደስታውም ዋናው ምክንያት ከትምህርቱ ጎን ለጎን ስራ ሰርቼ ገንዘብ አገኛለሁ የሚል ግምት ስለነበረኝ ነው፤ ነገር ግን የተጠበቀውን ያህል የስራ እድል አልነበረም፤ በዴንማርክ ሀገር ከሳለፍኩት አምስት አመታት ሁለቱን በትምህርት ያሳለፍኩ ሲሆን እየተማርኩም ስራ የመስራት ፍላጎት ቢኖረኝም ስራ ማግኘት ግል አልቻልኩም፡፡ ስራ ሲባል ታዲያ የፅዳት ሰራተኝነትም፣ አትክልተኝነትም፣ የጉልበት ስራም፣ ምግብ የማብሰል ስራም፣ ጋዜጣ የማዞር ስራም፣ የተገኘውን ስራ የመስራት ፍላጎት ነበረኝ፤ ስራዎቹን ለማግኘትም ብዙ ማመልከቻዎች አመልክቻለሁ፤ ነገር ግን አልተቻለም፡፡

 

በመጀመሪያው አመት የክረምት እረፍት ጊዜ በአንድ የአሜሪካኖች የምርምር ጣቢያ በጉልበት ሰራተኝነት ሰራሁ፤ በሁለተኛው አመት ክረምት እረፍትም እዛው ምርምር ጣቢያ ሰራሁ፤ ምርምሩ ጣቢያ በጎመንዘር ዘይት ላይ ነው የሚሰራው፤ ዋና አላማቸው የጎመንዘርን ዘይት ለሰው ጤና ተስማሚ እንዲሁም የማዳቀል ምርምር ነው፤ የጎመንዘር ዘይት በምርምር ካልተሻሻለ በውስጡ ካንሰር ሊያመጡ የሚችሉ ኬሚካሎች አሉት፤ በተጨማሪም ይህ የምርምር ተቋም እንደማኣድን የሚቆፈረውን የነዳጅ ዘይትን የሚተካ ከቅባት እህሎች ለተሸከርካሪዎች የሚሆን ዘይትም የመስራ አላማ አለው፡፡

 

ስራውን የተቀጠርኩት በመጀመሪያው አመት ከሁለት የሀገራችን ልጆች ጋር ስለነበረ ደስ የሚል ጊዜ ነበረን፤ ቢሆንም የመስክ ስራውም ቢሆን ለኔ ከባድ ነበረ፤ ዋናው ችግር ክፍያው በሰአት ስለሚከፈል አሰሪዎቹ ከሻይ እረፍት ጊዜ ውጪ በስራ መሀል እረፍት ስለማይፈቅዱ በጣም ይደክመኝ ነበረ፤ እኔ  ሀገራችን ብዙ ጊዜ ግብርና ስራ ሰርቻለሁ፤ የዴንማርኩ ለየት የሚያደርገው ብዙ እጅግ በፍጥነት እንድንሰራ መፈለጉ ነው፡፡ በእኔ አመለካከት ያንን አይነቱ ስራ እጅግ የሚያስጠላ ስራ፤ በትክክል ዘመናዊ ባርነት ነው፤ ምንም ደሀ ብሆንም መቼውንም ያንን አይነት ስራ አልመኝም፤ ይልቅ በዛ ስራ አጋጣሚ ስለዴንማርክ ግብርናና እንዲሁም ቀጣሪ ድርጅቶች ማሟላት ያለባቸውን መስፈርቶች አይቼ እጅግ ገረመኝ፤ የምርምር ድርጅቱ ሰራተኞች ሲቀጥር ለሰራተኞቹ በቂ ሽንትቤት፣ በቂ የመታጠቢያ ክፍል፣ በቂ የስራ ትጥቅ ማዘጋጀቱን በመንግስት አካላት ይገመገማል፤ የሚገርመው እኛን በጊዜያዊነት ሲቀጥሩን የኛ ስራ መስክ ላይ ቢሆንም ከነበሩት ሶስት መፀዳጃ ቤትና መጣጠቢያ ክፍል ለኛ የሚሆን ሶስት ተጨማሪ ሽንትቤትና መታጠቢያ ክፍል በብዙ ገንዘብ በጊዜያዊነት ተከራዩ፤ የምናድረው እዛ አይደለም፤ ለምን አስፈለገ ብለን ስንጠይቃቸው በዴንማርክ ህግ መሰረት ቀጣሪ ድርጅት ስራው ቦታ ለሰራተኞቹ ሁሉ የሚበቃ መታጠቢያና መፀዳጃ ቤት ያስፈልገዋል ብለው ነገሩን፤ የኛን ሀገር ብታዩ አልኩ በልቤ፤ 50 ሰራተኞችና ብዙ ተገልጋይ ደምበኞች ያሉት መስሪያቤት አንድ ሽንትቤትና ምንም መታጠቢያ ክፍል ላይኖረው ይችላል፤ እንዲሁም ውሀ የሌለው ሽንት ቤት ነው የሚሆነው አብዛኛን ጊዜ፤ ለነገሩ የመጠጥ ውሀ ያሌላቸው የሀገራችን ከተሞችና ቀበሌዎችም ብዙ መሆናቸውን ስለምናውቅ እድገት ሲባል የት ድረስ እንደሆነ ብቻ ግንዛቤ መውሰድ ነው፤ የዴንማርክንና የሀገራችንን የእድገት ልዩነት ዘርዝሬ ለመፃፍ አንድ ሙሉ መፄሀፍ አይበቃኝም፡፡

 

በምርምር ድርጅቱ የደቡብ ዴንማርክ ቆይታዬ ስለዴንማርክ ግብርናና በገጠር ስለሚኖረው ህዝባቸው የተሻለ ግንዛቤ ያገኘሁበት አጋጣሚ ነበረ፤ በስራችን ወቅት የኮንትራት ሰራተኛ የነበረች አንዲት የአከባቢው ወይዘሮ ነበረች፤ ስለሀገሮቻችን የፖለቲካና የዲሞክራሲ ልምድ ስንወያይ የዴንማርክ የፖለቲካ ስርአት እጅግ ያደገ መሆኑን ስነግራት ሴትየዋ ግን ብዙም ደስተኛ አለመሆንዋን ነገረችኝ፤ ይህንን የመሰለ ሰላማዊ ዲሞክራሲ እያላቸው ስለምን ደስተኛ እንዳልሆነች ስጠይቃት ዴንማርክ ሀገር ዲሞክራሲ እንደበዛባቸው ነገረችኝ፤ ሀሳቡ የሚገርም ነበረ፤ ምክንያቱም ዲሞክራሲ ሲበዛ ችግር ይኖረዋል ብዬ አስቤ ስለማላውቅ፤ ለምን ብዬ ስጠይቃት፣ ሀገራችን ዲሞክራሲ ስለበዛ በቤተክርስቲያኖቻችንም ጭምር ተመሳሳይ ፆታ የሆኑ ሰዎችን እስከማጋባት ደረሱ፤ ማህበረሰባችን ውስጥ ብዙ የከባድ ሱስ ተጠቂዎች አሉ፤ ልጆቻችንንም ከተመሳሳይ ችግር መጠበቅ አልቻልንም፤ ዴንማርክ ዲሞክራሲ በዝቶብናል ስትል ሀሳብዋን አጠናከረች፡፡

 

 

እናቱ የሞተችም፣ እናቱ ውሀ የወረደችም እኩል ያለቅሳሉ ይላሉ የሀገራችን ሰዎች

 

እኛ ሀገር ዲሞክራሲው እንጭጭ ስለሆነ አደጋው ለሰዎች ህይወት መጥፋት ነው፤ እነሱ ሀገር ደግሞ ሰዎች የፈለጉትን እንዲሆኑ ተፈቅዶላቸው ነው በቤተክርስቲያንም ጭምር እስከ ተመሳሳይ ፆታ ጋብቻ የደረሱት፤ ለሀገራቸው ህዝቦች ሁሉ ሰው ከተመሳሳይ ጾታው ጋር መጋባቱን ከቀጠለ አደገኛ ይመስለኛል፤ ምክንያቱም የሀገራቸው ህዝብ ቁጥር እየቀነሰ ነው፤ ስለሆነም ተመሳሳይ ፆታ ጋብቻው የህዝቡን ብዛት በበለጠ የሚቀንሰው ይመስለኛል፤ ምክንያቱም ከተመሳሳይ ፆታ ጋር የሚጋቡት ዜጎች ልጆች መውለድ የሚችሉበትን አጋጣሚ ስለሚያጡ ነው፡፡

 

እዛው ደቡብ ዴንማርክ በነበርን ጊዜ የአከባቢው ገበሬዎች ምርታቸውን እየሰበሰቡ ነበረ፤ የእርሻ ማሳዎቻቸው ስፋት ያስቀናል፤ በደቡብ ዴንማርክ፣ የሰሜን ጅርመን አጎራባች የሆኑት ማሪቦ ተብላ በምትጠራ ከተማ አከባቢ ሶልስቲድ በመባል ከምትታወቅ ነበር የቆየነው፤ በአከባቢው በብዛት ስንዴና ስኳር ድንች ይመረታል፤ ስኳር ድንቹ ለስኳር ፋብሪካ እንደግብአት የሚመረት ሲሆን ስንዴው ደግሞ ምርቱ ሲሰበሰብ ገበሬዎቹ በህብረት ስራ ማህበራቸው ጎተራ ያስቀምጡታል፤ ህብረት ስራው እያንዳንዱ ገበሬ ያመረተውን ስንዴ በኩንታል እየመዘገበ ይረከብና ቆንጆ ዋጋ በሚኖር ጊዜ ጠብቆ ይሸጣል፤ የዴንማርክ ገበሬዎቹ ሁሉ ምግባቸውን እንደከተማ ነዋሪ ከሱፕረማርኬት ገዝተው ነው የሚጠቀሙት፤ ስንዴ የሚያመርተው ገበሬ ለጊዜ ማሳለፊያው ያህል በጓሮ የሚተክላቸው አትክልት ቢኖሩም ለምግብ ፍጆታው የሚሆነውን ሁሉ ከሱፕረረማርኬት ገዝቶ ነው ሚጠቀመው፤ መሬቱ በመኪና ታርሶ በመኪና ስለሚታጨድ የዴንማርን ገበሬ ሀገራችን ካሉት ገበሬዎች ማወዳደር እጅግ ይከብዳል፡፡ ሁሉ ገበሬ የራሱን ትራክተር ራሱ እየነዳ ነው የሚያርሰው፣ እንዲሁም ትራክተሩ ቢበላሽ መጠነኛ ጥገና የሚያደርገው ገበሬው ራሱ ነው፡፡

 

 

 

እዛ በነበርኩበት ጊዜ የዘወትር ጥያቄዬ የራሳችን ሀገር ገበሬዎች መች ነው እንደነዚህ የሚሆኑት ብዬ ሳስብ የተለያዩ አማራጭ ሀሳቦች በአእምሮዬ ይመጣል፡፡ የመጀመሪያውና ትልቁ ጉዳይ የተበጣጠሰው የመሬት ይዞታ በገበሬዎች ህብረት ወደአንድ ትልልቅ ማሳዎች መመለስ ያስፈልጋል፤ ካልሆነ አሁን ባለው ሁኔታ የሀገራችን ገበሬ ቢበዛ ሁለት ሄክታር መሬት ነው የሚኖረው፤ ያቺው ሁለት ሄክታር የገሬዎቹ ልጆች አድገው የራሳቸው ትዳር ሲመሰርቱ ትከፋፈላለች፤ ቀስ በቀስ የግብርና መሬታችን በትራክተር ለመታረስ ወደማይችልበት ደረጃ ይደርሳል፤ ምክንያቱም አንድ ትራክተር ከተገዛ በቀን ብዙ ማሳ ማረስ ስለሚችል ገበሬዎቹ ማሳዎቻቸውን ድንበር በወረቀት ላይ አድርገው ወጥ በሆነ መንገድ ለዘመናዊ እርሻ እንዲመች ማደራጀት አለባቸው፡፡

 

የማይቻል ሀሳብ ሊመስለን ይችላል፡፡

 

ነገር ግን በሌሎች የአለማችን ክፍል ተሞክሮ ተግባራዊነቱ ተረጋግጧል፤ ስለሆነም የሀገራችን ግብርና በዘመናዊ መልክ ማደግ ካለበት ሁላችንም ትልልቅ ህልሞች ሊኖረን ይገባል፡፡ በተጨማሪም የገበሬውን የአስተሳሰብ ደረጃ ከፍ ማድረግ ይገባል፤ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ልጅ የአባቱን ድንበር በመግፋት እስከ ጥልና ፍርድቤት የሚደራረሱበት አጋጣሚ ብዙ ነው፤ መሰረታዊ ምክንያቱ ደግሞ ድህነትና አርቆ ማሰብ አለመቻል ነው፡፡ ችግሩን የመፍታት ሀላፊነት የሁሉም የተማሩ ዜጎች ግዳጅ ነው፤ በተለይ በግብርናና ልማት ዘርፍ የሰለጠኑ ባለሙያዎች እንዲሁም የመንግስት ሀላፊነት ነው፡፡

 

የውጪ ሀገር ስራን በተመለከተ ግን የሀገራችን ወጣት ውጪ ቢሄድ የስራው ሁኔታ ሊከብደው እንደሚችል አይገምትም፤ ነገር ግን ተራ የሚባለውን የፅዳት ስራም ለመስራት ምን ያህል እንደሚያደክምና እንደሚያሰለች እንዲሁም የሚያስፈልገው የቴክኖሎጂ እውቀት ብዙ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡

አንዱ ወዳጄ ስለውጪ ሀገር የስራ ሁኔታ ጠይቆኝ የፅዳት ስራ ልምዴን ነገርኩትና ስራው ይከብዳል፤ ቀለል አድርገህ አትየው፣ ያንኑ የፅዳት ስራም ለማግኘት ከባድ ነው ስለው ማመን አልቻለም፤ የፅዳት ስራ እንዴት ሊክብድ እንደሚችል ሊገባው አልቻለም፣ አንድም ቀን መጥረጊያ ይዞ ለማያውቅ ሰው ጽዳት ስራ ቀላል ነው ማለት ስህተት ነው፤ ፅዳት ሲባል ደግሞ በሀገራችን ቢሮዎች እንደሚፀዱት አይነት ሳይሆን በሰአት ተከፍሎ ቶሎ ቶሎ የሚሰራበት ስራ መሆኑንም መረዳት ያስፈልጋል፡፡

ህገወጥ ስራ

ትምህርቴን እንደጨረስኩ ግን ብዙ የመስራት ጉጉት ቢኖረኝም ስራ ማግኘት አልቻልኩም፤ ከብዙ ፍለጋ በኋላ በጥቁር ገበያ ወይም ህገወጥ መንገድ በአንድ የጃፓኖች የሱሺ ምግብ ፋብሪካ ውስጥ ስራ ጀምሬ ነበረ፤ ያ ፋብሪካ ኮፐንሀገን ከተማ አጠገብ ያለ ሲሆን ህጋዊ ድርጅት ነው፤ ነገር ግን የገቢ ግብር ላለመክፈል ሲል የስራ ፈቃድ የሌላቸውንና ሌሎችንም ከሌሎች ሀገሮች በስደትና በተለያዩ ምክንያቶች የመጡ ሰዎችን በሰአት 65 የዴንማርክ ብር እየከፈለ ያሰራ ነበረ፡፡

 

በህጋዊ መንገድ ሰራተኞችን በሙሉ ቀጥሮ ቢያሰራ ድርጅቱ ለሰራተኞቹ መክፈል ያለበት ገንዘብ ቢያንስ በሰአት 110 የዴንማርክ ብር ነው፤ ነገርግን ብዙዎቹ ድርጅቶች በተለይም የውጪ ዜጎች  ባለቤትነት ያላቸው የዴንማርክን ሀገር ህግ ጥሰው ሰራተኞችን በህገወጥ መንገድ ያሰራሉ፤ እግረ መንገዳቸውን የገቢ ቀረጡን ገንዘብ ለራሳቸው ያስቀራሉ፡፡ ነገር ግን ድርጅቱ ህገወጥ ሰራተኞችን ሲያሰራ ቢገኝ ወይም ሰራተኞቹን በህጋዊ መንገድ ሳይቀጥር እንደሚያስሰራ ቢደረስበት ትልቅ ቅጣት ነው ሚቀጣው፤ የንግድ ፍቃዱንም ሊወስዱበት ይችላሉ፡፡

 

ሰራተኞቹን በህጋዊ መንገድ መቅጠር ማለት አንድ ሰራተኛ እዛ ድርጅት ውስጥ መቀጠሩንና የተቀጠረበትንም የደሞዝ መጠን ለከተማው መዘጋጃ ቤት ማስታወቅና የስራ ስምምነታቸውንም ማስታወቅ ማለት ነው፡፡ ነገር ግን የስራ ፈቃድ የሌላቸው ሰራተኞች ህገዊ ስምምነት ማድረግ አይችሉም፤ ይህ ሁሉ መደረግ ያለበት ሰራተኛው ስራ ከመጀመሩ በፊት ነው፤ ከዚህ በኋላ ሰራተኛው በየወሩ በሰራተኛው የባንክ ቁጥር / በፍፁም በእጅ መክፈል አይቻልም/ ከሚከፈለው ገንዘብ ላይ የገቢ ግብር ይከፍላል ማለት ነው፡፡ ምናልባት ሰራተኛው በስራ ቦታ አደጋ ቢደርስበት ወይም ከአሰሪው ጋር አለመግባባት ቢፈጠር የከተማው መዘጋጃቤት የሰራተኛውን መብት ያስጠብቅለታል ማለት ነው፡፡ በተጨማሪም ድርጅቱ ከሰራተኛው የሚያገኘውን ገቢ ቀረጥ ይከፍላል ማለት ነው፡፡

 

ታዲያ እኔ ያንን ስራ መኖሩን ስሰማ ምንም የስራ ልምድ ባይኖረኝም በድፍረት ልሞክር ኄድኩኝ፤ ከመሄዴ በፊት ከኢትዮጵያዊያን ወዳጆቼ ምክር ተቀበለኩ፤ ምክሩም የስራ ልምድ አለህ ወይ ከተባልክ አዎ አለኝ ነው ማለት ኣለብህ፤ ልምድ የለኝም እንዳትል አይቀበሉህም ተባልኩ፤ እኔም እንደተነገረኝ አደረግኩ፤ በማግስቱ ሌሊት 9 ሰአት ቢሮ እንድትመጣ ተባልኩ፤ ሌሊት መሄድ ያስፈለገበት ምክንያት ድርጅቱ ማንም ሳያየው ህገወጥ ሰራተኞቹን ወደፋብሪካው ለማድረስ ነው፤ ማታ 9 ሰአት ላይ በቦታው ተገኘን፤ ምንም እንግሊዘኛ የማይችል አረብ ነው ይዞን የሚሄደው፤ ዴኒሽ ብቻ ይናገራል፤ እኔ በሰአቱ ዴኒሽ እየተማርኩ ቢሆንም ከሰውየው ጋር መግባባት የሚያስችለኝን ያህል ግን አልተማርኩም፡፡

 

በምልክት እየተግባባን ፋብሪካው ቦታ ደረስን፡፡ ስንደርስ 10፡30 አከባቢ ነው፤ ለጉብኝት የመጡ እንግዶች ዝርዝር የሚል ፎርም አምጥቶ ስማችንንና የመታወቂያ ቁጥራችንን አስመዘገበን፤ ማስመዝገቡ ያስፈለገበትም ምክንያት እንዳጋጣሚ ፖሊሶች ቢመጡና እኛን ስራ ላይ ቢያገኙን ለጉብኝት ነው የመጡት እንጂ ሰራተኞቼ አይደሉም ለማለት ነው፡፡ ፎርሙን ከሞላን በኋላ ቶሎ ታጥበን፣ ልብሳችንን በስራ ልብስ እንድንቀይር ተነገረን፤ ቀጥሎ ለሁላችንም ቦቲ ጫማ፤ ቱታ፤ ኮፊያ፤ የአፈንጫና አፍ መሸፈኛ፣ ጓንት ተሰጠን፤ ከዛ በሩ ላይ ያለ የጀርሞች መከላከያ ፈሳሽ ውስጥ ጫማችንን እየነከርን፣ እጃችንንም በኬሚካል ታጥበን ወደፋብሪካው ውስጥ ገባን፤ ማታውን ሲሰሩ ያደሩት ሰራተኞች በእኛ ተተክተው ሊወጡ ነው፡፡

 

 

 

ፋብሪካው አሰራሩ የበሰሉ የሱሺ መስሪያ ሩዝና ሌሎች ግብአቶች ቀርበው ምግቡን በትንሽ በትንሹ ማሸግ ነው፤ ምግቡ በብዛት ስለሚመረት ለተመጋቢው ጤንነት ሲባል እጅግ ከፍተኛ ጥንቃቄ ተደርጎ ነው ሚታሸገው፤ እኔ ሳህን መደርደር ስራ ተሰጠኝ፤ ሳህን ድርደራው ስራ ልክ በአየር መንገዶች ውስጥ ሻንጣ የሚያመላልሰው ተሸከርካሪ ጠረጴዛ ላይ ሱሺው ምግብ ማስቀመጫ የፕላስቲክ ሳጥን መሰል ሳህኖቹን ከፍቶ ተራ በተራ መደርደር ነው፤ ከዛ ቀጥሎ ያለው ሰራተኛ ከ 4 ወይም 5 የተለያዩ የምግብ አይነቶች ውስጥ አንዱን ሳህኑ ላይ ያስቀምጣል፣ ቀጥሎ ያለው ሰራተኛ ሁለተኛውን የምግብ አይነት እያስቀምጣል ሳህኑ የመጨረሻ ሰራተኛ ጋር ሲደርስ ተከድኖ በማሽን ይታሸግና ተደርድሮ ወደማቀዝቀዣ ክፍል ይወሰዳል፡፡

 

የእኔ ስራ ሳህን መደርደር ብቻ ሆኖ ሳለ የተሸከርካሪው ወንበር ፍጥነት ግን ከምችለው በላይ እየሆነብኝ ተቸገርኩ፤ በጣም በፍጥነት ሳህኖቹን መደርደር ይጠበቅብኝ ነበረ፤ እኔ ስዘገይ ከኔ ቀጥሎ ያለው ሰራተኛ ይዘገያል፤ አሰሪው እኔ ላይ ይጮህብኛል፤ ደንግጬ ስርበተበት ሳህኖቹን መሬት ላይ ተበተኑብኝ፤ የበለጠ ደነገጥኩ፤ ሳህኖቹን ልሰበስብ ጎንበስ ስል ሁሉም ሰራተኞች ጮሁብኝ፤ ለካ የወደቀ ሳህን ማንሳት ክልክል ነው፤ መሬት ላይ የወደቀውን ሳህን የማነሳው እኔ ሳልሆነ ሌሎች ሰራተኞች ናቸው፣ በየመሀሉ እየመጡ ድጋሜ መታጠብ ያለባቸውን እቃዎች ይሰበስባሉ፤ ሳህን ከመሬት ለማንሳት ገንበስ ስል ያየኝ አረቡ አሰሪ ሰውዬ መጣና እጄን ጎትቶ ይዞኝ ወጣ፤ ለምን ከመሬት ልታነሳ ሞከርክ ሲለኝ ዝም አልኩ፤ ‹በጣም ሲበዛ ቀስ ብለህ ነው የምትሰራው በዛ ላይ ምግቡን የሚያበላሽ ድርጊት ነው ያደረግከው፤ ስለሆነም ይህን ስራ መስራት የለብህም› ብሎ ይዞኝ ወጣና የሰራተኞች ምግብ የሚዘጋጅበት ኩሺና ውስጥ ይዞኝ ሄደና ምግብ ተበልቶባቸው ያልታጠቡ ሳህኖቹን እንዳጥብ አዘዘኝ፡፡

 

 

መጀመሪያ ጠረጴዛቹን አፅዳ ፤ቀጥሎ  ሳህኖቹን ከዛ መሬቱን ታፀዳለህ አለኝ፤ እሺ ብዬ ስራ ጀመርኩ፤ በመሃል መጣና እያፀዳሁ ቆሞ አየኝ፤ አሰራሬ አላማረውም መሰለኝ ተቀበለኝና እንዲህ ነው የሚሰራው ብሎ አሳየኝ፤ አሁንም ቆሞ ያየኛል፤ ቆሞ ሲያየኝ ደስ አላለኝም፤ መርበትበት ጀመርኩ፤ ለመፍጠን ነው የምርበተበተው፤ ጎበዝ ሰራተኛ ተብዬ የፅዳቱን ስራ በቋሚነት ለመቀጠር፡፡

 

ሰውየው የበለጠ እየተናደደ ሄደ፤ ይህንን ክፍል ለማፃዳት ከአንድ ሰአት በላይ ሊወስድብህ እኮ ነው፤ ቶሎ ቶሎ ለምን አትሰራም አለኝ፤ ዝም ብዬ ለመፍጠን ሞክርኩ፣ ነገር ግን ምንም አላስደሰትኩትም፤ የስራ ልምድ የሌለህ እንደሆነ ያስታውቃል፤ ለመሆኑ ተመሳሳይ ስራ ሰርተህ ታውቃለህ ብሎ ስጠይቀኝ አዎ ሰርቼ አውቃለሁ አልኩት፤ ውሸቴን ነው፤ የዋሸሁት ስራውን ላለማጣት ነው፤ ጠረጴዛውን ጨርሼ ወላሉን ማፅዳት ስጀምር ኬሚካል ተጠቀም አለኝ፤ ኬሚካሉ የቱ ነው ብዬ ስጠይቀው ተበሳጨና ከተደረደሩት ኬሚካሎች አንዱን አንስቶ ሰጠኝ፤ ውሸቴ አጋለጠኝ፣ ኬሚካሉን መጠቀም አልቻልኩም፤ ምክንቱም በምን ያህል ውሀ እንደሚበጠበጥ እርግጠኛ ስላልነበርኩ፤ ሄልፕ ሚ ብዬ እርዳታ ጠየኩት፤ እሱ ደግሞ ትእዛዝ ትሰጠኛለህ እንዴ ሲል በንዴት ጠየቀኝ፡፡

 

በሆዴ ውስጥ አንተን አይነት ያልተማረ ማዘዝ ትልቅ ነገር ነው እንዴ እያልኩ አይ ኬሚካሉን ምን ያህል መጨመር እንዳለብኝ ስለማላውቅ ነው አልኩት፤ በንዴት ተቀበለኝና ቶሎ ቶሎ ኬሚካሉን ከውሀው ቀየጠና መወልያውን ነክሮ መሬቱን መወልወል ጀመረ፤ እኔ ቆሜ አየዋለሁ እሱ ይወለውላል፡፡ ከዛ መወልወያውን ጥሎልኝ ወጣ፤ ስለሄደ ደስ አለኝ፤ ብዙም ሳይቆዩ አንዱን ሰራተኛ ይዞት መጣና እኔ እየወለወልኩ ቆመው እያዩኝ መሳሳቅ ጀመሩ፤ ስራውን አልወደደውም አለ ሌላኛው ሰራተኛ፤ ካልወደደው መምጣት የለበትም ነበረ አለ ሰውየው፤ ተናደድኩ፣ ቅጥል አልኩ፣ እውነት ነው፤ ለምን ሄድኩኝ? ለምንስ ህገወጥ ስራ ሰራለሁ? ለምንስ ሰርቼ የማላውቀውን ስራ በውሸት ልምድ አለኝ ብዬ መጣሁ? ራሴን መውቀስ ጀመርኩ፤ እንደምንም መወልወሉን ጨርሼ ልወጣ ስል ሰውየው መጣና ሁሉን ስራ እንደገና ደግሜ እንድሰራ ነገረኝ፤ በትክክል ስላልተሰራ ድገመው ብሎኝ ወጣ፤አማራጭ የለኝም፤ ደገምኩት፤ እኔ ስጨርስ መውጫ ሰአታችን ደረሰ፤ ከእስር ቤት የተፈታሁ ያህል እፎይታ እየተሰማኝ ወደቤቴ ሄድኩ፣ እዛ ስራ ቦታ ተመልሼ አልሄድኩም፡፡

የፅዳት ስራ

ከተወሰኑ ወራት በኋላ ሌላ የፅዳት ስራ ከኮፐንሀገን 150 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኝ ካሉንቦርግ በምትባል ከተማ አገኘሁ፡፡ ሰራው ፎቴክስ በሚባል የገበያ ማእከል ውስጥ ጽዳት ስራ ነው፡፡ ከርቀቱ በስተቀር ስራው ብዙም የሚከብድ አልነበረም፡፡ የስራ ሰአቱ ግን ከምሽት 3 ሰአት ነግቶ 12 ሰአት እስኪሞላ ድረስ የሚሰራ ነው፡፡ ሱፐርማርኬቱ በጣም ሰፊ ነው፤ የኔ የስራ ድርሻ የነበረው ዳቦቤታቸውንና ስጋቤታቸውን ማፅዳት ነበረ፤ የዳቦ ቤቱ ስፋት በግምት 300 ካሬ ሜትር ይሆናል፤ እንዲሁም ስጋ ቤቱ 200 ካሬ ሜትር አካባቢ ነው፡፡ ዳቦቤቱ ዳቦና ኬክ መስሪያ ብዙ ማሽኖች አሉበት፤ በተለይ የዳቦው ልውስ የሚለወስባቸው ሶስት ትልልቅ ገንዳዎች ለማጠብ አስቸጋሪ ነበሩ፤ በተጨማሪም ኬክ በሚሰራበት ወቅት የሚፈሰው የስኳር ልውስ ሊጥ ከመሬቱ ላይ በጣም ስለሚጣበቅ ለማስለቀቅ ብዙ መታሸት አለበት፡፡

 

አስተጣጠቡ መጀመሪያ ደረቅ ቆሻሻዎችን በመጥረግ ይጀመርና ቀጥሎ የሞቀ ውሃ ይደረግበታል፡፡ ከማሽኖቹ ውስጥ የተወሰኑት ውሀ የማይነካቸው ናቸው፤ ስለሆነም በጥንቃቄ መስራት ያስፈልጋል፡፡ ማሽኖቹ ውሀ ከነካቸው ስለሚበላሹ ለጥገና ከፍተኛ ወጪ ያስፈልጋል፡፡ ስራው ከመጀመሩ በፊት ተገቢ ስልጠና ያስፈልገዋል፡፡ ቢሆንም አንድ ምሽት እያፀዳሁ ሳለው በስህተት ውሀ የማይነካውን ማሽን ውሀ አስነካሁኝ፡፡ በመሆኑም ማሽኑን ለብልሽት ዳርጌው ነበረ፤ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያም ተሰጠኝ፡፡ የሰራው ሌላው ከባድ ጉዳይ ከኮፐንሀገን ተመላልሼ መስራቴ ነበረ፡፡ በባቡር ስለምመላለስ ባቡሮቹ የሚመጡት በ30 ደቂቃ ልዩነት ስለሆነ አርፍጄ መጥቼ ባቡር ሲያመልጠኝ እስከ አንድ ሰአት ድረስ ቆሜ መጠበቅ ነበረብኝ፤ በተጨማሪም ጠዋት ከስራ ወጥቼ ወደቤቴ ስመለስ ባቡር ላይ እንቅልፍ እየያዘኝ መውረጃ ፌርማታዬን አልፌ የምሄድበትም ጊዜም ነበረ፡፡

ለወደፊት  ቀድሞ  መዘጋጀት

በዴንማር ቆይታዬ ጊዜ ከሰራሁባቸው ቦታዎች አንዱ የዴንማርክ የሀይል ማእከል በመባል የሚታወቅ መስሪያቤት ነው፤ ለስድስት ወር ብቻ ገብቼ የእድሜ ልክ ልምድ ወስጄ ነው የወጣሁት፡ ቦታው የምርምር ማእከል ሲሆን ከኮፐንሀገን 40 ኪሎሜትር አከባቢ ሮስኪልዴ በምትባል ከተማ አጠገብ ሪሶ ተብሎ በሚታወቅ ትልቅ ግቢ ነው የሚገኘው፡፡ የኤሌክትሪክ ሀይልና የንፋስ ሀይል እንዲሁም የኒኩለር ሀይል ማእከል እንዲሁም የግብርና ምርት ነክ ጠለቅ ያሉ ምርምሮች ይሰሩበታል፡፡ እኔ ስሰራ እሰራበት የነበረው በገብስ ምርት ምርምር ነው፡፡ ምርምሩን በገንዘብ የሚደግፉት የቢራ ፋብሪካዎች ናቸው፤ አላማውም በአለም ሙቀት መጨመር ምክንያት ሊፈጠር የሚችለውን የምርት መቀነስ ለመከላከል የተሻሉ የገብስ ዘሮችን ማዘጋጀት ነው፡፡

 

ምርምሩ ወደፊት ከ70 አመት በኋላ ለሚመጣ የአየር ሁኔታ ተስማሚ የሚሆን የገብስ ዝርያ ማምረት ነበረ አላማው፡፡ ዋናው ጥያቄ ከ70 አመት በኋላ የሚኖረውን የአየር ንብረት እንዴት ያውቁታል ነው፤ እድሜ ለቴክኖሎጂያቸው፤ የወደፊቱ አየር ሁኔታ ትንበያ አላቸው፤ የአውሮፓ የሙቀት መጠን እስከ 4 ዲግሪ ሊጨምር ይችላል ተብሎ ነው የሚጠበቀው፤ ታዲያ ወደፊት የአለም ሙቀት ሲጨምር ከተለይዩ ፋብሪካዎች በጭስ መልክ የሚለቀቀው የካርቦንዳይ ኦክሳይድ አየር ይዘትም ይጨምራል፣ ካርቦንዳይ ኦክሳይድ አየር ደግሞ ሰብሎች ምግብ ለመስራት ከውሃና ከፀሀይ ብርሀን ጋር የሚያዋህዱት ግብአት ነው፤ በተጨማሪም የኦዞን ይዘትም ይጨምራል፡፡

 

በአውሮፓ ብዙ ዝናብ እንደሚኖርም ይጠበቃል፤ እንዲሁም የበረዶ ወራት ርዝመት ይቀንሳል፤ ለምርምሩ የሚሆኑትን የገብስ140 የገብስ ዝርያዎች ከተለያዩ የአለማችን ክፍሎች /ሀገራችንንም ጨምሮ/ በእጃቸው አስገብተዋል፡፡

 

ለነገሩ ገብስ ዝርያ መውሰዳቸው አይገርምም፤ የሰለጠኑት ሀገራት የተማሩ ልጆቻችንንም ስለሚወስዱ የሚገርም ነገር አይደለም፤ የጤፍንም ዘር እንደወሰዱብን ሰምቻለሁ፡፡

የተዘጋጁት ዘሮች የወደፊቱን 70 አመት የአየር ንብረት አስመስሎ የተሰራ የምርምር ክፍል ውስጥ ነው የተዘሩት፤ እኔ ስራዬ የገብሶቹን ተክሎች መንከባከብ፤ ገብሱ ሲደርስ ማጨድ፣ ዘሩንም፣ ገለባውንም ለየብቻ መሰብሰብ፣ ገለባው ከፍሬው መለየት፣ የተሰበሰበውን ገብስ ፍሬ ብዛት መቅጠር፣ የገለባውን ክብደት መመዘን፣ ወደኮምፒውተር ማስገባት፣ ወዘተ ነው፡፡

 

የሚገርመው ገብሱ የተዘራበት የምርምር ክፍል አሰራር ነው፤ ሙሉ ስሙ RERAF (Risø Environmental Risk Assessment facility) – a phytotrone controlled environment growth facility በመባል ይታወቃል፡፡ የምርምር ማእከሉ ሰው ሰራሽ የፀሀይ ብርሀንም አለው፤ እንዲሁም የተለያዩ የሙቀት መጠንና የተለያዩ የአከባቢ የአየር ይዘት፡፡ የአንድ ቀን ወጪው በሀገራችን ብር ሀያ አራት ሺ ብር አከባቢ ነው፤ ለስድስት ወር ምርምር የቤተ ሙከራው ወጪ ብቻ ወደ አምስት ሚሊየን ብር ይጠይቃል፤ የተመራማሪዎች ደሞዝ ክፍያ፣ የኬሚካሎች ወዘተ ሲጨመርበት ዋጋው ቀላል አይደለም፡፡

 

እዛ ቤተሙከራ ውስጥ ስሰራ ብዙ ጊዜ በሀሳብ ወደሀገር ቤት እየመጣሁ የሀገራችንን ዩኒቨርሲቲዎችና የምርምር ተቋማት ስራ አስባለሁ፤ የኛ ምርምር ለአንድ አመት ነው፤ በዛ ከተባል ለሁለት ወይ ለሶስት አመት፤ እነሱ የሚመራመሩት ለ70 አመት፡፡ እሰቲ አስቡት ርቀታችንን፡፡

 

ሌላው እጅግ የገረመኝ ነገር የዛ የምርምር ክፍል ሀላፊ ሙሉ ሳይንቲስት ናት፤ Rikke Bagger Jørgensen ትባላለች፡፡ መማርና መሰልጠን ማለት ምን ማለት እንደሆነ እንደምሳሌ ያሳየችን፡፡ ይህች ሳይነቲስት እኔን ለማስተማርና የተሻለ ሰው ለማድረግ የሚታደርገው ጥረት ይገርመኛል፡፡ እነሱ ጋር እየሰራሁ ነበር ሁለተኛ ልጃችን የተወለደችው፤ በሰኔ ወር ስራ እነሱ ገር ገብቼ በመስከረም ወር ሁለተኛ ልጃችን ተወለደች፡፡

 

የልጄን መወለድ ስነግራት የእናቴን ያህል ነው ደስ ያላት፤ እኔ በስራው ለመመስገን በትጋት ስሰራ ቶሎ ወደቤትህ ሂድ ብላ ትነግረኝ በበረ፤ አልፎ አልፎም ስራዬን ቤቴ ወስጄ እንድሰራ ትተባበረኝ ነበረ፤ ከሁሉ በላይ ግን ትህትናዋ በኛ ሀገር አነጋገር የቤት ሰራተኞች ወይም የአገልጋይ አይነት ነው፡፡ ሁሌም ፈገግታ አይለያትም፣ አንዳነዴ እየተሳሳትኩ ስራው ሲበላሽም በፈገግታ ነው የምታርመኝ፡፡

 

እስዋንና የኛን ሀገር የተማሩ ምሁራን ሳወዳድር የኛዎቹ ምንም ያልተማሩ ነው የሚመስለኝ፤ የኛ ሀገር ምሁራን ሁሉንም ማለቴ ባይሆንም ከስራቸው በፊት ስማቸው ይቀድማል፣ ዶክተር እከሌ ወይም ፕሮፌሰር እከሌ ተብለው ካልተጠሩ ያልተማሩ የሚመስላቸው ብዙ ናቸው፤ በኛ ሀገር ብዙ መማር ማለት ብዙ አለመስራት ሌሎች ብቻ ማዘዝ ከታች ያለውን አሳንሶ ማየት፣ እውቀት የኔ ብቻ ነው ብሎ የሌሎችን ሙያ ማጥላላት ወዘተ ብዙ ብዙ ችግሮች አሉ፡፡

ከሌሎች ሀገራት ልምድ

 

ወደታይላንድ የሄድነው ለመስክ ጉብኝት ነው፤ ትምህርታችን ግብርና ልማት ስለነበረ ከአውሮፓ ግብርና ይልቅ ለታዳጊ ሀገራት ምሳሌ ሊሆን የሚችል ግብርና ታይላንድ ሀገር ነበረ፤ በሀገራችን የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ለመስክ ጉብኝት ይዞ ለመሄድ መኪና ማግኘትና የተማሪዎችን የሁለት ቀን ወጪ መሸፈን እንደ ትልቅ ወጪ ይቆጠራል፤ የኮፐንሀገን ዩኒቨርሲቲ ግን ተማሪዎቹን ከዴንማርክ ታይላንድ ድረስ ወስዶ ተጨባጭ የመስክ ልምድ እንዲኖቸው ያደርጋል፤ ታይላንድ እውነትም ከአውሮፓ ትለያለች፤ለምሳሌ ምግባቸው እጅግ ይለያል፤ በሰሜን ታይላንድ ከቻንግማይ ከተማ ወጣ ብሎ ባነ ፓን ኢካ የምትባል ትንሽ የገጠር መንደር ነበረ የቆየነው፤ በአስተርጓሚ በመታገዝ ገበሬዎች በአከባቢያቸው ካለው የደን ሀብት ምን ጥቅም እንደሚያገኙ ቃለመጠይቅ እናደርግ ነበረ፡፡

 

 

አንዲት እናት የነገረችንን መቼም አልረሳውም፤ ከደኑ ውስጥ ለምግብነት የሚሆን እባብ፣ አይጥ፣ ወፎች፣ የወፎች እንቁላል፣ አሳማ፣ የጉንዳን እንቁላል፣ የማገዶ እንጨት፣ ማር፣ የቤት መስሪያ እንጨት ወዘተ እንደሚያገኙ በደስታ ነገረችን፡፡ እባቡን እንዴት አድርገው እንደሚይዙት ሳስብ ፈራሁኝ፡፡

 

ለታይላንድ የቱሪስት ገቢ ቁጥር አንድ የውጪ ምንዛሪ ገቢያቸው ነው፣ ከሀገራቸው የቱሪስት ማእከል ና የውጪ ምንዛሪ ምንጭ  ውስጥ እዛው ቻንግ ማይ አጠገብ የዝሆኖች ፓርክ አለ፡፡ በጣም የሚገርመው ዝሆኖቹን እንደሰው አሰልጥነዋቸዋ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ዝሆኖች ስእል ሲስሉና የእግር ኳስ ሲጫወቱ፣ በአከባቢው ትእይንታቸውን የሚመለከተውን ህዝብ ሰላምታ ሲሰጡ ሳይ የሰው ልጅ አእምሮና እውቀት ከሰው አልፎ ለእንሰሳትም በስልጠና መልክ እንደሚተላለፍ አይቼ ተደመምኩ፤ ዝሆኖቹ የሚስሉትን ስእሎች ቱሪስቶች በብዙ ዶላር ገዝተው ለማስታወሻ ይዘው ወደሀገራቸው ይሄዳሉ፡፡

 

ዝሆኖቹ ስእሉን የሚስሉት በአሰልጣኛቸው እገዛ ነው፡፡ አሰልጣኙ ትልቅ የስእል መሳያ ቦርድና ቀለምና ብሩሽ ካዘጋጀ በኋላ የቀለሙን ብሩሽ ለዝሆኑ ኩንቢ ካቀበለ በኋላ የዝሆኑን ጆሮ በተለያዩ አቅጣጫዎች በማንቀሳቀስ ዝሆኑ ምስሉን እንዲስል ያደርጋል፡፡ ትእይንቱን የበለጠ ለመረዳት የሚቀጥለውን ድህረገፅ ማየት ይቻላል፡፡

(https://www.google.com/search?q=elephants+drawing+picture+thailand)

 

የሌሎች ሀገራትን የትምህርት ተሞክሮ ወደሀገራችን ለመውሰድ ሊተኮርበት የሚገባው ገዳይ በሀገራችን ትምህርትንና ለትምህርት ያለን አመለካከት ብዙ መሻሻል ያለበት ነገር አለ፡፡ ተማሪዎች በክፍ ውስጥ ከሚማሩት በተጨማሪ ከመስክ ጉብኝት ብዙ እውቀት ያገኛሉ፡፡ ለምሳሌ የምግብ ሳይንስ ለሚማሩ ተማሪዎች ወደምግብ ፋብሪካዎች ሄዶ መጎብኘት በክፍል ውስጥ የሚማሩትን በቀላሉ እዲገነዘቡ ያግዛቸዋል፡፡

 

 

በተጨማሪም የሚማሩትን ትምህርት እንዴት ወደተግባር እንደሚቀይሩና በስራው አለም ያለው እውነታ ምን እንደሚመስል የተወሰነ ግነዛቤ ያገኛሉ፡፡ በተጨማሪም ከጉብኝት ተጨማሪ ሀሳቦችንና ግንዛቤ ይወስዳሉ፡፡ እኔ አውሮፓ ከቆየሁባቸው ጊዜ ይልቅ ታይላንድን ሄጄ መጎብኘቴ እጅግ ብዙ ነገሮችን እንዳውቅ ረድቶኛል፡፡ በሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ከኢትዮጵያ ውጪ ተማሪዎችን ይዞ መሄድ ባይቻልም ዩኒቨርሲቲዎቹ ያሉበትን አከባቢና ትልልቅ ፋብሪካዎችን እዲሁም የተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ቢጎበኙ ብዙ ግንዛቤ ያገኛሉ፡፡

 

እኔ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪ ሆኜ በ1997 ከመመረቃችን በፊት ወላይታ ሶዶ፣ አርባምንጭ፣ ኮነሶ፣ ደቡብ ኦሞ ጂንካ፣ ፊቼ፣ የአባይ በረሃን፣ ደጀን፣ ደብረማርቆስ፣ ዳንግላ፣ ባህርዳር፣ አውራምባን እነኚህን ቦታዎች ለመጀመሪያ ጊዜ የመጎብኘቱ እድል ነበረኝ፡፡ በዛ የ15ቀን ጉብኝት ስለሀገራችን እጅግ ብዙ ግንዛቤ አገኘሁ፤ በተለይ አውራምባና ጂንካ ያየሁትና መቼውንም አይረሳኝም፤ ቢሆንም ጉብኝቱን አንዳንድ መምህራን እንደብክነት ሲናገሩ ሰምቻለሁ፡፡

 

ተማሪዎቹን ቱሪስት አደረጉዋቸው ይህንን ሁሉ ጉብኝት ለምን ተፈቀደ ወዘተ በማለት አጋጣሚውን እንደስህተት የሚናገሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ ከኛ ጉብኝት ጀምሮ የተማሪዎች የትምህርታዊ ጉዞ የኪሎሜትር ርቀትም ዝቅ ተደርጎ መቀነሱን ሰምቻለሁ፡፡ ሁላችንም ልንገነዘበው የሚገባው ጉዳይ ሀገራችን ውስጥ የገንዘብ እጥረት ችግር የለም፤ ዋናው ችግር ያለውን ገንዘብ በሚገባ የማስተዳደር ችግር ነው ያለብን፤ ለተማሪዎች የመስክ ጉብኝት የሚወጣው በጀት የክፍል ውስጥ ትምህርትን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ መሆኑን ግንዛቤ መያዝ ያስፈልገናል፡፡ ልጄ ኬጂ 2 ነው የምትማረው፣ በእነሱ እድሜም ቀኑን ሙሉ ወንበር ላይ ተቀምጠው እንዲማሩ ነው የሚያደርጉት፤ አንድ ቀን ልጆቹ ከሚማሩበት መዋለ ህፃናት ወጣ ብለው አከባያቸውን እንዲጎበኙ አይደረግም፡፡

 

 

ብዙዎቹ የሀገራችን መምህራንና ትምህርት ቤቶች ትምህርትን ከመፅሀፍ ብቻ በጉልበት እንድንማር ነው የሚፈልጉት፡፡ ስለእንሰሳት የሚያስተምረው መምህር ላሞቹን ተማሪዎች እየነኩ እያዩ ቢማሩ የበለጠ እንደሚገባቸው መረዳት ያስፈልጋል፡፡

 

ይህ ሀሳብ የግል አስተያየት ስለሆነ ትክክልኛውን ውድድር ለማድረግ ከሁሉም ሀገራት ተጨባጭ መረጃ መውሰድ አስፈላጊነቱን በሀሳባችን ይዘን እኔ የበኩሌን አስተያየት ልስጥ፤ በቅርቡ ዩጋንዳን የመጎብኘት አጋጣሚ አግኝቼ ነበረ፤ ካምፓላንና አዲአበባን ሳወዳድር በተወሰነ መልኩ አዲስ አበባ ከካምፓላ የተሻለች እንደሆነች ተሰማኝ፤ ለምሳሌ በትራፊክ ደህንነት፡፡ የከተማ ጥራትም ቢሆን የኛዋ አዲስአበባ የተሻለ ደረጃ ያለች ይመስለኛል፤ በተረፈ የውጪ ሀገር ምንዛሬ ማግኘት በካምፓላ እንደልብ ነው፤ ለሀገራቱ የሚሰጠውን ጥቅም ባላውቅም፤ የውጪ ምንዛሬ እንደልብ በከተማዋ መገኘት ጠቃሚ ከሆነ ካምፓላ ከአዲስ አበባ ትሻላለች፡፡

 

ነገር ግን ሙስና በበዛበት ሀገራችንና በአጠቃላይ አፍሪካ ውስጥ የገንዘብ ዝውውር በተለይም ደግሞ የውጪ ምንዛሬ ላይ ጥንቃቄ መደረጉ ከፍተኛ ሀላፊነት ላይ ያሉትን ጥቂት ዜጎች አላግባብ ካልጠቀመ በስተቀር ለሀገር ጠቀሜታው ከፍ የሚል ይመስለኛል፡፡ የግል አስተያየቴ የውጪ ምንዛሬ እንደልብ ማግኘት ቢቻል በሙስና የተሰበሰበው የሀገራችን ህዝብ ገንዘብ  በቀላሉ ወደውጪ የሚላክና የሚጠፋ ይመስለኛል፡፡ ሌብነትን የመለካከያው አንዱ መንገድ የሌቦችን ተቀባይ መቀነስ ስለሆነ፤ ሌቦቹን ከሚቀበሉት አካላት ደግሞ አንዱ የውጪ ሀገራት ናቸው ሲባሉ በተለያዩ የአለም አቀፍ ሙስና ጥናት ድህረገፆች አንብቤያለሁ፡፡

 

ስለሆነም ሌባው ባለስልጣን የሰረቀውን ገንዘብ ወደውጪ ሀገር ከመላክ ይልቅ የተለመደውን ፎቅ ይሰራበታል፤ ፎቁ በስርቆት የተሰራ ቢሆነም እዚሁ ሀገራችን ለከተማ ውበት መሆኑ በተወሰነ መልኩ በጎ ነው፡፡

የታይላንድ ሀገር ቆይታዬ ከአንድ ወር ባይበልጥም ስለሀገራቸውና ስለህዝባቸው የኑሮ ዘይቤ በጎና መጥፎ ጎን የተወሰነ ልምድ መቅሰም ችያለሁ፤ ታይላንድ መካከለኛ ገቢ ውስጥ ያለች ሀገር ናት፣ ህዝቦችዋ እጅጉን እንግዳ ተቀባይ ናቸው፡፡ በሀገራችን አንድ የውጪ ሀገር ዜጋ ሲመጣ እቃ ለመግዛት ሲጠይቅ የተለመደው የገበያ ዋጋ ከፍ ተደርጎ ነው የሚነገረው፤ እቃ ሊገዛ የገባበት ሱቆ ሳይገዛ ቢወጣ ስድብ ሊከተለው ይችላል፡፡

 

የታይላንድ ሀገር ነጋዴዎች ግን ደንበኞቻቸውን በታላቅ ክብር ነው የሚያስተናግዱበት፡፡ የታይላንድ ታላቅ መጥፎ ጎን የሴትና አዳሪዎች መብዛት ነው፡፡ የሴቶቹ ጉዳይ እጅግ ያሳዝናል፡፡ በአውሮፕላን ማረፊ በር ላይ የወጣት ሴቶችን ፎቶ ለወሲብ ንግድ በአደባባይ የሚያስተዋውቁ ነጋዴዎችን በብዛት አይቻለሁ፡፡ ምግብን በተመለከተ የታይላንድ ህዝብ የተገኘውን ነው የሚመገቡት፡፡ በሰሜን ታይላንድ ቻንግማይ ከተማ አከባቢ ባን ፓን ኢካ በመባል በምትጠራ የገጠር ቀበሌ ከማህበረሰቡ ጋር እየኖርን የደን ሀብት ቁጥጥርና አጠቃቀም ስርአታቸውን ለማጥናት ነበረ ከዴንማርክ ወደታይላንድ የሄድነው፡፡ በሀገራችን ዪኒቨርሲቲዎች የመስክ ጉብኝት 5ኪሎ ሜትር ርቀት ሄዶ መመለስ ከባድ ሆኖ ተማሪዎች በክፍል ውስጥ ትምህርት ብቻ እንዲመረቁ የምናደርግበት ጊዜ ብዙ ነው፡፡ ታይላንድ ሄደንም ብዙ ተምረን ነው የተመለስነው፡፡ ለምሳሌ ምግብን በተመለከተ እባብ፣ እንቁራሪት፣ አይጥ፣ ጉንዳን፣ ወፎች፣ የወፎች እንቁላል፣ የጉንዳን እንቁላል፣ አሳማ፣ በአጭሩ ህይወት ያላቸውን እንሰሳት ሁሉ ይመገባሉ፡፡

 

ነገር ግን በግብርና መሬት አስተዳደር በኩል ታይላንድ ከተወሰኑ አመታት በፊት መሬት እንዲሸጥና እንዲለወጥ እንዲሁም የውጪ ዜጎችም ጭምር መሬት መግዛት እንዲችሉ አድርጋ ነበረ፤ የመሬት ባለቤትም ገበሬዎች ነበሩ. ቢሆንም ገበሬዎቹ መሬታቸውን ሸጠው ገንዘቡንም አባክነው በመጨረሻ በከተሞች ጎዳና ለልመና የተዳረጉበትን ሁኔታ አይተናል፡፡ ታይላንድ የቱሪዝም ገቢ ቁጥር አንድ የሀገሪቱ የውጪ ምንዛሪ ምንጭ ነው፡፡

 

 

 

ስለስዊዲንና ዴንማርክ ጉርብትና ያስተዋልኩት ነገር ሁለቱ ሀገራት አብረው የሚኖሩት እንደ አንድ ሀገር ነው፤ የሁለቱ ሀገር ዜጎች በነፃነት የፈለጉት ሀገር ሄደው መስራትና መኖር ይችላሉ፤ የተለያዩ ማህበራዊ ዋስትናም ተጠቃሚ ናቸው፤ የሁለቱ ሀገራት ድንበር ፍተሻ የለውም፡፡ የዱሮ ታሪካቸው ሲታይ ደግሞ ዴንማርክ ሰዊዲንን በቀኝ ግዛት ይዛ ነበረ፤ ዛሬ ግን ሰላም ናቸው፤ ልዩነታቸውን ማየት አይቻልም፡፡

 

እስቲ ራሳችንን እንጠይቅ፤ ሀገራችን ከጎሮቤቶችዋ ጋር እንዴት ናት፤ ከኤርትራ ጋር፣ ከሶማሊያ ጋር፣ ከሱዳን ጋር፣ ከኬንያ ጋር፣ ከጅቡቲ ጋር…መልሱን ለአንባቢያን ትቻለሁ፡፡ አንድ እውነታ አለ፤ ማንም ሀገር ጎሮቤት ጦርነት ኖሮ ዘላቂ እድገትን ሊያመጣ አይችልም፣ ምንክነያቱም፡- ከዛ ሀገር ጋር ንግድ ይቀንሳል፤ በጦርነቱ ምክንያት ስደተኞችን መቀበል ያስፈልጋል፣ ስደተኞች ብዙ ችግሮች ይዘው ይመጣሉ፣ ለሰላም ሲባል ድንበር አከባቢ የመከላከያ ሰራዊት መኖር አለበት ያም ተጨማሪ ወጪ ያስወጣል፡፡

 

ለምሳሌ የሴሪያን ጦርነትና ለጎሮቤት ሀገራት ያስከተለውን የስደተኞች ጫና እንደምሳሌ መውሰድ ይቻላል፡፡ እንግዲህ የሀገራችንም ዘላቂ ልማት መረጋገጥ ካለበት እንዲሁም ለጎሮቤቶቻችንም ዘላቂ ሰላም ሲባል በሰላም አብሮ መኖር የግድ ነው፡፡ ጀርመን ሀገር ሄጄ ያየሁት ከዴንማርክ ጋር ተመሳሳይ ነው፤ የሁለቱም ሀገር ዜጎች ከእንግሊዘኛ ይልቅ የራሳቸውን ቋንቋ ነው መናገር የሚፈልጉት፤ ልማታቸው ተመሳሳይ ነው፣ ሁለቱም ሀገራት ብዙ ቢራ የሚጠጡ ዜጎች ይበዛሉ፡፡

ካምፓላ

እድሉ ተገኘና የዩጋንዳዋን ዋና ከተማ ካምፓላ ለመጎብኘት ቻልኩ፡፡ ከኢትዮጵያ ውጪ ለመጀመሪያ ጊዜ ያየሁት ሀገር ዴንማርክ ኮፐንሀገንን ስለነበረ ሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች በምን ያህል ከሀገራችን እንደሚሻሉ ለማወቅ ወይም ባደጉና ባላደጉ ሀገራት መካከል ያለውን ልዩነት ለማስተያየት እንደምሳሌ የምወስዳቸው እዚሁ ሀገራችን የማውቃቸውን ከተሞችና የኑሮ ሁኔታ ብቻ ነበረ፡፡

ስለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ሲነሳ እኔ ከአውሮፓዊያን የተለየ የማውቀው ብዙም አልነበረም፡፡ ይልቁንም አውሮፓዊያኑ በተገኘው አጋጣሚ የሌሎችን ሀገራ የመጎብኘቱ ልምድ ስላለቸው ሁለት ወይም ሶስት ሀገራትን ሄደው የጎበኙ ብዙዎች ናቸው፡፡ ስለሆነም እነሱ በኣፍሪካ ሀገራት ለጉብኝት ሄደው የጎበኙትን ይነግሩኛል፡፡

ወደዩጋንዳ ስሄድ ከዴንማርክ፣ ከጀርመን፣ ከታይላንድ፣ ከስዊዲን፣ ከኬንያና ከሀገሬ ከኢትዮጵያ ያየሁትን ነገሮች በአእምሮዬ በመያዝ ነው፡፡ ታዲያ ዩጋንዳ ስደርስ ብዙም የተለየ ስሜት አልነበረም የተሰማኝ፡፡ ብዙ ነገሮቹ ከሀገራችን ጋር ተመሳሳይ ናቸው፡፡ መጀመሪያ ካምፓላ የወላይታ ሶዶ ወይም የጎንደርን የተወሰኑ ገፅታዎች እንዳላት ነው የተሰማኝ፡፡ የመሬቱ ወጣ ገባማነት፣ዳገትና ቁልቁለቱ ከጎንደር ጋር ያመሳስላታል፡፡ የመንገዶችዋ ጥበት፤ የትራፊኩ ግራ አጋቢነት/በተለይ የሞተር ሳይክሎቹ ብዛትና ፍጥነት እንዲሁም የመንገዱን ግራ ጥግ ይዘው መንዳታቸው/ የተለመደ ነገር አይደለም፤ በዚህ ረገድ ነኔ የኛዋ አዲስ አበባ ትሻላለች፡፡

የዪጋንዳን ዜጎች እንግዳ አክባሪነታቸውን አድንቄላቸዋለሁ፡፡ በተጨማሪም በአዲስ አበባችን እንደምናየው ብዙ የመንገድ ላይ ለማኝ አላየሁም፡፡ እንደከተሞቻችን ፈረንጅ ሲታይ ለማኙ ሁሉ ይሰበስብ ከሆነ ብዬ ልብ ብያለሁ፡፡ ነገር ግን ምንም ለማኝ አላየሁም፡፡ ሌላው የሚገርመው ነገር ዩጋንዳ የክርስቲያን ሀገር መሆንዋ ነው፡፡ የክርስቲያን ሀገርነቱ በመንግስት ደረጃ የታወቀና በዩኒቨርሲቲዎችም ጭምር ስብሰባዎች ሲጀመሩና ሲጠናቀቁ በፀሎት መጀመርና በምስጋና መዝጋት የተለመደ ነው፡፡

አንዱን የዩኒቨርሲቲ መምህር ስለጉዳዩ አማክሬ የተነገረኝ የኢዲአሚን መንግስት በነበረ ጊዜ ሀገራቸው የሙስሊም ሀገር ነበር የምትባለው፡፡ አሁን ስልጣን ላይ ያለው ሲመጣ ደግሞ የክርስቲያን ሀገር ተባለች፡፡

 

 

የክርስቲያን ሀገርነቱን ለማስረገጥም መንግስት ተቀይሮ ለመጀመሪያ ሰሞን በየመንግስት መስሪያቤቶች የስብሰባ መወያያ ርእስ ሲያዝ የፀሎትና የምስጋና ፕሮግራም እንደአንድ አጀንዳ እንደሚያዝ ነገረኝ፡፡ አሁን አሁን የሀይማኖታዊ ስርአቱ ቀዝቀዝ ማለቱን ነገረኝ፡፡ እኔ በተገኘሁበት የዩኒቨርሲቲ ስብሰባ መክፈቻ ንግግር የተደረገው በፀሎት ከተከፈተ በኋላ ነበረ፡፡ ይህን አይነቱን አሰራር ከሃገራችን በጣም የተራራቀ ሆኖ ያገኘሁት ሲሆን የሀገራቸው ህዝቦች ሀይማታዊ መቻቻል አስደምሞኛል፡፡ ስብሰባዎቹ ላይ የእስልምና ሀይማኖት ተከታይ ቢኖር ቅድሚ ተሰጥቶት ስብሰባውን በፀሎት እንደሚጀምሩ ተነግሮኛል፡፡

ሌላው ልዩነት፣ ዩጋንዳ ሀገር ብዙ የውጪ ሀገር ባንኮች አሉ፡፡ የውጪ ምንዛሪ በየቦታው አለ፡፡ ይህም ከሀገራችን ጋር እጅግ የሚያራርቃቸው ነው፡፡ ታዲያ ይህ ሁሉ የውጪ ባንክ ቢኖርም ዩጋንዳ ከኢትዮጵያ በተለየ መልኩ ያደገች አትመስልም፡፡ ይልቁንም በአንዳንድ ነገሮች ሀገራችን የተሻለች ናት፡፡ ማቶኬ በመባል የሚታወቀውን ከሙዝ የተሰራ ገንፎም ያልተጠበቀ ምግብ ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡

ወደ ዩጋንዳ እየሄድኩ አውሮፕላን ውስጥ አጠገቤ የተቀመጡ ኢትዮጵያው ተሳፋሪ በአንድ የሀገራችን ትልቅ መስሪያቤት ለ30አመት ያህል አገልግለዋል፡፡ አዳዲስ የንግድ ተቋማትን መመስረት በተመለከተ ስልጠና ለመስጠት ወደቦስትዋና እየሄዱ ነበረ፡፡ ቦስትዋና ሀገር ብዙ የሀገራችን ሀኪሞች አሉ ይባላል፡፡ ምን ያህል እውነት ነው ብዬም ጠይቄ ነበረ፡፡ አዎ ብዙ የሀገራችን ሀኪሞች አሉ አሉኝ ሰውየው፡፡ እንዴት ነው ሀገራችንን የሚጎዳ አይመስልዎትም የባለሞያዎቹ ስደት ስላቸው አዎ ይጎዳል፡፡ ባለሙያዎቹ ግን ተጠቃሚ ናቸው አሉኝ፡፡ በዚህ የተነሳ ስለሀገር ብዙ ተወያየን፡፡ ሰውየው 5 ልጆች አሉዋቸው፡፡ ከ5 ልጆቻቸው 4ቱ አሜሪካን ሀገር ነው ያሉት፡፡ ሁለቱ ሀኪሞች አንዱ መሀንዲስ ሌላኛው የኮምፒውተር ኢንጂነር፡፡

 

 

 

ስለልጆችዎ ምን ይሰማዎታል የሚል ጥያቄም አቅርቤ ነበረ፤ ከሀገራቸው ውጪ ስለመስራታቸው የእርስዎ አስተያየት እንዴት ነው ስላቸው እጅግ ደስተኛ መሆናቸውን ነገሩኝ፡፡ በተጨማሪም እንዲህ ብለው ሀሳባቸውን አጠናከሩ፤ እኔ እስከማውቀው ድረስ አብዛኛው ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣንና የተማረው ቤተሰብ ሁሉ ልጁ ውጪ ሀገር እንዲሰራና እዛው እንዲኖር ነው የሚፈልገው፡፡ እኔም የተለመደውን ነው ያደረግኩት ብለው ሀሳቡን በአጭሩ ነገሩኝ፡፡

ወደኢትዮጵያ ስንመለስ ደግሞ ናይሮቢ ላይ አብራኝ ተሳፍራ አብራኝ የተቀመጠችው ልጅ ወደቤሩት ለመሄድ ፈልጋ ከኢትዮጵያ መጥታ ኬንያ ላይ ተይዛ እየተመለሰች ነው፡፡ ብዙ ከማልቀስዋ የተነሳ ፊትዋ አባብጦ ነበረ፡፡ ለሳምንት ያህል ጊዜ እዛው ናይሮቢ አውሮፕላን ማረፊ ውስጥ እንደሰነበተች ነገረችኝ፡፡ በጣም የሚገርመው ደግሞ ልጅቲቱ ከሳውዲ ከተመለሱት አንዷ ናት፡፡ ሳውዲ ሄደሽ አይተሽ ለምን ድጋሜ ትሳሳቻለሽ ችግሩን አይተሽው የለም እንዴ ስላት፣ አይ የአክስቴ ልጅ እዛ ስላለች እስዋ ጋር ሄጄ ልሰራ ነበረ አለችኝ፡፡ ለሁሉም ኢትዮጵያችን እንዲህ ናት፡፡

ገንዘብ ያለው በገንዘቡ ከፍሎ ገንዘብ የሌለው ደግሞ ህይወቱን ሸጦ ወደውጪ ይሄዳል፤ ልጆቹን ይልካል ወዘተ፡፡ ለዜጎችዋ መመኪያ የሆነች ሀገር መሰራት አለበት፤ እስካሁን ኢትዮጵያዊ ዜግነት ከስደት ሊያድነን አልቻለም፡፡ ለትምህርትም ይሁን ለስራ፣ ብሩህ አእምሮ ያላቸውን ልጆቻችንን ወደውጪ ልከን ሀገራችንን እናሳድጋለን ብለን ማሰብ የለብንም፡፡ ሀገር የሚያድገው በሰው ልጆች ነው፤ ስለሆነም ስለሀገራችን ስናስብ እድገትዋን ሊያመጡ የሚችሉ ዜጎችዋን እንደምንም ብለን እዚሁ ሀገራቸው ላይ ሰርተው ራሳቸውንና ሀገራቸውን እንዲቀይሩ ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡

 

አባትነት በዲያስፖራው አለም

 

ይህ ለብዙ አባቶች መነገር ያለበት ታሪክ ነው፤ እኔ አንዷ ልጄ ሀገራችን፤ ሌላዋ ልጄ ደግሞ ውጪ ሀገር ነው የተወለዱት፤ የመጀመሪያ ልጄ ስትወለድና ሁለተኛዋ ልጄ ስትወለድ ስለልጅ፣ ስለእናትነትና ስለአባትነት የነበረኝ አመለካከት ብዙ ተቀየረ፤ ምክንያቱም ልጄ ውጪ ስትወለድ ሀኪሞቹ ማዋለጃ ክፍል ውስጥ ገብቼ ሁሉን ነገር ማየት እንዳለብኝ ስላደረጉና መታየት አለበት ብለው ስለሚያምኑ፤ የምጥን ከባድነትና አስጨናቂነት በአይኔ እያየሁ ክብደቱን ተረድቻሉ፤ ማዋለጃው ክፍል ውጪ መቆምና ውስጥ ገብቶ ሁሉን ነገር ማየት እጅግ ይለያያሉ፤ ስለሆነም አባቶች ሁሉ እንደምንም ብላችሁ ልጆቻችሁ ሲወለዱ ማዋለጃ ክፍል ገብታችሁ ብታዩ ለሚስቶቻችሁ እንዲሁም ለልጆቻችሁ ያላችሁ ስሜት እጅግ ይቀየራል፤ ስለሆነም የእናትነትንና የወላጅነትን የጋራ ስሜት በመካፈል ለትዳራችሁ መከፈል የሚገባውን መስዋእትነት እንድትከፍሉ ያግዛል ብዬ አምናለሁ፡፡

 

በእርግጥ አባትነት ምንም ቢሆን እናትነትን ሊተካ አይችልም፤ ምክንቱም ከእናቶች ሸክም ውስጥ የወሊድን ብቻ ብንመለከት የምጥን ህመምና አጠቃላይ ስሜት ለመረዳት በራስ ላይ ሲሆንና የሰው ሲሆን ይለያያል፡፡ ባለቤቴ ልጃችንን ስትወልድ አጠገቧ ስለነበርኩ ውጪ ሆኜ የስዋን ስቃይ ከመስማት ውስጥ ገብቼ በአይኔ እያየሁ ችግሩን መካፈል ለኔም እንደአባት የምችለውን ያህል የምጥን ህመም እንድካፈል አድርጎኛል፤ በጆሮ እየሰሙ በአይን ማየትና በጆሮ ብቻ መስማት ስለጉዳዩ በሚኖረን ስሜት ላይ ልዩነት መኖሩ ግልፅ ነውና፡፡

 

በውጪ ሀገር ልጅ መውለድን ሌላው የተለየ የሚያደርገው፣ በውጪ ሀገር ልጅ ሲወለድ እህቶች፣ አያቶች፤ ተመላላሽ ሰራተኛ፣ ጎሮቤት፤ ዘመድ አዝማድ ሁሉ እንደልብ ስለማይገኝ ሀገራችን ከተለመደው የአባትነት ልምድ እጅግ በተለየ መልኩ የተሻለ ልምድ ሊኖረኝ ቻለ፡፡

 

 

ታዲያ ልምዱ አባቶችን የሚያስደስት መስሎን መታለል የለብንም፤ እውነቱን ለመናገር፣ ውጪ ሀገር ከነበረኝ ህይወት ውስጥ እጅግ ከባዱ ልጅ ማሳደግ ነው፡፡ ሀገራችን እኮ፣ ከአባቶች ጋር ሲነፃፀር ለእናቶች ቢከብድም ለአባቶች ግን አባትነት በጣም ምቹ ነው፤ ምክንያቱም አባት ከፈለገ ተመላላሽ ሰራተኛ ይቀጥራል፤ ካልሆነም እህቱን ወይ እናቱን ወይም አያቱን ወይም የዘመዱን ልጅ ብቻ አንድ ሰው የሚያግዘው ይኖራል፤ ስለሆነም የሽንት ጨርቅ ለማጠብና ቀኑን ሙሉ ስራ ቀርቶ ልጁን ይዞ የሚውልበት አጋጣሚ ምንም እድሉ ላይኖረው ይችላል፤ ስራ ቀርቶ ከልጅ ጋር ቀኑን ሙሉ እቤት ውስጥ የሚያሳልፉ የሀገራችን አባቶች ስንቶቹ እንደሆኑ መልሱን ለአንባብያን እተዋለሁ፤ ውጪ ሀገር ግን ከባልና ሚስት በስተቀር ብዙውን ጊዜ ሌላ ዘመድ የለም፤ ተመላላሽ ሰራተኛ መቅጠር ይቻላል፤ ዋጋው ግን አይሞከርም፡፡

 

ለምሳሌ ዴንማርክ ሀገር አንድ ተመላላሽ ሰራተኛ ለመቅጠር በሰአት ቢያንስ 300 የሀገራችን ብር መከፈል አለበት፡፡ ሰራተኛዋ በቀን ለሶስት ሰአት ብትሰራ 900 ብር ማለት ነው፤ ሀያ ሰባት ሺ የሀገራችን ብር በወር መከፈል አለበት ማለት ነው፡፡ ይህ ለሀገራችን ዜጋ አይደለም እዛው ለሚኖሩት የሀገሩ ሰዎችም ከባድ ነው፡፡ በቀላሉ የሰው ልጅ ጉልበት ዴንማርክ ሀገር እጅግ ውድ ነው፤ ሰው ማለት የተማረንም ያልተማረንም ይጨምራል፡፡ ሀገራችን ላይ ግን በወር በአንድ ሺ ብር ያውም ቀን ከለሊት ሰርታ ለቤት ሰራተኛ የምንከፍለው ክፍያ፤ ይህን ሁሉ እየሰራችም ክብር የላትም፤ ክብር ለመስጠት ሲሞከርም አልፎ አልፎ ሰራተኛዋ ራስዋ ክብርዋን ታወርደዋለች፡፡ ለምሳሌ ገና ስራ እንደያዝኩ ለመስክ ስራ ወደወላታ ሶዶ ሄጄ ነበረ፤ ስመለስ ሁለት ኪሎ ቅቤ ገዝቼ ተመለስኩ፤ ተመላላሽ ሰራተኛ ነበረችኝ፤ ሰራተኛዋ ቅቤውን አንጥራ በእቃ እንድታስቀምጥ ነግሬያት ወደስራ ሄድኩ፤ ከእለታት አንድ ቀን ያለወትሮዬ ከስራ ቦታ ጠዋት በ4አሳት አከባቢ ወደቤቴ ተመለስኩ፡፡

 

 

 

 

ስመለስ ሰራተኛዋ ውጪ ልብስ እያጠበች ነበረ፤ ወደቤት ውስጥ ስገባ በፔስታል የተቋጠረ የነጠረ ቅቤና በርበሬ እንዲሁም ሽሮ፤ ጨው፤ ስኳር ፊትለፊት ተቀምጦ አገኘሁ፤ ምንም እንዳላየ ሰው ወጣብዬ ስራ እንዴት ነው ስላት እየተርበተበተች ቆንጆ ነው አለችኝ፡፡ቶሎ ብዬ ግቢውን ለቅቄ ወጣሁ፤ በማግስቱ ደሞዝዋን አስቤ ሰጥቼ በሰላም ሸኘሁዋት፡፡

 

ሌላም ሰራተኛ እጅግ ችግረኛ የነበረች ልጅ በልመና እኛ ቤት ገብታ፤ መጀመሪያ የመጣች ለሊት ባለቤቴን እግርሽን ካላጠብኩሽ ስትላት የነበረች ልጅ ቀስ በቀስ ሀገር እየለመደች ስትሄድ እጅግ አሳዝናን ሄዳለች፡፡ ሰራተኞች ብቻ አይደሉም አሰሪዎችም ከባድ ችግር እንዳለባቸው እናውቃለን፤ ሶፋ ላይ አትቀመጡ፤ የተረፈ ምግብ ብቻ ተመገቡ፤ ከቤት አትውጡ፤ ቤተክርስቲያን አትሂዱ ወዘተ የሚሉ አምባገነን አሰሪ ቤተሰቦች መኖራቸውን መርሳት የለብንም፡፡ ለሁሉም የቤት ሰራተኞች እጅግ ታላቅ ባለውለታችን ናቸው፤ በተለይ ለአባቶች፤ ምንም ቢሆን ልጆቻችንን ለማሳደግ የሚችሉትን አድርገዋልና፤ የምንከፍለቸው ክፍያና ለሰራተኞቹ የምናሳያቸው ባህሪ አልፎ አልፎ ኢ ሰብአዊ ቢሆንም፡፡

 

የቤት/የተመላላሽ  ሰራተኛ ጥቅም የሚታየን ወደውጪ ሀገር ስንሄድ ነው፤ ደስ የሚለው ውጪ ሀገር ኑሮው በራስ መተማናችን እንዲቀየር ያደርገናል፤ ልብሱን ማጠብ የማይችል ወይም ለማጠብ ሞክሮ የማያውቅ ብዙ የሀገሬ ወጣት አለ፤ ምክንያቱም በወር 200 ብር ከፍሎ ልብሶቹን ሙሉ ያሳጥባላ፤ ሀገራችን እኮ ሁሉ ሰው ቀጣሪ ነው፤ በሰለጠነው አለም ሰው ለመቅጠር እጅግ ከፍተኛ ገቢ ያስፈልጋል፤ ልብስ ለማሳጠብና ምግብ ለማብሰል የሰው ልጅ መቅጠር ዋጋው አይቀመስም፤ አዲስ አበባ አልፎ አልፎ እስከ ሶስት የቤት ሰራተኞች የሚቀጥሩ ወላጆች መኖራቸውን ሰምቻለሁ፤ ከሶስቱ አንዷ ስራዋ ልጅ መያዝ ብቻ ነው አሉ፤ ልጆች ለሚያሳድጉት ወላጆች ይህ ታላቅ ነገር ነው፤ የሚያሳዝነው ለሰራተኞቹ ነው፤ ሰራተኞቹ ቀን ተለሊት ስራ ይሰራሉ፤ ነገር ግን ለመኖር መሰረታዊ ነገሮችን ማግኘት አይችሉም፤ በተመሳሳይ የትምህርት ደረጃና የስራ ሰአት ሰራተኛዋ ወደሰለጠነው አለም ብትሄድና ስራ ብታገኝ ድህነትዋ ታሪክ ነው ሚሆነው፡፡

 

ወደድንም ጠላንም ሀገራችን ላይ የሰው ልጆች ክብር መረጋገጥ አለበት፤ አንድ ሰው ቀኑን ሙሉ ላቡን አፍስሶ ሲሰራ ውሉ ለምን ለምግብና ለትራንስፖርት ይቸገራል? መሆን የለበትም! መፍትሄውም የክፍያ መጠን በህግ የተደነገገ መሆን አለበት፤ ሰው ቀጥረው የሚያስሰሩ የግልም ይሁን የመንግስት ቀጣሪዎች መክፈል ያለባቸው በወር ለምግብ፣ ለቤትኪራና ለትራንስፖር፣ ለልብስ ወጪ የሚከፍል ትንሹ ክፍያ ደሞዝ መጠን በመንግስት መደንገግ አለበት፡፡

 

ስለልጆች ስንነጋገር የግድ መነሳት ያለባቸው ጉዳዮች አሉ፤ ለምሳሌ ልጆቻችን በተለያዩ ጊዜያት ይታመማሉ፤ ስለሆነም የልጆቻችን ህመም እጅግ  ያስጨንቃል፤ እኔ በበኩል ብዙ ጊዜ እጅግ ተጨንቄ ነበረ፤ ለምን ልጅ ወለድኩ እስከማለት ደርሼ አውቃለሁ፤ እየቆየ ሲሄድ የልጆች መታመም የግድ መሆኑን ተረዳሁ፤ የልጆች ህመም አይነቱና ጉዳቱ ቢለያይም በተደጋጋሚ ሚከሰት ነገር ነው፤ ለምሳሌ ጉንፋን በተደጋጋሚ ልጆችን ያማቸዋል፤ በነገራችን ላይ አውሮፓ ልጆች የማይታመሙ መስሎን ባንሳሳት ጥሩ ነው፤ ዴንማርክ ሀገር ልጄ ብዙ ጊዜ ትታመም ነበረ፤ ከሚታመሙት ህመሞች ዋናዋና ዎቹ ጉንፋን፣ ትኩሳት፣ አልፎ አልፎ ማስታወክ፣ ተቅማጥ ወዘተ ናቸው፤ ታዲያ ልጆቹ ሲታመሙ ወደመዋለህፃናት እንዳይመጡ ይከለከላሉ፤ ምክንያቱን ሌሎቹን ህፃናት እንዳይበክሉ ተብሎ ነው፤ የወላጆችን በተለይም የአባቶችን የውጪ ሀገር ኑሮ እጅግ ከባድ የሚያደርገው ጊዜ የልጆች ህመም ጊዜ ነው፤ ምክንያቱም ኢትዮጵያዊ አባቶች ከልጆች ጋር እቤት የመዋሉ ጉዳይ የተለመደ ስላልሆነ እጅግ ያስጨንቃል፡፡

 

ኢትዮጵያ ስንኖር ከቤት ወጣ ብለን ከወዳጆቻችን ጋር ጊዜን ማሳለፍ ብዙ አባቶች የምናደርገው ጉዳይ ነው፤ አንዳንዱ ደግሞ የእንግሊዝ እግር ኳስ ለማየት ወይም ድራፍት ለመጠጣትም ሲል ውጪ መቆየት የለመደ ነው፤ በሀገራችን ላይ ስንኖር ብዙ ገንዘብ ባናገኝም ምን ያህል ዘና ያለ ህይወት እንደምንኖር የሚገባን ውጪ ሀገር ሄደን የተወሰነ ጊዜ የሚያናግረንና ትንሽ ጊዜ አብረን የምናሳልፈው ሰው ስናጣ ነው፡፡

 

 

የሀገራችን አባቶች ማድረግ የሚገባን ጉዳይ፣ በሀገራችን እያለን ለልጆችና ለቤተሰብ የምንሰጠውን ጊዜ መጨመር ይኖርብናል፡፡ ይህ ምክር ለአንዳንዶቹ የማያስፈልግ ሲሆን ለሌሎቻችን ደግሞ በተደጋጋሚ መነገር ያለበት ነው፤ ለምሳሌ ባሎች ትዳር ከመመስረታቸው በፊት የለመድነው የነጻነት ህይወት አለ፤ ትዳር ሲጀመር በተለይ ደግሞ ትክክለኛው የትዳር ህይወት/ ልጅ ከተወለደ በኋላ ያለው/ ጊዜ ወደጭቅጭቅና መሰላቸትም የሚሄድበት አጋጣሚ አለ፤ ብዙ ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻላል፤ እኔ የራሴን ልጥቀስና ይህንን መጽሀፍ እያነበባችሁ አጠገባችሁ ከሚገኝ ሰው ቢቻል ከባል ወይ ከሚስት ካልሆነም ደግሞ ከእጮኛ፤ ካልሆነም ከእናትና ከአባት ጋር በመካከር ተጨማሪ ነጥቦች ሊጨመሩ ይችላሉ፡፡

 

ሚስቶች ወይም እናቶች መረዳት አለባቸው ብዬ የማምነው ነገር አንድ ባል ለልጆቹና ለቤተሰቡ ጊዜ መስጠት ቢኖርበትም የሰውየውን ባህሪና አብረውት የሚያዘወትሩትን ወዳጆቹን ባህሪ እንዲሁም ከትዳር በፊት የነበረውን የኑሮ ዘይቤ ልብ ማለት ያስፈልጋል፤ ለምሳሌ ብዙ ወንዶች ትዳርን እንደእስርቤት የሚፈሩበት ዋናው ምክንያት የለመዱትን ቀለል ያለ ህይወት እንደሚፈትነው ሲለሚሰሙ ነው፡፡ በተለይ በገንዘብ አያያዝ፣ ከሌሎች ጋር ጊዜን ከማሳለፍ፣ የእንግሊዝ እግርኳስ ማየት፣ ለአንዳንዶቹ መጠጥ ማዘውተር፣ ለሌሎቹ ደግሞ ጫት መቃም በተለይ ከቤት ውጪ ጫት መቃምና ማምሸት የመሳሰሉት ጉዳዮች የተለመዱ የወንዶች ድክመት ናቸው ማለት ይቻላል፤ አሁንም ይህ ድምዳሜ ሁሉንም ወንዶች የሚወክል ሳይሆን የተወሰኑትን እንደሆነ ማስታወስ እፈልጋለሁ፡፡

 

ስለሆነም ሚስቶቻችን የኛን ጠንካራና ደካማ ጎኖች ለይተው በጭቅጭቅና በቁጣ ሳይሆን ቀስ በቀስ ነገሮችን ማስተካከል አለባቸው ብዬ አምናለሁ፤ ይህንን ስል አብዛኞቹን ባሎች ወክዬ ለሚስቶች አቤቱታ ማሰማቴ ነው፡፡ በጫትና በአልኮል ምክንያት ብቻ ብዙ ችግር ላይ የሚወድቅ ትዳር እንዳለ አውቃለሁ፤ ቢሆንም ብዙ ጊዜ ነገሮችን በትእግስት ከመፍታት ይልቅ ወደእልህ ሄደን የራሳችንና የትዳር ጓደኛችንንም ህይወት እንጎዳለን፡፡

 

ወደሚስቶች ችግሮች ስንመለስ ደግሞ አሁንም ይህ ሀሳብ ሁሉንም ሚስቶች ባይመለከትም በአብዛኛው /በወንዶች አይን ሲታይ/ ሴት እህቶቻችን ትንሽየ የሆነችውን ነገር ትልቅ አድርጎ ማየት ችግር ያለባቸው ይመስለኛል፡፡ ለምሳሌ ብዙ ሚስቶች ቤት አያያዝ ላይ በደንብ አድርገው ባሎችን ይበልጣሉ፤ ታዲያ ልጆችና ባሎች እቤት የዋሉ ለት ቤት ይቆሽሻል፤ ቤት ቢቆሽሽም መፀዳት የሚችል ነገር ስለሆነ ቤት ቆሸሸ ብሎ ከባሎች ጋር ብዙ መጨቃጨቅ አስፈላጊ አይመስለኝም፡፡ በተጨማሪም ሴት እህቶቻችን በብልጭልጭ ነገሮች የሚታለሉ ይመስለኛል፤ ብዙ ወንዶች ጋር ስንወያይ ተመሳሳይ ችግሮች ሲጠቀሱ እሰማለሁ፤ በተለይ በሴት እህቶቻችን ዘንድ ለውበት ተብለው የሚደረጉ ብዙ ደካማ ጎኖች አሉ፡፡ መስተካከል አለባቸው፡፡ በተረፈ ሴቶች ውበትን እጅግ ከፍ ኣድርገው የሚያዩበት አይን መቀነስ ያለበት ይመስለኛል፤ ከራሳቸው ጀምሮ ብዙ የሚያደርጉት ነገር እንዲያምር ይፈልጋሉ፤ ቢሆንም ብልጭልጭ ነገሮች ከሚገባቸው በላይ ትኩረት የተሰጣቸው ይመስለኛል፡፡

 

በተረፈ ወንድም ሴትም በተቻለመጠን በራሳቸው አስበው ራሳቸው የተሻለ ነገር ያድርጉ እንጂ እንዲህ አድርግ፣ እንዲህ አድርጊ፣ ይህንን ግዛ፣ ይህንን ግዢ፣ ከእከሌ ጋር አትሂድ፣ ከእከሌ ጋር አትሂጂ ወዘተ የሚሉት የቁጥጥር ነገሮች ብዙ ጊዜ አላማቸውን አይመቱም፡፡ ለጭቅጭቅ መንገድ ይከፍታሉ፤ እኔ ብቻ አዋቂ፣ እኔ ብቻ ትክክል አሳቢ አይነትም ነገር አብሮ መኖርን ይጎዳል፡፡

 

ወደኢትዮጵያ መመለስ

 

መቼም ከምእራቡ አለም ጋር ሲነፃፀር የደሀ ሀገር ዜጎች ስለሆንን ነው መሰለኝ አንድ ኢትዮጵያዊ ወደ ውጪ ሀገር በተለይ ደግሞ ወደአውሮፓ፣ ወደአሜሪካ፣ ወደአውስትራሊያ ወዘተ ሲሄድ ላቅ ያለ ደስታ ይሆናል፤ ሰው ሁሉ እንኳን ደስ አለህ ብሎ፤ አጨብጭቦ ነው ዜናውን የሚቀበለው፤ አልፎ አልፎም ለሀይማኖት ተቋማት ስለት የሚያስገባም ብዙ እንደሚሆን እገምታለሁ፤ ለምሳሌ የሀገራችን ወጣቶች ዲቪ ሲሞሉ አብረው ስለት ይሳላሉ ይባላል፤ ስለቱም ደግሞ ይህ ዲቪ ከተሳካልኝ እንደዚህ አደርግልሀለሁ ብሎ ለአምላክ ቃል መግባት ማለት ነው፤ ታዲያ የስለቱ ጉዳይ አምላክንም ኪራይ ሰብሳቢ አይነት አድርጎ የማየት ባህላችን ነው ብለው የሚከራከሩ ሀገራችን ታማኝ ሀይማኖተኛ ወጣቶች እየተፈጠሩ ነው ሲባል ሰምቻለሁ፤ ለሁሉም ስለት መሳል ማለት ለምሳሌ አንድ ሰው ሎተሪ ሲቆርጥ እድሉ ለሱ እንዲሆን አምላኩን ያስቸግረዋል፡፡

 

ሎተሪው ውስጥ አምላክ ለባለስለቱ እንዲያዳላ፤ ከሚደርሰው ሎተሪ ደግሞ ሙሉ ሙሉ ሳይሆን  የተወሰነውን ቀንሶ ለፈጣሪው ይሰጣል፤ በዘመኑ አነጋገር ሙስና ይሰጣል ማለት ነው፤ ስጠኝና ልስጥህ፤ በእኔ እምነት አምላክ አንድን ሰው ለመርዳት ሰውየው የሚሰጠውን የምላሽ እጅ መንሻ የሚያስብ አይመስለኝም፡፡ ጉቦ ተለማምደናል፤ አድርግልኝና ላድርግልህ የሚል አይነት ስራ በዛሬይቱ ሀገራችን ላይ ከባድ የራስምታት የሆነ ይመስለኛል፤ ስለዚህ አሜሪካን ለመሄድ፣ ዲቪ ሎተሪ ለማሸነፍ፣ የትምህርት እድል ለማግኘት በተለይ ውድድር ያለባቸውን ነገሮች በስለት ለማሟላት የምንሞክረው ነገር አምላክን ኪራይ ሰብሳቢ የማድረግ አይነትና ሙስናን ስለተለማመድን የአምላክ ቸርነቱን፡፡

 

 

በነፃ ለሁላችንም የሚደረገውን አድልዎ አይነት ወይም አምርረን ስለለመንን የአንዳችንን እድል ለሌላው የሚሰጥ አድርገን ባንቆጥረው፤ ሎተሪ ለሁሉም እኩል የተሰጠ ሲሆን እጣውም የሚወጣው በዘፈቀደ እንጂ ፍቃዱ ከ1 ሚሊየን ብር ሎተሪ ግማሹን የሀይማኖት ቤት ስለሚያሰራበት አምላክ ለፍቃዱ ሰጠው አይነት አድልዎ አድርገን ባናስብ ጥሩ የመስለኛል፤ በአጭሩ ስለቱንም ብንቀንስና ስለወደፊት ህይወት ዛሬ የምንደሰተውን ብንቀንስ፡፡

 

ብዙ የሀገራችን ወጣት እኔንም ጨምሮ ውጪ ሀገር ሄደን ሳይሆን የመሄዳችን ዜና ሲሰማ እጅጉን እንደሰታለን፤ ዘመድ ሁሉ ተደስቶ ያስደስተናል፤ እድለኞች ናችሁ ተብለን ስላላየነው አለም ጮቤ ረግጠናል፤ አይደርስ የለምና ሁሉ ደርሶ የተደሰትንለትን ጮቤ የተረገጠለትን የውጪ ሀገር ኑሮ ደርሰን ስናየው ግን ላባችንን ሸጠን የምንኖርበት እንጂ ምንም ያንን ያህል እልልልል የሚያስብል እንዳልሆነ በተግባር አይቻለሁ፡፡ ውጪ ሀገር ደስ ይላል፤ ነገር ግን ሌሎች በሰሩትና ባሳደጉት ሀገር የመኖር እድሉ ስለተሰጠን ከመጠን በላይ መኩራራትና መደሰት የአስተሳሰባችንን ርቀት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ጉዳይ ነው፡፡

 

ውጪ ሀገር በጣም ብዙ አይነት ህይወት አለ፤ እጅግ የተሳካለት ሊባል የሚችል ህይወት የሚኖሩ የሀገራችን ዜጎች አሉ/በተለይ በቁሳቁስ ከተቆጠረ/፤ ካልሆነ ግን የኢትዮጵያዊ ታላቅነትና አዋቂነት መለካት ያለበት ያደገ ሀገር ውስጥ ሄዶ መኖር ስለቻለ ሳይሆን እውነትም ጎበዝ ስለሆነ የራሱን ሀገር ደሀ ህዝብ ለውጦ ስኬት ማስመዝገብ ከቻለ ነው፡፡ እኔ ውጪ ሀገር ለመቅረት የተቻለኝን ሙከራ አድርጌያለሁ፤ ያንን ሁሉ ሙከራ ያደረግኩት ከደሀ ቤተሰብ ስለተወለድኩ፣ በገንዘብ የምረዳቸው ሰዎች ስላሉ፣ አንድ ደረጃ መማር ስለምፈልግ እንጂ በፍፁም በፍፁም ውጪ ሀገር መኖር ደስ የሚል ነገር ስላለው አይደለም፡፡

 

 

 

 

ይህንን ስል ውጪ ሀገር ሰዎች በደል ይደርስባቸዋል ወይም ሰርተው መቀየር ይከብዳቸዋል ብዬ ሳይሆን አንደኛ በስራ አጥነት የተነሳ፣ ሁለተኛ ከህይወት ግብ የተነሳ፣ ሶስተኛ ከራስ ወገን ርቆ መኖሩ በራሱ የሚመጣው የአእምሮ ጫና ስላለ፤ አራተኛ ልጆች ለማሳደግ ከባድ ስለሆነ ወዘተ ብቻ ነው፡፡ ውጪ ሀገር ኖሮ መደሰት መቻልና አለመቻል የሞራል ጥያቄ ይበዛዋል፡፡ ለዛ ደግሞ ነገሮችን በጥልቀት መመልከት ይጠይቃል፡፡ በተለይ በተለይ በደንብ ለተማሩና ህይወታቸውን ከራሳቸው በላይ ለሀገራቸውና ለህዝባቸው መኖርን ተቀዳሚ ለሚያደርጉ ሁሉ ከራስ ወገን ርቆ መኖር ትልቅ የአእምሮ ቁስል ነው፡፡ አንድ ሰው በቂ ገንዘብ ካለው ወይም በደንብ የተማረ ከሆነ ሀብታም ሀገር ምን ይሰራል? ምንም! ለጉብኝትና ለመዝናናት ካልሆነ በስተቀር፡፡

 

አንድ ወቅት እዛው ዴንማርክ ሀገር ኮንፈረንስ ነበረ፤ ኮንፈረንሱ የዴንማርክና የአፍሪካ ኢንቨስተሮች አብረው መስራት የሚችሉበትን መንገድ ማመቻቸት አይነት ስብሰባ ነው፡፡ ዛሬ ድረስ የማልረሳው ንግግር የዴንማርክ ፕሮፌሰር ተናገረ፡፡ እናንተ የአፍሪካ ሰዎች ትገርማላችሁ አለ፤ እጅግ የምትገርሙት በዋናነት ደሀ ስለሆናችሁ ሳይሆን በሀገራችሁ ስራ ስትሰሩ ብዙ ነገሮችን ለራሳችሁ ኪስ እንጂ አርቃችሁ ለማህበረሰብ እንደሚጠቅም አርድጋችሁ አትሰሩም፡፡

 

እንደችግራችን ብዛት ቢሆን በተለይ ከተፈጥሮ ጋር በተያያዘ እኛ አውሮፓዊያን ወደእናንተ ፀሀይ መሰደድ ነበረብን፤ ነገር ግን በጣም አርቀን ስለምናስብ የአከባቢያችንን ተፈጥሮ በቴክኖሎጂ አሸንፈን እናንተን ከፀሀይ ወደበረዶ እንድትሰደዱ አደረግናችሁ፤ አፍሪካዊያን እኮ የታደላችሁ ናችሁ፤ ነገር ግን ትንሽ ልዩነት በመካከላችሁ ሲኖር ወንድማችሁን ለመግደልና በብድር የጦር መሳሪያ ለመዋጋት ዝግጁ ትሆናላችሁ፤ ዲሞክራሲ ቀልድ ይመስላችሁዋል፤ ከሌሎች ጋር ህብረት ፈጥራችሁ ንግድ ለመነገድ አትታመኑም፡፡

 

 

 

ትልቅ ድርጅት ለመክፈት ከናነተ ጋር ለመስራት የሚመጣውን የውጪ ዜጋ በሙስና አሰልችታችሁ ታባርራላችሁ፡፡ ስለሆነም መቀየር ካለባችሁ አሰራራችሁን መቀየር አለባችሁ፤ ያላችሁን የሰው ሀብት በአግባቡ መጠቀም አለባችሁ ወዘተ ብሎ ተናገረ…

 

የኛ አለማወቅ ጥልቀት አንዱ ማሳያ አንድ የሀገራችን ታዋቂ ጎበዝ የሂሳብ ተማሪ አሜሪካን ሀገር ነፃ ዜግነት ቢሰጠው ደስ ብሎን አጨብጭበን እንሸኘዋለን፡፡ ከሰው የበለጠ ሀብት ምን አለ? በተለይ የተማረ የሰው ልጅ፤ ሀገራችን ግን የተማሩ ልጆችዋን በቀጥታም ይሆን በተዘዋዋሪ አሳድጋ ለሌሎች እየሰጠች ነው፤ ባለሙያውም ተስፋ ይቆርጣል፤ የሀገሩን የፖለቲካ ችግር መታገስ አቃተው፤ ስሜታዊነት ሁሉ ነገራችንን ተቆጣጠረ፤ ሁሉ በሌላው ጣቱን መጠቆም ብቻ ሆነ፤ በእርግጥ የገንዘብ ችግር ያለበትና ገንዘብን እንደህይወቱ ዋና ግብ አድርጎ የሚኖር ሰው ወደውጪ ሀገር ሄዶ ገንዘብ ያገኛል፤ ዋናው ጥያቄ ያ ገንዘብስ ምን ይደረግበት? ምክንያቱም የሀገራችን ዋና ችግር ገንዘብ አይደለም፤ ምክንያቱም በገንዘብ የማይተመነውን የተማረ የሰው ልጅ በቀላሉ እያባከነች ነው፡፡

 

ስለሆነም ቆም ብለን ማሰብ አለብን፤ ከግለሰቦች ጥቅም ያለፈ የሀገርና የወገን የሚባለውን ጉዳይ በጥልቀት መመርመር አለብን፤ አለማችን በእውቀት እየተመራች ነው፤ ዋናው የሚያስፈልገን አዋቂ እና ለምን ብሎ የሚጠይቅ ትውለድ እንጂ በአልኮል ሰክሮ ከተቃራኒ ፆታ ጋር በሴሰኝነት የተለከፈ እንዲሁም ቤተሰቡንና ሀገርን አደጋ ላይ የሚጥል የባከነ ዜጋ አይደለም፤ ፍቅርም ቢሆን አርቆ ለሚያስብ ሰው ነው ትርጉም የሚኖረው፤ አእምሮው ገና እንጭጭ ለሆነው ግን ፍቅር ማለት ሴሰኝነትና ትውልድን በሱስ ማጀዘብ ነው፡፡ ሁላችንም ሀላፊነት አለብን፤ በመጀመሪያ ራሳችንን ማፅዳት፣ ቀጥሎ ቤታችንን፣ ቀጥሎ አከባቢያችንን፡፡

 

 

 

 

 

እውነት ላይመስል ይችላል

 

አንዲት ልጅ ለትምህርት አሜሪካን ሀገር ትሄዳለች፤ ከተወሰነ አመት በኋላ ባሏንና ልጆችዋን ትወስዳቸዋለች፤ አብረውም እየኖሩ ሰርተው ብዙ ሀብት ያፈራሉ፤ አዲስ አበባም ሁለት ፎቆችን ይሰራሉ፡፡ የልጅትዋ የትምህረት ቆይታዋና አሜሪካን ሀገር የመኖር ፍላጎትዋ ሲያልቅ ባልዋን ወደሀገራችን ብንመለስ ብዬ እያሰብኩ ነው ምን ይመስልሀል ትለዋች፤ ባልየው በበኩሉ ‹እኔ ወደሀገር ቤት መመለስ አልፈልግም፤ መመለስ ከፈለግሽ አንቺ መሄድ ትችያለሽ› ይላታል፤  ልጆቻችንስ ስትለው ልጆቹ ይምረጡና የሚመቻቸው ጋር ይሁኑ ይላታል፤ ሶስት ልጆች አላቸው/አንድ ሴት ልጅና ሁለት ወንድ ልጆች/፤ ታላቁ ልጅ ከአባቱ ጋር ሲቀር ሁለቱ ከእናታቸው ጋር ወደኢትዮጵያ ይመለሳሉ፤ እጅግ የሚያሳዝነው ውጤት ታላቅ ልጅ በቤተሰቦቹ ውሳኔ ተበሳጭቶ የራሱን ህይወት ያጠፋል፤ የልጁ እናት ስለልጁ መሞት ስትሰማ ለከባድ ህመም ትዳረጋለች፤ ይህንን አይነት ታሪክ እውነት ላይመስል ይችላል፤ በእውነት ተመሳሳይ ታሪኮች አሉ፡፡

 

ለብዙ የሀገራችን ዜጎች ወደአውሮፓና ወደአሜሪካ የመሄድ አጋጣሚ ሲገኝ ያለው ደስታ ሁሉ ወደሀገር ቤት ለመመለስ ተመሳሳይ አይደለም፤ በተለይ ባለትዳር ለሆኑትና በዲያስፖራው ላሉ ወገኖቻችን ወደሀገር ቤት መመለስ ትዳራቸውን ከባድ አደጋ ላይ ከሚያድረሱ በላይ ለፍቺና ለተለያዩ ችግሮች እንደሚያጋልጥ በውጪ ሀገር ያሉት ኢትዮጵያዊያን ያውቁታል፡፡ በዚህ ረገድ እኔ እጅግ እድለኛ ነኝ ማለት እችላለሁ፤ ምክንያቱም በሰላም ልጆቼን ይዤ ወደሀገሬ ለመመለስ በቅቻለሁ፡፡

 

የበለፀጉት ሀገራትን አይቶ ወደኢትዮጵያ የመመለስ ሌላው ተጋዳሮት በውጪ ሀገራት ያለው የኑሮ ምቾትና እዚህ ሀገራችን ካለው ጋር ሲነፃፀር ደስ የሚል ስሜት አለመፍጠሩ ነው፤ ለምሳሌ እኛ ከዴንማርክ ወደሀገራችን እንደተመለስን የራሳችንን ቤት ለመስራት ፈልገን መሬት ለመግዛት ማጠያየቅ ጀመርን፤ ነገር ግን ከደላላዎቹ ጀምሮ መዘጋጃቤት እንዲሁም ውልና ማስረጃ ቢሮዎች ስንመላለስ ያለው ውጣ ውረድ ሊጠቀስ ይችላል፤ በተጨማሪም በግንባታ ስራ ላይ ያለው የባለሙያዎች ምግባረ ብልሹነት፤ ለምሳሌ ውሸታቸውና ማጭበርበራቸው እልህ አስጨራሽ ነበረ፡፡ የሀገራችን የግንባታ ሰራተኞች ከሚገነቡት ስራ ተጨማሪ ገንዘብ ለማግኘት ብዙ ያጭበረብራሉ፤ ውሸት መረጃም ይሰጣሉ፤ እንዲሁም የሚሰሩትን ስራ ሆን ብለው ያበላሻሉ፤ አሸዋ የሚሸጡት አሸዋው ውስጥ አፈር ቀይጠው ይሸጣሉ፤ የኤሌክትሪክ ሰራተኞቻችን ተጨማሪ ገቢ ይሆናቸው ዘንድ የኤሌክትሪክ መስመሮችን ሆን ብለው አነካክተው ይዘረጋሉ፤ ይህ ሁሉ አንድ ውጪ ሀገር ኖሮ ወደሀገራችን የሚመለሰውን ዜጋ የሚያማርሩ ጉዳዮች ናቸው፤ ይህንን ስል ውጪ ያለው ህዝብ ከነኚህ ችግሮች ሙሉ በሙሉ ነፃ ነው ማለቴ አይደለም፡፡

 

መጠነኛ ችግረች ይኖራሉ፤ ነገር ግን በሀገራችን ያለው የባለሙያዎቻችን ለሙያቸው ታማኝ አለመሆን ሁላችንንም እጅግ የሚያበሳጭ ጉዳይ ነው፤ ነገር ግን ውጪ ሀገር ቆይቶ የሚመጡት ወገኖቻችን ታማኝነት የሰፈነበትና የህዝብ አገልግሎት አሰጣጥ ምቹ የሆኑ ሀገሮችን አይተው ስለሚመጡ የራሴ ብለው የመጡት ሀገር  ይህንን ያህል የሙያ አለመታመንና ሌብነት የተሞላ መሆኑ የበለጠ ያሳምማቸዋል፡፡ ይህንን ስል ውጪ ሀገር ሁሉ ነገር አልጋ በአልጋ ነው ማለቴ ሳይሆን በአብዛኛው ሰዎች ለሙያቸው ታማኞች ናቸው፤ እንዲሁም የመንግስት መስሪያቤቶች አሰራራቸው ግልጽና ቀልጣፋ ስለሆነ የአገልግሎት አሰጣጡ ለዜጎች በጣም የተመቹ ናቸው፡፡ በአበዛኛው ሀገራችን ላይ ግለሰቦች ከህግ የበላይ ሆነው ነው ህዝቡን የሚያገለግሉት፤ ስለሆነም ሙስና ሊስፋ ቻለ፡፡

 

የሀገራችን አሰራር ህጋዊ በሆነ የመንግስት መስሪያቤት እየተከናወነም አስተማማኝነት የለውም፤ ለምሳሌ በመሬትና ቤቶች ሽያጭ ጋር በተያያዘ ያለው አሰራር በአደባባዩ ሙስና የሚሰራበት እንደሆነ ግልፅ ነው፤ ለምሳሌ የኮንደሚኒየም ቤቶች የተሰሩት ለድሆች ሰለሆነ መሸጥ አይቻልም የሚለው ህግ አለ፤ ነግር ግን ሰዎች ቤቶቹን እየቸበቸቡ ነው፤ በዚህ መሀል እኔ ሙስና መስራት አልፈልግም የሚለው ሁሉ ሳይወድ በግዱ ሙስናው ስራ ውስጥ እጁን ይከታል፡፡ በሀገራችን የቤቶችና የመሬቶች አስተዳደርን በተመለከተ ውክልና የሚባለው እጅግ የሚገርም አሰራራችን ደላላዎች ምንም ያልደከሙበትን ሀብት ከህዝቡ እንዲሰበስቡ ሰፊ መንገድ የከፈተ ጉዳይ ነው፤ ለወደፊቱም መሻሻል አለበት፡፡

 

ስለሆነም በሀገራችን እጅግ የተስፋፋውን ሙስና ለመቀነስ  ከሁሉ በፊት ህጎች ሲወጡ የአፈፃፀም ጉዳዩችን ቀድሞ ማሰብ ያስፈልጋል፤ ለምሳሌ የኮንደሚኒየም ቤቶችን መሸጥ አይቻልም ስንል ቤቶቹ አለመሸጣቸውን እንዴት ማረጋገጥ ይቻላል የሚል አሰራር አብሮ መታሰብ አለበት፡፡ ወይም መሬት አይሸጥም አይለወጥም ስንል ምን ማለታችን እነደሆነና የአፈፃፀም ችግሮችን በየደረጃው መፍታት ያስፈልጋል፡፡ በተለይ ትንሽ ከተሞችን ለማሳደግ ህዝቡ ለቤት መስሪያ ቦታ ቢሰጠውና ያለውን ገንዘብ ቤቱን ለመስራት ቢጠቀም ቆንጆ ነው፤ በክልል ከተሞችና በአዲስ አበባ ደግሞ መንግስተ ደረጃቸውን የጠበቁ ትልልቅ መኖሪያ ቤቶችን ለሁሉም ቤት ፈላጊ እንዲዳረስ አድርጎ በፍጥነት ፍላጎቱን ማዳረስ አለበት፤ ዋናው ችግር ደግሞ ሙስናው ነው፤ እጅግ ጥንቃቄ ይጠይቃል፡፡

 

አሁን ባለው አሰራር በተለያዩ ደረጃዎች የሚወጡት ህጎች ተፈፃሚነታቸውን የሚከለክሉ ቀዳዳዎችም አብረው የሚዘጋጁ ይመስለኛል፡፡ ኮንደሚኒየም ቤቶችን መሸጥ ህገወጥ ነው የሚል ህግ ከማውጣታችን በፊት ከሁሉ በፊት ቤቶቹ የተባለለትን አላማ፣ ማለትም ቤት መስራት የማይችሉ ድሆች ቤቱን ማግኘታቸው መረጋገጥ አለበት፡፡ ቀጥሎ ቤቶቹ ለደሀው ተጠቃሚ ከተሰጡ በኋላ ግለሰቡ ቤቶቹን የሚሸጥ ከሆን የቤቱን ዋጋ ሶስት እጥፍ ለመንግስት ገቢያደርጋል የሚል በተዘዋዋሪ መቀጫ ቢኖረው ሰዎች ወደሽያጭ ከመሄዳቸው በፊት ጉዳቱንም እያሰቡ የቤት ባለቤትነታቸው ይጠበቃል ማለት ነው፡፡ ካልሆነ ደግሞ አንድ እጣው የደረው ግለሰብ ቤቶቹን የሚሸጥ ከሆነ ቤቱ ለመንግስት ተመላሽ ተደርጎ ለሌላ ተጠባባቂ  ይሰጣል የሚል አሰራር ቢዘረጋ ህብረተሰቡ በራሱ ህጉን የሚሽሩትን ይከታተላል፡፡ ይህ ሁሉ ካልሆነ ግን የደሃ ዜጎችን የቤት ፍላጎት መልሰናል ለማለት ችግር ይሆናል፡፡ ካልሆነ የቤቶቹን ባለቤትነት ለመንግስት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ምክንቱያም ቤቶቹ የመንግስት ከሆኑ ግለሰቦች ዝቅተኛ ኪራይ እየከፈሉ መኖር ይችላሉ፡፡

 

ውጪ ሀገር ኖረው ወደሀገር ቤት ለሚመለሱት የሀገራችን ዜጎች ትልቁ ፈተና ሌላ ሀገር ያለውን የኑሮ ሁኔታና የሀገራችንን በማስተያየት ደስ የማይል ስሜት የመፍጠሩ ጉዳይ ነው፡፡ ቆንጆ ነገሩ ደግሞ የሰው ልጅ እስከ ምን ድረስ መስራት እንዳለበት ተጨባጭ ልምድ ይዞ መምጣት መቻሉ ላይ ነው፡፡

ማህበራዊ ድህረገፆችና የሀገራችን ጉዳይ

እድሜ ለአደጉት ሀገራት ኢንጂነሮች፤ ቴክኖሎጂ በቀላሉ ቤታችን ይደርሳል፤ ቴክኖሎጂና ንግድ አለማችን አንድ መንደር እያደረጓት ነው፤ እጅግ ዘመናዊ ስልክ አሜሪካን ሀገር ሲመረት በሳምንት ጊዜ አዲስ አበባ ገበያ ይደርሳል፤ ኢንተርኔቱም የመረጃ ልውውጡን በዛው ልክ ፈጣን አድርጎታል፤ ለምሳሌ ፌስቡክ የሚባለው ማህበራዊ ድህረገፅ ተራርቀው ያሉት ህዝቦችን እጅግ አቀራርቦ መረጃም በዛው ፍጥነት እየተለዋወጥን ነው፡፡ እነኚህ ቴክኖሎጂዎች ቆንጆ መረጃዎችን በፍትነት የማስተላለፋቸውን ያህል መጥፎ መረጃዎችንም የዛኑ ያህል በፍጥነት እንደሚያስተላልፉ መረዳት አለብን፡፡

 

ስለሆነም ለወጣቱ ትውልድ የማህበራዊ ድህረገጽ አጠቃቀምን በተመለከተ አማራጭ መንገዶችን ማሳየት ለሀገርም ሆነ ለወጣቶቹ ህይወት ስኬት ጠቀሜታው የላቀ ነው፡፡ የራሴን ተሞክሮ በተመለከተ ለምሳሌ በ1999 ዓ.ም አከባቢ ስለ ፌስቡክ መጀመሪያ ስሰማ ለመጠቀም ፈቃደኛ አልሆንኩም ነበረ፤ ቀስ በቀስ ግን የራሴን አካውንት ከፈትኩ፤ አልፎ አልፎ እየገባሁ ሌሎች ወዳጆቼ የሚልኩትን ሀሳብና ፎቶዎች ማየት ጀመርኩ፤ እኔም ፎቶዬን መለጠፍ ጀመርኩ፤ እግረመንገዴንም ለብዙ ጊዜ የተለየሁዋቸውን ወዳጆቼን ማግኘት ጀመርኩ፤ ስለሆነም ፌስቡክ የመጠቀም ፍላጎቴ እየጨመረ መጣ፤ ከኢትዮጵያ ስወጣ ግን ፌስቡክ ዋናው ወዳጄ ሆነ፤ ትኩስ የሀገር ቤት መረጃ ከፌስቡክ ማግኘት ጀመርኩ፤ ቀስ በቀስም በጎ አድራጎት ስራ በፌስቡክ መስራት ጀመርኩ፤ ተሳካልኝም፡፡

 

 

ፌስቡክን በመጠቀም ከሰራናቸው በጎ ተግባራ ውስጥ ከዴንማርክ ወደሀገራችን በሁለት ዙር ለዩኒቨርሲቲዎች የላክነው መፅሀፍት፣ ለሜሪጆይ ሀዋሳ ለሚሰራው የአረጋዊያን ማእከል የተደረገ የገንዘብ ድጋፍና እንዲሁም በአርሲ ሮቤ ዲደአ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን በመፅሀፍት ለመርዳት የተደረጉትን እንደስኬት መጥቀስ ይቻላል፡፡

 

ቢሆንም እኔም እንደግለሰብ፣ እንዲሁም እንደ ሀገር ከፌስቡክ መጠቀም ያለብንን ያህል ተጠቅመናል ብዬ ግን አላምንም፤ በተለይ ችግረኞችን ለመርዳት፤ ትውልድን በመቅረፁ ረገድ፣ ብዙ እድል ቢኖርም የሚገባውን ያህል ግን የተጠቀምንበት አይመስለኝም፡፡ በተጨማሪም አልፎ አልፎ ፌስቡክ ላይ አንዳችን ከሌላው ጋር ሚዛናዊ የሆነ ውይይት ስናደርግ ማየት የተለመደ አይደለም፤ አንዱ ምክንያት ፌስቡክ ላይ ሁሉን ሰው ማወቅ አለመቻሉ ነው፤ አልፎ አልፎ ሰዎች ስማቸውን ቀይረው ጸያፍ ሀሳቦችን ሲለጥፉ ይታያል፡፡

 

መቼም በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ አንዳንዶቹ ሰዎች ክፉ ሀሳብ ብቻ የሞላቸው አሉና ራሳቸው ሰላማቸውን አጥተው የሌላውን ሰላም ለማሳጣት የሚሰሩ ፌስቡክ ላይ ይታያሉ፤ በተጨማሪም በተለይ ሴት ልጆችን ለፍቅር በመጠየቅ መሰናክል የሚሆኑም ሞልተዋል፡፡ ስለሆነም ወላጅና ወጣቶች እንዲሁም መምህራን ለወጣቶች ስለማህበራዊ ድህረገፆች አጠቃቀም ማስተማር አለብን፡፡ አትጠቀሙ ብንላቸው ተደብቀው ይጠቀማሉ፡፡

 

ይልቅ የሚያጋጥማቸውን ሁሉን ነገር በነፃነት እንዲነግሩን ግልጽ ውይይት ማድረግ ይገባል፡፡ በተጨማሪም ወጣቶች ከተራ ውይይትና ፎቶ መለጠፍ በዘለለ ጥልቅ ሀሳቦች ላይ  ትኩረት እንዲያደርጉ መደረግ አለበት፤ ስለሆነም ወላጆችና መምህራን ማድረግ ያለባቸው ነገር ፌስቡክ መጥፎ ነው ማለት ሳይሆን ከፌስቡክ ውስጥ ልጆቻችን እንዴት ተጠቃሚ እንደሚሆኑ በግልፅ ውይይት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም ጊዜው በቴክኖሎጂ አቅም ተቀይሮዋል፤ ቴክኖሎጂው ለኛ ለወላጆች ትርጉም ባይሰጠንም ልጆቻችን መጠቀማቸውን ይቀጥላሉ፡፡

 

 

ከፌስቡክ በተጨማሪም ልጆቻችን ዩቱብ የሚባለውን የቪዲዮዎች ድህረገፅ የፍቅር ፊልሞችን ብቻ ሳይሆን ከሚማሩዋቸው ትምህርቶች ጋር በተያያዘ በጣም ብዙ መረጃዎች ስለሚገኙ አማራጩን ማሳየት ያስፈልጋል፡፡ ዩቱብ/youtube/ ላይ ከአንደኛ ክፍል ሂሳብ ትምህርት ጀምሮ እስከ ዩኒቨርሲቲ ኮርሶች ድረስ ቪዲዮዎችን ማግኘት ይቻላል፡፡ ስለሆነም ተማሪዎችና ልጆቻችን ከፌስቡክ በተጨማሪ እነኚህን ድህረገፆች መጠቀም እንዲችሉ መምከርና መለማመድ አለባቸው፡፡

 

ማህበራዊ ድህረገፆች ለፖለቲከኞቻችን የጦርነት ሜዳም ሆነዋል፤ ጦርነት ከጫካ ውስጥ ወደማህበራዊ ድህረገፆች በመመለሳቸው ደግሞ ደስታ ሊሰማን ይገባል፤ ምክንያቱም በሰዎች ህይወት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ስለሚቀንሰው፤ ነገር ግን ወጣቱ ትውልድ ከማህበራዊ ድህረገፆች የሚያነበውን ሀሳቦች አመጣጥኖ መቀበል አለበት፤ በተጨማሪም ሀሳቦቹ አሁን ያለንበትን ዘመን መመጠን አለመመጠናቸውን መመርመር አለበት፤ ለምሳሌ ሀገራችን ብዙ ልዩነቶች አሉባት፤ ታዲያ ወጣቱ ትውልድ ልዩነትንና በሀይማኖትም ይሁን በብሄር ከሱ ከሚለዩት ጋር በሰለጠነና ዘመናዊ በሆነ መልኩ አብረው የመኖርን ክህሎት መማር አለባቸው፡፡ ለምሳሌ የቋንቋ ልዩነትን ሰላማዊ በሆነ መንገድ በመቀበል ወጣቱ የሚኖርበት አከባቢ የሚነገሩትን ቋንቋዎች በመማር  የልዩነትን ችግር ማጥበብ ይችላሉ፡፡ የአለማችን ህዝቦች ሁሉ የአንድ ሀይማኖት ተከታዮች፤ አንድ ቋንቋ ተናጋሪና የአንድ ብሄረሰቦች ቢሆኑ ኖሮ እጅግ ሰላማዊ አለም ይኖረን ነበር ብለን ለመናገር ባንደፍርም ልዩነት ግን በጥበብና በአርቆ አሳቢነት የሚታለፍ መሆኑን ማወቅ ይገባል፡፡

 

ልዩነት መጥቀሱ ያስፈለገበት ዋናው ምክንየት በማህበራዊ ድህረገጾች ላይ ብዙውን የሀገራችንን ወጣት ጊዜ የሚወስዱት ስለሀይማኖት ስለብሄር ስለተለያዩ ክልሎች መወያየትና መከራከር ናቸው፡፡ አንዳንዶቻችን የግለሰብንና የቡድንን እንዲሁም የአንድ ብሄርንና የአንድ ብሄረሰብን ልዩነት በሰከነ መንፈስ ከመረዳት ይልቅ አንድ ሰው የሚያጠፋውን ጥፋት እንደብዙሀን ጥፋት በማየት አላስፈላጊ ጭቅጭቅ ውስጥ ሲገቡ እያየን ነው፡፡ ሌላው ልንስማማበት የሚገባው እውነታ ዛሬ ያለንበት የሀገራችን ችግረች እጅግ ውስብስብና ከአያት ቅድመ አቶቻችን ጀምረው እየሰፉና እየተጨመረባቸው የነበሩ ናቸው፤ ስለሆነም ችግሮቹን ለመፍታት ከአባቶቻችን በተለየ አርቀን በማሰብ የዛሬ ቴክኖሎጂና ትውልድ ከደረሰበት እውቀት ጋር በማነፃፀር መሆን አለበት፡፡ በተጨማሪም ሁላችንም ለራሳችን ኢንዲሆንልን የምንፈልገውን ያህል ለሌሎች ስናደርግ ብቻ ሀገራችን በዘላቂነት እንደምትበለፅግ መረዳት አለብን፡፡ በአጠቃላይ ፌስቡክና ሌሎች ማህበራዊ ድህረ-ገፆች በሀገራችን ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ሂደቶች ላይ ከፍ ያለ ጫና እያሳደሩ ይቀጥላሉ፤ በተለይ በፖለቲካው በኩል ዱሮ የነበረውን የጫካ ውስጥ ጦርነት ማህበራዊ ድህረገጽ ማምጣቱ ይቀጥላል፤ እኛ ግን ከቴክኖሎጂው ጋር አብረን መዘመን አለብን፤ አንዳችን የሌላውን መብት ማክበር፤ በሰለጠነ መንገድ መወያየት፣ ጥላቻን ከአእምሮአችን ማስወገድና ሀሳባችንን ከእርኩስ አስተሳሰብ ነፃ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

ስራ አጥነት

 

የ21ኛው ክፍለ ዘመን ለየት ያለው ገጽታው የአለማችን የገንዘብ አቅም እጅግ እየጨመረ መሄዱና ቀድሞውን በድህነት የሚታወቅና ኢኮኖሚያቸው ከፍተኛ ያልነበረ እንደህንድና ቻይና የተለመደውን የምእራቡን አለም ባለሀብት ራስምታት ያስያዙበት ጊዜ ነው ብንል ብዙ የተሳሳትን አይመስለኝም፡፡ የቻይና፣ የህንድ፣ የብራዚልና የሩሲያ ኢኮኖሚዎች ማንሰራራት ከአለም የገንዘብ ድርጅት ጀምሮ እስከ አለም ባንክ ያሉትን ትልልቅ ድርጅቶችና እንደአሜሪካን ያሉትን ገናና ሀገራት ማሳሰቡ አልቀረም፤ ለምሳሌ በአሁኑ ወቅት ባለው የአሜሪካን የፕረዘዳንት ምርጫ ክርክር ወቅት በሪፐብሊካኑ ፓርቲ በኩል የቀረበው ተራምፕ ከአሜሪካውያን ኢኮኖሚ መዳከምና ከስራ አጥነት ጋር በተያያዘ ቻይናን በተደጋጋሚ ተጠያቂ ሲያደርግ ክርክሮቹን የተከታተልን መስማታችን ግልፅ ነው፡፡ በአውሮፓም ቢሆን የስራ አጥ ወጣቶች ቁጥር በጣም ከፍተኛ የሆነባቸው ሀገራት ለምሳሌ ግሪክ፣ እስፔን፣ ጣሊያን ወዘተ ሊጠቀሱ ይችላሉ፤ ጀርመኖችን ሳይጨምር አብዛኛው የአውሮፓ ሀገራ ከተለመደው በተለየ የስራ አጥ ወጣቶች ብዛት ከፍተኛ ነው፡፡ ስለሆነም ብዙ ያደጉ ሀገራት ከኢኮኖሚያቸው የተነሱ ችግሮች ላይ ነው ያለው፡፡ ያደጉት ሀገረት የኢኮኖሚ መዳከም ዋና ምክንያት ሀገሮቻቸው ብዙ መሰረተልማቶች የተገነቡ ሲሆን በሀገራቸው ከዪኒቨርሲቲ ለሚመቀሩት መሀንዲሶችና የግንባታ ባለሙያዎች እንዶሁም በማምረት ኢንዱስትሪዎች ውስጥ ለተሰማራው ሰራተኛም የስራ ዋስትና መሰጠት አልተቻለም፡፡ ምክንያቱም እነኚህ አዳዲስ እያደጉ ያሉት ሀገራት የምእራቡን አለም የነበሩትን የታዳጊ ሀገራትንና የራሳቸውንም ገበያ በርከሽ ምርት በማጥለቅለቃቸው ለአውሮፓና ለአሜሪካ ምርቶች ገበያ መቀነሱ ግድ ነበረ፡፡ እኔም በኖርኩበት በዴንማር ሀገር ብዙውን ሱፐርማርኬቶችና ሱቆች የሞሉት ምርቶች ከቻይና የመጡ ናቸው፡፡

 

ቻይና ለምን ልዩ ሆነች ብለን ልናስብ እንችላለን፤ ቻይና በአሁኑ ሰአት ከአሜሪካ ቀጥላ የአለማችን ቁጥር ሁለት ግዙፍ ኢኮኖሚ አላት፤ በተጨማሪም ቻይና ከአንድ ቢሊየን በላይ የህዝብ ብዛት ስላላት ለሚመረቱት ምርቶች ርካሽ  የሰው ሀይል  ስላላቸው በዝቅተኛ ዋጋ ለገበያ ማቅረብ ይችላሉ፡፡

 

ለምሳሌ ዴንማርክን ብንወስድ ሰው ተቀጥሮ ሚሰራበትን ስራ ትርፋማነት ከባድ ከሚያደርጉት ጉዳዮች አንዱ የሰራተኛው ትንሹ ደሞዝ በመንግስት የተደነገገ ስለሆነ ለምሳሌ የአንድ የጽዳት ሰራተኛ ደሞዙ በሰአት ቢያንስ 300 ብር ነው፡፡ ሰራተኛቸው በቀን ለ5 ሰአት ቢያፀዳ ክፍያው 1500 ብር ይሆናል ማለት ነው፡፡ ቻይናዎች ደግሞ አውሮፓ ከሚልኩት ምርቶች ውስጥ የተወሰነውን አፍሪካ ውስጥ ያመርታሉ፤ ኢትዮጵያዊያን እንደምሳሌ ብንወስድ ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚቀጥሩት ሰራተኛ በመንግስት የተቀመጠ የክፍያ መጠን ስለሌለ ለአንድ የጉልበት ሰራተኛ በወር 1500 ብር ሊከፍሉ ይችላሉ፡፡ እንግዲህ ልዩነቱን አስቡት፤ ዴንማርክ ሀገር ላለው ሰራተኛ 1500 ብር የሚከፈለው በአንድ ቀን ለ5 ሰአት ስራ ብቻ ነው፤ ሀገራችን ደግሞ ለአንድ ወር የሰራተኛ ክፍያ 1500 ብር ይከፈላል፡፡ ሁለቱን ሀገራት በቀጥታ ማወዳደር ባይቻልም ምርቶቹ በአውሮፓ ገበያ ሲቀርቡ ኢትዮጵያ የተመረተው ምርት ዋጋው ዝቅተኛ ቢሆንም አያከስርም፡፡

 

 

በተጨማሪም ዴንማርክ ሀገር ያለው አምራች ድርጅት ለሰራተኞች የጤና ኢንሹራንስ መክፈል አለበት፤ የስራ ደህንነታቸው የተጠበቀ ይሆናል፤ በሀገራችን ደግሞ ሰራተኛው ስራ ላይ እያለ ጉዳት ቢደርስበትም በቀላሉ የጤና ኢንሹራንስ ላይከፈለው ይችላል፡፡

 

ቢሆንም በሀገራችንም ስራ አጥነት መኖሩ ግልፅ ነው፤ ነገር ግን ዴንማርክ ሀገር ወይም አሜሪካን ሀገር ያለው ስራ አጥና ሀገራችን ያለው ስራ አጥ በተመሳሳይ ኢኮኖሚ ውስጥ አይደለም የሚኖሩት፤ ያደጉት ሀገራት ስራአጥነት በዋናነት ብዙ መሰረተ ልማቶች ተሰርተው ስላለቁ ኢኮኖሚው እንደሀገራችን ክፍተት የለውም፤ በሀገራችን ደግሞ ብዙ ያልተገነቡና ሰፊ ክፍተት ያለበት ኢኮኖሚ ነው ያለን፡፡

 

ለምሳሌ የቤቶችን ልማት ብንመለከት፤ በሀገራችን ብዙ ቤተሰቦች ቤት ተከራይተው የሚኖሩ ሲሆን የተወሰነ ገንዘብና ቋሚ ስራም እያላቸው የመኖሪያ ቤት ማግኘት ያልቻሉ ብዙ ናቸው፡፡ እነኚህ ቋሚ ስራ ያላቸው ዜጎች ቤት መስራት ይችላሉ፤ ቤት እንዲሰሩ ደግሞ ከደሞዛቸው በረጅም ጊዜ የሚከፈል የባንክ ብድር መመቻቸት ይኖርበታል፤ በተጨማሪም የቤት መስሪያ መሬት በቀላሉ መሰጠት አለበት፤ መንግስት ገቢውን ከመሬት ሳይሆን ቤቶቹ ተሰርተው ከሚገኘው የቤት ግብርና እንዲሁም በአዳዲሶቹ ሰፈሮች ከሚከፈቱት የንግድ ድርጅቶች ቀረጥ በመሰብሰብ በተዘዋዋሪ ገቢውን ማስጠበቅ ይችላል፡፡ ስለሆነም ቤቶች በቀላሉ መስራት ቢቻል ብዙ የግንባታ ስራዎች ስለሚኖሩ ለመሀንዲሶችና ለብረታብረት ሰራተኞች ወዘተ እጅግ ብዙ ስራ እድል መፍጠር ይቻላል፡፡

 

በግብርናውም ብንመለከተ ተመሳሳይ ትልቅ ክፍት የሆነ ኢኮኖሚ ነው ያለን፤ ለምሳሌ ሀገራችን ብዙ ትልልቅ የግብርና ምርቶችን ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች የላትም፤ በመሆኑም የግርርና ጥሬ እቃዎችን በቀጥታ ወደውጪ በመላክ የግብርና ፋብሪካ ውጤቶችን ከውጪ በብዙ ገንዘብ ታስገባለች፡፡ ለምሳሌ የምግብ ዘይትን ብንወስድ፤ ሀገራችን በጣም ብዙ የምግብ ዘይት ከውጪ ታስገባለች፤ ነገር ግን የቅባት እህሎች ሀገራችን ወደውጪ ከምትልካቸው ምርቶች ትልቅ ድርሻ ይይዛሉ፡፡ ወደውጪ የሚላከው የግብርና ጥሬ እቃ በሙሉ ሀገራችን ውስጥ በፋብሪካ ተቀነባብሮ አንደኛ ለወጣቶች የስራ እድል ይከፍታል፤ እንዲሁም ሀገራችን በውጪ ንግድ የምታወጣውን የውጪ ምንዛሬ ገንዘብ ይቆጥባል፡፡

ስለሆነም በሀገራችን የወጣቶችን የስራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ ሀገራችን በየዘርፉ ያለውን የኢኮኖሚ ክፍተት ለኢንቨስትመንት ክፍት ማድረግ አለባት፡፡

 

ቀላል መፍትሄ ለመጥቀስ ያህል እስቲ የሀገራችንን ከተሞች እንመልከት፤ ከሀዋሳ ወደቢሾፍቱ ስመላለስ ሁሌም በሀሳቤ የሚመላለስ ጉዳይ አለ፤ ሞጆ፣ አለምጤና፣ መቂ፣ ዝዋይ፣ አዳሚ ቱሉ፣ ቡልቡላ፣ አርሲ ነጌሌ፣ ኩየራ…እነኚህን ከተሞች ብንመለከተ ብዙ የማደግ አቅም ያላቸው ከተሞች ናቸው፤ አዲስ አበባና ሀዋሳ መሬት በነጻ መስጠት ባይቻልም፣ በነኚህ ትንንሽ ከተሞች እድገታቸው እንዲፋጠን የከተማ መሬት ለአከባቢው ህዝብ በቀላሉ መሰጠት አለበት፤ የተሰጠውን መሬትም ቶሎ ቤት እንዲሰራበት በባንክ ብድር በማመቻቸት የሀገርን አኮኖሚ ማሳደግና ለወጣቶችም ስራ እድል መፍጠር ይቻላል፤ ከአዳማ እስከ ድሬ ሼሁሴን ያለውን የሀገራችንን ክፍል ብንመለከት/ አዋሽ፣ ዴራ፣ ኢተያ፣ ሁሩታ፣ አርብ ገበያ፣ ዲክሲስ፣ ቡላላ፣ አርሲ ሮቤ፣ ሀቤ፣ አዴሌ፣ በሌ፣ ሴሩ፣ በዲ መደርሾ፣ ዋጂ፣ ሊሎ ጉራቲ፣ በረከት፣ ዋቤ፣ ድሬ ሼሁሴን/….እነኚህ ትንንሽ የገጠር ከተሞች ናቸው/… በነኚህ ከተሞች ዙሪያ ግን እጅግ ብዙ አርሶ አደርና አርብቶ አደር ይገኛል፡፡

 

የዚህ አከባቢ ህዝብ ኑሮ እንዲለወጥ የመንገድና የኤሌክትሪክ እንዲሁም የጤና የውሃ የከተሞች ቤቶች ልማትና ብድርና ቁጠባ እጅግ ያስፈልጋል፡፡ በተጨማሪም ከበዲ መደርሾ ጀምሮ ዋጂ፣ ሊሎጉራቲ፣ በረከት፣ ደሮ ዲባዩ፣ ሀዲዶ፣ መደርሾ፣ ዋቤና የመሳሰሉት አከባዎች ከፍተኛ የእንሰሳት እርባታ አቅም ያላቸው ቦታዎች ናቸው፡፡ ለዚህ ሁሉ የልማት አቅም መጀመርና ተግባራዊነት መንግስት ቆንጆ መንገድ መስራትና መብራት ማስገባት እንዲሁም ለአከባቢው ወጣቶች የብድር አገልግሎት መመቻቸት አለበት፡፡ በአጭሩ በየክልሎቻችን እጅግ ብዙ የልማት አቅም አለን፤ ስለሆነም የሀገራችንን ስራ አጥነት ከአውሮፓና ከአሜሪካ ጋር ማገናኘት አይቻልም፡፡ በሀገራችን ስራ አጥን መቀነስ የሚቻልበት አጋጣሚ አሁን ነው፡፡

 

ስራ አጥነትን ለመቀነስ የሀገራችን ወጣት ለስራ ያለውም አመለካከት መስተካከል ያለበት ይመስለኛል፤ ለምሳሌ በምእራቡ አለም አንድ የዩኒቨርሲቲ ተመራቂ በተማረበት ሙያ ስራ እስኪያገኝ ድረስ የተለያዩ የጉልበት ስራዎችን ይሰራል፤ ለምሳሌ እኔ ዴንማርክ ሀገር በነበርኩበት ወቅት የፅዳት ስራ ሰርቻለሁ፤ በእርሻ ማሳ ላይ የጉልበት ስራ ሰርቻለሁ፤ ምግብ የማብሰል ስራ ሰርቻለሁ፤ በተጨማሪም ስራዎቹን ባላገኝም የፖስታ ማመላለስ ስራ ለመስራት አመልክቻለሁ፤ አትክልተኝነት ስራም አመልክቼ ነበረ፤ በምግብ ቤትና በሆቴሎች ውስጥ የማስተናገድ ስራ ለመስራት የስራ ማመልከቻ ልኬ ነበረ፡፡

 

ብዙዎቹ በውጪ ሀገራት የሚኖሩ የሀገራችን የተማሩ ወጣቶች ከተማሩት ትምህርት ውጪ እነኚህን ከላይ የተዘረዘሩትን ስራዎች ይሰራሉ፤ ታዲያ ሀገር ቤት ያሉት ወጣቶች ስራ እስኪያገኙ ድረስ እነኚህን ስራዎች ቢሰሩስ ምን ችግር አለው ብለን ብንጠይቅ ሊጠቀሱ የሚችሉ ብዙ ችግሮች አሉ፤ ለምሳሌ ችግሩ ከወላጆችና ከጎሮቤት ወይም ከማህበረሰቡ ይጀምራል፤ የዩኒቨርሲቲ ተመራቂ ሆኖ የፅዳት ስራ ወይም የጉልበት ሰራተኝነትን እንደሞት የሚቆጥሩት ብዙዎች ናቸው፤ ባለፈው ሁለት አመታ ውስጥ ከዩኒቨርሲቲ የተመረቁ ተማሪዎች ኮብል እስቶን ማንጠፍ ስራ ለምን ይሰራሉ የሚል ብዙ አስተያየቶች በፌስቡክ ላይ ሰዎች ሲወያዩ አይቻለሁ፡፡

 

ነገር ግን በውጪ ሀገራት ካለው ተሞክሮ ማንኛውም የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ከተማረበት ሙያ ጋር ተቀራራቢ ስራ እስኪያገኝ ድረስ የተገኘውን ስራ እንዲሰራ ይበረታታል፤ ስለዚህ ኮብልስቶን የሚሰሩትን ወጣቶች ሞራል መንካት አላዋቂነት ነው፤ በተጨማሪም በሆቴሎች የማስተናገድ ስራ ባደጉት ሀገራት የሚፈለግ ስራ ነው፤ ዴንማርክ ሀገር አብራኝ የተማረች የዛ ሀገር ዜጋ ትምህርት ስትማርም በእንድ ሆቴል የማስተናገድ ስራ እየሰራች ነው፤ ማስትሬት ዲግሪዋንም ከጨረሰች በኋላ ስራ አስክታገኝ ድረስ የማስተናገድ ስራ እየሰራች ነበረ፤ የማስተናገድ ስራዋንነበክብር ነው የምትሰራው፡፡

 

 

ይህ በሀገራችን ቢሆን ህዝቡ ኡኡኡ ልጆቻችን ከዪኒቨርሲቲ ተመርቀው የሆቴል አስተኛጋጅ ሆኑ ብሎ  ክርክር እንደሚጀመር ከኮብል ስቶን ማንጠፍ ስራ የተሰጡትን አስተያየቶች በማየት መገመት ያቻላል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ሌላው የሀገራችን ችግር፣ የፅዳት ሰራተኝነት፣ የሆቴል መስተንግዶ ስራ፣ አትክልተኛነት፣ ተመላላሽ ሰራተኛነት፣ ወዘተ ክፍያቸው እጅግ ዝቅተኛ መሆኑ ነው፡፡

 

በቅርቡ ከዩኒቨርሲቲ በሳይኮሎጂ ተመርቃ ስራ እስክታገኝ ድረስ በአንድ ታዋቂ ሆቴል በመስተንግዶ ስራ ሰራሁ ያለችኝ ወጣት በሀገራችን ስራን አስመልክቶ ያለውን የተሳሳተ ግንዛቤ ከተሞክሮዋ አረጋግጣልናለች፤ በሆቴሉ ስትሰራ ብዙ የሆቴሉ ደምበኞች ልጅትዋን የሴትኛ አዳሪ ስራ እየሰራች እንደሆነ ነው የሚገነዘቡት፤ ብዙዎቹ ለተቃራኒ ፆታ ግንኙነት ይተይቁኛል አለችኝ፤ እጅግ ሞራል የሚነካ መሆኑን አስረዳችኝ፤ በተጨማሪም የክፍያው ጉዳይ ወጣቶችን የሚጎዳ ነው፤ አንድ እኔ የማውቀው ድርጅት ነው፤ እዛ ድርጅት ውስጥ የአንድ አልጋ የአንድ ምሽት የኪራይ ዋጋ 4000 ብር ነው፤ ነገር ግን እዛ ድርጅት ውስጥ በጽዳት ሰራተኛነት የምትሰራው ሰራተኛ የወር ደሞዝ 750 ብር ነው፡፡

 

ይህ እጅግ አሳፋሪ የክፍያ መጠን ነው፤ ሰራተኛዋ ተስማምታ ብትሰራም መንግስት እንደዚህ አይነቶቹን ድርጅቶች ከገቢቸው ጋር ተመጣጣኝ ክፍያ እንዲከፍሉ የክፍያ መጠን ማስቀመጥ አለበት፤ ምክንቱም በወር 750 ብር ደሞዝ የምትሰራው ሰራተኛ የቤት ኪራይ፣ የምግብ፣ የልብስና የጤና ወጪ በዚህ ደሞዝ መሸፈን አትችልም፡፡

 

ስለሆነም ማንኛውም ስራ የሚሰራ አምራች ዜጋ /የቤት ሰራተኞችን ጨምሮ/ ለመኖር የሚያስፈልጋቸውን መሰረታዊ ወጪ ማለትም የምግብ፤ የመጠለያና የጤና ክፍያ ከስራቸው ማግኘት አለባቸው፡፡ ለዚህም ደግሞ በውጪ ሀገራት እንደሚደረገው ከአንድ በላይ ስራ መስራት ይኖባቸው ይሆናል፡፡

 

 

ለማጠቃለል ያህል የሀገራችን የስራ አጥነት ችግርን ለመፍታት ትልቁን ሀላፊነት መንግስት መወጣት አለበት፤ ለምሳሌ የመንገድና የውሃ የመብራት አገልግሎቶችን በትንንሽ የገጠር ከተሞች በማስገባት፤ ሁለተኛ የብድር አገልግሎትን በማመቻቸት፤ ሶስተኛ በገጠር ከተሞች ዜጎች የቤት ባለቤት እንዲሆኑ መሬት በማከፋፈል፤ ለቀጣሪ ድርጅቶች ከገቢያቸው ጋር የሚቀራረብ ክፍያ እንዲከፍሉ ህግ በማውጣት፤ እንዲሁም ህዝቡና ወጣቱ ስራን በተመለከተ የአለመካከት ለውጥ ማምጣት፤ የዩኒቨርሲቲ ተመራቂ ተማሪዎች በተማሩት ሙያ ስራ እስኪያገኙ ጊዜያዊ የጉልበት ስራ ቢሰሩ እንደውድቀት መቁጠር አያስፈልግም፡፡

 

ሀገራችን አሁን ባለው ሁኔታ ትክክለኛ የገቢ ግብር እየከፈለ ላለው የመንግስት ሰራተኛ ዘላቂ የኑሮ መሻሻል ሲባል አንድ ሰራተኛ ለመኖር የሚያስፈልጉትን ዋና ዋና ነገሮች በተለይ ደግሞ የቤት ባለቤትነት ችግርን ለመቅረፍ ሰራተኛው ከመንግስት ባንኮች የረጅም ጊዜ ብድር ተመቻችቶለት መሬት በነፃ ተሰጥቶት ቤት ሰርቶ ልጆቹን እያሳደገ በሰላም የሚኖርበት ሁኔታ ሊመቻችለት ይገባል፡፡ ምክንያቱም የመንግስት ሰራተኞች ለቤት መስሪያ የሚሆን ገንዘብ ለመቆጠብ ብዙ ጊዜ ይወስድባቸዋል፡፡

 

ስለሆነም አላስፈላጊ ለሆነ የቤትኪራይ ወጪ ይዳረጋሉ፤ ነገር ግን ለቤት ኪራይ የሚከፍሉትን ገንዘብ ለመንግስት ባንኮች በየወሩ ገቢ በማድረግ የራሳቸው ቤት ባለቤት እንዲሆኑ ማድረግ ይቻላል፤ አሁን እየተሰራበት ያለው የኮንደሚኒየም ቤቶች የሰራተኛውን ችግር በተለይ በትንንሽ የገጠር ከተሞች ያለውን ችግር የፈታ አይመስለኝም፤ በተጨማሪም ለድሆች ተብለው የሚሰሩትን ኮንደሚኒየሞች ገንዘብ ያላቸው ባለሃብቶች ናቸው እየተጠቀሙበት ያሉት፤ ይህ የአሰራር ክፍተትም ጥብቅ የሆነ ቁጥጥር ይገባዋል፡፡

 

አመጋገባችን

 

በሙያዬ የግብርናና የአመገጋብ ስርዓት ባለሙያ ነኝ፤ በመሆኑም ከሙያዬም ጋር የተያያዘ መልእት በዚህ አጋጣሚ ማስተላለፍ ይጠበቅብኛል፡፡ ስለሀገራችን የአመጋብ ስርአት እጅግ ብዙ ስራዎች መሰራት አለባቸው፤ ምክንያቱም ሀገሪቱ ከሰባ በላይ የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች የሚኖሩባት እንደመሆንዋ መጠን የየብሄረሰቡ አመጋገብና ባህላዊ የምግብ አዘገጃጀት ሰፊ ልዩነት አለው፡፡ ቢሆንም በሀገራችን የአመጋገብ ስርአት ስልጠና ለብዙ ዘመናት ትኩረት ሳይሰጥ የቆየ ሙያ ነው፤ በሀገራን ለመጀመሪያ ጊዜ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ የአመጋብ ስርአት ስልጠና የተጀመረው በ1998 ዓ.ም  በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡

 

የመጀመሪያው የአመጋገብ ስርአት የድህረ ምረቃ ፕሮግራም በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሲጀመር  በፍላጎት ጥናት ስራው ላይ ለመሳተፍ እድሉ ነበረኝ፤በወቅቱ ብዙዎቹ የሀገራችን ባለሙያዎች ስለአመጋገብ ስርአት ግንዛቤው አልነበራቸውም፤ አብዛኛዎቹ ያነጋገርናቸው ባለሙያዎች የአመጋብ ስርአትን የምግብ ዋስትና አድርገው ነበር የሚረዱት፤ ቢሆንም ከአመጋገብ ስርአት ጋር የተያያዙት ችግሮች ለረጅም ጊዜ በሀገራችን ነበሩ፡፡ የመጀመሪያው የአመጋገብ ስርአት ስልጠና በአሜሪካን፣ በኒውዚላንድና በጀርመኖች ድጋፍ በድህረ ምረቃ ደረጃ እንዲከፈት ታላቅ አስተዋፅኦ ያደረጉት ዶክተር የወልሰው አበበና በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞው የቤተሰብ ሳይንስ ቴክኖሎጂና  ቀጥሎም የገጠርልማትና ቤተሰብ ሳይንስ ትምህርት ክፍል ባልደረቦች ለነበሩት በሙሉ፣ በእነሱ ጥረት ከ1998 ጀምሮ ሀገራችን በአመጋገብ ስርአት ሙያ ባለሙያዎችን ሊኖራት በመቻሉ ሊመሰገኑ ይገባል፡፡

 

ከ1998 ዓ.ም. በፊት ሀገራችን ውስጥ Home Science Technology/የቤተሰብ ሳይንስ ቴክኖሎጂ/ በመባል የሚታወቀው የስልጠና ዘርፍ ከጤና ሳይንስ ቀጥሎ ብቸኛው የአመጋገብ ስርአት ኮርሶች የሚሰጡበት የሙያ ዘርፍ ነበረ፡፡ ከ1994 በኋላ ግን የቤተሰብ ሳይንስ ቴክኖሎጂ የሚባለው የስልጠና ዘርፍ ወደገጠር ልማትና ቤተሰብ ሳይንስ ተለውጦ /እኔም በዚሁ ሙያ የመጀመሪያው ተመራቂ የመሆን እድሉን አገኘሁ/ ተማሪዎች ስለአመጋገብ ስርአት መሰረታዊ እውቀት እንዲኖራቸው ሁለት ኮርሶችን ይወስዱ ነበረ፡፡

 

የአመጋገብ ስርአት በአጭሩ የሰው ልጆች ስለሚመገቡት ምግብ የሚያጠና ሳይንስ ነው፤ በመሆኑም ሰዎች መመገብ ካለባቸው የተለያዩ የምግብ አይነቶች የሚያገኙትን ንጥረነገርና ምግቡ ሰውነት ውስጥ ገብቶ ለጤናችንና ለእድገት ጥቅም ላይ እንዲውል የሚያልፍበትን ሂደቶች፣ በተጨማሪም ከመጠን በላይ ወይም ከመጠን በታች ምግብ ስንመገብ የሚፈጠሩትን ችግሮችና መፍትሄዎቻውን፣ ከሰውነት ውስጥ የቆሻሻ አወጋገድ ወዘተ የሚያጠና ሳይንስ ነው፡፡ ስለሆነም የአመጋገብ ስርአት ከምግብ ዋስትና ጀምሮ ምግቦች ሰውነታችን ውስጥ የሚጫወቱትን ሚና ሁሉ ያጠቃልላል፤ በተጨማሪም ከአመጋገብ ጋር ተያይዘው የሚከሰቱት ችግሮች ብዙ አይነት ሲሆኑ፤ ችግሮቹንም በሁለት ዋና ዋና  ክፍሎች እንከፍላቸዋለን፤ አንደኛው ከምግብ ንጥረነገሮች ማነስ ጋር የተያያዘ የሚከሰቱ ችግሮች ወይም under nutrition ሲሆን ሁለተኛውን ደግሞ አንድ ወይም ደግሞ ከአንድ በላይ የሆኑ የምግብ ንጥረነገሮችን ከሚፈለገው በላይ አብዝተን በመውሰድ የሚከሰቱ ችግሮች ወይም over nutrition ናቸው፡፡

 

በሀገራችን ከምግብ እጥረት ጋር የተያያዙ ችግሮች በአለማችን ከፍተኛውን ደረጃ ከሚይዙት ውስጥ ይመደባሉ፤ ለምሳሌ የህፃናት መቀንጨር ችግር /ከእድሜያቸው ጋር ሲነፃፀር ብዙ የሀገራችን ህፃናትና አዋቂዎችም ቁመት አጫጭሮች ናቸው/፡፡ ይህ ችግር ደግሞ የአንድ ማህበረሰብ ለረጅም ከወላጆች ወደልጆች ሲተላለፍ የቀመጣ የአመጋገብ ችግርን የሚያመላክት ነው፤ ችግሩም በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የተለያየ ሁኔታ አለው፡፡ ከአምስት አመት በፊት በ2003 ዓ.ም.  በተደረገው ሀገር አቀፍ ጥናት፣ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የሚኖረው ማህበረሰብ በሀገራችን ደረጃ ትልቁ የህፃናት መቀንጨር ችግር  ያለበት ነው፡፡

 

 

ክልል የቀነጨሩ ህፃናት ከመቶ

በ2003 ሀገር አቀፍ ጥናት መሰረት

አማራ 52
ብኒሻንጉል 49
ድሬዳዋ 36
ትግራይ 51
ጋምቤላ 27
ኦሮሚያ 41
አዲስ አበባ 26
አፋር 50
ሀራሪ 30
ደቡብ 44
ሶማሊ 33

 

በአብዛኛ በገጠሩ የሀገራችን ህዝብ ዘንድ  የአመጋገባችን መሰረታዊ ችሮች ከሚባሉት ውስጥ ዋነኛው፣ የእንሰሳት ተዋፅኦ፣ አትክልትና ፍራፍሬ በብዛት አለመመገብና በእህል የተሰሩ ምግቦችን ብቻ ማብዛት ነው፡፡ በመሆኑም የመክሳት፣ የአእምሮና የአካል እድገት መቀንጨር፤ እንዲሁም እንደ ደም ማነስ፤ እንቅርት፣ የጥርስ መበለዝ፣ የአጥንት ጥንካሬ አለመኖር፣ በምሽት የማየት ችግር ወይም ዳፍንት እንዲሁም የሰውነት የበሽታ መከላከል አቅም ማነስ፣ የአእምሮ እድገት ዘገምተኛ መሆን ወዘተ ከምግብ ንጥረነገሮች ማነስ ጋር የተያይዞ የሚከሰቱ ችግሮች ናቸው፡፡

 

የከተማው ህዝባችን ችግር ደግሞ /በተለይ ገቢያቸው ከፍተኛ የሆነው ከተሜዎች/ አነስተኛ የአካል እንቅስቃሴ ማድረግና እንደ ጮማ፣ ቅባትና ዘይት፣ ስኳር፣ አልኮል ምግቦችን አብዝቶ መመገብ ሲሆኑ ከዚህ የተነሳም በከተሞቻን የስኳር በሽታ፣ ደም ግፊት፣ የኩላሊት በሽታ፣ ካንሰር፣ የጉበት ሀመሞች፣ ከመጠን በላይ ውፍረት በፍጥነት እየተስፋፉ ይገኛል፡፡ ይህ በከተሞቻን እየተስፋፋ የሚገኘው ከአመጋገብ ጋር የተያያዙ ችግሮች ያደጉት ሀገራትን ህዝቦች በመግደል የሚታወቁ ስለሆነ እጅግ ጥንቃቄ ማድረግ አለብን፡፡

 

ከአንድ በላይ የሆኑ ከምግብ ንጥረነገሮችን ከሚፈለገው በላይ አብዝተን በመውሰድ የሚከሰቱ ችግሮች ወይም over nutrition ጋር ተያይዘው የሚከሰቱትን የአመጋገብ ችግሮች  ደግሞ ለምሳሌ ከመጠን ያለፈ ውፍረት፣ የስኳር በሽታ፣ የኩላሊት ተጠጠር፣ የደም ግፊት፣ ካንሰር የመሳሰሉት ናቸው፡፡

 

ከነኚህ በሽታዎች ለምሳሌ የስኳር በሽታ በሀገራችን ከተሞች ያሉት ሆስፒታሎች በስኳር በሽተኖች ተጨናንቀዋል፡፡ በሽታውም በዋናነት የተሻለ የኑሮ ደረጃ የሚኖሩትን እንዲሁም ከተሜውን የሀገራችን ህዝብ በብዛት እየጎዳ ይገኛል፡፡ ከአመጋገብ ጋር የተያያዙ ችግሮችን በሙሉ መዘርዘር ባይቻልም በተለይ በከተሞቻችን በአስፈሪ ሁኔታ እየጨመረ ስላለው የስኳር በሽታ መሰረታዊ የሆኑ የመከላከያ ዘዴዎችን መጥቀሱ አስፈላጊ ነው፡፡ የስኳር በሽታ (diabetes mellitus) አንድ ሰው በደሙ ውስጥ ያለው የስኳር መጠን (serum glucose level) መሆን ከሚገባው በላይ ከፍ ብሏል ማለት ነው። ይሕ በሽታ አብዛኛውን ጊዜ በሂደት እና ከብዙ አመታት በኋላ የሚከሰት ነው። በመሆኑም እድሜያቸው ከ40 በላይ የሆኑ ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ሲጠቁ ይታያል ። አንድ ጥናታዊ ፅሑፍ እንደሚያመለክተው በጎንደር ከተማ እድሜያቸው ከ40 አመት በላይ ከሆኑት ሰዎች መካከል ከመቶ ሶስት የሚሆኑት የዚህ በሽታ ተጠቂ ናቸው ። ይህ አሃዝ አሳሳቢ መስሎ ላይታይ ይችላል። ነገር ግን በሽታው በተለይ ወፍራም (overweight) እና/ወይም አዘውትረው የአካል እንቅስቃሴ የማያደርጉ ሰዎችን የሚያጠቃ ስለሆነ፤ በተሻለ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ግለሰቦች በሚበዙበት ትልልቅ ከተሞች በርካታ የስኳር በሽታኞች እንዳሉ እሙን ነው።  አለም አቀፍ የስኳር በሽታ ምልክት ሰማያዊ ክብ ነው፡፡

 

ቀለል በሚል መልኩ ለማስረዳት የስኳር በሽታ ማለት በሰውነታችን ደም ውስጥ ያለው ስኳር በተገቢው መልኩ ወደሰውነታችን ህዋሳት መግባት ሳይችልና ለረጅም ጊዜ ብዙ ስኳር በደማችን ውስጥ ሲከማች የሚከሰት ነው፤ በጤናማ ሰው ከቆሽት የሚመነጭ ኢንሱሊን የሚባል ንጥረ ነገር በደማችን ውስጥ ያለው የስኳር መጠን ሲጨምር ህዋሶቻችን ስኳሩን ከደም ስሮቻችን ወደሰውነታችን ውስጥ እንዲያስገቡ ያደርጋል፤ ነገር ግን የስኳር በሽታ ታማሚዎች አብዛኞቹ ይህ ሆርሞን ህዋሶቻቸውን አያነቃቃም፤ ስለሆነም ብዙ ስኳር በደማቸው ውስጥ ይከማቻል፡፡ በደም ውስጥ የሚከማቸው ስኳር ደግሞ ለተለያዩ በሽታዎችና ለውሀ ጥም እንዲሁም ለረሃብ ይዳርጋል፤ የስኳር በሽታ በጊዜ ክትትል ካልተደረገበት በሽተኛውን ለአይነ ስውርነትና እንዲሁም ለብዙ ተያያዥ የጤና ችግሮች ይዳርጋል፡፡

 

ከዚህ ጋር ተያይዞ መነሳት ያለበት ጉዳይ የበሽታው መንስኤ ምንድን ነው የሚለው ነው፤  የስኳር በሽታ ዋና መነሻ በትክክል ምን እንደሆነ ባይታወቅም ስኳር በሽታ  ካለበት የቤተሰብ አባል በውርስ የተወሰነ የመተላለፍ እድል እንዳለው ጥናቶች ያሳያሉ፡፡

ይህንን በሽታ በተመለከተ ethiopianchurch.org በተሰኘ ድህረገፅ ዶክተር ወርቁ አበበ የስኳር በሽታ በተለይም ለኢትዮጵያውያን በሚል ርእስ ቀጥሎ የቀረበውን ፅፈዋል፡፡ ፀሀፊውን እያመሰገንኩ ሙሉ ሀሳቡን እንደሚከተለው አቀርባለሁ፡፡ በየአመቱ ህዳር 5 November 14) የአለም የስኳር በሽታ መታሰቢያ ቀን ነው፡፡ ዋና አላማው የበሸታውን በአሳሳቢ ደረጃ መስፋፋትና አሰከፊነት ለህዝብ በማሳወቅ ወይም በማስታወሰ የመከላከያ እርምጃ እንዲወሰድ ለማበረታታት ነው። በአለም ዙሪያ ባሳሳቢ ሁኔታ በመጨመር ላይ ካሉ በሽታዎች መካከል አንዱ የስኳር በሽታ መሆኑ ተመዝግቧል። ለምሳሌ ያህል የአለም የጤና ጥበቃ ድርጅት በአለም ደረጃ የዚህ በሽታ ሰለባዎች እ.አ.አ በ1985 ዓ.ም 30 ሚሊዮን መሆናቸውን በመግለፅ በ1995 ዓ.ም 135 ሚሊዮን ፤ በ2000 ዓ. ም ደግሞ 171 ሚሊዮን መድረሳቸውን አሳውቋል። በመጪው 2030 ዓ.ም ይህ ቁጥር እጥፍ ሊደርስ  እንደሚችልም ተተንብዮአል። በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ በአገር ደረጃ ምን ያህል የስኳር በሽተኞች እንዳሉ በውል አይታወቅም። ነገር ግን በአንዳንድ በተወሰኑ ቦታዎች በተካሄዱ አነስተኛ ጥናቶችና በሀኪም ቤት የምዝገባ ሰነዶች መሠረት ከአስር ዓመታት በፊት ገደማ ጀምሮ ከመቶ ዘጠኝ እጅ (9%) ሊደርሱ የሚችሉ የስኳር በሽተኞች እንደነበሩ ተገልጿል። በየሀኪም ቤቱ በየቀኑ ከሚመረመሩ በሽተኞች አኳያ ሲታይ በአሁኑ ጊዜ በአገሪቱ ከዚህ ቁጥር የሚበልጡ እንጂ ያላነሱ በሽተኞች ሊኖሩ እንደሚችሉ ይገመታል።

ከመቶ ውስጥ ከ90 እስከ 95 እጅ የስኳር ህመም ከጊዜ በኋላ የሚከሰት ሆኖ ሣለ ከቆሽት የሚመነጨው ኢንሱሊን ሥራውን እንደሚገባ ሊሠራ ባለመቻሉና ቀጥሎም መጠኑ በማነሱ ጭምር የሚመጣ ሕመም ነው። ይህም የስኳር በሽታ በዘር የመተላለፍ ፀባይ አለው።

የስኳር በሽታ ምልክቶች ምንድን ናቸው? ሁሉም የስኳር በሽታ አይነቶች ተወራራሽ የሆኑ ጸባዮችን የሚያሳዩ ቢሆንም እያንዳንዳቸው የራሳቸው የሆኑ ልዩ የመለያ ምልክቶች አሏቸው። ከዚህም ሌላ የእያንዳንዱ የሕመም ምልክቶች እንደ በሽተኛው ሁኔታ ሊለያዩ ይችላሉ። ዋናዎቹ የአይነት አንድ የስኳር በሽታ ምልክቶች የሚቀጥሉት ናቸው ።

 

  • አዘውትሮ መሽናት
  • በብዛት ውሃ መጠጣት
  • የአፍ መድረቅ
  • በብዛት መራብ
  • በብዛት ክብደት መቀነስ
  • አዘውትሮ በሆነው ባልሆነው መበሳጨት
  • የድካም ስሜት
  • የአይን ግርዶሽ

 

ሌላ መጠቀስ ያለበት ጉዳይ ብዙ የሆኑ የአይነት ሁለት የስኳር በሽተኞች ከላይ የተጠቀሱትን ምልክቶች በግልጽ ሳያሳዩ ለረጅም ጊዜ ሊቆዩ እንደሚችሉ ነው። የደማቸው የስኳር መጠን ከፍ ያለ ቢሆንም እነዚህ በሽተኞች መያዛቸውን ሳያውቁ በበሽታው ሊጎዱ የሚችሉ ናቸው። ስለሆነም ህብረተሰባችን በየጊዜው ወደጤና ተቋማት በመሄድ የጤና ምርመራ ማድረግ አለበት፤ ምንም የህመም ስሜት አለመኖር የጤናማነት ማረጋገጫ መሆን አይችልም፤ ሁላቸንም ሙሉ ጤናማ ነኝ ለማለት ተመርምረን ጤንነታችንን ካረጋገጥን ብቻ መሆኑን መረዳት አለብን፡፡ ምክንያቱም ምልክት ሳያሳዩ ብዙ ጊዜ የሚቆዩ ነገር ግን ከጊዜ ብዛት ለማከም አስቸጋሪ ደረጃ የሚደርሱ ህመሞች አሉ፤ ለምሳሌ የስኳር በሽታ፡፡

የስኳር በሽታ ጥንቃቄ ሳይደረግለት እንዲቀጥል ከተደረገ ምን ችግሮችን ያስከትላል? ይህ ሁኔታ እንዲቀጥል ከተደረገ በሽታው በተለያዩ የሰውነት አካላት ላይ የተለያዩ ጉዳቶችን በማምጣት ከፍተኛ የጤንነት መጓደልን ያስከትላል። የረጅም ጊዜ ዋነኛ ችግሮች ተብለው የተመደቡት ቀጥሎ የተዘረዘሩት ናቸው። የደም መዘዋወሪያ ቧንቧን በመጉዳት የደም ብዛት ወይም ግፊት የመጨመር በሽታን ማምጣት

  • የልብ በሽታ መከሰት
  • የአይን በሽታን ብሎም መታወርን ማስከተል
  • የኩላሊት በሽታን ማምጣት ወይም ማባባሰ
  • የስራስር (ነርቭ) በሽታና ከዚህ ጋር የተያያዙ ችግሮች ማስከተል
  • የደም መዘዋወርን ችግር በእግርና በሌሎች አካላት ውስጥ ፈጥሮ የተያያዙ ጉዳቶችን ማስከተል፤ በተለይም
  • ደግሞ ለእግር መታመምና መቆረጥ ምክንያት መሆን
  • ከመድረቅ አንስቶ የተለያዩ የቆዳ ህመሞችን መፍጠር
  • በአንጎል ውስጥ ደም የመፍሰስ ወይም የመርጋት ችግር መፍጠር

ለስኳር በሽታ መከሰት ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉ ጠንቆች አሉ? አይነት አንድን በተመለከተ የተረጋገጠ ቀጥተኛ የሆነ ጠቋሚ ምክንያት የለም። ነገር ግን በተዘዋዋሪ ከዚህ ጋር ግንኙነት ሊኖራቸው ይችላሉ ተብለው የሚታሰቡ ጥቂት አመልካች ነገሮች አሉ።  እነርሱም፦

  • በቤተሰብ ውስጥ ሕመሙ ቀደም ብሎ መታየቱ
  • ለአንዳንድ የጀርም አይነቶች (ቫይረስ) መጋለጥ
  • በትውልድ ጊዜ ልጆች ለአንዳንድ የበሽታ አይነቶች መጋለጥ ናቸው ።

አይነት ሁለትን አስመልክቶ የአንዳንድ ሰዎች በበሽታው የመያዝ ወይም ያለመያዝ ምክንያቶች በግልፅ የታወቁ ባይሆኑም፤ ቀጥሎ የሰፈሩት ጉዳዮች ብዙ ሰዎች በሽታውን በግልፅ ለማሳየታቸው በምክንያትነት ሊቀርቡ የሚችሉ ናቸው።

  • ሕመሙ በቤተሰብ ውስጥ መኖር
  • የሰውነት እንቅስቃሴ (ስፖርት) አለማድረግ
  • ውፋሬ ወይም ክብደት ከሚገባ በላይ መጨመር
  • በእድሜ መግፋት
  • ብዙ ጣፋጭ ምግቦችን፣ ጨው፣ ቅባት፣ ዘይት፣ ጮማ ስጋ፣ አልኮል፣ ስኳር መመገብ
  • በርግዝና ወቅት በስኳር በሽታ መታመም
  • ክብደቱ ከፍተኛ (ከ4 ኪሎ በላይ) የሆነ ልጅ መውለድ
  • የደም ብዛት ወይም ግፊት ከመጠን በላይ ሆኖ መገኘት
  • የልብ በሽታ መኖር

የስኳር በሽታንና ጠንቆቹን እንዴት ለመከላከል ወይም እንዳይባባሱ ማድረግ ይቻላል?

የበሽታውን ምልክቶች ማስተዋሉ ጠቃሚ ነው። ነገር ግን ምልክቶቹ በግልፅ ሳይታዩ፤ በተለይ አይነት ሁለትን የስኳር በሽታ አስመልክቶ፤ ለረጅም ጊዜ ህመሙ ሊኖር ስለሚችል፤ ስለሆነም ከሁሉ በፊት ማኛውም ሰው በየጊዜው ደሙን በመመርመር ከስኳር ነፃ መሆኑን ማረጋገጥ አለበት፤ ምክያቱም በሽታው ምልክት ሳያሳይ አደገኛ ደረጃ ሊደርስ ስለሚችል፡፡ በተጨማሪም የትኛውም አይነት የስኳር በሽታ ቢሆን የሕመሙ ምልክቶች ከታዩ ወዲያውኑ የዘመናዊ ሕክም ማግኘት አስፈላጊ ነው። እነዚህ ጥንቃቄዎች በጊዜ ከተወሰዱ እንደ በሽታው አይነት ሕመሙን ለመከላከል፤ ለማዘግየት ወይም ደግሞ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ የሚቻል ነው። ይህ ከተደረገ ሕመምተኛውን መርዳት ብቻ ሳይሆን በበሽታው ጠንቅ ለሕክምና ተብሎ ሊወጣ የሚችለውን ከፍተኛ የገንዘብ መጠን ለመቀነስ ያስችላል።

አንዳንድ የምርምር ጥረቶች እየተካሄዱ እንዳሉ ቢታወቅም አይነት አንድን የስኳር በሽታ ለመከላከል እስካሁን የሚቻል አልሆነም። ሆኖም በመድኃኒትና (ኢንሱሊን) ሌሎች ለጤንነት የሚበጁ እርምጃዎችን በመውሰድ በሽታው የሚያስከትለውን የአካል ጉዳት መቀነስና እድሜን ማራዘም ይቻላል። በአንፃሩ አይነት ሁለት በሽታን በጊዜ አስፈላጊ የሆኑ ለጤና ጠቀሜታ ያላቸውን እርምጃዎች በመውሰድ በሽታውን መከላከል ወይም ማዘግየት ይቻላል ። ነገር ግን እነዚህ እርምጃዎች የሚጠበቀውን ውጤት ለመስጠት ብቁ ሆነው ካልተገኙ በሽተኛው በመድኃኒቶችም ጭምር ሊታገዝ ይገባዋል። በእርግዝና ወቅት የሚከሰተውን የስኳር በሽታ መከላከል የሚቻል ቢመስልም የዚህ እርምጃ አስተማማኝነት አጠራጣሪ ነው። ስለሆነም ብዙውን ጊዜ መድኃኒቶችና ሌሎች ለጤና ጠቃሚ የሆኑ ነገሮች አብረው መወሰድ ይኖርባቸዋል።

ቀጥሎ የተመለከቱት ለሶስቱም የስኳር በሽታ አይነቶች መደረግ ያለባቸው መሠረታዊ ጠቃሚ ነገሮች ናቸው።

  • የደምን የስኳር መጠን መከታተል። ይህ የበሽታውን ሁኔታ ለማወቅ የሚረዳ መሠረታዊ መረጃ ሰጪ ተግባር ነው ። ቀጥሎ ሊወሰድ የሚገባውን እርምጃ ጠቋሚ ሊሆን ይችላል።
  • ጤነኛ የሆነ ምግብ መመገብ። ይህ ምግብ አትክልትና ፍራፍሬ በብዛት የያዘ ሆኖ ፤ ስኳርነትና ቅባት ነክ የሆኑ ነገሮች ያልበዛበት ቢሆን ጠቀሜታው ከፍ ያለ ነው። ሆኖም እንደ አሣ ዘይት፤ ተልባ፤ የወይራ ዘይት የመሳሰሉት በዚህ የሚጠቃለሉ እንዳልሆኑ መጠቀሰ አለበት።  ተጣርተው ከተፈጩ የእህል ዘሮች ይልቅ ገለባማ የሆኑት ለምግብነት ይመረጣሉ። በማዕድ ወቅት ምግብም ሲወሰድ በአንዴ ብዙ ከመመገብ ይልቅ ከፋፍሎ በየጊዜው መመገቡ የተሻለ ውጤት አለው።
  • ተገቢ በሆነ የሰውነት ክብደት ወይም ውፋሬ ላይ መገኘት
  • አዘውትሮ የሰውነት እንቅስቃሴ (ስፖርት) መሥራት። ለምሳሌ ያህል በየቀኑ ግማሽ ስዓት በመውሰድ በሳምንት ውስጥ ለአምስት ቀናት ያህል መሮጥ
  • ሲጋራ ወይም ትንባሆ ነክ የሆኑ ነገሮችን አለመጠቀም
  • አልኮል መጠጦችን መጠጣት ማቆም ወይም መቀነስ
  • ለተላላፊ በሽታ መከላከያ ተብለው የተሰጡትን ክትባቶች መውሰድ
  • ጨው በብዛት አለመጠቀም
  • በሰውነት ላይ ጭንቀት የሚያመጡ ነገሮችን በተቻለ መጠን መቀነስ ወይም ማስወገድ፤ በቂ የሆነ እቅልፍ ማግኘት
  • የእግርና የጥርስን ጤንነት መንከባከብ
  • ከሁሉም በላይ ስለ ጤንነት ሁኔታ አጠቃላይ ግንዛቤ ለማግኘት በየጊዜው በሕክምና አዋቂ መመርመር። ከላይ እንደተባለው ይህ ድርጊት ቀደም ብሎ አስፈላጊ የሆኑ እርምጃዎችን ለመውሰድ ይጠቅማል። ምርምር የሚደረግባቸው ነገሮች ብዛትና አይነት እንደ በሽታውና በሽተኛው ሁኔታ የሚለያዩ ቢሆንም ብዙውን ጊዜ የደምን ስኳር (ጉሉኮስን)፤ የኮሌስትሮልን፤ የደም ብዛት (ግፊት) መጠንና የአይንን ጤንነት፤ የልብን አሰራር፤ የኩላሊትን ጤንነትና የእግርን ደህንነት የሚመለከት ሊሆን የሚችል ነው።

ለስኳር በሽታ የተጠቀሱት መሰረታዊ ሀሳቦች ለካንሰር፣ ለደምግፊትና ለኩላሊት ህመምም ጠቃሚ መረጃዎች ናቸው፡፡ ከሁሉ በላይ መሰረታዊ መነሻና ልንከላከላቸው የምንችለውን ጮማና ቅባት እንዲሁም ዘይት መቀነስ፤ አልኮልና ጣፋጭ ምግቦችን መቀነስ፣ ጨው አብዝቶ አለመመገብ፣ የአካል እንቅስቃሴ ማድረግ፣ ክብደትን መቆጣጠር ያስፈልጋል፡፡

ለሁሉማ በሽታዎች ባይሆንም ከፍተኛ የክብደት መጨመር በተለይ ለደም ግፊት ቀላሉ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡

የእድገት መቀጨጭ/መቀንጨር/እስተንቲንግ/

Mental retardation/የአእምሮ መቀጨጭ/ ከሰውነት እድገት መቀጨጭ በበለጠ የአንድን ግለሰብ ወይንም ማህበረሰብ እንዲሁም የአንድን ሀገር ህብረተሰብ የእድገትና የልማት ሁኔታ ሊወስን የሚችል ከአመጋገብ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው የጤንነታችን መገለጫ ነው፡፡ ለዚህ መሰረታዊ ጉዳይ የስነምግብ/Human Nutrition/ ባለሙያዎች ብዙ የሚነግሩን አለ፡፡ ለምሳሌ የአእምሮ መቀጨጭ ጉዳይን አሳሳቢ ከሚያደርጉት ምክንያቶች አንዱ የአእምሮን መቀጨጭ በቀላሉ መለካት አለመቻሉ ነው፡፡ ምክንያቱም የአእምሮአችን እድገት ማለት የጭንቅላታችን ትልቅነት ወይም ትንሽነት ሳይሆን፣ የአእምሮ እድገት የሚለካው በተዘዋዋሪ አእምሮአችን በሚሰራው ስራ ወይም በውጤቱ ስለሆነ ነው፡፡ እኛን እንደሀገር ወይም እንደማህበረሰብ የእምሮአችንን ወይም የአስተሳሰባችንን የብስለት ደረጃ ስንመለከት ምሳሌ መጥቀሱ ሳያስፈልግ በብዙ ጎኖቹ ከሚጠበቀው በታች እንደሆነ ሁላችንም የምንስማማ ይመስለኛል፡፡

መገለጫዎቹ፣ ለምሳሌ የምግብ ዘይት ውስጥ ለጤናችን ጎጂ የሆኑ ነገሮችን ጨምሮ ገበያ ላይ ይዞ የሚወጣ ነጋዴ የአስተሳሰብ ብስለት ደረጃ የት ድረስ ነው ብለን መጠየቅ ያለብን አይመስለኝም፡፡ እንዲሁም የአገልግሎት ጊዜያቸው ያለፈ መድሀኒቶችን የአገልግሎት ጊዜያቸው እንዳላለቀ በማስመሰል አሽጎ መሸጥ እጅግ ከባድ የአስተሳሰብ መቀጨጭን የሚያሳዩ ናቸው፡፡ ሌላም ብዙ ብዙ ምሳሌዎች መጥቀስ ይቻላል፡፡ ብዙውን ጊዜ የሚያሳስተን ጉዳይ ለምሳሌ ዶክተር የተባለ ሁሉ ከፍተኛ የአስተሳሰብ ብስለት ያለው ይመስለናል፡፡ ነገር ግን የአእምሮ ብስለት ትምህርትቤት ጥሩ ውጤት ማምጣት ማለት ብቻ እንዳልሆነ ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ አንድ ሀኪም የአገልግሎት ጊዜያቸው ያለፈ መድሀኒቶችን የአገልግሎት ጊዜያቸው እንዳላለቀ በማስመሰል አሽጎ መሸጥ ከቻለ ምኑን ዶክተር ሆነው? ብዙ መማር ማለት፣ ለራስና ለማህበረሰብ ብዙ ዋጋ መስጠት ማለት ነው፣ ነገር ግን አንድ ሰው ከልጅነቱ ጀምሮ የአእምሮው እድገት የቀነጨረ ሲሆን ራሱንና ሌሎችን አደጋ ላይ የሚጥሉ ድርጊቶችን ቀለል አድረጎ ሊወስዳቸው ይችላል፤ ስለሆነም ለም ያልሆነ አፈር ላይ ወይም በትክክል የልታረሰ አፈር ላይ ተዘራ ዘር ምርት እንደሚቀንስ ሁሉ የሰው ልጆችም አስፈላጊውን ምግብ ከልጅነታችን ጀምሮ ካላገኘን ከራሳችን አልፎ ለልጅ ልጆቻችን የሚተርፍ የአስተሳሰብ እንጭጭነት እናወርሳለን ማለት ነው፡፡  እንደማህበረሰብ አርቆ የሚያስብ ትውልድ ለመፍጠር ማድረግ ከሚገባን ነገሮች ውስጥ አንዱ ለልጆችና ለእናቶች አስፈላጊውን እንክብካቤ ማድረግ አለብን፡፡

እንግዲህ ለመቀንጨር ችግረ መፍትሄው ምንድን ነው ብለን ብንጠይቅ፣ ከእናቶችና ህጻናት ጤናና አመጋገብ እንዲሁም በማህበረሰቡ ውስጥ ለሴቶችና ለእናቶች የሚሰጠው ቦታ ታላቁን ድርሻ አለው፡፡ ወደድንም ጠላንም ልጆች የሚወለዱት ከሴቶች ነው፤ ወንድ ለወንድ ብንጋባ፣ ወይም ሴቶችን ከሴቶች ብናኖር የተፈጥሮ ህግ አይቀየርም፤ በሰው ልጆች ታላቁን ነገር ማለትም ልጅ መውለድ የሚችሉት እናቶች ብቻ መሆናቸው፤ ለሀገራችን፣ለቤተሰባችን፣ለአለማችን በአጠቃላይ ለሰው ልጆች የምናስብ ከሆነ የሴቶችን ጤናማ አመጋገብ እንዲሁም በማህበረሰቡ ውስጥ ለእነሱ የሚደረገውን እንክብካቤ ከፍ ማድረግ አለብን፤ ይህ ማለት ግን ወንዶች እንክብካቤ አያስፈልጋቸውም ማልት ሳይሆን እናቶች ከወንዶች ይልቅ ልጅ የሚዘራባቸው የእርሻ መሬት እንደማለት ነው፤ በእርግጥ ዘሩም ቆንጆ እንዲሆን አባትም ሙሉ ጤናማ መሆን አለበት፡፡

ምክንያቱም እናቶች የሚወልዱት ልጆች ጤናና የአስተሳሰብ ደረጃ ከእናት እና ከአባት ቤተሰቦች በውርስ የሚተላለፍና ለእናቶችና ለህፃናቱ በሚደረጉ እንክብካቤዎች ይወሰናል፡፡ ለምሳሌ በእርግዝና ወቅት ለእናቶች ከፍተኛ እንክብካቤ መደረግ አለበት፡፡ ነገር ግን እንክብካቤዎቹ ከፍተኛ ልዩነት የሚያመጡበት የእድገት ደረጃዎች የተለያዩ ናቸው፤ ለምሳሌ አንድ እናት ልጅ ካረገዘችበት ጊዜ ጀምሮ 1000 ቀናት ማለትም ልጁ ተወልዶ ሁለት አመት እስኪሞላው ጊዜ በልጁ ህይወት ውስጥ ትልቅ ለውጥ ሊመጣ የሚችሉበት ጊዜያት ናቸው፤ 1000 days , best window of opportunity ተብሎም ይጠራል፤ ስለሆነም እናቶችም፣ አባቶችም፣ ማህበረሰቡም እነኚህን አሳሳቢ ጊዳዮች አውቀው ለወላጅ እናቶች እንክብካቤ ና የተመጣጠነ ምግብ በመበስጠት፣ የአስተሳሰብ እንጭጭነትን መዋጋት እንችላለን፤ ለሀገራችንም፣ለቤተሰባችንም፣ ለልጆቻችንም፣ ለአለማችንም ችግር ፈጣሪዎችን ሳይሆን ፣ ችግር ፈቺ ዜጎች እንዲወለዱ፣ አለማችን የተሻለች እንድትሆን፣ ካልሆነ ግን የአስተሳሰብ ችግራችንን በብሄረሰብ ምናምን እያሳበብን ችግር ስንደረድር የምንቆይ፣ የቁሳቁስና የአስተሳሰብ ድህነትንም ለልጆቻችን የምናወርስ ይመስለኛል፡፡

 

 

 

የከተሞች ፅዳት

 

የአከባቢ ንጽህና ዘመናዊነትን ከሚያሳዩት መስፈርቶች አንዱና ዋነኛው ነው፤ በተለይ በከተሞች አከባቢ ሰዎች በብዛት ስለሚኖሩ የቆሻሻ አወጋገድ ስርአታችን ዘመናዊ ካልሆነ የሚጠበቀውን ያህል ዘመናዊነት ለማምጣት ከባድ ይሆናል፡፡ የሀገራችን ዋና ከተማ ውስጥ ያውም የአፍሪካ መዲና አዲስ አበባ ውስጥ ያለው የቆሻሻ አወጋገድ ስርአት ዘመኑ ከደረሰበት የቆሻሻ አወጋገድ ስርአት እጅግ ወደኋላ የቀረ መሆኑን በቅርቡ ተከስቶ ከነበረው የቆሻሻ ክምችት ማረጋገጥ ይቻላል፡፡

የአንድ ሀገር ዋና ከተማ ውስጥ በ21ኛው ክፍለ ዘመን የቆሻሻ ክምር ማየት በምንም መስፈርት ተቀባይነት አይኖረውም፡፡ የአዲስ አበባን ቆሻሻ በተመለከተ አንድ ወቅት ከዴንማርክ ሀገር ሁለት ዴኒሽ  ወዳጆቼ ለስራ ወደአዲስ አበባ መጥተው በታክሲ ከፒያሳ ወደ መብራት ሀይል ልንሄድ እነሱ ካረፉበት ሆቴል ፒያሳ ዋናው ታክሲ ተራ የቄራና የመብራት ሀይል የሚጭኑበት ስንሄድ በመንገዱ ዳር ቆርቆሮ አጥር ስር የነበረው የሽንት ሽታ ምን ያህል እንዳሳፈረኝ አልረሳውም፡፡ይህን ምሳሌ ሳነሳ ግን አዲስ አበባ ቆንጆ ሰፈር የላትም ማለቴ እንዳለሆነ ልብ በሉ፡፡ ነገር ግን አንዱ የአዲስ አበባ ሰፈር ስለተፀዳና ስላማረ አዲስ አበባ አማረች ማለትአይቻልም፤ በከተሞቻችን በዋናነት የማስተውለው ችገር አንድን አከባቢ እጅግ ውብ እንዲሆን ይደረግና ሌላው ደግሞ ይረሳል፤ ሀዋሳ ከተማ ወስጥም ተመሳሳይ ችግር አያለሁ፤ ሀዋሳ እጅግ ቆንጆ ከተማ ናት፤ ነገር ግን አንዳንዱ የከተማዋ ክፍል የተረሳ ነው፤ ፒያሳና አረብ ሰፈርን ብናወዳድር የከተማ ውበቱ ስራ በዋናነት ትኩረት የተደረገው በፒያሳ ነው፤ አረብ ሰፈር፣ ኮረም የሚባሉት አከባቢዎች ያንን ያህል የከተማ ውበት ስራ አይታይም፡፡

በቅርቡ ባህርዳር ሄጄ በነበረ ወቅት ሀዋሳንና ባህርዳርን ሳወዳድር ዋናው ልዩነታቸው በጣናና በሃዋሳ ሀይቆች፣ በአየር ሁኔታና የኑሮ ውድነት ካልሆነ በስተቀር ሰው ሰራሽ በሆኑ ለውጦች ያንን ያህል ልዩነት አላየሁም፡፡ አዋሳም የሚያምሩ ቦታዎች አሉ ባህርዳርም እንደዛው፡፡ አዋሳም በጣም የሚያሳፍሩ ቆሻሻ ሰፈሮች አሉ ባህርዳርም የሚያሳፍሩ ቦታዎች አሉ፡፡ ጣና ላይ ተንሳፋፊ መዝናኛ ጀልባ ባለበት በኩል ዳር ዳሩን በእግር ስንሄድ የነበረው የሽንትና ሰገራ ሽታ ከባድ ከመሆኑ የተነሳ በሩጫ ለማለፍ መገደዳችንን አስታወሳለሁ፡፡ አሁንም የባህርዳር ትዝታዬ ይህ ብቻ ነው ማለቴ እንዳልሆነ ይታወቅልኝ፡፡ በተለይ በደሴቶቹ ላይ ባሉት ገዳማት ያየሁትን እጅግ ትልቅ ታሪክ ሁሌም አስታውሳለሁ፡፡

ዋናው ሀሳቤ፣ ከተሞቻችንንና በአጠቃላይ ሀገራችንን ያንን ያህል ሰው ሰራሽ ልዩነት/በተለይ በማሳመሩ ረገድ/ ያደረግን አይመስለኝም፡፡ ሰው ሰራሽ ልዩነት ማለት ለብዙሃኑ የሀገራችን ህዝቦች ሀገራችንን ለኑሮ ምቹ ማድረግ እና ውብ አከባቢ ማድረግን ማለቴ ነው፡፡ ሀገራችን ቆንጆ ናት፡፡ ነገር ግን ቆንጅናዋ የተፈጥሮ ነው እንጂ እኛ ኢትዮጵያዊያኑ በተፈጥሮ ውበትዋ ላይ ያንን ያህል ውበት የጨመርን አይመስለኝም፡፡ ደኖችዋን ጨፍጭፈናል፡፡ ወንዞችዋን በፋብሪካዎች ቆሻሻ በክለናል፤ ለእርሻ ምቹ የሆኑትን ቦታዎች አቅም በፈቀደ መልኩ ሸራርፈን ስንዴም፣ጤፍም፣እንሰትም፣ባህርዛፍም ወዘተ የተመቹንን ተክለንባቸዋል፡፡ የቻልነውንም ያህል ልጆች ወልደንባታል፡፡ ነገር ግን ሀገሪቱን ለኑሮ ምቹና ቆንጆ በማድረጉ ረገድ ብዙ ይቀረናል፡፡ ቢሆንም ግን እንደምሳሌ ሊጠቀሱ የሚችሉ ለየት ያሉ ቆንጆ ስራዎችም አሉ፡፡ በተለይ በከተሞቻችን አከባቢ፡፡ እነኚህ በጎ ለውጦችም የሚታዩት ዋና ዋና መንገዶች አከባቢ ነው፡፡

ለምሳሌ አዲስ አበባ፣ሐዋሳንና ባህር ዳርን ብንወስድ የተወሰኑ መንገዶች ላይ የሚታዩትን ቆንጆ ስራዎች ወደ ሁሉም መንገዶችና ሰፈሮች የተቻለውን ያህል ማዳረስ ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ የባህርዳር ውበት መዲናዋ ከፖሊ ካምፓስ አንስቶ በጣና ሀይቅ ዙሪያ ወደ ኩሪፍቱ በሚሄደው መንገድ ነው፡፡ ሓዋሳም በዋናነት ከገብርኤል ወደ ሀይቁ ዙሪያ  እንዲሁም ወደአሞራ ገደል አከባቢ ባሉት ስፍራዎች ነው፡፡ በእርግጥ አዳዲሶቹ ሰፈሮች አከባቢም በጣም ቆንጆ ስራዎች አሉ፡፡ ወደገበያውና ወደአረብ ሰፈር ስንሄድ ግን ያው ነው፡፡

 

 

አዲስ አበባም ብትሆን ከቦሌ ወደ 4፣5 እና 6 ኪሎዎቹ እንጂ ብዙ ሰፈሮችዋ አሁንም ቆሻሻና ለኑሮ ምቹ ያልሆኑ ናቸው፡፡ ጨርቆስ በመባል የሚታወቀውን ሰፈር በአንድ አጋጣሚ ሄጄ ባየሁት በጣም ነው ያዘንኩት፤ ቦሌንና አከባቢዋን በማስዋብ የሚመሰገነው የአዲስ አበባ አስተዳደር፣ ጨርቆስን የመሳሰሉትን አከባቢዎች ደግሞ ችላ በማለቱ ወቀሳ ይገባዋል፡፡ በነገራችን ላይ የከተማ ውበት ስንል የፎቆች ብዛት ማለት ሳይሆን በዋናነት የአከባቢ ንጽህናንና ውበትን ይመለከታል፡፡ ጋሽ አበራ ሞላ በአዲስ አበባ የጀመሩት ቆንጆ ስራ በሰፊው መስፋፋት አለበት፤ ብዙ የጋሽ አበራ ሞላ አይነት ዜጎችም ያስፈልጉናል፡፡ ከግለሰቦች ጥረት በላይ ግን መንግስት ሀላፊነት እንዳለበት ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡

የገጠሩንም የሀገራችን ህዝብ ኑሮ ብንመለከት ሁሉ ገበሬ አንድ አይነት ባይሆንም በዋናነት ብዙ መሻሻል ያለባቸው ነገሮች አሉ፡፡ ጣናንና አዋሽ ወንዝን ብንወስድ አዋሽ ወንዝ በዝናብ ጊዜያት ከመጠን በላይ ሞልቶ በዙሪያው የሚኖሩትን ገበሬዎች እንደሚያጥለቀልቅ ይታወቃል፡፡ በደረቁ ወቅት ከአዲስ አበባ ወደ ዝዋይ በሚወስደው መንገድ አጠገብ ወንዙን ብናይ በዙሪያው ያለው የግብርና መሬት ባዶውን ነው፡፡ ጥቃቅን የሽንኩርትና የቲማቲም እርሻዎች ቢኖሩም ከውሀው አቅም ሲነጻጸር ግን ምንም አልተሰራም ማለት ይቻላል፡፡ አባይ ወንዝ ከጣና የሚወጣበትን ቦታ በጀልባ ሄደን አይተነው ነበር፡፡ እዛም ያየሁትና ከሰዎችም ጠይቄ እንደተረዳሁት ያንን ያህል ትልቅ የሚባሉ የመስኖ እርሻዎች አለመኖራቸውን ነው፡፡ በግራም በቀኝም…መልሱ ያው አንድ አይነት ነው፡፡ ያለንን የተፈጥሮ ሀብት በአግባቡ አልተጠቀምንበትም፡፡ ይልቁንም ተፈጥሮ የሰጠችንን ፀጋ ከአያያዝ ጉድለት እያጠፋነው ነው፤ ወጣቱ ትውልድ በዚህ ረገድ ብዙ እንደሚጠበቅበት ልብ ሊለው ይገባል፡፡

ታዲያ ችግር መዘርዘር ብቻ ፋይዳ ያለው አይመስለኝም፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ችግርን ነቅሶ በማሳየት ተወዳዳሪ የለንም ይባላል፡፡ ዋናው ጉድለታችን ለችግሮቹ መፍትሄ ማበጀቱ ላይ ነው፡፡ የአእምሮ መቀንጨር ውጤት ሊሆንም ይችላል፤ ታዲያ መፍትሄው ምንድን ነው የሚለው የበኩሌን ሀሳብ እሰነዝራለሁ፤ ሌሎቻችንን መፍትሄዎቹን እናስብበት፡፡

 

ቁጥር አንድ አስተያየቴ ለእናቶችና ህፃናት ዘላቂ የሆነ እንክብካቤ ማድረግ፣ እጅግ ከባድ ድህነት ውስጥ ሆነው ያለገደብ ልጆች የሚወልዱት እናቶች መጠነሰፊ የባለሙያ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ይመስለኛል፡፡ ሁለተኛ የግብርናውን ልማት በተመለከተ በተለይ ወንዞችና ሀይቆች ባሉበት ቦታ እንዲሁም ከሰፈራዎች ራቅ ብለው ባዶአቸውን ያሉት ክፍት የገጠር ቦታዎች ለወጣት የዩኒቨርሲቲ ተመራቂዎችና ስራ ላጡ ወገኖች ተሰጥተው በባለሙያ ድጋፍ ወደልማት ቢለወጡ፡፡ ለምሳሌ የንብ እርባታ በተራራማ ቦታዎች ላይ በሰፊው ሊሰራ ይችላል፡፡

ሶስተኛ በከተሞች አካባቢ ለጎዳና ተዳዳሪዎች የስራ እድልም ሊሆን ይችላል ሽንትቤቶች ተሰርተው ሰዎች እየከፈሉ ቢጠቀሙ፡፡ እንዲሁም የጎዳና ተዳዳሪዎቸ በከተማ ፅዳት ስራ ቢቀጠሩ፣ ሽንት መሽናት ያስቀጣል ብለን በማስፈራራት ሰዎችን በመንገድ ላይ ከመሽናት አላቆምናቸውም፤ ስለዚህ ሽንትቤቶች ደግሞ በሰፊው ሰርተን ዎች ከፍለው እንዲስተናገዱ ብናደርግ፡፡ ሽንት መሽናት ያስቀጣል፤ ሽንት መሽናት ያስቀጣል፡፡ ማስፈራራያ ብቻ ዋጋ የለውም፣ መፍትሄውን ማሰብም ያስፈልጋል፤ ሽንት ለያዘው ሰው ሽንት መሽናት ያስቀጣል ብለን ማስፈራራት ሳይሆን የሽንት መሽኛ ቦታ ማሳየት ችግሩን ይፈታዋል፤ ሌላው ደግሞ ሁሉም ሰዎች በአከባቢያቸው ላለ ቆሻሻ ሀላፊነት እንዲወስዱ ቢደረግ፡፡ ከመኖሪያቤቶችና ከንግድቤቶች የሚወጡ ፍሰሽ ቆሻሻዎች ጎዳናዎች ውስጥ በስብሰው ሰፈር ሲያሸቱ ዝም መባል ያለበት አይመስለኝም፡፡

አስተያየቴ ትክክል ካልሆነ እታረማለሁ፡፡ ይህቺን የምንወዳትን ሀገር ወደፊት ልጆቻችንና የልጅ ልጆቻችን ይኖሩባታል፡፡ ምናልባት ጥቂት እድለኞች/ ውበት እንደተመልካቹ ነውና ያም እድል ከተባለ/ ልጆቻችንን ውጪ ሀገር/ለምሳሌ አሜሪካ/ ሄደን ስለወለድናቸው እዚህ ለመኖር እንደማይገደዱ ይታወቃል፡፡ እኔ እስከሚገባኝ ድረስ ግን የሌላ ሀገር ኑሮ በዋናነት ገንዘብና ቁሳቁስ ያስገኛል እንጂ እውነተኛ ደስታንና በራስ መተማመንን የሚፈጥር አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም  ሁሉ የተማረ ዜጋ ራሱንና ሀገሩን በማልማት የራሱ ሀላፊነት እንደሆነ የሚክድ አይመስለኝም፡፡

 

ምክንያቱም የሰለጠኑ የሚባሉት ሀገራት በዋናነት የዜጎቻቸው ውጤት ናቸውና፡፡ የኛም ልጆች የሰለጠኑት ሀገራት ዜጎች ቢሆኑም አንድ ቀን ግን የራሳችን ሀገር ለምን የተሻለ አትሆንም ብለው መጠየቃቸው አይቀርም፡፡ በጣም እርግጠኛ ነኝ፤ ከብዙ ሀገር ቤት ካሉት ወጣቶች የበለጠ በውጪ ያሉት ናቸው ስለሀገራችን ድህነት የሚያስቡት፡፡ ምክንያቱም አከባቢያቸውን ያያሉ፤ ስለራሳቸውም ይጠይቃሉና፡፡ የኔስ ሀገር ማለታቸው የግድ ነው፡፡ በዋናነት ግን ከመቶ ከዘጠና አምስት በላይ የሚሆነው ህዝብ እዚሁ ሀገር ይኖራል፡፡ የህዝቡም ብዛት እየጨመረ ስለሆነ የበለጠ አርቀንና ፈጥነን ማሰብ ያለብን ይመስለኛል፡፡

እኔ እንደዚህ ስል ውጪ ሀገር መኖር አልፈልግም ወይም አሁንም ለመሄድ አማራጮችን አልሞክርም ማለቴ አይደለም፡፡ ምንም ቢመቸኝ ምንም የተሻለ ስራ ቢኖረኝ ወገኖቼና የሀገሬ ህዝቦች ብሎም የአፍሪካ እንዲሁም የታዳጊው አለም ድህነት እስካለ ድረስ ከልቤ ልደሰት እንደማልችል አውቀዋለሁ፡፡ ይህንንም ውጪ በነበርኩ ጊዜ አይቼዋሁ፤ የዴንማርክ ዋና ከተማ ኮፐንሀገን እጅግ ውብ ከተማ ናት፤ ከተማዋ ለነዋሪዎችዋ አመቺ እንድትሆን ሁሌም ስራዎች አሉ፤ ልጆቼን ይዤ ኮፐንሀገን ከተማ ውስጥ ለመናፈስ ስወጣ በሀሳብ ወደሀገሬ እመጣ ነበረ፡፡

 

ከመንገዶቹ አሰራር ጀምሮ የቆሻሻ አወጋገድ ስርአታቸው፣ የልጆች መጫወቻ ቦታዎች ብዛትና ጥራት፣ የከተማውስጥ የደኖች ልማት፣ሰው ሰራሽ የከተማ ውስጥ ወንዞች፣ ወዘተ ሁሉም እጅግ አርቆ በማሰብ የተሰሩ ናቸው፤ ያንን ሁሉ ወደከተሞቻችን ሰርቆ ማምጣት ቢቻል የመጀመሪያው ሌባ እኔ ነኝ፤ በጣም የሚገርመው እኮ በከተሞቻችን ብዙ ትልልቅ ስራዎች አሉ፤ ለምሳሌ የኮንደሚኒየም ቤቶች ግንባታ እጅግ ትልቅ ስራ ነው፤ የሚያሳዘነው ነገር ታዲያ ቤቶቹን የሚገነቡት ድርጅቶች መጨረሻውን አያሳምሩትም፡፡

 

ቀላል ምሳሌ እስቲ በኮንደሚኒየም ቤቶች ያለውን የኤሌክትቲክ መስመሮች ዝርጋታ ልብ በሉ፡፡ ገመዶቹን ያለምንም ከለላ ክፍት አድርገው የተዉት ብዙ ቦታ ነው፤ ያ ሁሉ የሀገር ሀብት ወጪ የተደረገበት ግንባታ አጨራረስ ተንጠልጥሎ የሚቀርበት ምክንት ሊገባኝ አይችልም፡፡ ውጪ ሀገር ኖሮ ወደሀገራችን ለሚመለስ ዜጋ የሚከብደው ነገር ይህንን ሰማይና ምድር የሆነ የኑሮ ልዩነት ማየትና በቅናት መቃጠል ነው፤ ይህ አይነቱ ስሜት የሁሉም የታዳጊ/የደሃ/ሀገር ዜጎች ስሜት እንደሚሆን ይገባኛል፡፡ ዴንማርክ በነበርኩበት ጊዜ ከተለያዩ የአፍሪካና የኤሺያ ሀገራት የመጡ ዜጎች ጋር ስወያይ የጋራ ሀሳባችን ድህነት እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ ስለሀገር አስፈላጊነትና የሀገር ምን እንደሆነ አንድ አይነት አመለካከት ላይኖረን ይችላል፡፡

ነገር ግን ራሳችንን ከወላጆቻችን፣ከዘመዶቻችን፣ከወገናችን፣ከህዝባችን ውጪ አድርገን ማየት የምንችል ግን አይመስለኝም፡፡ ያ ስሜት ባይኖርማ ለምን የአሜሪካን ወታደሮች የስንት አፍሪካዊ ወጣቶች ህልም ከሆነችው ሀገራቸው ተነስተው አፍጋኒስታንና ኢራቅ ሄደው ሕይወታቸውን ይሰጡ ነበር? ወይስ ለምን አባቶቻችን በዱሮ ጊዜ ከጣሊያን ወራሪዎች ጋር ተፋልመው ያንን ሁሉ መስዋእት ከፈሉ? ለምንስ ያንን ሁሉ የእንግሊዝ ሀገር ወታደሮች አፍጋኒሰታን ውስጥ ሞቱ? ሀገር እጅግ ትልቅ ነገር ነው፤ የሰው ልጅ ማህበራዊ እንሰሳ ነው፤ ትልቁ የሰው መለኪያ ደግሞ ማህበራዊ አንድነቱና ለጋራ ችግሮቹ ዘላቂ መፍትሄ ማበጀቱ ላይ ነው፡፡ እኔ በራሴ ሰርቼ ተለውጬ ከሀገርም ርቄ ልኖር እችላለሁ፤ ነገር ግን የራሴ ሀገር ላይ ማግኘት ያቃተኝን ነገር ሌሎች ሀገር ሄጄ ለማግኘት ሳስብ ራሴን ለዘመናዊ ባርነት አሳልፌ ሰጠሁ ማለት ነው፡፡

ሀገራችን ብዙ ልጆችዋ ዘመናዊ ባርነት ገዝቶባታል፤ ብዙ እጅግ የተማሩ ዜጎቻችን በገንዘብ ተሸጠውባታል፤ የሀብታም ሀገራት ዜጎች አገልጋይ ሆነዋል፤ የራሳችን ሀገር ውስጥ ህዝባችን በባለሙያ ችግር እየተሰቃየ የራሳችን የተማሩ ምርጥ ልጆች ግን ለዘመናዊ ባርነት ተሸጠውብናል፡፡

 

አሁንም ብዙዎች ራሳቸውን ለሀብታም ሀገራት ለመሸጥ በዝግጅት ላይ ይገኛሉ፤ የራሳችን መሀንዲሶች ወደምእራቡ አለም ሲሰደዱ የቻይና መሀንዲሶች ወደሀገራችን እየተሰደዱ ነው፤ ከሞኚ ደጅ ሞፈር ይቆረጣል እንደሚባለው፤ በራሳችን ገበሬ መሬት ላይ የሌላ ሀገር ሀብታሞች እየከበሩ ነው፤ ይህ ግን መቆም አለበት፤ የራሳችን ልጆች በሀገራችን ሰርተው እንዲለወጡ ሁኔታዎች መመቻቸት አለባቸው፤ የሁሉንም ጥረት ይጠይቃል፤ ወጣቱም መስዋእትነት መክፈል አለበት፡፡

 

ዛሬ ያለውን የሰለጠነ አለም ብንመለከት አባቶቻቸው ብዙ መስዋእትነት ከፍለውላቸዋል፡፡ ጣሊያኖችን እንደምሳሌ ብንወስድ ለሀገራቸው ብልፅግና ሲባል ሀገራችን ድረሰው መጥተው ሞተዋል፤ ታዲያ እኛ ሌሎችን መውረር ባይኖርብንም የራሳችን ሀገር በሌሎች ሀገር ሀብታሞች ሲወረር ጥለን መሰሰደድ መፍትሄ መሆን የለበትም፡፡ ይህ እውን እንዲሆን ደግሞ መሪዎቻችን ግንባር ቀደሙ ሀላፊነት አለባቸው፡፡ በተለይ ለተማሩት ዜጎች ነፃነትና ክብር ማሳየት አለባቸው፡፡ የተማረ ሰው ብዙ ይጠይቃል፤ ብዙ ሂስ ያደርጋል፤ ጥያቄዎቹንና ሂሶቹን በሰላማዊ መነገድ ተቀብሎ መፍትሄ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ወጣቱንም የመፍትሄው አካል ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

አዎ የሰው ልጅ ከወገኑ ራሱን ነጥሎ ለማየት እጅግ የተለየ አስተሳሰብና ስሜት ያስፈልገዋል፡፡ በተለይ ደግሞ እንደ ሀገራችን ካሉ ደሃ ሀገራት የወጡ ዜጎች መቼውንም ቢሆን የሀገራቸውን ህዝብ ድህነት መርሳት የሚችሉ አይመስለኝም፡፡ የሀገራቸውን ቢረሱ የዘመድ የቅርብ ወዳጆችን ድህነት አይረሱም፡፡ ስለዚህ ከያለንበት ሆነን ለህዝቦቻችን እድገትና ብልጽግና የበኩላችንን ማድረግ ያለብን ይመስለኛል፡፡ ሀገራችንንና ራሳችንንም ከሚገባን በላይ ማዋረድ ወይም ከሚገባን በላይ መቆለል ያለብን አይመስለኝም፡፡ በቁመታችን ልክ ከፍ ብለን ለመሄድ ብንሞክር! አጎንብሰን መሄድ ወይም ተንጠራርተን ብንሄድ ትርፉ ትዝብት ነው፡፡

 

አንዳችን ሌላውን መማማር ያለብን ይመስለኛል፡፡ ቅርብ አስበን እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል አይነት ነገሮችን መተው ይገባናል፡፡  ከአስተሳሰብ እስርቤት መውጣት አለብን፡፡ እኛ አውቀን ከሆነ ወንድሞቻችንን ማሳወቅ አለብን፡፡ የአንዳችን ሀሳብ ከሌላችን በጣም የተለየ ሊሆን ይችል ይሆናል፡፡ ለምሳሌ የዚህ ፅሁፍ ሃሳብ ከእርስዎ ሀሳብ ጋር በጣም የሚራራቅ ከሆነ ራስዎን ለውይይት መጋበዝ ነው፡፡ ከኔ የተሻለ ካወቁ ሊያሳውቁኝ ይሞክሩ፡፡ እራስዎን ቅዱስ እኔን ደግሞ እርኩስ አድርገው ቢያስቡ ትርፉ ትዝብት ነው፤ ዘመናዊ ሰው ከራሱ የተለየ አስተሳሰብ እንዳለ ያምናል፤ ያን ማድረግ ከቻልን እኔና እርስዎ ሃላፊነት የሚሳማቸው ዜጎች እንሆናለን፡፡ የሰው ልጅን ክቡርነትና ታላቅነት አስበን የተሻሉ ዜጎችን ማፍራት ላይ ትኩረታችንን ብናደርግ፡፡ አለባበስ ወይም ቁሳቁስ ስላሳመርን ስልጣኔ የኛ የሚሆን አይመስለኝም፡፡ በጎ አስተሳሰብና በጎ ድርጊት ግን የተሻሉ ዜጎች ያደርጉናል፤ ወደድንም ጠላንም ራሳችንን መለወጥ የምንችለው ራሳችን ብቻ ነን፡፡ በተገኘው አጋጣሚ አስተያየት ለመቀበል ዝግጁ ነኝ፡፡ እስቲ ተወያዩበት፤ ብዙ ርቀት መሄድ ያለብን ይመስለኛል፡፡

ግብርናችን ምን ይመስላል

 

ግብርና የሀገራችን ዋናው የኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት መሆኑ ግልጽ ነው፤ በግብርና የሚተዳደረው የሀገራችን ህዝብ ከመቶ ከ75 በላይ ነው፤ ስለሆነም ግብርናውን ለማሳደግ ሀገራችን እጅግ አርቃ ማሰብ አለባት፤ ለምሳሌ ግብርናን በተመለከተ ሀገራዊ ራእይ ያስፈልገናል/ሀገር አርቃ የምታስበው እሷ ማን ናት ብላችሁ አትጠይቁኝ/፤ ገበሬዎቻችን በበሬ ጉልበት፣ በማረሻ፣ በሞፈር፣ በቀንበር ወዘተ ማረስ የሚያቆሙበት ጊዜ መቼ እንደሆነ ሀገራዊ ህልም ያስፈልገናል፡፡ ይህ ሀሳብ በአንድ ትውልድ ላይደረስበት ይችላል፤ ቢሆንም እስቲ ለሚቀጥለው ትውልድ ራእይ ዛሬ እንጀምር፤ እስከ መቼ ድረስ ነው ለአምስት አመት ብቻ የምናቅደው? እስከ መቼ ድረስ ነው የኛ ሀገር ገበሬዎች በበሬ አርሰው፣ በማጭድ አጭደው፣ በአፈር አውድማ ወቅተው፣ ከሶስት ወር የማይዘልቅ ምርት እያመረቱ የሚኖሩት? ይህ ትውልድ ህልም ከኖረው ቴክሎኖጂን ተጠቅሞ ብዙ ርቀት መሄድ ይችላል፤ ለልጅ ልጆቻችን የሚተርፍ ስራ መስራት እንችላለን፤ ህልማችንን ግልጽ አድርገን ለህልማችን እውን መሆን ደግሞ አንዳችን ከሌላችን በቤተሰብ፣ በሰፈር፣ በቀበሌ፣ በወረዳ፣ በዞን፣ በክልል፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ እንዲሁም ከጎሮቤት ሀገሮችም ጭምር ሰላማዊ የልማት ግንኙነት በማድረግ በቅዱስ ሀሳብ መሪነት ሀገራችን አንድ ደረጃ ወደፊት ማራመድ ያለብን ይመስለኛል፡፡ ቅዱስ ሀሳብ መሪነት መኖር ማለት አንዱ ከሌላው ጋር በሰላም አብሮ ሰርቶ ለመለወጥ ማሰብ፣ ከጥላቻ፣ ከጦርነት፣ ከቂም በቀልነት ነፃ መሆንና በዘመናዊ አስተሳሰብ ለጋራ ሰላምና ብልፅግና መስራት ማለት ነው፡፡

 

ለትምህርት በውጪ ሀገር በነበርኩበት ጊዜ ያስተዋልኩት ነገር፤ ያደጉት ሀገራት ገበሬዎች መሬታቸውን በህብረት ስራ አሰባስበው በጋራ ሰርተው ግብርናቸውን አሳድገዋል፤ ወደሀገራችን ስንመለከት ደግሞ አንድ የኛ ሀገር ገበሬ አራት ሄክታር መሬት ቢኖሩት፣ አራት ወንድ ልጆቹ ሲያድጉ፣ ቤተሰብ ሲመሰርቱ የአባታቸውን መሬት ይካፈሉታል፤ ከዛ መሬቱ ይጠባል፤ ወንድም የወንድሙን፣ ልጅ የአባቱን ድንበር መግፋት ይጀምራል፣ በድንበር ሰበብ በቤተሰብ ውስጥም ፀብ ይሆናል፤ አባትና ልጅ ወደፍርድቤት ይሄዳሉ፤ ድርጊታቸው የመጨረሻው ዘመን ደረሰ ያስብለናል፤ በእኔ አስተሳሰብ የዘመን መጨረሻ ስለደረሰ ሳይሆን ራሳችን የጋርዮሽ ዘመን የኑሮ ዘይቤ እየተከተልን፣ ተፈጥሮ የሰጠችንን ሀብት አባክነን ችግር ሲመጣ የመጨረሻ ዘመን የደረሰ ያስመሰልነው ይመስለኛል፤ ስለሆነም በድጋሜ አርቀን ማሰብ አለብን፡፡

 

የሰለጠነው አለም በጣም ትንሽ መሬት ላይ ምን ያህል ትርፋማ ምርት እንዲሚያመርት በዝዋይ አከባቢ ያለውን የአበባ እርሻ እንደ ምሳሌ መውሰድ ይቻላል፤ ለአበባ ምርት የዋለው ቴክኖሎጂ ሌሎች የምግብ ምርቶችንም ማምረት ይችላል፤ በቤት ውስጥ እርሻ አመቱን ሙሉ መምረት ይቻላል፤ በተለይ አትክልት፣ ዶሮ፣ የወተት ከብት ወዘተ፡፡ ለምሳሌ ቢሾፍቱ ያለውን ጀነሲስ እርሻ ብንመለከት እጅግ ትንሽ መሬት ላይ ነው ያንን ሁሉ ዶሮና የወተት ላሞች እንዲሁም አትክልት የሚያለሙት፡፡ ሩቅ ወደአውሮፓ ሳንሄድ እዚሁ ሀገራችንም ብዙ የዘመናዊ ግብርና ምሳሌዎች አሉ፡፡ በየግብርና ቢሮዎች ያለው ባለሙያ ገበሬውን ከኋላቀር አመራረት ዘዴ እንዲያላቅቀው መበረታታት አለበት፡፡

 

ዘመናዊ ትቴክኖሎጂም ሳንጠቀም፣ በህዝብ ብዛት ምክንያት መሬታችን እየተበጣጠሰ ሄደ፤ በቅርቡ ወደገጠር ዘመዶቻችን ጋር ሄጄ ነበረ፤ ዱሮ አንድ ትልቅ የእርሻ ማሳ የነበር መሬት አሁን በትልልቅ የባህር ዛፎች ተከፈለ፤ የእርሻ መሬት መሀል ባህርዛፍ መትከል ለምን አስፈለገ? ባህርዛፉ መሬቱን ያደርቀዋል፣ ውሀ የመሳብ ሀይሉ ከፍተኛ ነው ስላቸው፣ ወንድሞች በመሬት ድንበር ስለሚጣሉ ቋሚ ድንበር ስላስፈለገ ነው ተባለ፤ የሀገራችን ህዝቦችና ወጣቶች ሆይ፣ የሀገራችን ገበሬዎች አርቀው ማሰብ እና አርቆ የሚያስብ መንግስት ያስፈልገናል፡፡ ገበሬዎቹ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ብዙ አርቀው እንዲያስቡ አይጠበቅም፣ አንደኛ ብዙ አርሶ አደር በድህነት ውስጥ ይኖራል፤ በተጨማሪም አብዛኛው አርሶ አደር በሳይንስ ትምህርት እውቀቱ ብዙ አይደለም፡፡

 

ድህነት ውስጥ የሚኖር ህዝብ ለመኖር ሲል መሬት መገፋፋት አይደለም ሀብቱንም ሊዘራረፍ ይችላል፤ ለገበሬዎቻችን ዘላቂ ልማት ግን፣ መሬታቸው ውስጥ ድንበር ማበጀትና የባህርዛፍ መትከል ሳይሆን ጠንካራ የገበሬዎች ህብረት ያስፈልጋል፤ አባት ገበሬ ከሆነ ልጅ ደግሞ የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ውስጥ እንዲሰራ ይጠበቃል፤ ልጆች የአባትን መሬት ባይካፈሉ ቆንጆ ነው፤ ግብርናችን የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ያስፈልገዋል፡፡

  • እስከ መቼ ድረስ ቲማቲሙን ወደውጪ ልከን የቲማቲም ድልህ ከውጪ እናስገባለን?
  • እስከመቼ ድረስ ጥሬ ቡና ልከን የተፈጨ ቡና ከውጪ እናስገባለን?
  • እስከመቼ ድረስ የቅባት እህሎችን ወደውጪ ልከን የዘይት ምርት ከውጪ እናስገባለን?
  • እስከ መቼ ድረስ ቆዳና ሌጦ ወደውጪ ልከን የቆዳ ጫማና ሌዘር ልብሶችን በውድ ዋጋ ከውጪ እናስገባለን?
  • ሀገራችን እኮ የጣውላ ምርት ውጤቶችንም ጭምር ከውጪ እያስገባቸው ነው፤ ግን እስከ መቼ ነው ጠረጴዛና ወንበር ከውጪ የምናስገባው?

 

ሀገራችን እድገት ካስፈለጋት የእድገትን መስመር መከተል ግድ ይለዋል፡፡ ይህንን ሳናደርግ በዱሮ በሬ እያረስን ችግር አፍንጫችን ስር ሲደርስ በአምላካችንና በተፈርሮ ብናሳብብ ትርጉም የለውም፤ ሀገራችን በተፈጥሮ ሀብት የታደለች ናት፤ ነገር ግን ሀብታችንን አባክነናል፤ ቢሆንም ጊዜ ስላለን ቶሎ መባነን አለብን፡፡ ራቅ አድርገን ማሰብ እንጂ በየመንገዱ ቡና እያቀረርን የዘር ሀረጋችንን መቁጠር የትም የሚያደርሰን አይመስለኝም፣ እስቲ አስቡት፣ ምድራችን የአንድ ትውልድ እድሜ ያላት ይመስል በ20ኛው ክፍለዘመን የዘር ሀረጋችንን ትክክለኛ መነሻ ለማወቅ መላምት ስንደረድር፤ እጅግ የሚገርም ነገር ነው፡፡ ማንም የሰው ልጅ መነሻው የትም ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ክቡርነቱንና እጅግ ትልቅ የማስተዋል ፀጋ እንደተሰጠው ማመን ካልቻለ ችግር ነው፤ ይልቁንም የአእምሮአችንን ፀጋ እንጠቀምበት፤ እስከመቼ ድረስ ነው የቴክኖሎጂ ተቀባይ ሆነን የምንኖረው፤ እልህ ሊይዘን ይገባል፤ አውሮፕላን፣ መርከብ፣ መኪና፣ ኢነተርኔት፣ ባቡር፣ መድሀኒት ይህን ሁሉ መስራት የምንችልበትን አስተሳሰብና የኑሮ ዘይቤ ለልጆቻችን ማውረስ ሲገባን ጥላቻንና ድህነትን እንዳናወርሳቸው ዛሬ መጠንቀቅ አለብን፡፡ የተሰጠንን የአእምሮ ጸጋ መጠቀም አለብን፡፡

 

ለምሳሌ ላንጋኖ ሀይቅ ዙሪያ ብዙ መሬት አለ፤ ቢሆንም አብዛኛው መሬት በበጋ ወራት ባዶውን ነው ያለው፤ ለመስኖ እርሻ መሆን ይችላል፤ ልፎ አልፎ በመስኖ የሚለማውም መሬት ተቆራርጦ፤ ለትራክተር፤ ለትልልቅ ግብርና በማይመች ሁኔታ ተሸንሽኖ ይገኛል፡፡  መፍትሄው ለምሳሌ የገበሬዎች የህብረት ስራ ነው፡፡ የዴንማርክን ግብርና እጅግ ከፍተኛ ደረጃ ያደረሰው የገበሬዎች የህብረት ስራ ድርጅት ነው፡፡ በተለይ የዴንማርክ ገበሬዎች በወተት ምርት በኩል በህብረት ስራ በመታገዝ የደረሱበት ደረጃ ለአለማች የግብርና እድገት እንደምሳሌ ይጠቀሳል፡፡ የገበሬዎች የህብረት ስራ የሚያስፈልግበት ምክንያት በአብዛኛው የአለማችን ሀገራት በገበያ መር ኢኮኖሚ እየተመራን ነው፤ ስለሆነም ገበሬዎቻችን ተወዳዳሪነታቸውን ከፍ ለማድረግ በህብረት መስራት አለባቸው፡፡ ምክንያቱም በገበያ መር ኢኮኖሚ ውስጥ ተሽሎ መገኘትና ተወዳዳሪ መሆን ለስኬት እጅግ መሰረታዊ ስለሆነ፤ ገበሬዎች የህበረት ስራ ድርጅት ሲኖራቸው የባለሙያ እገዛ ለማግኘት እንዲሁም የምርት ግብአትን በአነስተኛ ዋጋ ለመግዛትና ምርታቸውን በተሻለ ዋጋ ለመሸጥ ጠንከር ያለ አቅም ይኖራቸዋል፡፡በተለይ በየጊዜው እየተሸነሸነ የሚሄደውን የመሬት ይዞታ ችግር ለመፍታት ገበሬዎቹ በህብረት ስራ መደራጀት የግድ ይላቸዋል፡፡ መንግስትና ባለሙያዎች እንዲሁም የግብርና ልማት ባለሙያዎች ለገበሬዎች የህብረት ስራ ትኩረት ሰጥተው መስራት አለባቸው፡፡ ታዲያ የገበሬዎቹን የህብረት ስራ ከሙስናና ከፖለቲካ ጉዳዮች በተቻለ መጠን ነፃ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በህብረት የተደራጁ ገበሬዎች መንግስት ላይ ጫና ሊያደርጉ ይችሉ ይሆናል፤ ቢሆንም ሊነሱ የሚችሉት ጥያቄዎች የመሰረተ ልማትና የልማት ጥያቄዎች ናቸው የሚሆኑት፡፡

 

ከዚህ ጋር ተያይዞ የገበሬዎቻችን አሰፋፈር ሁኔታም አሁን ባለው በዘፈቀደ ሳይሆን እንደ ውሀ፣ መብራትና የተለያዩ መሰረታዊ አገልግሎቶችን በቀላሉ ሊያገኙ በሚችሉበት መንገድ መሆን ያለበት ይመስለኛል፡፡ በደርግ መንግስት ዘመን ተጀምሮ የወደቀው የገበሬዎች ሰፈራ ሀሳብ በተሻሻለ ሁኔታ ሊሰራበት የሚያስፈልግ ይመስለኛል፡፡ መቼም ሀገራችን የህዳሴ ግድብን ጨምሮ ብዙ የኤሌክትሪክ ሀይል ፕሮጀክቶች እያሰበች መሆኑ ግልፅ ነው፤ ነገር ግን አሁን ያለው የገበሬዎች አሰፋፈር ለኤሌክትሪክ መስመርና ለውሀ መስመር ዝርጋታ አመቺ አይደለም፡፡ ነገር ገን የሀገራችን ገበሬዎች ምርታቸውን አምርተው ለኛ ለከተሜዎቹ እየመገቡ፣ እነሱም ከኛ የዘመናዊ ምርች መጠቀም አለባቸው፤ ለምሳሌ ሁሉማ የሀገራችን ገበሬ ቤቱ መብራት መግባትና ውሃም ቤቱ ድረስ በድረስ አለበት፤ እስከ መቼ ድረስ ነው የገጠሩ እናቶች ውሀ ከሩቅ ቀደተው ወደቤት የሚሸከሙት?

 

ስለሆነም በዘለቄታ የገበሬዎች መንደሮችና የህብረት ስራ ድርጅቶቻቸውን ማጠናከር የግድ ይለዋል፡፡ ይህችን የግብርናችን ጉዳይ በሌሎች ክፍሎች በስፋት እመለስበታለሁ፡፡

 

 

 

 

ሱስና ወጣቱ ህይላችን

 

በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ዘንድ ሱስና ሱሰኝነት ብዙ ሊሰራበት የሚገባ ችግራችን ነው፤ ለምሳሌ የጫት ሱስ ተጠቂነት በዋናነት ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሚጀምር ይመስለኛል፡፡ ከሀረር ወይም ከወንዶገነትና ከአዲስ አበባ የሚመጡ ተማሪዎች ስለጫትና ከጫት ጋር ተያያዥ ስለሆኑ ጉዳዮች ያላቸው ግንዛቤ ተመሳሳይ አይመስለኝም፤ የሀረሩ ወይም የወንዶገነቱ ተማሪ ጫት መቃምን ዩኒቨርሲቲ ከመምጣቱ በፊትም ያውቅ ይሆናል፤ እንዲሁም ጫት ቅሞ ባያውቅም በአከባቢው ጫት ስለሚመረትና በማህበረሰቡ ውስጥ በሰፊው ስለሚቃም  ስለጫት ያላቸው ግንዛቤ ላቅ ያለ ነው፤ ነገር ግን ከአዲስ አበባና ከአንዳንድ የሀገራችን ከተሞች የሚመጡና የገንዘብ ችግር የሌለባቸው በተለምዶ የቤት ልጅ የሚባሉት አይነት ተማሪዎች በተለይ እስከ 12ኛ ክፍል ሲማሩ በከፍተኛ የቤተሰብ ቁጥጥር ስር የነበሩት ዩኒቨርሲቲ ሲገቡ ቀኑን ሙሉ ታስሮ ከእስር እንደተለቀቀ ውሻ ዘለው ሱስ ውስጥ በመግባት የዩኒቨርሲቲውን ነፃነት አላስፈላጊ ሱስ ውስጥ ገብተው አላማቸውን ሊስቱ እንደሚችል ብዙ ተጨባጭ መረጃዎች አሉ፡፡

 

ጫት መቃም ብቻ ሳይሆን ከጫት በኋላ ወደመጠጥና ሌሎች ከባድ ሱሶች ሊሄዱ ይችላሉ፡፡ ስለሆነም ተማሪዎች ዩኒቨርሲቲ ከመግባታቸው በፊት ስለዩኒቨርሲቲ ህይወትና አብሮ ስለሚመጡት ፈተናዎች እንዲሁም የኑሮ ዘዴዎች መረጃ ማግኘት አለባቸው፡፡ከራሴ የህይወት ተሞክሮ ለማካፈል ያህል ከጥናት ጋር ተያይዞ ጫት ቅሜ አውቃለሁ፡፡ ጫት የቃመ ሁሉ ግን ፈተና ተፈትኖ ጥሩ ውጤት ያመጣል ማለት አይደለም፡፡ ጫትን በተመለከተ ቀጥሎ የተዘረዘሩትን ነጥቦች ልብ ማለት ያሰፈልጋል፡፡

1ኛ፡ ከተቻለ ለጥናት ተብሎ ጫትም ሆነ ቡና እንዲሁም ሌሎች አነቃቂ ነገሮችን አለመውሰድ

2ኛ፡ አነቃቂ ነገሮች መውሰድ የግድ ከሆነ ደግሞ ለምሳሌ ጫትን በትንሹ መውሰድ፣ ትንሽ ሲባል ምን ማለት ነው፣ ለምሳሌ ከግማሽ ሰአት በላይ ጫት ለመቃም አለመቀመጥ

3ኛ፡ ጥናት ወይም ለየት ያለ ስራ ከሌለ ጊዜ ለማሳለፍ ተብሎ ብቻ ጫት አለመቃም

4ኛ፡ ጫት አብረው የሚቅሙትን ሰው ሁኔታ ማወቅ፣ ምክንያቱም አንዳንዱ ተማሪ ከባድ ሱስ ውስጥ ስለሚሆን አዲስ ጀማሪውን ተማሪ ከአላማው ሊያስተው ይችላል፡፡

5ኛ፡ የዩኒቨርሲቲ ትምህርት ብዙ አነቃቂ ነገሮችን በመውሰድ ጥሩ ውጤት የሚያመጡበት ሳይሆን የተለያዩ መፅሀፍን በጥልቀት በማንበብና ሁሉንም የትምህርት ክፍለ ጊዜ በመገኘት ሁሉንም የሚሰጡ ስራዎች በጊዜው በመስራት የሚወጡት እንጂ ከክፍል በመቅረት፣ ጭፈራ ቤት በማምሸት፣ ብዙ ጫት በመቃም ወዘተ የሚወጡት ትምህርት አይደለም፡፡ ብዙ ተማሪዎች ጊዜያቸውን አላግባብ በማባከን ፈተና ሲደርስ ብቻ ቁጭ ብሎ በማደር ጥሩ ውጤት ማምጣት የሚመጡ ይመስላቸዋል፡፡ ይህ ትክክል አይደለም፡፡

ልማትና የልማት ተነሺዎች

 

ለሀገራችን ዘላቂ ልማት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ባሉትና በገበሬዎች ህይወት ላይ የሚደረገው ልዩነት ብዙ ለውጥ ያመጣል፤ ቢሆንም ለመንግስትና የግል ባለሀብቶች ኢንቨስትመንት ሲባል ብዙ የሀገራችን ገበሬዎች ካሳ እየተከፈላቸው ከመሬት እንደሚፈናቀሉና ከዚህም ጋር ተያይዞ ብዙ ክርክሮች በማህበራዊ ድህረገፆች እያነበብን ነው፤ ስለሆነም መፍትሄውንና የሌሎች ሀገራት ልምድስ ምን ይመስላል የሚለውን ማየት ጠቃሚ ይመስለኛል፡፡

 

ታይላንድ ሀገር ለትምህርታዊ ጉዞ ከዴንማርክ ሄደን በነበረበት ወቅት ያስተዋልኩትን እንደ ልምድ ላካፍል እወዳለሁ፡፡ የጉዞአችን ዋና አላማ የነበረው ማህበረሰብን መሰረት ያደረግ የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምና እንክብካቤን /community based natural resources management/ በተመለከተ ያሉትን ተሞክሮዎችና ተግዳሮቶች ለማጥናት ነበረ፡፡

 

ለጥናቱ ሰሜን ታይላንድ ቻንግ ማይ ተብላ በምትጠራ ከተማ አካባቢ የባን ፓን ኢካ ልዩ ቦታ የተመረጠ ሲሆን፣ ለሪፖርታችን የሚሆን መረጃ ለመሰብሰብ በአከባው በሚገኘው የደን ሀብት ውስጥ ገብተን የጎበኘን ሲሆን ብዙ ገበሬዎችንም ቃለመጠይቅ አድርገን ነበረ፤ እንዲሁም በቻንግ ማይ ዩኒቨርሲቲም ያሉ ምሁራንን አነጋግረን ነበረ፡፡ ከጉብኝታችን ከተወሰኑ አመታት በፊት ታይላንድ ሀገር ማንም የዉጪ ዜጋ መሬት መግዛት ይችል ነበረ፤ ገበሬውም ሙሉ የመሬት ባለቤት ስለሆነ መሬቱን መሸጥና መለወጥ ይችላል፤ ነገር ግን ብዙ ገበሬዎች መሬታቸውን ሸጠው ለችግር ነው የተዳረጉት፡፡ ከጥናቱ እንደተረዳነው በሰሜን ታይላንድ ባን ፓን ኢካ በሚባለው አካባቢ የነበሩ ብዙ ገበሬዎች መሬታቸውን ለሀገር ውስጥና ለውጪ ሀገር ባለሀብት ሸጠው ወደከተማ የገቡ ሲሆን ብዙዎቹም ገበሬዎች መሬታቸውን ሸጠው አምስት አመት ሳይሞላቸው መሬት ሸጠው ያገኙትን ገንዘብ ጨርሰውት፣ በቻንግ ማይ ከተማ ውስጥ ለልመና መዳረጋቸውን በቃለመጠይቁ ወቅት ተነግሮናል፡፡

 

ወደሀገራችን ስንመለስ ከመሬታቸው የተፈናቀሉት ገበሬዎች ካሳ ተሰጥቶአቸው የተነሱ ቢሆንም ያገኙትን ገንዘብ በትክክል ለዘላቂ ህይወታቸው መጠቀማቸው አጠያያቂ ነው፤ ስለሆነም ይህንን ችግር ለመቅረፍ መደረግ የሚገባውን የራሴን አስተያየት ልስጥና አንባቢያንም ብትመካከሩበት ለጋራ ሀገራችን እድገትና ለገበሬዎቻችን ከድህነት መውጣት የሚጠቅም ይመስለኛል፡፡

 

/እዚህ ጋር በቅርቡ አዲስ አስፋልት መንገድ ሊሰራ ታቅዶ ከመሬቱ ለሚነሳው ለአንድ ገበሬ ሶስት መቶ ሺ ብር ካሳ ይሰጠዋል፤ ገበሬው ሶስት መቶ ሺ ብሩን ሙሉ በመጠጥና ለሌሎች ብድር ሰጥቶ ጨርሶት ከልጆቹ ጋር ከባድ ፀብ ውስጥ እንደገቡ ሰማሁ፤ ለአንድ አርሶ አደር አንድ ሚሊየን ብርም ብንሰጠው ገንዘቡን እንዴት እንደሚጠቀምበት ስለማያውቅ ተመልሶ ደሀ ቢሆን ሊገርመን አይገባም፡፡ ስለሆነም መንግስት ለወደፊቱ ገበሬዎችን ለልማት ከእርሻቸው ላይ ሲያስነሳቸው የካሳ ገንዘብን ሙሉ በሙሉ ከመስጠት በዘላቂነት ሊጠቀሙበት የሚችሉትን ነገር ቢደረግላቸው ቆንጆ ነው፤ ለምሳሌ ቅያሬ ቦታ ለገበሬዎቹ ሲሰጥ ቤትም አብሮ ሰርቶ መስጠት፤ ታዲያ ቤቱን ለተወሰነ ጊዜ ድረስ መሸጥና መለወጥ እንዳይቻል ማድረግ ያስፈልጋል/

 

ለምሳሌ በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉትን ገበሬዎች እንደምሳሌ ብንወስድ በገበሬዎች ማሳ ላይ የተሰሩ ብዙ የጋራ መኖሪያ ኮንደሚኒየም ቤቶች አሉ፤ ግንባታዎቹ ከመጀመራቸው በፊት መሬቱን ሲጠቀሙት የነበሩት ገበሬዎች ካሳ ተከፍሎዋቸው ከመሬታቸው እንደተፈናቀሉ አምናለሁ፤ ነገር ግን የጋራ መኖሪያ ቤቶቹ ተሰርተው ለህዝብ ሲታደሉ ገበሬዎቹ የእድሉ ተጠቃሚ መሆን ነበረባቸው፡፡

 

በገበሬው መሬት ላይ ከሚገነቡት ግንባታዎች ገበሬዎቹ ከተሰጣቸው ካሳ በተጨማሪ የመጀመሪያ ተጠቃሚ መሆን ነበረባቸው ባይ ነኝ፤ ለምሳሌ አንድ ባለ 5 ፎቅ ኮንደሚኒየም ቢሰራ ከተሰሩት ክፍሎች የመጀመሪያውና ከወደመሬት ያለው ለመሬቱ ባለቤት ገበሬ ቢሰጥ ገበሬዎቹ አንደኛ ለልጆቻቸው የተሻለ ቤት አገኙ ማለት ነው፤ ሁለተኛ ቤቶቹንም እያከራዩ ብዙ ገቢ ማግኘት ይችላሉ፡፡ ካስፈለገ ቤቱ በፍጹም መሸጥና መለወጥ እንዳይቻል ማድረግም ይቻላል፤  ያንን አይነት አሰራር ብንከተል ደግሞ የተፈናቀሉት ገበሬዎች ህይወት ምን ደራጃ ላይ እንዳለ፣ መሬቱ ከመወሰዱ በፊትና ከተወሰደ በኋላ ገበሬዎቹ ያላቸውን የኑሮ ልዩነት በቀላሉ ማሳየት ይቻላል፡፡

 

የግል ባለሀብቶችም ቢሆኑ የገበሬዎችን መሬት ለኢንቨስትመንት ሲወስዱ በመሬቱ ላይ የነበሩ ገበሬዎችን ህይወት በዘላቂነት የሚለውጡበትን መንገድ እንዲያቅዱ መሬቱን ከመውሰዳቸው በፊት አስገዳጅ አሰራር ቢኖር ተፈናቃይ ገበሬዎቹ ከሚከፈቱት ኢንቨስትመንቶች ቀጥተኛ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ይቻላል፡፡

 

ሌላው አማራጭ ደግሞ የሀገራችን ገበሬዎች በህብረት ስራ ተደራጅተው በተሻለ የማምረት አቅም ምርታቸውን ለግብርና ምርት ማቀነባባሪያ ፋብርኪካዎች እንዲያቀርቡ ቢደረግ በቀላሉ ህይወታቸው የሚለወጥ ይመስለኛል፡፡

 

በደቡብ ዴንማርክ ያጋጠመኝን የገበሬዎች ህብረት ስራ እንደምሳሌ መጥቀስ እችላለሁ፤ በደቡብ ዴንማርክ ስንዴ የሚያመርቱ ገበሬዎች የስንዴ አምራች ገበሬዎች ዩኒየን አላቸው፤ ገበሬው ስንዴውን አምርቶ በቀጥታ ወስዶ ለዩኒየኑ ያስረክብና ስንት ኩንታል እንደሰጠ ይመዘገብለታል፤ ሁሉም ገበሬዎች ምርታቸውን አንድ ቦታ በአንድ ጎተራ ካጠራቀሙ በኋላ የገበሬዎቹ ዩኒየን የስንዴ ምርት ዋጋ ቆንጆ በሆነ ጊዜ ምርቱን ሽጦ ለአባላቱ ባስገቡት ኩንታል መጠን ገንዘቡን ወደባንካቸው ገቢ ያደርጋል፡፡

 

ስለሆነም የስንዴ አምራቾቹ ለየግል የስንዴ ምርታቸውን አያከማቹም፤ ለየግልም አይሸጡም፤ እንዲሁም ሁሉም ገበሬ ስለስንዴ ገበያ እኩል መረጃ ስለማይኖረው፣ የገበሬዎቹ ዩኒየን በባለሙያዎች እየታገዘ የስንዴ ምርታቸውን በቆንጆ ዋጋ ሸጦ ለገበሬዎች ያስረክባል፡፡ በተጨማሪም እዛው ደቡብ ዴንማርክ የስኳር ፋብሪካ ነበረ፤ በፋብሪካው ዙሪያ የነበሩት ገበሬዎች በሙሉ የስኳር ድንች ምርትም ያመርታሉ፤ ምርታቸውንም በቀጥታ ለፋብሪካው ያስረክባሉ፤ ፋብሪካው ለገበሬዎቹ ዋስትና ይሰጣል፤ ምርታቸው በማሳ ላይ እያለ ቢበላሽ ገበሬዎቹ ገቢያቸው አይቀነስም፤ እዲሁም የስኳር ድንችን አስተራረስና የምርት ግብአት ፋብሪካው ያቀርባል፤ የምርት ዋጋንም በተመለከተ የገሬዎች ዩኒየን ወይም ህብረት ስራ ድርጅት ከፋብሪካው ጋር በመመካከር ትክክለኛውን ዋጋ ያወጣሉ፤ ሌላው ቆንጆ አሰራር የስኳር ፋብርካው የሚጠቀመው ሰራተኞች በዋናነት የአከባቢው ገበሬዎች ልጆችን ብቻ ነው፤ ፋብሪካው ተማሪዎችን ወደዩኒቨርሲቲም እየላከ ስለፋብሪካው አሰራር ስልጠና እንዲወስዱ ያደርጋል፡፡

 

በዚህ መልኩ የአከባቢው ህዝብ ከአከባቢው ልማት ቀጥተኛ ተጠቃሚ እንዲሆን የዴንማርክን ገበሬዎች የህብረት ስራና የገበሬዎችንና የግብርና ምርት ማቀነባበባሪያ ፋብሪካዎችን ምሳሌ መጠቀም እንችላለን፡፡  በሀገራችን ትልቁ ማነቆ የህብረት ስራ ማህበራት ሲጀመሩ ሙስና ዋናው ችግር ይሆናል፤ የደርግ ጊዜ የህብረት ስራ ድርጅቶች/አምራቾች/ ታሪክ ጥሩ ምሳሌ ሊሆን ይችላል፤ ስለሆነም መጀመሪያ የህግ የበላይነትና ግለሰቦች የህዝብን ንብረት ሲዘርፉ ለፍርድ የሚቀርቡበት መሰረታዊ አሰራር መጠናከር አለበት፡፡ በሀገራችን ያሉት የገበሬዎች ዩኒየን አልፎ አልፎ ገበሬ ያልሆኑ ሀብታሞች ብቻ አባል የሚሆኑበት ድርጅትም እንደሆነ ሲነገር እሰማለሁ፡፡ ምንም ሆነ ምን ግን ሁሉም ደሀ ገበሬ በአከባቢው አባል የሚሆንበት የገብሬዎች የህብረት ስራ ዩኒየን ያስፈልጋል፡፡

 

ከታሪካችን እንደምንረዳው ለድህነታችን ዋናው መሰረት ግለሰቦች ከህዝብና ከመንግስት ሀብት ዘርፈው በቀላሉ መታለፋቸው፣ ሌብነት እንዲስፋፋ ከማድረጉም በላይ የህብረት ስራ ድርጅቶችን ውጤታማ እንዳይሆኑ የተደረጉበት አሰራር ብዙ ምሳሌዎች ይጠቀሳሉ፡፡

ህልም ያለው አመራር ወይም መሪ ያሚያስፈልገው ለዚህ ነው፤ በዚህ አጋጣሚ የቀድሞ የአዋሳ ግብርና ኮሌጅ፣ ቀጥሎም የደቡብ ዩኒቨርሲቲ፣ የአሁኑ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞ ዲን የነበሩት (ነብሳቸው ይማርና) ዶክተር ገረመው ሀይሌ ዛሬ የሀዋሳ ዚንዱስትሪ ፓርክ አጠገብ የሚገኘውን የዩኒቨርሲቲውን ዋና ግቢ በደርግ ዘመን ለዩኒቨርሲቲው ብለው አቅደው በሰፊው እንደተረከቡ ቀድሞ ከዶክተር ገረመው ጋር የነበሩ መምህራ ይነግሩናል፡፡ ዶክተር ገረመው ሀይሌ ሌሎችም ደስ ደስ የሚሉ ሀገራዊ የሆነ አላማ የነበራቸው ምሁር እንደሆኑ ሰማሁ፡፡ በአንድ ወቅት የኮሌጁ ተማሪዎች በደርግ መንግስት ታስረው እስርቤት ገብተው የኮሌጁ መምህራን እስርቤት ድረስ ሄደው እያስተማሩ ተማሪዎቹ ከእስር ሲለቀቁ ምንም ትምህርት ሳያመልጣቸው በሰላም መመረቃቸውን ስሰማ እጅግ ደስ አለኝ፡ ሁሉ ባለበት ስራና ሀላፊነት ደረጃ ህልም ማለም ማለት በዚህ ምሳሌ ነው፤ ከሶስትና ከአራት አመት አልፎ ከ30 እና ከ40 ቸመት በኋላ ሊመጣ የሚችለውን አለም አስቦ ለሚመጣው ትውልድ መረሰጥ መጣል ያስፈልጋል፡፡

በየዩኒቨርሲቲዎቻችን የዶክተር ገረመው ሀይሌ አይነት አኩሪ ሀገራዊ ስራ የሰሩ ብዙ እንደሚኖሩ ይታመናል፡፡ ስለሆነም ደራሲዎቻችን በሚፅፉት መጽኀፍት እንደነኛ አይነት የሀገር ኩራት የሆኑ ዜገችን ስል ለትውልድ ቢያስታውሱ ቆንጆ ነው፡፡ እኔ ብዙ መጽሀፍ ብጽፍ የመቂዶኒያ ማእከል መስራች የሆነውን ስሙን በሁሉ ውስጥ መጥቀስ እወዳለሁ፤ ምክንያቱም ቢኒያም ለብዙ የተረሱ የአእምሮ ህሙማን የሀገራችንን ዜጎች ከለላ መሆን የቻለ የሀገራችን ደሀ ህዝቦች ባለውለታ ነው፤ እግዚአብሄር እድሜውን ያርዝምልን፡፡

የፆታ እኩልነት

 

አሁንም ከዩኒቨርሲቲዎቻችን በብዛት የሚባረሩት ሴቶች ናቸው፤ ባደጉት ሀገራት ደግሞ ከወንዶች ይልቅ ትልቁን ውጤት የሚያመጡት ሴቶች ናቸው፤ ለምሳሌ ዴንማርክ ሀገር እ. አ. አ በ2011 ዓ.ም በተደረገ ሀገር አቀፍ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና የሂሳብ ትምህርት ውጤት የሴት ተማሪዎች አማካይ ውጤት ከወንዶቹ አማካይ ውጤት በአስር ይበልጥ ነበረ፤ በሀገራችን ደግሞ ስንመለከት የሴት ተማሪዎች ውጤት ከወንዶቹ እጅግ አነስተኛ ሆኖ እናገኛለን፤ ለምሳሌ በቅርቡ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በአንድ ፕሮግራም ተማሪዎች ላይ በተደረገ ጥናት፣ የሴት ተማሪዎች ውጤት ከወንዶች ጋር ሲነፃፀር እጅግ አነስተኛ መሆኑን አረጋግጠናል፡፡ ምክንያ ምንድን ነው? ምንስ መደረግ አለበት?

 

በእኔ አስተያየት መፍትሄው መጀመሪያ ከእናቶች ይጀምራል፡፡ አልፎ አልፎ እናቶች ወንዶችን ‹ሴታሴት› ሲሳደቡ እንሰማለን፤ ወይም ‹እስዋ ወንዳወንድ ናት› ብለው ሴቶችን ሲያሞግሱ እንሰማለን፤ ይህንን አይነቱ ስር የሰደደ የማህበረሰባችን አመለካከት በወንድ ልጆችና በሴት ልጆች መካከል ተመሳሳይ አመለካከት አለመኖሩን ያሳየናል፤ አንዲት እናት ወንድ ልጅ ወለደችና ሴት ልጅ ወለደች በሚለው መካከል ማህበረሰቡ በማበላለጥ የሚሰጠው አስተያየት ዛሬም ድረስ አልተለወጠም፡፡ ለወንዶችና ለሴቶች የተሰጡት ጫወታዎችና ስራዎች ሁሉ በተዘዋዋሪ የሴት ልጆችን የትምህርት ስኬት የሚጎዱ ናቸው፤ እንዲሁም በገጠርና አልፎ አልፎ በከተማ የሚኖሩት ሴት ልጆች በቤት ውስጥ የስራ ጫና ስላለባቸው በትምህርታቸው ውጤታማ የመሆን እድላቸው እየቀነሰ ይሄዳል፡፡ ደስ የሚለው ነገር በአዳዲሶቹ ልጆቻችን ይህ ታሪክ እየተቀየረ ይመስለኛል፡፡ የኔ ልጅ የምትማርበት ክፍል ውስጥ ደረጃ የሚይዙት ሴቶች ናቸው፡፡ ለሁሉም ማህበረሰባችን የፆታ እኩልነትን ለማረጋገጥ ብዙ መስራት አለበት፡፡

 

የማህበረሰባዊ ሀብት

 

በሀገራችን ድርቅ ሆነ፤ እህል ደረቀ፤ እንሰሳት ሞቱ፤ ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እግዚአብሄር ዘረጋች፤ መንግስታችንም እጆቹን ወደምእራቡ ሀገራት ዘረጋ፤ ሀብት በብዙ መንገድ ሊለካ ይችላል የሚል ፅሁፍ በቅርብ ጊዜ አንብቤ ነበረ፤ የሀብት መለኪያውም በተለመደው የቁሳቁስና የገንዘብ ብዛት ሳይሆን የማህበረሰብ ሀብት ነው፤ ከተጠቀሰው ምሳሌ ለሀገራችን ወጣት ለማስረዳት እኔ የመጀመሪያ ዲግሪ መመረቂያ ምርምር ስሰራ ሀዋሳ ከተማ ዙሪያ ገጠር ውስጥ ነበር የሰራሁት፤ ለምርምሩ ስራ ተሰጠን ገንዘብ 200 ብር ነበረ፤ ገንዘቡ ከትራንስፖርት ተርፎ ለገበሬዎቹ ክፍያ ለመክፈል አይበቃም ነበረ፤ መረጃ ለመሰብሰብ በቦታው እንደደረስን  የመጣንበትን አላማ ለገበሬዎቹ አስረዳናቸው፤ መቼውንም የማይረሳኝ ጉዳይ ገበሬዎች ሙሉ በሙሉ በንፁኅነት ለስራችን የምንፈልገውን መረጃ ሰጡን፤ ለእንግድነታችንም ታላቅ ክብር ተሰጠን፤ ቢሆንም ገበሬዎቹ በድህነት ውስጥ ነው የሚኖሩት፤ በድህነት ውስጥ ቢኖሩም ህይወታቸው ደስታ ነው፤ ለእንግዶቻቸው ደስ የሚል ፈገግታ ነው የሚሳዩት፤ ሰብአዊነት በህይወታቸው ውስጥ በደንብ እንዳለ መረዳት ይቻላል፤ እንግዲህ ማህበረሰባዊ ሀብት የሚባለው ይህ ነው፡፡ በ21ኛ ክፍለ ዘመን ገንዘብ ና የገንዘብ ፍቅር እጅግ እየጨመረ ስለመጣ ሰዎች ማህበረሰባዊ ሀብታቸውን እያጡ መጥተዋል፤ ለምሳሌ ጎሮቤትነት፤ ወላጅነት፤ ቤተሰብ፤ ወንድማማችነት ወዘተ ቦታቸው ዝቅ እያለ ነው፡፡ ወንድም ወንድሙን ለገንዘብ ብሎ የሚጠላበት ጊዜ ላይ ደርሰናል፤ ህግም ለቁሳቁስ ሀብት ቅድሚ በመስጠት ለማህበረሰባዊ ሀብት ቦታ አለመስጠትን የሚያሳይ ነውና ያለንን ማህበረሰባዊ ሀብት ዘመኑ ካመጣው ከመጠን ያለፈ የቁሳቁስ ፍላጎት አደጋ መጠበቅ ያለብን ይመስለኛል፡፡ ምክንቱም የኛ ማህበረሰብ  በተለይ በገጠሪቱ የሀገራችን ክፍል የሚኖረው ትልቁ ሀብቱ ማህበረሰባዊ አንድነቱ ነው፤ ማህበረሰባዊ አንድነታችንን ቆንጆ ገፅታውን ጠብቀን በሚጎድልበት እጠናከርን መሄድ አለብን፤ ለምሳሌ በገጠር የሚኖሩት የሀገራችን ህዝቦች ለሰርግና ለለቅሶ አመቱን ሙሉ ያጠራቀሙትን ገንዘብ በሁለት ሳምንት ጨርሰው ለችግር የሚጋለጡበት አጋጣሚ አለ፤ ይህ ደግሞ ጎጂ ልምድ ነው፤ ነገር ግን ለችግር ጊዜ የሚተባበሩት ነገር ቆንጆ ስለሆነ መበረታታት አለበት፡፡

 

 

ውይይቶቻችን

ወጣቶቹ እንደጀልባ፣ እንደአውሮፕላንና እንደመኪና ሊያገለግል ስለሚችል የቴክኖሎጂ ፈጠራ፤ HIV ለካንሰር ለስኳር በሽታና ለኢቦላ ወዘተ ህመሞች መፍትሄ የሚሆኑ የሳይንስ ግኝቶች ፈጠራ፤ሰዎችን የበለጠ ሊያቀራርቡ የሚችሉ የኮምፒውተር ግኝቶች፤አለም አቀፍ ስለሆኑ ትልልቅ የንግድ ሀሳቦች፤ የፀሃይ ሀይልን በመጠቀም የሚሽከረከሩ መኪናዎች ወዘተ ይወያያሉ፡፡

በዚኛው አለም ያሉ ወጣቶች ደግሞ የትኛው ብሄር ከሁሉ ይበልጣል? የትኛው ሀይማኖት ነው ትክክል? የትኞቹ ልብሶችና ጫማዎች ያምራሉ? የቶቹ ስሞች ናቸው ደስ የሚሉት? በሰፈራቸው ስላሉ ኮረዳዎች የፍቅር ህይወት…ወዘተ ይወያያሉ፡፡ የፌስቡክ ላይ ውይይቶችንን ልብ ብሎ የተከታተለ ሰው ይህንን ሊያረጋግጥልኝ ይችላል፡፡ ይህ ግን መቀጠል የለበትም….

የአስተሳሰብ ድህነት ወይስ ሰይጣን?

 

ተፈጥሮ የተቻላትን ያህል እጆችዋን ሞላ አድርጋ የተፈጥሮ ሃብቶችዋን ለግሳናለች፡፡ ምንም እንኳን ያሉን የተፈጥሮሀብቶች ህዝቦቻችንን ከድህነት ለማላቀቅ የሚስችሉና በአለም ገበያ እጅግ ተፈለጊ የሆኑ ናቸው ማለት ባይቻልም የሀገራችን ህዝቦችን ከረሃብ ለመታደግ የሚበቁ መሆናቸው አጠያያቂ አይመስለኝም፡፡ ቢሆንም የተፈጥሮ ሃብቶቻችን ለኛ ጠቃሚ መሆን በሚችሉበት መልኩ አገልግሎት እንዲሰጡ አድርገናቸዋል ማለት አይቻልም፡፡ ለምሳሌ ወንዞቻችንን ብንወስድ ተገድበው ወደመስኖና ሀይል ምንጭ ካለትቀየሩ ጠቃሚ ናቸው ማለት ያስቸግራል፡፡   ስለችግሮቻችን ስንወያይ ያሉንን በጎ ጎኖች ዘንግተን ወይም ሆን ብለን ጨለምተኛ መንገድን መርጠን እንዳልሆነ መግባባት አለብን፡፡ ሀገራችንና ዜጎችዋ ችግር ፈጣሪዎች ብቻ ሳንሆን ሊነገርልን የሚገቡ ብዙ በጎ ጎኖች እንዳሉን መታወቅ አለበት፡፡ ቢሆንም ደግሞ እኛ ኢትዮጵያውያን ከሌሎች ሀገራት በተለየ መልኩ በጎ ነን፡፡ ከሌሎች በተለየ መልኩ አንዳችን ለሌላው በጎ እናስባለን፤ ከሌሎች በተለየ መልኩ ታማኝ ነን፤ ከሌሎች በተለየ መልኩ ለሀይማኖታችንና ለህሊናችን ተገዢዎች ነን ብለን ብንሰብክ እስቲ ከየትኞቹ ሀገራት ተብለን መጠየቃችን አይቀርም፡፡

እኔ እስከሚገባኝ ድረስ አለም ተነፃፃሪ ናት፡፡ አንዱን የተሻለ ሌላውን ደግሞ ያነሰ ብለን ስንል ሁለቱን በማወዳደር መሆኑን መረዳት ያለብን ይመስለኛል፡፡ ስለሆነም ሀገራችንና ህዝቦችዋ ከሌሎች ሀገር ህዝቦች የተሻሉ አርቆ አሳቢ፤የተሻለ የሚተሳሰቡ፤በተሻለ ታማኝ፤ በተሻለ ስራ ወዳድ፤የተሻሉ ጀግኖች…ወዘተ ብለን ስንደረድር ተጨባጭ ማንነታችንን መመርመር ያለብን ይመስለኛል፡፡ ለምሳሌ የሀገራችን ህዝቦች ከሌሎች ህዝቦች በተሻለ ሁኔታ ይተሳሰብሉ ስንል በየመንገዱ ዳር አሳዳጊ የሌላቸው ህጻናት የሚታዘቡን ይመስለኛል፡፡ ብዙ ገንዘብ ያላቸው ባለሃብቶች እዚህ ሀገራችን እያሉ የሌላ ሀገር ሀብታሞች ወላጅ አልባ ልጆቻችንን ለማደጎ ሲወስዱልን እያየን የሀገራችን ህዝቦች ከሌሎች ሀገራት ዝህቦች በተሻለ ሁኔታ ይተዛዘናሉ ይረዳዳሉ ብንል ራስን ማታለልም ሊሆንብን ይችላል፡፡ በእርግጥ የሀገራችን ህዝቦች ተካፍለን የመብላት ልምድ አለን፡፡ ነገር ግን ተካፍለን የምንበላው ከሚመስለን ጋር ብቻ ነው፡፡

ለምሳሌ የበአላትን ጊዜ እንውሰድ፡፡ ጎሮቤት ጎሮቤቱን፣ገንዘብ ያለው አቻውን፣የተማረው የተማረውን፣ዘመድ ዘመዱን፣ሰራተኝ የስራ ባልደረባውን፣ አማኝ አማኙን…ወዘተ እንጂ ሀብታም ከደሃው ጋር ወይም በየቤተክርስቲያናቱ በር ላይ ስለፈጣሪ አምላክ ብለው ከሚለምኑት ጋር ተከፋፍሎ መብላትና አብሮ መደሰት ልምዳችን አይደለም፡፡  የምንካፈለው ወይም የምናካፍለው ውለታ ለመመለስ ወይም ዝምድናን ለማጥበቅ ወይም እርዳታ ፍለጋ እንጂ በዋናነት ለመረዳዳት አስበን አይመስለኝም፡፡ ለአንዳንዶቻችን ደግሞ የሀገራችን ህዝቦች ተካፍለው ይበላሉ ስንል ከአንድ ገበታ ብዙ ሰው የሚበላውን ባህላችንን መሰረት አድርገው ነው፡፡ በዚህም ረገድ ከአንድ ገበታ እንጂ እያንዳንዱ ሰው የየራሱ ሳህን ይዞ መብላት ስስታምነት ነው ብሎ ማሰብም ስህተት መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ አሁን አሁን እኮ በገጠርም ጭምር እንጀራ ቁርጥና በሳህኖች መስተናገድ የተለመደ እየሆነ ነው፡፡

ስለዚህ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብረው ነው የሚበሉት የሚባለው አባባል እስከምን ድረስ እውነት እንደሆነ ሁላችንም ብናስብበት ጥሩ ይመስለኛል፡፡ የማይካደው እውነታ በገጠር አከባቢ አንዱ ቤት ምግብ ካለ ጎሮቤት ለጎሮቤት የሚረዳዱት ልምድ አለ፡፡ እንዲሁም ገበሬዎች ትንንሽ ድግስ ሲኖራቸው ከመጠን በላይ በመደገስ ያመረቱትን ጨርሰው ለችግር እንደሚዳረጉ ስለሚታወቅ ያንን አይነቱ ልምድ ደግሞ ትክክል እንዳይደለ ለገበሬዎች ትምህርት እየተሰጠ ነው፡፡ ስለዚህ የኛ አብሮ መብላት ከሌላው አለም ለየት የሚያደርገን እስከምን ድረስ ነው?

ሌላው ሊታሰብበት የሚገባ ነገር እኛ ኢትዮጵያዊያን ለጋራና ለሀገራዊ ሀብታችንን ምን ያህል ታማኝ ነን? ለመሆኑ እኛ ከሌላው አለም ህዝቦች የተሻለ እምነት ሊጣልብን ይችላል? የሀገራችን የተማሩ ባለሙያዎች የህዝብን ጥቅም አስቀድመው ከውጪ ሀገራት ጉዳት ይከላከሉናል? ከግለሰብና ከጋራ ሀብት ለየትኛው የተለየ ክብር፣የተለየ ጥንቃቄ እናደርጋለን? ኢትዮጵያዊያን በቡድን የሚሰሩ ስራዎች፣ በቡድን ሰርቶ ውጤታማ በመሆኑ ረገድ ትልቅ ችግር አለባቸው ተብለን እንታማለን፡፡ ሀሜቱ ልክ ነው ወይስ አይደለም? በእግር ኳስ ሊሳካልን አልቻለም፡፡ በሩጫ ግን በአለም ታዋቂ ነን፡፡ የቡድን ስራ ችሎታችንን ዝቅተኛ ነው ብለው የሚተቹን እንደምሳሌ የሚያቀርቡት የሩጫና የእግርኳስ ውጤቶቻችንን እጅግ መራራቅ እንደምሳሌ መውሰዳቸው ልክ አይደለም? ሩጫውን እንተወውና ወደግለሰብና ወደመንግስት ድርጅቶች እንምጣ፡፡ ሆስፒታሎችን እንደምሳሌ መውሰድ እንችላለን፡፡ ወይም ዩኒቨርሲቲዎችን፡፡ እኔ ለዩኒቨርሲቲዎቹ የበለጠ ቅርበት ስላለኝ በኛ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የታዘብኩትን እንደምሳሌ ልጥቀስ፡፡ በኛ ኮሌጅ በጣም ቆንጆ ሊባል የሚችል የመምህራን መዝናኛ ክበብ አለ፡፡ የክበቡ ግንባታ ወጪ ሚሊየኞች ሊደርስ እንደሚችል እገምታለሁ፡፡ ቤቱ ከውጪ ሲታይ ደረጃውን የጠበቀና ቆንጆ ነው፡፡ ውስጥ ያለውን መስተንግዶና ያሉትን የምግብ፣የመጠጥና ሌሎች አገልግሎቶች ስንመለከት ግን እዛዉ ኮሌጁ ውጪ ወደሀይቁ ዳር በቅርብ የተጀመሩትና ስራ የሌላቸው ወጣቶች ተደራጅተው የሚሰሩባቸው መዝናኛ ቤቶች እጅግ የተሻለ አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ ስለሆነም ብዙዎቹ የኮሌጁ መምህራንና ሰራተኞች በምሳ ሰአት ከባዱን የአዋሳን ፀሀይ ተቋቁመው እነኛ ደሳሳ ጎጆዎች ድረስ ሄደው ተዝናንተው ይመለሳሉ፡፡ የመምህራን መዝናኛ ክበባችን ይሄ ሁሉ ገንዘብ ወጪ ተደርጎበት እንደዚህ አምሮ ተሰርቶ ለምን የመምህራንን ፍላጎት ሟሟላት አልቻለም? እነኚህ የግለሰብ መዝናኛ ክበቦች ለምን የበለጠ ተመራጭ ሆኑ? ለምሳሌ እኛ መዝናኛ ክበብ ውስጥ እርጎ መጠጣት አይቻልም፡፡

በኮሌጃችን የወተት ላሞች እርባታ ቢኖርም የወተት አቅርቦቱ እጅግ ውስን ስለሆነ የኮሌጁ ሰራተኞችን የወተት ፍላጎት ማሟላት አልቻለም፡፡ ስለሆነም ያን የመሰለ ቆንጆ የመምህራን መዝናኛ ክበብ ቢኖረንም እርጎ መጠጣት ስንፈልግ ወደ ግልቤቶች መሄድ ግድ ይለዋል፡፡ ነገር ግን በከተማው ውስጥ ያሉትን የእርጎ ቤቶች ብናያቸው በአንድ ወይ በሁለት ግለሰቦች በጣም ትንሽ ካፒታል መሰረት አድርገው ነው የሚንቀሳቀሱት፡፡ ሆኖም የብዙ ተጠቃሚዎችን ፍላጎት ነው የሚያስተናግዱት፡፡ በነኚህ ንግድቤቶችና በኛ የመምህራን ክበብ መካከል ያለው ዋናው ልዩነት የባለቤትነት/የየኔነት/ ጉዳይ ይመስለኛል፡፡ የግለሰቦች ድርጅቶች በቀላሉ ውጤታማ ሆነው እየተሻሻሉ ይታያሉ፡፡ ከሀገራችን ድህነት ጀርባ የመንግስትና የህዝብ/የማህበራት/ወዘተ ድርጅቶች ውድቀት ዋናው ችግር ይመስለኛል፡፡ ትምህርትቤቶቻችን፣ ሆስፒታሎቻችን፣ ዩኒቨርሲቲዎቻችን፣ ባንኮቹ፣ የመድህን ተቋማት፣ የትራንስፖርት ድርጅቶች፣ የመንገድና የመሰረተልማት ግንባታ ድርጅቶች ሁሉ እጅግ ሰፊ ሙስናና የንብረት ብክነት ምንጭ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን ንጹህ ህሊና ይዘው የሚገቡ ወጣቶችም ሙስና ተለማምደው ለገዛ ሀገራቸው እድገት እንቅፋት መሆንን ተምረው የሚወጡበት ቀጥሎም የሙስናንና የጋራ ሃላፊነት መውሰድ ያለመቻልን መጥፎ ልምድ የሚማሩበት ሆነው በመጨረሻ ደኃ የሆነ ማህበረሰብ፣ ከሁሉ በላይ ደግሞ የቁሳቁስ ድህነት ሳይሆን የአስተሳሰብ ድህነት የተንሰራፋበት ማህበረሰብ ተረክበው ይኖራሉ፡፡

እኔ እስከሚገባኝ ድረስ በማህበረሰባችን ውስጥ ያለው ዋናው ችግር፣ የጋራ ሃብታችን የማናችንም አይደለም የሚል የተሳሳተ ግንዛቤ ይመስለኛል፡፡ ይህን መሰሉ አስተሳሰብ ደግሞ በዚህ ትውልድ የተፈጠረ አዲስ ነገር ሳይሆን ከአባቶቻችን የተወረሰ የጋራ ሃላፊነት ያለመውሰድና የአስተሳሰብ ድህነት ችግር ይመስለኛል፡፡ ለችግሮቹ በብዛት የሚሰጡት ምክንያቶች የቁሳቁስ ድህነት ናቸው፡፡ ወደሃይማኖቱ ስንወስደው ደግሞ ሰይጣን አሳሳተን በሚል ችግሮቻችን ማህበረሰባችን ውስጥ እንዲቆዩ ሊሆን ችሎአል፡፡ ለምሳሌ አንድ አማኝ ግለሰብ ለሀይማኖታዊ አላማ ተብለው የተሰበሰቡ ሀብቶችን ለራሱ የግል ጥቅም ሲያውለው፤መይም ከገንዘብና ከሌሎች ጥቅማጥቅሞች ጋር ተያይዞ በግለሰቦች ጋር አለመግባባት ሲፈጠር ሴይጣን አሳሳተው/አሳሳታቸው ብለን ነው የምናልፈው፡፡ የሰይጣን ማሳሳት መሰረቱ ግን የግለሰቦች ንቃተ ህሊና አለማደግና የተሳሳተ አስተሳሰብ ይመስለኛል፡፡ ለራሳችን ጊዜያዊ ፍላጎቶች ሲባል ስንሳሳት ሰይጣን አሳሳተን ብለን ጥፋተኝነትን ሳንቀበል ሌላ አካልን ተጠያቂ አድርገን ችግሮቻችንን ስንደጋግም እንታያለን፡፡ ስለዚህ ሰይጣን አሳሳተን ብለን ከማለታችን በፊት የአስተሳሰባችንን ጤናማነት ማረጋገጥ አለብን፡፡ የሰው ልጅ ከተሰጠው ታላቅ ፀጋ አንዱ እርኩስም ይሁን የተቀደሰ አስተሳሰቦችንና መንፈሶችን መራሱ በጎ ፈቃድ ወደራሱ መሳብ መቻሉ ነው፡፡ ጤናማ አስተሳሰብ ያለው ሰው ለሰይጣናዊ  ድርጊቶችና አስተሳሰቦች ተገዢ ሊሆን አይችልም፡፡ ክፋትን የሚያስብ ሰው ለራሱም ሆነ በአከባቢው ላሉ ሰዎች የክፋት ድርጊቶች መነሻ ሊሆን ይችላል፡፡ በጎ የሚመኝ ደግሞ አእምሮውን በጎ መንፍስና በጎ ስሜት ይሞላዋል፤ በጎ አስተሳሳብ ሲደጋገም የተቀደሰ ሀሳብና ድርጊት እንዲኖረን ያደርጋል፤ ክፉ ሃሳብ በተደጋጋሚ ስናስብ ደግሞ የክፉ ድርጊቶች እንድንሆን ያደርገናል፤

መንግስታዊ ወይም የሀገር ወይም የማህበራት ሀብቶቻችንን ለማባከንና በሙስና ለማጭበርበር ለኛ ቀላል ነው፡፡ ስለእውነት መነጋገር ካስፈለገ፣ ከተሞቻችን እጅግ ብዙ ምሳሌ መንግስታዊ ተቋማትን ማየት ይቻላል፡፡ በብዙ  የመንግስት ቢሮዎች አላስፈላጊ ብክነት አለ፤ ይህ ደግሞ የሚከሰተው የኔነት ስሜት ሳይኖር ሲቀር ነው፤ ወጣቱ የህዝብን ንብረት እንደራሱ እንዲንከባከብ መበረታታት አለበት፡፡

መዋለ ህፃናት

ሽልማት ወይስ ቅጣት፤ ለልጆቻችን ትክክለኛው የመማሪያ መንገድ የቱ ነው፤ ልጆቻችን መቀጣት አለባቸው ወይስ የለባቸውም የሚለው ሀሳብ ብዙዎችን ያጨቃጭቃል፤ አንዳንዶቹ ወዳጆቼ ልጆች መቀጣት እዳለባቸው በመፅሀፍ ቅዱስም ጭምር እንደተፈቀደ በመጥቀስ ልጆቻችንን መቅጣት አለብን፤ ልጆች ካልተቀጡ ባለጌ ይሆናሉ፤ ትእዛዝ አይሰሙም ይሉናል፡፡ ነገር ግን ከሰለጠነው አለም የልጆች አያያዝና ከስነልቦና ምሁራን የሚሰጠውን አስተያየት ስንሰማ ልጆቻችንን መምታት ለልጆቹ ስብእና አላስፈላጊ መሆኑን ነው፤ የኛ ሀገር መዋለ ህፃናት ልጆቹን ያለእድሜያቸው ድርሰት እንዲያነቡ ነው የሚፈልጉት፤ የ4አመት ልጆችን ቀኑን ሙሉ ትንሽ ክፍል ውስጥ አጉረው ማዋላቸው ሳይበቃ ልጆቹ እንቅልፋቸው ሲመጣ ወንበር ላይ የሚያስተኙም መኖራቸውን ሰምቻለሁ፡፡ ልጆች እንዴት የሚማሩበት ወንበር ላይ ይተኛሉ ተብሎ ቢጠየቅ የመዋለ ህጻናቱ ባለቤቶች ጥያቄዎቹን አይቀበሉም፤ ቢቀበሉም ወደተግባር አይተረጉሙም፤ መፍትሄው የቁጥጥር ስርአት ማበጀት ብቻ ነው፤ አንድ መዋለህፃናት ሲከፈት ምን ምን መሟላት አለበት የሚለውን ባለሙያዎች ገምግመውት መስፈርቱን ሲያሟላ ብቻ ቢከፈት፡፡

ሁሉ ነገር ንግድ፣ ሁሉ ነገር ውሸት፣ ሁሉ ነገር ለገንዘብ ብቻ ተብሎ ትውልድ መጎዳት የለበትም፡፡ ወላጆችና መንግስት እጅግ ሊያሰተውሉት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ልጆቹ በሳምንት ቢያንስ ለአንድ ቀን ከክፍ ውጪ የተለያዩ ነገሮችን እያደረጉ አካላዊ እድገታቸውም በእንቅስቃሴ የተሞላ መሆን አለበት፡፡ የ4 አመት እድሜ ህፃናት የቀለም ትምህርት የሚማሩበት ጊዜ ሳይሆን እየተጫወቱ የሚያድጉበት እድሜ ነው፡፡ የከተሜነት ህይወት እየጨመረ ሲመጣ ወላጆች ልጆቻችንን የሚያሳድግልን ሰው ችግር ስለሚሆን የግድ ወደመዋለህፃናት መሄዳችን አይቀርም፣ ታዲያ መዋለ ህፃናቱ ልጆቻችንን ዘመናዊ በሆነ መልኩ መያዝ አለባቸው፤ ካልሆነ ግን አላስፈላጊ ለሆነ ስብእና ይዳረጋሉ፡፡

ከቴክኖሎጂ ምን ያህል እየተጠቀምን ነው

በሀገራችን የህዝብ አገልግሎት ቢሮዎች በብዛት የሚታዩት ችግሮች መሰረታዊ መነሻ ስራዎችን በኋላቀር ዘዴ መስራትን መለመልመዳችን ይመስለኛል፤ ለምሳሌ በመዘጋጃቤት የቤት ባለንብረቶች መዝገብ የሚቀመጠው በወረቀት መረጃዎች ነው፤ መረጃዎቹም በሳይንሳዊ ዘዴ ስላልተቀመጡ የአንዱን ባለጉዳይ ዶሴ ፈልጎ ለማግኘት ከሳምንት በላይ የሚፈጅበትን አጋጣሚ አይቻለሁ፤ ከሳምንት በላይ ጊዜ መውሰዱ ብቻ ሳይሆን አንዳንዴ ዶክመንቶቹ ተፈልገውም ላይገኙ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን በየከተሞቻችን መዘጋጃቤት ውስጥ መረጃዎቹን ለማደራጀትና በቀላሉ ተፈልገው የሚገኙበትን የመደርደሪያ ቁጥርና የመሳሰሉትን መረጃዎች ለመያዝ የሚሆኑ በቂ ኮምፒውተሮች አሉ፤ ኮምፒውተሮቹ ግን ሰው ካልሰራባቸው ራሳቸው ስራውን መስራት አይችሉም፤ በወረቀት የተያዘ መረጃ በአንድ ቀን እሳት አደጋ ይጠፋል፤ በኮምፒውተር የተቀመጠው መረጃ ግን በቀላሉ ኮፒ ተደርጎ አስተማማኝ በሆነ ምንገድ ሊቀመጥ ይችላል፡፡

ሌላ ምሳሌ ልጥቀስ፤ እኔ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ በነበርኩበት ጊዜና ዛሬ በተማሪዎች የቴክኖሎጂ አጠቃቀም መካከል ብዙ ልዩነት አለ፤ የአሁን ተማሪዎች ብዙዎቻቸው ኢንተርኔት ያለው ሞባይል አላቸው፣ በኛ ጊዜ ግን ተመሳሳይ አልነበረም፡፡ ቢሆንም አሁን ያሉት ተማሪዎች የተፈጠረውን የቴክኖሎጂ እድል በአግባቡ የተጠቀሙበት አይመስለኝም፤ ለምሳሌ ስልኮቻቸው ላይ ትምህርት ነክ ነገሮችን ከኢንተርኔት ፈልገው ማንበብና የሚሰጡ የቤት ስራዎችን በተሻለ ምልኩ መስራት ሲችሉ ብዙዎቹ ተማሪዎቻችን ዝም ብለው ፌስቡክ ላይ ፎቶ ብቻ ሲያዩ ጊዜያቸውን የሚጨርሱ ይመስለኛል፡፡ ከታወቀበት ኢንተርኔት ያለው ሞባይል ብዙ ስራዎች ሊሰራ ይችላል፤ ለዚህ ደግሞ ችግሩ ተማሪዎች ሞባይል ቢገዙም አጠቃቀሙን ላያውቁበት ይችላሉ፤

በእርግጥ በህዝባችን መካከል ብዙ የገቢ ልዩነት አለ፤ ነገር ግን የገቢ ልዩነቱ ከሁሉ በላይ የፍላጎት ልዩነት የሚፈጥር ይመስለኛል፤ ሁሉ ሰው ቁሳቁስ ይፈልጋል፤ ሁሉ ሰው መኪና ይፈልጋል፤ መኪና ስለኖረው ግን ለሀገርና ለወገን የሚጨምረው የተለየ ነገር ያን ያህል አይደለም፤ ቁሳቁሱ ሁሉ ልዩነትን ለማሳየት አላማቸው ያመዝናል፤ እኔ ከማን አንሼ በሚል ስሜት፡፡  ቁሳቁሶቹን ባገኘን ቁጥር ሌብነታችን ከጨመረ፤ ሙስናው ከጨመረ፣ ማግኘታችን ጥቅሙ ምንድን ነው?

ጦርነት

ይህንን ጥያቄ ለመመለስ የውስጥም ይሁን የውጪ ጦርነት ለባቸውን ሀገራት ያሉበትን ሁኔታ ማወቅ በቂ ይመስለኛል፤ ለምሳሌ ሴሪያ፤ ሊቢያ፣ የመን፣ ደቡብ ሱዳን የመሳሰሉትን፡፡ የሀገራችንንና የኤርትራን ጦርነትንም ብንመለከተ ከጥቅሙ ጉዳቱ ብቻ ነው የተረፈን፤ ሁለት ደሀ ሀገራት ናቸው በሌላቸው ሀብት ያውም በብድር ወደጦርነት የገቡት፤ ስለሆነም ካለፈም ታሪካችን ተምረን የወደፊቱን አለም ለልጆቻችን ጥሩ ማድረግ አለብን፡፡ ጦርነት መንግስታትን ከስልጣን ሊያባርር ይችላል፤ ለድሆች ከድህነት መውጣት ግን መፍትሄ ሆኖ አያውቅም፤ ስለሆነም ድህነታችንን እስበን፣ እንዲሁም ለዘላቂ ሰላምና ለዘላቂ ልማታችን ሲባል ለፖለቲካ ችግራችን በተቻለ መጠን ጦርነትንና የሀይል እርምጃን እንደመፍትሄ መውሰድ የለብንም፤ ይልቁንስ ሁሉንም የፖለቲካ አካላት ያማከለ በውይይት የሚፈታ የፖለቲካ ሂደት ያስፈልገናል፡፡

ሁለተኛ አመት ተማሪዎች ሆነን ፋርም አፍሪካ የሚባል መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ከየክፍሉ ከፍተኛ ውጤት ያላቸውን ተማሪዎች መርጦ ለጉብኝት ወደይርጋጨፌ፤ አማሮ፤ ኮንሶ፣ አርባምንጭ ወስዶ አስጎብኝቶን ነበረ፤ በዛ አጋጣሚ በደቡብ የሀገራችን ክፍል ዲላን፣ ይርገጨፌን፣ ጨለለቅቱን፣ የአማሮን የመስኖ እርሻ፣ ኮንሶን፣ አርባምንጭን፣ ሶዶን፣ አላባን ማየት ቻልኩ፡፡ የአርባምኝጩ የነጭ ሳር ፓርክ፤ የእግዜር ድልድይ በመባል የሚታወቀው በአባያና ጫሞ ሀይቆች መካከል ያለው ቦታ፣ የአርባምንጭ የአዞ እርባታ፣ ብዙ ደስ የሚል ጊዜ ነበረን፡፡ እኔና ሙሉነሽ የገልቤሳን ትምህርት ክፍል ወክለን ነበረ፤ በዛ አጋጣሚም የህይወት ትዝታ አተረፍኩኝ፤ በየመንገዱ ይታዩ የነበሩት አበቦች ስለስነህይወትም ብዙ ማሰብ እንድችል እድሉን ፈጠረልኝ፤ በእርግጥ አበባ/ FLOWER/ የህይወት መሰረት ነው፡፡

ስለግሎባላይዜሽን

 

አንዱ የፌስቡክ ወዳጄም ስለግሎባላይዜሽን የሚከተለውን ፃፈ፤ ግሎባላይዜሽን ዓለምን በአንድ ስልጣኔ፣ ማለትም በምእራቡ ዓለም ስልጣኔ፣በሊብራል የኢኮኖሚ ስርዓት ሰበብ በዓለም ላይ ነግሶ የሚገኘው የኢኮኖሚ ሚዛን መዛባት እና የኑሮ ክፍተት ቀውስ ተባብሶ እንዲቀጥል ያደርጋል፡፡ ማሕበራዊ ግፍ ይበልጥ ተጠናክሮና አይሎ ቢሊዮኖችን ማማቀቁን ይቀጥላል፡፡ በአለማችን 225 ግለሰቦች የ2.5 ቢሊዮን፣ ማለትም የዓለማችንን ግማሽ ሕዝብ ሐብት ይዘዋል፡፡ አሜሪካ ውስጥ የ3 ግለሰቦች ሐብት የ48 የተባበሩት መንግስታት አባል ሐገራትን ሐብት ይመጥናል፡፡ በሐብት ቁጥጥር ብቻ ሳይሆን በአወጣጥም ተመሳሳይ ሚዛን መሳት እናስተውላለን፡፡ ዓለም፡- ለአውዳሚ የጦር መሣሪያዎች በዓመት 480 ቢሊዮን ዶላር፣ ለአደንዛዥ እጽ 400 ቢሊዩን ዶላር፣ ለአስካሪ መጠጦች 105 ቢሊዮን ዶላር፣ በአሜሪካና በአውሮፓ ውስጥ ለሚገኙ ውሾችና ድመቶች 67 ቢሊዮን ዶላር ወጭ ታደርጋለች፡፡ ከላይ ለተገለጹት አልባሌና አጥፊ ነገሮች በዓመት የሚወጣው የገንዘብ መጠን 1 ትሪሊዮን 442 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን፣ ለጤና፣ ለትምህርትና ለምግብ የሚወጣው ዓመታዊ ወጭ ግን ከ19 ቢሊዮን ዶላር(ከ1.3%) የበለጠ አይደለም፡፡ ይህውም ለትምህርት 6 ቢሊዮን ዶላር (0.41%)፣ ለመጠጥና ለምግብ 13 ቢሊዮን ዶላር (0.89%) ፡፡

የአለማቸን ሀብት ክፍፍል እውነትም የሚገርም እኮ ነው፤ ለምሳሌ እስቲ የእግር ኳስ ተጫዋቾችን ደሞዝ እንደምሳሌ እንመልከት፤ Forbes የሚባለው ድህረገፅ የ20 እግር ኳስ ተጫዋቾችን ዘርዝሮ ነበረ፤ ከነሱም ውስጥ የሪያል ማድሪዱ ሮናልዶ ታክስን ጨምሮ በሳምንት ወደ14 ሚሊየን ብር፤ የባርሴሎናው ሜሲ በሳምንት 10 ሚሊየን ብር፤ ዝላታን ኢብራሂመቪች በሳምንት 5 ሚሊየን የሚገመት ብር ይከፈላቸዋል፡፡

እሰቲ አስቡት፤ የነኚህ የሶስቱ ተጫዋቾች የአንድ ሳምንት ደሞዝ ብቻ ወደ29 ሚሊየን ብር ነው ማለት ነው፤ አለማችን እንደዚህ አይነት ናት፤ ማንኛውም ጤናማ አእምሮ ያለው ሰው ከእግር ኳስ ተጫዋችና ከአዋላጅ ነርስ ለአንድ ማህበረሰብ እጅግ የሚያስፈልገው የቱ ነው ቢባል አዋላጅ ነርስ እንደሚል ጥያቄ የለውም፤ ነገር ግን እነኚህ ተጫዋቾች ባላቸው እውቅና የአንድ ትልቅ የህዝብ ሆስፒታልን ሙሉ በሙሉ ሊያሰራ የሚችል በጀት በላይ በአንድ ሳምንት ብቻ ያገኛሉ፡፡ ስለሆነም አለማችን እጅግ ከሚጠቅም ነገር ይልቅ ወደሚያስደስት ነገር ያዘነበለች ናት፤ እግር ኳስ ተጫዋች እኮ ሲጫወት እየተዝናናም ነው፤ አንድ የህዝብ ሀኪም ግን የህዝቡን ህመም በህሊናው አብሮ እየታመመ ነው ስራውን የሚሰራው፤ ነገር ግን የሀብት ክፍፍሉን ስንመለከት ያደጉትን ሀገራትንም ጨምሮ በተለይ በቅርብ ጊዜ የትምህርትና የህክምናን በጀት የመቀነስ አዝማሚ ይታያል፤ ነገር ግን የስፖርተኞችና የዘፋኞች ገቢ እየጨመረ ነው፤ ከዘፈንና ከትምህርትቤት የቱ ይበልጣል? ለምን የዘፈኑን ገበያ ትልቅ ቀረጥ አድርገውበት የትምህርትቤትንና የህክምናን በጀት አይጨምሩም ብለን ብንጠይቅ መልሱ በቀላሉ አይገኝም፤ ስለሆነም አሰላለፋችንን መምረጥ ያለብን ይመስለኛል፤ ቅድሚ መስጠት ያለብን ለየትኛው ነው?…ለሚያስደስተው ነው ወይስ ለሚጠቅመው?

የመኪና አደጋ

በቅርቡ በአዲስ አበባ ከተማ የመኪና አደጋ የደረሰ ሲሆን አደጋውን የደረሰው ግለሰብ ተጥቶ እያሽከረከረ መሆኑን አደጋው የደረሰበት በፌስቡክ ላይ ጠቅሶ በውጪው ሀገራት እንደሚደረገው ሁሉ የትራፊክ ፖሊሶች ሾፌሮች ምን ያህል አልኮል እንደጠጡ የሚያሳይ መሳሪያ መጠቀም አለባቸው ብሏል፤ በሀገራቸን በከፍተኛ ሁኔታ አምራች ዜጎችን እየገደለ ካለው የሞት ምክንያት የትራፊክ አደጋ እጅግ ከፍተኛ ቦታውን እንደሚይዝ ምንም ጥርጥር የለውም፤ ስለሆነም ለሀገር እድገትና ለዜጎች ህይወት ዋስትና ሲባል እጅግ ጥብቅ የሆነ የትራፊክ ህግ ተግባራዊ እንዲደረግ ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም አደጋ ከመድረሱ በፊት ጥፋተኞች ከፍተኛ ቁጥጥር እየተረደገባቸው ክቡር የሆነውን የሰው ልጆች ህይወት ማዳን መቻል አለብን፡፡ በተጨማሪም የትራፊክ ፖሊሶች ጥፋተኛ አሽከርካሪዎችን ለህግ ከማቅረብ ይልቅ አጋጣሚውን ለራሳቸው የግል ጥቅም ቅድሚያ በመስጠት በየቀኑ ገንዘብ ተቀብለው ችግሮች እንዳታረሙ እያረደጉ ይታያል፤ ስለሆነም ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት/በተለይ አሽከርካሪዎችና የመኪና ባለቤቶች እንዲሁም ትራፊክ ፖሊሶችና የመንገድ ትራንስፖርት ደህንነት ብዙ እንደሚጠበቅባቸው መረዳት ያስፈልጋል፡፡

አምስቱ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ከመሬት መንቀጥቀጥ ሸሽተው ወደቤተሰብ ሲሄዱ በመኪና አደጋ አዋሽ ወንዝ ላይ መሞታቸው፣ አዲስ አበባ በመኪና አደጋ የሞተችው ሰብለ በቤቶች ድራማ ላይ እንደ ትርፌ የምትሰራው፣ የልጅነት አብዶ አደጌ አስራት ካሳዬ ከዩኒቨርሲቲ ሊመረቅ ጥቂት ወራት ሲቀሩት በመኪና አደጋ የሞተው፣ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የ2008 ተመራዊ የነበረችው የትግክራይ ክልል ተወላጅ ተማሪ በመኪና አደጋ የሞተችም፣ ሶስት የቤተሰብ አባላትዋን በመኪና አደጋ ያጣችው የሀዋሳዋ፣ ስንቱን መዘርዘፍ ይቻላል፡፡ እንግዲህ የሀገራችን የመኪና አደጋ ስንት ዜጎችን እንደጨረሰብን በየቤቱ ችግሩ የደረሰበት ሰው ያውቀዋል፡፡ እጅግ የሚያሳዝነው ነገር ዛሬም ነገም ወደፊትም ችግሩ መቀጠሉ ነው፡፡ መንስኤዎቹ ምንድን ናቸው ቢባል፤ የአሽከርካሪና የተሸከርካሪ ሁኔታ ትልቁን ድርሻ ይይዛሉ፡፡ ከሀዋሳ ደብረዘይ ተመላልሼ ስለምሰራ በመንገዶቻችን ላይ ያለውን ሁኔታ በየሳምንቱ አያለሁ፡፡ አንዳንዱ ሾፌር በጫት መርቅኖ በሰአት በ150 እና በ140 ኪሎሜትር ሲነዳ መኪናው አደጋ ሊያደርስ ይችላል የሚለውን ምንም ሳያስተውል ነው፤ ምክንያቱም አስተሳሰቡ በሚቅመው ጫት ስለሚረበሽ፤ አንዳንዱ ደግሞ እጅግ ስለሚስገበገብ ሶስት ሰኮንድ ቆም ብሎ መጠበቅ ሲችል ደርቦ ለማለፍ ሲል፣ መይም ቴክኒክ ብልሽት ያለባቸውን መኪኖች ለገንዘብ ቁጠባ ሲባል ከገበያ ያለማውጣት፣ የተበላሸ የመንገድ ሁኔታ፣ የትራፊክ ፖሊሶች ቁጥጥር መቀነስ፣ ሙስናና ከሚፈቀደው በላይ መጫን፣ የአሽከርካሪ ብቃት ማነስ በተለይ ሲኖትራክ መኪኖችን የሚነዱ ወጣቶች በፍትነት መንዳትን እንደ ጀብዱ በመቁጠር በየቀኑ የንፁሃንን ህይወት እዲሁም የራሳቸውንም ህይወት ሲቀጩ ይውላሉ፡፡

ስለሆነም ችግሩ እጅግ አሳሳቢ ነው፤ የሀገራችን ህዝቦች በጥልቀት ሊያስቡበት ስለሚገባ በዚህ ፅሁፍ ይህንን ሀሳብ ላካትት ወሰንኩ፡፡ እስቲ አስቡት ከሀገራችን ህዝቦች ውስጥ የራሱ መኪና ያለው የሰው ቁጥር ውስን ነው፤ ወደፉት ሁላችንም መኪና ሲኖረን አደጋው ምን ሊሆን እንደሚችል፡ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ከኤችአይቪ የበለጠ የመኪና አደጋ የሀዝባችንን ህይወት እየቀጠፈ ይገኛል፡፡ እባካችሁ እንጠንቀቅ፡፡ በአዲስ አበባ አዳማ ፈጣን መንገድ ላይ ያንን የመሰለ አለም አቀፍ ደረጃ ባለው መንገድ ላይም እጅግ አሰቃቂ አደጋዎች እየደረሱ ነው፤ ደረጃውን የጠበቀ መንገድ ሰርተን የሰዉ በተለይ የመኪና ሾፌሮች አስተሳሰብ እጅግ ዝቅተኛ ደረጃ ስላለ አደጋ መቀነስ አልተቻለም፡፡ አስተሳሰብ ከሁሉ በላይ የሆነ ሀብት ነው፤ የወረደ አስተሳሰብ ያለው ሰው ህ,ለራሱ ህይወትም ዋጋ አይሰጥም፤ ወጣቱ ትውልድ ለራሱ ህይወት ዋጋ እንዲሰጥ ልብሱና ጫማው ብቻ ሳይሆን አእምሮው እንዲሰለጥን ሁላችንም የሚቻለንን ማድረግ አለብን፡፡

የህግ የበላይነት

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ስኬት ለሌሎቹ የሀገራችን መንግስታዊ ተቋማት ለምሳሌ ለዩኒቨርሲቲዎች፣ ለባንክ፣ ለመብራ ሀይል፣ ለቴሌ፣ ለፖስታ፣ ለትራንሰፖርት፣ ለውሃ፣ ለትምህርት ወዘተ ጥሩ ምሳሌ መሆን ይችላል፤ ዋጋው ውድ ቢሆንም አየር መንገዳችን እጅግ ጥሩ የምቾት ደረጃ ላይ እንደሚገኝ በየአመቱ የሚታተሙትን የአየር ትራንስፖርት ሪፖረቶች ማየት በቂ ነው፡፡

አንድ አዲስ አበባ ከተማ ተወልዶ ያደገ ወጣት ከዩኒቨርሲቲ በአከባቢ ጤና ይመረቅና ቆንጆ የስራ እድል ሶማሊ ክልል ያገኛል፤ ተማሪው ለስራው የሚያስፈልጉትን መስፈርቶች በብዛት ያሟላ ሲሆን በሶማሊና ቋንቋ አለመቻል ምክንያት ስራውን ሳያገኝ ይቀራል፤ ልጁም ከቃለመጠይቅ ሲመለስ ሶማሊ ክልል ሄዶ ለመስራት የአከባቢውን ቋንቋ መጠየቁ ስህተት እንደሆንና አማርኛ እስከተናገረ ድረስ መቀጠር እንደነበረበት በፌስቡክ ላይ ጠቅሶ በዚህ ከቀጠለ የሀገራችን አንድነት ጥያቄውስጥ እንደሚገባ ይዘረዝራል፤ የልጁን ሀሳብ ተከትሎ ሌሎች ደግሞ በአዲስ አበባ የቻይና ኩባኒያዎች ውስጥ ተቀጥሮ ለመስራት ቻይንኛ እየተማርን የራሳችንን ህዝብ ለማገልገል ግን የአከባቢውን ቋንቋ ለመማር ፈቃደኛ የማንሆንበት ምክንያት ትክክል አይደለም ሲሉ ይከራከራሉ፡፡ እንግሊዘኛ የአለማችን መግባቢያ ቢሆንም ጀርመን ሀገር ሄዶ በእንግሊዘኛ ብቻ መስራት መፈቀድ አለበት ማለት እንደማያስኬድ ሁሉ በሀገራችንም አብዛኛው ህዝብ አማርኛ ቢናገርም ወደክልሎችና ገጠር ቦታ ሄደን የአከባቢውን ቋንቋ አለመጠቀም ለህዝቡ ንቀት ማሳየት ነው የሚሉም አሉ፤ እኔ ዴንማርክ ሀገር በቆየሁበት ጊዜ የዴንማርክን ቋንቋ መማር ግድ ነበረብኝ፤ ስለሆነም የሀገራችን ወጣቶች ሀገራችን የብዙ ብሄር ብሄረሰቦች ሀገር መሆንዋን በመረዳት እንደምንም ብለው አማርኛ እንግሊዘኛና አንድ ወይም ሁለት የሀገራችንን ቋንቋ ቢለማመዱ በጣም ቆንጆ ነው፡፡

ታሪካችን

እንደማንኛውም ሀገር የኛ ሀገርም ብዙ ታሪኮች አሏት፤ ታሪኮቹ ደግሞ የተወሰኑት ቆንጆ ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ መጥፎ ታሪኮች ናቸው፤ ለምሳሌ ዱሮ የነበሩት መሪዎች ስልጣናቸውን ለማስጠበቅና የሚከፈላቸውን ቀረጥ ለማብዛት ወደተለይዩ የሀገራችን ክፍሎች በመዝመት ተዋግተዋል፤ በውጊያዎቹም ጊዜ የተደረጉ አሳዛኝ ታሪኮች አሉ፤ በሌሎች ሀገራም ተመሳሳይ ታሪክ እንደነበረ እንረዳለን፤ ስለሆነም የዛሬው ትውልድ ካለፈው ታሪክ በመማር የዛሬንና የነገን የሀገራችንን ታሪክ ቆንጆ ማድረግ ያስፈልጋል፤ ለዚህ ደግሞ በወገንተኝነትና በጭፍን አንዱን የዱሮ መሪ ታሪክ ከመደገፍ ወይም ከመቃወም ምክንያዊ ሆኖ ችግሮቹን በማውገዝ በጎ ጎኖቹን ደግሞ በመውሰድ ወደተሻለ አንድነት መሄድ አለብን፤ ካለሆነ ግን አሁን እንደምናየው አንዱን መሪ ፍጹም ትክክል  ሌላውን ደግሞ ፍፁም የተሳሳተ ማድረግ የሀሳብ አናሳነትን ማሳያ ይመስለኛል፡፡

ለምሳሌ ለስልጣን ሲባል ከተለያዩ የውጪ ሀይሎች ጋር በመተባበር የሀገር ውስጥ ነገስታትን መውጋት በዱሮ ጊዜ የተለመደ እንደነበረ የሀገራችን ታሪክ ፀሀፊዎች በተለያየ መልኩ ይነግሩናል፤ ነገር ግን ማንኛውም ከውጪ ሀገር ጋር የሚደረግ የፖለቲካ ስምምነት ሄዶ ሄዶ የውስጥ አንድነትን የሚጎዳ መሆኑን መረዳት የግድ ነው፤ ምክንያቱም ትክክለኛው ስምምነት መምጣት ያለበት ከውጪ ሀገር ሀይሎች ጋር ሳይሆን ከሀገር ውስጥ ተቃዋሚዎች ስለሆነ ነው፤ ሀገራችን ህብረ ብሄር ስለሆነች ብዙ አይነት ሀሳቦችና ብዙ አይነት ፍላጎቶች ያሉባት መሆኑን ተረድተን አንዳችን ከሌላው ጋር ለመስራት መዘጋጀትና ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልግ ወጣቱን ትውልድ ማስረዳት ያስፈልጋል፤ ካልሆነ ግን የፖለቲካ ችግራችንን ለመፍታት ሮጠን ወደአውሮፓ መንግስታት ወይም ወደአረብ መንግስታት ጋር የምናደርገው ስምምነት የሀገራችንን ህዝቦች ችግር በመፍታት ከድህነት ሊያወጣን አይችልም፤ ወደድንም ጠላንም መተባበር አማራጭ የለውም፤ መተባበር ደግሞ መፈቃቀድን መሰረት ያደረገና አንዱ የሌላውን ፍላጎትና ህልውና በመረዳት መሆን አለበት፡፡ የመጠፋፋት ፖለቲካ የትም የሚያደርሰን አይመስለኝም፡፡

ዱሮንና ዘንድሮ፣ ለምሳሌ አዲስ አበባ ዱሮና ዘንድሮ ምን ትመስላለች ከተባለ ዱሮም ዘንድሮም የነበሩትን መጠየቅ ነው፤ ቢሆንም ዘንድሮ ያሉትን መጠየቅ ቀላል ነው፤ ዱሮ የነበሩትን ለመጠየቅ ግን የዱሮዎቹ አሁን የሉም፤ ከ100 አመት በፊት ያለውን የሀገራችንን ታሪክ ለማወቅ የግድ ወደማንበብ እንመለሳለን፤ የሚነበቡትም ቢሆኑ ተመሳሳይ ሀሳብ የላቸውም፡፡ ፖርቹጋላዊው አንድ ሀሳብ ሲፅፍ፤ ጣሊያናዊው ስለሀገራችን ታሪክ ከፖርቹጋሉ የተለየ ይሰጣል፤ግብፃዊው ሌላ ታሪክ፤ የሰሜኑ ኢትዮጵያዊ ሌላ ታሪክ፤ የደቡቡ ሌላ ታሪክ ልዩነቱ ብዙ ነው፤ መሰረታዊው ችግር ደግሞ ፀሀፊያኑ ከወገንተኝነትና ነፃ አለመሆናቸው ነው፡፡

ስለዚህ የዛሬው ትውልድ ምን ተሻለው?? የኔ የግል አስተያየቴ ለዛሬ አብሮነታችን ዋናውን መሰረታችንን ዛሬን አድርገን ከታሪክ ጥቂት ወስደን፤ ነገን የተሻለ ለማድረግ መስራትና መታገል ነው፡፡ ታሪክን ዋና መሰረታችን ስናደርግ እርስበእርስ በሚጋጩ ሀሳቦች ግራ የምንጋባ ይመስለኛል፡፡ የዛሬዋ ሀገራችንም ብዙ ተጨባጭ እውነታዎች አሉባት፤ ሀገሪቱ ብዙ ፍቅር፤ ብዙ ልማት፤ ብዙ መሻሻል እንዳለባት ለመረዳት ብዙ ታሪክ ማንበብ የግድ አይመስለኝም፤ ሀገራችንን በተመለከተ ብዙ ነገር ግልፅ ነው፤ ሀገራችን ደሃ ናት፤ ድርቅ ሲሆን ከሀብታም ሀገራት ስንዴ መለመናችን የማይካድ ሀቅ ነው፤ ህዝቦችዋ ከሊቅ እስከ ደቂቅ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ድሆች ናቸው፤ ወይም ለሀገሪቱ ድህነት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ተጠያቂ ናቸው፤ መጠኑ ቢለያይም እድሉ ሲገኝ ወጣቱ፣ የተማረው፣ ያልተማረው፣ ፖለቲከኛው፣ መምህሩ፣ የሀይማኖት አባቶች ወዘተ ሁሉም ከሀገሪቱ እየተሰደዱ ነው፤ ለመሰደድም ይፈልጋሉ፡፡

ዛሬ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ስለእውነትና ስለህዝቡ መስዋእትነት የሚከፍለው ማን እንደሆነ ለመረዳት እጅግ ይከብዳል፤ ቢሆንም በተሸለ አስተሳሰብና አሰራር ነገን የተሻለ ለማድረግ መታገል ነው፤ ምንም ቢሆን ሁሉም በደስታና በእኩልነት የሚኖርባት ሀገር መሰራት አለባት፤ ሀገራችን ተለውጣ የተሰደዱት ወደሀገራቸው ደስ እያላቸው ተመልሰው የሚኖሩባት፣ ዜጎች ሰርተው የሚቀየሩባት ሀገር መሰራት አለባት፤ የሀገራችን ታሪክ መቼውንም ቢሆን የተወሰኑ ችግሮች የተወሰኑ በጎ ነገሮች አለበት፤ ማንም በታሪክ ታላቅ ስለሆነ ዛሬን ደካማ ከሆነ ደካማ ይባላል፤. ሀገራችን ቆንጆ ሀገር ለመሆን እጅግ ብዙ ርቀት መሄድ አለባት፤ ለዛ ደግሞ መፍትሄው ወጣቱ ጠንክሮ መስራት እንዳለበት  እና ጠንክሮ እንዲሰራ ማበረታታት ያስፈልጋል፤ የሀገራችን ህዝቦች  በየአቅጣጫው ጠንክረው መስራት አለባቸው፤ ታዲያ በስግብግብነት የህዝብን ሀብት በሙስናና በስርቆት መጨረስ አለባቸው ማለቴ አይደለም፤  ሀገራችን ከቻይና ጋርም ከአሜሪካ ጋርም ከኢራን ጋርም ከእስራኤል ጋርም ከግብፅ ጋርም ከሱዳን ጋርም ከሶማሊያ ጋርም ከኤርትራ ጋርም ፣ .ከሁሉም ጋር በሰላም ለመስራት የሚቻለውን ሁሉ ማድረግ ያስፈልጋል፤ ይህ ቀላል እንዳልሆነ ግልፅ ነው፡፡

እዚህ መሃል እጅግ ብዙ እንጭጭ አስተሳሰብ ያላቸው የሚያማምሩነገር ግን የተሳሳተ አስተሳሰብ ያላቸው መሪዎችና ባለስልጣናት መኖራቸውን መረዳት ያስፈልጋል፤ ስለሆነም የሀገራችን መከላከያ ማጠናከር እዲሁም ወጣታችንንም አርቆ እነዲያስብ ማድረግ የግድ ነው፡፡  ጥፋት ለሚየስቡትና ጥፋት ለሚየሰደርጉት፣ የሚያደርጉትን ስለማያውቁ ይቅር እንላቸዋለን፡፡

አይናችን ይከፈት፤ ሌሎችን ሳይሆን ራሳችንን እንፈትሽ፤ ስለሌሎች ሳይሆን ስለራሳችን በጎ እናስብ፤ የሌሎችን ሳይሆን የራሳችንን ቤት እናፅዳ፤ ኦርቶዶክስ ከሆንክ መጀመሪያ የኦርቶዶክስን ቤት አፅዳ፤ ሙስሊም ከሆንክም መጀመሪያ የሙስሊምን ቤት  አፅዳ፤ የራስህን ትዳር፣ የራስህን የቀን ተቀን ውሎ በማሻሻል ጀምር፣ መጀመሪያ የራስህን ሰላም ፍጠር፤ ሰላምህ ካንተ ሲተርፍ ወደሌሎች ይዳረሳል፡፡

የራስህ ሰላም ከሌለህ ሰላማዊውንም ትረብሻለህና፤ ሁሉ ከራስ ሲጀምር ቆነጆ ነው፤ ቀኑን ሙሉ እግዚአብሄርን በመፍራት እንኑር፤ መንገድህን ለእግዚአብሄር አደራ ስጥ፤ ነገር ግን ቀኑን ሙሉ ቁጭ ብለህ ውለህ ህብሰተ መና እንደዝናብ አይዘንብም፤ በአል ሲደርስና በሰንበት ቀናት ቤተክርስቲያን እያስቀደስን፣ አልፎ አልፎ ደግሞ ጭፈራ ቤት እያደርን፣ በማህበራዊ ድህረ-ገፆች የሌሎችን ሀይማኖት ማንቋሸሽ መቆም አለበት፤ በየአከባቢው ብዙ ግብዞች ነን ያለነው፤ ሲፈልገን የሀይማኖት ተቋማት ደህንነት ጠባቂ መስለን እንታያለን፤ የቀን ተቀን ውሎውአችን ግን ምንም የአማኝ ስነምግባር የሌለው ብዙዎች ነን፡፡ በመምሰልና በስም ብቻ መንጋጋት፣ ክርስትናችን  ከማንነታችንና ከቀን ተቀን ምግባራችን መታየት አለበት፡፡ ውሸት፣ሀሜት፣ስድብ፣ስርቆት፣ ስስት፣ በሀሰት መመስከር ወዘተ ስር ሰደው ማህበረሰባችንን እናስቸግራለን፡፡

ወዳጆቼ ራሳችንን እንመርምር፤ ከራሴ ጀምሮ ሁላችንም እጅግ ብዙ ክፍተቶች አሉብን፤ ሀይማኖታችን የጥል መሰረት ብቻ ባናደርገው ጥሩ ነው፤ የብሄረሰብ ልዩነታችን ዘላቂ ልማታችንን አንቆ ይዞ ለደካማና አስመሳይ ግለሰቦች አቋራጭ ሀብት መሰብሰቢያ መሆን የለበትም፡፡ ክርስትና በቤተክርስቲያን ግቢ ብቻ የሚተገበር መሆን የለበት አይመስለኝም፤ አረ በቤተክርስቲያን ግቢም እጅግ ብዙ ነገሮችን እየታዘብን ነው፤ በደመነብስ መከተል ይበዛል፤  ተምረን እንዳልተማርን የምናደርገው ጉዳይ ሰብአዊ ክብራችንን ከማውረድና አንዳችን ሌላውን ከመኮነንና ከማሳሳት ያለፈ የትም አያደርሰንም፤ ከሊቅ እስከ ደቂቅ፣ ሁሉ ራሱን ይፈትሽ ! ድህነትን ለልጆቻችን ማውረስ የለብንም፡፡ ወዳጆቼ…..በሀገራችን ውስጥ ያለውን የሙስናና ያለመታመን ችግሮች መሰረታዊ ምክንያት ሳስብ ሁሌም የሚገርመኝ ነገር ነው፡፡ ከህዝባችን 90 ከመቶው በላይ ሀይማኖተኛ ነው፡፡ ነገር ግን እግዚያብሄር የለም፤ አምላካችን ገንዘባችን ነው ከሚሉት፤ ከዛም አልፈው ከተመሳሳይ ፆታ ጋር እስከመጋባት ከደረሰው አለም ካሉ ህዝቦች ያነሰ ታማኝነትና ይህ ሁሉ ሙስና የተስፋፋው በሀገራችንና በደሃ ሀገራት ነው……

ለዚህ ሁሉ ልዩነት መሰረታዊው ምክንያት ድህነታችን/የገንዘብ፣የቁሳቁስና የአስተሳሰብ ድህነታችን/ ይሆን?…ሌላ ምንም ምክንያት መኖር የሚችል አይመስለኝም፡፡

የምናደርገውን ስለማናውቅ ይቅር ካላለን በስተቀር ፡)

ይህ ሁሉ ፀሎት፣ፆም፣ ዝማሬ፣ የሀይማኖት ተቋማት፣ የሀይማኖት መምህራን…ይህን ሁሉ የሀይማኖት ታሪክ ይዘን….በተቃራኒው ደግሞ የነኚህ ሁሉ ማህበራዊ ችግሮች ባለቤት የመሆናችን ነገር እጅግ አሳሳቢ ነው፡፡ መዋሸትና መስረቅ አለመቻል ሞኚነት መስሎ እስኪታይ ድረስ?? አለባብሰው ቢያርሱ ባረም እንደሚባለው…. ለመታየት ብቻ የምናደርገውና የምንኖረው ነገር ለልጅ ልጆቻችን ዋጋ የሚያስከፍለን ይመስለኛል፡፡ ግራ የሚያጋባ ነገር እኮ ነው…..በቅርቡ ደግሞ የሀይማኖታዊ ክብረ በአልንም ጭምር በቢራ ፋብሪካዎች እስፖንሰር ማድረግ ተጀመረ…..እውነት ያንን ያህል የማስተዋል ችግር ኖሮብን ይሆን?…..እስቲ ንገሩኝ፤ እሴቶቻችንና የማህበረሰባችን ቀን ተቀን ኑሮ እኮ እጅግ የተራራቁ ናቸው….ምክንቱ ምንድን ነው?? የተለየ ሀሳብ ካላችሁ ብታካፍሉኝ….

ድህነት ምንድን ነው?

ሁላችንም ሀብታም መሆን እንፈልጋለን፤ ሀብት ደግሞ ህይወታችንን በብዙ መልኩ የተሻለ ያደርጋል፡፡ ስለሆነም ሀብታምነት ሁልጊዜም የሚያስፈልግ ስለሆነ ወጣቶቻችን ሀብታም እንዲሆኑ ማበረታታት ያስፈልጋል፡፡

ዋናው ጥያቄ ያለው ሀብታምነት ማስፈለጉ ላይ ሳይሆን እንዴት ሀብታም እንሁን የሚለው ላይ ነው፤ ሀብታም ለመሆን መጀመሪያ ሀብት ምንድን ነው የሚለውን በጥንቃቄ ማየት ያስፈልጋል፡፡

ጉርብትና

ጉርብትና ትልቅ ነገር ነው፤ በተለይ በሀገራችን ባህል ጎሮቤት ማለት እንደቤተሰብም ሊቆጠር ይችላል፤ ጎሮቤቶች የቀን ተቀን ህይወታቸው የተሳሰረ ነው፤ ሰው ከቤት ራቅ ብሎ ሲሄድ ወይም አደጋ ሲደርስበት አደራ የሚለው ወይም ችግሩን የሚያካፍለው ለጎሮቤቱ ነው፡፡ ጉርብትና በቤተሰብ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን ሀገራትንም ከጎሮቤቶቻቸው ጋር ልክ እንደቤተሰብ ብዙ የሚያስተሳስሩ ነገሮች አሉ፡፡ የጋራ ደህንነት፣ የጋራ ሰላም፣ የባህል ልውውጥ፣ የጋራ ንግድ፣ የጋራ ገበያ ሊጠቀሱ ከሚችሉት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ በዴንማርክና በስዊዲን መካከል ያለውን ጉርብትና ሳይ እጅግ እቀናባቸዋለሁ፡፡ ሀገራቱ የጠበቀ ግንኙነት ስላላቸው ሁለት ሀገራትም አይመስሉም፡፡ ለምሳሌ አንድ የዴንማርክ ዜጋ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ወደስዊዲን መሄድ ይችላል፣ ቪሳ አያስፈልገውም፣ ሄዶም እቃ ገዝቶ ወደሀገሩ መመለስ ይችላል፤ ስራ ካገኘም ተመላልሶ መስራት ይችላል፤ ከዴንማርክ ዋና ከተማ ኮፐንሀገን ወደስዊዲን የጠረፍ ከተማ ማልሞ ለመድረስ ከ45 ደቂቃ ያነሰ የባቡር ጉዞ ነው፤ የባቡሩ ሀዲድ 17 ኪሎ ሜትር በውሀ ውስጥ የተዘረጋ መስመር ነው፤ ሀገራቱ የደረሱበት ድንቅ የእድገትና የጎሮቤትነት ስሜት እጅግ ያስቀናል፤ ሀገራችንስ? አኛስ ከጎሮቤቶቻችን ጋር ያለን ግንኙነት ምን ይመስላል?

ሀገራችን ከጂቡቲ ጋር የፈጠረችው ጥብቅ ትስስር የሚያስመሰግንና ከሌሎች ጎሮቤት ሀገራት ጋርም ሊኖረን ለሚችለው ትስስር እንደ ቅርብ ምሳሌ ሊወሰድ ይችላል፤፡ ሀገራችን የጅቡቲን ወደብ በመጠቀም ከውጪ የሚመጡ ሸቀጦችን በቀላሉ ወደሀገር ውስጥ የምታስገባ ሲሆን ጅቡቲ ደግሞ የባህር በር በማከራየት ከሀገራችን ብዙ ገቢ ታገኛለች፤ የጋራ ጥቅም ማለት ይህ ነው፤ የኤርትራስ ጉዳይ?  የኤርትራ ጉዳይ ደግሞ ከጅቡቲው ጋር ሲነፃፀር በጣም አሳሳቢ ደረጃ መሆኑ ያሳዝናል፤ የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች ቀድሞ እንደአንድ ሀገር ይኖሩ የነበሩ መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ሰላማዊ ግንኙነት ቢኖር በንግድና በጋራ ጥቅም ትስስር የት ደረጃ መድረስ እንደሚችሉ ሲታሰብ ጉዳዩ ለመጪው ትውልድ የቤት ስራ መሆኑን ያሳያል፡፡ ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እንዲኖራት ካስፈለገ፣ ከሁሉም ሀገራት ጋር እጅግ አርቆ ማሰብን በተሞላ የዲፕሎማሲ ስራ ዘላቂ ሰላም መፍጠር መቻል አለባት፡፡ በአለማችን ላይ የትኛውም የሰለጠነ የሚባል ሀገር ከጎሮቤት ሀገራት ጋር ከባድ ጦርነት ውስጥ አይገባም፤ በቅርቡ የተፈጠረው የሩሲያና የዩክሬን ጦርነትም ቢሆን ምን ያህል ሰቆቃ በዜጎቻቸው ላይ እያደረሰ እንደነበረ ለሁላችንም የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፤ ከዛ ባለፈ ግን የአውሮፓና የካናዳ እንዲም የአሜሪካ፣ የጃፓን ሰላማዊ ግንኙነት ሲታሰብ የቀድሞ ታሪክ ምንም የጦርነት ታሪክ ቢሆንም በሀገራቱ መሪዎች አርቆ አሳቢነት ከጠላትነት ወደወዳጅነት ተመልሰው የጋራ የሰላም ጦር፣ የጋራ ገበያ፣ የጋራ የምክክር መድረኮችን ወዘተ መፍጠር ችለዋል፤ ለምሳሌ ያህል እንግሊዝንና ጀርመንን ብንመለከተ በታሪካቸው እጅግ ከባድ የሚባል የጦርነት ጊዜ አሳልፈዋል፡፡ በተለይ እንግሊዞች በጀርመኖች ላይ ከባድ የጦር ውድመቶችን አድርሰዋል፤ ዛሬ ላይ ያሉበትን የአብሮ መስራትና የጋራ ጥቅምን የማስጠበቅ ሂደት ስንመለከተ የነበረውን ታሪካቸውን ረስተው ለሀገራቸው ህዝቦች ዘላቂ ሰላምን እንዳረጋገጡ መረዳት ይቻላል፤ የጃፓንና የአሜሪካንን የዛሬ ግንኙነት ስንመለከት አሜሪካ አውዳሚ የጦር መሳሪያ በመጠቀም በአለማችን መቼውንም የማይረሳውን በሄሮሺማና በናጋሻኪ ከተሞች ጥቃት በማድረስ በጃፓን ህዝብ ላይ እጅግ ትልቅ ውድመት አደረሰች፤ ነገር ግን ይህ ትልቅ የጦርነት ቁስል ቢኖርም ጃፓኖች ከተመሳሳይ ጦርነት በራሳቸው ውሳኔ በመራቅ አሜሪካንንም ጨምሮ ከሌሎች ሀገራት ጋር በሰላም ወደመኖር ፊታቸውን አዞሩ፤ በቀርቡ የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ኦባማ ጃፓን ሀገር ሄደው በጦርነቱ ወቅት ለሞቱት የጃፓን ዜጎች የመታሰቢያ አበባ ያስቀመጡ ሲሆን ለጃፓን ህዝብም የይቅርታና የጥልቅ ሀዘን ስሜታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ከላይ የጠቀስኩት የጃፓንና የአሜሪካንና እንዲሁም የጀርመንና የእንግሊዝ የዱሮ የጦርነት ታሪክ ሀገራችን ከጎሮቤቶችዋ ጋር ሊኖራት ለሚችለው ግንኙነት ጥሩ ምሳሌ መሆን ይችላል፤ ሰላም ከሁሉ በላይ የሚያስፈልግ መሆኑንና የሀገር መሪዎች ሰላማዊ የአብሮ መኖር ምሳሌ በመሆን ለህዝባቸው ዘላቂ ሰላምና ልማት ማረጋገጥ እንደሚችሉም ያሳያል፡፡

ለትምህርት ዴንማር በነበርኩ ጊዜ ብዙ የኤርትራ ዜጎችን የማናገር አጋጣሚ ነበረኝ፡፡ ሁሉም ከድህነት አምልጠው የሄዱና የኛኑ አይነት ሰርተው ራሳቸውን የመቀየር አላማ ያላቸውና ሰው አክባሪ ናቸው፡፡ ሀገራቸው ድህነት መኖሩንና ውጪ ሀገር ሰርተው የሚያገኙትን ገንዘብ ለዘመዶቻቸው እንደሚልኩም ነግረውኛል፡፡ በዊጪ ሀገር የሚኖሩ የሀገራችን ዜጎችም ሰርተው የሚያገኙትን ገንዘብ ወደሀገር ቤት በመላክ ደሀ ወላጆችና ዘመዶቻቸውን እንደሚረዱ ሁላችንም እናውቃለን፡ ከአለማችን ተጨባጭ ሁኔታ የምንረዳው ጉዳይ ማንም ሀገር ዘላቂ ሰላም እንዲኖረው ከጎሮቤቶቹ ጋር ጥሩ ግንኙነት ያስፈልገዋል ፡፡ ሰላማዊ ግንኙነት ሲኖር ንግድና የጋራ እድገት ይኖራል፡፡ ኤርትራና ሶማሊያ ሰላም ቢሆኑ ሀገራችን የሁለቱንም ወደቦች በመጠቀም በንግድና በጋራ ሰላም የተሸለ ተጠቃሚ ትሆናለች፤ ሀገራቱም ከሚያስክፉሉን የወደብ ቀረጥ ተጠቃሚ ይሆናሉ /ወይ ተዋግተን አንዱን ወደብ የኛ እስካላደረግነው ድረስ፤ ውጊያ ግን የዱሮ ነው፤ ዘመናዊ ሰው አይዋጋም፤ በሰላም አብሮ ይኖራል እንጂ/፤ ፡፡ ስለሆነም እያንዳንዳችን የሰላምና የአንድነት አምባሳደሮች መሆን አለብን፡፡ ሰይጣናዊ አስተሳሰብ አእምሮአቸውን ሞልቶ ሁሌም ጥላቻ የሚሰብኩትን መስማት የለብንም፤ ይልቁንም የተሳሳቱትንም አርመን ለጋራ እድገትና ሰላም መስራት አለብን፡፡ ከጎሮቤቶቻችን ጋር ሰላም ማውረድ አለብን፤ ሁላችንም የሰላም አምባሳደሮች እንሁን፡፡  እኔም ሰው አንድ የስዊዲን ዜጋም ሰው ከሆነ፤ ዴንማርክና ስዊዲን በሰላም አብረው ከኖሩ፣ ኢትዮጵያና ኤርትራ ለምን በሰላም አብረው አይኖሩም?

ሰላም ከሌለ ጦርነት ይከተላል፤ ምንም ቢሆን ጦርነት ሁሌም ጦርነት ነው፤ ምክንያቱም  ጦርነት ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ ለመግደል ዘመቻ ስለሆነ፤ ጦርነት እንዲኖር ደግሞ አንዱ ወገን ወይም ሁለቱም አእምሮአቸው ሠይጣናዊ በሆነ አስተሳሰብ ሲሞላ ነው፡፡ እስቲ አስቡት፣ በድርቅ ለተራቡ ወገኖቻችን እርዳታ እየጠየቅን ሁለት ደሀ ሀገራት አሁንም በ21ኛው ክፍለ ዘመን ለመገዳደል ስንዘጋጅ፡፡  ግድያ የምንም መፍትሄ መሆን አይችልም!!

ጃፓንና አሜሪካ በሰላም አብረው እየኖሩ እያየን እኛ ግን አልወጣልንም፤ ጎሮቤቶቻችንን እያየን? ሊቢያ፣ ሴሪያ፣ የመን፣ ኢራቅ፣ ሱዳን፣ ሶማሊያ ወዘተ፤ ከነኚህ ሀገራት ምን እየተማርን ነው?

እኔ የምፈልገው ሰላም የሰው ልጅ ደምና ህይወት የተከፈለበት ሳይሆን አርቆ በማሰብና በጋራ ስምምነት የሚመጣውን ሰላም ነው፡፡ ለሀገሬ የምመኝላት ሰላም አርቆ በማሰብ የሚመጣውን ሰላም ነው፤ ምንም ቢሆን ራሳችንን ከጦርነት ማራቅ አለብን፤ ይህ ማለት የሀገር መከላከያ ሰራዊት አይኑረን ማለት አይደለም፤ ጠንካራና የማይደፈር ሰራዊት ሊኖረንም ይገባል፤ ነገር ግን መሪዎቻችን ከነጂቡቲና ከኬንያ ጋር የፈጠሩትን ሰላም አይነት ከኤርትራና ከሌሎቹም ጎሮቤቶች ጋር ለመፍጠር የሚቻለውን ሁሉ ማድረግ አለባቸው፡፡

ከግብፅ ጋር ከተደራደርን ከኤርትራ ጋር የማንደራደርበት ምክንያት ምንድን ነው??

ዘረኝነት ማለት ምን ማለት ነው?

ሀገራችን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ምሳሌ ብንወስድ፤ በአሁን፣ በ2008 መጨረሻ፣ በተለየዩ የሀገራችን ክፍሎች በሚከሰቱ ግጭቶች የሰው ህይወት እያለፈ መሆኑን ሁላችንም እናውቃለን፡፡ ታዲያ ለነኚህ ችግሮች የያንዳንዳችንን ምላሽ ብንመለከት/እድሜ ለፌስቡክና የሀገራችንን ህዝቦች ሀሳብ ከያለንበት ሆነን እያየን ነው/፤ አልፎ አልፎ የምናስተውለው ነገር፣ ፈረንሳይ ሀገር ሰዎች ሲገደሉ የፌስቡክ ፎቶውንም ጭምር በፈረንሳይ ባንዲራ የሚቀየር የሀገራችን ዜጋ ከሀገር ውስጥም ከውጪም ብዙ ነበረ፣ ጋምቤላ  አደጋ ሲፈጠር ደግሞ ምንም እንዳልተፈጠረ ዝም ብለናል፤ ወይም ጎንደርና አምቦ ስለተፈጠረ ችግር ቀን ተለሊት ትንታኔ እየሰጠን ዶዶላ ላይ ለተፈጠረው ደግሞ ጆሮ ዳባ ልበስ ብለናል፤ አዲስ አበባ ወይም ትግራይ ውስጥ ለተከሰቱ ችግሮች ቀን ተለሊት ኡኡኡኡ ብለን ጎንደር ወይም ሀረር ለተከሰቱት ደግሞ አስታራቂ መስለናል፤ በአጭሩ ሚዛናዊነትና ሰብአዊነትን መሰረት በማድረግ ሳይሆን ለአንዱ ብሄረሰብ ወይም መንደር የበለጠ መቆርቆርና የሌሎችን ህመም ደግሞ እንደ ደስታ በሚያስቆጥር መልኩ ዝም ማለት አልፎ አልፎም ቢሆን አስተውለናል፤ በአጭሩ አንድን ብሄረሰብ ወይም ቡድን በጭፍን መውደድ መይም መጥላት፤ በእኔ ግንዛቤ በቀጥታም ባይሆን በተዘዋዋሪ እንደዚህ አይነቶቹ ሁኔታዎች የዘረኝነትን ስሜት የሚያሳዩ ይመስለኛል፤ ስለሆነም ሁላችንም ራሳችንን መፈተሽ አለብን፤ ከነኚህ ሁሉ ችግሮች ነፃ የሆነ ኩሩ ኢትዮጵያዊ ማን ነው??

ይህ ችግር ደግሞ ባልተማሩት ብቻ ሳይሆን በተማርነውም ዜጎች ውስጥ በሰፊው አለ ብዬ አምናለሁ፤ ይብዛም ይነስም ሁላችንም ውስጥ ይቺ የዘረኝነት ስሜት ትኖራለች፤ ለምሳሌ ፌስቡክ ላይ ብዙ ምሳሌዎች አሉ፤ ስም መጥቀስ አልፈልግም፤ ችግራችን ከግለሰቦች ጋር ሳይሆን ከአስተሳሰብ ጋር ስለሆነ፡፡ ከስምንት አመት በፊት ኦባማ የአሜሪካን ፕሬዘዳንት ሆኖ ሲመረጥ ብዙዎች ጥቁር አፍሪካዊያን እጅግ ተደስተን ነበረ፤ ኦባማ ሲመረጥ ብዙ አፍሪካውያን ለአፍሪካ በጎ ተግባራትን ተስፋ አድርገን ነበረ፤ እውነታው ግን የአሜሪካን መሪ ለአፍሪካ በጎ ለማድረግ ጥቁር መሆን የለበትም፤ በተጨማሪም የአሜሪካን የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ መንግስት በተቀየረ ቁጥር የሚቀያየር ሳይሆን በተለያዩ ጊዜያት የሚመረጡት መንግስታትም የሀገራቸውን ብሄራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ይሰራሉ፤ ስለሆነም ኦባማ ጥቁር ስለሆነና የአፍሪካዊ ደም ስላለበት የአሜሪካንን ሀገራዊ ጥቅም ችላ ብሎ ለአፍሪካ በጎ ነገር ያደርጋል ብሎ ማሰብ ትልቅ ስህተት ነው፤ የሀሳቡ ምንጭም ስልጣን መያዝን ለአንድ ወገን ማዳላት አድርገን ስለምንጠብቅ ነው፤ ከሀገራችን ታሪክና አሁን ካለው ተጨባጭ ሁኔታ የምንገነዘበው፣ የፖለቲካ ስልጣን ለተወሰኑ ወገኖች አላስፈላጊ ጥቅም የሚሰጥበት አጋጣሚ መሆኑን ነው፤ ይህ አይነቱ አሰራር ደግሞ ሀገራዊ ጥቅማችንን የሚጎዳና አብዛኛውን ህዝብ ለማገልገል አመቺ አሰራር አይደለም፤  ስለሆነም ትቁር አፍሪካዊ የአሜሪካን ፕሬዘዳንት ሆኖ ሲመረጥ ደስተኛ ብንሆንም ከደስታችን ጀርባ ግን ብዙም ባትሆን ትንሽዬ የዘረኝነት ስሜት መኖሩን መካድ የለብንም፤  ውድ የሀገሬ ልጆች፣ ችግሮቻችንን በዘላቂ ሁኔታ ለመፍታት ሁላችንም ራሳችንን ከዘረኝነት ነፃ አድርገን ስለእውነትና ስለሰብአዊነት ማሰብ ያለብን ይመስለኛል፡፡ ዛሬ ሀገራችንን ግራ እያጋባ ያለው ጭፍን የሆነ የዘረኝነት ስሜት ነው፤ ሁሉም ራሱን መፈተሽ አለበት፡፡ ከሁሉ በላይ የሚያሳዝነው ደግሞ የዘረኝነቱ ስሜት ሀገራዊ አንድነታችንን እያዳከመ ለጋራ ጥቅም ሳይሆን አጋጣሚዎችን ተጠቅመው ጥላቻ ለሚሰብኩና የራሳቸውን ኪስ ለመሙላት ለሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች አመቺ ሁኔታ መፈጠሩ ነው፡፡ የማይገባ ጥቅም ማግበስበስ የሀገራችንን ህዝቦች የወደፊት ተስፋ እንዳያጨልም የተቻለንን ማድረግ አለብን፡፡ እኔም፣ አንተም፣ አንቺም፣ ሁላችንም በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የችግሩ ባለቤቶች መሆናችንን መካድ የለብንም፡፡

በየትኛውም የሀገራችን ክፍል ለሚነሱት ችግሮች የሰከነና ሚዛናዊ መፍትሄ በመፈለግ የተሻለ ሁኔታ ለልጆቻችን እንዲፈጠር መስራት አለብን፤ በስሜታዊነትና በመገዳደል የትም መድረስ አንችልም፤ መገዳደል መፍትሄ ቢሆን በሀገራችን ታሪክ በጦርነት የሞቱ ወጣቶች ብዛት በቂ መሆን ነበረበት፤ ነገር ግን ችግሮቹ በዘላቂነት አልተፈቱም፤ ዛሬም ብዙ ችግሮች እያየን ነው፤ ለዚህ ደግሞ ብቸኛው መፍትሄ እኛው የሀገሪቱ ዜጎች ነን፡፡

ብዙ ብሄረሰቦች የሚኖሩበት ሀገር በአለም ኢትዮጵያ ብቻ አይደለችም፤ መልካም አስተዳደርና ተጠያቂነት ካለ ግን ብዝሀነት ያንን ያህል ችግር አይደለም፤ ለምሳሌ አሜሪካን ብንወስድ የአለማችን ህዝቦች ስብስብ ናት፣ ሁሉም ግን ከሞላ ጎደል በሰላም ይኖራሉ፤ እንደ ህንድ፣ ጋና ናይጄሪያ ኬኒያ የመሳሰሉትን የሀገራትንም ብንመለከት በብዙህነት ከኛ በተሻለ እድገትና ዲሞክራሲ የሚኖሩ ናቸው፤ ስለሆነም ሀገራችን ሁሉም በእኩልነት የሚኖሩባት እንድትሆን ሁሉንም ሰብአዊነትን መሰረት አድርገን በአንድነት ለዘላቂ ሰላማችን መስራት አለብን፡፡ ከጎሮቤት ሀገሮች ለምሳሌ ከየመን፤ ከሊቢያ፣ ከሴሪያ፣ ከኢራቅ፣ ከደቡብ ሱዳን ወዘተ መማር አለብን፡፡

እርኩስ መንፈስና እርኩስ አስተሳሰብ በተላበሰ በስሜታዊነት ተነሳስተን ምንም ሰላም ማምጣት አንችልም፤ ይልቅ ተባብረን መንግስት ሀገሪቱ ወደተሻለደረጃ መድረስ እንድትችል የፖለቲካ ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት እንዲችል ጫና እናድርግ፤ ይህ ደግሞ የአንድ ትውልድ ስራ ብቻም አይደለም፤ በየጊዜ ችግሮች ሊከሰቱ ስለሚችሉ ተከታታይ የሆነ ሰላማዊ ሂደቶችን ማስፈን አለብን፡፡

አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ እጅግ ብዙ ውሸትና ሙስና በሀገራችን ህዝቦች ዘንድ እየተስፋፋ ነው፡፡ ቆም ብለን አርቀን ማሰብ አለብን፤ የዚህ ሁሉ ጭፍን አካሄዳችን የመጀመሪያው ተጎጂ ደሀው የሀገራችን ህዝብ መሆኑንም ልብ ማለት አለብን፡፡

 

የፖሊስ ሰራዊት የደሀ ልጆች ናቸው፤ ወታደሮቻችን ለኛ ሰላም ህይወታቸውን ለመስጠት የተዘጋጁት የደሀ ልጆ ናቸው፤ በሙስና ለሚፈጠረው ችግርም የመጀመሪያ ሰለባ የደሀ ልጆች ናቸው፡፡ ሁሉም ቆም ብሎ ማሰብና በማሰተዋል መኖር አለበት፤ ሰላም የአንድ ወገን ስራ ብቻ አይደለም፤ በሰላም አብሮ መኖርም አንዱ ለሌላው በበጎ አድራጎት የሚሰጠው ሳይሆን ለጋራ ጥቅም ተብሎ የሚደረግ ነው፤ ለምሳሌ የጀርመኖችንና የእንግሊዝን እንዲሁም የአሜሪካንንና የጃፓንን የቀድሞና የአሁን ታሪክ ልብ እንበል፡፡

ቋንቋና ብሄረሰብ

እኔና አንዲት የአሜሪካን ዜጋ ለስራ ወደደቡብ ኢትዮጵያ ሄድን፤ እኔም የህዝቡን ቋንቋ መናገር አልችልም፤ በራሴ ሀገር፣ ከራሴ ሀገር አርሶ አደሮች ጋር በአስተርጓሚ መግባባት እንዴት ያሳፍራል?? መቼም የደሃ ሀገር ገበሬዎች ሆነው ነው እንጂ የፈረንሳይ ወይም የጀርመን ገበሬዎችን በእንግሊዘኛ እናስተምራችሁ ቢባል ሊፈጠር የሚችለውን ችግር አስቡት አስቲ፤ እጅግ አስፈላጊ የሆነ ትምህርት ለገበሬዎቹ እያስተማርን የግድ አስተርጓሚ እንጠቀማለን፤ ለ10 ወይም ለ30 አመት ድረስ ክህብረተሰቡ ጋር ኖሮ የዛን አከባቢ ነዋሪ አርሶአደር ቋንቋ መናገር የማይችል የሀገሬ ዜጋም ይኖራል፤ አሜሪካን ሀገር ያንን ያህል ጊዜ ኖሮ እንግሊዘኛ አለመናገር ማለት ነው፡፡ ያሳፍራል፤ እኔም በራሴ እያፈርኩ ነው፤ ቋንቋ የደካሞች አቋራጭ መጠቀሚያ መሆኑ ቢያሳዝንም ገበሬዎቹ ግን ከራሳቸው ሀገር ዜጋ በራሳቸው ቋንቋ የመግባባት መብት አላቸው፡፡ ምን ዋጋ አለው፤ ፖለቲካውና አድልዎውን ስንጨምርበት አንድነትም ልዩነትም፤ ሁለቱም ዋጋ ያጣሉ፤ ዋጋ አሳጣናቸው፤ ለኛ የሚበጀው የቱ ነው ብለን ግራ እንድንጋባ ሆነ፤ ምክንያቱም ሁሉ ነገራችን አርቆ ማሰብና ሚዛናዊነት ስለሚጎድለው፤ ጨፍነን ነገሮችን ስለምናደርግ፤ ራሳችንን ለመጠየቅ ዝግጁ ስላልሆንን፤ ከራሳችን ይልቅ ሌሎች ውስጥ ጉድለት ስለምንፈልግ፤ ለዛ ነው በ21ኛው ክፍለ ዘመን እንደጋርዮሽ ዘመን የምግብና የውሃ እንዲሁም የመጠለያ ጥያቄ ሀገር እስከመካድ ድረስ የሚያደርሰን፡፡

ራሳችንን መጠየቅ አለብን፤ ምን ያህል ነው ራሳችንን የምናከብረው፤ ምን ያህልስ ነው ሀገራችንንና ህዝባችንን የምናከብረው፤ ስራ ፍለጋ ሄጄ የአከባቢውን ቋንቋ መናገር መቻል አለብህ ስለተባልኩ፤ ኡኡኡኡአ ተበደልኩ በሀገሬ ላይ ኡኡኡአ እንላለን፤ አዎ እና መጮሁን ስለምንችልበት፤ ለዛ ለደሃውስ ገበሬ ማን ይጩህለት፤ ማንስ ይፃፍለት፤ በራሱ ሀገር፣ ከራሱ ሀገር የተማሩ ዜጎች ጋር በአስተርጓሚ ሲግባባ፤ የራሱን ሀገር የተማሩ ዜጎች እንደውጪ ሀገር ዜጎች ሲመለከታቸው፤ ለደሀውስ ገበሬ ማን ኡኡኡ ይበልለት?

ዛሬ በአዲስ አበባ የቻይና ቋንቋ ትምህርት ከፍሎ መማር የተለመደ እየሆነ ነው፤ ግን ለምን? ቻይንኛ ያንን ያህል ከፍለን መማር ያስፈለገበት ምክንያት ለሀገራቸን ብሄራዊ ጥቅም ብለን ነው? መልሱ ግልጽ ነው፤ የስራ እድልን ለመፍጠር ነው፤ ስለሆነም ሶማሊ ክልል ሄዶ ለመስራት ግን ሶማሊኛ መማር እንደሚያስፈልገን ቀድመን አውቀን መዘጋጀት ነበረብን፤ ይህ ማለት አማርኛ በሶማሊ ክልል ለስራ አይበቃም ማለቴ አይደለም፤ ነገር ግን ሁሉም የሶማሊ ማህበረሰብ አማርኛ ተናጋሪ ስላልሆነ ባለሙያዊ ሶማሊኛ፣ የአከባቢው ሰው ደግሞ አማርኛ እንደተጨማሪ ቋንቋ ቢማሩ ሰጥቶ መቀበል ይሆናል ማለት ነው፡፡ ሶማሊ ክልል የስራ እድል እንዲኖረው የሚፈልግ የሀገራችን ዜጋ ከአማርኛ በተጨማሪ ሶማሊኛ ተናጋሪ ቢሆን እጅግ ደስ ይላል፤ እንግሊዘኛ የአለም መግባቢያ ቢሆንም ፈረንሳይ ሀገር ሄዶ ሰርቶ ለመኖር ግን ፈረንሳይኛ መናገር የግድ ነው፤ ይህ ማለት ደግሞ ፈረንሳይ ሀገር የሚኖር ሰው እንግሊዘኛ መናገር የለበትም ማለት አይደለም፤ በተመሳሳይ ሁኔታ ሶማሊ ክልል ለመስራት የሚሄድ ወጣት ሶማሊኛ ማወቁ የሀገራችንን አንድነት ያጠናክራል እንጂ አያዳክምም፤ ይህንን መጥቀስ ያስፈለገበት ምክንያት በአሁኑ ጊዜ በተለይ ከክልል ቋንቋ ጋር ተያይዞ የሀገራችን አንድነት እየደበዘዘ ነው የሚል በተደጋጋሚ የሚሰማ አስተያየት አለ፤ ቢሆንም ብዞዎቻችን በሀገራችን ከሚነገሩት ቋንቋዎች አንዱን ብቻ ነው የምንናገረው፤ ነገር ግን ከአማርኛ በተጨማሪ ሁለት ወይም ሶስት ቋንቋ መናገር ብንችል

በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ተዘዋውረን የመስራት እድላችን ከፍ ይላል፤ በተለያዩ የአለማችን ክፍሎች በስራ ተዘዋውሬ ያየሁትም ብዙ ጊዜ ሰዎች ቋንቋቸውን ስንናገርላቸው ደስ ይላቸዋል፤ ዴንማርክ ሀገር እንግሊዘኛ መናገር እየቻሉ ከውጪ የመጡ ዜጎች በራሳቸው የዴኒሽ ቋንቋ  ደስ ይላቸዋል፡፡ የአንድን ማህበረሰብ ቋንቋ መናገርም ለራሳችን የስራ እድልና የቀን ተቀን ህይወትን ቀለል ከማድረጉ በላይ ለዛ ማህበረሰብ ያልንን ክብር ያሳያል፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያዊ ሆኜ አማርኛ ብቻ፣ ወይም ኦሮምኛ ብቻ፣ ወይም ትግርኛ ብቻ መናገር በቂ ነው ብለን ማሰብ ትልቅ ስህተት መሆኑን መገንዘብ አለብን፡፡ አማርኛ መናገር የማይችልን ወጣት አማራ ክልል ሄዶ እንዲሰራ መጠበቅ ስህተት ነው፤ በተመሳሳይ ሁኔታ ትግርኛ መናገር የማይችል ዜጋ ትግራይ ክልል በቀላሉ ሰርቶ እንዲኖር መጠበቅ ስህተት ነው፤ ኦሮምኛ ብቻ መናገር የሚችል ወጣት ሶማሊ ክልል ሄዶ ሰርቶ እንዲኖር መጠበቅም ስህተት ነው፤ የሳይንስ እውቀት ብቻ በቂ አይደለም፤ ማህበረሰብንም ማወቅ ያስፈልጋል፤ ማህበረሰብን ማወቅ ማለት ደግሞ የዛን ማህበረሰብ ቋንቋ ከመናገር ይጀምራል፡፡

አሜሪካን ሀገር የሚኖር ሰውም ከእንግሊዘኛ በተጨማሪ እስፓኒሽ ቢናገር የስራ እድሉ ይጨምራል፡፡ ዴንማርክ ሀገርም ቢሆን ከሀገሩ ቋንቋ በተጨማሪ እንግሊዘኛ መናገር የስራ እድልን ይጨምራል፤ ለሁሉም አለማችን ወይም ሀገራን በአንድ ቋንቋ ብቻ በቀላሉ የምንኖርባት ቦታ አይደለችም፤ ይልቅ ራስን ብቁ አድርጎ መገኘት ነው፡፡ የሀገራችን ችግርም የቋንቋ ብዛት ሳይሆን ሰዎች ስለቋንቋ ያለን ግንዛቤ ጥቂት አለመሆኑ ነው፤ የቻይናን ቋንቋ ከፍለን ለመማር ተነሳሽነት ካለን፣ ሶማሊኛም ከፍለን ብንማር ጉዳት የለውም፣ ይልቅ እጅግ ይጠቅማል፡፡ እናውቃለን፤ ቻይንኛ መማር ብዙ ገንዘብ ብንከፍልለትም ጥሩ ስራ ያሰገኛል፤ ከገንዘብ ያለፈ ምክንያት ግን ሊኖረን ይገባል፤ ሀገራዊ ጥቅምና የህዝብ ክብር!

ሰሞኑን አዲስ አበባ ነበርኩ፤ አንዱ ሰፈር የቋንቋ ትምህርት ቤት ማስታወቂያ አየሁ፤ ሁሉም ቋንቋዎች የውጪ ሀገር ናቸው፤ ቻይንኛ፣ ጀርመንኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ ስፓኒሽ…. አንድ የውጪ ዜጋ ወደሀገራችን ሲመጣ ቀደም ብሎ አማርኛ መማር ይፈልጋል፤ የሚሰራው ኦሮሚያ ውስጥ ከሆነ ኦሮምኛ መማር ይጀምራል፣ የራሳችን ዜጋ ግን ከአዲስ አበባ ወደመቀሌ ለስራ ቢመደብ የአከባቢውን ቋንቋ ለመማር ብዙም ፍጎት አያሳይም፣ ለመማር ቢፈልግም ትምህርት ቤት የለም፡፡ እኔ 5 አመት ዴንማርክ ስኖር የነሱን ቋንቋ ለምጄ መጣሁ፤ 10 አመት ሀዋሳ ስኖር ግን ሲዳምኛ ለመማር አልቻልኩም፤ መማር ብፈልግም ትምህርት ቤቱ የለም፡፡ የአለማችን የቋንቋ ልዩነት ታሪካዊ አመጣጡም ለበጎ ባይሆንም፣ አሁን ባለንበት ጊዜ ግን ቋንቋ ማንነትና ባህል ነው፤ ስለሆነም በሰላም አብረን ለመኖር በተቻለ መጠን አንዳችን የሌላውን ቋንቋ ብንማር የራሳችንንም ለሌሎች ለማስተማር ብንሞክር ቆንጆ ነው፡፡ ካልሆነ ግን አንድነታችን ጉድለቱን ጠብቆ ይቆያል ማለት ነው፡፡ እንደመፍትሄ በሀገራችን ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች በምርጫ ሁለት ወይም ሶስት ተጨማሪ አዳዲስ ቋንቋ እንዲማሩ ቢደረግ ቆንጆ ይመስለኛል፡፡ የወላይትኛ ቋንቋ መናገር ብችል ከወላይታው ጋር ብንነጋገርበት ደስታን ይጨምራል፡፡ ወላይታውም የሱን መግባቢያ ለመማር እንደምፈልግ ሲረዳ መቀራረባችን ይጨምራል፡፡ እኔ አውሮፓ ቆይቼ የተማርኩት ይህንን ነው፡፡ ብዙ ቋንቋ መናገር መቻል እንደ ቆንጆ ነገር ነው የሚታየው፡፡

የኛ ሀገር የውጪ ሀገራትን ቋንቋ ገንዘባችንን ከፍለን እየተማርን ነው፤ የሀረጋርንን ግን ከወዳጆቻችን መማር እንችላለን፤ ዶርም ውስጥ አብረውን ከሚማሩት ተማሪዎች መማር እንችላለን፤ ዋናው ፍላጎት ነው፤  ሀገራችንም ብዙ ቋንቋ ስለሚነገርባት የሀገራችንም ወጣቶች ከሶስት በላይ ቋንቋ መናገር እንዲችሉ ማስተማር ያስፈልጋል፡፡

የቻይንኛ እውቀትም ቆንጆ ነው፡፡ ቅድሚያውን ግን ለራሳችን ብንሰጥ ባይ ነኝ፡፡ ሲዳማ ውስጥ መስራት ስናስብ ሲዳምኛ መማር አለብን፤ አማራ ውስጥ መስራት ስናስብ አማርኛ መማር አለብን፤ ሶማሊ ውስጥ መስራት ስናስብ ሶማልኛ መማር አለብን፤ ነገር ግን የኦሮምኛ ተናጋሪ ሆኜ ሶማሊ ክልል ውስጥ በኦሮምና ብቻ መስራትን ማሰብ ሞኝነት ነው፤ ይልቅ ሶማሊ ክልል ለመስራት ሶማሊኛና አማርኛ የግድ መሆኑን ማወቅ አለብን፤ እንግሊዘኛም ማወቅ ደግሞ እዛው ሶማሊ ክልል ከውጪ ሀገር ዜጎች ጋር ለመስራት ቀላሉ መንገድ ነው፡፡

ልማት

አሁንም ስለብሄረሰብ ፖለቲካ ልፅፍ ነው፡፡ ሀገራችን ከሰባ በላይ ብሄረሰቦች እንዳሉ እናወቃለን፡፡ እነኚህ ብሄረሰቦች ሁሉም መቶ በመቶ እኩል የእድገት ደረጃ፣ እኩል የልማት ተጠቀሚ፣ እኩል የህዝብ ብዛት፣ እኩል የተፈጥሮ ሀብት፣ እኩል የተማረ የሰው ሀይል ወዘተ አላቸው ብዬ ብከራከር ከእውነት የራቀ እንደሆነ ግልፅ ነው፡፡ በብሄረሰቦቹ መካከል ብዙ ልዩነቶች አሉ፡፡ ልዩነቶቹ ሊኖሩ የቻሉት አንድም ከተፈጥሮ ሀብትና አንድም ከመሀል ሀገር ካላቸው ርቀት በተጨማሪም ከተማረ የሰው ሀብት ቁጥር ወዘተ ጋር ይገናኛሉ፡፡ ከልዩነቶቹ መካከልም የተወሰኑት ሰው ሰራሽ ናቸው፡፡ ታዲያ ሰው ሰራሽ የሆኑት ችግሮች ሆን ተብሎ

የአንዱ ብሄረሰብ ተወላጆች በሙሉ በሌላው ላይ ያደረሱት ሳይሆን በዋናነት በፖለቲካ ስልጣን ላይ የነበሩ የተወሰኑ ግለሰቦች አርቆ አሳቢነት የጎደለው ውሳኔ ውጤቶች ናቸው፡፡ ምክንያቱም ከታሪካችን እንደምናነበው የሀገራችን መሪዎች የፖለቲካ ስልጣን ላይ ሲወጡ በዋናነት ህዝቡን ለማገልገል ሳይሆን ህዝብን በመጠቀም የህዝብን ንብረት፣የህዝብን ጉልበትና የህዝብን ደም ጭምር ለራሳቸውና በዙሪየቸው ላሉ ጥቂት አድርባዮችና ወሬ አቀባዮች ሲጠቀሙ ነው የኖሩት፤ ለዚህ ደግሞ ጥሩ ማሳያ የሚሆነን የትኛውም የሀገራችን ብሄረሰብ ወይም ክልል ከሌላው በበለጠ የበለፀገ አለመኖሩን ነው፡፡ ለምሳሌ ወደሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ሄደን ስንጎበኝ ከደቡቡና ከምስራቁ እኩል፣ አልፎ አልፎም በባሰ ሁኔታ በድህነት ውስጥ የሚኖር ደሀ ህዝብ እናገኛለን፡፡ ታዲያ በሰሜን የሀገራችን ክፍል ያሉት ብሄረሰቦች የደቡቡን ወይም ምስራቅ ያሉት ብሄረሰቦች ለሰሜኑ ወዘተ ድህነት ተጠያቂ ናቸው ብለን ለማለት  ያህል የተጨበጠ መረጃ የለንም፡፡ አንድ የሀገር መሪ ከሆነ ብሄረሰብ መጥቶ ስልጣን ስለያዘና መሆን የማይገባቸውን ድርጊቶች አድርጎ ካለፈ ያ መንግስት የመጣበትን ብሄረሰብ ተወላጆች በሙሉ በጅምላ መኮነን እንጭጭ አስተሳሰብ ይመስለኛል፡፡

አሁን ወዳለንበት ሁኔታ ስንመጣ፤ በተለይ በቅርብ ጊዜ አንዱን ብሄረሰብ በተለየ ሁኔታ ተጎጂ ወይም ተጠቃሚ የሚያስመስሉ ሀሳቦች በዚሁ ፌስቡክ ላይ እየበዙ ነው፡፡  ከሰባ ብሄረሰቦች ውስጥ የራሳችንን ብሄር ብቻ አውጥተን የዛ ብሄር መብት አስከባሪ ለመሆን ስንወስን የሌላ ብሄረሰብ ተወላጆች እየታዘቡን እንደሆነ መረዳት አለብን፡፡ ስለእውነት የሚናገር ሰው የአንድ ቤሀረሰብን አላግባብ መጠቀም ወይም መጎዳት ለማውገዝ የዛ ብሄረሰብ ተወላጅ መሆኑ የግድ አይደለም፤ አንድ ግለሰብ ወይም ጥቂት ግለሰቦች ሙስና ሊሰሩ ይችላሉ፤ ብሄረሰቡ በሙሉ ሙስና እየሰራ ነው ማለት ግን ስህተት ነው፡፡ የተወሰኑ ግለሰቦች አንድን ብሄረሰብ ለይተውም የልማት ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚፈልጉ መካድ የለብንም፤ ያንን አይነቱን ድርጊት በመፈፀም ሌቦች ሌብነታቸውን በህዝብ ለማሳበብ የሚጠቀሙት ስልት ነው፡፡ ምክንያቱም ህዝብ የሚገባውን እንጂ የስርቆት ልማት ስለማይፈልግ ነው፡፡ አንድ ሀገር ወይም አከባቢ ልማት ይገባዋል፤ አከባቢው ወይም ሀገሩ መልማት ያለበት ግን በስርቆት ሳይሆን በራሱ ጥረት ከሌሎች ጋር በህብረት በመሆን በመስራት ነው፡፡ ነገር ግን ህዝባችን ሌብነትን የሚያበረታታበትም አጋጣሚ አለ፤ ለምሳሌ ቻይናዎች መንገድ ስራ ፕሮጀክት ውስጥ የሚሰራ ወዳጄ ብዙ ግልፅ ሌብነት መኖሩን ነግሮኛል፤ የቻይና ስለሆነ መስረቅ ግን ለሌላ ስርቆት የሚለይበት ነገር የለም፤ የሌሎችን ስረቅ የወንድምህን አትስረቅ ተብሎ የተፃፈ የለም፤ ሌብነት ሌብነት ነው፤ ለሁሉም ደካማ መሪዎች ሰርቀው ከአንዱ ወደሌላው የሚወስዱት ድርጊት የመሪዎቹ ጥፋት እንጂ የህዝቡ እንዳልሆነ መረዳት አለብን፡፡

እውነት ነው የብሄረሰብ እኩልነት ያስፈልጋል፤ ነገር ግን የሀገራችንን ተጨባጭ ሁኔታ ማሰብ አለብን፡፡ ሁሉ ልጅ በእናትና በአባት ቋንቋው ቢማር በጣም ደስ ይለኛል፡፡ ማንኛውም ገበሬ በአስተርጓሚ የግብርና ትምህርት ባይነገረው በጣም ደስ ይለኛል፡፡ ያ መሆን ካለበት ደግሞ ለሁሉም በራሱ ቋንቋ ትምህርትቤት መከፈት አለበት፡፡ ትምህርት ቤት ለመክፈት መምህራን ቀድመው መሰልጠን አለባቸው፡፡ የቤተመፅሀፍት ቀድመው መኖር አለባቸው፡ ቴሌቪዢንም እንደዛው፡፡ ጋዜጠኞች መሰልጠን አለባቸወ፤ያ ሁሉ ቀስ በቀስ ሊደረስበት ይችላል፡፡ ይህ ሁሉ ካልሆነ ለአንዱ ብሄረሰብ ብቻ ሀብት ከሰማይ እንደዝናብ አይዘንብም፤ አርቆ አስቦ ቀስ በቀስ ሁሉንም ማዳረስ ይቻላል፡፡ ዋናው መሰረታዊ ጉዳይ አንድን አከባቢ ወይም ወረዳ ወይም ሀገር ወደዘላቂ ልማት ለማድረስ ከራሳቸው ጥቅም በፊት የህዝቡን ጥቅም አስቀድመው የሚሰሩ ዜጎችና መሪዎች ያስፈልጋሉ፡፡ እስካሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ግን ህዝብን የግል መጠቀሚያ የሚያደርጉ ዜጎቻችን ብዙ ናቸው፡፡ የወደፊት ስራችን መሆን ያለበት ለህዝብ ታማኝ የሆኑ ዜጎችን ማብዛት ነው፡፡

እስካሁን በአማርኛ፣ በሶማሊኛ፣ በትግርኛ፣ በኦሮምኛ፣ በሀረሪ፣ በአፋርኛ (ሌሎቹን እርግጠኛ አይደለሁም) የቴልቪዢን ፕሮግራሞች አሉ፡፡ በራስ ቋንቋ መማርም ተጀምሯል፡፡ በንፁህ ልብ ስናየው ቀስ በቀስ ሁሉም የራሱን ያገኛል፡፡ ስለሆነም ተበደልኩ የሚል ይጠፋል ብሎ ማሰብ ይቻላል፡፡ ታዲያ ሁሉም የየራሱን እንዲያገኝ የሚደረገው ጥረት አንድነታችንን እንዳያደበዝዝ መጠንቀቅ አለብን፤  የኛ ችግር ልማት ሊመጣ የሚችለው የራሳችን ብሄረሰብ ተወላጅ ስልጣን ሲይዝ ነው ብለን ማሰባችን ላይ ነው፡፡

ይህንን እንድናስብ ያደረገን ደግሞ አድልዎ የበዛበት የስልጣን አጠቃቀምን በየጊዜው ስለምናይ ነው፤ መሪዎቻችን ህዝቡን በእኩል ቢያገለግሉ ይህ ሁሉ ቀውስ ባልተፈጠረ ነበረ፤ አንድ መሪ ስልጣን ሲይዝ ምንም ያልተማረ ወንድሙ ወይም ዘመኑ ባለስልጣን ይሆናል፤ ይህ በሀገራችን በሰፊው የሚታይ እውነታ ነው፤ የባለስልጣን ዘመድ ወይም ወገን መሆን የሚመጣው ጥቅም አለ፤ በከተሞች ጭምር ኮብል እስቶን ሲነጠፍ መጀመሪያ የሚሰጠው የባለስልጣናት ሰፈር መሆኑን ማህበረሰቡ በሰፊው ሲወያይ እሰማለሁ፤ ይህ ነው እንጭጭ አሰራር ማለት፣ ይህ ደግሞ የመሪዎቹን የአስተሳሰብ ብስለት ደራጃ ያሳያል፡፡

እኔ የተወለድኩባት ከተማ አርሲ ሴሩና በአጠቃላይ የአርሲ ዞን በሀገራችን ካሉ ዞኖች በምርት ከፍተኛ ከሚባሉት ይጠቀሳል፤ እንዲሁም አርሲ ዞን ከአዲስ አበባ በሁለት ሰአት ርቀት ላይ የሚገኝ መሀል ሀገር ነው፤ የመሰረተ ልማቱ እደገት ግን እጅግ የዘገየ ነው ማለት ይቻላል፤ በተለይ የከተሞች እድገትና የመንገድን ሁኔታ ብንለመከት፤ አርሲ ሮቤን በምሳሌ ብንወስድ ብዙ የገጠር ከተሞችን የምታገኛኝ የሻሸመኔ አይነት ከተማ ናት፤ የእድገት ደረጃዋ ግን በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ ታዲያ ከወዳጆቼና ህብረተሰቡም አልፎ አልፎ ሲወያይ ስሰማ አርሲ ዞን እንደሌላው የሀገራችን ዞኖች ያላደገበት ምክንያት ከአርሲ ዞን የወጡ ብዙ ሚኒስተሮች ስለሌሉ ነው ይባላል፤ ይህም እስካሁን ስልጣን ላይ የነበሩና አሁንም ያሉት ባለስልጣናት የሚያደርጉትን አድልዎ ከመረዳት ይመስለኛል፡፡

ሀገራችን የተፈጥሮ ሀብት ሀብታም ናት፤ የሀገሪቱ መሰረታዊ ድህነት በመሪዎች ነው፤ ሀገራችን በፖለቲካ መሪዎች ደሀ ናት፤ በአስተሳሰብ ሩቁ አስበው ከራሳቸው ጥቅም በፊት የህዝብን ጥቅም የሚስቀድሙ የፖለቲካ መሪዎች እንደሚያስፈልጉን በተደጋጋሚ መጠቀስ ያለበት ጉዳይ ነው፡፡

መሀይምነት፣የህዝብ ብዛት፣ ጎጂ ባህል ፣የቴክኖሎጂ አለመኖር፣ ያለውንም ቴክኖሎጂ በትክክል መጠቀም አለመቻል፤ ከሁሉ በላይ ደግሞ ሙስና፣ ወገንተኝነት፣ ለህዝብና ለሀላፊነት ታማኝ አለመሆን፣ ለድህነታችን እነኚህን ነገሮች መዘርዘር ይቻላል፡፡ የህዝባችንን ችግሮች ጠለቅ ብለን ብንመለከ፤ ከእምነት ተቋማትም ጭምር ይሰረቃል፡፡ እንግዲህ ሰው ከራሱ ሀይማኖት ቤት ከሰረቀ፣ በተለይ ደግሞ የዛ ሀይማኖት መሪ ሆኖ እያገለገለ ተመልሶ የሚሰርቅ ከሆነ፣ ይህ የአስተሳሰብ ድህነት ማለት ይህ አይደለም? ስለሆነም እባካቹ ችግሮቻችንን በጥልቀት እንመርምር፡፡

የኛ ዲያስፖራዎች

በውጪ የሚኖሩ የሀገራችን ዜጎች እድሉን አግኝተው ለመሄድ ሲወስኑ አብዛኞቹ ሰርተው ራሳቸውንና ደሀ ወገናቸውን ለመለወጥ የሄዱ ናቸው፤ አንዳንዶቹ ለትምህርት፣ ሌሎቹ ደግሞ በፖለቲካ ስደት፤ ቢሆንም በተለይ ሰርተው ገንዘብ ለማግኘት የሚሰደዱት ወጣቶች ውጪ ሀገር እንደደረሱ ስራ በቀላሉ ላያገኙ ይችላሉ፤ ስራ አግኝተው ገንዘብ ለወላጆቻቸውና ለዘመዶች ሲልኩ ሀገር ቤት ያለው ዘመድ ውጪ ሀገር ያለውን ችግር አይረዳም፤ ከውጪ የሚላክ ገንዘብ የሚያልቅ አይመስልም፡፡ ልጅ ውጪ ያላቸው ወላጆች ማህበረሰባችን ዘንድ ለየት ያለ ክብርም ይሰጣቸዋል፡፡ምክንቱም ልጆቻቸው ብዙ ብር ይልኩላቸዋል የሚል እምነት ስላለ፤ ለብድርም፣ ለእርዳታም፣ ውጪ ሀገር ልጆች ላቸው ወላጆች ጋር መሄድ የተለመደ ነው፤ ልጆቻቸው እኮ አሜሪካን ሀገር ነው የሚኖሩት ተብሎ ሲነገር ከጀርባው ብዙ ብር ይልካሉ፣ ገንዘብ አይቸግራቸውም የማለትም መልእክት አለው፡፡ ስለሆነም ውጪ ካለው ልጅ ወይም ዘመድ ገንዘብ እንዲላክ ይጠበቃል፤ ውጪ ያለውም ልጅ ይህንን በደንብ ያውቀዋል፡፡ ከ24ሰአት ውስጥም እስከ 16 ሰአት በስራ ያሳልፋል፤ የውጪ ሀገር ኑሮ ደግሞ ውድ ስለሆነ ለራስ ኑሮና ሀገር ቤት ላለው ወዳጅ ዘመድ ለሚላከው የሚበቃ ገንዘብ ለማግኘት እንቅልፍ ሳይተኛ ቀን ተለሊት ይሰራሉ በዲያስፖራው የሚኖሩ ወገኖቻችን፤  ብዙዎች ወገኖች ደግሞ ከውጪ በሚላክ ገንዘብ ጥሩ ደረጃ የደረሱ ቢሆሩም የዛኑ ያህል በውጪ ገንዘብ ህይወታቸው የተበላሸም ብዙ ናቸው፡፡

ለምሳሌ ሚስቱን ወይም ባልን ወደውጪ ልኮ ከሌላ ሰው ጋር የፍቅር ህይወት መጀመርና ከውጪ በሚላከው ገንዘብ ሁለተኛ ትዳር የሚመሰርቱ ሞኖራቸውም አይካድም፤ አርቆ ማሰብ የተሳናቸው ወገኖቻችን ብዙ ናቸው፣ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ብንወስድ ከውጪ በሚላክ ገንዘብ አደንዛዥ ነገሮችን የሚያዘወትሩ፣ በሱስ የሚለከፉና በየምሽቱ ወደጥናት ሳይሆን ወደስካርና ወደጭፈራ ቤት የሚመላለሱ ብዙ ናቸው፡፡ ውጪ ሀገር ወነድም ያለው ተማሪ በየቀኑ ጭፈራ ቤት ያመሻል፤ ውጪ ያለው ወንድሙ ግን ቀን ተለሊት ላቡን አፍስሶ ነው ብሩን የሚልከው፡፡

 

 

እዚህ ሀገር ቤት ዩኒቨርሲቲ እየተማረ ሱስ የተለማመደው ወጣት የሚገዛለትን ስልክ ተሰረቀብኝ በሚል ሰበብ ሸጦ ጫትና ሲጋራ ገዝቶ ሲያበቃ አሜሪካን ወይም ካናዳ የለውን ወድንሙን በኢሜይል ይጨቀጭቃል፤ ብር ላክልኝ፤ ስልኬ ተሰረቀ ነው ሰበቡ፤ ሁሌም ሰበብ በመደርደር ገንዘብ ማስላክ፤ በገንዘቡ ራስን መጉዳት የብዙ ወጣቶች ህወት መሆኑን እያስተዋልን ነው፤ በሀገራችን ከውጪ የሚመጣ ብር በድካም የሚገኝ የማይመስለው ብዙ ሰው ነው፡፡ መፍትሄውም፣ በውጪ የሚኖሩት ወገኖቻችን የሚልኩት ብር ምን ደረጃ እንደደረሰ በተለያየ መንገድ መከታተል አለባቸው፡፡ ለተማሪዎች ቢሆን ከሚፈለገው በላይ ገንዘብ መላክ የተማሪውን ህይወት ማበላሸት መሆኑን መገንዘብ አለብን፡፡

ይልቁንስ የኛ ዲያስፖራዎች ሀገራቸው ዘላቂ ሀብት እንዲኖራቸውና ሀገር ቤት መጥተው በገንዘባቸውና በእውቀታቸው ህዝባቸውን እንዲያገለግሉ ማበረታታት ያስፈልጋል፡፡ ውጪሀገር ያሉ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በሙሉ አቅም በፈቀደ መጠን በሀገራችን የኢንቨስትመንት ዘርፍ ውስጥ ቢሳተፉ ሀገራችን እጅግ ተጠቃሚ ነው የምትሆነው፡፡  አንድ ልብ ማለት ያለብን ጉዳይ ግን ውጪ ሀገር ስለኖረ ብቻ አንድ ኢትዮጵያዊ ሲለሀገሪቱ የስራ ፈጠራና የንግድ ሁኔት በደንብ ያውቃል ማለት አይቻለም፡፡ መሬት በነፃ ቢታደል ሁሉ ዲያስፖራ ላይጠቀመው ይችላል፤ አለመታደል ሆኖ ብዙዎቻችን ከተገችው ትንንሽ በጎ ነገር የራሳችንን የግል ጥቅም ብቻ በማባረር፤ ያገሩን ሰርዶ ባገሩ በሬ የሚባለውን የቆየ ሀሳብ ወደተግባር ሳናወርደው እንቀራለን፡፡

ውጪ ለሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የተለየ የማበረታቻ ድጋፍ ሲደረግ ከዚህ ቀደምም ሰምቻለሁ፤ ለዲያስፖራዎች መሬት በነፃ ይሰጣል ሲባል፣ አብዛኞቹ ምንም ያላቀዱለትን የኢንቨስትመንት ሀሳብ ቶሎ ቶሎ ሰርተው ወደሀገር ቤት መጥተው መሬት ይወስዱና ሽጠውት ተመልሰው ወደውጪ ሄዱ ተባለ፡፡ የኛ ነገር እንደዛ ነው፤ ያ ባይሆንማ ለምን የ100 ሚሊዮን ህዝቦች ሀገር ሆነን ደሀ እንሆን ነበረ? በአጭሩ አርቀን ማሰብ ችግራችን ነው፡፡ ሀገር ቤትም ሆነን ውጪ ሀገርም ኖረን የአስተሳሰብ ዘመናዊነትን በቀላሉ አንላበስም፤ ልብሳችንና አነጋገራችን ብቻ ይዘምንና ምግባራችን አድሮ ቃሪያ ይሆንብናል፤  የሆነ ሆኖ የወደፊቱ ጊዜ ብዙ ባለሃብቶች ብዙ ስራ ፈጣሪዎች የሚያስፈልጉበት ጊዜ ነው፤ ወደድንም ጠላንም የሀገራችንን ዘላቂ ሰማልና ልማት ማምጣት የሚችለው የራሳችን ዜጎች ብቻ ነን፤ እኛ ኢትዮጵያዊያኑ ስራ መፍጠር ባንችል የተሻለ የንግድ እውቀት ያላቸው የቻይና የህንድና የአውሮፓ ወዘተ ኢንቨስተሮች በገዛ ሀገራችን ሰርተው ይከብራሉ እየከበሩም ነው፤ ጨው ለራስሽ ስትይ ጣፍጭ ነው ነገሩ፡፡

ሁሌም ኡኡኡአ ፖለቲካ ፖለቲካ ፖለቲካ እያልን ትክክለኛውና ለሀገርና ለወገን የሚጠቅመው ስራ ሳይሰራ ችግር እያወራን እድሜያችን ማለቅ የለበትም፤ ሁላችንም የሀገራችንን ሁኔታ በቅርበት መከታተልና ለውጥም ለማምጣት ንቁ ተሳትፎ ማድረግ ያለብን ይመስለኛል፤ ሀገራችን ችላ ስንል ወይም ጥለን ስንሰደድ ደካማ የሆኑት ሰፊ ሜዳ አገኙ ማለት ነው፤ ሀገራችንንና ህዝባችንንም አደጋ ላይ፣ ራሳቸውንም አደጋ ላይ ይጥላሉ፤  የተለመደውን የድህነት ዜናም ለአለም መስጠት እንቀጥላለን፡፡ ማለባበስ ያለብን አይመስለኝም፤ ለሀገራችን ችግር ፖለቲከኞች ብቻ መፍትሄ መምጣት አይችሉም፤ ብዙ ስራ ፈጣሪ፣ ብዙ አስተማሪ፣ ብዙ ሀኪሞችም ወዘተ ያስፈልጉናል፡፡ ስደት መፍትሄ መሆን አይችልም!

ነገር ግን ውጪ ስላሉ ዜጎች ከመታሰቡ በፊት እዚሁ ሀገራችን ላሉና ስራ መፍጠር ለሚችሉ ወገኖች የሚፈለገው ማበረታቻ፣ ብድርና ቁጠባ አገልግሎት በሰፊው መመቻት አለበት የሚል እምነት አለኝ፡፡  ኢትዮጵያዊ ዲያስፖራ የየራሳችን ወንድምና እህቶች መሆናቸውንና ብዙዎቹ ሀገራችንን/ዘመዶቻቸውን፣ ወንድም እህቶቻቸውን/  በመርዳት ቀን ከለሊት የሚደክሙ መሆናቸውን መዘንጋትም የለብንም፤ ሀገራችን ቁጥር አንድ የውጪ ምንዛሬ የሚታገኘዉ ከዲያስፖራው ከሚላክ ገንዘብ መሆኑንም መርሳት የለብንም፤ ስለዚህ ለዲያስፖራው የተደረገውን ማበረታቻ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እያልን፤ ሀገር ቤት ያሉት ወገኖችም ደግሞ ተቀዳሚው ድጋፍና ማበረታታቱ ያስፈልጋቸዋል፡፡

ሀብት ምንድን ነው?

ሀብትን በሁለት ትልልቅ ክፍሎች መክፈል እንችላለን፤

  • አንደኛው የቁሳቁስ ና የገንዘብ ሀብት
  • ሁለተኛው ደግሞ የእውቀትና የማህበረሰብ ሀብት ናቸው

የቁሳቁስ ና የገንዘብ ሀብት

የተለመደው የሀብታምነት መለኪያውና ብዙው ሰው በቀላሉ የሚረዳው የገንዘብና የቁሳቁስ ሀብትን ነው፤ ለሰው ልጅ ለመኖር መሰረታዊ ከሆኑት ነገሮች ጀምሮ እንደየደረጃው ሊኖረን የሚገቡት እንደ ገንዘብ፣ ቤት፣ ልብስ፣ ምግብ፣ መኪና፣ የጤና አገልግሎት፣ ትምህርት፣ የመጠጥ ውሀ፣ መብራት፣ ስልክ ወዘተ እያልን ብዙ የሀብት መለኪያዎችን  መዘርዘር እንችላለል፡፡ እነኚህ ሀብቶችም ለህይወታችን በጣም አስፈላጊ ናቸው፤ ስለሆነም ሁላችንም ጠንክረን በመስራት ልናገኛቸው ይገባል፡፡

በርትቶ ሰርቶ በራስ ድካምና ላብ የሚገኝ ሀብት ትክክለኛ ሀብት እንደሆነ ከተስማማን በተጨባጭ በሀገራችን በየከተሞቻችንና በገጠር ቀበሌዎችም የምናስተውለው የሀብታምነት መንገዶች ምን ምን ናቸው ብለን ብንጠይቅ፣ በተለይ በመንግስት መስሪያቤቶችና በንግዱ አለም የሀብታምነት ዘዴዎች ሙስናና ማጭበርበር እንዲሁም የሌሎችን ሀብት በመቀማት የራስ እንደሆነ በመጠቀም ሀብታሞች የተባሉ ብዙ የህብረተሰባችን ክፍሎች እንዳሉ መስማማት አለብን፤ እንዲሁም የራሳቸውን ጉልበትና ጊዜ አፍስሰው ቀን ከለሊት ሰርተው ሀብታም የሆኑም መኖራቸውንም መዘንጋት የለብንም፡፡ በራሳቸው ጥረት ሀብታም የሆኑትን እያበረታታን በሌብነት፣ በሙስናና በማጭበርበር ሀብታም የሚሆኑት ደግሞ ለሀገራችን እድገት እንቅፋት ስለሆኑ፣ ለልጆቻችን ስራ አጥነት ዋና ተጠያቂ ስለሆኑ፣ በከተሞቻችን ለሚታዩት ችግሮች ዋና ተጠያቂ ስለሆኑ፣ እንደዛ አይነቱን ሀብታምነት ማበረታታት የለብንም፡፡

ችግሩንም ለማቅረፍ ትምህርት ቤቶች፣ የሀይማኖት ተቋማት፣ ወላጆች፣ ዘመድ፣ ጓደኞች፣ የስራ ባልደረቦች ሁሉ የየበኩላቸውን ሀላፊነት መወጣት አለባቸው፡፡ አንድ ሰው ሙስና ሲሰራ ወይም ሲያጭበረብር ወይም ሲሰርቅ ከህዝብ ተደብቆ አይደለም፤ ሁሉም ሰው ማወቅ ባይችልም የተወሰኑ ሰዎች ስለሌብነቱ ያውቃሉ፤ አልፎ አልፎም ተባባሪ ይሆናሉ፡፡ ነገር ግን ሀጢአት ሲደጋገም ፅድቅ ይመስላል እንደሚባለው ሙስናና ሌብነት ሲደጋገሙ ትክክለኛ አሰራር እንደሆኑ ሁላችንም እንዳንበከል ከመሰረቱ ችግሮቹን ለመቅረፍ በየደረጃው መወያየትና መፍትሄ መፈለግ አለብን፡፡

ለምሳሌ የንግዱን አለም ብንመለከተ ለገበያ የሚቀርብ የጤፍ ምርት ላይ አሸዋ በመጨመር፣ በርበሬ ላይ ቀይ አፈር በመጨመር፣ የአገልግሎት ጊዜው ያለፈ መድሀኒት በመሸጥ፣ ከሰል ውስጥ አፈር በመጨመር፣ ወተት ላይ ውሀ በመጨመር፣ ማር ላይ ስኳር በመጨመር፣ ክብደት የሚመዘንባቸውን ሚዛኖች በማሳሳት ወዘተ የሌሎችን ህይወት አደጋ ላይ በማድረግ ሀብት የሚሰበስቡ ነጋዴዎች ብዙ ናቸው፡፡

በስርቆትም የሚከብሩ ብዙ ዜጎች መኖራቸውንም መርሳት የለብንም፤  ለምሳሌ የሌሎችን መኪና እቃ በመፍታት፣ ቤት በመዝረፍ፣ ሞተር ሳክሎችና ባጃጆች በመስረቅ፣ ሱቅ በመስበር፣ ኪስ በመግባት፣ በግንባታ ስራ ሲሚንቶ በመስረቅ፣ ወይም የሚገነቡ ቤቶችን ከሚጠበቀው ደረጃ ባነሰ በመገንባት በየደረጃው ከቀላል እስከ ከባድ ስርቆት የሚሰርቁ እጅግ ብዙ ናቸው፡፡

በመንግስት መስሪያቤቶችም፣ ለውሃና ለጤና የተመደበውን በጀት በሙስና ለራ ጥቅም በማዋል፣ የተለያዩ ቢሮዎችና ግንባታዎች ሲገነቡ ለስራው ከሚያስፈልገው እጅግ ከፍ ያለ ገንዘብ በመጠየቅ ለራሳቸው ጥቅም የሚያውሉ ብዞዎች ናቸው፡፡

ስለሆነም ማህበረሰባችንና ወጣቶች ይህንን አይነቱን በማጭበርበር የሚሰበሰብ ሀብትን ማውገዝና ጥፋተኞችንም በመምከርና በማስተማር ችግሩን መቀነስ የግድ ነው፡፡ የሀይማኖት አባቶችም መጀመሪያ ራሳቸው ከሙስናና ከስርቆት ነፃ መሆን አለባቸው፤ ቀጥሎ ደግሞ በየእምነቱ ያለውን አማኞች ከስርቁትና ከማጭበርበር ራሳቸውን እንዲያርቁና እንዲፀየፉ ማስተማር ያስፈልጋል፡፡

  • ሁለተኛው ሀብት ደግሞ የእውቀትና የማህበረሰብ ሀብት ናቸው

ሁለተኛው የሀብት አይነት በሀገራችን በብዙሀኑ ህብረተሰብ ዘንድ እንደሀብት የታወቀ አይመስለኝም፤ ለምሳሌ የእውቀት ሀብት ማለት ለሰው ልጆች መኖር መሰረታዊ የሆኑትን ነገሮች በተሻለ ቴክኖሎጂ መስራት መቻል፣ እንዲሁም የተለመዱትን የማህበረሰብ ችግሮች በሳይንስና በምርምር ውጤቶች መፍታት ማለት ነው፡፡ ሌላ ምሳሌ እንውሰድ፤ ብዙዎቹ የአረብ ሀገራት የነዳጅ ሀብት አላቸው፤ ነዳጃቸውን ያገኙትም ከተፈጥሮ ነው፤ ነዳጁን ከመሬት ውስጥ አውጥቶ ለመጠቀም ግን ያንን ያህል እውቀት የላቸውም፤ እውቀቱን ከሰለጠኑት ሀገራት ይገዛሉ፤ ቴክኖሎጂዎችን ከአሜሪካንና ከአውሮፓ ይገዛሉ፤ የራሳቸውን ቴክኖሎጂ የመስራት አቅማቸው ካላቸው የተፈጥሮ ሀብት ጋር ሲወዳደር ብዙ አይደለም፡፡ ሀገራችንም በአለም ላይ ግንባር ቀደም የቡና አምራች ብትሆንም ዘመናዊ የቡና ማቀነባበሪያ መሽኖችን ከውጪ ታስገባለች፤ ነገር ግን በእድገት ከፍተኛ ደረጃ የደረሱት እነአሜሪካና አውሮፓ ትልቁ ሀብታቸው የቁሳቁስ ሀብት ሳይሆን የእውቀት ነው፤ መኪና መግዛት ነው ወይስ መኪና መስራት ነው ትልቅ እውቀት የሚፈልገው? መኪና የሚሰሩትንና አንድ መንግስት መስሪያቤት ውስጥ ሙስና ሰርተው ውድ መኪና የሚገዙትን የእውቀት ደረጃ ማወዳደር አይቻልም፤ መኪና ለመግዛት ገንዘብ ብቻ ያስፈልጋል፤ ገንዘብ ደግሞ በስርቆትም ይገኛል፤ በስርቆት መኪና መስራት ግን አይቻልም፡፡

ስለሆነም በአለማችን እጅግ ውድ የሆነውና ዘላቂ የሆነው ሀብት የዘመናዊ እውቀትና ክህሎት እንዲሁም የቀና አመለካከት  ሀብት መሆኑን ሁላችንም መረዳት አለብን፡፡ ልጆቻችንንም ሀብታም እንዲሆኑ ስናደርግ በአለማችን ታላቁን ሀብት፣ የዘመናዊ እውቀትና ክህሎት እንዲሁም የቀና አመለካከት  ሀብት እንዲያገኙ ማድረግ ያስፈልጋል፤ ምክንያቱም የቁሳቁስ ሀብት መሰረቱ አስተማማኝ አይደለም፣ በተለይ አሁን ባለንበት የ21ኛው ክፍለዘመን የቁሳቁስ ሀብት ምንም ዋስትና አልሆነም፤ ይልቁንስ የእውቀት ሀብት ነው አለማችንን እየመራ ያለው፡፡ ለምሳሌ ኢራቅን ወይም ሴሪያን እንመልከት፡፡ ሁለቱ ሀገራት በአለማችን በነዳጅ ዘይት ሀብታም ከሚባሉት ሀገራት ቀዳሚ ናቸው፤ የጦርነታቸው መነሻ ምንም ቢሆን፣ ነገር ግን ሀብታቸው ከእርስ በእርስ ጦርነት አላዳናቸውም፤ ይልቁንስ ሀብታቸውን ለጦር መሳሪያ መሸመቻና ወንድማቸውን ለመግደል ነው እየተጠቀሙበት ያሉት፤ በእርግጥ ጦርነት ጀርባ ያደጉት ሀገራት እንዳሉበት ቢታመንም ለጦርነቱ ይህንን ያህል መባባስ ዋናው ተጠያቂዎች መንግስትና ተቃዋሚ ቡድኖቹ ናቸው፡፡ በጦርነቱ የደረሰባቸው ጉዳት እጅ ያሳዝናል፤ ለሞቱትም ነብሳቸውን ይማር!

የእውቀት ሀብት ደስ የሚለው ነገር በቀላሉ አለመዘረፉ ነው፤ የእውቀት ሀብት ባለቤቱ አዋቂው ብቻ ነው፤ በአጭሩ የአንድን ማህበረሰብ ሀብት በሚገነቡት ቤቶች ውበትና በመኪናዎቹ ብዛት ብቻ መለካት ስህተት ነው ማለት ነው፤ ይልቁንስ የህዝቡን የአርቆ አሳቢነት ደረጃ መገምገምም ያሰፈልጋል፡፡ ቤቶች በስርቆት ሊገነቡ እንደሚችሉ እያየን ነው፤ ዘላቂ ሀብት ግን እውቀት ይጠይቃል፤ ህልማቸው ትልቅ የሆኑ ሀገራት ወደጨረቃና ፀሀይ ላይ ለመድረስ እየሰሩ ነው፤ እኛ ደግሞ የቱ ብሄረሰብ ከየትኛው እንደሚበልጥ መልስ ለመስጠት አእምሮአችንንና ትውልዱን እየጠየቅን ነው፤ በእውቀት ሀብት የበለፀጉት ሀገራት ለበሽታዎች መድሀኒት ሲፈልጉ እኛ ደግሞ የብሄረሰቦቻችንንና የነሉሲን የዘር ሀረግ ፍለጋ ምርምር ላይ ነን!

እንጭጭ አስተሳሰብ የበላይነትን ሲይዝ፣ የትውልዱ ህልም የሌለው ይሆንና በየጫት ቤቱ ቁጭ ብሎ ህይወቱን በጨለማ ይመለከታል፡፡ ይህ ማለት ስለብሄረሰቦች የሚጠየቁ ጥያቄዎች ምንም መሰረት የላቸውም ማለቴ አይደለም፤ ነገር ግን የ24 ሰአት ስራችንና ውይይታችን ብሄረሰቦች ተኮር ሲሆን ግን ስህተት ነው፡፡ ድህነት ከመሰረቱ ካልተነቀለ፣ ክፍፍላችንና ልዩነታችን ብሄረሰብ ደረጃ መሆኑ ቀርቶ ቤተሰብ ድረስ የሚወርድ ይመስለኛል፤ መፍትሄው ከፖለቲካ መሪዎች ይጀምርና ቤተሰብና ግለሰቦች ጋር ይደርሳል፤ ፖለቲከኛ ብቻውን ለውጥ ማምጣት አይችልም፤ የትውልድን አእምሮና አስተሳሰብ ወደበጎውና ዘላቂ ህልም እንዲኖረው መንገድ የሚያሳዩ ልሂቃን ያስፈልጉናል፡፡ በበጎ ስራቸው የተመሰገኑ፣ እምነታቸውን በስራ የሚያሳዩን አባቶችና እናቶች ስፈልጉናል፡፡

አለማችን በዘፈቀደ እየኖሩ አሸናፊ የሚሆኑባት ምድር አይደለችም፤ እኛ ቀና አስተሳሰብ ቢኖረን፣ ሀገራችን በተፈጥሮ ሀብት የታደለች ናት፣ ሀብቱን ለዘቂ ልማት ለመጠቀም ምሳሌ መሆን የሚችሉ ዜጎች ያስፈልጉናል፤ ወጣቱ በአግባቡ የሚመራው መሪ ያሰፈልገዋል፡፡

በሙስና ከተጨማለቁ መምህራንና የሀይማኖት መሪዎች ወጣቱ ምን ይማራል? የራሱን የግል ጥቅም ከሚያሳድድ ዶክተር ወጣቱ ምን ይማር? ከትዳራቸው ውጪ ሌላ ትዳር ከሚመሰርቱ ወላጆች ወጣቱ ምን ይማራል? የአገልግሎት ጊዜው ያለፈበት መድሀኒት ከሚሸጡ ነጋዴዎች ወጣቱ ምን ይማራል? የተማሪዎችን ስብእና የሚጎዱ ንግግሮች ከሚናገሩ መምህራን ወጣቱ ምን ይማራል? የሌሎችን ብሄረሰብ ከሚያንቋሽሹ ወላጆች ልጆች ምን ይማራሉ? የሌሎችን ሀይማኖት ከሚያንቋሽሹ ወላጆች ልጆች ምን ይማራሉ? የዘራነውን ነው የምናጭደው! ስለሆነም የተሻለ ነገር ማሰብና የተሻለ ነገር መስራት መጀመር አለብን፤ በተጨማሪም በጎ ባህላችንንም መጠበቅ አለብን፤ ለምሳሌ የመረዳዳት ባህላችን መቀጠል አለበት፤ ከኢትዮጵያ ውጪ በኖርኩባቸው አመታት የሀገራችን ተወላጆች ወላጅ ዘመዶቻቸውን ለመርዳት ምን ያህል እንደሚደክሙ አይቻለሁ፤ ይህ መበረታታት ያለበት ነው፤ ነገር ግን ውጪ ሀገር ለፍተው የሚረዱንን ወገኖቻችንን ደግሞ ተስፋ በማድረግ በየመጠጥ ቤቱና በየካፌው ተወዝፎ የሚውለውን ወጣት የስራ ፍቅር እንዲኖረው፣ ሰርቶ መቀየርን እንዲለምድ ምክር ያስፈልጋል፡፡

አንድ ተጨማሪ ምሳሌ ልጥቀስ፤ በሀገራችን የሞባይል ስልክ ሲሰርቅ የተያዘ ወጣት እስኪሞት ሊደበደብ ይችላል፤ ወጣቱ የሰረቀው የቁሳቁስ ሀብት ነው፤ ነገር ግን ያ ወጣት ተመክሮ፣ ለሌብነት ያነሳሳው ችግር ምን እንደሆነ ከታወቀ በኋላ ራሱ የሞባይል ጥገና ባለሙያ ሊሆን ይችላል፤ ከአንድ የመንግስት ሆስፒታል በጀት ሰርቆ ፎቅ የሚሰራ ባለስልጣን ደግሞ ምንም ላይደረግ ይችላል፤ ይህ ሁሉ የቁሳቁስ ሀብትን ለማግኘት ራስንና ወገንን አደጋ ላይ መጣል ነው፤ ስለሆነም ማንኛውም ማህበረሰብ ከቁሳቁስ ሀብት በፊት የእውቀት ሀብት እንደሚያሰፈልገው መረዳት ያስፈልጋል፡፡

በሀገራችንና በአፍሪካችን እስካሁን የተደረጉትን ጦርነቶች ልብ ብለን ብናስተውል መሰረታዊ መንስኤዎቻቸው የአርቆ አሳቢነት ችግር ነው፡፡ ለምሳሌ ደቡብ ሱዳንን እንመልከት፤ ደቡብ ሱዳን ከሱዳን ለመገንጠል እጅግ ብዙ ጦርነቶች ሲደረግ ነበር የቆዩት፤ ነገር ግን ራሳቸውን እንዲችሉ ከተደረገ በኋላ ወዲያውኑ በታሪካቸው ታይቶ የማይታወቅ ጦየእርስ በእርስ ጦርነት አደረጉ፤ በአለም ደረጃም ከባድ ሀዘንን ያስከተለ የሰው ልጆች እልቂት ተከተለ፤ እንግዲህ ልብ ማለት ያለብን እንደዚህ አይነቶቹን ሂደቶች ነው፡፡ የደቡብ ሱዳን ጦርነት መንስኤ ምንድን ነው ብንል የስልጣን ፉክክርና ሙስና ነው፤ በተጨማሪም የውጪ ሀይሎ እጅም ይኖርበታል፤ ምክንያቱም ደቡብ ሱዳን የነዳጅ ዘይት ባለቤት ናት፡፡ ብዙ የነዳጅ ሀብት ቢኖራቸውም ሀብታቸውን የተጠቀሙት ወንድሞቻቸውን ለመግደል እንጂ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት አይደለም፡፡

የሀገራችን ወጣቶችም ማስተዋል ያለባቸው ነገር ሀገራችን ውስጥ ከሚከሰቱት ጦርነቶችና ግጭቶች ጀርባ አርቆ ማሰብና አውቀት ባለመኖሩ እንጂ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ጦርነት የዱሮ ሰው ተግባር እንደሆነ መታወቅ አለበት፡፡ ይህ አሁን የምንኖርበት ዘመን በእውቀት የበላይነት የምናሸንፈው እንጂ ከጎሮቤቶቻችን ጋር ጦርነት ስለገጠምን አይደለም፡፡ ጦርነት መንግስታትን ለመቀያየር እንጂ ዘላቂ ሰላም ሲያመጣ አልታየም፤ የራሳችን ታሪክም ጥሩ ማሳያ ነው፡፡

የማህበረሰብ ሀብትንም ከሌሎቹ ሀብቶች እኩል በጥንቃቄ መረዳት አለብን፤ የማህበረሰብ ሀብት የምንለው ደግሞ አንድ አከባቢ የሚኖሩ ህዝቦች ከዱሮ ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣና ለራሳቸው ዘላቂ ሰላምንና አብሮ መኖርን እንደ ቆንጆ ባህል ያኖሩትን ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ በቤተሰብና በጎሮቤት መካከል ያለው የመረዳዳት መንፈስ፤ በፖለቲካውም ደግሞ ለምሳሌ በኦሮሚያ ያለው የገዳ ስርአት የማህበረሰብ ሀብት ማሳያ ናቸው፡፡ እነኚህ አይነቶቹ ማህበረሰብ እሴቶች ለሁሉም ዜጎች እንደሚጠቅሙ ተደርገው ያገለግላሉ፡፡ ለምሳሌ የቤተሰብና በጎሮቤቶች  መካከል ያለውን መረዳዳት ብንወስድ አንዱ ተመችቶት ሲኖር ጎረቤቱ እንዳይቸገር ታስቦ የተዘጋጀ የማህበረሰብ ሀብት ነው፡፡ በሰለጠነው አለም አንዱ ችግር የማህበረሰብ ሀብት እየጠፋ መሄዱ ነው፤ ስለሆነም ያሉንን መልካም እሴቶች ማቆየት አለብን፡፡

 

 

ቡናና ጤፍ

ቡና ለሀገራችን ብዙ ነገር ነው፤ ቡና ኢኮኖሚያችን ነው፤ ቡና ባህላችን ነው፤ ቡና ግብርናችን ነው፤ ቡና መለያችን ነው፤ ቡና መድሀኒታችን ነው፤ ቡና ለክብረ በአላት ማድመቂያም ነው፤ ቡና ጊዜ ማሳለፊያችን ነው፤ ቡና መነቃቂያችንም ነው፤ ቡና እንግዳ መቀበያችን ነው፤ በተጨማሪም ሀገራችን የቡና መገኛ ሀገር መሆንዋን እናውቃለን፡፡

ቡና ለኛ ይህንን ሁሉ ሆኖ ታዲያ ዘመናዊ የቡና መፍጫ መሳሪያን ለመጀመሪያ ጊዜ መስራት ከማን ነበረ የሚጠበቀው? ወደድንም ጠላንም እኛ ስለቡና የምናውቀው ባህላዊውን ሁሉ እንጂ ለተቀረው አለም ቡናን በተመለከተ ያበረከትነው ብዙ የቴክኖሎጂ ውጤት የለንም፡፡ ስለሆነም ቡናን ጥሬ እቃውን ነው ለአለም ያበረከትነው፤ ቡና የኢኮኖሚያችን ምሰሶ የመሆኑን ያህል ስለቡና ያደረግነው ምርምር ያንን ያህል አይደለም፡፡ በተለይ ቶክኖሎጂን በመጠቀም ረገድ፡፡ ስለሆነም ከቡና ንግድ የሚገኘው ትርፍ ለሰለጠኑት ሀገራት ተተወ፡፡

ቡናን የተመለከተ ሁሉ እውቀት መኖር የነበረበት በኛው ሀገር ነበረ፤ ቡናን ብቻ ሳይሆን የቡናን ማሽኖች በሙሉ ለአለም ገበያ ማቅረብ ነበረብን፡፡  ቡናን በዘመናዊ መልኩ ቆልተን፣ ፈጭተን፣ አሽገን ለአለም አቀፍ ገበያ እናቀርባለን ለማለት መጀመሪያ አለም የደረሰበትን የቡና ቴክኖሎጂ መለማመድ፣ ተለማምደንም ለዛ እውቅና ማግኘት አለብን፡፡ እኛ የቡና ምርትን ቢኖረንም ቡናን ቆልቶና ፈጭቶ ለአለም ገበያ ማቅረብን ብዙ ትልልቅ የአለም አቀፍ ድርጅቶች ባለመብት ሆነውበታል፤ ገበያው ውስጥ መግባትም በጣም ከባድ ነው፤ አሁን ያለንባት አለም በቀላሉ፣ የዱሮ አስተሳሰብና አሰራር በመከተል ብዙ ርቀት መሄድ አይቻልም፡፡

መሰረታዊው ነገር ዘመናዊ ሆኖ መገኘት ነው፡፡ ቡና የተወለደው እኛ ሀገር ነው ብለን ብንጨፍር፣ ብንዘምርም፤ የቡና ንግድን ዳጎስ ያለ ትርፍ ለቡና አብቃይ ደሀ ገበሬዎቻችን ለማድረስ እኛ የተማርን የምንባለው ትውልድ በቴክኖሎጂው ዘርፍ ፈጠን ብለን ራሳችንንና ልጆቻችንን ማለማመድ ማሰልጠን ያሰፈልጋል፤ ካለሆነ ኢትዮጵያ ሀገሬ ኡኡኡ ወድሻለሁ ምናምን ማለት ዋጋ የለውም፤ ምክንያቱም የተሻሉ ሀገሮች ደሃዋን ሀገራችንን ከጉሮሮዋ ነጥቀው የራስዋን ሀብት ወስደው መልሰው ሲሸጡላት፤ ከቁጭት ያለፈ ምንም አንፈይድም፡፡ ጥሩ ዜጋ ጥሩ ሀገር ወዳድ ለመሆንም ጥሩ አፍቃሪ ለመሆንም ብዙ አዋቂ ዜጎችና እውቀት ያስፈልገናል፡፡ ፍቅር ፍቅር ያዙኝ ልቀቁኝ ማለት የትም አያደርስም፡፡ ትርጉም ያለው ፍቅር ነው የሚያስፈልገን፡፡ ይህችን ሃሳብ እንድጥፍ ያነሳሳኝ በቡና ገበያ ትልቅ ባለሙያ እንዴት ያደጉ ሀገሮች ሀገራችንን የቡና ቴክኖሎጂና ንግድ የበዪ ተመልካች እንዳደረጉዋት በቁጪት ሲነገር ከሰማሁ ጀምሮ ነው፤ እውነት ነው ከቡና ትርፍ ለማግኘት አንድ ሀገር ሙሉ የቡና ተክልና ምርት መኖር በቂ አይደለም፤ መሰረታዊው ነገር የቡናውን ቴክኖሎጂና አለም አቀፍ ጥራት ይዞ መገኘት ነው፡፡

ልብ ያለው ልብ ይበል፡፡

ሀገራችን ከሁሉ በላይ እውቀት ያለው እውቀቱንም ወደተግባር የተረጎመ ትውልድ ያስፈልጋታል፤ በሀገራችን እጅግ ጥልቅ እውቀት ያላቸውን ልጆች የሰለጠኑት ሀገራት በትምህርት እድለ ሰበብ ይወስዱብናል፤ የፖለቲካ፣ የብሄር ችግር፣ የዘር፣ የማህበራዊ፣ የሙስና አለመታመን ወዘተ የሚሉት ነገሮች አላዋቂና ችግረኞች እሰከሆንን ድረስ ሁሌም አብረውን ይኖራሉ፤ አይናችንን መክፈት ያለብን ይመስለኛል፤ ካልሆነ ግን መቶ ሚሊየን ህዝብ ቢኖረንም የአህያ ባል ከጅብ አያስጥልም እንደሚባለው ይሆንብናል፡፡ እንደግለሰብና እንደሀገር፣ በየደረጃው አርቀን ማሰብ ካቻልን፣ ልጆቻችንን ከስደት መከላከል አንችልም፤ ገበሬዎቻችንም የእርዳታ እህል መቀበላቸውን በቀላሉ ማስቀረት ይከብደናል፡፡

ስለቡና የተጠቀሰው ሀሳብ ለጤፍም ተመሳሳይ ነው፤ ጤፍና ቡና የኛ ናቸው፤ ምርቱም፣ ቴክኖሎጂውም፣ የአለም ገበያው ትልቁ ትርፍም በመጀመሪያ የኛ መሆን አለበት፡፡ በምኞት ብቻ ደግሞ የኛ መሆን አይችልም፤ እጅግ አርቀን በማሰብ ራሳችንንና ትውልዱን በእውቀት ማስታጠቅ ያስፈልጋል፡፡

 

ትንሽ የሚመስሉ ትልልቅ ተግባራት

ጀምስ ቦወን የሚባል የእንግሊዝ ሀገር ዜጋ በጎዳና ላይ ሲኖር ‘‘A street cat named Bob’’ ቦብ ስለሚባል የጎዳና ላይ ድመት መፅሀፍ ፅፎ ነበረ፤ ቦወን ወላጆቹ ከትዳራቸው ሲፋቱ ለከፍተኛ የሞራል ውድቀት ተዳርጎ ነበረ፤ እንዲሁም የወላጆቹ ትዳር ሲፈርስ ከእናቱ ጋር ወደአውስትራሊያ ሄዱ፤ ትምህርትቤትም አስገቡት፣ ቢሆንም ቦወን ትምህርቱን አልወደደውም፤ ቀጥሎም ትምህርቱን አቋረጠ፤ ቀጥሎም ወደእንግሊዝ ተመለሶ ከእህቱ ጋር መኖር ጀመረ፤ ቢሆንም ብዙም ሳይቆይ ወደጎዳና ህይወት ወጣ፤ ቀጥሎ አደንዛዥ ነገሮችን መጠቀም ጀመረ፤ ቀጥሎም ቦወን ተመሳሳይ ችግር ያለባቸው ሰዎች ወደሚያገግሙበት ማእከል ተወስዶ የመኖሪያ ቤት ተሰጠው፡፡ እዛ ማገገሚያ ቦታ ነው ይህንን ብቸኛውን ድመት ያገኘው፡፡

ቦወን ቦብ ብሎ ስም ያወጣለትን የዱር ድመት እንደምንም አለማምዶ ካስጠጋው በኋላ ጓደኛው ያደርገዋል፡፡ ድመቱም ሰውየውን ለመደው ሰውየውም ድመቱን ለመደው፤ እጅግ ተስማሙ፤ ድመቱም ለማዳ ሆኖ ከጎዳና ተዳዳሪው ሰው ጋር በየቀኑ መንገድ ዳር መዋል ጀመረ፡፡

እጅግ የሚገርመው ታሪክ ደግሞ በጎዳና ላይ ይተዳደር የነበረው ቦወን ለብቻው ቁጭ ብሎ ሲለምንና ድመቱን ይዞ ሲለምን የሚያዝንለት ሰው ብዛት እኩል አልነበረም፤ ሰውየው ድመቱን ይዞ ሲቀመጥ የብዙ ሰዎችን ትኩረት መሳብ ጀመረ፡፡

በመሆኑም ብዙ ሰዎች ለድመቱም ብለው ገንዘብ ይሰጡት ጀመረ፤ ድመት የሚወዱ ሰዎች ድመቱን ለመንካትና ስለድመቱ የህይወት ታሪክ ለማወቅ ጠጋ ብለው ያወያዩት ነበረ፤ ይህ የጎዳና ላይ ሰው ድመቱን በማለማመዱ ሳያስበው ህይወቱ ተለወጠ፡፡

ቦወን ድመቱ ባለውለታዬ ነው ብሎ ነው የሚገልፀው፤ በድመቱ ሰበብ በጎዳና ህይወቱ ጥሩ ገቢ ማግኘት ጀመረ፤ ቦወን ቀስ በቀስ ከጎዳና ኑሮ ጋዜጣ ማዞር ጀመረ፤ እንዲሁ ቀስ በቀስ ታዋቂ ፃሀፊ ሆነ፡፡

ስለድመቱና ስለሰውየው ይህንን ያህል ለመግቢያ ከጠቀስኩ ወደሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ብንመለስ፣ በሀገራችን ብዙ የጎዳና ላይ ህፃናት አሉ፤ ለነኚህ ህፃናት ከለላ ብንሰጣቸው አንድ ቀን ልጆቹ ትልልቅ ሲሆኑ ባደረግነው በጎ ስራ ደስተኞች እንሆናለን፡፡

ለምሳሌ ለጣሊያን የእግር ኳስ ብሄራዊ ቡድን የሚጫወተው ማሪዮ ባሎቴሊ በልጅነቱ ጋናዊ ዜግነት የነበራቸው ስደተኛ ወላጆቹ ለልጃቸው ህክምና ወጪ መክፈል ሲያቅታቸው አንድ አይሁዳዊ መሰረት ያለው ሀኪም ወስዶ እንዳያሳደገው በህይወት ታሪኩ ውስጥ ተጠቅሶ ይገኛል፤ ዛሬ ባላቶሊ ታላቅ ተጫዋች ስለሆነ በልጅነቱ ከለላ የሰጠው ሀኪም ለልጁም ለወላጆቹም እንዲሁም ለሀገሩ ለጣሊያንም ታላቅ ባለውለታ ነው፡፡ በእርግጥ ሁሉ ልጆች እንደ ባላቶሊ ይሆናሉ ማለት ባይቻልም እያንዳንዱ ልጅ ግን የተፈጠረለት አላማ አለው፤ እኔና እናንተ ደግሞ ያንን አላማ ከግብ ለማድረስ ምክንያቶች ነን፡፡

በሌላ ታሪክ፣ በቅርቡ አንዲት ቱሪስት ብራዚል ለጉብኝት ሄዳ አንድ ጎዳና ዳር የተጣለ ውሻ አግኝታ ወደሀገርዋ ስትመለስ ውሻውን ይዛው ትመለሳለች፤ ያ ውሻ አፉ አካባቢ የአሳማ መሰል ቅርፅ ነበረው፤ ለየት ያለውን የፊቱን ቅርፅ ለማየት እጅግ ብዙ ውሻ አፍቃሪዎች ወደዚህች ሴት ቤት ይመላለሳሉ፤ ስለሆነም ይህች ሴት በውሻው ሰበብ ገንዘብ ማግኘት ጀመረች፤ ዋናውን ስራዋንም ትታ ውሻውን ለቱሪስቶች በማስጎብኘት ና ፎቶውን በመሽጥ ትልቅ ሀብት ማካበት ችላለች፡፡

በሀገራችን ብዙ ተመሳሳይ ነገሮች ይኖራሉ፤ ምንም ጥቅም አይሰጡም ብለን የረሳናቸው ነገሮች፤ ዋናው ምሳሌ በጎዳና ያሉት ወገኖቻችን ናቸው፡፡ በሰለጠነው አለም ድመትና ውሻ ማሳደግም ውለታ ነው፡፡ እኛ ሀገር ደግሞ ወላጅ አልባ ልጆችን ብንረዳና አስተምረን ብናሳድግ በረከት ነው፡፡ በተለይ ሀይማኖተኛ ለሆነው የሀገራችን ህዝብ ይህንን ማስረዳት ብዙ ከባድ መሆን የለበትም፤ በእርግጥ ስራውን መጀመር እጅግ ትልቅ ውሳኔና የመንፈስ ጥንካሬ ይጠይቃል፤ በአዲስ አበባ የማቂዶኒያ ማእከልን የመሰረተው ቢኒያም ጥሩ የቅርብ ምሳሌ ሊሆነን ይችላል፤ ምክንያቱም በሀገራችን እስካሁን ካየሁት እጅግ የተለየና ለሀገርና ለወገን ትልቅ ጠቀሜታ ያለው ስራ በቢኒያም መሰረት እየተሰራ ይገኛል፤ ሁላችንም እንደቢኒያም ብናስብና አስበንም ወደተግባር ብንቀይር በሀገሪቱ ያሉት ችግረኞች ሁሉ ባልኖሩ ነበረ፤ ነገር ግን ብዙዎቻችን ስስታሞችና ቁሳቁስ አፍቃሪ ነን፤ ራሳችንን ለሌሎች አሳልፈን አንሰጥም፤ ብዙ ሀብት እያለው የራሱን ወንድምና እህቶች መርዳት የሚቸግረው ብዙ ሰው ነው፡፡

ነገር ግን የቢኒያምን አይነት ማእከል መመስረት የማንነታችን ትልቁ ግብ ቢሆን ሁላችንም ግን በአከባቢያችን ላሉት ችግረኞች ዘላቂ መፍትሄ ብናስብ ጥሩ ነው፣ በተጨማሪም የተጀመሩትን ማጠናከርም እንደቢኒያም ያሉት ጎበዞች የጀመሩትን አላማ ከግብ ማድረስ ነው፤ በጉብኝት ወቅት ያየሁት ማቂዶንያ ማእከል በብዙ በጎ አድራጊ ግለሰቦች ድጋፍ የሚተዳደር መሆኑን ነው፤ ያለው በገንዘቡ የሌለው ገቡልበቱ ድጋፍ እንደሚያደርግ አይቻለሁ፡፡ በሲስተር ዘቢደር ዘውዴ የሚመራው የሜሪ ጆይም ለችግረኞች ታላቅ ድጋፍ እያደረገ የሚገኝ ነው፡፡ ስለሆነም እነኚህ የተጀመሩት ትንንሽ ተግባራት አላማቸውን እንዲያሳኩ የሁላችንም ድጋፍ ያስፈልጋል፡፡

በሰለጠነው አለም ችግረኞችን የመርዳት ዘመቻ ይደረጋል፤ በጎ አድራጊዎች ቤት ለቤት ዞረው ድጋፍ ያሰባስባሉ፤ በሀገር አቀፍም በአንድ ቀን ከፍተኛ ገንዘብና ቁሳቁስ ይሰበሰባል፡፡    እኛስ ምን እያደረግን ነውየሌሎችን ብሄረሰብ ከሚያንቋሽሹ ወላጆች ልጆች ምን ይማራሉ ? መልሱን ሁላችንም ልናስብበት ይገባል፡፡

 

 

ውጪ ግንኙነት

እስካሁን በሀገራችን ዩኒቨርሲቲዎች ስራ ካለኝ ቆይታ፤ አንድ የሀገራችን ዩኒቨርሲቲ ሄደን ከየቶቹ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ነው አብራችሁ የምትሰሩት/ኮላቦሬሽን ያላችሁ/ ብለን ብንጠይቅ፤ ከአሜሪካ፣ከአውሮፓ፣ከካናዳ፣ከኤሲያ፣ ከአውስትራሊያ ወዘተ ያሉ ዩኒቨርሲቲዎችን ስም እንሰማለን፡፡

ሀገር ውስጥ ካሉት ዩኒቨርሲቲዎች ጋርስ ቢባል፣ ያንን ያህል መልስ የሚኖር አይመስለኝም፡፡ በዚህ ዘርፍ እጅግ ትልቅ ክፍተት አያለሁኝ፡፡ ምሳሌ መጥቀሱ አስፈላጊ ስላልሆነ ተወዋለሁ፡፡ ይባስ ብሎ አንዱ ኮሌጅ ከሌላው የተጣሉበት ዪኒቨርሲቲም ሊያጋጥመን ይችላል፡፡ የጥሉ ምንጭም የዩኒቨርሲቲዎቻችን ልሂቃንና አንዳንድ ፕሮፌሰሮች ለሀገራዊ ጥቅም ሳይሆን ለአንድ ሙያ እንዲሁም ለግል ጥቅም ቅድሚ በመስጠት አንዱን ኮሌጅ ከሌላው እስከማጣላት የደረሱበት ሁኔታ አለ፤  ታዲያ ይህ እውነታ አብሮ የመስራት ክህሎታችንን ጥያቄ ውስጥ ያስገባዋል፡፡ ከሌሎች ጋር አብረን መስራት አንችልም እንዳይባል ይሀው ባህር ተሻግረን፣ሀገር አቋርጠን ትብብር እየፈጠርን ነው፡፡ ወደራሳችን ሲመጣ ግን ቢከፍቱት ተልባ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን አብረን መብላት እንጂ /ከሌላው አለም በተለየ አብረን መብላታችንንም እኔ እንጃ/ አብረን መስራት ላይ ችግር አለብን፤ ለምሳሌ ስፖርቱን ተመልከቱ፤ በሩጫ ተሳካልን፤ በእግርኳስ ግን ብዙም አልተሳካልንም፤ እስቲ ተወያዩበት፣ እኛ ኢትዮጵያውያን አብሮ የመስራት ክህሎታችን መሻሻል የለበትም? የሀገራችን ዶክተሮችና ፕሮፌሰሮችስ፣ የሚጠበቅባቸውን የህል ግዴት እየተወጡ ነው? ውጪ ሀገራትን የማምለኩ ችግር በተማሩት ትልልቅ ልሂቃንም ዘንድ ያለ ችግር ይመስለኛል፡፡

ልማት

ዛሬ ከአዲስ አበባ ወደሀዋሳ እየተጓዝን ስለሀገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ተነሳና….ብዙ ብዙ ጉዳዮች ተጠቀሱ፤ ታዲያ ዋናው አጀንዳ የነበረው የብሄረሰብ ጉዳይ ነው፤ እንዲሁም በብሄረሰብ ሰበብ እየተሰራ ያለው ሙስና፤ የዚህች ሀገር ዋናው ራስምታት በብሄረሰብ ሰበብ የሚነሱ ችግሮችን የምንፈታበት መድሀኒት አለመኖሩ ነው፤ አንዱ ይሰርቅና ሲያዝ በብሄረሰብ ያሳብባል፤ ሰዎች በንግድ ስራ ተጣልተው ጥሉን በብሄረሰብ ማሳበብ፤ ሀይማኖት ሲጨመርበትማ ችግሩ ራስምታት መሆኑ ቀርቶ ደም ብዛት ይሆናል፡፡ 3000 አመት ሙሉ የወረደ አስተሳሰብ ዋጋ ሲያስከፍለን ያሳዝናል፡፡

ይህ ትውልድ መሰረታዊ ችግሮችን ማየት እንዲችል አስተሳሰቡን የሚያበራ ዘመቻ ያስፈልጋል፡፡

አንድ የማይካድ እውነታ አለ፤ ሀገሪቱ ከሰባ በላይ ብሄረሰቦች ባለቤት ናት፤ ሁሉም የየራሱ ጥያቄዎች አሉት፤ በመሀል ደግሞ ደካማና በብሄረሰብ ሰበብ አላግባብ መክበር የሚፈልጉና አላግባብ የከበሩ ሀሳባቸው እንጭጭ የሆነ ግለሰቦች አሉ፤ ትክክለኛውን የብሄረሰቦች ጥያቄ ወደሌብነትና ወደግለሰብ ጥቅም የሚቀይሩ እጅግ ብዙ የአስተሳሰብ ድሆች አሉ፤ ለሀገሪቱ ግን ሁሉም ያስፈልጋሉ፤ ሁሉንም ዜጋ ማስተማርና ወደዘላቂ ልማት ትኩረታችን መመለስ ያለበት ይመስለኛል፡፡

ሌባን ማሰርና መግደል ከባድ አይደለም፤ መገዳደል በቀደሙት ዘመናት ችግራችንን  የፈታንበት ዋና መሳሪያ ነው፤ ተገዳድለን ግን ዘላቂ ሰላም ማግኘት አልቻልንም፡፡ በኦሮሞ ህዝብ ስም፣ በአማራ ህዝብ ስም፣ በትግሬ ህዝብ ስም፣ በሲዳማ ህዝብ ስም፣ በወላይታ ህዝብ ስም፣ በሶማሊ ህዝብ ስም ወዘተ የደሃውን የሀገራችንን ህዝቦች ተስፋ የሚያጨልሙትን ለመዋጋት መዘጋጀት ግድ ይለዋል፤ ቀስ በቀስ አይቀርም፡፡ ሌቦች ሁሉ ለፍርድ የሚቀርቡበት ጊዜ ይመጣል፤ ህዝቡ በስሙ የሚነግዱትንና ለልማቱ እየሰሩ ያሉትን ለይቶ ማወቅ አለበት፡፡ ዛሬ በሀገራችን ክልሎችና ዞኖች በዋናነት የሚተዳደሩት በአከባቢው ተወላጆች ነው፤ የአከባቢ ልጅ ሆኖ ግን የራሱን አከባቢ ህዝብ ንብረት ለራሱ የግል ጥቅም የሚነግድ እጅግ ብዙ ነው፤  ለውሃና ለጤና ለአከባቢ ልማት የሚመደበውን ገንዘብ ለግለሰብ ህንፃ ግንባታ ማዋል የተለመደ እየሆነ መምጣቱን በተለያየ ጊዜ እየሰማን ነው፤  የሀገራችን ህዝቦች በስማቸው የሚነግዱትን ደካማዎች ለመዋጋት መዘጋጀት አለባቸው፡፡ የአንድ ብሄረሰብ ተወላጅ መሆን  ብቻ ሳይሆን በትክክል ለብሄረሰቡ  ዘላቂ ልማት መስራት ያስፈልጋል፤ ህዝቡ ጥላቻ የለበትም፤ የህዝቡ ችግር ድህነት ነው፤ እግዚአብሄር ሀገራችንን ይጠብቅ፤ አይናችንን እንክፈት፤ አርቀን እናስብ፤ ራሱን የሚያከብርና ለእውነት የሚቆም ትውልድ መፍጠር አለብን፡፡

በአስተሳሰብ እድገት

ያደጉት ሀገሮች ከኛ የሚሻሉት በዋነኛነት በአስተሳሰብ እድገት ነው። ከኛ በተሻለ ስለሚያስቡ ጥሬ ቡና ገዝተው የተፈጨ ቡና ይሸጡልናል። ከፈለጉ የጦር መሳሪያዎች ሰጥተው ወንድሞቻችንን እንድንጨርስ ያደርጋሉ። ብሩህ አእምሮ ያላቸውን ልጆቻችንን በገንዘብ አታለው ይወስዳሉ። ባንኮቻችንን በኢንተርኔት እንዲሰሩ አድርገው በእነሱ ቁጥጥር ስር ያደርጋሉ። ብዙ ምሳሌዎች መጥቀስ ይቻላል። አርቀው ማሰባቸው እንዲቆጣጠሩን አስቻላቸው።  አንዱ ወዳጄ፣ ሀገራችን ውጪ ካሉ ዜጎች ገቢ እያገኘች እንዴት ስደት ሀገር ይጎዳል ትላለህ ብሎ ጠየቀኝ። ልጆቻችን ውጪ ሰርተው ደሞዝ ነው ሚከፈላቸው። ሰው ሰርቶ ለስራው ደመወዝ ሲከፈለው ድካሙ ሁሉ ጠቀሜታው ሁሉ የዛችን ደመወዝ ያህል ነው ማለት አይደለም።

ለምሳሌ አንድ የቀዶ ጥገና ሀኪም ብንወስድ፣ አንዲት እናት በቀዶ ጥገና ሲያዋልድ ሀገራዊ ጠቀሜታው በገንዘብ አይለካም።  ባለሙያው ለሚያገለግለው ህዘብ እጅግ ትልቅ አገልግሎት ያበረክታል። የሰው ልጅ ያውም የተማሩ ባለሞያዎች ወደውጭ ልኮ ለሀገራችን አይነት ደሀ ሀገር ገንዘብ ማግኘት ማለት እጅግ ትልቅ ኪሳራ ነው። ባለሞያው ያደገ ሀገር በመስራቱ በገንዘብ ተጠቃሚ ነው። እንደተማረ ሰው: እንደ ደሀ ሀገር ዜጋ ግን ኪሳራ ነው። የሀገሬ እናት እየሞተች የሀብታም ሀገር ባለጠጋ ባገለግል ዘመናዊ ባርነትን ወድጄ ተቀበልኩ ማለት ነው። የኔ አስተያየት ይህ ነው። ውጪ ሀገር ሰርቶ መኖር ገንዘብ ያስገኛል። ነገር ግን፣ ሀገራዊ ጥቅምን ይጎዳል፣ በራስ መተማመንን ሀገራዊ ኩራትን ያሳጣል። የሰው ልጅ ትልቁ ሀብቱ አእምሮው ነው። አእምሮው ለገንዘብ ከተሸጠ ግን የፈለገውን ገንዘብ ቢያገኝ ደስተኛ መሆኑን አይችልም። በተለይ ኢትዮጵያዊ ኩሩው በነጮች ቅኝ ግዛት ህመሙ ነው። ድህነትን እሳት ያቃጠለው ይላል ያገሬ ሰው። ድህነት በተለይ የአስተሳሰብ ድህነት ህሊናን ለገንዘብ ያስቀይራል።  ማደግ ካለብን አስተሳሰባችን ይደግ። ካልሆነ ሁሌም አናድግም።  አስተሳሰባችን ካላደገ ህሊናችን ለአስተሳሰብ ሀብታሞች ባሪያ መሆኑን ይቀጥላል። ስለሆነም ውጪ ሀገር መኖር ገንዘብ እንደሚያስገኝ ባውቅም፣ ጥሩ አይደለም የምለው ሀገረራዊ ጥቅምን ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው፤ በገንዘብ ቢሆንማ ሁላችንም ተሰደን ብዙ ብር ማምጣት እንችላለን፣ ቻይናዎች ግን በሀገራችን ሰርተው ከብረው ይጠብቁናል፡፡

ውጪ ሀገር

ስለ ውጪ ሀገር ህይወት ሀገር ቤት ያለነው ኢትዮጵያዊያን አስተሳሰብ ውስጥ በቀላሉ ሊቀየር የማይችል እጅግ የሚያማልል ስእል ተስሏል፡፡ ለዚህ ደግሞ ብዙ ምክንቶች አሉ፡፡ አንደኛው ምክንያት የዉጪ ሀገር ስራ ደሞዝ ቆንጆ መሆኑ ነው፡፡ ሁለተኛው ውጪ የሚኖሩት ወገኖቻችን ከሚልኩልን ፎቶዎችም ይሁን እዚህ ለእረፍት ሲመጡ ከሚያሳዩን የተለያዩ ነገሮች በመነሳት ምንም የውጪ ሀገርን መጥፎ ነገር ማየት አይቻልም፡፡ ሰማይ ጠቀስ ፎቅ ስር ፎቶ ተነስተው ሲልኩልን የራሳቸው ሳይመስለንም አይቀርም፡፡

የሚሰሩትን ስራ ዝርዝርና የቀን ተቀን ውሎአቸውን ሊነግሩን አይፈልጉም፤ ቢነግሩንም አናምናቸውም፡፡ እውነቱንም ቢነግሩን አናምናቸውም፤ እኔ ስለውጪ ሀገር ለብዙ ወዳጆቼ እየነገርኩ አያምኑኝም፤ ወጣቱ ውጪ ሀገር ስራ ብዙ ገንዘብ እንደሚያስገኝ ብቻ ነው የሚያውቀው፣ ብዙ ብር የሚከፈልበት ስራ ሁሉ ቆንጆ ስራ አለመሆኑን ሰርተን ያየን እናውቀዋለን፤ ወደድንም ጠላንም እጅግ ብዙ የሀገራችን ዜጎች /ሀብታሞችንም ጨምሮ/ ያለምንም በቂ ምክንያት እንደምንም መንገዱን አግኝተው ወደ ውጪ መሄድ ይፈልጋሉ፡፡

 

 

ብዙ ወጣት መሰደድ ይፈልጋል፤ በሀይማኖታቸው ስለትም ጭምር የሚሳሉ አሉ፤ ልጃቸው እኮ ውጪናት ልጆቻቸው ውጪ ናቸው፤ ዘመዶቻቸው ውጪ ናቸው፤ ከውጪ ነው የመጡት፤ በአጭሩ (ውጪ) የምትባለው ቃል ጭንቅላታችን ውስጥ እጅግ ትልቅ ቦታ ይዛለች፡፡ ሁላችንም ሀብታሞች ብንሆንና ፖለቲካ ችግሮች ባይኖሩብንም፣ ወደውጪ የማሰቡ ጉዳይ የሚቀር አይመስለኝም፡፡ ውጪ ሀገር መሄድ ጎጂ አይደለም፡፡

ለምሳሌ ውጪ ሀገር ሄዶ መማር ብዙ የሀገራችን ወጣት ተማሪዎች የሚመኙት ጉዳይ ነው፤ መሆንም አለበት ባይ ነኝ፡፡ ሄዶ ውጪ መቅረት ግን ኪሳራ ነው፤ ኪሳራውም ለሀገር ነው፤ በአጭሩ ሄዶ ማየትን የሚያህል ነገር የለም፡፡ ትልቁ ችግር በህገወጥ መንገድ፣ ምንም የተጨበጠ ነገር ሳይኖረን፣ አይናችንን ጨፍነን ወደጭለማ የምንሄደው ነገር ነው መታረም ያለበት፡፡ በሀሳቡ ብንስማማ ምን ይደረግ ለሚለው ጥያቄ ምን መልስ እንስጠው? የውጪ ሀገር በዋናነት የሚስማማው ሀገር ቤት እጅግ ድሆች ለነበሩ፣ በትምህርታቸው ገፍተው ያልሄዱ፣ ሀገር ቤት ስራ አጥ የሆኑ ወይም የጉልበት ስራ በጥቂት ደሞዝ የሚሰሩ፣ የቤት ሰራተኞች፣ ዘበኞች፣ የታክሲ ሾፌሮች ወዘተ ሀገር ቤት የሚከፈላቸውና ውጪ የሚከፈላቸው ሲነፃፀር እጅግ ብዙ ልዩነት አለው፡፡

ነገር ግን በህጋዊ መንገድ ካልሆነ በህገወጥ መንገድ ሲኬድ እጅግ ትልቅ አደጋ ነው ያለው፤ ህይወትን ማጣት፤ እርስ ቤት መግባት፣ አውሮፓ ወይም አሜሪካን ሳይደረስ መንገድ ላይ መቅረት ወዘተ አደጋዎች አሉ፡፡ በተጨማሪም የቋንቋ ችግር አለ፤ ሀገራችን የፅዳት ስራ መስራትና የሰለጠነ አለም የፅዳት ስራ ተመሳሳይ አሰራር አይደለም፡፡ ከተቻለ ስልጠና መውሰድ ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ የለመንጃ ፍቃድ፣ ዝም ብሎ መሄድ አደገኛ ነው፡፡ ወጣቶቻችን ስለስደት ከማሰባቸው በፊት ብዙ ዝግጅት፣ ብዙ መረጃ እንደሚያስፈልጋቸው መረዳት አለባቸው፡፡ አደራ አደራ በህገወጥ መንገድ ወደውጪ ለመሄድ አታስቡ፤ በተጨማሪም በህጋዊም ብሆን በባህር ጉዞ በፍፁም አትሂዱ፡፡ ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ!

ፍቅርና ጥላቻ

ፍቅር ምንድን ነው? ጥላቻስ? ስለፍቅር ስናስብ ተቃራኒውን ጥላቻንም ማሰብ ግድ የሚል ይመስለኛል፡፡ የፍቅርን ምንነት ለማወቅ ጥላቻን ማሰብ የበለጠ ፍቅርን መረዳት እንድንችል የሚረዳን ይመስለኛል፡፡ ንፁህ ፍቅር ፍፅም የሆነ፣ እጅግ ትልቅ ጥልቀትና ትርጉም ያለው ውድ ነገር ይመስለኛል፡፡ ፍቅርን ለመረዳትም አፍቃሪን ማሰብ የግድ ነው፡፡ ፍፁም ፍቅር ሊኖር የሚችለው ፍፁም አፍቃሪ ሲኖር ብቻ ይመስለኛል፡፡ ፍፁም የሆነ አፍቃሪ ደግሞ የአለማችን ፈጣሪ ብቻ እንደሆነ በእምነት መፅሀፍት በሰፊው ተዘግቧል፡፡ ስለሆነም ምንም እንከን የሌለበት ንፁኅ ፍቅር መኖር ካለበት እጅግ ረቀቅ ያለ አስተውሎ ያለው አፍቃሪ ማስፈለጉ ግልፅ ነው፡፡ እንግዲህ ፍፁም ፍቅር የፈጣሪ አምላካችን ባህሪ ከሆነ ፍፁም ጥላቻ ደግሞ የዲያቢሎስ ባህሪ ይሆናል ማለት ነው፡፡

የፈጣሪንና የዲያቢሎስን ባህሪ ትተን ወደራሳችን የአለማዊ ሰዎች አብሮ መኖር ስንመለስ፣ ፍፁም ፍቅርና ፍፁም ጥላቻ ምን እንደሆኑ ለመረዳት የተወሰኑ ነጥቦችን መዘርዘር ማስፈለጉ የግድ ነው፡፡ በተለያዩ አጋጣሚዎች እንደምናየው ወይም እንደምንሰማው፣ በዛሬ ጊዜ ብዙዎቻችን አፈቅርሀለሁ፤አፈቅርሻለሁ፣ ሀገሬን አፈቅራለሁ፣ ስራዬን አፈቅራለሁ፣ብሄረሰቤን አፈቅራለሁ ወዘተ ብለን እንናገራለን፡፡

አንዳችን በሌላችን ፍቅር መንደዳችንን እንነግራለን፣ አፍቃሪ መሆናችንን ለማሳየት በልብሶቻችን ላይም ጭምር አሳትመን እንለብሳለን፡፡ ለምሳሌ ‹‹I love Ethiopia›› የሚሉትን በተለያዩ አልባሳት ላይ ታትመው ማየት የተለመደ ነው ፡፡ ዋናው መሰረታዊ ጥያቄ ግን ለምንድን ነው የምናፈቅረው? ስራችንንስ ቢሆን ለምንድን ነው የምናፈቅረው? ስለተፈቃቀርን አንዳችን ለሌላችን ምን እናደርጋለን? የፍቅራችንስ ዘለቄታ እስከ ምን ድረስ ነው? ወዘተ የሚሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ እንሞክር፡፡

ብዙ ጊዜ የምናፈቅረው ጥሩ ነገር ያደረገልንን ሰው ነው! ፍቅራችን ለሁሉም ሰዎች ሳይሆን እኛን በበለጠ ላገለገሉን ወይም ከሁሉ የተሻለ ጥቅም ያገኘንበትን ሰው እናፈቅራለን፡፡ እስቲ እናስበው፤ መፋቀር ማለት አንዱ ሌላውን ማስደሰት ብቻ ነው እንዴ? የፍቅር ትርጉም ገብቶናል? አፍቃሪ ልብና አፍቃሪ አስተሳሰብ ሲኖረን ፍቅራችን ከጥቅም ነፃ መሆን ያለበት ይመስለኛል፡፡ በጎ የሚያደርጉላችሁን ብቻ ብታፈቅሩ ፍቅራችሁ ከግብዞች ፍቅር በምን ይለያል ብሎ ይጠይቃል መፅሃፉ፡፡ አዎ፤የሚጠቅሙንን ሰዎች ወይም የሚያስደስቱንን ሰዎች እናፈቅራለን፤ የማይጠቅሙንን ግን አናፈቅርም፤ ስለሆነም ፍቅራችን የመጠቃቀም ፍቅር እንጂ እውነተኛ ፍቅር አይደለም፡፡ ቆርቆሮ/ቁሳቁስ ነገሮችን ስናይ ፣ የኔ ውድ አፈቅርሻለሁ፤ አፈቅርሀለሁ ነው የኛ ነገር፡፡ ያቺ ገንዘብና ብልጭልጭ ነገር ስትጠፋ ወይም የለመድነው ወይም የጠበቅነው አልገኝ ሲል፣ ፍቅራችን የደረሰበት ይጠፋናል፡፡

ስለዚህ ፍቅርና ጥላቻችን መሰረቱ እስከምን ድረስ ነው? የሆነን ነገር ወይም ግለሰብ ስናፈቅር ወይም ስንጠላ ምክንያታዊነታችን እስከምን ድረስ ነው? እስቲ ከልባችን የምናፈቅረውን ሰውና ነገሮች ደግመን እናስብ፣ መሰረታችን ምንድን ነው? የብዙዎቹ የመጠቃቀም ፍቅር አይደለምን?

ጥላቻስ? ፍፁም ፍቅር የቅዱስ መንፈስ ባህሪ ስለሆነ ፍፁም ጥላቻ ደግሞ በተቃራኒው የዲያቢሎስ ባህሪ ነው ማለት ነው፡፡ ጤናማ አስተሳሰብ ያለው ሰው ልቡ በፍፁም ጥላቻ መሞላት አይችልም፤ ሚዛናዊ ሰው በደል ሲደርስበት የበደሉን መነሻ በሰከነ መንፈስ ሊገነዘብ ይሞክራል፤ ስለሆነም የበደሉን መንስኤ በመረዳት ጤናማ አእምሮ ያለው ሰው በደለኛን ይቅር ይላል፤ ሌሎችን ሲበድልም ይቅርታ ይጠይቃል፡፡ ስብእናው ደካማ የሆነ ሰው ደግሞ ቂም ለመቋጠር ትንሽ ሰበብ ይበቃዋል፡፡

በነዚህ መሰረታዊ ሀሳቦች ከተስማማንና በአስተሳሰባችን ትክክለኛነት ከተስማማን ፍቅራችን ምክንያታዊ ሆኖ ከጥላቻ ነፃ የሆነ ይሆናል፡፡ እንዲሁም ከሌሎች ተጠቃሚ መሆናችንን ብቻ የፍቅራችን መሰረት አናደርግም፡፡ አፍቃሪ ልብ ካለን መሚያፈቅሩንና ከሚጠቅሙን ወገኖችና ነገሮች አልፈን ሌሎችንም ሰዎች የማፍቀር ፍላገት ሊኖረን ይገባል፡፡ እውነተኛ ፍቅር ለሁላችን፡፡

አንዲት ልጅን እጅግ የሚወዳት ወጣት ነበረ፤ ወጣቱ ልጅትን ከመውደዱ ብዛት ከእናቱ የበለጠ ይወዳታል ያስብላታልም፤ ልጅት ፍፁም ንፁህ ሰው ናት ብሎ ያምን ነበረ፤ ስለሆነም እጅግ ተዋደዱ፤ የግል ዩኒቨርሲቲ ከራሱ ገንዘብ ከፍሎ አስተማራት፤ አስመረቃት፤ ተመርቃ ግን አንድ ወር ጊዜ ውስጥ ሌላ ሰው አገባች፤ ልጁም እጅግ በጣም አዘነ፤ ጤናውም ታወከ፤ ልጅት ሌላ ያገባችበት የራስዋ ምክንያት ይኖራታል፤ ዋናው ጉዳይ አንድን ሰው ፍፁም አድርጎ መሳሉ ላይ ነው፤ ፍፁም የሆነው ፈጣሪ አምላካችን ብቻ ነው፤ ስለሆነም ወጣቶች ሲዋደዱ አንዳቸው ሌላውን እንደፍፁም ባይተያዩ ቆንጆ ነው፡፡ ምክንያቱም ሰዎቹ ሁሌም ይሳሳታሉ፤ መጠኑ ቢለያይም ስህተት የሌለበት ሰው የለም፤ ስለሆነም ማንንም የምንወደውን ሰው ከስህተት ፍፁም አድርጎ መጠበቅ ስህተት ነው፡፡

ብዙ ጊዜ የፍቅራችን ወይም የጥላችንን መስመር የሚያገናኘው ገንዘብ ነው፤ ሰዎች በገንዘብ ምክንያት እንዋደዳለን፤ በገንዘብ ምክንያትም እንጣላለን፤ ነገር ግን ከገንዘብ ባለፈ ፍቅር መስዋእትነት የሚከፈልበት እንደሆነ መረዳት አለብን፡

ትዳር

አንዱ ወዳጄ ለትዳር የምትሆነውን ሴት ልጅ መፈለግ ከጀመረ አስር አመት ሊያልፈው ነው፤    በእሱ መስፈርት እስካሁን የሚያገኛቸው ሴቶች ሁሉ የወረዱ ናቸው ይለኛል፡፡ የወረዱ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ለማብራራት ብዙ መፃፍ ስላለብኝ ልተወውና….አጭሩ ምክሬ አንደኛ ለዉበት ያለህን ግምት ዝቅ አድርግ፤በጣም ጥሩ ሚስት ማለት የግድ በጣም ቆንጆ ሚስት ማለት እንዳልሆን እወቅ፤ንቃተ ህሊና የሚባል እጅግ ትልቅ ነገር መኖሩን ልብ በል፡፡ አንዳንድ ሴቶች ከወንዱ ጋር ትዳር ሲመሰርቱ ለወንዱ ብለው የሚያደርጉት የሚያስመስሉት አሉ፤ ትዳር ግን በጎ አድራጎት አይደለም፣ ለእሱ ወይም ለእስዋ ተብሎ የሚመሰረት ሳይሆን ለጋራ ጥቅምና ለመረዳዳት፣ ልጆች በጋራ ለማሳደግ፣ የጋራ ህልምን እውን ለማድረግ፣ ሰርቶ አብሮ ለመለወጥ፣ ችግርን አብሮ ለማሳለፍ፣ ደስታን አብሮ ለመካፈል፡፡

በአጭሩ የሰው ልጆች ትልቁን ቅድስና አብሮ ለመካፈል ነው፤ ስለሆነም ትዳር ለደስታ ተብሎ ብቻ የሚመሰረት አለመሆኑን የምትገነዘብ ሴት ልጅ መፈለግ አለብህ፤ አንተ እንደምትመርጥ ሁሉ ሴቲቱም እንደምትመርጥህ እወቅ፤ትዳር ማለት የእድሜልክ ስምምነት መሆኑን ተረዳ፤  ብዙ ሴቶች በቀጥታ ባይናገሩትም ለገንዘብና ለማቴርያል ነገሮች ከፍ ያለ ግምት ይሰጣሉ፤ ይህ መሰረታዊ ነገር ነው፤ ያ ደግሞ ለመጥፎ ሳይሆን ከኛ ከወንዶቹ በተሻለ ሴቶች ጠንቃቃ ስለሆኑ ነው፡፡ በመሆኑም ብዙ ጊዜ ሴቶች ስራ ባይኖራቸውም ስራ ያለው ወንድ ያገባሉ፣ ስራ የሌላቸው ወንዶች ግን ስራ ያላትን ሴት ልጅ አያገቡም፤ ወንዶች የበላይነት ባለበት ማህበረሰብ ውስጥ ስለምንኖርም ሊሆን ይችላል፤ ይህ ማለት ወንዶች ገንዘብ አያስፈልጋቸውም ማለቴ አይደለም፤ ጉዳዩ ገንዘብ ብቻ አይደለም፣ ልጃገረድ ሴቶች ፍለጋ ብቻ ብዙ አመት የሚጠብቅ ወንድም ብዙ ነው፤ ታዲያ ለብዙ አመት ልጃገረድ የሚፈልገው ወንድ ከሌሎች ሴቶች ጋር ምንም ግንኙነት ሳያደርግ አይደለም፡፡ ለራሱ ከብዙ ሴቶች ጋር እየተኛ ልጃገረድ ብቻ ነው የማገባው ብሎ ማሰብ በራሱ የአስተሳሰብ ችግር ነው፡፡ አንድ ወንድ ልጃገረድ የነበረች ሴት ልጅ አገባ ማለት ሰላማዊ ትዳር ይኖረዋል ማለት አይደለም፡፡ በእርግጥ በሽታን ለመከላከል ሲባል ሁለቱም የመጀመሪያቸው ቢሆን ጥሩ ነው፣ ቢሆንም፣ ለስኬታማ ትዳር ከሁሉ በላይ የጋራ አላማና የመግባባት ስሜት እንደሚያስፈልግ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ በእርግጥ ወንዶችም ሆነ ሴቶች ከጋብቻ በፊት የወሲብ ህይወት ባይጀምሩ እጅግ ይበረታታል፤ በተለይ ለሴት ልጆች ከጋብቻ በፊት የሚደረገው የወሲብ ግንኙነት ወደእርግዝናና ሌሎች ችግሮች ስለሚያደርስ ቀድሞ መጠንቀቁ ይመከራል፡፡

ለተላላፊ በሽታዎች ተጋላጭነቱ ለወንዶችም ለሴት ልጆችም ተመሳሳይ ነው፡፡ ብዙዎቻችን የትዳር አጋራችንን ስብእና ምንም እንከን የማይወጣለት እጅግ ቆንጆ እንዲሆን እንፈልጋለን፤ ነገር ግን ሁሉም ሰው የየራሱ ጠንካራና ደካማ ጎኖች እንደሚኖሩት ማስተዋል አለብን፡፡ በተጨማሪም መደማመጥ ያሰፈልጋል፡፡ ያላገቡ ወዳጆቼ ትዳር ውስጥ ፀብ መኖሩን አያውቁም፤ በእርግጥ ባለትዳሮች የሚጣሉበትም አጋጣሚ አለ፤ የሀሳብ መለያየት መኖሩም የግድ ነው፤ ስለሆነም የሚፈጠሩትን አለመግባባቶች ቀለል አድርጎ መውሰድ ያስፈልጋል፡፡

ትዳር የእድሜ ልክ የአብሮነት ስምምነት ስለሆነ የጋራ ህይወት ለማቀድ ብዙ የሚያጨቃጭቁ ሀሳቦች ይኖራሉ፤ በተለይ ከልጆች መወለድ በኋላ ትዳር ፈታኝ ሊሆን ይችላል፤ ምክንያቱም የልጆች መታመም አለ፤ የአከራዮች ጭቅጭቅ አለ፤ ከስራ ቦታ የሚፈጠር ችግር ይኖራል፤ ከወሊድ ጋር ተያይዞ እናቶች ሊታመሙ ይችላሉ ወዘተ፤ ስለሆነም ትዳርን ስኬታማ ለማድረግ በጥንካሬና በመተሳሰብ መኖር ያስፈልጋል፡፡

የሰው ልጅ ውስብስብ የሆነ ፍጡር ነው፤ ከትዳር በፊት የነበረው ባህሪ ከትዳር በኋላ ሊቀየር ይችላል፤ ለውጦቹም አንዳንዴ ጠቃሚ ናቸው፤ ለምሳሌ አንድ ወንድ ልጅ ከትዳር በፊት ጭፈራ ቤት የሚያዘወትር ከሆነ ሚስት አግብቶ ልጅ ሲወልድ ግን የልጆቹ ፍቅር የኑሮ ዘይቤውን እንዲቀይር ሊያደርገው ይችላል፡፡ ስለሆነም ከትዳር በፊት ያለውን አይቶ ሁሉን ነገር መደምደም አይቻልም፤ ምክንያቱም ሰዎች ወደበጎም ወደመጥፎም ስለሚቀየሩ፤

አንድ ልብ ልንለው የሚገባ ነገር አለ፤ ብዙ ወንዶች ጭቅጭቅ ይጠላሉ፤ ለምሳሌ ወንዶች ብዙውን ጊዜ ገንዘብ በቀላሉ እናጠፋለን፤ እናባክናለን ማለት ነው፤ ብዙ ጊዜ ከቤት ውጪ ስናሳልፍ ገንዘብ የምናወጣበት አጋጣሚ ይበዛል፤ ብዙ ወንዶች እኔንም ጨምሮ ችላ ባዮች ነን ፤ ነገሮችን ችላ ብለን እናሳልፋለን፡፡ ሴቶች እህቶቻችን ደግሞ ሁሉን ነገር በጥልቀት መወያየት ሊፈልጉ ይችላሉ፤ ቀስ በቀስ ጭቅጭቅም ይፈጠራል፤ መጠኑ ቢለያይም  ወደድንም ጠላንም ጭቅጭቅ የሌለበት ትዳር ያለ አይመስለኝም፤ ይልቁንም ጭቅጭቆቹን የምንፈታበትን መንገድ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ ባለትዳሮች ሊገዙ በሚፈልጉት ሶፋ ቀለምም ሊጣሉ ይችላሉ፤ ባል ሰማያዊ ቀለም ሲል ሚስት ደግሞ ቀይ ይሁን በሚል፣ ወይም በልጆች ስም አወጣጥ ሊጣሉ ይችላሉ፣ በገንዘብ አጠቃቀም ሊጣሉ ይችላሉ፤ ስለሆነም ለመቻቻል መዘጋጀት እንጂ ምንም ጉድለት የሌለባት ሚስት፣ ወይም ጉድለት የሌለው ባል በአለም ሙሉ ፈልገን ማግኘት የምንችል አይመስለኝም፤ የተቻነውን ያህል ግን ተናግረን ማሳመን የምንችለውን ሰው መምረጥ ያስፈልጋል፡፡

አንዳንዱ ወንድ መስፈርቱ የሀይማኖት መመሳሰል ሊሆን ይችላል፤ እኔ ግን አያሳምነኝም፤ ምክንያቱም ከተመሳሳይ ሀይማኖት መሆን ማለት ለዘላቂ ትዳር ዋስትና አይደለም፡፡ በሀገራችን በብዛት የምናውቃቸው ትዳሮች የሚመሰረቱት ተመሳሳይ ሀይማኖት ባላቸው ጥንዶች መካከል ነው፤ ነገር ግን ብዙ ፍቺዎችን፤ ብዙ የትዳር ውስጥ ድብብቆሽ እናያለን እንሰማለንም፡፡ ጥሩ ትዳር የአምላክ ስጦታ ነው፤ በተጨማሪም ጥሩ ትዳር መመስረት ዋጋ ያስከፍላል፡፡ ጥዳር ዘላቂ እንዲሆን ባለትዳሮች መስዋእትነት መክፈል አለባቸው፣ ጥሩ ትዳር ማለት ደግሞ ቪላ ቤታ ያላቸው ጥንዶች፣ ሚሊየነር የሆኑ ባለትዳሮች ማለት እንዳልሆነ ልብ ማለት አለብን፤ ይልቁንስ በትዳር ውስጥ የጥንዶቹ ንቃተ ህሊና ጥሩ ካልሆነ ገንዘብ እየበዛ ሲሄድ የትዳራቸው መፍረሻ ሰበብም እየበዛ የሚሄድ ይመስለኛል፡፡ ለሁሉም ሚስት በመፈለግ የተቸገረውን ወዳጄን እባክህ እጮኛህ ባንተ መስፈርት ከመቶ 80 አከባቢ ካመጣች አግባት፤ ታዲያ ለውበት ብዙ ቦታ አትስጥ፤ ውበት እጅግ ያሳስታል፤ የሴት ልጅ ውበት አስተሳሰብዋ መሆኑን አትርሳ፤ የወንዶቹ ምክር ለሴት ልጆችም ይሆናል፡፡

ትዳራችን የተባረከ ይሁን!  ልብ በሉ፣ ሠጥቶ መቀበል የሚባል ነገር አለ፡፡ ይሄም ሀሳብ ከንቃተ ህሊና ጋር የሚገናኝ ነገር ነው፡፡ የመጨረሻ አስተያየቴ ትክክለኛ ባልና ሚስት የሚኖሩት ልጅ ከተወለደ ቀጥሎ ነው፤ በፍቅር አባዜ የነበረው ሞቅታ ቀስ በቀስ ይቀዘቅዝና ልጆች ስንወልድ ትክክለኛውን ትዳር መኖር እንጀምራለን፡፡ በነገራችን ላይ እስቲ ሁለት የንግድ ቤቶችን እንውሰድ፤ አንዱ መፅሀፍት ቤት ሲሆን ሌላው ጫት ቤት ነው፤ ሀገራችን ካለው ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት የትኛው ቤት የበለጠ ገበያተኛ ያለውና የቱ የበለጠ አትራፊ ይመስልዎታል? ለተጠቃሚው፣ ለሃገርና ለትውልድ የበለጠ ጠቀሜታ ያለውስ የትኛው ዘርፍ ነው? የነዚህ ጥያቄዎች መልሶች ናቸው የትዳራችን ምሳሌ ሚሆኑት፣ ጊዜያዊ ስሜትን ማርካት ማለት ትዳር ማለት አይደለም፣ የወሲብ ህይወት ብቻ ትዳር አይደለም፤ ይህንን ሁሉ ለመረዳት ደግሞ የባለትዳሮች የአስተሳሰብ ርቀት ይወስነዋል፡፡

በተጨማሪም የንግድ ስራዎቹ የአዲሱን ትውልዳችንንና የንግድ ስራችንን እድገት በተወሰነ መልኩ የሚያሳዩት፤ መልሱ ምንም ይሁን ምን፣ ሰንበትንና ቅዳሜን  ከጫት መቃሚያ ቀን ይልቅ መፅሀፍት ለማንበቢያነት የሚናፍቅ ትውልድ ይፈጠር ዘንድ እመኛለሁ፡፡ ብዙ ትዳሮችን አደጋ ላይ እየጣሉ ካሉት ችግሮች አንዱ ለትዳር አለመታደል/ሴሰኝነት በተለይ በከተማ አከባቢ ደግሞ ሱስ ነው /የጫት፣ የመጠጥ፣ የተቃራኒ ፆታ፣ የአደንዛዥ ነገሮች ወዘተ/ ፡፡  ጥሩ ሚስት ግን ባልዋን ከዚህ ሁሉም አይነት ሱስ ልታድነው ትችላለች፡፡ ጥሩ ባልም እንደዛው፤ ካልሆነ ግን አንተ እነዲህ አጠፋህ አንቺ ይህንን አጠፋሽ በሚል ንዝንዝ ትዳር አይመሰረትም፡፡

ጉዲፈቻ

የሀገራችን ወላጅ አልባ ህጻናት በጉዲፈቻ ከሚሄዱባት ሀገራት አንዷ ዴንማርክ ናት፤ እኔ ዴንማርክ በነበርኩ ወቅት አንዲት ማሾ የምትባል ልጅ ከሀገራችን በጉዲፈቻ ሄዳ ለማደጎ የወሰዱዋትን ቤተሰብ አባላት አልወደደቻቸውም ነበረ፤ ልጅትዋ ለማደጎ ስትሰጥ ወላጅ እናትዋ የኤችአይቪ ቫይረስ በደምዋ ስለተገኘ ሳልሞት ልጄን ላመደጎ ልስጥ ብላ መሆኑን ሰምቻለሁ፤ ቢሆንም ለማደጎ የተሰጠችው ማሾ የወሰዱዋትን ቤተሰቦች እጅግ ትልቅ ጭንቀት ሆነችባቸው፤ ልጅት ምንም ብትደረግ ሰዎቹን እንደአውሬ ማየት ጀመረች፤ ቀስ በቀስም ታማሚ ስለሆነች ለማደጎ የወሰዱት ወላጆች ለከተማ አስተዳደር አስረከቡዋት፤ ቢሆንም መፍትሄው ውስብስብ ነበረ፤ ልጅትዋ ወደወላጆችዋ ትመለስ ሲባል ቶሎ ስምምነት ላይ ለመድረስ እነደከበደ ሰምቻለሁ፡፡

የዛች ልጅ ጉዳይ አጠቃላይ የሀገራችንን የውጪ ሀገር ጎዲፈቻ እንደቀየረው ሰምቻለሁ፡፡ መሰረታዊ ችግሩ ለማደጎ መሰጠት ያለባቸውን ምንም አማራጭ የሌላቸውን ልጆች ትተን አማራጭ ያላቸውን መላካችን ነው፤ ልጆቹ ለማደጎ ከተሰጡ በኋላም ምንም ክትትል አለማድረግና ልጆቹን ከወላጆቻቸው ዘመዶች እንዳይገናኙ መደረጉ ነው፡፡ ለወደፊቱ የውጪ ሀገር ጉዲፈቻ መኖር ካለበት እጅግ ጥንቃቄ ተደርጎ ቢደረግና ልጆቹ ወደውጪ ከሄዱ በኋላ ክትትል ቢደረግ፤ ከዘመዶች እንዲገናኙ ስምምነት ውስጥ ቢኖር፤ ማደጎው የማይስማማቸው ልጆች ደግሞ መመለስ እንዲችሉ ስምምነት ውስጥ ቢካተት እላለሁ፡፡ ከሁሉ በላይ ግን የሀገራችንን ልጆች እዚሁ ሀገር እንዲያድጉ መንግስት መሰረታዊ የሆነ እቅድ አቀዶ ወደተግባር ቢቀይር፡፡

ወላጅ አልባ ህፃናትን ለውጪ ሀገር ጉዲፈቻ መስጠት ትክክል ነው ወይስ አይደለም የሚሉ ክርክሮችን እሰማለሁ፡፡ የወላጅ አልባ ህፃናት ጉዳይ እጅግ ውስብስብ ችግር ስለሆነ መፍትሄውንም ለማበጀት ከመንግስት፣መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች፣ ከሀይማኖት ተቋማትና ከማህበረሰቡ ጠለቅ ያለና መጠነሰፊ እቅድና ቁርጠኝነት ያስፈልጋል፡፡ እንደእኔ አስተያየት እኛ ኢትዮጵያዊያን ችግራችንን በራሳችን የመፍታቱ ቁርጠኝነት በጣም አናሳ መሆኑ ነው እንጂ ህፃናቱን ለማደጎ መስጠቱ አላስፈለጊ ነው ባይ ነኝ፡፡ ሁሉ ኢትዮጵያዊ ተመሳሳይ ነው ማለት ባይቻልም ለሰውልጆች ያለን ክብር ዝቅ ብሎ ለቁሳቁስ ያለን ፍቅርና ክብር ከፍ ባይል ኖሮ ልጆቻችንን ለማሳደግ ሀገራችን በቂ ሀብት አላት፡፡ አንደኛ መፍትሄው ልጆች መውለድ ያለባቸው እናቶች ብቻ መውለድ እንዲችሉ ቢደረግ፡፡ መውለድ የሌለባቸው እናቶች የቶቹ ናቸው ቢባል ለምሳሌ በጎዳና ላይ የሚተዳደሩ፤ እጅግ ድህነት ውስጥ የሚኖሩ፤ በገጠሩም ከ5 ልጆች በላይ ያላቸው ነገር ግን የእርሻ መሬት የሌላቸው እጅግ ደሀ እናቶች፤ ከከባድ ህመም ጋር የሚኖሩ ወዘተ፡፡

አንዲት ደሀ እናት ልጅ ወልዳ ልጁ ለማደጎ ወደ ውጪ ሀገር ቢላክ የበለጠ ብዙ ልጆች ለመውለድ እንደምትበረታታ ምንም ጥያቄ የለውም፡፡ ከሴትየዋም አልፎ ሌሎች ድሆችም ቢሆኑ ልጅ ወልደው ወደውጪ ሀገር ለመላክ መውለዳቸው አይቀርም፡፡ ሁለተኛ ደረጃ ልጅ በማደጎ ለመውሰድ ወደሀገራችን የሚመጡትን የውጪሀገር ዜጎች ማንነት የማወቅ እድላችን በጣም አነስተኛ ነው፡፡ ስለሆነም የተሻለ ህይወትን ተስፋ አድርገን ለማደጎ የምንሰጣቸው ልጆች ለበለጠ ስቃይ ሊጋለጡ ይችላሉ፡፡ ተጨባጭ መረጃዎችንም አይተናል፡፡ ሶስተኛው ጉዳይ ልጆችን በማደጎ መላክ እንደንግድ ድርጅት ተጀምሮ ልጆችን ወደውጪ ሀገር በመላክ አላማ ወደውጪሀገር ማደጎ የሚላኩቱ እጅግ ደሃ የሆኑትና በጣም አስቸኳይ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሳይሆኑ እዚሁ ሀገር ቤት ወላጆቻቸው ጋር በጥቂት እርዳታ ሊኖሩ የሚችሉ ህጻናት ናቸው፡፡

አራተኛው ሀሳብ ልጆችን ለማደጎ የሚወስዱት የውጪ ሀገር ዜጎች ዋናው አላማቸው ምንድን ነው? ልጆቹን መርዳት ወይስ ለራሳቸው የተለየ ፍላጎት የሚለው ነው፡፡ እንግዲህ ትልቁ ፈተና ብዙ ወላጅ አልባ ህፃናት በየጎዳናው እያየን ምንም እርዳታ ሳናደርግላቸው ቀርተን አላማቸው ምንም ይሁን ምን ድሆቹን ልጆች እናሳድጋቸው ስጡን ተብለን ስንጠየቅ አይሆንም የሀገራችን ገፅታ ስለሚጠፋ ልጆቹ ማደጎ መላክ የለባቸውም ብለን መከራከር አግባብ አይደለም፡፡ መሆን ያለበት ትክክለኛ እርምጃ ሁሉ ግለሰብና ድርጅት የበኩሉን ሀላፊነት እየተወጣ ከኛ የመርዳት አቅም በላይ የሆኑትን ብቻ ለሌሎች መስጠጥ ነበር፡፡ ግን ምን ዋጋ አለው፡፡ የሀገር ፍቅራችን የአዞ እምባ ሆነ፡፡ ሀገራችንን እንወዳታለን እያልን እየዘመርን ልጆችዋን ለመርዳት ግን ቁርጥ እርምጃ ካልወሰድን ራሳችንን መደለል ነው፡፡ ሁላችንም ልጆቹን ለመርዳት የየበኩላችንን መወጣት አለብን፡፡

ከሁሉ በላይ ግን የሀይማኖት ተቋማትና መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተባብረው አንድ ትልቅ ማእከላዊ የዜጎች መጠለያ መስራት አለባቸው፡፡ እንዲሁም በየሰፈሩ ወላጅ አልባ ልጆችን በመርዳት ሰበብ የበጎ አድራጎቱን ስራ ወደ ሰው ልጆች ንግድ ቀይረው እየሰሩ ያሉትንም አጭበርባሪ ድርጅቶች መቆጣጠር ያስፈልጋል፡፡ በተጨማሪም የጋራ ሀላፊነት/collective responsibility/ መውሰድ መቻል አለብን፡፡ የሀገራችንን ባንዲራ ለብሰን ስለሄድን ሀገራችንን ወደድን፣ሀገራችን አደገች ማለት አይቻልም፡፡ በዋናነት ሀገር ማለት ሰው መሆኑን፤የሀገር ፍቅርና እድገት ማለት ለዛሬና ለወደፊቱ ለልጆቻችን የሚተርፉ ችግሮችን ሊፈቱ የሚችሉ ትልልቅ ሀገራዊ ተቋማትን ዛሬ መገንባት መጀመር ያስፈልጋል፡፡ ሌላው ትልቁ አማራጭ ሀሳብ መውለድ የሌለባቸው እናቶች መስፈርት ተዘጋጅቶ የወሊድ መከላከያ እርዳታ እንዲያገኙ ቢደረግ፡፡ መቼም ሁሉም ማለት ይቻላል ባለትዳሮች ልጆቻቸውን አቅደው የሚወልዱት በወሊድ መከላከያ እርዳታ ነው፡፡ እነዚህ በጣም ደሀ እናቶች ግን ከግንዛቤ እጥረትና ከችግር የተነሳ የወሊድ መከላከያ አማራጮችን አይጠቀሙም፡፡

ድሆቹ እናቶች ልጅ መውለድ ፈልገው ሳይሆን ተረግዞ ነው የሚያገኙት፡፡ ልጅ ክቡር ነገር ነው፡፡ ስለዚህ አይናችን እያየ የሚወለደውን ልጅ መርዳት የማትችል እናት የወሊድ መከላከያ አግኝታ አለመውለድ ስትችል አርግዛ እንድትወልድ ዝም ስትባልና የተወለደው ልጅ በምግብ እጦት ስሰቃይ ዝም ማለት ለህሊናችንም ይከብዳል፡፡ ከሀይማኖታዊ አስተምሮትና ስርአት ጋር በማይጋጭ መልኩ መፍትሄዎችን በየአቅጣጫው ማፈላለግ ያለብን ይመስለኛል፡፡

የዩኒቨርሲቲ  ተማሪ በሀገራችን

የዩኒቨርሲቲ ትምህርት ለብዙ ወጣቶች የወደፊት ህይወታቸውን መሰረት ጥለው የሚወጡበት ቢሆንም ለጥቂቶች ግን ከቤተሰባቸው ይዘው የመጡትን ቆንጆ ማንነት አጥተው፣በከባድ ሱስና አደገኛ ወንጀል ተበክለው፣ ለራሳቸውና ለሀገራቸው እንዲሁም ላስተማራቸው ቤተሰብ ከባድ ችግር ሆነው የሚወጡበት መሆኑን አስተውለን ይሆን?…በጣም የሚያሳዝነው ደግሞ በብዛት መጥፎ ስብእና ይዘው ከዩኒቨርሲቲ የሚወጡት ተማሪዎች የከተማ ልጆች፣ ውጪ ሀገር እህት ወይም ወንድም ያላቸው፣ የሀብታም ቤተሰብ ልጆች መሆናቸው ነው፡፡ የጥፋታቸው መሰረትም ችግር ሳይሆን ልጅነት፣ቤተሰብ ጋር በነበሩ ጊዜ በከባድ ቁጥጥር የቆዩና የዪኒቨርሲቲ ህይወታቸው ከቤተሰባቸው እስርቤት ነፃ የሚሆኑበት አይነት የሆነባቸው፣ ቆንጆ ሴት ተማሪዎች፣ አልፎ አልፎም የደሃ ቤተሰብ ልጆች ናቸው፡፡ ለነዚህ አይነት ተማሪዎች ህይወት መበላሸት ተጠያቂው ማን ነው ብንል የመጀመሪያዎቹ ተማሪዎቹ ራሳቸው ቢሆኑም ሌሎች ብዙ አካላትን በየደረጃው መደርደር ይቻላል፡፡

ለምሳሌ የዩኒቨርሲቲዎቻችን የተማሪዎች አገልግሎት ቢሮዎች ድክመት የመጀመሪያው ሊሆን ይችላል፡፡ ምክንያቱም ተማሪዎቹ ከቤተሰባቸው ወተው ወደዩኒቨርሲቲዎች ሲመጡ በዋናነት ቤተሰብን የሚተካው አካል የዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎች አገልግሎት ቢሮ ነው፡፡ ስለዚህ እነሱ ቀጥተኛ ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በሶስተኛነት ደረጃ ደግሞ ለተማሪዎቹ ከመጠን ያለፈ ብር የሚልኩ ከሀገር ውስጥም ሆነ ከውጪ ሀገር ያሉ ዘመዶችም ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ይህም የሚሆነው ብዙውን ጊዜ ከልምዳችንም እንዳየነው ወደጫት ቤት፣ ወደጭፈራቤት፣ ወደሲጋራው፣ ወደመጠጥቤቱ በተደጋጋሚነት የሚሄዱት ተማሪዎች የኢኮኖሚአቅማቸው የተሻሉት ተማሪዎች ስለሆኑ ነው፡፡

በእርግጥ ተማሪዎች ገንዘብ ይላክልን ብለው ሲጠይቁ ነው የሚላክላቸው፡፡ በሱስና በአላስፈላጊ ህይወት የተጠመዱት ተማሪዎች ከዘመዶቻቸው እንዴት ሰበብ ፈጥረው ገንዘብ መቀበል እንዳለባቸው በደንብ ያውቁበታል፡፡ ለምሳሌ ላልተማረ ወንድም እህታቸው ወይም ለዘመዳቸው /ባዮሎጂ ላቦራቶሪ ውስጥ እቃ ስለተሰበረብኝ የቅጣት ብር ክፈል ተብያለሁ፣ ስልኬ ተሰረቀብኝ፣ ላብቶፔ ተሰረቀብኝ፣ ለተማሪዎች የጉብኝት ጉዞ ከኪሳችን ነው የሚስከፍሉን/ ወዘተ በማለት እንደምንም የሚፈልጉትን ብር ያስልካሉ፡፡   ቢሆንም አንድ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ በወር ውስጥ ለዋና ዋና ወጪዎች ከሚያስፈልገው ገንዘብ ያለፈ ገንዘብ መላክ የልጁን ወይም የልጅትዋን ህይወት በተዘዋዋሪ መንገድ ማበላሸት መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡

 

በተጨማሪም በተለይ ቆንጆ የዩኒቨርሲቲ ሴት ተማሪዎችን በየሆቴል ቤቶች ላሉ ማስተዋል ለተሳናቸው ሳጋቱራ ባለሀብቶች በማከራየት ስራ የተሰማሩ ደላላዎችም ናቸው፡፡ በትልልቅ ከተሞች ውስጥ ያን አይነቱ ድለላ ስራ እየተለመደ መምጣቱን ጉዳዩን በቅርብ የሚያውቁ ነግረውኛል፡፡ ሴቶቹም ተማሪዎች በጌጣጌጥ ግዢ ወጪ፣ በየቀኑ በመጨፈርና በመዝናናት ወጪ ራሳቸውን አደገኛ ቦታ ስላስቀመጡ ለደላላዎቹ ቆንጆ አጋጣሚን ፈጥረዋል፡፡ በአንድ ምሽት ለአንዲት ሴት ተማሪ እስከ 3000 ብር በመክፈል መጫወቻ ከማድረግም አልፈው የሴቶቹን ተማሪዎች የወደፊት ህይወት ወደሴትኛ አዳሪነት የሚለውጡ ባለሀብቶች እንዳሉ አንድ የሚኒባስ ሾፌር በተጨባጭ መረጃ ነግሮኛል፡፡ እስቲ አስቡት፤በአንድ ምሽት 3000 ብር ማግኘት የለመደች ወጣት የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ከተመረቀች በኋላ ምን ስራ ብትሰራ ነው ያን ያህል ገቢ የምታገኘው….በተዘዋዋሪ ሴትኛ አዳሪ ሆና የሳጋቱራ ባለሃብቶች መደሰቻ ሆና ቀረች ማለት ነው፡፡ ወይም በበሽታ ተይዛ ለራስዋም ሆነ ላስተማሩዋት ቤተሰቦችዋ የሀዘን ምንጭ ሆነች ማለት ነው፡፡ ለሀገርም ሸክም ሆነች ማለት ነው፡፡

እኔ በ1994 ዓ.ም. የቀድሞው ደቡብ የአሁኑ ሀዋሳ ዩኒቨረስቲ ተመድቤ ስገባ አብሮን የገባ ጎበዝ ተማሪ በጫትና በከባድ ሱስ ሰበብ ከባድ ሌባ ከመሆን አልፎ ሀዋሳ ከተማ ውስጥ ተገድሎ የውሃ መውረጃ ቱቦ ውስጥ የተገኘን ልጅ ታሪክ በደንብ አስታውሳለሁ፡፡ ሌሎችም ብዙ ተማሪዎች አሉ፡፡ ስለሆነም እባካችሁ ወላጆች፣ ወንድም እህቶች ከሀገር ውስጥም ይሁን ከውጪ ገንዘብ ለተማሪዎች የምትልኩ እባካችሁ ተማሪዎቹ ያሉበትን ሁኔታ በራሳችሁ መንገድ ለመከታተል ሞክሩ፡፡ ጅብ ካለፈ ውሻ እንደሚባለው እንዳንሆን፡፡

ስለወሊድ መቆጣጠሪያ

ባለትዳሮች የሚወልዱትን የልጆች መጠን ለመወሰን ያላቸው ዋናው ዘዴ የወሊድ መቆጣጠሪያ መጠቀም ነው፤ በተለይ በአሁኑ ጊዜ የኑሮ ውድነትም ስላለ ሊወለዱ የሚገባቸን ልጆች ቁጥር መወሰን ግድ ይሆናል፡፡ ነገር ግን የወሊድ መቆጣጠሪያን በተመለከተ በተለያዩ የሀይማት አስተምሮዎች በኩል ተቃውሞ ሲደረግ እንሰማለን፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ የእስራኤል መንግስት እዛ ሀገር ለሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እስራኤሎች ያለእውቅናቸው የወሊድ መከላከያ መድሀኒት ሰጣቸው የሚለው ወሬ በሀገራችንና በአንዳንድ የውጪ ሀገር ድህረገፆች መነጋገሪያ ሆኖ ነበር፡፡ ድርጊቱ የወሊድ መከላከያ የተሰጣቸውን እናቶች ሰብአዊ መብት የተጋፋ ነው በሚል ሰፋ ያለ ውይይት ሲደረግ ነበር፡፡ እኔም ስለጉዳዩ እያሰብኩ ነበረ፡፡ ለመሆኑ የወሊድ መከላከያ መጠቀም ምን ጠቀሜታ አለው? ምንስ ጉዳት አለው? እኛ ባለንበት ክፍለዘመን የወሊድ መቆጣጠሪያ የሚጠቀሙት የትኞቹ የህብረተሰብ ክፍሎች ናቸው? ሀብታሞቹ ወይስ ድሆች? የተማሩ ወይስ ያልተማሩ? ብዙ ልጆች ያላቸው ወይስ የሌላቸው? መንግስታት ህዝባቸው የወሊድ መቆጣጠሪያ እንዲጠቀም የሚፈልጉት ምን ሲሆን ነው?

 

ሀገራችን የወሊድ መቆጣጠሪያ የሚጠቀሙት ከገጠር ይልቅ በከተማ የሚኖሩ እናቶች ናቸው፡፡ በቅርቡ በሀገራችን የተደረገ ሀገር አቀፍ ጥናት እንደሚያሳየው በከተማ የሚኖሩ እናቶች በገጠር ከሚኖሩት እጥፍ የወሊድ መቆጣጠሪያ ይጠቀማሉ፡፡ በተጨማሪም አንድ መይም ሁለት ልጆች ያላቸው እናቶች ስድስት ወይም ከዛ በላይ ልጆች ካላቸው እናቶች የበለጠ የወሊድ መከላከያ ይጠቀማሉ፡፡ በክለሎች መካከልም ያለውን ልዩነት ስናይ በአዲስ አበባ ከመቶ ስልሳ አምስት እናቶች የወሊ መከላከያ የሚጠቀሙ ሲሆን በሶማሊ ክልል ከመቶ ሁለት እናቶች ብቻ ናቸው የወሊድ መከላከያ የሚጠቀሙት፡፡ የትምህርት ደረጃቸው ከስምንተኛ ክፍል በላይ የሆኑ እናቶች ምንም ካልተማረት እናቶች ጋር ሲነፃፀሩ የወሊድ መቆጣጠሪያ የመጠቀም እድላቸው በእጥፍ ከፍ ያለ ነው፡፡ በተጨማሪም ሀብታም እናቶች ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ካሉት በሁለት እጥፍ ከፍ ያለ የወሊድ መቆጣጠሪያ ዘዴዎችን ይጠቀማሉ፡፡ እንግዲህ የወሊድ መቆጣጠሪያን በተመለከተ በሀገራችን ያለው ተጨባጭ ሁኔታ በአጭሩ ይህን ይመስላል፡፡

ለመስክ ስራ ወደገጠሪቱ የሀገራችን ክፍሎች ስሄድ በአንድ ቤት ውስጥ ብዙ ህፃናት አያለሁ፤ አንዳንድ እናቶች የመጀመሪያውን ልጅ እያጠቡ ሁለተኛው ልጅ ሊወለድ መድረሱን ሳይ እጅግ ያሳዝነኛል፤ ለነኚህ እናቶች፣ በተለይም ከ4 ልጆች በላይ ያላቸውና የኑሮ ደረጃቸው በጣም ዝቅተኛ ለሆኑት የወሊድ መቆጣጠሪ መድሀኒት እንደ ክትባት ቢሰጣቸው ስህተት ነው ማለት ይቻላል? በገጠሩ የሚኖሩትና ምንም ያልተማሩት እናቶች ማርገዛቸውንም ሳያውቁ ነው እርግዝና የሚመጣባቸው፡፡ እነኚህ እናቶች ከተማሩትና በከተማ ከሚኖሩት ጋር ሲወዳደሩ መረጃ የማግኘት እድላቸው ዝቅተኛ ስለሆነ ራሳቸው አስበውበት ወስነው የወሊድ መቆጣጠሪያ ላይጠቀሙ ይችላሉ፡፡ ስለሆነም የተማሩትና በከተማ ያሉት እናቶች ይጠቅመናል ብለው እየተጠቀሙ መሆኑን ያለን ተጨባጭ መረጃ ስለሚያሳይ እጅግ ደሀ ለሆኑትና ከአራት በላይ ላላቸው እናቶችም እንደ ክትባት ቢሰጣቸው ያንን ያህል ጉዳት የሌለው አይመስለኝም፡፡  እሰቲ እንወያይበት፡፡

 

ምንም ጥያቄ የለውም የወሊድ መቆጣጠሪያ የሰውልጅ ከፈጠራቸው ድንቅ የቴክኖሎጂ ግኝቶች አንዱ ነው፡፡ በወሊድ መቆጣጠሪያ ምክንያት የሰው ልጆች የሰዎችን የመራባት የተፈጥሮ ህግን ከሞላ ጎደል በቁጥጥራቸው ስር ያደረጉበት ይመስለኛል፡፡ እንደእኔ አስተያየት የወሊድ መከላከያ የሰለጠኑ፣የተማሩ፣ቤተሰባቸውን አቅደው መኖር የሚፈልጉ ቤተሰቦች በዋናነት የሚጠቀሙ ይመስለኛል፡፡ ከድሆች ይልቅ ሀብት ያላቸው አባወራዎች በአብዛኛው የወሊድ መቆጣጠሪያ ይጠቀማሉ፡፡ ዋናው ልዩነትም የእውቀት ልዩነት እንዲሁም የሀይማኖትና የተለያዩ ባህላዊ እሴቶች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን እጅግ ጠበቅ  ያለ ሀይማኖታዊ እምነት ካላቸው እናቶች በተለየ አብዛኞቹ እናቶች የወሊድ መቆጣጠሪያ የሚጠቀሙ ይመስለኛል፡፡ ለዚህም እንደማስረጃ ከዙሪችንና በየከተሞቻችን ያሉ እናቶችን የልጆች ብዛት ብናይ የአብዛኞቹ እናቶች የልጆቻቸው ብዛት ከአራት የበለጠ አይደለም፡፡ ነገር ግን አብዛኞቹ እናቶች አማኞች ናቸው፡፡ የበለጠ ተጨባጭ ማስረጃ ከተፈለገ ቀደም ብዬ የተቀስኩትን የሀገራችንን የስነህዝብና የጤና ሪፖርት ውስጥ በከተማና በገጠር ያሉ እናቶችን የወሊድ መቆጣጠሪያና የልጆች ብዛት ልዩነት ማየት በቂ ነው፡፡

እንግዲህ ዋናው ጥያቄ የሚመጣው የተማሩትና በኢኮኖሚያቸውም የተሻለ ደረጃ ያሉ እናቶች የወሊድ መቆጣጠሪያ ከወሰዱ ድሆች እናቶች ግን በልጆች ብዛት በድህነት ሲሰቃዩ ዝም ብለን ማየቱ አግባብ ነው ወይ የሚለው ነው? በተቃራኒው ደግሞ የሚነሳው ጥያቄ ስለደሃዋ እናት የልጆች ቁጥር የምንወስንላት እኛ እነማን ነን የሚለው ነው፡፡

ጉዳዩን በመጀመሪያው ጥያቄ መሰረት ካሰብነው ለድሆቹ እናቶች አውቀውትም ሆነ ሳያውቁት የወሊድ መቆጣጠሪያ መስጠቱ ብዙም የተሳሳተ ላይሆን ይችላል፡፡ ምክንያቱም ለተማሩትና በገንዘብ አቅማቸውም ጭምር የተሻሉት እናቶች የሚመርጡትን ምርጫ ነው የመረጥንላቸው እንጂ ለጉዳት እንዲዳረጉ ታልሞ የተደረገ ስላልሆነ ተብሎ ልናስረዳ እንችላለን፡፡ በዛ አስተሳሰብም የእስራኤል መንግስት ብዙ ተሳሳተ ብለን ድርጊታቸውን ላናወግዝ እንችላለን፡፡ ከዚህ በተለየ ግን የወሊድ መቆጣጠሪያው የተሰጠው ለደሃውም ለሀብታሙም፣ለተማሩትም ላልተማሩትም፣ ብዙልጆች ላላቸውም ምንም ልጅ ለሌላቸውም፣ለወጣት ሴቶችም እንዲሁም በእድሜያቸው ገፋ ላሉትም ከሆነ ድርጊቱ  ቤተሰብን በእቅድ እንዲወልዱ ሳይሆን የነዛን ማህበረሰብ የዘር ሀረግ ቀጣይነት ለማጥፋት የታለመ ሊመስል ይችላል፡፡ እንግዲህ የእስራኤል መንግስት ከኢትዮጵያ በቅርቡ ለሄዱት እናቶች የወሊድ መቆጣጠሪያ ያለፈቃዳቸው ሰጣቸው የሚለውን ዜና እንጂ ስለተሰጣቸው እናቶች ዝርዝርና መድሀኒቱም ለሁሉ እናቶች ያለምንም መስፈርት የተሰጠ መሆኑን አላነበብኩም፡፡ የግል አስተያየቴ ግን መድሀኒቱ የተሰጠው ለምሳሌ ከስድስት ልጆች በላይ ላላቸው፣ እድሜያቸው ለገፋ እናቶች፣  በጣም ችግረኛና ደሃ ለሆኑት እናቶች ፣ እንዲሁም በህመም ለሚሰቃዩ ወዘተ እናቶች ከሆነ ድርጊቱ ብዙም ጎጂ ላይሆን ይችል ይሆናል፡፡

እስቲ የእስራኤሉን መንግስት ድርጊት ትተን ወደራሳችን ሀገር እንመለስ፡፡ እኔ ለስራ ወደገጠር የሀገራችን ክፍሎች በሄድኩ ቁጥር እጅግ የሚያሳስበኝ ጉዳይ በገጠሩ የማያቸው ህፃናት ቁጥርና ልጆቹ ያሉበት የጤና ሁኔታ ነው፡፡ በጣም የሚያሳዝነው በጣም ደሃ የሆኑ ቤተሰቦች ውስጥ ከስድስትና ከሰባት ልጆች በላይ ማየተ የተለመደ ነው፡፡ አልፎ አልፎ ደግሞ አንዳንድ እናቶች አንዱን ልጅ እያጠቡ ሌላውን አርግዘዋል፡፡ በቤቶቻቸው ውስጥ ብዙ የሚበላ ምግብ የለም፡፡ ለልጆቹ ልብስ ችግር ነው፡፡ ጫማ የሚታሰብ ነገር አይደለም፡፡ ከእናቶቹ አንዲትዋን ተጨማሪ ልጅ ለመውለድ ትፈልግ አትፈልግ ስንጠይቃት እስዋ እንደማትፈልግ ባለቤትዋ ግን እንድትወልድ እንደሚፈልግ ትነግረናለች፡፡ ወይም ሳታስበው እንዳረገዘች ትነግረናለች፡፡ ታዲያ ይህችን አይነትዋን እናት ሀኪሞች የወሊድ መቆጣጠሪያ መድሀኒት ቢሰጡአት ብዙ በደል አደረሱባት ማለት እንችላለን? ሀኪሞቹ እኮ ለራሳቸው ቤተሰብ የሚጠቀሙትን ነው ለእናቶቹ ያደረጉት፡፡ በራስዎ እንዲደረግ የማይፈልጉትን ለሌሎች አታድርጉ የሚባለውን የሚፃረር አይደለም፡፡ እሰቲ ተወያዩበት፡፡

ዴንማርክ ሀገር ያየሁት እውነታ ግን ለየት ይላል፤ በቅርቡ የዴንማርክ መንግስት አንድ የህፃናትን መዋያ ሊዘጋ መሆኑን ለውይይት አቅርቦ ነበረ፤ ምክንያቱም ደግሞ ማህበረሰቡ ልጆች መውለድ እየተወ በመሆኑ ማእከሉ ከሚቀበላቸው ህፃናት ቁጥር ጋር ሲታይ መኖሩ አስፈላጊ ስላልነበረ ነው፡፡ የአብዛኛው ያደጉት ሀገራት ችግር የህዝብ ቁጥር መቀነስ ነው፤ ስለሆነም የወሊድ መቆጣጠሪያ ያንን ያህል አይበረታታም፡፡ መንግስትም ለሚወለዱት ልጆች ነጻ ህክምናና ትምህርት እንዲሁም ገንዘብ ድጎማ ያደርጋል፡፡ እንዲሁም ሆኖ የዛ ሀገር እናቶች ልጆች ለመውለድ ብዙም ፈቃደኛ አይደሉም፡፡ አንድ የዛን ሀገር ዜጋ እንደነገረኝ የዴንማርክ መንግስት ለልጆች ና ለወላጆቻቸው የሚያደርገው ድጎማ የዛን ሀገር ዜጎች ሳይሆን በስደት ከአፍሪካና ከመካከለኛው ምስራቅ የሚመጡትን እናቶች ብዙ ልጆች እንዲወልዱ እንዳበረታታቸው ነግሮኛል፡፡ በእርግጥ በደሀ ሀገራት ያለው ልምድ ስንመለከተ ልጆች የሚበዙት በኢኮኖሚያቸው ዝቅተኛ በሆኑትና ብዙ ባልተማሩ እናቶች ቤት ነው፡፡ ስለሆነም ያደጉትን ሀገራት የባሰበት የወሊድ መቆጣጠሪያ አጠቃቀም የሚመከር ባይሆንም በሀገራችን ደግሞ ተወልደው በየጎዳናው ትምህርት ቤት መዋል በሚገባቸው እድሜ ምግብ የሚለምኑትን አይነት ልጆችተወልደው ከሚሰቃዩ የወሊድ መቆጣጠሪያ ይመከራል፡፡ የዴንማርክ የህዝብ ብዛት እየቀነሰ ያለበት ምክንያት እናቶቻቸው እጅግ የተማሩ ስለሆኑና ከቤት ውጪ ስራም ስለሚበዛባቸው ለልጆቹ እንክብካቤ ጊዜ የለም ከማለትም ይሆናል፡፡ለደሀ እናቶች የወሊድ መቆጣጠሪያ መስጠትን የምንቃወም ከሆነ ድሆቹ እናቶች ለሚወልዱት ልጆች የምግብና የጤና እንዲሁም የትምህርት ወጪ ለመሸፈን ዝግጁ መሆን አለብን፤ ካልሆነ ግን በሰው ቁስል እንጨት እንደሚባለው ይሆንብናል፡፡

ትልቁ ሌባ ማን ነው?

እስቲ ስለሌብነት እንነጋገር፡፡ ቀጥሎ ከተዘረዘሩት ሌቦች ሀገርን የሚጎዳው ና ከባዱ ሌባ ማ ነው? 1ኛ፡ የሚበላውና የሚያድርበት የሌለው የጎዳና ተዳዳሪ ገበያ ቦታ ሄዶ ሙዝ ሲሰርቅ ቢያዝ 2ኛ፡ አንድ የመድሀኒት ነጋዴ የአገልግሎት ዘመኑ ያለፈ መድሀኒት ሲሸጥ ቢያዝ፡፡ 3ኛ፡ አንድ ባለታክሲ 5 ብር ለሚከፈልበት ጉዞ 20 ብር አስከፍሎ ቢከሰስ፡፡ 4ኛ፡ አንድ የፍርድቤት ዳኛ ጉቦ ተቀብሎ ወንጀለኛውን ሳይሆን ንፁህ የሆነውን ግለሰብ ወደእስርቤት እንዲገባ ቢፈርድቤት 5ኛ፡ አንድ የሀይማኖት አባት ለእምነት ድርጅታቸው የተዋጣን ገንዘብ ለራሱ የግል ጥቅም አውሎ ቢያዝ 6ኛ፡ አንድ የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣን ለገጠር የመጠጥ ውሀ የተመደበ በጀትን ለግል መኪና ገዝቶ ቢያዝ፡፡ 7ኛ፡ አንድ ባለሀብት ቀጥሮ ለሚያሰራቸው ሰራተኞች ደሞዝ ሳይከፍል አባረራቸው፡፡ 8ኛ፣ አንድ ስራ አጥ ወጣት ታክሲ ውስጥ ከሰው ኪስ ስልክ ሰርቆ ቢያዝ፤ እስኪ ከላይ ከተዘረዘሩት ውስጥ ከባድ ጥፋት ያጠፋው ማንኛው ነው?

ሀይማኖት በትምህርት ቦታዎች

በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ከሀይማኖት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ብጥብጦችን ለማሰቀረት ሲባል ተማሪዎች ወጣ ያለ ሀይማኖታዊ አለባበስ ከመልበስ እንዲቆጠቡ ተወስኖ በየዩኒቨርሲቲዎቹ ውስጥ የተለየ ሀይማኖታዊ እንቅስቃሴዎችና አለባበሶች የተከለከለ ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ብዙ ሀይማኖተኛ ተማሪዎች ለምን ሀይማኖታዊ ልብስ አትልበሱ እንባላለን በሚል ከፖሊሶች ጋር ሲጨቃጨቁ ይስተዋላል፡፡ ምናልባት ቁጥጥሩም ከተባለውና ከሚፈለገው በላይ ሄዶ ተማሪዎችን የሚያበሳጭ ደረጃ ደርሶ ይሆናል፡፡ ሀይማኖታዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ሁሌም ወደአእምሮዬ የሚመጣው ሀሳብ ሀይማኖት ለምን የችግር መንስኤ ተደርጎ ድንደሚወሰድ ነው፡፡ ሀይማኖተኞች አማኝ ስለሆኑ ብቻ አንዳቸው ከሌላው ጋር በሰላም ለመኖር ሀይማኖትን ለምን ለሰላምና ለአብሮ መኖር እንደሰበብ መጠቀም እንዳልተቻለ አይገባኝም፡፡

ሀይማኖተኝነቱና ሀይማኖታዊ አለባበሱ ሁሉ ለመታየት ብቻ እየመሰለ ነው፡፡ አንድ አማኝ ተማሪ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ከትምህርቱ ውጪ ሀይማኖታዊ ድርጊቶችንና አለባበሶችን ከማድረግ ቢቆጠብ ችግሩ ምንድን ነው? ለሌሎች ሰላምና ምቾት እስከፈጠረ ድረስ የራሱን ሀይማኖትና ሀይማኖታዊ አለባበሱን ለግሉ አድርጎ ከሌሎች የዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ጋር ሲቀላቀል ግን እንደተማሪ ቢቀላቀል ምን አለበት? ዛሬ ዛሬ ከሞባይል ቴክኖሎጂ መስፋፋት ጋር ተያይዞ ሴት ተማሪዎች ሞባይል ይዘው ፈተና ክፍል እየገቡ ቶሎ ሰርተው የሚወጡ ተማሪዎች ውጪ ሆነው መልስ ደውለው እንደሚነግሩዋቸው ተደርሶበታል፡፡ በሀይማኖት ሰበብ የሚለብሱት ልብስ ለስርቆት አላማ ዋለ ማለት ነው፡፡ ስለሆነም ሀይማታዊ ድርጊታችን የቆንጆ ስብእናና ምሳሌ ሊሆን የሚችሉ ድርጊቶች ለማድረግ እንዲሁም በሰላም ከሌሎች ጋር መኖር ካላስቻለን፤ ሁሌም በሀይማኖት ሰበብ በደል ደረሰብኝ እያልን ብጥብጥ መፍጠርና ችግር መዘርዘር መቼ ልንተው ነው ?

ለምሳሌ ክርስቲያኖችን ልውሰድ፤ ስንቱ ክርስቲያን ተማሪ ነው ትክክለኛ ክርስትና ስብእና የሚታይበት? ስንቱ ክርስቲን ተማሪ ነው ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ፈተና ክፍል የማይኮርጅ ወይም የማያስኮርጅ? በአጭሩ ክርስትናን መኖር ለምን አቃተን? እስከመቼ ድረስ ነው ቤተክርስቲያን ሄደን እያስቀደስን፣ሀይማኖታዊ ትምህር እየተማርን፣ መዝሙሮች እየዘመርን፣ ፀሎት እያደረስን፣ ሀይማኖታዊ አለባበስ እየለበስን፣ ከቤተክርስቲያን ተመልሰን የቀን ተቀን ህይወታችንን ስንኖር ግን እየዋሸን፣ እየተጣላን፣እየተሳደብን፣ እየሰረቅን፣ እያመነዘርን፣ ሙስና እየሰራን፣ በሀሰት እየመሰከርን፣ የማይገባንን ጥቅም /የቤተክርስቲያንን ገንዘብም ጨምሮ/ እያጭበረበርን ወዘተ እስከመቼ ነው ይህንን አይነት ህይወት የምንኖረው? ሁላችንም ራሳችንን መጠየቅ ያለብን ይመስለኛል፡፡

ክርስቲያኖች ብቻ ሳንሆን ክርስቲያናዊ ስብእና እጅግ ያስፈልገናል፡፡ ሀይማኖታዊ ብቻ ሳንሆን ሀይማኖታዊ ስብእና እጅግ ያስፈልገናል፡፡ በእርግጥ በዩኒቨርሲቲ በሮች ላይ በዘበኝነት የተቀመጡት ዘበኞች ተማሪዎቹን በአግባቡ ያናግራሉ ብዬ በድፍረት መናገር ቢያቅተኝም፣ ክርስትና ግን የሰላም ሀይማኖት ነው፣ ለምሳሌ በግቢ ውስጥ ነጠላ ለብሶ መሄድ የሚያስፈልግ ከሆነ ለመማር ክፍል ስልሄድም ነጠላ መልበስ ይኖርብናል ማለት ነው፤ ይህም ማለት ነጠላው ለሀይማኖት አላማ የተለበሰ ሳይሆን የተለመደ የቀን ተቀን ልብስ ነው ማለት ነው፤ ለምሳሌ ሙስሊም እህቶች ሰውነታቸውን ሁሌም ሽፍነው ነው የሚሄዱት፣ ክፍል ሲማሩም፣ ገበያ ሲሄዱም፣ ለመዝናናት ሲሄዱም አብዛኞቹ ሰውነታቸውን ይሸፍናሉ፡፡ ስለሆነም ሰውነትን የሚሸፍን አለባበሳቸው በሀይማኖት ቦታቸው ብቻ ሳይሆን በቀን ተቀን ኑሮዋቸው የሚከተሉት ነው፡፤ ስለሆነም ሰውነታቸውን ሸፍነው ወደመማሪያ ክፍል ቢመጡ ያሳምናል፡፡ ነገር ግን ቤተክርስቲያን ለመሄድ ብቻ ነጠላ የሚለብስ ክርስቲያን ወጣት ዩነቨርሲቲ ግቢ ውስጥ ነጠላ መልበሱ አያስፈልግህም ቢባል ባያምነበትም ከሌሎች ጋር ለመኖር ሲል ቢቀበለው ያንን ያህል ችግር ያለው አይመስለኝም፡፡ ይህን ሀሳብ ከፖለቲካ ነፃ በሆነ አስተሳሰብ ብቻ ነው ማየት ያለብን፡፡ ጉዳዩን ፖለቲካ ካደረግነው ግን ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ቤተክርስቲያን ወይም መስጊድ ይሰራልኝ ብሎ የሚጠይቅ ተማሪም ተከራክሮ ሊያሸንፍ ይችል ይሆናል፡፡

የሀገራችን ህዝቦች ሀይማኖትን በተመለከተ እጅግ ቆንጆ የሚባል የመከባበርና በስምምነት አብሮ የመኖር ታሪክ አላቸው፡፡ ስለሆነም የተማርን የምንባለው በየዩኒቨርሲቲዎችና የተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት ላይ የምንገኝ ዜጎች ህዝቡ ያቆያቸውን እሴቶች እንደምንም ብለን በመቻቻል የማቆየትና የየግልና የጋራ ሀላፊነት እንዳለብን ማወቅ አለብን፡፡ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በፖለቲካና ትምህርት ነክ ጉዳዮች ተያይዞ መጨቃጨቅ የተለመደ ነው፤  ነገር ግን የብሄረሰብና የሀይማኖታዊ  ጉዳዮችን በተመለከተ የኔ ብሄረሰብ ይበልጣል፣  የኔ ሀይማኖት ይሻላል፣ ወዘተ በሚሉ ሀሳቦች ላይ ሰፊ ክርክርና ጭቅጭቅ ማድረግ አላስፈላጊ ወደልሆኑ ነገሮች እንደሚያደርሱን መረዳት አለብን፡፡

ዩኒቨርሲቲ ደግሞ ሳይንሳዊ እውቀት እንጂ ሀይማኖታዊ እውቀት ለመማር የምንገባበት ቦታ አይደለም፡፡ ይልቁንም በሀይማኖታችን ጠንክረን ሀይማኖታዊ ስብእና ቢኖረን ለራሳችንም፣ ለቤተሰቦቻችንም፣ አብረውን ለሚማሩት ተማሪዎችም፣ ለደሀ ሀገራችንም የነገ ተስፋዎች እንሆለን፤ በተጨማሪም ሀይማኖታዊ ህይወታችን በሳይንሳዊ አለም የሚያጋጥሙንን ችግሮች በትእግስት ለማለፍ ይጠቅመናል፤ ስለሆነም የሀገራችን ልማት የወደፊት ሞተሮች እንሆናለን፡፡ ከዛ ባለፈ ግን ለምን ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ሀይማቴን እንዳላስፋፋ ተከለከልኩ ብለን ችግር ከፈጠርን ግን ለራሳችንም ሳንሆን፣ ለሌሎችም እንቅፋት ሆነን፣ ለሀገራችንም ኪሳራ አመጣን ማለት ነው፡፡ ንቃተ ህሊናው የተሻለ ዜጋ ያስፈልገናል፡፡ በሰበብ አስባቡ ችግር ፈጣሪ ሳይሆን ችግር ፈቺ ዜጎች ያስፈልጉናል፡፡

በሀገራችን ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ተማሪዎች ከተለያዩ ብሄረሰቦችና ሀይማኖት ተሰባስበው በአንድ ዶርም ውስጥ እስከ 6 ወይም 8 ሆነው አብረው ይኖራሉ፡፡ በዚህ ተጨባጭ ሁኔታ ተማሪዎች የትምህርትና የዶርም ቆይታቸው ያማረ እንዲሆን አብረው ከሚኖሩት ጋር እንደወንድም በመተያየት አብረው መኖር አለባቸው፡፡ አንዳንዱ ተማሪ አልፎ አልፎ ሀይማኖታዊ መዝሙሮችን ወይም አለማዊ ዘፈኖችን ድምፅ ከፍ አድርጎ በማዘፈን ዶርም ውስጥ አብረው የሚኖሩትን ተማሪዎች የሚረብሹበት አጋጣሚ አለ፤ ተመሳሳይ አጋጣሚ ሲፈጠርም በመመካከርና በመቻቻል መፍትሄ መፈለግ ያስፈልጋል እንጂ አላስፈላጊ የሀይማት ክርክር ውስጥ መግባት አያስፈልግም፡፡ ዩኒቨርሲቲ ለየት የሚያደርገው ብዙ ወጣቶች በብዛት በአንድነት በመኖር የተሻለ ዜጋ ለመሆን የሚታገሉበት ቦታ ነው፡፡ በሂደቱ ከሚፈጠሩት ሁኔታዎች አንዱና ትልቁ ጉዳይ መቻቻልና ሙሉ ትኩረትን ወደትምህረት የማድረግ አስፈላጊነት ነው፡፡ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ብዙ ፈተና አለ፤ ከቤተሰብ ተለይቶ መኖር በራሱ አንድ ትልቅ ፈተና ነው፤ በተጨማሪም የተለያየ ባህሪና ፍላጎት ካለው ሰው ጋር መኖር ሌላ ፈተና ነው፤ የምግቡ ሁኔታም ፈተና ነው፣ የትህምህርቱ ክብደትም ፈተና ነው፣ የተቃራኒ ፆታ ፍቅርም /በተለይ ለሴት ተማሪዎች/ ትልቅ  ፈተና ነው፤ የሀይማኖትና የብሄረሰብ ልዩነት ሌላ ፈተና ነው፤ የተለያየ ሀይማኖት ተከታይ ጋር አንድ ቤት መኖር ፈተና ነው፤ ከተለየ ባህል ተስማምቶ መኖር ፈተና ነው፤ ካልሲውንና እግሩን ከማያጥብ ተማሪ ጋር አንድ ቤት ውስጥ መኖር ፈተና ነው፣ ሲተኛ በጣም ከሚያንኮራፋ ሰው አጠገብ መተናትም ፈተና ነው፡፡

በእኩለ ለሊት ድምፁን ከፍ ድርጎ እየሳቀ ስልክ ከሚያወራ ተማሪ ጋር መኖርም ፈተና ነው፤ ጫት ከሚቅምና ሲጋራ ከሚያጨስ ተማሪ ጋር አንድ ዶርም መኖር ፈተና ነው፤ ስለሆነም ውጤታማ ተማሪ ሆኖ ለመመረቅ እነኚህን ሁሉ ፈተናዎች በአሸናፊነት በመወጣት ነው፡፡ ጫት መቃም ሰይጣናዊ ድርጊት ነው እየተባለ ያደገ ተማሪና ወላጆቹም፣ ጎሮቤሮቹም፣ ሰርግ ቦታም፣ ለቅሶ ቤትም፣ መምህራኑም፣ ተማሪዎችም፣ ፖሊሶችም፣ የመንግስት ባለስልጣናትም፣ የሀይማኖት አባቶችም በአጭሩ አብዛኛው የማህበረሰቡ አባላት ጫት ከሚቅሙበት ማህበረሰብ የመጡ ወጣቶች ዪኒቨረሲቲ አንድ ዶርም ውስጥ ይገናኛሉ፤ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ጫት መቃም ባይፈቀድም ጫት ገዝቶ ቀነጣጥቦ ፓንቱ ውስጥ አድርጎ ይዞ ገብቶ ዶርም ውስጥ የሚቅም ብዙ ተማሪ አለ፡፡ በዚህ ሁኔታ መቻቻል የግድ አስፈላጊ የሆነ መፍትሄ ነው፡፡

የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ለጥናት ሲባል ብዙ ነገሮችን ይሞክራል፤ አንዳንዱ ሲያጠና ያዘምራል፤ ካልዘመረ ማጥናት የማይችል ብዙ ነው፤ እኔ ሳጠና አጤረራ አወጣለሁ/አጤረራ ማለት እኔ እስከማውቀው ድረስ የቃሉ ምንጭ ጫት ከሚቅሙ ተማሪዎች የተገኘ ሲሆን ትርጉሙ በአጫጭር መቁረጥ ማለት ነው/ ስለሆነም እኔ ሳጠና አጫጭር ማስታወሻዎችን እወጣለው፡፡ አንዳንዱ ደግሞ ሲያጠና ምንም ድምጽ መስማት የለበትም፤ ሌላው ጫት መቃም አለበት፤ አንዳንዱ ቡና መጠጣት አለበት፤ ሌላው ብዙ ጊዜ መደጋገም አለበት፤ አንዳንዱ የታደለ ደግሞ

አንዴ አንብቦ ብዙ ያስታውሳል፤ አንዳንዱ ደግሞ የሚያጠና ሰው አጠገቡ ሲኖር በፍርሀት በደንብ ያጠናል፤ አንዳንዱ ደግሞ ድምፁን ከፍ ኣድረጎ ሲያነብ ነው በደንብ የሚያጠናው፤ አንዳንዱ ፈተና ሲቃረብ ብቻ ያጠናል፡፡ እኔም ፈተና እየከበደኝ ሲመጣ የአጠናን ስልቴንም ቀይሬ ጫት እየቃምኩ ለማጥናት ሞክሬ ነበረ፤ ቢሆንም ጫት ተቅሞ ብዙ ማንበብ ቢቻልም የተነበበውን ሁሉ ማስታወስ እንደማይቻል ከራሴ ተሞከሮ አይቻለሁ፡፡

ይልቁንም እጅግ ውጤታማ የሆነ የጫት አቃቃም ሆኖ ያገኘሁት ለ20 ደቂቃ ብቻ ጫት ከተቃመ በኋላ ቶሎ ወደቤተመፅሀፍት በመሄድ ንባብ መጀመርና ጥናት በሌለበት ወቅት ጫት አለመቃምን ነው፡፡ በዚህ የአቃቃም ዘዴ የ15 ብር ጫት ለ10 ተማሪዎች ሊበቃ ይችላል፡፡ ለ2 ደቂቃ ብቻ የሚቃመው ጫት ቡና እንደመጠጣት ሊቆጠር ይቻላል፤ በእኔ ተሞክሮ ቡና ለሊቱን ሙሉ እንቅልፍ እንዳልተኛ ስለሚያደርገኝ ለጥናቴ ተመራጭ አልነበረም፤ ስለሆነም በዩኒቨርሲቲ ቆይታዬ ቡና በመጠጣት አጥንቼ አላውቅም፤ ጫትን በተመለከተ ወጣጦች እጅግ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው፤ የመጀመሪያው ጥንቃቄ ሰውነታቸው ጫትን እየተለማመደ ይሄድና ለማጥናት ጫት መቃም የግድ አስፈላጊ ወደሚሆንበት የከባድ ሱሰኝነት ደረጃ እንደሚደርስ መገንዘበ ነው፡፡

ስለሆነም ጊዜ ለማሳለፍ የሚደረገው የጫት መቃም ልምድን ማስወገድ አለባቸው፤ በተጨማሪም ለማጥናት ጫት መቃም የግድ አስፈላጊ ከሆነ ከ20 ደቂቃ በላይ ቁጭ ብሎ መቃም አእምሮን ከመጠን በላይ ስለሚያነቃቃ የማስታወስ ሀይልን ይቀንሳል፡፡ በተጨማሪ ደግሞ ጫት የመቃም ልምድ የሌለው ተማሪ ፈተና ሊከብደኝ ይችላል በሚል ፍርሀት ጫት መቃም መጀመር የለበትም፡፡ በዩኒቨርሲቲ ህይወት ውጤታማ ለመሆን ከሁሉ በላይ የሚመከረው ዘዴ ጊዜን በአግባቡ መጠቀም ነው፡፡ ተማሪው የሚማራቸውን ትምህርቶች ከስር ከስሩ የሚያጠና ከሆነ ፈተና በሚደርስበት ወቅት ምንም የፍርሀት ችግር አይኖርበትም፡፡ ፈተና ሲደርስ የሚፈሩትና አላስፈላጊ ለሆነ ሱስ የሚጋለጡት ተማሪዎች በተለይ ከከተሞች የሚመጡት የሀብታም ቤተሰብ ልጆች ጊዜያቸውን በጭፈራና በመዝናናት አባክነው ፈተና ስደርስ ብዙ የጥናት ስራ ስለሚጠብቃቸው ጭንቀት ውስጥ ይገቡና ለፍርሀትና ለጭንቀት ማስታገሻ ጫት ይቅማሉ፤ ጫት የቃመ ሰው አእምሮው ስለሚነቃቃ አላስፈላጊ ድፍረት ውስጥ ይገባል፡፡ መርቅነው የሚነዱ ሾፌሮችም አደጋ የሚያደርሱት የቃሙት ጫት ከመጠን በላይ ስለሚያነቃቃቸው የሚያሽከረክሩትን መኪና ከመጠን በላይ ይነዳሉ፡፡  የመኪና አደጋም ይፈጠራል፡፡ ጊዜውን በአግባቡ የማይጠቀም የዩኒቨርሲቲ ተማሪም በአንድ ምሽት ደብተሮቹን በሙሉ አንብቦ ይጨርስና ፈተና ክፍል ሲገባ ማስታወስ ያስቸግረዋል፡፡

ከዩኒቨርሲቲ መመረቅና ስራ አጥነት

ከስምንት አመት በፊት ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት ልቀጠር ከምኖርበት አርሲ ሴሩ ከተማ ተጠርቼ ወደሀዋሳ መምጣት ነበረብኝ፡፡ ለስራው ለመጠይቅ ስጠራ ከዩኒቨርሲቲ መመረቄን አስመልክቶ ወላጆቼ ትልቅ ድግስ ደግሰው ነበር፡፡ በድግሱም ሰበብ ወላጆቼ ብዙ ብር አውጥተዋል፡፡ ምንም ድግስ መደገስ የለበትም ብልም እናት አባቴ ሊሰሙኝ ስላልፈለጉ ደስ ባላቸው መልኩ ለክርስቲያንም ለሙስሊምም እምነት ተከታዮች ታርዶ ትልቅ ድግስ ተደገሰ፡፡ ቢሆንም ለስራው ቃለመጠይቅ ወደሀዋሳ ስሄድ አባቴ ለድግሱ ብዙ አውትቶ ስለነበረ ምንምአልነበረውም ስለሆነም አባቴ በከተማችን ካሉት አራጣ አበዳሪዎች አንዱ ዘንድ ሄዶ 150 ብር ተበደረ፡፡

የተበደረውም 150 ብሩን እስከነወለዱ ከአንድ ወር በሁዋላ ሊመልስ ነው፡፡ በአንድ ወር 100 ብር የሚወልደው 10 ብር ነው፡፡ በጣም የሚገርመኝና የማልረሳው ጉዳይ አራጣ አበዳሪው ሰው ለአባቴ ያበደሩት 150 ብር ቢሆንም የ150 ብሩን ወለድ 15 ብር ቀንሰው 135 ብር ሰጥተውት መጣ፡፡ የተበደርከው 150 የተቀበልከው ግን 135 ብር፣ ለምን 150 ብር አልሰጠህም ስለው አበዳሪው ወለዱን ላትሰጠኝ ትችላለህ በሚል ፍራቻ ነው ቀድሞ 15 ብር የቀነሰው አለኝ፡፡ እጅግ ገረመኝ፤ አሳዘነኝም፡፡ ከሁሉ በላይ ያዘንኩት የነበረው ግን በራሴው ወላጆች ነበር፡፡ ከሳምንት በፊት ትልቅ ድግስ ደግሰው ነበር፡፡ ድግሱ አያስፈልግም ስላቸው ሊሰሙኝ አልፈለጉም፡፡ ምክንያታቸው የነበረው የብዙ ሰው ውለታ አለብን፡፡ እኛ ከማን እናንሳለን? አንተ ደግሞ ጎበዝ ተማሪ ነህ፤ በዲግሪ ነው የተመረከው፤ ሰው ምን ይለናል ወዘተ የሚሉ ምክንያቶችን ደረደሩልኝ፡፡ ቢሆንም ከሳምንት በኋላ ትምህርት የተማርኩለትን ስራ መስራት እስክጀምር ድረስ የሚያስፈልገኝን ወጪ ሊሸፍኑልኝ አቃታቸው፡፡ ይህንን አይነቱ ችግር በብዙ የገጠር ኢትዮጵያ ቤተሰቦች ዘንድ የተለመደ ነው፡፡

ትንሽ ድግስ ቢጤ ካለች ቤት ያፈራን ሁሉ ጭርስ አድርጎ ይደገሱና ከዛ ቤተሰቡ ችግር ላይ ይወድቃል፡፡ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሚባለው ዪኒቨርሲቲው ባወጣው ማስታወቂያ ተወዳድረን ሁለት ተማሪዎች አልፈን ለቅጥር ከተጠራን በኋላ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ ሀላፊዎች የቅጥር ውላችንን ለመፈረም ፍቃደኛ አልነበሩም፡፡ ምክንተቸውም እነኚህ ልጆች ተቀጥረው ምን ሊሰሩ ነው? እስቲ በትምህርት ክፍሉ ያለው የሰውሀይል ፍላጎት ተሰርቶ ይምጣልን አሉ፡፡ የሰው ሀይል ፍላጎት የሚጠየቀው ሰራተኛ ለመቅጠር ማስታወቂያ ወጥቶ፤ ኮሚቴ ተዋቅሮ፤ውድድር ተደርጎ፤ በውድድሩ ያለፉና ተጠባባቂዎች ከታወቁ በኋላ ነው ወይስ በፊት? እኛ እኮ ኑና የቅጥር ፕሮሰስ ጨርሱ ተብለን ነው የተጠራነው…ብዙ ወጪ አውጥተናል፤ቤት ተከራይተናል…ወዘተ ብለን ብንጠይቅም ሰሚ የለም፡፡

የትምህርት ክፍላችንን ስንጠይቅ ኮሌጁን ጠይቁ ይሉን ነበር፡፡ ኮሌጁን ስንጠይቅ የዩኒቨርሲቲውን መሪዎች ጠይቁ ይሉን ነበር፡፡ እንዲሁ ሲያንገላቱን እዛው ግቢ አንድ መምህራችን ፕሮጀክት ስለነበራት እዛው በተሻለ ደሞዝ ተቀጠርን፡፡ እንግዲህ አስቡት 135 ብር ተሰጥቶኝ ነው ከቤተሰቦቼ ጋር የተሸኘሁት፡፡ ነገር ግን በተለያዩ ምክንያት የለሽ ሰበቦች ስራውን ተከለከልን፡፡ እድሜ ለጓደኞቼ፤ ገንዘብ ተበድሬ እንደምንም ያቺን ጊዜ አለፍኩ፡፡ አንዳንዴ ዩኒቨርሲቲዎቻችን የአሰራር ምሳሌ መሆን ሲገባቸው እጅግ የወረዱ አሰራሮች ሲሰሩ ማየት ያሳዝናል፡፡

እዛው ዩኒቨርሲቲ እያስተማርኩ ቅድስት ማርያም ዪኒቨርሲቲ ለርቀት ተማሪዎች ቱቶሪል አስተምር ነበር፡፡ ከእለታት አንድ ቀን እዛው ቅድስት ማሪያም ትምህርት ቤት ለማስተማር እየሄድኩ ነው፡፡ ቦታው ቅርብ ስለሆነ በእግሬ ነው የምሄደው፡፡ ነገር ግን የማስተማሪያ ቦታ ተቀየረ ተብሎ ክላስ ሊጀምር 5 ደቂቃ ሲቀር ተደወለልኝ፡፡ በጣም የሚገርመው በኪሴ ምንም ብር የለኝም ነበር፡፡ ምን ላድርግ? ታክሲ መያዝ አለብኝ፡፡ ካልሆነ በእግሬ ከሄድኩ እዛ ስደርስ የትምህርት ክፍለጊዜው ያልፋል፡፡ ግን ብር አልያዝኩም፡፡ አንዲት ቢክ እስክሪብቶ ኪሴ አለች፡፡ ያለኝ አማራጭ ያቺን እስክሪብቶ መሸጥ ነው፡፡ አንዱ ሊስትሮ ጋ ጠጋ ብዬ ባክህ ይቺን እስክሪብቶ ግዛኝ አልኩት፡፡ አዲስ እስክሪብቶ ናት፡፡ ዋጋዋ አንድ ብር ነው፡፡ ልጁ 50 ሳንቲም ሰጠኝ፡፡ አላመነታሁም፡፡ ተቀበልኩት፡፡ ከዛ የ50 ሳንቲም መንገዱን በታክሲዋ ሄድኩኝ፡፡ ተማሪዎቹ ካሉበት ቅርብ ርቀት ላይ ጣለችኝ፡፡ ሁለት ሰአት አስተምሬ ስጨርስ 500 ብር አካባቢ ተቀበልኩና ወደቤቴ ተመለስኩ፡፡

የሆነው ነገር ዛሬ ድረስ ይገርመኛል፡፡ ምንም ሳንቲም ኪሴ ውስጥ ሳይኖር ከቤቴ መውጣቴና እስክሪብቶዬን መሸጤ፡፡ ህይወት እንደዚ ናት፡፡ ውጣ ውረዱና እነኛን ውጣ ውረዶች በብርታት ስናልፍ ደስታ ይሰጠናል፡፡ አንዳንዴ ሳስበው ችግር የሕይወት ማጣፈጫ ቅመም ይመስለኛል፡፡ ችግር ያለበት ህይወት አያሰለችም፡፡ ሰዎችን ለጥረት ያነሳሳል፡፡ በእርግጥ በሀገራችን መአት ችግሮች እያሉ ምንም ችግሮች የሌሉብን ይመስል ኩራታችንና ማን አለብኝነታችን አይቻልም፡፡ የተራቡ ልጆች በየመንገዱ ላይ እያየን አልፈን እጅግ ትልቅ ስራ እየሰራን ይመስል ቢጠሩን የማንሰማበት ጊዜ አለ፡፡ የሚያማምሩ ሸሚዞችና መኪና ነገር ከኖረን በቃ፡፡ ህይወት ሙሉ ናት ማለት ነው፡፡ ሁላችንም እንደኢህ አይነቶች ነን ማለቴ አይደለም፡፡ ብዙ አርቆ አሳቢ ዜጎችም አሉን፡፡

ቢሆንም ጥቂት ወንድሞችና እህቶቻችን በተሳሳተ አስተሳሰብ ተመርተው ክፍል ውስጥ ሲያስተምሩ የተማሪዎችን ሞራል የሚነኩ፤እጅግ ከባድ ስድቦች የሚሳደቡ፤ ወይም የድሆችን የስራ እድል መንገድ የሚዘጉ፤የሀገርና የወገን ሀብት ለግል ጥቅማቸው የሚያውሉ…ወዘተ የሉም ማለት አይቻልም፡፡ ይልቁንስ የዜጎቻችንን ንቃተ ህሊና ከፍ ለማደረግ፤ አንዳችን ለሌላው የበጎ ምግባር ምሳሌ መሆን ይጠበቅብናል፡፡ ለዚህ ደግሞ በተሻለ የመማር እድል ያገኘን፣ የገንዘብና የቁሳቁስ ችግር የሌለብን ወዘተ ያለንን በማካፈል፤ ያሳደገንና ያስተማረንን ማህበረሰብ ችግሮች ለመፍታት መፍትሄ መፈለግ አለብን፡፡

ሌባን ለመያዝ?

በሀገራችን ብዙ ሙስና መኖሩ ይታወቃል፤ ስለሆነም የሙስና መኖርን መዘርዘር ሳይሆን ሙስናውን ማቆም የሚቻልበትን መንገድ ማፈላለጉ እጅግ ታላቅ ጠቀሜታ አለው፡፡ የመጀሪያው አማራጭ ባንኮቻችንን እንደፖሊስ መጠቀም ነው፡፡ ባንክ እንዴት ፖሊስ ይሆናል ብለን ልንጠይቅ እንችላለን፤ ነገር ግን ይቻላል! የሰለጠነው አለም ሌቦችን ከሚይዝባቸው መንገዶች ትልቁ ባንክ ነው፤ ወንጀለኞችንና ሌቦችንም ጭምር በባንክ ተከታትለው ይይዛሉ፤ በተጨማሪም የገቢ ቀረጥ መጠንን ለመወሰን ሀገራት በዋናነት የባንክን መረጃ ይጠቀማሉ፤ የገንዘብ ዝውውር መቁጥጥር ስር መዋል አለበት፤ በእርግጥ የገንዘብ ዝውውርን መቆጣጠር ለገንዘብ እንቅስቃሴ አመቺ ባይሆንም ዋናው የሀገር ጥቅም ስለሆነ የገንዘብ ዝውውርን አቀላጥፈን ለሌቦች ቀዳዳ ከማበጀት ዝውውሩን ቀንሶ ሌቦቹን መያዝ ያስፈልጋል፡፡ የመጀመሪያው እርምጃ በባንክቤት አካውንት ለመክፈት ሁሉም ሰው ተመሳሳይ ስምና ተመሳሳይ አድራሻ እንዲሁም መታወቂያ ቁጥር እንዲኖረው ነው፤ ስለሆነም አንድ ሰው ከአንድ በላይ መታወቂያ እንዳይኖረው መደረግ አለበት፤ መታወቂያው ላይም እያንዳንዱ ግለሰብ የት ባንክ አካውንት እንደከፈተና የከፈተበት ጊዜ ምልክት መደረግ አለበት፡፡

ይህ እጅግ አስፈልጊ ነው፤ አሁን ባለን አሰራር አንድ ሰው የፈለገውን ያህል የባንክ አካውንት በሀገሪቱ ባንኮች ሁሉና በየቅርንጫፎቻቸው መክፈት ይችላል፤ ይህም ወንጀል አይደለም፣ እንዲሁም በሁሉም ባንኮች በየቀኑ የፈለገውን ያህል ገንዘብ ማስቀመጥ ይችላል፤ ከባንክም ገንዘብ አውጥቶ ቤት መግዛት ይችላል፤ መኪናም መግዛት ይችላል፡፡ ማንም የገንዘቡን ምንጭ የሚጠይቅ የለም፤ ቢጠየቅም እጅግ የተጋነነ ከሆነ እንጂ ከያንዳንዱ ባንክ አንድ ሰው ያወጣው ገንዘብ የምናውቅበት መንገድ የለንም፤ ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ገንዘቡን ከየት አመጣሀው የሚል ጥያቄ የለም፤ ለምሳሌ ሰዎች መኖሪያ በት ሲገዙና ሲሸጥ ቤቱን የሚገዛው ግለሰብ የገንዘብ ምንጭ መታወቅ አለበት፤ በአሁኑ ወቅት ምንም ስራ በሌለው ሰው ስም ቤት መግዛት ይቻላል፤  ተማሪው ቤት የሚያስገዛ ገንዘብ ከየት አመጣ ብሎ የሚጠይቅ ስርአት የለንም፡፡

በየከተሞቻችን ብዙ ባለቤት የሌላቸው ቤቶችና ፎቆች አሉ ሲባል የምንሰማው ክትትላችን ደካማ ስለሆነ ነው፤ በመሆኑም ለሌብነትና ለሙስና መንገዱን ሰፋ አድርገነው ነው የሰራነው፤ በዚህ አይነት አሰራር እንዴት ሌባ መያዝ ይቻላል? የሀገራችንን ነጋዴዎችና ባለሃብቶች የገቢቀረጥስ እንዴት ይታወቃል??? ስለገቢ ቀረጥ ጉዳይ አንዱን ወዳጄን ስጠይቀው፣ ሀገራችን ውስጥ ትክክለኛ የገቢ ቀረጥ ከፋይ የመንግስት ሰራተኛ ብቻ ነው አለኝ፤ እውነት ነው፡፡ ነጋዴው ገቢው ስንት እንደሆነ በምን ይታወቃል?? ለምሳሌ ከገጠር አከባቢ ሰንጋ በሬዎች የሚነግዱት ገበሬዎች ትርፍ ስንት እንደሆነ የገቢዎች ባለስልጣን እንዴት ያውቃል? የሀገራችን ገቢ ቀረጥ ጉዳይ አይንን ጨፍኖ እንደመራመድ አይነት ነው፤ በጋርዮሽ አሰራር ስለሆነ የምንሰራው ኮምፒውተር ቢገዛ፣ ኢንተርኔት ቢገባ፣ አሰራራችን መቼውንም ሊጸዳ አይችልም፡፡ ሌላው ቢቀር አንድ ሰው ከሁለት በላይ የባንክ አካውንት እንዳይኖረው ማድረግ አይቻልም?? ወይም ከአንድ በላይ የባንክ አካውንት ከተከፈተ የሁለቱ ባንኮች አሰራር መናበብ አለበት፤ ለነገሩ ብዙ የባንክ አካውንት መክፈት መቻሉና የገቢ ቀረጥ ጉዳይ ግልፅ አለመሆኑ የሚጠቅመው ሌቦችን ነውና ሁሉም ለሌብነት እንዲያመች ከደሀው የሀገሪቱ ህዝብ ስር እየተሰረቀ በመንግስትም በግልም ባንኮች ሁሉ አካውንት እየከፈተ ለስርቆቱ ያመቻቻል፡፡ ባንኮቻችን አለም አቀፍ አሰራር እንዴት እንደሆነ ሳያውቁ ቀርተው ሳይሆን ጉዳዩን ችላ በማለት ቀዳዳዎቹን መዝጋት ያቃታቸው ይመስለኛል፡፡ ይህንን ሀሳብ ለመጻፍ ያነሳሳኝ ዴንማርክ ሀገር ስለባንክ አሰራር የማውቀውን ያህል ለራሴ ሀገር በመመኘት ነው፡፡

ከዴንማርክ ሀገር በነበረኝ ልምድ ማንም ሰው ተነስቶ በየባንኩ የባንክ ደብተር ማውጣት የለበትም፤ የሚያወጣ ከሆነም መታወቂያው ተመሳሳይ ስለሆነ መንግስትና የገቢ ግብር ባለስልጣን ሙሉ ገቢውን በሙሉ ማወቅ ይችላሉ፤ ምክንያቱም የእያንዳንዱ ዜጋ መታወቂያ ስለዜጋው የገቢ ምንጭ፤ አድራሻ፤ ቋሚ ንብረት፣ የጤና፣ የትምህርት፣ የቤተሰብ ሁኔታ፣ ወዘተ ከመታወቂያው ጋር ይገኛል፤ ስለሆነም የአመታዊ ገቢና የቋሚ ንብረት መረጃው በግልፅ ስለሚታወቅ ለሌቦች አመቺ አይደለም፡፡ ይህ ሀሳብ ከእውነት የራቀ ሊሆን ይችላል፤ ከተወሰኑ አመት በፊት ባንክ በሞባይል መጠቀም እንችላለን ቢባል ማመን አንችልም ነበረ፤ ዛሬ ግን ብዙም አይደንቀንም፤ ቴክኖሎጂው እጃችን ስለገባ፤ ለወደፊትም ሀገራችንን ከሌቦች ለመከላከል የእያንዳንዱን ግለሰብ የገንዘብ ምንጭና ንብረት ወደመቆጣጠር መሄዳችን አይቀርም፤ ለሁሉም ብዙ አርቆ የሚያስብ ትውልድ ያስፈልገናል፤ የራሱን ጥቅም ከሀገር ጥቅም የማያስቀድም፡፡

የልጆቻችን ትምህርት ቤት

ከልጆቻችን የትምህርት ቤት ውሎ የምንሰማቸው አስገራሚ የመምህራን ንግግሮች
በቅርቡ እኔና አንድ ዶክተር እንዲሁም ሾፌር ስለልጆቻችን የትምህርትቤት ውሎና የሰማናቸውን ጉዳች ስንወያይ፣ በአሁኑ ወቅት በሀገራችን በማስተማር ሙያ ላይ የተሰማሩ መምህራን ስነምግባር ምን ደረጃ ላይ እንደለ ስንገመግም ነበረ፡፡ መጀመሪያ ሾፌሩ በቅርቡ የገጠመውን ችግር ነገረን፤ አንዲት የዘመድ ልጅ 6ኛ ክፍል ተማሪ ናት፡፡ ተማሪዋ ገጠር አድጋ ወደከተማ ዘመድ ጋር ሆና ለመማር ነው የመጣችው፡፡ ልጅቱ አይናፋር ናት፡፡ ከክፍላቸው መምህራን አንዱ መምህር ይህችን ልጅ በተደጋጋሚ ይዘልፋታል፤ ባገኘው አጋጣሚ ተማሪዎችን ያስቅባታል፤ ‹ትምህርት ቤት ላይሽ ላይ ቢሰራም አይገባሽም› ወዘተ እያለ ደካማ ተማሪ መሆንዋንና ተስፋ አስቆራጭ ንግግር ይናገራታል፡፡ ከእለታት አንድ ቀን ልጅቱ ትምህርትቤት ትቀራለች፤ ለምን እንደቀረሽ ማስረጃ አምጪ ይላታል፡፡

የልጅቱ ቤተሰብ ሾፌሩ ደብዳቤ ይፅፋል፡፡ መምህሩ አልቀበልም ይላታል፡፡ የትምህርትቤቱ ርእሰ መምህር ጋር ሄዳ ታመለክታለች፡፡ ርእሰ መምህሩም ከመምህሩ ጋር ጨርሱ እኔን አያገባኝም ይላታል፡፡ ይህ ሁሉ የሚሆነው ልጅቱ አይናፋርና ከገጠር የመጣች ስለሆነች ነው፡፡ ልጅት ትግስቷ ሲያልቅ ለመጨረሻ ጊዜ መምህሩን ክፍል እንዲያስገባት ትጠይቀዋለች፡፡ መምህር አሁንም እንደለመደው ይህ ቡናቤት አይደለም፤ የትም እየዞርሽ መጥተሸ መግባት አትችይም ወዘተ በሚል አሳፋሪ ንግግር ይናገራታል፡፡ ልጅት በጣም ስለተኛደደች መምህሩን ዘላ አንገቱን ታንቀዋለች፤ ኡኡታ ይቀልጣል፤ ከትምህርት ቤት ትባረራለች፡፡ በዚህ ጊዜ ሾፌሩ ዘመድ ተጠርቶ ይሄዳል፤ ችግሩ ምን እንደሆነ ፊት ለፊት ንገሩን ሲባል ልጅቱ መምህሩ ምን ያህል አሳፋሪ ንግግር ሲናገራት እንደቆየ በወላጅ ፊት ትናገራለች፤ መምህራኑና ርእሰመምህሩ ጥፋቱ የመምህሩ እንደሆነ ይረዳሉ፤ ቀጥሎም መምህሩ የተማሪዋን ወላጅ ይቅርታ እንዲጠይቅ ይደረጋል፡፡

ይህ አንድ ምሳሌ ነው፤ሁለተኛው ታሪክ የዶክተሩ ልጆች በከተማው ውድ ከሚባሉት የግል ትምህርትቤት ነው ሚማሩት፤ እዛም ያለው ዜና አሳዛኝ ብቻ ነው፤ ወላጅ ልጄ ቆንጆ ትምህርት ቤት እየተማሩልኝ ነው ብሎ ሲጠብቅ፣ አንዳንድ ምግባረብልሹ መምህራን የልጆችን አእምሮ የሚጎዳ ተግባር ይፈፅማሉ፤ በአጭሩ አንዳንድ መምህራን እጅግ አሳፋሪ ስድቦችን  ተማሪዎችን ይሳደባሉ፤ ፈተና የወደቀን ተማሪ ‹ትምህርት ቤት ላይህ ላይ ቢሰራም አይገባህም› ብሎ የተናገረ መምህር መኖሩንም ሰምቻለሁ፤ ሁሉ መምህራን እንዳልሆኑ ግልፅ ቢሆንም አንድ ተሳዳቢ መምህር የተማሪዎችን ስብእናና በራስ መተማመን ለማጥፋት በቂ ነው፡፡የኔ ልጅም የነገረችኝ እጅግብዙ የመምህራን ስድብ ታሪኮች አሉ፤ እኔ ተማሪ በነበርኩበት ወቅት አንድ ተማሪ ከእለታት አንድ ቀን የሂሳብ የቤት ስራ ስላልሰራ 40 ጊዜ መገረፉን አስታውሳለሁ፤ አንድ ጥያቄ ሁሌም አእምሮዬ ውስጥ ይመላለሳል፤ እኛ ስልጣኔ ይህንን ያህል ዳገት የሚሆንብን ለምንድን ነው??? ከዴንማርክ እንደተመለስን ልጄ አዲስ አበባ የግል ትምህርትቤት ትማር ነበረ፤ አማርኛ መምህርዋ አምስት ጊዜ እጅዋን ገረፈቻት፤ ለምን ብዬ ስጠይቅ ‹ልጅህ በአማርኛ ክፍለጊዜ ስእል ትስላለች፣ ትምህርቱን ትንቃለች› ተባልኩ፤ አስቡት እስቲ፤ የአንደኛ ክፍል ተማሪ በአማርኛ ክፍለጊዜ ስእል ስለሳለች በአማርኛ መማርን ንቀት ነው ተብሎ መግረፍ፤  እንግዲህ በዚህ አይነት ስርአት የተማረው ልጅ ነው ነገ ፖሊስ የሚሆነው፤ ወይም የቢሮ ሀላፊ፤ አምባገነንነትን ነው የተማረው፤ እየገረፍን ያሳደግነው ተማሪ ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን እንዴት እንጠብቃለን? ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ እንደሚባለው፤ የልዘራነውን እያጨድን እኮ ነው፤ ጫማና ሸሚዛችን ዘመናዊ ቢሆን ምን ዋጋ አለው፤ አስተሳሰብና ምግባራችንም አብሮ ዘመናዊ መሆን አለበት፡፡

ሙስናን ለመዋጋት ሙስናን የሚጠየፍ ትውልድና ለሙስና ምቹ ያልሆነ ዘመናዊ አሰራር ያስፈልጋል፤ ሊገድል የመጣ ጌታዬ ቢሉት አይመለስም ይላል የሀሬ ሰው፤ ሰው ለሌብነት ራሱን ካሳመነ ማስተካከል በጣም ከባድ ነው፤ ነገር ግን ሌባ አንዴ ሰርቆ ሁለተኛ የሚደግመው የመጀመሪያው ሌብነት ሲሳከለት ነው፤ ስለሆነም ሌቦችንም የሌቦች ተቀባዮችንም ነው ቀዳዳ ልንዘጋባቸው የሚገባው፤ ካልሆነ ውድድሩ እየበዛ በሄደ ቁጥር በአቋራጭ መክበር የሚፈልጉትም አብረው መብዛታቸው ጥያቄ የለውም፡፡

ስራ ምንድን ነው

በአምስት አመት የዴንማርክ ሀገር ቆይታዬ ብዙ አይነት ስራዎችን ሞከርኩ፤ ከሶስተኛ ዲግሪ እስከ ማስትሬት ትምህርት፣ የፅዳት ስራ፣ የፖስተኛ ሰራተኛነት፣ የምግብ ዝግጅት፣ በጎ አድራጎት፣ ሽማግሌዎችን መንከባከብ፣ አትክልተኛ፣ መስተንግዶ፣ የግብርና ስራ፣ የምርምር ስራ፣ የጋዜጠኝነት ወዘተ….ይህንን ሁሉ የስራ ማመልከቻ ስልክ የተገኘውን ከመሞከር በማለት እንጂ ሁሉንም መስራት ስለምወድ አይደለም፡፡ የጋዜጠኝነት ስራውን እንደ ሪፖርተር ለመስራት አመልክቼ ለፈተና ተጠራሁ፤ የተሰጠኝ ፈተና ደግሞ በኮፐንሀገን ዪኒቨርሲቲ ከተማሩት የውጪ ሀገር ተማሪዎች ውስጥ ትምህርታቸውን ከጨረሱ ጀምሮ ምን ያህሉ ዴንማርክ ቀሩ ዴንማርክስ ምን ያህል ጥቅም አገኘች የሚል ጥያቄ ነበረ ፡፡ ለፅሁፉ መነሻ የሚሆነኝ መረጃ ተሰጠኝና ከሁለት ገፅ ባልበለጠ ፅፌ እንዳቀርብ ተጠየቅኩ፤ የስራው ቋንቋ እንግሊዘኛ ስለነበረ ስራውን የማገኘው መስሎኝ ደስ አለኝ፤ የድምፅ መቅረጫ ይዤ ቃለመጠይቅ ሳደርግ በሀሳቤ ተደሰትኩ፤ የተሰጠን ፅሁፍ ብዙ መረጃዎችን የያዘ ነበር፤ በመግቢያው ላይ እንደሚለው የዴንማርክን የኢኮኖሚ ችግር ለመፍታት ከውጪ ሀገር የተማሩ ወጣቶችን ወደዴንማርክ መሳብ አንዱ መፍትሄ እንደነበረ ተጠቅሷል፡፡ ዋናው ጥያቄ ምን ያህል የተማሩ ወጣቶች ወደዴንማርክ መጡ ስንቱስ ዴንማርክ ሀገር ቀሩ የሚለው ነበረ፡፡

ዴንማርክ የተማሩ ወጣቶች ዴንማርክ ሀገር እንዲቆዩ የዴንማርክ መንግስት የተለያዩ ማበረታቻዎችን ይሰጣል፤ ለአንዳንዶቹ ሙሉ የትምህርት እድል ይሰጣል ለምሳሌ ለእኔ የተሰጠው አይነት ማለት ነው፤ ሌሎች ትምህርት በነፃ ይደረግላቸዋል፣ ሌሎቹ ደግሞ የራሳቸውን የትምህርትና የመኖሪያ ወጪ ከራሳቸው ኪስ ይከፍላሉ፡፡ ትክክለኛ መረጃ ባይኖርም የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው ብዙ የውጪ ሀገራት ተማሪዎች ወደዴንማርክ እየመጡ ነው፤ በ2011 እንደ አውሮፓ አቆጣጠር 22315 ተማሪዎች በዴምናርክ የነበሩ ሲሆን ከነኚህ ውስጥ 8673 ማስትሬት ዲግሪና 2278 ደግሞ ዶክተሬት እየተማሩ ነበረ፡፡ በ2011 በዴንማርክ ያሉት የነበረው የተማሪዎች ቁጥር በ2010 ከነበሩት የውጪ ተማሪዎች  ጋር ሲነፀጸር በ14 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡  የውጪ ሀገር ተማሪዎች የዴንማርክን ኢኮኖሚ የመጥቀም አጋጣሚ ነበራቸው? በየአመቱ 1000 የውጪ ዜጎች ከአንድ ተኩል እስከ ሶስት ቢሊየን ብር ለዴንማርክ ኢኮኖሚ ድጋፍ ያደርጋሉ፡፡ መረጃው እንደሚያሳየው፣ ከምእራቡ ሀገራት ውጪ የሚመጡት ተማሪዎች እንደ አውሮፓ አቆጣጠር እስከ 2050 ድረስ ለዴንማርክ ኢኮኖሚ የበለጠ አትራፊ ናቸው፤ ምክንያቱም ትምህርታቸውን ሲጨርሱ  ወደሀገራቸው በቀላሉ ስለማይመለሱ ነው፡፡ ከ2050 በኋላ ግን ከምእራቡ ሀገራት ውጪ የሚመጡት ተማሪዎች ብዙም አትራፊ አይሆኑም፤ ምክንያቱም እድሜያቸው እያረጀ ብዙ እንክብካቤ ስለሚፈልጉና እነኚህ ሰዎች ብዙ ልጆች ስለሚወልዱ ነው፡፡

እንግዲህ አንድ የሀገራችን ወጣት የትምህርት እድል አግኝቶ ወደውጪ ሀገር ሲሄድ ሁላችንም በጣም ደስ ይለናል፡፡ ውጮ ሀገር ሄዶ ሊማር ነው፤ የትምህርት እድል አገኘ፤ እድለኛ ነው፤ እድለኞች ናችሁ ወዘተ በማለት ሁሉን ነገር በበጎ አይተን ጎበዝ ተማሪዎቻችንን ወደውጪ በነፃ እንልካለን፤ እውነታው ግን ወደውጪ የሚሄዱት ወጣቶች ከተመቻቸው ተምረው እዛው ነው የሚቀሩት፤ የሀገራችን ህዝቦች የተማሩ ጎበዝ ልጆቻቸውን ለሌላ አሳልፈው ሰጡ ማለት በቀላሉ ይህ ነው፤ እኔ የመጀመሪያ ዲግሪዬን ስማር አብረውኝ ከነበሩት ተማሪዎች ከመቶ 20 የሚሆኑትና ጥሩ ውጤት የነበራቸው ተማሪዎች ከሀገራችን ውጪ ይኖራሉ፡፡ ወዳጆቼ ውጪ ሀገር ተምረው እዛ ሰርተው ሲኖሩ ለራሳቸው ቆንጆ ክፍያ ይከፈላቸዋል፤ ስለሆነም በግለሰብ ደረጃ ብናስበው ምንም ጉዳት ላይኖር ይችላል፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ ስናስበው ግን ሀገራዊ ጥቅማችን የሚጎዳ ነው፤ በሀገራችን ዩኒቨርሲቲ ትምህርት ከተጀመረ ጀምሮ እዚህ ሀገራችን ከ1ኛ ክፍል ጀምረው እስከ መጀመሪያ ዲግሪ ድረስ የተማሩትን ወጣቶች ለውጪ ሀገር ሀብታም ሀገሮች ስትሰጥ በገንዘብ የማይተካ ኪሳራ ትከስራለች፤ ምክንቱም አንድ የተማረ ባለሙያ ለሀገር የሚሰጠውን ፋይዳ በገንዘብ ብቻ መለካት ትልቅ ስህተት ይመስለኛል፤ ከሀብት ሁሉ ትልቁ ሀብት የሰው ልጅ ነው፤ በተለይ የተማረ የሰው ልጅ ደግሞ ያደጉትን ሀገራት አሁን ያሉበት ደረጃ ያደረሰው የተማረ ሰው ጭንቅላት ውጤት ነው፤ስለዚህ ሀገራችን በሌላት ገንዘብ አልፎ አልፎም በብድር ገንዘብ ያስተማረቻቸውን ውድ ልጆችዋን በትምህርት እድል ሰበብ እየተወሰደባት ነው፤ ልብ ይበሉ፣ የትምህርት እድል ማግኘቴ ለእኔ ብዙ ጠቅሞኛል፤ ስለሆነም በቅርቡ የትምህርት እድል ባገኝ ወደውጪ ሀገር መሄዴ አይቀርም፤ ነገር ግን ትምህርቴን ውጪ ሀገር ለመማር ስሄድ በዋናነት ገንዘብ ፍለጋ ነው የምሄደው፤ ካልሆነ ለሀገራችን ህዝብ በቀጥታ ጠቃሚ የሆነ ትምህርት መማር ያለብኝ እዚሁ ሀገሬ በራሳችን መምህራን ነው፤ በነገራችን ላይ የሀገራችን ፕሮፌሰሮች በቀለም ትምህርት አቅማቸው በአለምም ተወዳዳሪ ናቸው፤ ዋናው ስራችን መሆን ያለበት ባለሙያዎቻችን ለስራቸው ታማኝ ሆነው የሚያውቁትን እውቀት ከግለሰብ ጥቅም ባለፈ ለሀገር እንዲጠቅም አድርጎ ማስተማሩ ላይ ነው፤ በአሁኑ ጊዜ እያስተዋልኩ ያለሁት ነገር ብዙ የተማሩ የምላቸው የሀገሬ ምሁራን የወረደ አስተሳሰብና ሙስና እንዲሁም ለሙያ አለመታመን እየተጠናወታቸው ነው፡፡ ለዚህም ደግሞ መሰረታዊው ችግር ዘመን የመጣው የቁሳቁስ ውድድር ውስጥ ራስን በማስገባት ጎሮቤታችን አንድ ሰው በሙስና ፎቅ ስለሰራ እኛ ሙስና ባለመስራታችን የተሞኘን አይነት ስሜት እየተሰማን ነው፡፡ ስለሆነም የተለያዩ ሀገርን የሚጎዱ ምርምሮችና ምርቶች ቢኖሩም ምሁራኑ በገንዘብ በመታለል ለወገን መከታ ሳይሆኑ የሚቀሩበትን ሁኔታ እያስተዋልን ነው፤ ይህ ችግር ይብዛም ይነስም በሀገር ውስጥ ያለነውንም ቢሆን እንዲሁም ውጪ ሀገር ያለነውን የሀገራችን ምሁራን ይመለከታል፡፡ የተማሩ ዜጎች ስደት ለሀገር እንደሚጎዳ እያወቅንም ችግሩን ለመቅረፍ ለወጣቱ የውጪ ሀገርን ትምህርት ችግር ስናስተምር አንታይም፤ እንዲሁም አልፎ አልፎ ሀገራችን ደሀ መሆንዋንም እወቅን ህዝብን ወደማያልቅ ብጥብጥ የሚያስገቡ ሀሳቦችንም እናራምዳለን፡፡ ዘመናዊ ባርነትን አምነን በመቀበል የሀገራችንንና የህዝባችንን ችግር ከመፍታት ይልቅ ለጥላቻና ለመራራቅ መንገድ እናመቻቻለን፡፡

የስራ ቦታ ደህንነትና የጤና ዋስትና

በሀገራችን አሰሪ ድርጅቶች ለሰራተኞቹ የጤና ዋስትና የማይሰጡት ለምንድን ነው፤ ለምሳሌ አንድ ሰው ግንባታ ስራ እየሰራ አደጋ ቢደርስበት ለአደጋው የጤና ዋስትና መሰጠት አለበት፤ ከውጪ ሀገር ቆይታዬ ከተማርኩት ነገሮች አንዱ ሰራተኞች የስራ ዋስትና እንዳላቸው ነው፡፡ በተለያዩ መንግስታዊና የግል ድርጅቶቹ በአነስተኛ ደሞዝ የሚሰሩትን ሰራተኞች የስራ ደህንነት ቢመረመር እጅግ አደገኛ ደረጃ እንደሚሆኑ አያጠራጥርም፤ ለምሳሌ መነፅር ሳያደርጉ ብረት የሚቆርጡ፣ ያለሄምሌት የግምባታ ስራ የሚሰሩ፣ ጓንት ሳያደርጉ የሚቆርጡ፣ የአፍንጫ፣ የአፍና የአይን መሸፈኛ ሳያደርጉ መስራት የተለመደ ነገር ሆነ፡፡ ደቡብ ዴንማክ ሶስት ሰራተኞች ተቀጥረን ለኛ ሲባል ጊዚያዊ ተጨማሪ ሽንት ቤትና መታጠቢያ ቤት እንዲያስገቡ መደረጉን አስታውሳለሁ፡፡

ለአራት የኮንትራት ሰራተኞች የመታጠቢያ ክፍልና ለቀን ተቀን ስራቸው ሙያው የሚፈልገውን የደምብ ልብስ እንዲሁም የጤንነት ጥንቃቄ ለማቅረብ ቀጣሪው ድርጅት ከተገደደ፣ በሀገራችን ያሉ ቀጣሪ ድርጅቶች ደግሞ ሰራተኞቻቸው ስራ እየሰሩ ጉዳት ሲደርስባቸው ለምን የጤና ዋስትና አይሰጣቸውም የሚለውን ሳስብ ምንም መልስ የለኝም፡፡ የሀገራችን ኢንዱስትሪዎች ለባለሃብቱ ትርፍና ጥቅም ታስበው እንጂ ለሰራተኛቸው ዋስትና የተሰሩ አይደሉም፡፡ ለምሳሌ በሀገራችን መዲና ሲሚንቶ በጅምላ የሚሸጥበት ገበያ ውስጥ የሚሰሩትን ሰራተኞች ሁኔታ ከጎተራ ወደቄራ በሚወስደው መንገድ በስተ ግራ በኩል አይቼ ነበረ፡፡ ሰራተኞቹ የሲሚንቶው አቧራ አፋቸውና አፍንጫቸው እንዳይገባ ምንም የተደረገላቸው ጥንቃቄ የለም፤ሰራተኘኞቹ ከስራ ሲወጡ ፊታቸው በሲኒምቶ ተሸፍኖ ነበረ፤ አፍንጫቸው አፋቸው በሙሉ፤ በየቀኑእነኚህ ሰራተኞች ያንን ያህል ሲሚንቶ ወደሳምባቸው እየገባ ለመተንፈሻ አካል ህመም እንደሚዳረጉ ጥየቄ የለውም፡፡ ነገር ግን ለነኚህ ሰራተኞች ባለሀብቶቹ ምን የጤና ዋስትና አስበዋል፡፡

የስልጣን ጉዳይ

በቅርቡ ዲያቆን ዳኤል ክብረት በሀገራችን  ከስልጣን ጋር ተያይዞ /መውጣትና መውረድ/ በሚል ርእስ ቀጥሎ የቀረበውን ሀሳብ በፌስቡክ በኩል አስነብቦን ነበረ፡፡ በነገራችን ላይ ዲያቆን ዳንኤል በፌስቡ ከማውቃቸውና እጅግ ጠቃሚ ሀሳቦችን ከሚያስነብቡ ዜጎቻችን አንዱ ነው፡፡ ዲያቆን ዳኤልን እያመሰገንኩኝ የፅሁፉን መልእት እንደሚከተለው አጠር አድርጌ አቀርባለሁ፡፡

ዳንኤልና ወዳጁ ማኅበረሰባችን ከሥልጣናቸው የሚወርዱ ሰዎችን በበጎ የመቀበል ልማድ አለው ወይ? በሚል አሳብ ሲወያዩ  ‹ከሥልጣን ወርደው በሰላም የኖሩም በመከራ ያሳለፉም ዐውቃለሁ› ዐፄ ካሌብ ሥልጣናቸውን ትተው አባ ጰንጠሌዎን ገዳም ሲገቡ በልጃቸው በገብረ መስቀል ዘመን የደረሰባቸው መከራ የለም፡፡ ምናልባት ግን ያን ጊዜ የክርስትናው ጣዕሙ ያልጠፋበት ዘመን በመሆኑ ይመስለኛል፡፡ በጎንደር ዘመን ግን አድያም ሰገድ ኢያሱ ሥልጣናቸውን ትተው ገዳም ቢገቡ ተተኪዎቻቸው የመነኑበት ድረስ መጥተው ገድለዋቸዋል፡፡ ሁለቱም በኢትዮጵያ ተፈጽመዋል ብሎ ለወዳጁ ይነግረዋል፡፡
ወዳጁ ግን ‹ባህሉ ከሥልጣን ለወረደ ሰው ክብር የሚሰጥ አይደለም፡፡ ከዚያ ይልቅ ሹምን ያበረታታል፡፡ ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል የሚለውም የዚህ ምስክሩ ነው› ብሎ የገጠመው ለዳንኤል ይነግረዋል፡፡ ከባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ኮሌጆች የአንዱ ዲን የነበረ ሰው መኪናም፣ አበልም፣ ሥልጣንም፣ ክብርም ነበረው አለ፡፡ ሲወጣ ሲገባም እጅ ነሺው፣ ደጅ ጠኚውም ብዙ ነበረ አለ፡፡ በኋላ ታዲያ በአንዳንድ ጉዳዮች ምክንያት ከኃላፊነቱ እንዲነሣ ይወሰናል፡፡ ስብሰባው የተደረገው በዚያው እርሱ ይመራው በነበረው ኮሌጅ ግቢ ውስጥ ነበር፡፡ በግቢው ውስጥም ሊወርድ ነው የሚል ጭምጭምታ ይወራል፡፡ ማታ ስብሰባው ሲጠራ እንደሚነሣ ሠራተኞቹ አምነዋል፡፡ እንዳመኑትም አልቀረ ኃላፊነቱን በቅርቡ ለተተኪው አስረክቦ ከቦታው እንዲነሣ ተወሰነ፡፡ ዲኑም ስብሰባውን ጨርሶ ወደ ቤቱ ለመሄድ መኪናው ውስጥ ገባ፡፡ ከግቢ ሲወጣ ጥበቃው አስቆመው፡፡ ከዚህ በፊት ይሰጠው የነበረው ሰላምታ ቀረና ‹ወዴት ነው?› አለ ጥበቃው፡፡ ዲኑ ተናድዶ ‹ከዚህ በፊት ወዴት ስለምሄድ ነበር የምትከፍተው› አለው፡፡ ‹ያ ሌላ፣ ይኼ ሌላ› አለ ጥበቃው፡፡ ‹አሁን ክፈተውና ልሂድበት› አለው ዲኑ፡፡ ‹የለም ጌታው እንደ ድሮው አይደሉምኮ፤ ወርደዋል፡፡ ከወረዱ ወዲያ መኪና ይዘው መሄድ አይፈቀድም፡፡ ማውጫ ያምጡ›› አለውና ዐረፈ፡፡ መኪናውን ይዞ ለመውጣት የቻለው ከእርሱ በኋላ የመጡት ሌሎች ኃላፊዎች በሰጡለት ትእዛዝ ነው፡፡

ታድያ ይህንን እያየ ማን ሞኝ ሥልጣኑን ይለቃል? አንድን ሰው በሥራው፣ በዕውቀቱ ወይም በውጤቱ ሳይሆን በሹመቱ የማክበር የቆየ ልማድ አለን፡፡ ዳንኤል ሌላም ምሳሌ አከለ፤ ከዓመት በፊት ወሎ ገጠር ውስጥ ገብቼ በእግር እየተጓዝን አንድ ወፍራም ዱላውን የያዘ፣ ቦላሌ ሱሪ ያጠለቀ፣ ምንሽሩንም የታጠቀን ገበሬ አላፊ አግዳሚው ሁሉ እጅ ሲነሣው አየሁ፡፡ አብሮኝ የነበረው ወዳጄም ለእኔ እንኳን አድርጎት የማያውቀውን መሬት ሊወድቅ ትንሽ እስኪቀረው ድረስ ነበር እጅ የነሣው፡፡ እንዲህ ሲያደርግ ያየሁት ቤተ ክርስቲያን ሲሳለም ብቻ ነበር፡፡ ገርሞኝ እልፍ ስንል ‹ሰዉዬው ምንድን ነው?› ስል ጠየቅኩት፡፡ አንድ የክልል ባለ ሥልጣን ስም ጠራና ‹የእርሱ ወንድምኮ ነው› አለኝ ሲል ይተርካል፡፡ በመጨመርም /እንኳን የሹም ሚስቱ፣ ወንድምና እኅቱ፣ ይኮራ የለም ወይ የሩቅ ጎረቤቱ/ የሚል በደርግ ጊዜ የተገጠመ በሹም የመኩራትን ርቀት የሚያሳይ የጎጃም ሥነ ቃል ይነግረናል፡፡ ይሄ በሹመትና በሹም ወዳጅ የመኩራት አባዜ በኋላ ላይ ከሹመት መሻርን፣ መውረድንና መልቀቅን በጸጋ እንዳንቀበለው የሚያደርግ ነው፡፡ ኩራቱ ከልክ ስለሚያልፍ ሐፍረቱም ከልክ ያልፋል በማለት /ኩራትና ትዕቢት የሞሉት ኣናት፣ ሰይፍና ጎራዴ የመቱት አንገት፣ አይገላገሉም እንዲህ በቀላሉ፣ ከመሬት ላይ ወድቀው ካልተንከባለሉ/ ተብሎ የተቀኘን ዜማ ይጠቅሳል፡፡

በሀገራችን ሰው በሥልጣን ሲኖር ዘመድ ወዳጁን መጥቀሙን፣ ለሀገሩና ለአካባቢው ሰዎች መወገኑን፣ የቅርብ ዘመዶቹን ጥግ ጥግ ማስያዙን ባህሉ እንደ ነውር ሳይሆን እንደ ጨዋነት ነው የሚቆጥረው፡፡ በየአካባቢውና በየቢሮው ባለ ሥልጣናቱ ሲቀያየሩ ‹የገንፎ ምንቸት ውጣ፣ የጎመን ምንቸት ግባ› የሚባለውም ለዚህ ነው፡፡ ሁሉም ባለ ሥልጣን አልጋውን የሚሸከሙ የራሱ ኪሩቤል፣ መንበሩንም የሚያጥኑ የራሱ ሱራፌል አሉት፡፡ በኛ ሀገር ባለ ሥልጣን ከሹመቱ ሲወርድ ብቻውን አይወርድም፡፡ ቤተሰቡ፣ ጓደኞቹ፣ ዘመዶቹ፣ ወዳጆቹ፤ ጎሳዎቹ፣ አብሮ አደጎቹ ሁሉ ናቸው ከሥልጣን የሚወርዱት፡፡ መውረድ ከባድ የሚሆነውም ለዚህ ጭምር ነው፡፡ ከሹመቱ የወረደ ዕለት ደግሞ፡-/ ሹምና ቅቤ ቅል ሁለቱ አንድ ናቸው፣ የወደቁ ለታ የለም የሚያያቸው/ ይባላል፡፡

ዳንኤል ሀሳቡን ሲያብራራ እንዲህ ይለናል፤ በሀገራችን ቅቤ ቅል የተከበረ ነው፡፡ እንዲህ እንደዛሬው ‹ኮለስትሮል› የሚባል መጋኛ ከመምጣቱ በፊት ቅቤ መብላት የጌትነት መለኪያው ነበርና፡፡ የቅቤ ቅል ወዛም ነው፡፡ አይጥ እንዳይደርስበት ከፍ ብሎ ይቀመጣል፡፡ እንደ ሹም፡፡ ከወደቀ ግን መሠበሩ አይቀርምና ፈላጊ የለውም፡፡ ልክ እንደ ሀገራችን ሹም፡፡ መውረድ ሁለት ቦታ የሚገኙ ጥቅሞችን ያሳጣል፡፡ በአንድ በኩል በወንበር የሚያገኙትን፣ በሌላ በኩል ደግሞ በወንበሩ ክብርና ሥልጣን ምክንያት የሚያገኙትን፡፡ በዕውቀት፣ በውድድር፣ በጥረት፣ በገንዘብ፣ የማይገኙ በሥልጣን ብቻ የሚገኙ ጥቅሞች በሀገራችን ብዙ ናቸው፡፡ ሌላው ቀርቶ በሚያገኙት ደመወዝ መኪና ለመግዛት ዕድሜያቸውን ሙሉ የሚፈጅባቸው ሰዎች በቀላሉ መኪና የሚያገኙት ከተሾሙ ነው፡፡ በሀገራችን ሊቅ ከተናገረው ይልቅ ባለ ሥልጣን የተናገረው ዜና ስለሚሆን ታዋቂነት በቀላሉ የሚገኘው በሹመት ነው፡፡ ውጭ ሀገር በቀላሉ የሚኬደው በሹመት ነው፡፡

ቤት በቀላሉ የሚገኘው በሹመት ነው፡፡ ጉዳይ በቀላሉ የሚፈጸመው በሹመት ነው፡፡ ሀብት በቀላሉ የሚገኘው በሹመት ነው፡፡ እነዚህ ነገሮች በትምህርት፣ በጥረት፣ በውድድርና በልቀት ደረጃ የሚገኙ ቢሆኑ ኖሮ አንድም የሹመትን ፍቅር፣ አለያም ደግሞ የመውረድን ሥጋት መቀነስ በተቻለ ነበር፡፡ ትምህርት ቤት ለመመዝገብ እንኳን የሹም ልጅ ነው ከተባለ ነገሩ ያልቃል፡፡ የእምነት ባለ ሥልጣናት እንኳን የሚኮሩት በሚያውቁት አምላክ ሳይሆን በሚያውቁት ባለ ሥልጣን ነው፡፡ ሹመት በወንበሩ ብቻ ሳይሆን ስለ ወንበሩ የሚያስገኛቸው ጥቅሞች አሉት፡፡ ሳይንቲስቱን ሥራ በዛበት ብሎ የዕድር ልቅሶ ይቅር አይለውም፡፡ ባለ ሥልጣኑን ግን ይቅር ይለዋል፡፡ ‹እርሳቸው ስብሰባ ይበዛባቸዋል› ይባላል፡፡ እርሳቸው ለደቂቃ ልቅሶ ሲመጡ ግን ‹ከሌላቸው ጊዜ አጣበው› ተብሎ ይደነቅላቸዋል፡፡

አንተን ሳይሆን ወንበርህን የሚያከብረው ሰው መቀመጥ ባትፈልግም ኖር ይልሃል፡፡ ያንተን ጸሎት እግዜር በቅርበት መስማት ያለበት ይመስል ቤተ ክርስቲያን ስትገባ እንኳን ከፊት ትቆማለህ፡፡ ይህንን እያሰበ ነው ሹሙ ሁሉ መውረድን እንደ ገሃነም የሚፈራው፡፡ ‹ፔንዱለም የሚመለሰው በሄደው መጠን ነው› እንደሚባለው፡፡ የሹመቱ ክብርህ እንደ ተራራ ስለሚገፋ፣ የሽረቱ ውርደትህም እንደ እንጦሮጦስ ይወርደል፡፡ ብርሃኑ ድንቄ እንደጻፉልን በንጉሥ በካፋ ጊዜ ሹም የነበሩት ሊቅ ተሽረው ታሥረው ውኅኒ እያሉ ፈቃጅ ቢያጡ ‹አልቦ ዘመድ ጊዜ ተዋርዶ – በተዋርዶ ጊዜ ዘመድ የለም› ብለዋል፡፡ ሹም እንደ ሰው እንዴት ነው የሚኖረው? የሚለውን ባህላችን የቀረጸው አይመስለኝም፡፡ ሽሙጥ፣ ንቀትና ግልምጫ ሳይደርስበት እንዴት ነው መኖር የሚችለው? ለዚህም ሳይሆን አይቀርም ትርጓሜያችን ‹በሰጠሁበት አገር ለምኜ፣ በተሾምኩበት ሀገር ተዋርጄ አልኖርም ብሎ ሀገር ጥሎ ጠፋ› የሚለን፡፡ ዛሬ ዛሬ ዩኒቨርሲቲዎች በዝተዋል፡፡

በቁጥራቸው ልክ ፕሬዚዳንቶችና ምክትል ፕሬዚዳንቶች አሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ ሹሞች ሲወርዱ የት ነው የሚሄዱት? ሲሰግድ የነበረ ጥበቃ ‹አሁንማ ወርደሃል› እንደሚላቸው ያውቁታል፡፡ ስንቱን የተሻረ ሹም አምባሳደር አድርገን አንዘልቀዋለን፡፡ አንዳንዴ ሳስበው ‹በሰጠሁበት ሀገር ለምኜ፣ በተሾምኩበት ሀገር ተዋርጄ› የሚለው የቆየ ባህል ይመስለኛል የቀድሞ ሹመኞችን አምባሳደር አድርጎ ከሀገር የሚያወጣቸው፡፡ ዳንኤል ቀጥሎም፤ የሹመት ዘመን ሲያበቃ የኖሩበትን አካባቢ ጥሎ መሄድ የቆየ ታሪካችን አካል ነው፡፡ የመጨረሻው የዛግዌ ንጉሥ በይኩኖ አምላክ ሲሸነፍ የዛግዌ የጦር መሪዎችና መሳፍንት አስቀድሞ የዛግዌ ነገሥታት የንግሥናቸው ቦታ ላስታን ትተው ጠንካራ ድጋፍ ወደነበረበት ወደ ሰሜን(ኤርትራ) ሄደዋል፡፡ በዛግዌና በአድከመ መልጋ(ኤርትራ) አካባቢ፣ ሸዋ ላስታን በወረረ ጊዜ የመጡ እንደሆኑ የሚናገሩ ሕዝቦች አሉ፡፡ እነዚህ በዛግዌ ነገሥታት ከተሾሙት የአካባቢ መሪዎች ጋር በመሆን ይኩኖ አምላክን ለተወሰነ ጊዜ ተቋቁመውት ነበር፡፡ በ1261ዓም ለደብረ ሊባኖስ ዘሺምዛና የተሰጠው የርስት ስጦታ እንደሚያመለክተው የዛግዌ ወገኖች ድላንዳ የተባለ ንጉሥ አንግሠው ነበር፡፡ ስድስት ወታደራዊ መሪዎች ያሉበት ምክር ቤትም ነበራቸው፡፡

በ1263 ዓም ንጉሥ ኩዊናት በተባለ ንጉሥ አማካኝነት ሌላ ርስት ስጦታ እናያለን፡፡ በዚህ ጊዜ የተዘረዘሩት አለቆችም ሌሎች ናቸው፡፡ ይህም የዛግዌ ዘመን በይኩኖ አምላክ የንግሥና ጊዜም ቢሆን ለተወሰነ ዘመን መቀጠሉን የሚያሳይ ነው፡፡ ዘመነ መሳፍንት ሲያልቅም የመጨረሻዎቹ ራሶች ደብረ ታቦርን ለቅቀው ወደ የጁ ነው የሸሹት፡፡ በሀገራችን ታሪክ የሹም ዘመድ ብቻ ሳይሆን የሹም በቅሎ፣ ፈረስ፣ ውሻ፣ ከብት ይፈራል፡፡ ይከበራል፡፡ በአድያም ሰገድ ኢያሱ ዘመን ቢላዋና ድቁስ በአንገቱ ላይ አሥሮ የሚዞር ጠቦት ነበረ እየተባለ የሚነገረው ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ማን ይነካዋል? ነው ነገሩ፡፡ እንደ ክፍለ ዮሐንስ ያለ የዕውቀትም የሞራልም ሊቅ ካልሆነ በቀር፡፡ ‹አትንኩኝ የሹም ዶሮ ነኝ› የሚለው አባባል ዝም ብሎ አልመጣም፡፡ የሹም ዶሮ ስጦ ብትበትን፣ ጓሮ ብትፈልስ የሚናገራት ስለሌለ ነው፡፡ እንኳን ከብቱ የሹም ዛፍ እንኳን ልዩ ክብር አለው፡፡

በመጨረሻም ፤ ትሆነኝ ነበረ ሞፈርና ቀንበር፣ የሹም ዛፍ ሆንክና ይበላሃል አፈር በማለት ከሹመት ጋር የነበረንን የተለየ ክብር ይነግረናል ዲያቆን ዳንኤል፤  እናም ሹሞቹ ሆይ፤ እናንተም ስትወጡ ዕወቁበት፡፡ እኛም ስትወርዱ እንወቅበት ብሎ ሀሳቡን ይጨርሳል፡፡ እንግዲህ ልብ በሉ፤ ሁላችንም በየሰፈራችንና በየሙያችን ዘርፍ ከሹሞች ጋር ተያይዞ ብዙ የምናሰተውለው ነገር አለ፤ ለባለስልጣን ከሚገባው በላይ ክብርና ዝና ስለምንሰጥ እነሱም ከስልጣናቸው ለመነሳት ሞት መስሎ ይታያቸዋል፡፡ በቅርቡ አንድ የስዊዲን ሀገር ፀሀፊ ስለአፍሪካ ፖለቲካና ፖለቲከኞች እንዲህ ሲል የፃፈውን አንብቤ ነበረ፤ /አፍሪካዊ ሀገር መሪ ስትሆን የሁሉ ነገር ባለቤት ነህ፤ ነገር ግን ከስልጣን ስትወርድ ምንም ነገር የለህም፤ ህይወትህም የራስህ መሆኑን ማረጋገጥ አትችልም ሲል ተናገረ፡፡ ታሪካችንም የሚነግረን ተመሳሳይ ምስክርነት ነው፡፡ ከዚህ በፊት የነበሩን መሪዎች አብዛኞቹ ከስልጣናቸው ማብቃት በኋላ የጠበቃቸው ስደትና ሞት ነው፡፡ የሊቢያውን ጋዳፊ መጨረሻም ምን እንደሆነ እናውቃለን፡፡  ለመሪዎቻችን ልቦና ይስጣቸው፤ ስልጣናቸውንም በቀላሉ እንዲለቁ ከስልጣናቸው ማብቃት በሀዋላ ከስልጣን መውረድን የሚያበረታታ ማህበረሰብ እንዲፈጠር እንመኛለን፡፡

አሰሪና ሰራተኛ

አሰሪና ሰራተኛ አገናኝ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሌለን ለምንድን ነው?…አሰሪና ሰራተኛ አገኛኝ ለጉልበት ሰራተኛና ለቤት ሰራተኞች ብቻ ነው ያለው ማን ነው?  በሰለጠነው አለም ስራ አጦችን ወደስራ ለማምጣት ቀን ተለሊት የሚሰራ የመንግስት ቢሮ አለ፡፡ እኛ ሀገር ለምን ተመሳሳይ መስሪያቤት እንደሌለ ሳስብ መልስ አጣለሁ፤ እስቲ አንድ የገጠር ወጣትን አስቡት፤ ትምህርቱን ጨረሶ ወደቤተሰቡ ሲመለስ ምንም የስራ ማስታወቂያ ማየት አይችልም፤ ጋዜጣ የለም፤ ታዲያ ይህ ወጣት እንዴት ስራ ያግኝ?  ሌሎች ጎጂ ነገሮችን ቢሆን ከፈረንጅ ሀገር ኮርጆ ለማምጣት የሚወስድብን ከ6ወር ጊዜ ያነሰ ነው፡፡ ይህንን ለምን መኮረጅ አቃተን?  ጥቅሙ ለቀጣሪ ድርጅቶችም ነው፤ ሰራተኛ ሲፈልጉ ደውለው የሚጠይቁት፣ ስራ አጦችም ለስራ ፍለጋ የሚያመለክቱበት የመንግስት መስሪያቤት ያስፈልገናል፤ ውጤቱም የሀገር እድገት ነው ምክንያቱም ብዙ ሰው ስራ ሲቀጠር ብዙ የገቢ ግብር መሰብሰብ ስለሚቻል…..ወዳጆቼ ሊታሰብበት ያስፈልጋል፣ የቤት ስራችን ብዙ ነው፤ ከአለም እጅግ ርቀን ነው ያለነው…

በሀገራችን ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች እየተሰሩ መሆኑ በተለይ በቱሪዝም ኢንዱስትሪው በኩል ለሀገራችን የሚኖረው ጠቀሜታ እጅግ ላቅ ያለ በመሆኑ የበለጠውን የሚያበረታታ ነው፡፡ ቢሆንም አዳዲሶቹ ዘመናዊ ሆቴሎች ሰራተኞቻቸውን የሚያስተዳድሩበት ሁኔታ መስተካከል አለበት፡፡ አንዲት ምሳሌ ልጥቀስ፤ በሰለጠነው አለም የሆቴል ቤት ስራ እጅግ የተለመደ ነው፤ በዲያስፖራው አለም ካሉት የሀገራችን ዜጎች አብዛኞቹ የሚተዳደሩት ከሆቴል ጋር የተያያዘ ስራዎችን በመስራ ነው፡፡ ለምሳሌ የሆቴል ፅዳት ስራን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በጥራት ደረጃ በከተሞቻችን እየተሰሩ ያት ሆቴሎች አንዳንዶቹ ባደጉት ሀገራት ካሉት ብዙም አያንሱም፡፡ ነገር ግን እኛ ሀገር ባለው ዘመናዊ ሆቴል ውስጥ የሚሰሩት ሰራተኞች ደሞዛቸው ከሚሰሩት ስራ ጋር ሲነፃፀር እጅግ አነስተኛ ነው፡፡ ለምሳሌ የመፀዳጃ ክፍል ፅዳት ሰራተኞችን ብንመለከተ፤ ሰራተኞቹ አንድ ሰው መፀዳጃ ቤት ገብቶ በወጣ ቁጥር ነው ከስር ከስር ጠብቀው የሚያጸዱት፤ ቀን ከለሊት ሽንትቤት በርላይ ቁጭ ብለው ተጠቃሚ ገብቶ ሲወጣ የሚያፀዱትን ሰራተኞች አይቼ ደሞዛቸውን ስጠይቅ በወር ከ800 ብር አይበልጥም፡፡ 800 ብር በአንድ ወር ለሰራተኛዋ ምን ያደርግላታል፤ የቤት ኪራይ ስንት ነው፤ የምግብ፣ የትራንስፖርት፣ የልብስ፣ የሳሙና ወዘተ፡፡

የሆቴሉ ባለቤትስ በወር ስንት ብር ገቢ ያገኛል፤ ለምሳሌ 50 አልጋ ቢኖረው፤  አንዱ አልጋ በቀን 500 ብር ቢከራይ በ30 ቀናት ውስጥ 50በ500በ30 በትንሹ ሰባት መቶ ሀምሳ ሺ ብር ማለት ነው፡፡ የዜጎች ክብር ከፍ እያለ ሲሄድ የሰራተኞቹም ደሞዝ ከፍ ማለት አለበት፡፡ ዘመናዊ ሆቴል ሀገራችን ውስጥ ሲሰራ ሆቴሉ ለሰራተኞቹ የሚከፍለውም ክፍያ አብሮ መዘመን አለበት፡፡ መብታቸውንም ለማስከበር ሰራተኞቹ በሙያቸው መደራጀት አለባቸው፤ የሆቴል ሰራተኞች ማህበር፤ ሆቴልን እንደምሳሌ ወሰድኩኝ እንጂ የአምራች ፋብሪካዎችም ተመሳሳይ ነው፤ የፋብሪካዎቹ ትርፍና የሰራተኞቻቸው አያያዝና ደሞዝ አብረው አይሄዱም፤ ለዚህ ሁሉ መፍትሄው የፋብሪካ ሰራተኞች ማህበር ነው፤ በሰለጠነው አለም የሰራተኞች ማህበራት ግንባር ቀደም የሰራተኛ መብትና ጥቅም ተከራካሪ ናቸው፤ በተለይ ፋብሪካ ስራ ውስጥ ሰራተኛው በስራ ላይ ሳለ ጉዳትም ሊደርስበት ይችላል፤ ባለሀብቱ የሚገባውን የካሳ ክፍያና የህክምና ክፍያ ላይከፍል ይችላል፤ የተጎዳውም ሰራተኛ ከባለሀብቱ ጋር የመከራከር ገንዘብና ጉልበቱ ፤ላይኖረው ይችላል፤ ስለዚህ የሙያ ማህበራት የግድ ናቸው፤

የካሳዬ ታሪክ

 

ካሳዬ የቱ ነው? ካሳዬ የሀገራችንን ሰው ስም ማለቴ አይደለም፤ ካሳዬ የሙያ ማህበር ነው፤ ዴንማርክ ሀገር ትምህርቴን እንደጨረስኩ የሙያ ማህበር አባል ሆኜ ነበረ፤ ከሙያ ማህበር አባልነት ጋር ተያይዞ ስራ ያሌላቸው የዩኒቨርሲቲ ተመራቂዎች የሚከፈል ክፍያ ነበረ፤ በእነሱ ቋንቋ ኤ ካሴ ይሉታል፤ እኛ ደግሞ ካሰዬ ብለን በሚገባን ቋንቋ የቀልድ ስም አወጣንለት፤ ተማሪዎች ከዩኒቨርሲቲ ለመመረቅ ሲቃረቡ ዩኒቨርሲቲው የቀጣሪ ድርጅቶችና የአምራች ፋብሪካዎች እንዲሁም የተለያዩ የሙያ ማህበራትና የመንግስት መስሪያቤቶች ራሳቸውን ለተመራቂ ተማሪዎች ለማስተዋወቅ እንዲችሉ ዝግጅት ያዘጋጃሉ፡፡ ዝግጅቶቹን ጆብ ፌየር ወይም የስራ ፎረም /ትእይንት/ የሚል ስም የሚሰጡት ሲሆን በእለቱ ተማሪዎችም ሲቪ አዘጋጅተው የተመረቁትም የትምህርት መረጃቸውን ኮፒዎች ይዘው በዝግጅቱ ይሳተፋሉ፤ በዛ አጋጣሚ ከቀጣሪ ድርጅቶችና ከሙያ ማህበራት ጋር በቀጥታ የመገናኘት እድል ይኖራቸዋል፤ በእለቱም ከተማሩት ትምህርት ጋር ተቀራራቢ የሆነውን የሙያ ማህበር መርጠው፣ መብትና ግዴታቸውን አውቀው የአባልነት ፎርም ይሞላሉ፤ በተጨማሪም የተግባር ትምህርት ወይም ደግሞ የበጎ ፈቃደኝነት ስራ እድልም ይኖራል፤ የመመረቂያ ወረቀት መነሻ ሀሳብና የገንዘብ ድጋፍ ወዘተ በእለቱ ማግኘት ይቻላል፡፡

የሙያ ማህበራት አባልነት፣ በመጀመሪያ ደረጃ ባለሙያዎችን ስራ በመፈለግና የራሳቸውን ድርጅት መክፈት ለሚፈልጉትም የብድርና የቴክኒክ ድጋፍ ያደርጋሉ፤ እንዲሁም ባለሙያዎቹ ስራ ከያዙ ጀምሮ በስራቸው ላይ ከአሰሪያቸው ጋር አለመግባባት ቢፈጠር፤ ከስራቸው ቢባረሩ፣ ስራ እየሰሩ የአካል ጉዳት ቢደርስባቸውና አሰሪያቸው ተገቢውን ህክምናና የካሳ ክፍያ ባይከፍላቸው ማህበሩ ጠበቃ ገዝቶ ጉዳዩን ወደፍርድቤት በመውሰድ ለሰራተኛው መብት መረጋገጥ ይከራከራሉ፤ በተጨማሪም ሰራተኛው የኮንትራት ጊዜው አብቅቶ ስራ ቢያጣ የስራ ኢንሹራንስ ክፍያ ይከፍሉለታል፤ ከሙያው ጋር የተያያዙ የተለያዩ ስልጠናዎችም ይሰጣሉ፤ ለአባላት የትምህርት እድል ያፈላልጋሉ፤ ሙያውን በተመለከተ ከተለያዩ ምንግስታዊና ምንግስታዊ ካልሆኑ አካላት ጋር በመነጋገር የሰራተኞች ደሞዝ ተመጣጣኝ ሆኖ እንዲስተካከል ያደርጋሉ፤ እንዲሁም ባለሙያዎቹ ሰፊ የስራ እድል እንዲኖራቸው በተለያዩ ሴክተሮች የቅጥር መደብ እንዲኖር ይከራከራሉ፡፡ በአጭሩ ለአንድ ባለሙያ የሙያ ማህበሩ ዋስትናው ነው ማለት ይቻላል፡፡

ከሙያ ማህበራቱ ተጠቃሚ ለመሆን ከሰራተኛው የሚጠበቀው በአባልነት መመዝገብና በየወሩ መዋጮ መክፈል ነው፡፡ ለምሳሌ እኔ አባል የነበረኩበት የሙያ ማህበር ከግብርና ጋር ተዛማጅነት ያላቸው ባለሙያዎች ያሉበት ማህበር ነበረ፡፡ በወር የምከፍለው ክፍያ አንድ ሺ ብር ቢሆን ስራ እስካገኝ ድረስ ከማህበሩ በየወሩ እስከ አስር ሺ ብር ይከፈለኝ ነበረ፡፡ ምናልባት የስራ አጥ ቁጥር ሲጨምር ማህበሩ ሊከስር ይችላል ብለን እናስብ ይሆናል፤ ነገር ግን የስራ አጥ ቁጥር ሲጨምር መንግስት የሙያ ማህበራትን ይደጉማል፤ ምክንያቱም የሙያ ማህበራት  ኢኮኖሚን በማረጋጋት ለመንግስት ትልቅ ጠቀሜታ ነው የሚሰጡት፤ በተጨማሪም አባላት ማህበሩ ውስጥ በአባልነት የሚመዘገቡት ጥቅም ለማግኘት ብቻ ሳይሆን ሙያቸውን ለማሳደግና በሙያው የሚሰለጥኑ ዜጎች መጉላላት እንዳይደርስባቸው ለማድረግ ነው፡፡ ስለሆነም በሰለጠነው አለም አብዛኛው ሰራተኛ የሙያ ማህበራት አባል ነው፡፡ እኔ አባል የነበርኩበትን ማህበር አስተባባሪዎች ስለማህበሩ አመሰራረትና የገንዘብ ምንጭ ጠይቄ የተሰጠኝ ምላሽ ማኅበሩ ከአንድ መቶ ሺ በላይ አባላት ያለው ሲሆን ከነኛ ውስጥ ስራ አጥ የሆኑት ከመቶ ሶስት እጅ አይሞሉም፡፡

ስለሆነም ማህበሩ ለስራ አጦች በየወሩ ገንዘብ ቢከፍልም አትራፊ ነው፤ ምክንያቱም መንግስትም ማህበሩን በገንዘብ ይደጉማል እንዲሁም በየወሩ ከአባላቱ የሚሰበስበው ገንዘብ ለስራ አጦች ከሚከፈለው ክፍያ እጅግ ይበልጣል፡፡

በዴንማርክ ሀገር ተማሪዎች የነበርን እኔና ሌሎች የሀገሬ ወጣቶች ስለማህበራቱና ስለኢንሹራንስ ክፍያው ስንሰማ እጅግ ተደመምን፤ ዴንማርክ እንዴት የተቀደሰች ሀገር ናት ስንልም አደነቅናት፤ እውነትም ዴንማር በታላቅ አርቆ ማሰብ የተሰራች ሀገር ናት፤ እንዲሁም ባለሀብቱና መንግስት እንዲሁም የሀገሪቱ ዜጎች ከራሳቸው በላይ ሀገራቸውንና የህዝባቸውን ጥቅም ከፍ እንዲያደርጉ የተመቻቸ ስርአት ያለባት ሀገር ናት፤ ዴንማርክንና ሀገሬን ሳወዳድር የልዩነቱ ብዛት ከሚገመተው በላይ ይሆንብኛል፡፡ በተለይ በተለይ ታማኝነትን በተመለከተ፣ ሁሉንም ማለት ባይቻልም አብዛኛው የሀገራችን የተማረ የሚባለው ዜጋ እጅግ የወረደ እንደሆነ የሚያሳዩ ብዙ ምሳሌዎች መጥቀስ ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ከጋራ ጥቅም ይልቅ የራስ ጥቅምን ማስቀደም. ለሙያ ታማኝ አለመሆን በሀገራችን በብዛት ይታያል፡፡ ቢሆንም አሁንም መጀመር እንችላለን፡፡ ለምሳሌ የሙያ በሀገራችን ብዙ የሙያ ማህበራት አሉ፣ ማህበራቱ በየሙያቸው ስራ አጥ ለሆኑ ወጣቶች ከላይ የጠቀስኩትን አይነት አገልግሎት መጀመር ማቀድ አለባቸው፡፡ ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ መጀመሪያ ለሌሎች ወገኖች የማሰብና የመቆርቆር ስሜት በሁላችንም ልብ ውስጥ መፈጠርና ወደተግባር ለመለወጥ ጉጉት መኖር አለበት፡፡ ይህ በአጭሩ በተግባር የተደገፈ ሀገር ወዳድነት ማለት ነው፤ ካልሆነ ሙያዊ እውቀታችን የጋን ውስጥ መብራት ይሆናል ማለት ነው፡፡

ላለመታመናችን ግን መሰረታዊው ምክንያት የድካማችንን ያህል ተጠቃሚ የምንሆንበት ስርአት መስራት ባለመቻላችን ይመስለኛል፤ ምክንያቱም አሁን እስከደረስንበት የእድገት ደረጃ ድረስ ሀገራችን ውስጥ ስራ መስራት ለኑሮ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን እንድናገኝ ዋስትና መሆን አልቻለም፡፡ ለምሳሌ በተለየዩ የሀገራችን ከተሞች ገበያዎች አከባቢ ያለው ሁኔታ ልብ ብለን ብናስተውል ቀኑን ሙሉ ከባድ ሸክም በመሸከም የሚሰሩ ወጣቶች ቁጥር እጅግ ብዙ ነው፤ ቢሆንም ወጣቶቹ ለድካማቸው ተመጣጣኝ የሆነ ገቢ አያገኙም፡፡ በተቃራኒው ደግሞ አንዱ ቁጭ ብሎ በአንዲት የስልክ መልእት በብዙ ሺዎች የሚቆጠር ሀብት ያካብታል፤ ወደድንም ጠላምን ሰርቶ መኖር ዋስትና ሳይሆን ሲቀርና ስራ የማይሰሩ ደግሞ የተንደላቀቀ ኑሮ ሲኖሩ ሀገር ወደመፍረስ ትሄዳለች ማለት ነው፡፡ ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ የሚባለው የአባቶች ተረት ልብ ሊባል ይገባዋል፡፡

አንድ ሰው መለወጥ  የሚችለው ብቸኛው አማራጭ በመስራት ነው፤ ስራ የሚሰራው ዜጋ ደግሞ ቢያንስ ለመኖር መሰረታዊ የሆኑትን ነገሮች ለምሳሌ ቤት ምግብና ልብስ የጤና ወጪ የመሳሰሉትን ማግኘት መቻል አለበት፡፡ ይህ እንዲሆን ደግሞ መንግስት በየጊዜው እየተሻሻለ የሚሄድ በአንድ ሰአት ማንኛውም ቀጣሪ ድርጅት መክፈል ያለበትን ትንሹን  የደሞዝ መጠን በህግ መወሰን አለበት፡፡ ይህም በሰራተኛውና በአሰሪው መካከል ተመጣጣኝ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር ያደርጋል፡፡ እንደሚታወቀው ማንኛውም አምራች ድርጅት ከሚጠቀመው የምርት ግብአት ውስጥ የሰው ልጅ ትልቁ ግብአት ነው፤ ቢሆንም እስካሁን ድረስ በሀገራችን ለሰው ልጅ ተገቢው ክብር የተሰጠ አይመስለኝም፤ አሜሪካን ሀገር ሰዎች ሽንትቤት አፅድተው ቤትና መኪና መግዛት ከቻሉ ሀገራችን ላይ በተመሳሳይ ስራ መኪናና ቤት መግዛት ባይቻልም ተመሳሳይ ስራ ለሚሰራው ሰው እጅግ መሰረታዊ የሆኑትን የቤት ኪራይ፣ የምግብ፣ የልብስ የትራንስፖርት ወጪ ሊሸፍን የሚችል ክፍያ መጠን በህግ መደንገግ አለበት፡፡ ምክንያቱም በሀገራችን ከተሞች የቤት ኪራይና የምግብ ዋጋ ከሚፈለገው ደሞዝ በላይ እየጨመረ ቢሄድም የሰራተኛው ደሞዝ ደግሞ በዛው መጠን ከፍ ስለማይል ዜጎች በመደበኛ ስራ ላይ ሆነው ለመኖር እየተቸገሩ እንደሆነ የአደባባይ ሚስጢር ነው፡፡ ስለዚህ ለምን ዝም ይባላል?

እስቲ ስለቤት ሰራተኞች ጥቂት እናስብ፤ እኔ በመምህርነት ሙያ የሚከፈለኝ ክፍያ በመንግስት የተደነገገ የደሞዝ መጠን ነው፤ ግለሰቦች በየቤታቸው ቀጥረው ልጆቻቸውን እንዲንከባከቡላቸው የሚያደርጉት የቤት ሰራተኞችም ዜጎች ናቸው፤ እንዲሁም ልጅን የማሳደግ ስራቸው ከማንኛውም ስራ እኩል ለሀገራችን ትልቅ ጠቀሜታ አለው፤ ነገር ግን የቤት ሰራተኞች ስራ በሀገራችን የሚፈለገውን ያህል የመንግስትና የህግ ድጋፍ ያገኘ አይመስለኝም፤ በሰለጠኑት ሀገራት የቤትና የፅዳት ሰራተኞችም የሙያ ማህበራት አላቸው፡፡ ምክንያቱም የፅዳት ስራም ብዙ የሙያዊ ስራዎች አሉት፣ እንዲሁም ፅዳት በማጽዳት የሚተዳደሩት ሰራተኞችም የገቢ ቀረጥ ይከፍላሉ፤ ስለሆነም ማንኛውም ስራ ለሰራተኛው የገንዘብ ወይም የቁሳቁስ ጠቀሜታ እስካስገኘ ድረስ እንዲሁም ስራው ማህበረሰብን የማይጎዳ እስከሆነ ድረስ የህግ ከለላና የሙያ ማህበር ያስፈልገዋል፡፡ ነገር ግን ለዜጎችና ለሀገር ጎጂ የሆኑ አደንዛዥ ነገረሮችን በማምረትና በመሸጥ የሚተዳደሩት ግን በማህበረሰቡ መወገዝ አለባቸው፤ እንዲሁም መንግስትም ለማስቆም ጥብቅ እርምጃ መውሰድ ይጠበቅበታል፡፡

በእርግጥ በአብዛኛው ሀገራት የመንግስት አካላት በብዛት የባላሃብቶችን ጥቅም የሚያስከብሩ ናቸው፤ ባደጉትም ሀገራት ቢሆን በፖለቲካና በህዝብ አስተዳደር ውስጥ ባለሀብቶች እጅግ ትልቅ ሚና ነው ያላቸው፤ ለዚህ እንደምሳሌ የአሜሪካንን ፖለቲካ ማየት በቂ ነው፡፡ ነገር ግን የሰራተኞች የሙያ ማህበራት ክፍተቱን ለመሙላት እጅግ ታላቅ ጠቀሜታ አላቸው፡፡ በሀገራችን የተወሰኑ የሙያ ማህበራ ቢኖሩም ማህበራቱ የሰራተኞችን ጥቅም ለማስከበር ብዙም ሲንቀሳቀሱ አይታይም፡፡ ስለሆነም ሰራተኞቹ መብታቸውን የሚያስከብሩ ብዙ የሙያ ማህበራትን መመስረትና ጠቀሜታቸውንም ከፍ ለማድረግ መስራት እደሚገባቸው ልብ ማለት ያሰፈልጋል፡፡

 

 

ከእለታት አንድ ቀን ከቢሾፍቱ ወደሀዋሳ እየሄድኩ ሞጆ ላይ አንድ የዘመኑን V8 መኪና የሚያሽከረክር ሾፌር ጋር የመሄድ እድሉ አጋጠመኝ፡፡ ወደሀዋሳ እየሄድን ከሾፌሩ ጋር መወያየት ጀመርን፤ የመኪናው ባለቤት ታዋቂ ባለሀብት መሆኑን ገነረኝ፤ ባለሀብቱ ለስራ ወደሀዋሳ መምጣት ፈልጎ የመንገዱ ሰላም ስላጠራጠረው ከመኪና ይልቅ በአውሮፕላን ወደሀዋሳ ለመሄድ ይወስናል፤
ነገር ግን ሀዋሳ ሲደርስ የሚንቀሳቀስበት መኪና ስለሚያስፈልገው ሾፌሩ መኪናውን ሀዋሳ ይዞለት እዲሄድ ያዘዋል፡፡

ባለሀብቱ ሾፌሩን እኔ የመንገዱ ደህንነት ስላሰጋኝ በአውሮፕላን እሄዳለሁ፣ አንተ ደግሞ መኪናውን ይዘህ ሀዋሳ አውሮፕላን ጣቢያ ጠብቀኝ ይለዋል፡፡ የባለሀብቱ አስተሳሰብ ሾፌሩን እጅግ አሳዝኖታል፡፡ በመሆኑም እኔ በመኪናው ዘመናዊነት ተደምሜ ስለመኪናው የተሰማኝን አድናቆት ስነግረው ሾፌሩ ግን እንዲህ ሲል ተናገረ፤ /መኪናው ቆንጆ ነው፤ ነገር ግን የመኪናው ባለሀብቶች አስተሳሰብ እንደመኪናው ዘመናዊ አይደለም ብሎ አስደነገጠኝ/፤ ለምን ብዬ ብጠይቀው…. የመኪናው ባለሀብት ለህይወቱ ደህንነት ፈርቶ በአውሮፕላን  ሄደ፤ እኔም ቤተሰብና ልጆች አሉኝ፤ በእርግጥ የሱን ያህል ሀብታም አይደለሁም፤ ነገር ግን ለራሱ ደህንነት በሚፈራው መንገድ እኔን ሂድ ማለቱ እጅግ አሳዝኖኛል፤ አልሄድም ብል እንጀራዬ ነው፤ የቤትኪራይ አለብኝ፣ የልጆቼ ትምህርት ቤት ክፍያ አለ፤ ሹፍርና መተዳደሪያዬ ስለሆነ የአለቃዬን ትእዛዝ ተቀብዬ እየሄድኩ ነው፤ በዚህ አጋጣሚ የተደረዳሁት ነገር አለቃዬ ስለኔ ህይወት ምንም እንደማያስብ ነው…/ ብሎ ሲነግረኝ አንጀቴን በላው፡፡ ይህ ሾፌር እምቢ ማለት ይችላል፤ እሱ እንዳለው  ሹፍርና መተዳደሪያው ነው፡፡

ምንም እንኳን መንገዱ ሰላማዊ የነበረ ቢሆን የመኪናው ባለቤት የደሀውን ሾፌር ህይወት ለአደጋ ልኮታል፤ በጣም የሚገርመው ደግሞ ሾፌሩ ዝዋይ ሲደርስ ባለሀብቱ ሀዋሳ አውሮፕላን ጣቢያ ደርሶ ነበረ፤ ስለሆነም፣ /አሁን ከአውሮፕላን ስለወረድኩ ቶሎ ናና ውሰደኝ ብሎ ደወለ/፤ ሚስኪኑ ሾፌር /ጌታዬ እኔ እኮ ገና ዝዋይነኝ/ ሲለው ባለሀብቱ ተቆጡ፡፡ /እስካሁን ምን እየሰራህ ነው በማለት/፤ በለሊት ውጣ ብዬህ አልነበረም ወይ ሲል በስልኩ ውስጥ ቁጣው አስተጋባ፡፡ እንግዲህ አስቡት፣ መንገዱ ለደህንነት ያሰጋል ብሎ እያሰበ ሾፌሩን መላኩ አንሶት በለሊት ተነስቶ ከአውሮፕላን በፊት ሀዋሳ ቀድሞ ገብቶ እንዲጠበብቀው መጠበቁ እጅግ ያሳዝናል፡፡ ሌላው ልብ ማለት ያለብን ነገር በዛ አጋጣሚ ያ ሾፌር አደጋ ቢደርስበት ለህይወቱና ለጤናው ካሳ እንደሚከፈለው ምንም ማረጋገጫ የለንም፡፡

የዚህ የሾፌር ታሪክ ስለሀገራችን የስራ ሁኔታና በአሰሪና ሰራተኞች መካከል ያለውን መሰረታዊ ችግር ያሳየናል፡፡ በተጨማሪም የሀገር ደህንነትና ሰላም ሲዛባ የመጀመሪያውን ትልቅ ዋጋ የሚከፍለው ደሀው የሀገሪቱ ህዝብ መሆኑን ነው፡፡  ችግሮች ሲከሰቱ ባለሀብቱና የመንግስት ባለስልጣናት ሁሌም አማራጭ አላቸው፤ ነገር ግን ደሃው ሰራተኛ ግን ለእንጀራው ሲል፣ ልጆቹን ለማሳደግ ሲል፣ የቤት ኪራይ ለመክፈል ሲል፣ መሰረታዊ ነገሮችን ለማግኘት ሲል ህይወቱን መስዋእት ያደርጋል፡፡ ስለሆነም ሁላችንም ቆም ብለን ማሰብ አለብን፡፡ በተለይ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ችግሮች እንዳሉ ይታወቃል፤ በዚህ በ 2008 ዓ.ም. ብዙ የፖለቲካ ችግሮችና ተያይዞም የሰው ህይወት መጥፋትን እያስተዋልን ነው፡፡

እባካችሁ እባካችሁ ተመሳሳይ ችግሮች ሲከሰቱ አንዳችን ለሌላው ከለላ እንስጥ፤ በሀገራችን ታሪክ የጦርነትንና የእርስበርስ ግጭትን ከፍተኛ ዋጋ ሲከፍሉ የኖሩት ድሆች መሆኑን አንርሳ፤ በየከተሞቹ አድማ ለመበተንና በድንበር አካባቢ ጦርነት ሲነሳ ደሙንና ህይወቱን የሚከፍለው የባለስልጣን ልጅ መስሎን ከሆነ እጅግ ትልቅ ስህተት ነው፡፡ በሀገር ውስጥና በውጪም ለራሳቸው ሰላማዊ ቤት ውስጥ ሆነው ትእዛዝ የሚያስተላልፉት የሀገር ደህንነትን በተመለከተ የባሰ ነገር ቢመጣ ብዙም ላይጎዱ ይችላሉ፡፡ በችግሮቹ የሚፈናቀለው፣ የሚጨፋጨፈው ግን የደሀው ልጅ ነው፤ እባካካችሁ እያስተዋልን፡፡

በቅርቡ አንድ ከዩኒቨርሲቲ የተመረቀ ተማሪ ለፈተና ወደአዲ አበባ እየመጣ እሱ የተሳፈረው መኪና ከፖለቲካ ጋር በተያያዘ ችግር በእሳት ሲቃጠል መኪናው ላይ የነበሩት በሙሉ ህይወታቸውን ለጥቂት እንዳተረፉ ሰምቻለሁ፡፡ የመኪናው ባለሀብት እኮ የሞቀ ቤት ውስጥ ነው ያለው፤ ንብረቱን ለማውደም ስንል አብረን የምናወድመውን የድሆች ህይወት ማሰብ አለብን፡፡ ፖለቲካችንንም በተመለከተ ለውጥ ለማምጣት ስናስብ  እጅግ ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ መሆን አለበት፤ ስለሆነም ፖሊሶችም ህይወት ከማጥፋት ሌሎች አማራጮችን መጠቀም አለባቸው፤ እንዲሁም ህዝቡና ወጣቱም ጥያቄዎቹን እጅግ በተረጋጋና ሰላማዊ በሆነ መንገድ የግልና የመንገስት ንብረቶችን ሳይጎዳ ጥያቀዎችን ቢጠይቅ ችግሮቹንና ተያይዘው የሚከሰቱትን የህይወት መጥፋት መቀነስ ይቻላል፡፡ መቼም የህዝብ ጥያቄ ባደጉትም ሀገራት ያለ ነገር ስለሆነ በሚቀጥሉት አመታት ተመሳሳይ ጥያቄዎች እንደሚኖሩ ጥርጥር የለውም፤ ይልቁንም የጥያቄዎቹን መሰረታዊ እውነታዎች ስንመለከት ለምሳሌ የወጣቶች ስራ አጥነትና በስራ ላይ ያለው ዜጋ ማግኘት ያለበትን ጥቅም አለማግኘት ለህዝባዊ ተቃውሞዎች አንዱ መንስኤ ሊሆን ይችላል፡፡ ስራአጥነትን ለመቀነስና የባለሙያዎችን ሙያዊ ጥቅም ለማስከበር ደግሞ የሙያ ማህበራት ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ ስለሆነም ከሙያና ከስራ እድል ጋር ተያይዘው ላሉት ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ የሙያ ማህበራትን ማጠናከር ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡ ሀገራችንን የተሻለ ቦታ ለማድረስና ልጆቻችን የበለጠ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ብዙ የውጪ ሀገራት ተሞክሮ አለን፤ ወጣቱ ትውልዳችን ሀገሩንና ራሱን ለማሻሻል ወደውጪ መሰደድ የግድ ላይሆንም ይችላል፡፡

አዋሽ ወንዝ ስያላግጥብኝ

ከሀዋሳ ወደ አዲስአበባ በሚወስደው መንገድ ስመላለስ አዋሽ ወንዝ ጋር ስደርስ ውስጤን ቁጭት ብጤ ይቆነጥጠኛል፤ በዚህ አጋጣሚ በቅርቡ ሀዋሳ የመሬት መንቀጥቀጥ በነበረ ጊዜ ተደናግጠው ወደቤተሰቦቻቸው ለመመለስ በጉዞ ላይ እያሉ አዋሽ ወንዝ ድልድዩ ላይ ከባድ የመኪና አደጋ ተከስቶ ህይወታቸው ላፈው የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ነብሳቸውን በገነት ያኑራቸው፣ ለወላጆቻቸውም መፅናናትን እየተመኘሁ፤ አዋሽ ወንዝን በተመለከተ የዘወትር ቁጭቴ ምንጭ ስለሆነው ጉዳይ ልጥቀስ፡፡

በሀገራችን ካሉት ትልልቅ ወንዞች የአዋሽን ያህል ጠቀሜታ ላይ የዋለ ወንዝ ያለ አይመስለኝም፤ ቢሆነም ወንዙ ጋር ደርሼ ምስጋና ሳቀርብለት ወንዙ በምፀት ፈገግታ ይመለከተኛል፡፡ ባለውለታችን ነህ ስለው አይዋጥለትም፤ ወንዙ ባደረገልን ውለታ የተደሰተ አይመስልም፤ አንድ ቀን እዋሽ ወንዙ አከባቢ የተለመደው የመኪና ግጭት ነበረና መንገዱ ተዘጋግቶ ወርደን በእግራችን የመሄድ አጋጣሚ ነበርና በዛች አጋጣሚ ወንዙን ቀረብ ብዬ አናገርኩት፤ ወንዙ ከመሙላቱ የተነሳ በአከባቢው የነበሩትን የገበሬዎች መሬት አጥለቅልቆት ነበረ፤ አዋሽ ምነው ጨቀንክባቸው ስለው አሁንም በምፀት ፈገግታ ሸኘኝ፤ ከወንዙ ሁለት መቶ ሜትር አከባቢ ርቀት ላይ ያለው የገበሬዎች መንደር ግን የአትክልት ምርት በጓሮ ውስጥ አይታይም፤ የቤት እንሰሳቱም የመኖ ችግር ያለባቸው ይመስላል፤ ስለገበሬዎቹ እያሰብኩ እያለሁ አዋሽ ደወለልኝ፣ የት ደረስክ ሲለኝ ከወንዙ 300 ሜትር አከባቢ የሚገኘው የገበሬዎች መንደር አከባቢ መሆኔን ነገርኩት፣ ጎሮቤቶቼ እንዴት ናቸው ሲለኝ ሰላም ናቸው ነገር ግን ላሞቻቸው የግጦሽ ሳር የላቸውም፣ በጓሮም የአትክልት ምርት አይታይም አልኩት፣ ቅድም አጠገቤ ደርሰህ ስታመሰግነኝ አይገባኝም ያልኩት የጎሮቤቶቼን ኑሮ በቅርበት ስለማውቀው ነው፤ ያንተን አይነቶቹ የግብርና ባለሙያዎችና የውሀ ምህንድስና ባለሙያዎች መኖራቸውን የምታውቁ አይመስለኝም፤ ገበሬዎቹ ግን በየጊዜው መጥተው ችግራቸውን ያዋኙኛል፣ የግብርና ባለሙያዎችነን ባዮቹ እናንተ ስለነኚህ ገበሬዎች ህይወት ምን የምትሰጡት አስተያየት አለ ሲለኝ የምመልስለትን አጣሁ፣ ስልኩን ዘጋሁትና አጠገቤ የነበረውን አንዱን መንገደኛ ማወያየት ጀመርኩ፣ መንገደኛው ከጀርመን ሀገር የመጣ እንግዳ ተማሪ ነው፣ ወንዙ ብዙ የማልማት አቅም አለው፡፡

ነገር ግን ፈጣሪ የሰጠንን ይህንን ፀጋ በአግባቡ ከመጠቀም ይልቅ ከሀብታም ሀገራት ስንዴ መለመን ቀላል አማራጭ ሆነብን እንጂ፣ አዋሽን ከሌሎች ወንዞች ልዩ የሚያደርገው በተለይ ወደሃዋሳ በሚሄደው መንገድ በኩል ያለው የወንዙ ክፍል ከአከባቢው የመሬት ጠለል ጋር ተቀራራቢ መሆኑ ነው፤ ስለሆነም ወንዙን በመጠቀም የመስኖ እርሻ ለማስፋፋት እጅግ ምቹ መሆኑ ነው፡፡ ቢሆንም የሚፈለገውን ያህል አገልግሎት ላይ አልዋለም፤ አንዳንድ ወጣቶች ትንንሽ የመስኖ ውሀ ጀነሬተር ገዝተው ሽንኩርትና ቲማቲም እያመረቱበት ይገኛል፡፡ ቢሆንም የመስኖ ስራው በተበጣጠሰ መሬት በአብዛኛው ከአከባቢው ገበሬ በኪራይ የሚሰሩት ስለሆነ አጥጋቢ ምርት አይመረትም፡፡ ነገር ግን ያንን ያህል የማምረት አቅም ለውን መሬት መጠነ ሰፊ የሆነ የመስኖ ስራ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ከሀገር ውስጥ ፍጆታ በላይ ለውጪ ሀገር የሚላክም ያህል ምርት ማምረት ይቻላል፤ የአትክልት ምርቶች ማቀነባበሪያ ፋብሪካም እዛው አዋሽንዝ አካባቢ መሰራት አለበት፡፡

እስቲ አስቡት ወንዞች ሞልተው ገበሬዎቹን በሚያፈናቅሉበት ሀገር የቲማቲም ድልህ ከአረብ ሀገራት የምናስገባ ህዝቦች ምን እንባላለን? ከመቶ ከሰባ አምስት እጅ በላይ የሆነው የሀገራችን ህዝብ በግብርና እየተሰማራ በ21ኛ ክፍለ ዘመን የፍራፍሬ ጭማቂ ከውጪ ሀገር ማስገባት ማለት ትልቅ ኪሳራ ነው፤ ሀገራችን ኢትዮጵያ ውሃ እጅግ ትልቅ ሀብቷ ነው፤ በግብርና የሚተዳደር ሀገር ውሃን በክብር መጠቀም አለበት፤ እኛ ግን ያለንን የተፈጥሮ ሀብት በትክክል መጠቀም አልቻልንም፤ ብዙ የተፈጥሮ ሀብት መኖር በራሱ በቂ አይደለም፤ ዜጎች የስራ እድል መፍጠር እንዲችሉ መበረታታት አለባቸው፤ ለዚህ ደግሞ ለምሳሌ የብድር አገልግሎት ያስፈልጋል፤ ቴክኖሎጂ መጠቀም ያስፈልጋል፤ ከሁሉ በላይ ለገንዘብ ብድርና ለቁጠባ ቅርብ መሆን ያስፈልጋል፡፡

ማንኛውም ልማት እውን እንዲሆን ገንዘብ ያስፈልጋል፤ ገንዘብ ለማግኘት ደግሞ ካሉት አማራጮች ዋነኛው የባንክ ብድር አገልግሎት ነው፤ በሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ደግሞ ከባንክ ብድር ለመበደር መንገዱ ጥምዝምዝ ነው፤ ለምሳሌ እኔ የመኖሪያቤትና ቋሚ ስራ አለኝ፣ ነገር ግን ከባንክ ገንዘብ ለመበደር ቀላል አይደለም፡፡ እስቲ አስቡት፣ ትምህርት ተምሬ ስራ ያዝኩኝ፣ የተቻለኝን ያህል ቆጥቤም ቤት ሰራሁ ነገር ግን ቤቴን ዋስ አድርጌ ገንዘብ ከባንክ መበደር ካልቻልኩ እንዴት ለሌሎች የስራ እድል መፍጠር እችላለሁ ተብሎ ይታሰባል? የሀገራችን የኤኮኖሚ ስርአት ሁኔታ በተለይ የመንግስት የገንዘብ አሰራር ለዜጎች ቅርብ መሆን አለበት፤ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ባንኮቻችን ሚሊይነሮችን ብቻ ለማገልገል የተከፈቱ ነው የሚመስሉት፣ የኔ አይነቱ ደሀ ግን ገንዘቡን ባንክ ማስቀመጥ ካልሆነ በስተቀር ከባነኮቹ ገንዘብ ለመበደር መንገዱ ረጅም ዳገት ነው፡፡

በቅርቡ ለስራ ጉዳይ ኬንያ የመሄድ እድል ነበረኝ፤ ናይሮቢ ከተማ ውስጥ ብዙ አለም አቀፍ ባንኮች አይቼ ጠቀሜታውንና ጉዳቱን ከወዳጆቼ እየተወያየን ነበረ፣ ኬንያዊያን ገንዘብ ከባንክ ተበድረው ንግድ እንዲከፍቱ ባንኮች በተደጋጋሚ እንደሚያበረታቱዋቸው ነግረውኛል፤ እኛ ሀገር ግን ታሪኩ ሌላ ነው፣ ዴንማርክ ሀገር ደግሞ አንድ የዴንማርክ ዜጋ ከባንክ ገንዘብ ለመበደር የሚያስፈልገው የዴንማርክ ዜግነትና የሚበደረውን ገንዘብ ሊጠቀምበት የፈለገው ሀሳብ ብቻ ነው፡፡ እኔ እዛ በነበርኩበት ጊዜ ካስፐር የሚባል አብሮኝ ሁለተኛ ዲግሪውን የተማረ የዴንማርክ ዜጋ ነበረ፤ ካሰፐር የሴት ጓደኛ ነበረችው፤ ካስፐርና የሴት ጓደኛው ተማሪ ሆነው ተጋብተው ከባንክቤት ገንዘብ ተበድረው የመኖሪያ ቤት ገዝተው ነበረ፤ ካሰፐር አንድ ቀን ቤቱ ምሳ እንድበላ ጋብዞኝ በሄድኩበት ወቅት ስለሀገራቸው የባንክ አገልግሎት በሰፊው አስረዳኝ፤ ከባንኩ ቤት ለመበደር ዜግነቱና የተማረ ዜጋ መሆኑ ብቻ በቂ እንደነበረ ሲነግረኝ በሀሳብ ወደሀገሬ በርርኩኝ፡፡

ሀገራችን ላይ ከዩኒቨርሲቲ የተመረቀ ወጣት ዲግሪውን ይዞ ባንክቤት ሄዶ ቤት ልገዛ ስለምፈልግ ብር አበድሩኝ ብሎ ቢጠይቅ የሚመለስለት መልስ ምን ሊሆን እንደሚችል ሁላችንም እናውቃለን፤ በእርግጥ ገንዘብን የሚህል ነገር ዝም ብሎ ለማንም ሰው እበድር ማለት ከባድ ቢሆንም፣ አንደኛው ጉዳይ ግን ወጣቱ የሚበደረው ገንዘብ ከዜግነቱ በላይ አለመሆኑን ሁላችም መረዳት አለብን፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ጤናማና ቋሚ ስራ ያላቸው እንዲሁም ከራሳቸውም ይሁን ከቤተሰባቸው ተያጅ ማቅረብ የሚችሉት ወጣቶች የብድር ስርአት ሊመቻችላቸው ይገባል፡፡ ቀስ በቀስ ወደሰለጠኑት ሀገራት የማህበረሰብ አገልግሎትና መሰረተ ልማት ደረጃ መድረሳችን የሚቀር አይደለም፤ ስሆነም ለሀገራችን ወጣቶች የዛሬ 10 ወይም 30 ወይም 40 አመት ሊኖር ስለሚገባ አሰራር ዛሬ መነጋር መጀመርና በሀሳባችን የሉትን አማራጮችና ችግሮቹን እንዲሁም መፍትሄዎቹንም ጭምር መወያየት መጀመር ጠቀሜታው ላቅ ያለ ይመስለኛል፡፡

ከዴንማርክ ወደኢትዮጵያ እንደተመለስኩ የራሴ የሆነ የንግድ ድርጅት ይኖረኛል የሚል እምነት ነበረኝ፣ የነበረችኝን ትንሽ  ብርም ለንግድ ለማዋል አስቤ ወደተግባር ለመግባት ያለውን ሂደት ጥናት ሳደርግ የራስን ስራ የመጀመሩ ጉዳይ ቀላል አይደለም፣ ወይም እኔም ትክክለኛ የስራ ፈጠራ አስተሳሰቡ አልነበረኝም፤ ውጪ ሀገር ሄዶ መማር ማለት እዚህ ሀገር ቤት የሚገኘውን የስራ ገበያ በትክክል መረዳት አለመሆኑን ልብ ማለት ይገባል፡፡

በተለይ የኔ አይነቱ ምንም የንግድ ልምድ የሌለው የቀለም ትምህርት ላይ ብዙ ጊዜ ህይወቱን ያሳለፈ ወጣት፣ ንግድ ከመጀመሩ በፊት ገበያውን ያጠናል፣ ትርፋማነትን ያስባል፣ የካፒታል አቅሙንም ይገመግማል ወዘተ… ወደሀገር ቤት ከተመለስኩ ከስድስት ወር በኋላ የራሴን ስራ የመጀመር ሀሳቡን ትቼ ወደመንግስት ስራ ተመለስኩ፣ ሀሳቤን ከመቀየሬ በፊት አንዱን ባንክ ማናጀር የማናገር እድሉ ነበረኝ፣ ቤትና ቋሚ ስራ አለኝ ስለዚህ ቤቴን አስይዤ ገንዘብ ተበድሬ የራሴን ስራ መፍጠር እፈልጋለሁ ብዬ ስጠይቅ የነበረው ምላሽ አሉታዊ ነበረ፡፡ ባንኩንና የሀገራችንን ኢኮኖሚ ስርአት ታዝቤ ዝም አልኩኝ፡፡ ይህንን ስል ወጣቱ ስራ ለመፍጠር ፈልጎ ገንዘብ ለመበደር ያለው አማራጭ ሙሉ በሙሉ ዝግ ነው ማለቴ አይደለም፤ በተለይ በጥቃቅንና አነስተኛ በኩል ያለው እድል ጎበዝ ሆነው የስራ ፈጠራን ውጣውረድ በትእግስት ለማሳለፍ ለሚያስቡ ወጣቶች ትልቅ እድል ነው፡፡

በከተሞቻችንም እጅግ ውጤታማ የሆኑ በጥቃቅንና አነስተኛ የተጀመሩ ስራዎችን መጥቀስ ይቻላል፤ ለምሳሌ ሀዋሳ ከተማ የፍቅር ሀይቅ ዙሪያ ያሉት መዝናኛዎች መጀመሪያቸው በጥቃቅንና አነስተኛ መሆኑን ሰምቻለሁ፤ እኔ መጀመሪያ በ1994 ለትምህርት ሀዋሳ  ስመጣ ሀዋሳ ሀይቅ ዙሪያ የዛሬውን ያህል መዝናኛዎች አልነበሩም፤ ዛሬ ግን ብዙ ወጣቶች በመዝናኛው አከባቢ ህዝቡን በማዝናናት ገቢ እገኙ መሆኑን ሳይ እጅግ ደስ ይለኛል፤ ሀገር የምትቀየረው ጥቂት ሀብታሞች በመኖራቸው ብቻ ሳይሆን ልክ ፍቅር ሀይቅ ዙሪያና በሌሎችም ስራዎች የታየውን አይነት ወጣቶች የራሳቸውን ስራ ሰርተው ገንዘብ አግኝተው የገቢ ግብር መክፈል ሲጀምሩ ነው፡፡ ስለሆነም በሀገራችን ያሉትን በጎ ስራዎች እያበረታታን የጎደለውንና በሰለጠነው አለም ያለውን የተሻለ አሰራር ደግሞ ከሀገራችን ተጨባጭ እውነታ ጋር በማመሳሰል ቀስ በቀስ  እውን ማድረግ አለብን፡፡

ሀገራችን ከድህነት መውጣት የምትችለው ሀገር በቀል አምራችና የንግድ ተቋማት ሲበዙ ነው፣ ይህ እውን እንዲሆን ደግሞ መንግስትና የብድር ተቋማት፣ ባንኮቻችንና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ዘመናዊ የሆነ ራእይ ሰንቀው መንቀሳቀስ አለባቸው፤ በየደረጃው ከራሳቸው የግል ትርፍ በላይ ራቅ አድርገው የሚያስቡ ብዙ መሪዎችም ያስፈልጉናል፤ በመሆኑም አዋሽንም ሆነ ሌሎቹን የተፈጥሮ ሀብቶቻችንን ለሀገራችን ዘላቂ ልማት መጠቀም እንችላለን፡፡

 

ሀዋሳ ከተማ

ሀዋሳ ከተማ በሀገራችን አሉ ከሚባሉ ከተሞች ግንባር ቀደሚ የሚያደርጋት ብዙ ነገሮች አሉ፤ የመጀመሪያው መንገዶችዋ ናቸው፤ ሓዋሳ ደስ የሚሉ መንገዶች ነው ያላት፤ እንዲሁም ህብረ-ብሄራዊነትዋም ከአዲስ አበባ ብዙም አይለይም፤ እኔ ላለፉት 15 አመታት/ውጪ የነበርኩበትን ጊዜ ሳይጨምር/ ጀምሮ ሀዋሳ ስለነበርኩ ስለከተማዋ ለውጥ ብዙ ምስክርነት መስጠት እችላለሁ፤ ሀዋሳ በብዙ መልኩ ጥሩ እየሆነች ነው፡፡ ሀዋሳ ከተማ የክርስትና ትምህርት ደሴትም እየሆነች ነው፡ ሌሎቹን ከተሞች አላውቅም፣ እኔ ሀዋሳን ከ1994 ዓ.ም. ጀምሮ አውቃታለሁ.. የሀዋሳን ለውጥ መናገር እችላለለሁ…… የግለኝነት አዙሪት አስተሳሰባችንን ካላጨለመው በስተቀርም የሀዋሳ ህዝብና አከባቢው በሀገራችን አሉ ከሚባሉት ትሁት ህዝቦች አንዱ ነው…. ስለሌሎቹ ከተሞች ያላችሁበት ምስክርነት መስጠት ትችላላችሁ… ለስራ ወደገጠር ሄጄ ለኔ መቀመጫ አምጥተው በየዋህነት መሬት የሚቀመጡ ብዙ እናቶችን አይቻለሁ…. እምነታቸውና ስብእናቸው ታላቅ ነው… ታዲያ ህዝቡ ከሀይማኖት ትምህርት ተስፋ ይዞ ይመለሳል… ጭንቀቱን ተንፍሶ ይመለሳል… ሆስፒታሎች የሚፈለገውን ያህል አገልግሎት አይሰጡም… ደሀው ህዝባችን ለህመሙ ነፃ ህክምና ከእምነት ቦታዎች ይጠይቃል….በፀሎትና በፀበል ድነናል ብለው ደስ የሚላቸው ብዙ ናቸው… የሚፈለገውም መጀመሪያ ፈውስና ደስታ ነው….. ዝርዝሩን ከፈውሱ በኋላ እንነጋገራለን አይነት ነው…. ባካችሁ ህዝቡን ተረዱት…. ህዝቡ የሀይማኖት አስተማሪዎችን ከፈጣሪ ጋር አያይዞ ነው የሚያምናቸው….. ሰባኪዎች ናቸው ሀላፊነት ያለባቸው… ህዝቡን አለመከፋፈልና ወደትክክለኛ መንገድ መምራት ያለባቸው… ዋናው ችግር የህዝቡን እምነት በገንዘብ ለመለወጥ በሚደረገው ትግል የእምነት ጎራ ፈጥሮ ልዩነት ለማድረግ በሚደረገው ስብከት ነው…… ለሁሉም ሐዋሳ የክርስትና እምነት ደሴትነትዋ እየጨመረ እየሰፋ እየሰፋ ነው… ደስ ሊለን ይገባል… ከጥላቻ የራቀ ትምህርትም ህዝቡን ማስተማር ያስፈልጋል

 

ሀረቄና ከሰል

በዚህ መፅሀፍ መደምደሚያ በሀገራችን ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚኖሩ እናቶችና አባቶች ልጆቻቸውን ከሚያስተምሩባቸው የገቢ ምንጮች ውስጥ ሀረቄንና ከሰልን እንደምሳሌ ብጠቅስ ደስ ይለኛል፡፡ በእርግጥ ሀረቄ ዘስካሪ መጠጥ ሲሆን ለደሀ እናቶች የገቢ ምንጭ ቢሆንም ሀረቄ ለሚጠጡ አባቶች ደግሞ የገንዘባቸው ጠር ነው ማለት ይቻላል፤ ሀረቄን መጥፎ ነው ስንል ቢራም፣ ውስኪም፣ ቮድካም፣ ጠጅም ወዘተ መጥፎ መሆናቸውን አብሮ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ እኔ እስከማውቀው ድረስ ሀረቄና ጠጅ ከቢራና ከውስኪ እኩል በከፍተኛ ገንዘብና በብዛት ሲጠጡ አላየሁም፤ ምክንያቱም ሀረቄና ጠጅ የራሳችን ሀገር ስሪቶች ሆነው የአልኮል መጠናቸውም በው ባይታወቅም በተለይ ውስኪ መጠጣት ግን የስልጣኔ መለኪያ ሆኖም ሳይታይ የሚቀር አይመስለኝም፤ ሀረቄ ከጠጪዎች ይልቅ ሀረቄ ለሚያወጡት ደሀ እናቶች ብዙ ዋጋ በማስከፈል የሚመረት መጠጥ ነው፤ እናቶቻችን ሀረቄን በማዘጋጀሩ ሂደት እጅግ ብዙ ድካም ይደክማሉ፤ ሀረቄን ማውጣቱ የእናቶችን   ጉልበትና ጊዜ በብዛት ይጠይቃል፤ ሀረቄ ለማውጣት ከብቅል ዝግጅት ጀምሮ ጌሾ መውቀጥ፣ የአሻሮ እህል መግዛት፣ አሻሮ መቁላት፣ ጋን በወይራ ማጠን፣ አሻሮ ማስፈጨት፣ እንኩሮ ማዘጋጀት፣ የአረቄ ቂጣ መጋገር፣ ድፍድፍ መሙላት፣ ውሀ መቅዳት/በተለይ ገጠር አከባቢ ውሀ በእንስራ ማመላለስ/፣ እንጨት መልቀም፣ አረቄውን ለማውጣት እንስራ ማዘጋጀት፣ ከቀርከሀ ወይም ሸንበቆ መሳቢያ ማዘጋጀት፣ የእንስራውን ክዳን ቅል ማዘጋጀት፣ ኮዳ መከራየት ወይም ከጎሮቤት መዋስ፣  ዋዲያት ማዘጋጀት፣ አረቄው በሚወታበት እለት ማሰሮውም እሳት ላይ መጣድና ድፍድፉን መጨመር፣ እሳት እያሞሩ ማማሰል፣ ሲፈላ እንስራውን መክደንና መሳቢያውን በውሀ የተሞላው ዋዲያት ጋር በሚደርስ መልኩ አስተካክሎ  ከኮዳው ጋር ማገናኘት፣ እየፈላ ያለው ድፍድፍ ጭስ ወደውጪ እንዳይወጣ በጨርቅና በሊጥ መጠቅጠቅና ማፈን፣ ቀጥሎ ቀስ በቀስ እሳት መቆስቆስ/እናቴ ሀረቄ በምታወጣበት ወቅት የእኔ ስራ እሳት መቆስቆስ ነበረ/ እሳቱ ቀስ በቀስ እየተቆሰቆሰ ዋዲያ ውስጥ የተሙላውን ውሀ ኮዳው ማሞቅ ሲጀምር በእጅ ሙቀቱ እየተለካ በጣመም ሲሞቅ አረቄው ይወጣል፤ ብዙ ከፈላ ሀረቄው ሳቢያ ስለሚበዛበት ጥንካሬው ይቀንሳል/ሳቢያ ማለት የአልኮል መጠኑ በውሀ የምክንያት የቀነሰ ሀረቄ ማለት ነው/ …. እንግዲህ ከዚህ ሁሉ ድካም በኋላ ነው አንድ ወይም ሁለት ሊትር ሀረቄ የሚገኘው፡፡ ድፍድፉ እስኪያልቅ ህደቱ ይቀጥላል፤ ከዛ ሁሉ ድካም በኋላም ሀረቄው ቆንጆ ሊሆንም ላይሆንም ይችላል፤ ሀረቄ ቆንጆ ነው የሚባለው ንጹህ ውሀ ሲመስልና ሲቀዳ ደግሞ አረፋ የሚኖረው ከሆነ ነው፤ እንዲሁም ሲቀመስ የአልኮሉ ጥንካሬ አረቄውን ቆንጆ ወይም መጥፎ ሊያስብለው ይችላል፤ ቆንጆ ሀረቄ ሲሆን እኛም ግማሽ መለኪያ ይቀዳልናል፡፡ ለሁሉም ክብር ሀረቄ አውጥተው ልጆቻቸውን ለሚያስተምሩ እናቶች!

ከሰል ደግሞ የሀገራችንን የደን ሀብት በከፍተኛ ሁኔታ እያጠፋ ያለ፣ ነገር ግን የደሀ ወገኖቻችን የገቢ ምንጭ ነው፤ የሀረቄውን ህል ከሰልም እጅግ አድካሚ የሆነ የዝግጅት ስራ አለው፤ ከሰል ሲዘጋጅ መጀመሪያ ትልልቅ የእንጨት ግንዶችና ቅርንጫፍ ይሰበሰባል፤ ከተሰበሰበ በኋላ በአጫጭር ይቆረጣል፣ ከተቆረጠ በኋላ፣ መሬት ጉድጓድ ይቆፈራክ፣ አፈሩ ጉድጓዱ ጫፍ ይከመራል፣ ቀጥሎ እሳት ጉድጓዱ ውስጥ ይያያዛል፣ እሳቱ እንዲቀጣጠል ደረቅ እንጨት ይደረደርበታል፣ ቀጥሎ እርጥቡ ግንድ ቀስ በቀስ ይደረደርበታል፣ እሳቱ እየተቀጣጠለ ሳለ በእጠል ይታፈንና አፈር ይጫንበታል፣ በተቻለ መጠን ምንም አየር በቀጥታ እዳይገባና ጭስም እንዳይወጣ ይታፈናል፤ ከሰሉ በቅርብ ክትትል፣ ቀን ከለሊት ክትትል ተደርጎበት አየር ገብቶ እንዳይቃጠል፣ ጭስ ሲወጣ በቅጠልና በአፈር በማፈን ለሶዝት ወይ አራት ቀን እንዲቆይ ይደረጋል፤ በአምስተኛው ቀን የታፈነው ሲከፈት ከሰል ይገኛል ማለት ነው፤ ዋናው አደጋ ምናልባት ማታ እኩለሊት ባለቤቱ ደክሞት እንቅፍ ቢጥለው ከሰሉ አየር አግኝቶ ሙሉ በሙሉ አመድ ሊሆን ይችላል፤ ከሰሉ ያ ሁሉ ጉልበት ከወጣበት ጀምሮ ኪሳራ ሊሆን ይችናል፤ ግራር፣ ብሳና፣ ዋንዛ የመሳሰሉት ቆንጆ ከሰል ይሆናሉ፤ ነገር ግን እነኚህ ዛፎች የደን ሀብታችን ዋና መሰረት ናቸው፤ በመሆኑም ከሰል በማክሰል የሚተዳደሩት ወገኖቻችንን እያሰብን አማራጭ የገቢ ምንጭ ሊፈጠርላቸው ይገባል፤ ምክንያቱም የከሰሉ ስራ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ይበልጣል፡፡

የማሟሻዬ ክፍል 2  መጨረሻ …..

 

ልብ ይበሉ:  የዚህ መፅሀፍ ዋጋ ቀድሞ የተወሰነ አይደለም

 

ሀሳቡ ለሌሎች እንዲደርስ ያድርጉ፤ እንዲሁም አስተያየትዎን ይላኩልኝ

 

 

ይገባዋል የሚሉትን ዋጋ ደግሞ በንግድ ባንክ ቁጥር 1000160852902 ይላኩልኝ

 

 

ከገቢው 20% በአርሲ ሴሩና ሮቤ ዲደአ ትምህርትቤቶች ቤተ-መፅሀፍት ለመክፈት ይውላል፤

 

የመፅሀፉ ዋና አላማ የገንዘብ ትርፍ ለማግኘት ሳይሆን ወጣቶችን እንዲፅፉና እንዲያነቡ ማነሳሳት ነው

 

 

ለበመጠ መረጃ

 

fikadureta@gmail.com

 

twitter: @fikadureta

 

ስልክ +251922129883

 

የዛሬ አመት በክፍል ሶስት እንገኛን

ሀገራችንን ሰላም ያድርግ (ሰላም እናድርግ፣ ሰላማችንን የምናመጣው እኛ ነን)

ያለውን የሰጠ ንፉግ አይባልም…